የሰሜኑና የደቡብ ንጉሦቻችን

Wednesday, 10 August 2016 14:09

 

ወሰንሰገድ መሸሻ በላቸው / This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. /

በሐገራችን ኢትዮጵያ በሰሜን ጫፍ ጎልታ የምትጠቀሰው የዛሬዋ ሃገር ትግራይ ያውም አድዋ ናት። ዳሩ ሲወሰድ መሐሉ ዳር ይሆናል በሚለው ስሌት ኤርትራ ተገንጥላ ለጊዜው ከኢትዮጵያ ካርታ ተፍቃ ትግራይ የሰሜኑ የኢትዮጵያ ዳርቻ/ጠረፍ ሆናለች። ደቡብ ደግሞ የደቡብ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦችን የያዘ ሌላው ደቡባዊ ዳርቻችን ቢሆንም በተለይ ወላይታ ደግሞ የደቡቡ አንዱና ዋናው የሐገራችን የታሪክ ክፍል ሆኖ እናገኘዋለን።

ከሰሜን የተንቀሳቀሰው ኢህአዴግ በደቡብ ህዝቦች እጅግ ከልብና በፍፁም ታማኝነት  በመደገፉ ዛሬ የስልጣን መተካካቱ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰሜናዊ የአድዋው መለስ እንደዋዛ ወደ ደቡባዊ የወላይታው ኃይለማርያም ተዘዋውሯል።

የ3ኛው የዓለም ጦርነትን ያስነሳሉ የሚባሉ መተናኮሻዎችና የተነገሩ ትንቢቶችን፣ ቅኝ ገዢዎች በአፍሪካ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ችግር መፍጠራቸውን፣ በዚህም ሰበብ ያልሰለጠኑ ሕዝቦች በመሆናቸው እናሰልጥናቸው በሚሉ ኃይሎች መያዟን፣ ሀብቷንና የዜጎቿ ጉልበት መበዝበዙን፣ ሰዎቿ በባርነት እንደእንስሳ መዋረዳቸውን በገደምዳሜ በሁለት ክፍል ለማየት ከጀልን።

በመፅሐፍ ቅዱስ ከ40 ጊዜ በላይ የተጠቀሰችው ሐገራችን /ኩሽ/ ኢትዮጵያ በሥነ ፍጥረት መረጃዎች፣ በመልክአ ምድር አቀማመጥ ኢትዮጵያ የሚለው ስያሜ ከግብፅ በስተደቡብ ኩታ ገጠም ሆኖ እስከ ሕንድ ውቅያኖስ የሚደርስ ዘርና ቀለምን፣ ትውልድን የሚያመለክት መጠሪያ መሆኑ ይታወቃል። የአረቡ አለም ዋልታ ሆና የምትገመተው ግብፅ ናት።

ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ሁለት የፅርዕ ቃላት ተገጣጥመውና ተያይዘው ጥቁር ወይንም ጠይም በሚል የአንድነት ቃል ተጠቃልሎ በአካባቢው ለሚኖረው ሕዝብ የመጠሪያ ስም በመሆን ያገለግላል። ሀገሪቱንም ኢትዮጵያ ያሰኛት የኗሪዎቹ ደም ግባት ነው የሚለው ሐሳብም በብዙዎች ዘንድ የተደገፈ ነው።

ከልደተ ክርስቶስ በፊት 284 ዓመት ሰብአ ሊቃናት ብሉይ ኪዳኑን ከእብራይስጥ ወደነገረ ዮናኒ ሲተረጉሙ በእብራይስጥ ኩሽ ይባል የነበረውን ሁሉ ኢትዮጵያ ብለው ተርጉመውታል። ብሉይ ኪዳንን መፃፍ የተጀመረውም ከልደተ ክርስቶስ በፊት መሆኑና ኢትዮጵያም ብሉይ ኪዳኑን የተቀበለችው ከልደተ ክርስቶስ በፊት በ1000 ዓመት አካባቢ መሆኑ ታውቋል።

በመፅሐፍ ቅዱስ ኩሽ ወይንም ኢትዮጵያ የሚለው ክልልም በየጊዜው የመስፋትና የመጥበብ ሁኔታ ያጋጠመው ቢሆንም የምድረ ኢትዮጵያ ማእከል ሰሜናዊቷ አክሱም ፅዮን እንደነበረች የሐይማኖት መፅሐፎችን ዋቢ አድርጎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ &0 ዓ.ም/2000/ መፅሐፍ አብራርቷል።

በእብራይስጥ ቋንቋ ኩሽ የሚለው መጠሪያ ኢትዮጵያ ለምትባለው አገር የተሰጠ ትርጉም ነው። ኩሽ ማለት ደግሞ የኖህ የልጁ ልጅ የካም ልጅ ነው። ሙሴ የኩሽ መሬት ሲል ይጠቅሳታል። ስፋቷንም ከትግሪስና ኤፍራጥስ ወንዞች እንደምትዋሰን በኦሪት ፍጥረት 2፡13 ተመልክቷል።

ኦሪት ዘፍጥረት 2፡13 የሁለተኛው ወንዝ ስም ግዮን ነው፣ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከባል ይላል። በእብራይስጡ ኩሽ የሚለው ቃል ሦስት ትርጉሞች ይኖሩታል። በአንደኛ ትርጉሙ ከካም ልጆች መካከል አንዱ የሆነውን ኩሽን ይመለከታል።

በታሪካዊ ጥናታቸው ታላቅ ክብርና ዝና የተጎናፀፉት እነዶ/ር ዊልሒለም ጀስነየስ ደግሞ ኩሽ የጥቁሮች አባት ወይም የዘር ግንድ ነው ብለውታል። በሁለተኛ ትርጉሙ የዚህ የሰው ልጅ ነገድ የሆነው ሁሉ ኩሽ ወይንም ኩሻውያን ተብለው እንደሚጠሩ ያሳያል። በዚህ ትርጉሙ መልከ ጠይም ለሆነው ሕዝብ እንደመጠሪያ የተሰጠ ስያሜ መሆኑ ይታወቃል። ይሁንና መልከ ጠይም የሆነው ሕዝብ ሁሉ የኩሽ ዘር ነው ማለት ግን አይደለም ይላሉ።

እነ ዶ/ር ዊልሒለም እነዚሁ ጎሳዎች በመጀመሪያ ወደ አረብ ባሕረ - ሰላጤ ቀጥሎም ቀይ ባሕርን ተሻግሮ ወደ ሚገኘው ደቡባዊ ግብፅ መሥፈራቸውን ገልፆታል። በሦስተኛ ትርጉሙ መልከ ጠይም የሆነው ሕዝብ የሚኖርበት መጠሪያ ስም ከግብፅ ደቡብ እስከ ሕንድ ውቅያኖስ ያለው አካባቢ መሆኑ ታውቋል።

በእነ ዶ/ር ዊልሒለም ጥናት 3ኛው ክፍል በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙት ጥቁሮች የኩሽ ዘሮች መሆናቸውን በጥናታቸው አመልክተው ሲያጠቃልሉም ‹እርግጥ ነው የኩሽ ትውልድ ያለባቸው ጥቁሮች በዘፍጥረት ምእራፍ 10ቁ 7 የተጠቀሱት በአፍሪካ ውስጥ ተበታትነዋል› ብለው አስፍረዋል።

የግሪክ ልሒቃንም በበኩላቸው በኢልያስና በኦዲሴ የቅኔ መፃህፍታቸው በኢትዮጵያ የሚኖሩት ሕዝቦች እጅግ ኃያላን፣ ጀግኖች፣ ደጎች፣ ርኅሩኆች፣ እንግዳ ተቀባዮች፣ ከሰዎች ሁሉ በውበትና በቁመት የሚበልጡ ኃያላንና በጣም ውቦችና ክቡራን ናቸው ብሎ ፅፏል። ኩሽ የኖህ የልጅ ልጅ የካም ልጅ ነው። ካም 4 ልጆች ነበሩት። እነዚህም oሳ/oሽ/፣ ሚስራይ፣ ፋይ፣ ከንዓን ይባሉ ነበር። እነሱም ከሱዳን ጀምሮ እስከ ኤርትራ ባሕር ድረስ ያለውን አገር ይገዙ ነበር።

ከልደተ ክርስቶስ 800 ዓመት በፊት ግሪካዊው ገጣሚ ሆሜር በስነፅሁፉ ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመ፣ ስለኢትዮጵያውያንና ስስለሚኖሩበት አካባቢ በሥነ ፅሑፍ የገለፀና ኢትዮጵያ የትኛውን አካባቢ እንደያዘች በግልፅ ያመላከተ መሆኑ ታውቋል።

ከሆሜር በኋላም ከልደተ ክርስቶስ መወለድ በፊት በ490 የተወለደው የባለ ታሪኮች አባት ተብሎ የሚታወቀው ታሪክ ፀሐፊ ሄሮዶቱስ በበኩሉ ኢትዮጵያውያን የሚኖሩበት ሐገር በከግብፅ ደቡብ በመለስ የሚገኝ፣ ቀይ ባሕርንም ተከትሎ የሚሄድ አካባቢ እንደነበርና ሄሮዶቱስ የአባይ ወንዝ ከኢትዮጵያ ከአንድ ትልቅ ተራራ መዳፊያ እንደሚመነጭና ርዝመቱም ከመነሻ እስከ መድረሻው በ12 ሽህ ማይልስ እንደሚደርስ በመግለፅ አጠናክሮታል። እስራኤልን ከግብፅ ያወጣው ታላቁ ነቢይ ሙሴ የኢትዮጵያ አማች መሆኑንና የኢትዮጵያን ሕዝብና ምድር ሁልጊዜ ከግብፅ ጋር በማያያዝ መፅሐፍ ቅዱስ ፅፏል።

ታላቁ የመልክዐ ምድር ምርምር ሊቅ የነበረው እስትራቦ የኢትዮጵያ ድንበሮች በሰሜን ግብፅ፣ በደቡብ የሕንድ ውቅያኖስ መሆኑንና አባይ ወንዝ ከኢትዮጵያ ተነስቶ ወደ ሰሜን የሚፈስና የሚመነጨውም ከአንድ ትልቅ ተራራ ስር ነው ብሎ ፅፏል።

የብሉይ ኪዳን አበው ነቢያት ደግሞ ‹ኢትዮጵያ ኩሽ የሚለው ቃል ሁለተኛ ትርጉሙ ዘርዐ ትውልድን የሚያመለክት ሲሆን በሦስተኛ ትርጉሙ ይህ ዓይነት ዘርዐ ትውልድ የሚኖርበት አካባቢ የመጠሪያ ስም ሆኖ መገኘቱና ኢትዮጵያ መሆኗ›ን አረጋግጦ ገልፆታል። ሱዳንና ግብፅን ሲያጠጡ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ወንዞች ዐባይና ተከዜ በመፅሐፍ ቅዱስ የተገለፁና የታወቁ ናቸው። የኢትዮጵያ ግዛት እጅግ በጣም ሰፊ እንደነበርም በመፅሐፍ ቅዱስ ተገልፆአል።

ግብፆች በ3,000ና 1,000 ዓመት መካከል በሐውልታቸውና በብራና /ፓፒረስ/ ፅሑፋቸው /ሂዩሮግሊፍ/ ላይ እንዳሰፈሩት ኢትዮጵያን ብዙ ጊዜ የo አንዳንድ ጊዜ የደቡብ ምድር እያሉ ገልፀዋታል። ግብፆች ከዐባይ እስከ ኤርትራ ባሕር ድረስ ያለውን አገር ፑንት ብለው ይጠሩትም ነበር።

ከክርስቶስ በፊት 720 ኑብያ በነበረው ከተማ ናባታ የነገሠው ኢትዮጵያዊው ፒአንኪ ከግብፅ ሰሜን ደርሶ በሜዴትራንያን ባሕር አቅራቢያ ፈርኦንን ድል አድርጎ ነገሠ፣ ከእርሱ ቀጥሎ የነገሠው ወንድሙ ሻባካ ከ712-700 ዓ.ዓ.፣ ከሻባካ ቀጥሎ ሻባታካ ከ701-690 ነግሦ፣ ከ690-663 ቲርሃካ ነገሠ። ከቲርሃካ ቀጥሎ ከ663-655 በግብፅ ከነገሠው ኢትዮጵያዊ ንጉሥ ታንታሞ በኋላ የኢትዮጵያ ነገሥታት ታሪክ ተቋረጠ።

በማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 12 ላይ ንግሥተ አዜብ ይህን ህዝብ ለመፋረድ ትነሳለች… ብሏል። በግዕዝ አዜብ ማለት በደቡብና በምእራብ መካከል ያለ አገር ነው። የደቡብ ንግሥት ንግሥተ አዜብ ከነገደ ዮቅጣን በኋላ ከመጡት ውስጥ ነች።

oሳም/oሽ/ አምስት ልጆች ወለደ። እነዚህም ሳባ፣ አዌልጥ፣ ሰብታ/አቢስ/፣ ሬጌም፣ ሰበቅታ ሲሆኑ በኢትዮጵያ ከካም ከሰብታ/ሳቢታ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ2545-2513 ለ30 ዓመታት ነግሠዋል። ከሰበታህ እስከ ጲኦሪ 1ኛ ከ2000 - 1985 ከነገደ ካም 22ቱ በኢትዮጵያ የነገሱት ነገስታት ለ560 ዓመታት ድረስ ቆይተዋል። ኖኅ ሴምን ይወልዳል። ሴም ኤቦርን፣ ኤቦር ዮቅጣንን ወለደ። ዮቅጣንም 13 ልጆች ነበሩት። ስለዚህ ነገደ ዮቅጣን የሴም ልጆች በመሆኑ ነገደ ሴም/ነገደ ዮቅጣን/ በሚል የዘር ሐረግ ተተካ።

የዮቅጣን ልጆች አምስቱ ሳባ፣ ኦባል፣ አፌር፣ አቤሚኤል፣ ዐዊላ በጲኦሪ 1ኛ ዘመነ መንግስት ሳባ የተባለው በትግራይ፣ ኦባል በአዳል/አፋር/እና አፌር ደግሞ በኦጋዴን ነበሩ። ሦስቱ ነገደ ዮቅጣን ከኦጋዴን ከአዳል/አፋርና ከትግራይ ተላልከውና ተስማምተው በትግራይ ከነበረው ሰሜናዊው ሳባ ዘር አክሁናንስን ሳባ 2ኛ ብለው አነገሱት።

በወቅቱ በሕንድ ንጉስ በራማ ይገዙ እንደነበርና እነዚህ አንድነት ፈጥረው ራማን በማሸነፍ አባርረው ኢትዮጵያን ከመገዛት፣ ሕዝቡን ከባርነት ነፃ ስላወጡ አግዓዝያን ተባሉ ይባላል። ሰሜን መራሹ ኢህአዴግ ኢትዮጵያ የ100 ዓመት ታሪክ ያላት ሐገር ናት በሚልበት ወቅት አግዓዚ የሚል ጦር ሰይሞ ደርግን ለመናድ ይንቀሳቀስ እንደነበር ስናስብ የረጅም ዘመን ታሪክ የላትም ማለታቸው ሳይሆን የ100 ዓመት ታሪክ ሰራንላት ማለታቸው መሆኑን ያኔውኑ ተረድተንላቸው ነበር።

በግዕዝ ቋንቋ አግዓዘ ማለት ነፃ አወጣ/ነፃ አውጭዎች/ አገሪቱ ደግሞ ብሔረ አግአዚያን ተብላ ቋንቋቸውም ግዕዝ ተባለ። አግአዝያን የተባሉት ሦስቱ ወገኖች በተለይ ሰሜናዊውን ግዛቶች ኤርትራንና ትግራይን አጣምረው ይገዙ እንደነበር ማንሳቱ  በመጠኑ ጠቋሚ ነጥብ ይሆነናል።

ከአጋዝያን ወገን ትልቁ ሳባ ከወገኖቹ ጋር ከአካለ ጉዛይ ከሽመዛና ጀምሮ እስከ መዲናው አክሱም መላውን ሰሜናዊውን የትግሬ አውራጃ ሁሉ እየገዛ ኖሯል። የአግዓዚያን ወገን ኦባል አዳልንና ደንከልን ይዞ ጅቡቲን እያዋሰነ ገዝቷል። ሌላው የአግዓዚ ወገን ኦፊር የተባለው ነገድ ደግሞ ወርቅ እስከሚወጣበት እስከ አዶላ፣ ሐረርን እስከ ኦጋዴን ምስራቃዊ ግዛቶችን አጠቃለው ገዝተዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ክፍለ ዓለም በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ የምትገኝ የረጅም ዘመን ታሪክ ያላት ሐገር ብትሆንም ኢህአዴግ ከሰሜን ውየናው ጀምሮ ለፍልሚያ ሲጓዝ አዲስ አበባንና መላ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ በኋላም ኢትዮጵያ የ100 ዓመት ታሪክ ያላት አገር አድርጎ ለጥቂት ጊዜያት አሳነሳት። በኢትዮጵያ/በአማራ/ በቅኝ ተገዝቻለሁ በሚል የሻእቢያ አዲስ የነፃ አውጭነትና የመገንጠል ታሪክ ቅዠት ሲባል የተቀመረ በመሆኑ በባድመ ላይ ኤርትራ በሰነዘረችብን ወረራ ሳቢያ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ለባንዲራችን መከበር፣ ወደ ነፈጓት ክብሯ መመለስና ለመገለጫነቷ መዋል በማስቻሉ የ3000 ዘመን ታሪክ ባለቤትና ኩሩና ጀግና ልጆች ያሏት ሐገር ናት እንዲሉም አስገደደ።

የታሪክ ቁመራቸውን ከልሰው ከ3000 ዓመት በላይ በነፃነት የቆየች ሐገር ናት ብለው በፍጥነት በመቀየር የአክሱማውያንን ስልጣኔ በኢትዮጵያዊነት አስረጂ አድርገው መከራከር ጀመሩ። ኢትዮጵያውያኑን ቅሪተ አካላት ሉሲና ድንቅነሽን ይዘው የ3 ሚሊዮን ዘመን ታሪክ ባለቤት እንደሆነችና የሰው ዘር መገኛ ኢትዮጵያ እንደሆነችም ሽንጣቸውን ገትረው መከራከሩን ቀጠሉ።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የብዙ ሽህ ዓመታት ባለ ታሪክ መሆኗን የኢህአዴግ የታሪክ ምሁራን አሳምረው ማወቃቸውን በአግዓዚ ጦር ስያሜያቸው ብቻ እንኳን መቀበል አይቸግርም። ለዘመናት ድንበሯንና ነፃነቷን አስከብራ የኖረች ሐገር መሆኗን ለፕሮፓጋንዳነት መጠቀም ፈልገው የፀና ታሪኳ አድርገውም ገፉበት። ከዚያም የ3 ሚሊዮን ዓመት ባለታሪክነቷን የሉሲን አፅም መያዣ አድርገው በይፋ ሰሩበት። የአግዓዝያን ወገን ትልቁ ሳባ ትግራይንና ኤርትራን ባንድ አድርጎ የመግዛቱ እሳቤ በታሪክ ቁመራ በውስጠ ታዋቂነት ለነኢሳያስ አፈወርቂና ለመለስ መራሹ ግንባር ትንሹ ሳባነትን አነሳሳ ብሎ መገመት ያስችላል።

ኢትዮጲስ 1ኛ ከ1856-1800 ዓ.ዓ. ከልደተ ክርስቶስ በፊት 56 ዓመት ነግሶ ሐገሩም ኢትዮጵያ መባሏን ድርሳናቱ አስፍረዋል። ኢትዮጲስ 1ኛ ከሞተ በኋላ ካሉት 5 ልጆቹ ውስጥ በመንግስቱ የተተካው ልጁ ላክንዱን ነው። ኢትዮጲስ 2ኛ ሳባ የተባለው የአክሁናስ የልጁ ልጅ የቡልቃ ልጅ ነው።

ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ከልደተ ክርስቶስ በፊት በአንድ ሽህ ዓመት/‹ኢትዮጵያ ታበፅሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር›/ ‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች› ብሎ ዘምሯልና።

ከተማቸውን ማእረብ ላይ አድርገው የነገሱት የሳባ ነገሥታት በኢትዮጵያ የሚገኘውን መረብ የሚባለው የወንዝ/የዠማ ስም በዘመኑ በኢትዮጵያ ግዛትነቱ የተጠቀሰ ነበር። የሳባ የራይዳን የሐድራሙትና የያማናት ነገሥታት ዋና ከተማ ዛፋር ይባል የነበረና ሌላው ትልቁ ከተማ ናግራን እንደ ነበር/ከዚያ በኋላ የሒሚያር መንግስታት የተባሉበት ጊዜም ነበር።

የአክሱም ነገሥታት የሒሚያር፣ የራይዳንና የሳባውያን፣ የሳልሔንና የቲአማ ነገሥታት ተብለው በታሪክ ተጠርተዋል። የአክሱም ንጉሥ ኤዛና ሐውልት ላይ አስፅፎ የክብር መጠሪያው አድርጎም አስቀርፆት ተገኝቷል።

በአረብ ሐገር የኢትዮጵያ እንደራሴ የነበረው አብርሃ በማእሪብ ከተማና በሰንዓ ከተማ/የየመን መናገሻ/ ብዙ ትልልቅ ቤተክርስቲያናት በወቅቱ አሰርቶ ነበር። በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ብዙ የአረብ ሐገሮችን ይዛ የነበረች ጠንካራና የታወቀች ሐገር እንደነበረች ታሪክ አስፍሮታል።

በሳባውያን ፊደል ሳ የነበረው በአረብኛ ተለውጦ ሻ ሆኖ መቅረብ ጀመረ። ሀበሻ መባልም ተጀመረ። በብሉይ ኪዳን በዘፍጥረት ምእራፍ 10 በኖኅ ዘር ውስጥ 2 ሳባዎች እንዳሉ እናያለን። 1ኛው ትውልድ የኖኅ ልጅ የካም የልጅ ልጅ የሆነው ሳባ ነው። ሆኖም ከሌላው ለመለየት ሻባ ይሉታል። የካሙ ነገድ ኑብያው የኢትዮጵያ የነገድ አባት በመሆኑ ሳባ ኖባ እየተባለ ይጠራል። ከካም ነገዶች ውስጥ በኢትዮጵያ/አሁን በኤርትራ የምትገኘው/በከረን አውራጃ የሚገኙት ቢለን፣ በጎንደር አካባቢ የሚገኙት ቅማንቶች፣ በቋራና በላስታ የሚገኙት አገዎች እስካሁን ትስስሩን አያይዘው በአካል ተራርቀው ይገኛሉ።

2ኛው ትውልድ ደግሞ ኖኅ የካምን ወንድም ሴምን፣ ሴም አርፋክስድን፣ አርፋክስድ ሳላህን፣ ሳላህ ኦቤርን፣ ኦቤር ዮቅጣንን፣ ዮቅጣን ሳባን ይወልዳል። ነግሥተ ሳባ ከዚህ ነገድ የተገኘች ናት። ሀበሳን፣ ሂማርያት የሚሉ ስያሜዎች ተሰጥቷቸው ነበር። በአክሱሞች ዘመን ኢትዮጵያዊነትን ይልቁንም የሳባንና የሀበሳትን ሥያሜ እያደበዘዘው ቢመጣም የሳባውያን የሀበሳን ነገድነት እስካሁን ለኢትዮጵያዊነት መገለጫ ሆኖ ቀጥሏል። ሀበሳት የተባሉት የሀበስ ልጆች ናቸው። ኢትዮጵያ በሀበሳት ስም ሀበሻ የመባልን ስም እንደያዘች ዘልቃለች ይሉናል።

በአፈ ታሪክነት እንደተጠቀሰው መጀመሪያ በትግሬ ዘንዶ ይመለክ እንደነበርና የማክዳ/የንግሥተ አዜብ/ አባት ዘንዶውን በብልሃት ገድሎ ሰሜናዊቷን ትግሬን በበላይነት መግዛቱን ታሪክ መዝግቦታል። የማክዳ አባት ሲሞት  ልጁን ማክዳን አንግሰው ንግስት ዐዜብ ተብላ ባጠቃላይ ትግሬን ገዛች ይሉናል።

በክብረ ነገሥት ማክዳ ስትባል፣ በመፅሐፈ ነገሥት ደግሞ ሳባ ትባላለች። ሳባ በአክሱም አጠገብ የሚገኝ የቦታ ሥም ሲሆን ዐዜብ ደግሞ በደቡብና በምእራብ መካከል ያለ አካባቢ ነው። በመሆኑም ከኢየሩሳሌም በዐዜብ አካባቢ የሚገኙትን ኢትዮጵያንና የመንን ትገዛ ስለነበር የተሰጣት ስም መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ንግስት ዐዜብ ብዙ ሰራዊትና 500 ደናግል/ልጃገረዶችን አስከትላ ወደ እየሩሳሌም መሄዷ እውነተኛ ታሪክ ሆኖ ቀጠለ።  እነዚህ ልጃገረዶች ለፈላሻነት የነበራቸው ሚናም ቀላል አልነበረም።

ክርስትና ወድ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት በብሉይ ኪዳን እምነተ አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈፀምባት ሀገር ነበረች። የብሉይ ኪዳን እምነት ወደ ሀገሪቱ የገባው ከክርስቶስ ልደት በፊት በአንድ ሽህ አመት አካባቢ ንግሥተ ሳባ በኢየሩሳሌም ጉብኝት አድርጋ ከተመለሰች በኋላ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያኒቱ ጅውዶ ክርስቲያን/ ከብሉይ ኪዳን ወደ ሐዲስ ኪዳን የተሸጋገረ ሕዝብ ቤተክርስቲያን ተብላለች።

ቀዳማዊ ምኒልክ/እብነ ሐኪም ከንግሥተ አዜብና ከንጉሥ ሰሎሞን ተወለደ። ምኒልክ ማለት ምን ይመስል ምን ያምር መሆኑም ተፅፏል። የእብነ ሐኪም/ምኒልክ ዘር ወርዶ ወርዶ ከናልኬ የተወለደው ባዚን በኢትዮጵያ ነግሦ 8 ዓመት ያህል እንደገዛ እየሱስ ክርስቶስ በእየሩሳሌም ያለአባት ከድንግል ማርያም ተወለደ። የባዚን ዘር ወርዶ ወርዶ አግዱር ሰይፈ አርአድን ወልዶ ሰይፈ አርእድ አብርሀ አጽብሃን ወለደ። የስክንድርያው ጳጳስ አናቴዎስ ወደ ኢትዮጵያ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃንን የመጀመሪያው ጳጳስ አድርጎ ሾሞ ላከ።

እየሱስ በተወለደ በ315 ዓመት አብርሃ አጽብሃ አክሱምን ሠሩ። የአብርሃ ዘር ወርዶ ወርዶ ሰልዓዶባ እልዓሜዳን ወልዶ እልአሜዳ ሲነግስ 9ኙ ቅዱሳንን አባ አሌፍ፣ አዘባ ጽሕማ፣ አባ አረጋዊ/ዘ ሚካኤል የሚባለው/፣ አባ አፍጼ፣ አባ ገሪማ፣ አባ ጰንጤሌዎን፣ አባ ሊቃኖስ፣ አባ ጉባ እና አባ ይምአታን ከሮም ከግብፅ አስመጥቶ ኃይማኖትን ባገራችን አቀኑ።

በንጉሥ ሐርቤ ዘመነ መንግሥት ጳጳሳት ከግብፅ እስክንድርያ መምጣታቸው እንዲቀርና ከኢትዮጵያውያን መካከል ተመርጦ እንዲሾም በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ግብፆቹ አልፈቀዱም። በ19ኛው ክ/ዘመን 4ኛው አፄ ዮኃንስ /ከቴዎድሮስ ሞት በኋላ/ ሲነግሡ የንጉሥ ሐርቤ ያልተሳካለትን ለማሳካት ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት እንዲሾሙላቸው ቢጠይቁም ለሳቸውም አልተፈቀደላቸውም። ሆኖም አፄ ዮኃንስም 4 ግብፃውያን ፓትሪያርኮች እንዲላኩላቸው መልሰው በመጠየቃቸው አቡነ ዮኃንስን፣ አቡነ ጴጥሮስን፣ አቡነ ሉቃስንና አቡነ ማቴዎስን ሾመው ላኩላቸው።

በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመን 4 ኢትዮጵያውያን ቆሞሳት አቡነ አብርሃም፣ አቡነ ይስሐቅ፣ አቡነ ጴጥሮስ/ሰማእቱና አቡነ ሚካኤል በግንቦት 25/ 1921 ዓ.ም በካይሮ በቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን በእስክንድርያው በብፁእ ወቅዱስ አቡነ ዮኃንስ 19ኛ እጅ ተቀብተው ተሾመዋል።

የእልዓሜዳ ዘር ወርዶ ወርዶ አፄ ካሌብን ይህ ዘር ዖደ ጎሽ ላይ ደርሶ፣ ዖደ ጎሽ ዓይዙርን ወልዶ ዓይዙርም ነግሦ ሕዝቤ አጠገቤ እየመጣ ቀርበውኝ ፊቴን እያዩ እጅ ይንሱኝ ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው ብሎ አዘዘ። በነገሠ በግማሽ ቀኑ ግን እሱን እጅ ለመንሳት ክልከላው የተነሳለት ሕዝብ በከፍተኛ ግፊያና በፈጠረው መጨናነቅና ትርምስ ንጉሥ ዓይዙርን ረጋግጠው ገደሉት። እናም ከፍተኛ ተከፋይ የሆኑ ቦዲ ጋርዶችና አጃቢዎች ግድ አስፈላጊ መሆናቸው ታምኖበት ፊታቸውን ወደ ሕዝቡ አዙረው እንደ ጅምብራ የሚገተሩና የነገሡት እነሱ እንጂ ያጀቡትና የሚጠብቁት መሪ/ንጉሥ መሆኑን የዘነጉ ሰዎች ተፈጠሩልን።

የምኒልክ ስርወ መንግስት/የዳዊት ዘር ወዳልሆኑት ወደ ዛጔ ዘውዱ የተሸጋገረው የአንበሳ ውድም ልጅ በድልነዓድ ዘመን ሲሆን የዛጔ ስርወ መንግስትን ተረክቦ ለ333 ዓመታት ስልጣኑን ይዘው ከሐርቤይ በኋላ ለዳዊት ዘር የእድም አስግድ ልጅ ለሆነው ለይኩኖ አምላክ ተመልሷል።

ይኩኖ አምላክ 15 ዓመት ነግሦ የልጅ ልጆቹ የልጅ ልጆች ድረስ ዘውዱ ወርዶ 33 ዓመት ወደ ነገሠው እስከ ዳዊት ደርሶ በዳዊት ዘመነ መንግሥት የእየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል፣ የኩርዓተ ርእሱ ሥዕል፣ የእግዝእትነ ማርያም ሥዕል፣ እየሱስ በዕለተ ዓርብ የለበሰው ከለሜዳ ከእየሩሳሌም ከሮም በአንድ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መጡ።

በ7ኛው መቶ ዓመት ሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ በእስልምና ተከታይ አረቦች በመወረሩ ከጊዜ በኋላ በቀይ ባሕር አካባቢ ቀይ ባሕርን ተከትሎ እስከ ህንድ ውቅያኖስ እስልምና እየተስፋፋ በመምጣቱ የአክሱም መንግሥትና ቤተክርስቲያን ከሌላው ዓለም ጋር የነበራቸው ግንኙነት ተቋረጠ። 

ከሁለተኛው ዳዊት የልጅ ልጅ ልጅ የወረደው ንግሥና ዘርዓ ያእቆብ ድረስ ወርዶ ለ34 ዓመት ነገሠ። የሱ ዘር የሆነው የልጁ የበእደ ማርያም ልጅ ናዖድ ለሁለት ጊዜ ያህል ስልጣን እየያዘ በራስ አምዶ አማካይነት ስልጣኑን ተነጥቆ ስለነበር፣ በ3ኛው ጊዜ መንግስቱ ፀንቶለት ለ16 ዓመት ኢትጵያን በገዛበት ወቅት ራስ ዓምዶን አስይዞ መሬት አስቆፍሮ እስከ ደረቱ ድረስ በሕይወቱ ከነነፍሱ በቁሙ ቀብሮ በጭካኔ እንስሳት በላዩ ላይ አስነድቶበት አስገደለው።

የናዖድ ልጅ ልብነ ድንግል/ስመ መንግስቱ ወናግ ሰገድ/ ነግሦ ግዛቱና ሐገሩ ከፍተኛ ሰላም ስለሰፈነበት በዚህ አዝ፣ በሰራዊቱ መብዛት ታብዮ፣ እባክህ አምላኬ ጦር አምጣልኝ ብሎ ለፈጣሪው በትጋት በመፀለዩ ግራኝ መሐመድን ፈጣሪው አስነስቶ ጦርነት የላከለትና ከነልጁ ከገላውዴዎስ ጋር የተማረረባትንና ያዘነባትን በቀላሉ የማትገኘዋን ሰላም ለማጣት የፀለየበትንና የተማፀነበትን ጦርነት ፈርቶና ፈርጥጦ ትግሬ ገብቶ ተደበቀ። የሸሻትንና የተማረረባትን ሰላም ሳያገኝ የፀለየበትንም የጦርነት ጥሙን ሳይወጣው ደንብሮ በሸሸበትና በተደበቀበት በሰሜናዊዋ የኢትዮጵያ ትግሬ በሠራዬ በስደት እያለ ሞተ።

አፄ ገላውዴዎስ ስመ መንግስቱ አጥናፍ ሰገድ ከሰራዬ ተነስቶ ብዙ የትግሬ ነፍጠኞችን አስከትሎ ተከዜን ተሻግሮ ሣርኩሳ በሚባል አገር ሰፍሮ ከግራጁ አህመድ ጋር ጦርነት አድርገው ግራጁ ድል ሆኖ ሲሸሽ አባረው ገደሉት።

በልብነ ድንግልና በግራጁ ጦርነት ሳቢያ በሐገራችን ግልፅ በሆነ በእርዳታና ድጋፍ ስም ፖርቱጋሎችና ቱርኮች ጣልቃ መግባት የቻሉበት ሁኔታ ተፈጠረ። ገላውዴዎስ በድሉ ተፅናንቶ ከትግሬ በሸዋ አድርጎ አማራ ሳይንት ከተመ። በርበሬ ከሚባል እንጨት የተሰራችና ከእየሩሳሌም ያስመጣትን ታቦት ድንግል ማርያም በተወለደችበት ቀን ስምዋን ልደታ አሰኝቶ ተድባበ ማርያም ላይ አስቀደሰ። 19 ዓመት ነግሦም ግዛቱን አስፋፍቶ ሞተ።¾

ይምረጡ
(5 ሰዎች መርጠዋል)
1075 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 999 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us