የፃድቃን ኑዛዜ “አውቀን እንታረም”

Wednesday, 17 August 2016 13:44

 

በዶክተር ልዑል ጃገማ (ከካህናት መንደር)

 

ሜጄር ጄኔራል አብይ አበበ የተባሉ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የጦር መኮንን በአንድ ወቅት “አውቀን እንታረም” ሲሉ አንዲት አነስተኛ መጽሀፍ አዘጋጅተው ነበር። ዳሩ የስጋ ዘመዳቸው የሆኑት አጼ ኃይለስላሴ ባይወዱላቸውም ቅሉ። እኔ ዛሬ የጄኔራል አብይ አበበን ርዕስ ተውሼ ለመጻፍ የተገደድኩት በቅርቡ የቀድሞው የህወሓት ታጋይና የጦር አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳዔ ሰሞኑን አንድ መጣጥፍ ማዘጋጀታቸውን ሰንደቅ ጋዜጣ ላይ መመልከቴ ነው። ጄኔራል ፃድቃን ላቀረቡልን የኑዛዜ እና የማሳሰቢያ መልዕክት ሳላመሰግናቸው አላልፍም። ሆኖም ከጄኔራሉ ሀሳብ ተነስቼ የማልስማማባቸውንና ከእውነት ልንታረም የሚገባንን ነጥቦች አንስቼ የጄኔራል ፃድቃንን ጽሁፍ ባነበብኩበት ጋዜጣ ላይ መልስ ለማዘጋጀት ስላሰብኩ ነው።


የሌተናል ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሣዔ የአስተሳሰብ ቅኝት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ካደረጉት ሃሳቦች መካከል የሚከተለውን የምንባብ ክፍል በጥሞና ስናጤን ነው።
“ከዚህ ከ1997 ዓ.ም ምርጫ ጋር ተያይዞ የሚነሳ አንድ መጥፎ ጠባሳ አለ። ይኸውም በምርጫ እኔ አሸንፌያለሁ፣ እኔ አሸንፊያለሁ በሚል የተሟሟቀ ክርክር ውስጥ ቅንጅት በግልፅ በአደባባይ ዘረኛ የሆነ ፕሮፖጋንዳ ማስፋፋት ጀመረ። ውስጥ ለውስጥ በተደራጁ ሃይሎችም ይህንን ፀረ የትግራይ ተወላጆች የሆነውን ዘመቻቸውን አስፋፋው ይህንን ዘረኛ አስተሳሰባቸውን በተገቢው መንገድ አላስተባበሉም። ኢህአዴግ ደግሞ ይህንን አድሃሪ ዘረኛ ፕሮፖጋንዳ አስተጋባው ሊፈጁህ ነው…።”
ከዚህ በላይ ከተጠቀሰው ምንባብ ተነስተን የሚከተሉትን ሃሳቦች ብቻ መሰንዘር ሃሳቡን ጠቋሚ ያደርገዋል።

 

 


1ኛ. “ከ1997 ዓ.ም ጋር ተያይዞ የሚነሳ አንድ ጠባሳ አለ።” የምትለው ሀረግ የሚያስማማን ሲሆን ጠባሳውም በሁለት የተከፈለ ነው። እርሱም የፍርሃት ጠባሳ እና የሞት ጠባሳ ናቸው። የትግራይ ህዝብ ፍርሃት አድሮበታል፤ በዘረኝነት የተነሳሱ ሀይሎች እንዲጠፋ ተቀስቅሶበታል። ለዚህም ቅንጅት የትግራይን ህዝብ ይቅርታ አልጠየቀም ይላሉ። ይህ አስተሳሰብ የትግራይ ህዝብ ሊበደል ነበር የሚል ሀሳብ ነው። ከዚህ ሀሳብ የምንረዳው ጸሃፊው የሚያምኑበት ዋናው ነገር እንደ ህወሓት እንደሆነ፤ ከህወሓት የተለየ ሀሳብ እንደሌላቸውና አሁንም ቅንጅት የዘር ቅስቀሳ አድርጎ እንደነበረ ነው። ይህ መጣራትና መስተካከል የሚገባው ኀሳብ ነው። የዘር ቅስቀሳው የሃሰብ ፕሮፓጋንዳ ወይስ ሌላ? ቅንጅት በተደራጀ መልክ የጠየቀው ወይስ ሌላ? ለምሳሌ የምኒልክ የልጅ ልጆች መጡብህ፤ አማራ መልሶ ሊገዛህ ነው። ደርግ ኢሰፓ፤ የነፍጠኛ ልጆች መጡብህ እያሉ የቀሰቀሱ የህወሀት-ኢህአዴግ ልጆች እንዲያስተባብሉ ለምን አልጠየቁም? የትግራይ ህዝብ ማስፈራራት ደርሶበታል የሚለውን ቅዠት እንቀበለውና የሞቱ ንጹሃን የኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ ለምን ይቅርታ አልተጠየቀም? ጸሃፊው አማራ ጠላትህ ነው ብሎ ያስተማረው ወያኔ ተሳስተን ነበርን ብለው እንዲጠይቁ አልጠየቁም። ይሁን እንጂ በግፍ ስለተጨፈጨፉት፤ በተግባር ስለሞቱት፤ በግብር ስለገደሉት ትንፍሽ ሳይሉ የሃሳብ ወይም የምናብ ጠባሳን ማጉላት ፈልገዋል። ፍላጎት ብቻውን እውነት እንዳይደለ አላጤኑትም ወይም ለማመን አልፈለጉም።


2ኛ. የዘረኝነት ቅስቀሳ ከ1997 ዓ.ም ጀመረ የሚለው ሀሳብ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርገው ዘረኝነት የ1997 ዓ.ም ምርጫ ቅስቀሳ ውጤት ነው ለማለት ተፈልጎ ነው፡፡ ይህ አያስኬድም። ዘረኝነት በአንድ ወቅት ብቻ ወይም ወር ውስጥ እንዴት ሊፈጠርስ ይችላል? የዞረ ድምር አይመስለዎትምን? ይህንንም በተለወጠ አዕምሮ መመርመር እና በመንፈስ ልዕልና ማመን ያሻዋል። ህብረተሰቡ እራሱን እንዲፈትሽ የሚጽፍ ሰው ወያኔንም ራሱን እንዲፈትሽ መሞገት ይገባዋል።


3ኛ. ዘረኝነትን አሰፋፋው:- “መስፋፋት” የሚለው ቃል ፈጠረው ከሚለው የተለየ ነው። የተስፋፋው ያለው ነው። ያለውና የነበረውን አድሎ የቅስቀሳ መንፈስ ነው ያስፋፋው ማለት ይቻል ይሆናል። ምንአልባት ይህ የተከሰተው የዚህ መንግስት አወቃቀር የፈጠረው ሊሆን ይችላል። በእርግጥ ያን ያህል የተጋነነ የዘረኝነት ችግር ነበር ብሎ ማሰብም አይቻልም ነበር። ጥላቻ ነበር ይሁን እንጂ ይህን ጥላቻ በሀይል አፍነን ያዘነው ማለትም ይመስላል። ቢቀበሉትም ባይቀበሉትም የኢትዮጵያ ህዝብ አብሮ የመኖር ታሪክ የወለደው መቻቻል እንጂ የህወሓት ሀይል አይደለም ህዝቡን ከግጭት ያዳነው። ይህንን እርሰዎም ያምኑበታል።


4ኛ. ፀረ ትግራይ የሆነ ድርጅቶች ውስጥ ለውስጥ ተደራጁ የሚለው መረጃ ከኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ የተወሰደ ሀሳብ ከመሆኑ ውጪ እነ እገሌ ተደራጁ ብሎ መናገር እስካልተቻለ ድረስ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ የፕሮፓጋንዳ እና የምናብ ድርሰት ነው። አያስኬድም። ይህም ሊታረም የሚገባው ሃሳብ ነው። አገር በምናብ ፈጠራ አትመራም።
5ኛ. የመንግስት ድርሻ የተከሰቱ ሊከሰቱ፣ ያሉ ወይም ወደ ተግባር የተጠጋጉ ሀሳቦችን ማረም እንጂ ማስፋት አይደለም። ኃላፊነት የጎደለው ህወሓት ፀረ ህዝብ የሆኑ መፈክሮችን እያሰማ መጥቶ የስልጣን ማማው ላይ ተቆናጠጠ። የተለያዩ ተቋማትን ተቆጣጥሮ በአድር ባይ ጋዜጠኞችና መጣጥፎች በቴሌቪዥን እና በፖለቲካ ስብሰባዎች ጸረ ህዝብ አቋሙን አንጸባረቀ። ህዝብም ሰማው። ግን ተፋው።


ለምሳሌ ፀረ አማራ ፕሮፓጋንዳ ሲያሰማ የነበረ መንግስት ምን አባነነውና የሩዋንዳ እልቂት ትዝ ያለው? ወይም የዘመረው? መጠየቅ የነበረበት ያለበትና የሚኖርበት ጉዳይ ነው። የዚህ ማወራረጃው ብሔራዊ እርቅ እና ንሰሃ ነው። ይህ ግን የፖለቲካ ቁማርን የተላበሰ ድንክዬ ጨዋታ መሆን የለበትም። ብዙሃኑ ያሸንፋልና። መሸሽ አይቻልም። ታሪክ ዕድሜ ልክን ሲያሳብቅ ይኖራልና።


ሌተናል ጄኔራል ጻድቃን የኢህአዴግ (ህወሓትን) በስልጣን ያቆየውን ምሰሶ በጥልቀት የመረመሩበት ሂደት መሳጭ እና ተገቢ ምልከታ ነው፡፡ ሃሳቡ እንዲህ ተጽፏል።
“በዚህ ሁኔታ ኢህአዴግ ከተቃዋሚዎች የሚሰነዘርበትን ተቃውሞ መቋቋም የቻለው በመቶዎች የሚቆጠር የሰው ህይወት በመግደል ነው። የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንና አባላትም ወህኒ ወረዱ። በዚህ ሂደትም ሁለት ግልፅ የሆኑ መልእክቶች ተላለፉ። አንድ፥ የፖለቲካ ስልጣን እንዲሁ በቀላሉ በምርጫ አሸንፍያለሁ ስለተባለ እንደማይሰጥ። ሁለት፥ የመንግስትን ስልጣን የተቆጣጠረው አመራር ስልጣኑን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመጋራት ያሸነፈን የፖለቲካ ሃይል በሰላማዊ መንገድ ማስተናገድ ሳይሆን የፀጥታ ሃይሎችን ተጠቅሞ እንደሚያጠፋ ግልፅ ሆነ። የኢህአዴግ መንግስት በፖለቲካዊ አስተሳሰብ ብልጫና ይህ ብልጫ የሚያስገኝለትን የሕብረተሰብ ድጋፍ ሳይሆን የመንግስት ስልጣን በመቆጣጠሩ የሚያገኘው የፀጥታ ሃይሎች ድጋፍ በስልጣን መቆየት መወሰኑን ግልፅ አደረገ።”


የህወሓት ብልጫ፤ “ብልጫ” የሚለው ቃል መስተካከል ይገባዋል። የበለጡ የመሰሉ ወይም የብልጫ መንገዶች ሁሉ ብልጫ ሊያመጡ አይችሉም የሚያስፈጽሙለት የሚከተሉት ናቸው። ሠራዊቱ፣ የሃሰት ጸረ-ትግራይ እንቅስቃሴ አለ ብሎ ማሳመንና የበላይነትን እስከመጨረሻው ማስቀጠል ናቸው፡፡ በመሆኑም


1ኛ. የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በተለይም ፀረ ትግራይ እንቅስቃሴን ውዥንብር ፈጠራ መሆኑንና ይህን በመፍጠር ማህበራዊ ፍርሀት ለመፍጠር መንቀሳቀሱ አንዱ ሲሆን ይህ ግን በትግራይ ማህበረሰብ ዘንድ እንደጸሀፊው ሀሳብ ግቡን ቢመታም በጠቅላላው ማህበረሰብ ዘንድ የፈረሰ ጨዋታ መሆኑን የሚያሳየው ዘረኛ ያሉት ቅንጅት እንደ ድርጅት ጠፍቶም ቢሆንም አገራችን አጣብቂኝ መንገድ ላይ ትገኛለች ብለዋልና።
2ኛ. ኢህአዴግ ለመሸነፍ ያልተዘጋጀ መሆኑን በውስጥ ታዋቂ ማመኑ፣
3ኛ. ኢህአዴግ በምርጫ ስልጣኑን እንደማይለቅ በውስጥ ታዋቂ ማመኑ፣
4ኛ. ኢህአዴግ በሰራዊቱ ኃይል የመቀጠል ፍላጎት እንዳለው በውስጥ ታዋቂ ማመኑ፣
5ኛ. ሰራዊቱ ሊታረም የማይችልና ከላይ እንዳነሱት ወገንተኝነቱ ለትግራይ እንደሆነና ምናልባትም ሊታረም የሚችለው ህወሓት ሊታረም ብቻ ነው የሚል ሃሳብ በመያዙ፣
6ኛ. ሰላማዊ ትግል የተሟጠጠ ዋጋ ቢስ እና የማይሰራ እንቅስቃሴ መሆኑን የፖለቲካ ምህዳሩን ያጠበቡት አካላት መንግስት የጦር ሰራዊቱ እና በምሽጉ ውስጥ የተሰባሰቡ ፀረ ዴሞክራሲ ሃይሎች እንደሚዘውሩት በመታየቱ። ይህ አውቀውም ይሁን ሳያውቁት የፈነጠቁት መረጃ ነው። ይህም ያስመሰግነዎታል፣
7ኛ. የህብረተሰቡ አሰተሳሰብ (ፍላጎት) የኢህአዴግ የስልጣን ምንጭ እንዳይደለ ጽሁፉ አንጸባርቋል። ይህ ደግሞ የህወሓት//ኢህአዴግ ህዝባዊነት የሞተ መሆኑን ያሳያል። በመሆኑም የህዝብ ድምፅ ተራ የማስመሰል የፖለቲካ ጨዋታ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡


ጸሀፊው አንድ የሚያሳስባቸው ጉዳይ አለ፡፡ ይህም የኢህአዴግ መንግስት በማህበረሰቡ የተጋረጠበት ከባዱ ችግር አድርባይነት ነው ይሉናል። ሀሳቡ እውነት መሆኑን የምናየው የኢህአዴግ ፓርቲ አባላት በኦሮሞ እና በአማራ ክልል (ደህዴን ፈራ ተባ እያ የሚከተል ነው) በግልጽ ወገንተኝነታቸውን ለህዝብ በማሳየታቸው የተገለጠላቸው ይመስለኛል። አድርባይነት የኢህአዴግ ትልቁ ችግር መሆኑን መንግስት አምኗል። ይህ እንግዲህ ጸሀፊውና ኢህአዴግ እየተቀባበሉ የሚመጋገቡ ያደርጋቸዋል። በሌላ በኩል የአድርባይነት ያለባቸውን ፓርቲዎች አዳክሞ ቢያንስ አድርባይነት ያልታየባቸውን ህወሓትን አንጥሮ እና አጠናክሮ በማውጣት የበላይነት ለማረጋገጥ የተላከች ብቻኛ መልዕክት ትመስላለች።


በአንደኛነት አድርባይነት የተላበሱት የህወሓት ሰዎች ናቸው ወደሚል ትርጓሜ የሚያመጣን የአደርባይነት መለኪያው ፖለቲካዊ ወገንተኝነት በመሆኑ ነው። ጸሀፊው ቆም ብለው ሊፈትሹት የሚገባው ነገር ባለፉት 25 ዓመታት ትግራይ ውስጥ ይህ ነው የሚባል ተቃውሞ በህዝቡ ዘንድ ያልተነሳው ለምንድን ነው? ታፍኖ ነው ከተባለ የትግራይ ህዝብ ደርግን የመሰለ አፋኝ እንዴት አፈንግጦ እና ተጋፍጦ በአሸናፊነት ሊወጣ ቻለ? ጀግንነቱ የት ሄደ?


ዝምታው የመጣው በሁለት ምክንያት ነው። አንድም የትግራይ ህዝብ አልተበደለም አለዚያም ወያኔ ከደርግ የባሰ አፋኝ በመሆኑ ታፍኖ ነው። አንደኛውን ምክንያት ወሰድን እንበል። የትግራይ ህዝብ አልተበደለም የሚለውን ብንወስድ የትግራይ ህዝብ በስርዓቱ ተጠቃሚ ነው ወደሚል ድምዳሜ ይወስድናል። ይህ ባይሆንና ሁለተኛውን ምክንያት ብንወስድ ደግሞ ወያኔ ከደርግ የባሰ ጨቋኝ ነው ካልን መሻሻል የሌለው የማይለወጥ በሰላማዊ ትግል ሳይሆን በትጥቅ ትግል በመፋለም የሚለወጥ ድርጅት ነው የሚለው ሃሳብ ተገቢ ሊሆን ነው ማለት ነው። ከህወሓት መማር ይህች ናት። ሶስተኛው መላምት ደግሞ ወያኔ አፋኝ ነው ካልን በሰው አገር በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ለምን ወጥተው በግልጽ መታገል አቃታቸው? ይህ መልስ የሚሻ ጉዳይ ነው።


ጸሃፊው ከተናገሩት ነቅሰን የምናወጣው ስህተት የኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ “አድርባይነት” እንደ አዋጭ የፖለቲካ መንገድ ተወሰደ የምትለው አመለካከት አንዷ ናት። ጸሀፊው ሊሰሙት የፈለጉትን ብቻ ሊሰሙ መፈለጋቸውን ጽሁፉ አሳይቷል። ኢህአዴግ አንድ ለአምስት የሚለው አደረጃጀት ውሸት መሆኑን ቢያንስ የኦሮሞ እና የአማራ ትግል ፉርሽ አድርጎታል። ይህ አድርባይነት ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ይህ ሁሉ ሲሆን አገር ሲታመስ አባላት የት ሄዱ? ያስብላል። አድርባይነት በህብረተሰቡ ውስጥ አለ የሚሉት ኢህአዴጎችም ሆኑ ጸሀፊው የኢትዮጵያን ህዝብ አደረጃጀት የስነ ልቦና ጦርነት እና አጥቂነት ባህሪ አላጤኑም። ይህ የዝምታ የትዝብት እና የይሁንታ ማለትም ምን አገባኝ ቀን ሲያልፍ የሚል ፍልስፍናውን ከመዘንጋት የመጣ ነው፡፡ ህብረተሰቡ አድርባይነት ያጠቃው አይመስለኝም። ህብረተሰቡ አድርባይ ሆኖ ወይስ በዝምታ እያጠቃ ነው? መልስ ያሻዋል። ይህችን ስነ ቃል ማጤን ተገቢ ነው።


“እግዜር ምድር ወርዶ ጉዱን ነግሬው
የደላኝ መስሎታል ተመስገን ብለው”


ተመልከቱ! እንደ ስነ ቃሉ አባባል እንኳን ወያኔን ከስልጣን ወርዶ እግዚአብሔርም ከምድር ከወረደ ኢትዮጵያውያን ጉዱን ይነግሩታል ማለት ነው።
ጸሀፊው ሀቅ መፈንጠቅ መጀመራቸው ያስመሰግናቸዋል። ሀቁን የፈነጠቁት ከረጅም ዓመታት በኋላ መሆኑ በጥርጣሬ ምልከታ ብናየውም የተናገሩትን ይዘን ለምን ዛሬ በማለት መሞገት ተገቢ አይሆንም። ዛሬ ታይቷቸው ቢሆንስ? ከዛሬ ነገ ይሻሻላል ብለው ቢሆንስ? አቶ ስዬ አብርሃ “የኢትዮጵያ እስር ቤት የኦሮሞ መንደር ሆነ” ያሉት እኮ ከታሰሩ በኋላ ነበር። ይህ የሚያሳየው በወያኔ ውስጥ መኖር የመንግስትን ሙሉ መረጃ እንደማይሰጥ ሲሆን በሌላ በኩል ነገሩ የተገለጠላቸው ቁስሉ ሲወጋቸው ገብቷቸው ሊሆንም ይችላል። በእሳቸው አነጋገር ቢያንስ ጸሃፊው አጸደቅነው የሚሉት ህገ መንግስት አፈር ከድሜ ሲበላ የአድርባይነቱ ሰለባ ነበሩ። ለህገ መንግስት እና ለእኩልነት የታገለ ሰው ጫካ መግባት ካለበት አሁን ነበር የሚያስብል ሁኔታ ተፈጥሮ እንዴት በዝምታ ተዋጡ ያስብላል። ወይንስ አሁን ሲመሩት የነበረው ድርጅት የወደቀ (የተዳከመ) ስለመሰላቸው የተቃውሞ ማርከሻ መጻፋቸው ነው? ይህን እርሳቸው ያውቁታል። እኛም ብንሆን እንጠረጥራለን ቢያንስ በእነዚህ ሀረጎች። ይታያላቸውን እንይላቸው ከዚያም እንጠርጥራቸው፡፡


1. የትግራይ ህዝብ በመሃል አገር እየተገለለ ነው (ጥላቻ ይንጸባረቅበታል) ይታያል
2. የትግራይ ህዝብ ተጠቃሚ መስሎ ይታያል፤
3. በሰራዊቱ ውስጥ አድርባይነት ይታያል፤
4. በኢህአዴግ ውስጥ አድርባይነት ይታያል፤
5. በህብረተሰቡ ውስጥ አድርባይነት ይታያል የሚሉት ይጠቁማሉ።


እነዚህን ሁነቶች አንስቶ መወያየትና በየትኛውም ጊዜ ሀሳብን ማንጸባረቅ ተገቢ ኃላፊነት ነው። ማዘናጊያ ግን ሊሆን አይገባም።
ጸሀፊው ካነሱት አንድ ሀሳብ እጅግ አመራማሪ ነገር ይታያል። ይህም እንዲህ የምትለው ምንባብ ናት።
“ሆኖም ይህ ከላይ የተገለፀው ሁኔታ ረጅም መቆየት ስለማይችል ሕብረተሰቡ ከሚሸከምው በላይ ስለሆነበት የመንግስት የስራ አስፈፃሚው አካል በሕብረተሰቡ ላይ የሚፈፅመው በደል ስለበዛበት፣ ከዚሁ ጋርም የኑሮ ውድነቱ፣ ስራ አጥነቱ፣ ለችግሮቹ መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ግልፅ አቅጣጫዎች አለማየቱ ጋር ተቀላቅሎ የኢህአዴግ መንግስት በምርጫ መቶ በመቶ አሸንፍያለሁ ባለበት ማግስት በከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞ እና ሌሎች ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ገብቷል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ቢያንስ ችግሮቹ የሚገለፁበትን መልክ በማንሳት በግልፅ ችግር አለብኝ እንዲል አስገድዶታል። ከላይ ከተጠቀሰው ፖለቲካዊ ሁኔታ ተነስቼ ሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ሶስት ቢሆኖች (scenarios) ያሉ ይመስለኛል።”


ይህች ንባብ ብሶት የወለደው የምትለውን የኢህአዴግ ዜማ አስታወሰችኝ። ህብረተሰቡ ከሚሸከመው በላይ የሆነበትን ችግሮች እንውሰድ ቢያንስ በጸሃፊው ምልከታ።
1. የመንግስት ስራ አስፈጻሚ የሚያደርሰው በደል፣
2. የኑሮ ውድነት፣
3. ስራ አጥነት፣


ህወሓት/ኢህአዴግ መቶ በመቶ ምርጫውን ማለትም ጊዜያዊ የኃይል ብልጫውን አሸንፌያለሁ ባለ ማግስት ችግሩ ህዝቡን ለአመጽ አነሳሳው ይሉናል። ይህ ከሆነ የህብረተሰቡ ችግር እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት በትግራይና በትግራይ ማህበረሰብ ውስጥ የሉም ወይ? የትግራይ ህዝብ መቶ በመቶ ደጋፊዬ እና አባሌ ነው የሚባለው ተቃውሞ የማያሳየው ለምንድን ነው? ወይንስ በትግራይ የኑሮ ውድነት የለም? ወይስ በትግራይ ልጆች መካከል ስራ ማጣት የለም? ይህ ከሆነ እንግዲህ ትግራይ እንደ ህዝብ አልተጠቀመም የምትለዋ ንግግር ፉርሽ ልትሆን ነው ማለት ነው። የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች እንዳይሆን። ይህ ምን ማለት ነው? ከላይ ከተዘረዘሩት ሶስት ነጥቦች አንድ መጨመር ያለበት የትግራይ የበላይነት አለ የሚለውን ሃሳብ ማጥናት ይገባል፡፡ ነገሩ ካለ (የትግራይ የበላይነት) አቧራ ቢያስነሳም፣ ለመዋጥ የምታስቸግር ሂስ ብትሆንም መዋጥና መታረም ነው።


በሌላ በኩል የትግራይ ምሁራንና ባለሃብቶች በትግራይ ከሚደርስባቸው ችግር የተነሳ ወደ መሃል አገር (አዲስ አበባ) እየፈለሱ ነው የተባሉት አዲስ አበባ ሲመጡ ለምን ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት ችግሮች ሊደርስባቸው አልቻለም? ከደረሰባቸው ደግሞ ለምን ሲቃወሙ አይታዩም? ወይስ በመሃል አገር ሌሎች እንደሚሉት ጥቅማቸው የተጠበቀላቸው ዜጎች (ምናልባትም አብዛኛው ህዝብ እንደሚለው አንደኛ ደረጃ ዜጋ) ሆነው ይሆን?

የማመንና ያለማመን መንታነት፡- ፈፋውን ይሻገሩ!
የጸሃፊው ፅሁፍ አንድ ወደፊት ሁለት ወደ ኋላ አንድ ወደ ኋላ ሁለት ወደ ፊት አንድ ወደ ግራ ሁለት ወደ ቀኝ እያሉ በምጥ የወለዷት ሰሞነኛ ልጃቸው ናት። አስቦ መናገር የአንድ አዋቂ ሰው ምልክት እና ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ መለኪያ ነው፡፡ አንዳንዶች የእሳቸው ልጅ ሳትሆን የሌሎች ሰዎች እርሳቸውንም ጨምሮ የጋራ ልጅ ናት ይላሉ። አንዳንዶች ደግሞ የለም የጄኔራሉ የጉዲፈቻ ልጅ ናት ይላሉ። ለእኔ “እኔ ነኝ” ካሉ የግድ የእሳቸው ነው ብሎ ማመን ይገባል። ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ አቅም ያጣሉ ብዬ አላስብም። የሰውን ችሎታ በጭፍን ማቃለል አይስማማኝም። ምሁራዊም አይደለም። ይህን ካልኩ በኋላ የጄኔራሉን መንታ ልብ እና የማመንና ያለማመን መንታ መንገድ እንመርምር ወደሚለው ልሻገር። በነገራችን ላይ ወታደር አንድ ልብ ወይም ቁርጥ መንገድ ይመርጣሉና ጄኔራሉ ውትድርናውን ውልቅ አድርገው ጥለው ስለሚኖሩ ይሆናል ባለመንትያ ልብ የሆኑት።


የጸሃፊውን የእምነት ቃል እናጢን። የጸሃፊው የእምነት ቃል በአራት ክፍል ከፍዬ ሳጤነው የሚከተለውን ይመስላል።
1ኛ አውቀው ያመኑት
ጸሀፊው አውቀው (Deliberately) የተቀበሉት የተባለው አምስት ነገሮችን ለመቀበል ፈቃደኛ በመሆናቸው ብቻ ነው። አውቀው ያመኑት የሚል ንዑስ ርዕስ የሰጠሁት አውቀው ያመኑት ሆነ ሳያውቁ ያመኑት ሲሆን ከዚያም አልፎ ለብቻቸው ሲሆኑ አውቆ ወደ ማመን ያሸጋግሩት ይሆናል የምለውን ነው። ማን ያውቃል፡፡ ያም ሆነ ይህ ለህዝቡ በግልፅ እንዲነበብ ከለቀቁት አስተሳሰባቸው ብቻ ተነስተን አውቀው ስላመኑት ነገር ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል።

አውቀው ያመኑት ቃል አንድ
ኢትዮጵያ እጅግ አጣብቂኝ መንገድ ላይ ትገኛለች ያሉት የመጀመሪያው አውቀው ያመኑት ቃል ነው። ይህ ማለትም ማንም የሚቀበለውን የሚያየውንና የሚሰማውን ጥቅል የኢትዮጵያ ህዝብ አመጽ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ መቀበላቸው ነው። አንዳንድ ሰው ይህ ታዲያ ምን ያስገርማል ሊል ይችላል። አዎ እውነትን እያዩ መቀበል አይደንቅም። በከሀዲያን እና አድርባይ ፓርቲ ውስጥ ተኮትኩቶ ያደገና ያሳደገ ሰው ወደዚህ የመንፈስ ልዕልና በፈቃዱ መጥቶ በእውነት ለመጠመቅ መወሰኑ ትልቅ የህሊና ጉልበት ይጠይቃል። የክህደቱ ቁልቁለት እጅግ ጥልቅ ነውና።

አውቀው ያመኑት ቃለ ሁለት
ሁለተኛው የእምነት ቃል ለትግራይ ህዝብ መልዕክት ሲያስተላልፉ የሰጡት የእውቀት የእምነት ቃል ነው። ይኸውም ህዝብ በጠላው የጦር ሀይል ተማምኖ እየጨቆኑ እና እየገዙ መኖር ዘላለማዊነት ያለው ዋስትና እንደማይሆን አምነዋል። ቢያንስ ይህን ለማመን የግንባሩ ግንባር ቀደም የህወሓት መሪ መሆናቸውን ያሳያል። ከታሪክ የተማሩ ብቸኛው ሰው ያደርጋቸዋል። ያለፉትን መንግስታት ታሪክ በደንብ እና በሚገባ ሁኔታ ማጤናቸው ግብዓት ሆኖላቸው አይተናል። አውቆ ማመን ይላሉ ይህች ናት!!
“ሞት ክህደት ነው ሲተረጎም፤ ፈራሽ መሆን ነው መክሰም
የሩቁን አለማየት ፤የኋላውን አለማጤን አለማለም
አጥፍቶ መኖር …ከዚያም ወድሞ ማውደም” የምትለዋን ሥንኜን ሳያነቡ አልቀረም።

አውቀው ያመኑት ቃል ሶስት
ህወሓት /ኢህአዴግ/ ቢያንስ ከ1997 ዓ.ም ምርጫ (ብልጫ) በኋላ በህዝብ ምርጫ ስልጣን ላይ ያልተቀመጠ ድርጅት መሆኑን አምነዋል። ከዚሁ ጋር አፈና መኖሩንና የዴሞክራሲ ጠላቶች ኢህአዴግ በሚባለው ድርጅታዊ መዋቅር ውስጥ ተሰግስገው መኖራቸውን አምነዋል። ጸሀፊው ዋናውን አብዬ (አብዮተኛ) ፀረ ዴሞክራሲ ግለሰብ ሳያነሱ፤ ስም ሳይጠቅሱ አፋኝ የተቆጣጠረው ድርጅት መሆኑን አምነዋል። ይህን ደግሞ አውቀው ነው ያመኑት። የጸሀፊውን እመነት አደንቃለሁ። ለዚህም በፈለጉት መንገድ እንደወታደር የእጅ ሰላምታም ሆነ እንደ ሲቪል ከወገቤ ሸብረክ ብዬ ምስጋና አቀርባለሁ።

 

አውቀው ያመኑት ቃል አራት
ጸሀፊው የህወሓት ታጋዮችን ሲገልጹ ጀግኖች እንደነበሩ አውቀው አምነዋል። ሁሉም ትግሬ በዚህ ይስማማል። ኢህአዴግም ግንቦት 20ን ሲያከብር ይህን ሳይናገር ያለፈበትን ዘመን አናውቅም። ወይም አልሰማንም። አልሰማሁም የሚል ወዲህ ይበል። ጸሀፊው ግን ከዚህ በመዝለል ሀቁን ገልጸውልናል። የትግራይ ታጋዮችም ሆኑ ባለፈው መንግስት ስር የነበሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ጀግኖች ነበሩ ብለውናል። አስደናቂ ምልክታ ነው። ኢህአዴግ ያሸነፈበት ዋናው ምክንያት የዓላማ ጥራት ነው ብለውናል። ያስኬዳል። የኢትዮጵያ ወታደር ደግሞ በመንግስት ተጽዕኖ ምክንያት የተሰለፉ ባይሆኑም የዓላማ መዘባረቅ እንዲሸነፉ እንዳደረጋቸው መግለጻቸው ጥሩ ምልክታ ነው። ይህም ያስኬዳል። ከዚህ በመነሳት ጸሃፊው “ጀግንነት” በቂ አይደለም እያሉን ነው። ጀግና ዋና መሳሪያው ዓላማ እና ሊኖርበት የወሰነው የዓላማ ጥራት ነው። ድንቅ ፍልስፍና ስለሰጡን አድንቀነዎታል። እርሰዎንም ከጀግና ወገን ለማሰለፍ በግሌ እደፍራለሁ፤ እውነቱን ለመናገር ደፍረዋልና። ሀቂ ማለት ይህች ናት!! ከዚሁ ጋር አንድ ላስታውስ የምፈልገው ህውሓት ያለፈውን መንግስት የተዋጋው ብቻውን ሆኖ ሳይሆን ከጎኑ ሻዕቢያ፣ ወያኔ ራሱ ፣ኢህዴን፣ መኢሶን፣ ሲአን፣ ኦነግ፣ ኦብነግ፣ ዓረቦች እና አሜሪካ ነበሩና ነው። ስልጣን ላይ የወጣው ህወሓት ብቸኛ ጀግና አያደርገውም። ለዚህም ሌተናል ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳዔን የመጀመሪያ ምስክር አድርጌ ጠርቻለሁ። ሁሉም ጀግኖች ነበሩ የምትለዋን አሰመርሁባት!!!!!!!!!
“አማራ እና ትግሬ
ኦሮሞ እና አደሬ
በአንድነት የኖሩ
የእናንተ ወላጆች በአንድነት ነበሩ
ሁሉም አንድ አይነቶች ጀግኖችም ነበሩ
አንዱ አንዱን አክብሩ፡፡
ሀድያ ከምባታ
ምናችሁ ተፋታ?
ሲዳሞ እና ጋሞ
ምን አጣላችሁ ደግሞ?” የምትለውን ስንኜን አስታወሰችን። ዳሩ በዘረኞች መንደር የሚያነብ ሲኖር አይደል!!
በሌላ ጊዜ አብዛኛው ታጋይና የታጋይ ማህበረሰብ አባላት የሚዘነጉት ደርግ/ኢሰፓን ማሸነፍ አማራን ከማሸነፍ ጋር ያገናኙታል። ይህ አይገናኝም። በብዙ ምክንያቶች የሚያገናኛቸው ምንም ምክንያት የለም። የትግራይ ህዝብ እና የአማራ ህዝብ አልተዋጉም። ካልተዋጉ ደግሞ አልተሸናነፉም። በጭራሽ። ይህ ሀቅ አንድ ነው። አማራን አርቀን ቀብረነዋል አማራ ተሸንፏል የሚለው ሀረግ ቅዠታዊ ምናብ ነው። የማይሆን የማይሳካ እና ሊታሰብ የማይገባው በጭራሽ።

አውቀው ያመኑት ቃል አምስት
ዋናውንና የመጨረሻውን የእምነት ቃላቸውን ስንቀበል እንዲጠበቅ የሚፈለገው ህገ መንግስት በራሱ በህወሓት/ኢህአዴግ /መናዱን አውቀው አምነዋል። ወይንም ተገድቧል ብለውናል፡፡ በሌላ እነጋገር ተሸራርፎአል እያሉን ነው፡፡ ይህ በእውነት ጸሀፊውን ታጋይ ያደርጋቸዋል። ከብዙ የዝምታ ዓመታት በኋላ ብዕር አንስተው ለመሞገት የተነሱ ታላቅ ሰው አድርጓቸዋል። ህገ መንግስቱን መናድ የሀገሪቱ ርዕሰ ወንጀል ነው። ቢያንስ ጸሀፊው እንዳመለከቱት እንዲጠበቅ የሚፈልጉት (ህገ መንግስቱ) ህግ አውጭው ተርጓሚው እና አስፈጻሚው ንዶ የጨረሰውን ህገ መንግስት ነው፡፡ ጸሀፊው ታላቅ የሆኑበትን ይህን ሃሳብ ይዘን ህወሓት/ኢህአዴግን ፍርድ ቤት መገተር ነበረብን። ሆኖም ግን ምን ያደርጋል ተርጓሚውና አስፈጻሚውም ንዶታል። በመሆኑም ህገ መንግስት ናዱ የተባሉ ግለሰቦች ሁሉ ዛሬ ከእስር ቤት ነጻ መውጣት ነበረባቸው!!!!።
2ኛ. ሳያውቁ ያመኑት
ጸሀፊው የስነ አመክንዮ (Logic) ድርዳሮሽ ሲያሰካኩ አፈትልከው ያመለጡ ሳያምኑ ያመኑበት ወይም ሳያውቁ ያመኑት እውነታን አግኝተናል። ለቸር ሰው ይስጠውና! ከቸር ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ ይሏል ይህች ናት።

 

ሳያውቁ ያመኑት ቁጥር አንድ
“ከአንዳንድ የትግራይ ተወላጆች ጋር ስንወያይ (ብዙሃን ቁጥር መሆኑን እንገነዘባለን) አሁን ያለውን የትግራይ የበላይነት (አሁን ባለው መንግስት ላይ ያለንን “የበላይነት”) እንዴት እናስቀጥል (ካጣን የምትለዋ ቃል ፍታቴ ናት) የሚል ጥያቄ በውይይታችን ተነሳ ይላሉ። በዚህች ሀረግ ውስጥ ሁለት ቃላት ጸሃፊውን ሰንገው ይዘዋል። እነርሱም 1ኛ የትግራይ የበላይነት እና 2ኛ እንዴት ይቀጥል (እንዳናጣ) የሚሉት ሀረጋት ናቸው። የትግራይ የበላይነት የሚለው ሀረግ አንድም ሃሳቡና ፍላጎቱ መንገሱን እና ሁለትም የበላይነት መኖሩን ማረጋገጡ ነው። እንዴት እናስቀጥል (እንዳናጣ) የምትለዋ ሀረግ ደግሞ እውነትን ታሳብቃለች። “ማስቀጠል” (እንዳናጣ) የሚለው ቃል ያለው እንዲቆይ ማድረግ ነው። ይህ ማለት ላለፉት 25 ዓመታት ያረጋገጡትን የትግራይ የበላይነት ለሚመጡት ዓመታትም ማስረገጥ ነው። የበላይነቱን ካመኑ በኋላ ለማስቀጠል መፈለጋቸው አጠያያቂ ነው። ከዚህ በመነሳት የጸሃፊውን ዓላማ መጠራጠር የተፈለገው ለዚህ ነው። ጸሃፊው የበላይነቱን ማስቀጠያ መንገዱ ላይ ሳይሆን አይቀርም ከሌሎች የትግራይ ተወላጆች ለየት ያሉበት መንገድ። በትልቋ አትዮጵያ የትንሿን ትግራይን ጥቅም ማስጠበቅ ተገቢ ነው፡፡ በትንሿ ትግራይ የበላይነት የትልቋን ኢትዮጵያ ጥቅም የማይሞከር ነው፡፡ ጸሃፊው በዚህ ያምናሉ፡፡

ሳያውቁ ያመኑት ቁጥር ሁለት
ጸሃፊው ሌላ በዚህ ቦታ ላይ የፈነጠቁት እውነታ የትግራይ ህዝብ ዋናው ጭካኔ እና ክፋት የመነጨው ታላቅ መስሎ ለመታየት ከሚደረገው ሽርጉድ ነው። “የትግራይ ህዝብ ታላቅ መስሎ መታየት አለበት ይላሉ” ይሉናል። ልብ በሉ የጄኔራሉ ወዳጆችና አብረዋቸው የሚወያዩት እንደ እኔ አይነት ተራ ዜጎች አይደሉም። ወዳጆቻቸው የህወሓት ባለስልጣናት ናቸው ብሎ መገመት ስህተት አይሆንም። በመሆኑም ታላቅ መስሎ የመታየት ፍላጎት ያሳዩት እነዚህ ቱባ ባለስልጣናት ናቸው። ከሆኑት በላይ መስሎ መታየት ለምን አስጨነቃቸው? ሌሎቹን ህዝቦች እንደ ጠላት የመቁጠር ዝንባሌ ያለ ይመስላል። መምሰል ከውስጥ ከሚፈልቅ መፍረክረክ የሚወጣ የእንግዴ ልጅ ነው። በመሆኑም ህወሓት የያዘውን ጀግንነት እና እውነተኛ ማንነትን ለመቀበል የተሳነው ይመስላል።

ሳያውቁ ያመኑት ቁጥር ሶስት
የትግራይን ህዝብ ማጠናከርና አጠናክሮ ማውጣት የጸሃፊው ዋና ግብ መሆኑን ከጽሁፉ ተረድተናል። በእርግጥ “ኢትዮጵያ እንድትጠናከር እፈልጋለሁ” ይላሉ። ይህንም ለማሳካት ቃል ገብተዋል። እናመሰግናለን። ይሁን እንጂ ህወሓት አሁንም ህወሓት ነው የሚል ድምዳሜ ይፈነጥቃል።
3ኛ ሰግተው ያመኑት
ጸሃፊው አውቀው ካመኑትና ሳያውቁ ካመኑት ሌላ ሰግተው ያመኑት ሃቅ አለ። ከእነዚህ ሀቆች ውስጥ
1ኛ የትግራይ ህዝብ መገለል ደርሶበታል የምትለዋ አንዷ ናት። ህዝቦች በመፈቃቀድ በመተማመንና በመከባበር በመሰረቱት ህገ መንግስት ላይ ተማምነው በፈጠሯት አዲሲቷ ኢትዮጵያ ለዚያውም “እኩልነት በሰፈነባት” አገር ለምን የትግራይ ህዝብ ተለይቶ መገለል ደረሰበት? መገለል የደረሰበት ቀደም ሲል የተነሳ የስልጣን ጥመኝነትና ፍትሃዊ ያልሆነ የሃብት ክፍፍል በመኖሩ ሊሆን ይችል ይሆን? መልስ ያሻዋል። ለማንኛውም ግን ፈርተው (ሰግተው) አምነዋል።
2ኛ “በሀይል የገዙ ገዥዎች ወድቀዋልና የእኛም የመውደቅ እድል እየፈጠነች እየመጣች ነው” በማለት በስጋት ያመኑት ሌላው ነው። ድርጅታቸው በውድቀት ዋዜማ መሆኑን አምነዋል።
3ኛ “የትግራይ ህዝብ ተጠቃሚ ይመስላል” የሚለው ሃረግ ሳይወዱ በግድ ሰግተው ያመኑት ነው። ለምን የአማራ ህዝብ ወይም የኦሮሞ ወይም ደግሞ የሲዳሞ ህዝብ አታጋዮች ህዝባችን ተጠቃሚ ይመስላል ብለው አልሰጉም? ክቡር ሆይ በባዶ ነገር ላይ ተነስቶ ሰው አይጠረጥርም። ፍተሻውን በጥልቀት በማድረግ በህዝቡ ላይ የሚደርሰውን ችግር ያጢኑ፡፡ ማን ምን እያደረገ ነው? የሚለውን በተከፈተ ጆሮ ልብ እና ምርመራ ማጤኑ ተገቢ ነው።
4ኛውና የመጨረሻው የጸሀፊው የስጋት እምነታቸው “የትግራይ ህዝብ የጥቃት ሰለባ ሊሆን ይችላል” የምትለዋ ናት። በእርግጥ ይህ ከፍተኛ ስጋት ነው። ስጋት ደግሞ በእውቀት ከተጠና እውነት ነው የሚሆነው። በመሆኑም ይህን ለመከላከል መስራትዎ ተመስጋኝ ያደርገዎታል።

4ኛ በወከባ (ፕሮፓጋንዳ) ያመኑት
በወከባ ወይም በፕሮፓጋንዳ ያመኑት የተባለበት ምክንያት ጸሃፊው በማህበረሰቡ መካከል ገብተው በነጻነት እየተጫወቱ ያላካበቱት መረጃ የስጋታቸው ምንጭ ስላልሆነ ነው። እስኪ ልጠይቀዎ! ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ውጪ፤ ከኢህአዴግ ሌላ፤ ከህወሓት ውጪ ፤አድርባይ ያልሆነ የመረጃ ምንጭ አለዎትን? ያለዎት አይመስለኝም። ካለዎት ደግሞ ሊሰሙት ወይም ሊቀበሉት አልፈለጉም። ለምሳሌ ከቴሌቪዥን ጣቢያ በወከባ ካመኑት መካከል


1. ቅንጅት የዘረኝነት ቀስቃሽ ነው ያሉት ከኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ የመነጨ ነው፣
2. በህብረተሰቡ ዘንድ አድርባይነት አለ ያሉትም ከኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ የመነጨ ነው፣
3. የሩዋንዳ እልቂት ፍርሃት ከኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ የመነጨ ነው፣
4. መሪዎቹ ትግሬ ቢሆኑም ወታደሩ ከህዝቡ የመጣ ነው ያሉት ከህወሓት መንደር ያገኙት የካድሬ ውይይት ብንለው ያስኬዳል፣
በነገራችን ላይ ክቡር ሆይ የአማራ መንግስት ስትሉት የነበሩት እኮ ሁሉም አማራ ስልጣን ላይ ወጥቶ አልነበረም። ሁለት አማራ አይታችሁ ነበር እንጂ። ይህኛው መንግስት እያደረገ ያለውን ግን ሁሉም የሚያየው የሚዳስሰውና የሚያውቀው ሃቅ ነው። ብዙ የትግራይ ሚኒስትሮች ይታያሉ። በዚህስ እጅግ ተረቱ!!


“ክቡር ሆይ እጅጉን ተረቱ
ዓይነዎን ቢከፍቱ ከእውነት ባለተፋቱ
ታግለው አታግለውን ስለ ሃቅ በሞቱ፡፡
የእርስዎን ውለታ በሳልነው፣
ባቆምነው፣
ተርከን በጻፍነው፣
ቋሚ አርገን በያዝነው፣
በቅርጽ በሀውልቱ።
ምክር ልምከርዎት ይጠጉ ከእውነት
እውነትን ሸፋፍነው በጽሁፍ ቢከትቡት
ይጠረጠራሉ ማንም አያምነዎት፡፡” የምትል ስንኝ ቋጠርኩለዎት።

የጀመሩትን የእውነት መንገድ ይቀጥሉ፡፡ ምናልባ አጽብሃ ወ አብርሃ ዘ ኢትዮጵያ ይሆኑ ይሆናል፡፡ ስምዎም ምስጥር የተመሰጠረበት ነው፡፡ ጻድቃን እና የትንሳኤ ስራ፡፡
በስተመጨረሻም የጸሃፊውን የስጋት ሁነቶች (scenarios) እየተጋራሁ በመፍትሔ ሀሳቦች ላይ ልዩነት አለኝ። ጸሃፊው በጥገናዊ ለውጥ ሲያምኑ እኔ በዚያ ተስፋ ማድረግ ካቆምኩ ሰነባበትኩ። በመሆኑም በጸሃፊው የመፍትሔ ሀሳብ ላይ ለምሳሌ “መከላከያ ሀብት መሰብሰብ የለበትም፣ የማይመለከተውን ስራ አይስራ” የሚለው ሀሳብ ትክክል ቢሆንም ትልቁ የህብረተሰቡ የችግር ምንጭ የመከላከያው ግዝፈት አይደለም፡፡ ይህም አይመስለኝም ህብረተሰቡን ያሰጋው። አፈናው የወጣው የአንድ አካል ሁለት ገጽታ ከሆኑት መከላከያ እና የፖለቲካ ድርጅቶች ነው። ቢያንስ እርስዎ የመከላከያን ወገንተኝነት ለማን እንደሆነ በጽሁፈዎ በማንጸባረቀዎ ቁጥር አንድ ምስክር ይሆናሉ በማለት ተስፋ አደርጋለሁ።
የእርሰዎን የመፍትሔ ሀሳብ በሚከተሉት ምክንያቶች ለመቀበል ያስቸግረኛል።
1. የመፍትሔ ሀሳቦችዎ ወደ አንድ ወገን ያጋደሉ በመሆኑ ፤
2. መልክ አልባ መፍትሔዎች በጽሁፈዎ ተንጸባርቀዋል። የሚፈልጉት ለውጥ ወይስ ጥገና አንዱን የግድ መርጠው ይንገሩን።
3. ህገ መንግስቱ ተንዷል ወይስ የመናድ አደጋ ነው የገጠመው እርስ በእርሱ የሚጣረስ ሀሳብ በጽሁፈዎ ይንጸባረቃል። ከተናደ የናደውን ህወሓት/ኢህአዴግ መታገል ወይስ ከእውነት ሸሽቶ ሌሎችን መውቀስ (ሊንዱ ነበር ብሎ በመላምት መሳብ ዕውቀታዊ አይመስለኝም)
4. ስህተትን አውቆ መታረም እና መጸጸት ወይስ ሊከሰቱ ይችላሉ በሚሏቸው ነገሮች ላይ መንጠልጠል። “አውቀን እንታረም” የምትለዋን የጄኔራል አብይ አበበን ድርሰት እንዳነበቧት ተስፋ አደርጋለሁ።
5. አውራውን ትቶ መንጋውን መውጋት ትክክል አይደለም። ፍሬውን ትቶ ገለባውን መውቃት ይሆናል። ስለሚሊተሪው የበላይ አካል ተነጋግሮ ችግርን በመፍታት ወደ ተራ ወታደሩ መምጣት ይቻላል። ሁለቱን ግን ማሳከር አይገባም። ህወሓትን ትቶ ኢህአዴግን ማረም ልክ አይደለም። ህወሓት ኢህአዴግን ትቶ ተቃዋሚውን ማጥቃት የድርጅተዎ የሻገተ የማጥቂያ መሳሪያ ነው። እርሱን መታገል ይገባል።
6. የማጥቂያ መሳሪያዎችን ማክሸፍ ላይ ብዙም አልተናገሩም። ለምሳሌ የሽብርተኝነት ህግ የጸረ ሙስና ህግ እና የልማት (ህዳሴ) ፀር የሚሉ ቃላት መሳሪያዎች ናቸው። ህዝቡ አውቋል። ለዚህም ምሳሌ ኦሮሞ “አሸባሪውን” ኦነግን ደግፎ ኦነግ ነኝ አለ። ሙስሊሙም የታሰሩ መሪዎችን ወክሎ እኛም እነሱ ነን አሉ እኮ! የባህር ዳር ህዝብ ሁላችንም ግንቦት ሰባት ነን አሉ። እንግዲህ ኦሮሞ እና አማራ እንዲሁም ሌሎች ህብረተሰቦች አሸባሪ ተብለው የተጠሩትን ነን ሲሉ በተግባር አባል ሆነው ይመስለወታልን? አይመስለኝም። ህጉ ወላቃ እንደሆነ መናገራቸው ይመስለኛል። እንግዲህ ሁሉንም የኦሮሞ እና የአማራ ህዝብ አሸባሪ ብላችሁ ለመክሰስ በጀተ እና እስር ቤቱም አይበቃም ብለው ወዳጆቸዎን ይምከሩ። የትግራይ ህዝብ አንድ ቀን ሲከፋው ሁላችንም ሻዕቢያ ነን እንዳይለን እሰጋለሁ።
በአክብሮት እሰናበታለሁ።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
925 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 886 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us