የጎንደር የተቃውሞው መንፈስና የአማራ ክልል ከተሞች፤

Wednesday, 17 August 2016 13:43

 

ከስናፍቅሽ አዲስ

“ሰላም ከምንም ይቀድማል” የሚለውን መርህ የማይገነዘብ አካል ይኖራል የሚል እምነት የለኝም። በጎብኚ መዳረሻነት የሚታወቁት የአማራ ክልል ከተሞች ባሳለፉናቸው ሰላሳ ቀናት የስጋት ቀጠና ሆነው ከርመዋል። ተረጋጋች የተባለችው ጎንደር የመረጋጋቷ ምልክቶች ምንድን ናቸው? ከተረጋጋችዋ ከተማ ጀርባ ዘላቂ ሰላምን የሚሻው የኢኮኖሚ መሰረቷስ ወዴት እያመራ ይሆን?

የጎንደር የገቢ ምንጭ ንግድና ቱሪዝም ነው። ለንግድና ለቱሪዝም ዘርፍ ከካፒታል በላይ ሰላም ወሳኝና ዋና ጉዳይ ነው። ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ለተከታታይ ቀናት የዘለቀና ወር ያስቆጠረ ስጋት ያጠላባት መዲና በውጪ ጎብኚዎች የሚደራው አብያተ መንግስታቷ ጭምር ጭር ብሎ መዋል ጀምሯል።

ህዝባዊ ጥያቄን ተከትሎ የተከሰተው ግርግር በሁለቱም ወገኖች በመላ የተያዘ አይመስልም። መንግስት የመጣው ይምጣ በሚል አቋሙ ግትር ሲል ለመንግስት አናንስም የሚሉ ገበሬዎችም ይለይልን አሉ እየተባልን ነው። ይሄ ቀላል ችግር ቢመስልም እንደ ጋንግሪን ስር ሰዶ አገሪቷን ሊገድል የሚችል ክስተት ነው። ጥይት በሚጠየፍ ኢንዱስትሪ ኑሮዋን የምትገፋው ከተማ ጥይት እንደ ዜማ ሲንቆረቆርባት ማየት ልብ ይሰብራል።

አሁን መንግስት ከተሞቹ መረጋጋታቸውን እየነገረን ነው። በችግሩ መባባስ ሰዓት ብዙዎቹ የከተማዋ ሆቴሎች ተዘግተው ነበር። ከቀናት ቆይታ በኋላ ተመሳሳይ ችግር የገጠማት ባህር ዳርም ብትሆን ዓለም በጣና ፎረም መዲናነቷ ስሟን ካዳረሰው፣ በዩኔስኮ ባገኘችው ተደጋጋሚ ክብር ከተወራላት በላይ ብጥብጧ ገኖ ርዕሰ ጉዳይ ለመሆን በቃ። የአውሮፓ ሀገራት ዜጎቻቸውን ወደ ባህር ዳር እና ጎንደር ከመሄድ እንዲታቀቡ መከሩ። ዛሬም ድረስ ይሄንን ምክራቸውን አላነሱትም።

መረጋጋቱ በራሱ ትልቅ ጉዳይ ቢሆንም የመረጋጋቱ ምንጭ ህዝባዊ ነው? ህዝባዊ አይደለም? የሚለውን ግን መንግስት ራሱን ይጠይቅ። መረጋጋቱ የአመጹ መንስኤ የሆኑ ችግሮችን በመፍታት፤ ግልጽና ነጻ በሆነ ውይይት ችግሮችን በመገምገም የመጣ መረጋጋት አለመሆኑ ግን እሳቱን የማጥፋት ዘመቻ ላይ ብቻ የተተኮረ አስመስሎታል።

አወዛጋቢ የሆኑ ክስተቶች የተስተናገዱበትን ይሄ አመጽ ከክልሉ መንግስት አቅም በላይ ነበር ወይስ አልነበረም የሚለውም ከህዝብ የተሸሸገ ጉዳይ ሆኗል። በሀገሩ ጉዳይ መረጃ የተነፈገው ህዝብ አሁንም በጉዳዩ ላይ የጠራ ግንዛቤ አለው ለማለት አያስደፍርም። የወልቃይትን የማንነት ጥያቄ ተከትሎ ወደ ይገባኛል ጥያቄ አመራ ቀጥሎ ደግሞ “የህወኃት የበላይነት ይቁም” የሚል መፈክር መስተጋባት ጀመረ። ይሄ ህዝባዊ ወይስ ፓርቲያዊ፤ የገበሬው ብቻ ወይስ የብአዴንም ሰዎች ሹክሹክታ?

ችግሩን ለማብረድ መከላከያ ሠራዊት ገብቷል። መከላከያ ችግር ለማብረድ ወደ አንድ ክልል የሚገባው ደግሞ በህገ መንግስቱ በግልጽ በተቀመጠው አግባብ ችግሩ ከክልሉ መንግስት አቅም በላይ ሲሆን ነው። ከክልሉ መንግስት አቅም በላይ ሆነ የሚባለው ችግር ደግሞ ጥቂቶች ያስነሱት ተብሎ ሌላ ስም ሲሰጠው እየሰማን ነው። እነዚህ ጥያቄዎች አንዱ ካንዱ የሚጣረሱ፤ በየትኛውም ወገን ጥርት ያለ መረጃ የማይሰጥባቸው ሆነው ተስተውለዋል።

ይሄ ሁሉ ሆኖ ከተሞቹ “ወደ መደበኛ ህይወታቸው ተመልሰዋል፤ ህዝቡም ተረጋግቷል” የሚለውን ዜና አድምጠናል። መረጋጋትና ሰላም የሁሉም ወገን ፍላጎት ነው። መረጋጋቱ ግን ከራሱ ከህዝቡ የመጣ፣ ህዝቡ ያመነበት፣ በካድሬዎች የአቋም መግለጫ ጋጋታ ላይ ያልተመሰረተ መሆን ይገባዋል። ሰላም በውሸት አይመጣም። ሰላምን በፖለቲካዊ ስራ ማረጋገጥ አይቻልም። ሰላምን በጉልበት ለማምጣት መሞከርም ቀን ጠብቆ ዳግም የሚደፈርስ ሰላም መጠንሰስ ነው። ስለሆነም መንግስት አሁንም የተነሱ ጥያቄዎችን ማድመጥ፣ ማብላላትና መመለስ ይኖርበታል። ይሄ ነው አስተማማኝ ሰላም አግኝተናል የሚለውን ማረጋገጥ የሚያስችል ስልት፤ የጎንደርን ድባብ ወደ ነበረበት ተመልሷል የሚለው ዜና ተስተጋብቶ ሳያልቅ ከሰኔ 8-10 ቀን 2008 ዓ.ም. ሶስት ቀናት የሚቆይ ከቤት ያለመውጣት አድማ በከተማዋ ተጠራ፤ የከተማዋን ጎዳናዎች ጭር ያደረገው ይህ አድማ ተመልሷል የተባለው ሰላም ከግምገማ ራሳቸውን ማዳን የፈለጉ ካድሬዎች የውሸት ሪፖርት እንጂ ህዝባዊ መሰረት ያለው ውጤት እንዳልሆነ አሳይቷል።

አሁን የከተማዋ የሆቴል ገበያ ከአልጋዎቹ እንኳን ተነስተን ብንመለከተው የመያዝ አማካይ እድል በግምት ወደ 8 በመቶ ወርዷል። ሱቆች ከሚከፈቱበት የሚዘጉበት ጊዜ በዝቷል። የንግድ እንቅስቃሴዋ ተዳክሟል። የባህር ዳር ከተማም ብትሆን በተመሳሳይ ቀስ እያለ የሚሸረሸር የንግድ እንቅስቃሴ ድባብ ውስጥ እየገባች ነው።

ሰሚ ካለ

የመንግስት ሹማምንት መስማት አለባቸው። የሚናገሩት ለህዝብ መረጃ የሚሰጥ እውነት ሊሆን ይገባል። የክልሉ መንግስት መቆጣጠር ያቃተው አመጽ ተከስቶ ነው መከላከያ የገባው? የክልሉ መንግስት መከላከያ ይግባልኝ ብሎ ጠይቋል? የክልሉ መንግስት አመጹን መቆጣጠር አቃተው ለማለት የሚቻልበት አግባብስ አለ? የአማራ ልዩ ኃይል ተመልካች የፌዴራል ፖሊስ አድማ በታኝ የሆነበት ምስጢርስ ምን ይሆን? እነዚህን ጥያቄዎች የሚመልስ መረጃ ህዝቡ ይፈልጋል። በሌላ በኩል አመጹን በሆደ ሰፊነትና የህይወት ህልፈትንና የአካል ጉዳትን በሚቀንስ መልኩ ለመከላከል መንግስት ብዙ መስራት ይኖርበታል። ህዝቡም ጥያቄዎቹን ታከው የዘር ግጭቶች እንዳይስፋፉ፤ በሀገር ልጆች መካከል እልቂት እንዳይፈጠር፤ በቀማኞች ከሚታቀድ ዘረፋ ንጹሃን የላባቸው ፍሬ እንዳይነጠቁ መጠበቅ አለበት።

ከዚህ በኋላ ሁለቱም ወገኖች መደማመጥ አለባቸው። አመጽን የሚቀሰቅሱና መንግስት ጉያ ሆነው የመንግስት ወገን መስለው የተተራመሰች ሀገር ለመፍጠር እኛ እንዲህ ነን የሚሉ፤ መከላከያውን የአንድ ብሔር ነው አይነት የዘራቸው የጀግንነት ውጤት አድርገው ችግሩን የሚያፋፍሙትን አደብ የሚያስገዛ ብሔራዊ የደህንነት አካል ከፈዘዘበት መንቃት አለበት። ካድሬዎች የኔ ወረዳ ሰላም ነው። የኔ ከተማ ህዝብ ይሄን አይደግፍም እንደውም ያወግዛል ለማለትና አጋጣሚውን ወደ በለጠ ሹመት ከፍ የሚባልበት መድረክ አድርጎ ለመጠቀም የሚጣደፍ ካድሬዎችን በንስር ዓይን መመልከት ይሻል። ህዝቡን አስፈራርቶ አደባባይ እንዳይወጣ ማድረግ ህዝቡ የተቃውሞ ስሜት እንዳይኖረው ማድረግ ማለት አይደለም። ህዝቡን አስገድዶ አቋም መግለጫ እንዲሰጥም ማድረግ ችግሩን ማለባበስ እንጂ ማጽዳት አይደለም። እናም ሳይረጋጉ የተረጋጉ ከተሞችን የማረጋጋቱ ስራ ህዝብን ያሳተፈና ያሳመነ መሆን ይገባዋል።¾

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
667 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 809 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us