የሰሜኑና የደቡብ ንጉሦቻችን

Wednesday, 24 August 2016 14:21

 

ወሰንሰገድ መሸሻ በላቸው / This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. /

ካለፈው የቀጠለ

 

አግዓዝያን የተባሉት የነገደ ዮቅጣን ነገስታት 52 ጊዜ መንግስትን የያዙ ሲሆን ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ1985 ዓመት ጀምሮ እብነ ሐኪም/ቀዳማዊ ምኒልክ እስከነገሠበት እስከ 982 ዓመት ለ1003 ዓመት ቆይተዋል።

የደርግ መንግስት ትንቢቱ ይፈፀም ዘንድ ፈጣሪ አምጥቶ የደፋብን ታላቅ መአት ነበር። ሌሎቹ ደግሞ እሱን ደፍተው በተራቸው እንዲሰፍሩብን ፈጣሪ እንደገና ደፋብን። በመዝገበ ቃላት መአት መቅሰፍት፣ መከራ፣ ጭንቀት፣ ወዮታ የሚል ፍች ያለው ሲሆን መአት ወረደን ደግሞ ድንገተኛ መከራ፣ ያልታሰበ መአት፣ መቅሰፍት ሁኖ ወረደ፣ አገር አጠፋ ብሎ መዘገበ ቃላቶች ይፈቱታል። ደርግ ትውልድን ፈጅቶ ቢያልፍም፣ ከዱር የወጡ ቢሆንም በስደት ስም ዘመናዊነትንና ስልጣኔን የተላበሱ ሰሜነኞች ባፍጢሙ ደፍተው መአት ይዘው ተክተውታል።

በእብራይስጥ ቋንቋ ሰሜን ማለት ዳርቻ ወይም መጨረሻ ማለት ሲሆን የዓለምን ሉል በጥንቃቄ ቢመለከቱ ከእስራኤል ሰሜናዊ ዳርቻ የምትገኘው አገር ደግሞ ሶቪየት ኅብረት ናት። ደርግ ሶቪየት ጋር ጨንጓራውን ገልብጦ አንድነት ከመፍጠር ባለፈ ሶቪየት በሃገራችን ውስጥ ያለች አንድ ክፍለሃገር ሆና እንደዜጋ በቅናሽ የሚኖሩባት ባለቤት አልባ ሐገር አደረጓት። ዛሬ ከሶቪየት ያላቀቀን ፈጣሪ አሻሽሎ ለቻይና አሳልፎ ሰጥቶናልና ተመስገን ማለት ግድ ይላል።

ሰሜናዊቷ ሶቪየት በሌኒን አደራጅነትና መስራችነት የሶቪየት ኅብረት ኮሚኒስት ፓርቲ ተመሰረተ። በ1898 የመጀመሪያው ጉባኤ ከተካሄደ በኋላ የሩሲያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ሌበር ፓርቲ ሲንቀሳቀስ ቆይቶ በሁለተኛው ጉባኤ ላይ ቦልሼቪኮችና ሜንሸቪኮች ሁለት ጎራ ፈጥረው ልዩነት በመከሰቱ የመላ ኅብረት ቦልሼቪኮች ኮሚንስት ፓርቲ በመባል ሲጠራ ቆይቶ በ1952 በ19ኛው የፓርቲው ጉባኤ ላይ የሶቭየት ኮምኒስት ፓርቲ የሚለውን ስያሜ ይዞ ለብዙ ዓመታት ተንቀሳቅሷል።

የወዝአደሩን የበላይ ገዥነት፣ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት፣ የገበሬውን ጥያቄና የመሳሰሉት ዓበይት ጉዳዮች ላይ ቦልሼቪኮች ያነሷቸውን ነጥቦች ሜንሼቪኮች ጨርሶ አልተቀበሉትም፣ እንደ እኛ አገር የዘመናችን ፖለቲካና ፖለቲከኞች ማለት ነው።

የመጀመሪያው የዓለም አቀፍ ኮሚኒስት ድርጅት ከኅዳር 29 - ታኅሳስ 8/1847 ድረስ በለንደን በተደረገው ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ የድርጅቱን ፕሮግራም እንዲያረቅቅ ኃላፊነቱ ለማርክስ ተሰጠ። ማርክስ ፍሬድሪክ ኤንግልስ ጋር በመሆን የነደፉትና በየካቲት 1848 የመጀመሪያው የኮሚኒስት ፓርቲ ፕሮግራም ኮሚኒስት ማኒፌስቶ ወጣ። ‹ከእያንዳንዱ እንደችሎታው ለእያንዳንዱ እንደ ፍላጎቱ› የሚለው የኮምኒስት ክፍፍል መርህ መሆኑን እናስታውስ።

የቻይናው ማኦ ትሴ ቱንግ በ1920 በነማርክስ የተዘጋጀውን ኮሚኒስት ማኒፌስቶን አንብቦ ለትግል የተነሳ ከ1893-1976 የኖረ ከገበሬ ቤተሰብ የተወለደ የኮሚኒስት ቻይና መስራች ነው። ፀረ- ኃይማኖት የሆኑት ኮሚንስቶችና ሶሻሊስቶች ዘለው ፈርጠው ቢወድቁም ቢንኮታኮቱም ኮሚንስቱም ሶሻሊስቱ ሁሉ መልሶ የቤተ እምነቶች ዋና ኃይማኖተኛ ሆነው በቅፅበት ተቀየሩ። አቶ መለስም ጫካ እያሉ የአልባንያ ኮሚኒስት ፓርቲ አቀንቃኝ ሆኑ ምንም እንኳን ጨንጓራቸውን ገልብጠው ከጊዜው ጋር እራሳቸውን ተሀድሶ ቢያደርጉለትም።

ነቢዩ መሐመድ የትውልድ ሐረጋቸው ከነቢዩ ኢብራሂም/አብርሃም ልጅ ከኢስማኤል የሚመዘዘውና 30 ትውልድ ላይ የደረሱት ከገናናው ቁረይሽ ከሚባለው ነገድና/ጎሣ/ የ22 ዓመት ጎልማሳ ከነበሩት ከነጋዴው አባታቸው ከአብደላህና ከእናታቸው ከአሚናት ቢንቱ ውኃብ ተወለዱ።

ነጋዴው አብደላህ በረጀብ ወር ያረገዙትን ሚስታቸው አሚናህን ትተው ለንግድ ወደ ሻም/ሶርያ በመሄድ ገዛ/ጋዛ ደርሰው ሲመለሱ እግረ መንገዳቸውን ወደ ዘመድ ቤት ጎራ ይላሉ። ሆኖም ባጋጣሚ በድንገት ይታመሙና ለአንድ ወር በእንግድነት ባረፉበት ቤት ይቆያሉ።

እመት አሚናህ በእርግዝናቸው ወቅት በየወሩ አብርሃም/ኢብራሂም፣ ሙሳ፣ ሩሕ፣ እስማኤል፣ ኢሳ፣ ዳውድ፣ ሱለይማን የመሳሰሉት ነቢዮች በየተራ ዘወትር በሕልማቸው እየታዩዋቸው አይዞሽ አትባቢ ባለእድል ነሽ፣ ይህ ያረገዝሽው ሕፃን የመጨረሻው ታላቁ ነቢይ ነው እያሉ ያፅናኗቸው ነበር።

በ6 ወር የእርግዝና ጊዜያቸው መልአኩ ጅብሪል በሕልም ተገልፆላቸው አሚናህ ሆይ የዓለምን ጌታ አርግዘሻልና ደስ ይበልሽ፣ ሲወለድ ስሙን መሐመድ ብለሽ ጥሪው ሚስጥርሽንም መሸሸግ አለብሽ ብሏቸው እንደነበር ድርሳናት አስፍረዋል። በዘመኑ የነበሩ ጠንቋዮችና ኮከብ ቆጣሪዎችም ነቢይ የሆነ ኮከብ ወጥቷል። በዚህ ባለንበት ዘመንም ይወለዳል ይሉ ነበር። 

ነቢዩ መሐመድ በ570 ዓ.ም ሰኞ ዕለት በእስያ ክፍለ ሐገር በቀይ ባሕር አጠገብ በቅድስቲቱ ከተማ በመካ ተወለዱ። ነቢዩ መሐመድ የተወለዱ እለት እንደ ፀሐይ የሚያበራ ብርሃን ቀበሌውን ሁሉ አበራው፣ ወገግ አደረገው። ጮራው እስከ ቡስራ/ሐውራን ድረስ ተፈናጥቆ መታየቱን እናቱ አሚናህ፣ በአካባቢው የነበሩ አዋላጆችና ሰዎች በወቅቱ ገልፀዋል።

የፋርስ ሰዎች በእሳት ያመልኩ ስለነበር ሺህ ዓመት ያህል ነዲዱ ሳይጠፋ የቆየውን እሳት እሳቸው በተወለዱበት እለት ጠፍቶ አደረ ብለዋል። መበዘን የሚባል ሊቅ፣ የአረብ ፈረሶች ግመሎችን እየመሩ ከአረብ በርሃ ተነስተው የደጅላንና የፋራትን/ቴግሪስና ኤፍራጥስ/ ወንዝ አቋርጠው በመሻገር የፋርስን አገር ሲወርሩትና ከቤተመንግስቱ ላይ 14 ጉልላቶች እየተገነጠሉ ሲወድቁ ያየውን አስገራሚ ሕልም ለንጉሱ ነገረው።

ንጉሱም ደንግጦ ይህንን ህልም እንዲፈታለት ሰቲህ ወደሚባል ጠንቋይ በመላኩ በአረብ ውስጥ አንድ ትልቅ ነቢይ ተወልዷል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ተከታዮቹ አገርህን ይይዟታል። ከእናንተ 14 ሰዎች በመተካካት ከነገሱ በኋላ የመንግስታችሁ ፍፃሜ ይሆናል ብሎ እንደ ፈታለትና ይህም በእርግጥ እንደተፈፀመ፣ በየቦታው የነበሩ ብዙ ጣዖታት ከየስፍራቸው እየተናወጡ መውደቃቸውን የጣዖታት አምልኮ ፍፃሜ እንሆነም ተመዝግቧል።

የሰሜኑ ጥንስስ የህውሃት ኢህአዴግ አባል ድርጅት የሆነውና በ1984 ዓ.ም የተመሰረተው የደቡብ ህዝቦች ንቅናቄ ያፈራውና ደቡብን የወከሉት ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰሜነኛውን መለስን ተክተው የነገሡ የኢትዮጵያ መሪ ናቸው።

ከደርግ ውድቀት ማግስት ጀምሮ ከሰሜነኞቹ እነ መለስ ጋር የሚቆሙ የሚታመኑ የደቡብ ልጆች በማስፈለጋቸው በደቡብ ከሚገኙ ብሔረሰቦች ውስጥ የተማሩ ሰዎችን አፈላልጎ በማነጋገር ብሔራዊ ድርጅት ማቋቋም አስፈለገ።

ኢህአዴግ ጉራጌ ውስጥ የጉራጌን ብሔረሰብ፣ ወላይታ ውስጥ የወላይታን ብሔረሰብ፣ ሀዲያ ውስጥ የሃዲያን ብሔረሰብ፣ ከምባታ ውስጥ የከምባታን ብሔረሰብ የሚወክሉ የተማሩ የሚሏቸውን ሰዎች አፈላልገው በመመደብና ኮንፈረንስ አዘጋጅተው የድርጅት ምስረታ ጉባኤም ተደርጎ በድርጅቱ ውስጥ አቶ ኃይለማርያምም ባጋጣሚው ተከስተዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኘው የወላይታዎች ስርወ መንግስት በ1250 እ.ኤ.አ መጀመሩን፣ የዳሞት ስርወ መንግስትና የወላይታ ስርወ መንግስት በመባል በሁለት ተከፍለው ይተዳደሩ እንደነበር በ1954 ሲኤፍ ባኪንግሃምና ጂ ደብልዩ ቢ ሀንቲንግ ፎርድ የተባሉ ሳም ሪከርድ ኦፍ ኢትዮጵያ በሚል ርእስ ባቀረቡት የምርምር ጥናታቸው ገልፀውታል።

ወላይታ በዓፄ ምኒልክ አስተዳደር ውስጥ እስከተጠቃለለበት ድረስ በርካታ ነገሥታት ተፈራርቀውባታል። ነገሥታቱም ካዎ/ንጉሥ ይባላሉ። ከነዚህ ካዎዎች/ነገሥታቱ መካከል ከ1560 ጀምሮ የነገሱት ካዎ ሚካኤል፣ በ16ኛው መቶ ክ/ዘመን ካዎ ግርማ፣ በ17ኛው መቶ ክ/ዘመን ካዎ ገዝሃኝ፣ በ17ኛው ክ/ዘ/መባቻ ካዎ አዳዩ፣ በ18ኛው መባቻ ካዎ ሊባና፣ ከ1740-1761 ካዎ ቴቤ፣ ከ1761-1800 ካዎ ኦጎቶ፣ ከ1800-1835 ካዎ ኢማሞ፣ ከ1835-1845 ካዎ ዳሞታ፣ ከ1845-1886 ካዎ ጎቤ፣ ከ1886-1890 ካዎ ጋጋ እና የመጨረሻው የወላይታ ንጉሥ የነበሩት ከአፄ ምኒልክ ተዋግተው በመንግሥታቸው ሥር የተጠቃለሉትና ከ1890-ጥቅምት1895 የኖሩት ካዎ ጦና ወላይታን እየተፈራረቁ መርተዋል። 

ወላይታ ከካዎ/ንጉሥ ጦና በኋላ እስከ አፄ ኃይለስላሴ ውድቀት ድረስ ከመሃል ሐገር በሚላኩ አስተዳዳሪዎች ስትመራ ቆያታለች። በደርግ ዘመን በሲዳሞ ክ/ሐገር ስር ተጠቃላ ወላይታና ሶዶ አውራጃ ተባለች። ከደርግ ውድቀት በኋላ በብሄር ፖለቲካው ክልል 9 ስር እንድትጠቃለል ተደርጋ የክልሉ ማእከል ሆና ክልል 7. 8. 9. 10 እና 11 አንድ ላይ በመጠቃለል የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ተብሎ በክልል ደረጃ ሲደራጅ ወላይታም በዞን ደረጃ ተደራጀች። እናም ከዚህ ዞን የተገኙት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ካዎ ኃይለማርያም የሚለውን የወላይታ ካባ ሳይደርቡ፣ በወላይታ ሳይገደቡ በመላው ኢትዮጵያ የተሰየሙ ደቡባዊው የመጀመሪያው የሐገር መሪ ሆኑ።

ኃይለማርያም ደሳለኝ ሐምሌ 19/1965 በወላይታ ቦሎሶ ሶሬ በምትባል ቦታ ተወለዱ። በዚያው በቦሎሶ ሶሬ ተምረው በ1988 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሲቪል ምህንድስና በባችለር ዲግሪ ተመርቀው በአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ/ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት ሰርተዋል።

በዩኒቨርስቲው ቆይታቸው ባገኙት ተጨማሪ የትምህርት እድል በፊንላንዱ ቴምበር ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ በአካባቢ ጥበቃ በሳኒቴሽን ኢንጂነሪንግ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተቀብለው በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ለ13 ዓመታት በዲንነት አገልግለዋል።

በ1990ዎቹ መጨረሻ ወደ ፖለቲካው በመግባት በኢህአዴግ አባልነት ተመዝግበው መንቀሳቀስ ጀመሩ። እድል የምትከተላቸው የወላይታው ኃይለማርያም የደቡብ ም/ፕሬዚደንት በመሆን እየሰሩ ሳሉ ፕሬዚደንቱ አባተ ኪሾ በሙስና ተከሰው ስልጣናቸውን ሲነጠቁ ኃይለማርያም ተተክተው/ወርሰው ከ2001-2006 ድረስ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፕሬዚደንት ሆኑ። ታማኝነታቸው በመረጋገጡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነትና ም/ጠቅላይ ሚንስትርነትን ደርበው በመለስ አገዛዝ ስር ሲሰሩም ሰሜናዊው መለስ በመሞታቸው ጠቅላይ ሚንስትርነቱንም ከሰሜን ወደ ደቡብ ዞሮ በተመሳሳይ እድል እንደዋዛ ለሚገዟቸው ሊገዙ የመለስ ዙፋን ላይ ተቀመጡ፣ የመለስን ቡራቅ ዘውድ ደፉ፣ በደወ ሥልጣን ተቀበሉ። ከሶስት አመት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ደግሞ በምርጫ ጠቅልለውት እስካሁን ድረስ ይዘውታል። ለውሃ ልማትና ዝመና በትምህርት የተዘጋጁት ኃይለማርያም በተከነበለችባቸው እድል የሐገር መሪ ሆኑ።

አፍሪካ ከቅኝ ገዢዎች መምጣት በፊት መጠነኛም ቢሆን በራስዋ የውስጥ ሂደት ላይ የተመሰረተ ዕድገት ታሳይ ነበር። ከ16ኛው እስከ 18ኛው ምዕተ ዓመት የነበረው ጊዜ አንዳንድ ሐገራት የዕድገት ኃይላቸውን ያጠራቀሙበት፣ የዓለም ገበያ የተፈጠረበትና እየሰፋም የሄደበት፣ በምእራብ አውሮፓ የጥሪት ክምችት መፈጠሩና ታዳጊ በመባል የተፈረጁት ሐገራት ደግሞ በተቃራኒው መራቆትና በይበልጥ ወደ ጥገኝነት የገቡበት ጊዜ ነበር።

የአውሮፓውያን መስፋፋት ቅድመ ካፒታሊስት ኅብረተሰብ የበታችና የወራሪዎቹ ኃይል ተገዢ ሆኑ። ባንዳንድ አካባቢ በሰሜንና በደቡብ አሜሪካ ነዋሪ የነበሩ ዜጎች ባብዝሃኛው ተደመሰሱ። በቦታቸውም ከአውሮፓ የተሰደዱ ነዋሪዎች፣ ከተለያዩ የአፍሪካ ሐገሮች በባርነት በተጋዙ ሰዎች ተተኩበት። የእነዚህ ጉልበት፣ ጥሬ እቃ፣ የተለያዩ የእርሻ ምርት ውጤቶችን ዘርፈው በመውሰድ በአውሮፓ ለካፒታል ክምችት ከፍተኛ ድርሻ አበረከቱ።  

አፍሪካ በ15ኛው ምዕተ ዓመት የነበረችበት ደረጃ በዜጎቿ በሚሰሩ ዕደ ጥበባትና ምርጥ የእጅ ስራዎች በክህሎት የተካኑ ዜጎች ባለቤትና የበለፀገች ሐገር ነበረች። ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ኑብያ፣ ሞሮኮ፣ ምዕራብ ሱዳን፣ ዚምባብዌ፣ ቤኒን እጅግ የዳበሩና ከአውሮፓውያን የሚስተካከሉ ሐገሮች ነበሩ። በምርት ጥራት ጊኒ፣ ሞሮኮ፣ ሰሜን ናይጀሪያ፣ ማሊ፣ ካታንጋና ዛምቢያና ሴራሊዎን ተጠቃሽ ሐገሮች ነበሩ። ቅኝ ገዢዎች በሰበብ አስባቡና በጥቂት የአፍሪካ ተወላጆቹ ራስ ወዳድነት አጋዥነት ሳቢያ በራስዋ የውስጥ ሂደት ተመስርቶ የነበረው ዕድገቷን አጠፉት።

አውሮፓ በወታደራዊ መስክ በተለይም በጦር መሳሪያ የበላይነት መያዝና ከሌሎች ሐገሮች አንፃር ሲታይ አውሮፓ የነበረባትን ቁሳዊና ሰብአዊ ድኅነት በገዛቻቸው ሐገራት ሐብት ላይ መመስረቷ ፍላጎቷን አሳደገው። አፍሪካውያንና እስያውያን የሚፈልጉትን ከአውሮፓውያን ማግኘት አይችሉም፣ አውሮፓውያን ግን ከአፍሪካም ሆነ ከእስያ የሚፈልጉትን በቀላሉና በፍጥነት ማግኘት በመቻላቸው ለልዩነት መስፋት አስተዋፅኦ አድርጓል።

ከማርኮፖሎ ታሪካዊ የምድር ጉዞ ጀምሮ እስከ ቫስኮደጋማ የባህር ጉዞ፣ ከዚያ በኋላም ብሪትሽ ኢስት ኢንድያ ኩባንያና ሌሎች መሰሎቹ ያደረሱት ብሔራዊ የሐብት ዘረፋ ጥቂቶቹን ማበልፀግ፣ አብዝሃኞቹን ሐገሮች ደግሞ ጨርሶ ያራቆተ ጉዳይ ነበር።

በአፍሪካ በ16ኛው ምዕተ ዓመት የባሪያ ንግድን አስፋፍተው አህጉሪቱን የብጥብጥና የመመሰቃቀል፣ ዜጎቿን በግፍ መጨፍጨፍና መግደልን ስራየ ብለው ተያያዙት። የዜጎቿ ቁጥር ተመናመነ፣ በጎሳዎች መካከል የእርስ በርስ ብጥብጥና ጦርነት የሚከፈትበትን ሁኔታ ፈጥረው እርስ በርስ እንዲተላለቁና እንዲፋጁ አደረጓቸው።

አፍሪካ ውስጥ የሚመረቱትን እዚያው አፍሪካ ውስጥ እንዲሸጥ እንጂ ወደ አውሮፓ ገበያ እንዳይደርሱ ሲያደርጉ ኖረው በመጨረሻም ከአፍሪካ የሚመረት የኢንዱስትሪ ምርት ቆሞ የአፍሪካን ጥሬ እቃዎች ብቻ ወደ አውሮፓ እያጋዙ የአውሮፓ ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ አምራች ሆኑ። በእደ ጥበብ ይተዳደሩ የነበሩ የአፍሪካ ሙያተኞች ወደ እርሻ በመሰማራታቸው የመሬት ጥበት ተከሰተ። ከቅኝ አገዛዝ በፊት በዶማ ይቆፍሩ የነበሩ ብዙ አፍሪካውያን ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ሆነው የራሳቸውን መንግስት ሲመስርቱም በዶማ የሚቆፍሩ ሆነው ነው የተገኙት።

የአፍሪካ ኢኮኖሚ እያሽቆለቆለ ሄዶ፣ የምግብ ተመፅዋች ሐገር አደረጓት። ማንነታቸው በቅኝ ገዢዎቻቸው ተቀየረባቸው፣ ሁለመናቸው ከስር ከመሰረቱ ተናግቶ የራሳቸው የነበረውን እያስጣሉዋቸው ገዢዎቻቸው የሰጧቸውንና ያሰመሩላቸውን ብቻ እንዲያጠብቁ ተደረጉ፣ እናም ሆኑ። በቅኝ ገዢዎቹ የተተኩት የአገሬው መሪዎች እንደ ገዟቸው ገዢዎቻቸው እነሱም የራሳቸውን ዜጎች በሰለጠነ ባርነት ቀጥቅጠው ከእንስሳ አሳንሰው ገዟቸው። ይህ ስልት የዳበሩ/የበለፀጉና በሌላ በኩል ደግሞ ታዳጊ/ያልበለፀጉ ወይም ኋላቀር ሐገሮች የሚል ብዙ እርቀት የተለያዩ ረድፎችን ፈጠረ።

የዳበሩ የበለፀጉ/ሀብታሞቹ በጅምላ ሰሜን ተብለው የተሰየሙ ሲሆን ያልበለፀጉት ኋላቀሮቹ ታዳጊ ሐገራት ደግሞ ድሆቹ ደቡብ ተብለው ተሰይመው መንቀሳቀስ ጀመሩ። ደቡብ የሚባሉት ኋላቀር ሐገሮች አዲስ የሆነ የኢኮኖሚ ስርአት እንዲለወጥ፣ ሰላም፣ የጦር መሳሪያ ቅነሳና ለሰው ልጆች ደኅንነትና ብልፅግና እና ሚዛናዊ አሰራር እንዲኖር የሚጠይቁ ሆነው ሲሰለፉ፣ ሰሜን የተባሉት ደግሞ ይህ እንዲሆን የማይፈልጉና እንደበለፀጉ ለመኖር በተቃራኒው የተሰማሩ ሆኑ።

ሰሜን - ደቡብ ግንኙነት በበለፀጉትና ባልበለፀጉት መካከል ያለ ግንኙነት ሆኖ ቀረበ። ሆኖም በታዳጊ ሐገሮች የተፈበረኩ ሸቀጦች ወደ ሐገራቸው በብዛት እንዳይገቡ በኢንዱስትሪ የዳበሩ ሀገሮች በታሪፍና በመሳሰሉት የሚያደርጉት ግደባ ወይም እገዳ ኋላቀር ሀገሮች ንግዳቸውን እንዳያስፋፉና ለሸቀጦቻቸው ገበያ እንዲያገኙ አሲረው ሰርተዋል።

ዓለም አቀፍ የታሪፍና የንግድ አጠቃላይ ስምምነት/General agreement on tarrif and trade/ በዓለም በሚነግዱ እቃዎች ላይ የሚጣለውን ታሪፍና ለንግድ እንቅፋት የሚሆኑ ሌሎች ነገሮችን ለማስወገድ የሚጥር ድርጅት በ1947 ተቋቁሟል።

የአረቡ አለም ሰዎች እስራኤልን በፍፁም አይፈልጓትም። የኢራኑ መሪ አህመዲን ነጃድ እስራኤል ከዓለም ካርታ መሰረዝ አለባት ብለው በቅርቡ በድፍረትና በይፋ የተናገሩትንና የግብፁ መሪ ናስር ደግሞ ግንቦት 1967 ባደረጉት ንግግር ዋናው ዓላማችን እስራኤልን ለመደምሰስ ነው ማለታቸውን በማስታወስ የአረብ ብሔረተኝነት እንዲያጎነቁልና መልኩን ቀይሮ አክራሪነትን ፈጥሮ አሸባሪ ናቸው እንዲባሉ መነሻ ሆኗል።

የኢራኑ አህመዲን ነጃድ ከኤርትራው ኢሳያስ ጋር ባደረጉት ድርድርም ቀይ ባህርን በመጠቀም የአረቡ ዓለም መሪ ለመሆን መጣራቸውን እና የኑክሊየር ማብላያ በመገንባት ይህን የታመቀ ሽምቅ ምኞታቸውን እውን ለማድረግ ተንቀሳቅሰው ጊዜው ሲደርስ ከስልጣን ወርደዋል።

ግብፅ አውሮፓን፣ እስያንና አፍሪካን የምታገናኝ ድልድይ በመሆኗ መሸጋገሪያ የሚል ስያሜ ተሰጥቷታል። ናስር የመሰረቱት ወታደራዊና አረባዊ ብሄርተኝነት ስሜት የፖለቲካ የትምህርትና የባህል ማእከልነትን አቀዳጅቷታል። ናስር በአረቡ ዓለም የፈጠሩትን ተቀጣጣይ ስሜት በአብዮታዊ አስተሳሰብ ከምዕራባውያን ብዝበዛ ነፃ ለመውጣት የሚያስችለንን ጦርነት እናካሂድ እያሉ በፉከራ በመናገር ለአፍሪካውያንና አረባውያን የመሪነት ስልጣን እስከ መቀዳጀት ደርሰዋል። የአረብ መሪዎች ደግሞ ናስርን ጠልፎ ለመጣል የተወሳሰቡ ሴራዎችንና ወጥመዶችን ያዘጋጁላቸው ነበር። ሁሉም የአረብ ሀገር መሪዎች በየግላቸው እራሳቸውን የአረቡ ሐገራት መሪ አድርገው ስለሚያስቡ በመተባበር ፋንታ እርስ በርሳቸው በመናናቅ ይጠላላሉ፣ ይናናቃሉም።

ናስር ይህች ዓለም መድረክ ናት ይላሉ። በመድረኩም ላይ ግብፅ ዋነኛዋ ተዋናይ ናት ብለው አፋቸውን ሞልተው ይናገሩ ነበር። ናስር የመድረኩን ትእይንት በ3 ከፍለውታል። 1ኛ. ዋናው ትእይንት የአረቦች ዓላማና አንድነት 2ኛ. አፍሪካውያን የሀገራቸው ባለቤቶችና የሀብታቸው ተጠቃሚ ለመሆን ከነጮች/ከኢምፔሪያሊስቶች ጋር መተናነቅ አለባቸው 3ኛ. ሁለቱን የተውኔት ክፍሎች የሚያስተባብረው የዓለም ንቅናቄ ደግሞ እስልምናና እስልምና ብቻ ስለሆነ የአረብ ኅብረተሰባዊነት መስፋፋት አለበት ብለው ሳይታክቱ ጥረዋል።

ለኤርትራ ገንጣዮችም የነፃ ትምህርት እድል በካይሮ እንዲያገኙና አረባዊነትን ባህሉንና ቋንቋውን እንዲያውቁ፣ እስልምናን ተቀብለው እንዲያስፋፉ ለማድረግ በጥንካሬ ሳይታክቱ ሰርተዋል። እንደ ተቋም እንዲደራጁ የሎጅስቲክ፣ የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግም የመገንጠል ጥያቄው እርሾ ሆነዋል። እስራኤልን ደምስሶ ፍልስጥኤምን ነፃ ማውጣት አለብን የሚለው መሪ ሃሳብ በሁሉም የአረብ ሀገራት መሪዎች የሚፈከር ዋና መፈክር ስለሆነም እሳቸውም ፈክረው አስፈክረዋል።

ነቢዩ ዳንኤል በምዕራፍ 10 ቁጥር 42 ላይ ከብዙ ዘመናት በፊት የደቡብ ንጉሥ ብሎ መሰየሙንና በፍፃሜው ዘመንም የደቡብ ንጉሥ ከእርሱ ጋር ይዋጋል፣ የሰሜኑም ንጉሥ ከሰረገሎችና ከፈረሰኞች ከብዙ መርከቦች ጋር እንደ አውሎ ነፋስ ይመጣበታል ማለቱ ይታወቃል።

ግብፅ በእስራኤል ላይ እጅዋን እንድታነሳ የሚገፋፋትና የሚያነሳሳት ይሁዳዊ ሐሳዊ መሲህ እንደሚነሳ፣ ሮም ውስጥ ከሚነሳው አምባገነን መሪ ጋር የሚተባበርና የሚያሳስትም ይሆናልም ብሏል። የደቡብ ንጉሥ በእስራኤል ላይ ጦርነት እንደከፈተ ወዲያውኑ የሰሜኑ ንጉሥ ሩስያም እንደምትከተልም ዳንኤል ጨምሮ ተንብይዋል። የደቡብና የሰሜን አገሮች የመካከለኛው ምስራቅ ድልድይ ወደ ሆነችው ግብፅ ይገባሉ ብሏል።

ነቢዩ ዳንኤል በትንቢቱ እጁን በአገሮች ላይ ይዘረጋል። የግብፅም ምድር አታመልጥም በወርቅና በበግርም መዝገብ ላይ በከበረችም በግብፅ ዕቃ ሁሉ ላይ ይሰለጥናል። የሊቢያና የኢትዮጵያ ሰዎችም ይከተሉታል የሚል በዳንኤል 11፡42-43 ሰፍሯል።

በፀረ-እስራኤል ዘመቻ ደግሞ ሶቪየት ህብረት/ሩስያ በአዝማችነት የምትሳተፍ መሆኗን በትንቢቶች ሁሉ እየተገለፀ ነው። ሩስያ መራሹ ጦር የሰሜኑ ንጉሥ ተብሎ እንደሚጠራና የዚህ የሰሜኑ ንጉሥ የሚመራው ጦር ተባባሪ የሚሆኑት የነገደ ኩሽ ዘር የሆኑት የአፍሪካው ጦር የደቡብ ንጉሥ ተብሎ እንደሚጠራ ትንቢቶቹ አስፍረውታል።

የያፌት የበኽር ልጅ ጋሜር እስከናዝ ሪፋትና ቴርጋሜ ድረስ ትውልዱ ቀጥሏል። ሩስያ ለምትዘምትበት ዘመቻ ትልቁን ድርሻ ይወጣሉ ተብለውም ተገምተዋል። እነዚህ ነገዶች የሰፈሩት ከጥቁር ባሕር በስተሰሜን ነበር። እነዚህ ጎሳዎች በኋላ ጀርመናውያን መባላቸውንም ሰነዶች ይነግሩናል። በዘመናዊቷ ፖላንድ፣ በቼኮዝሎቫክያ፣ በምስራቅ ጀርመን በዳኑብ ወንዝ አካባቢ መስፈራቸውንና በዘመናዊቷ ምስራቅ አውሮፓ ሰፍረው ምስራቅ ጀርመንና የስሎባክ ሐገሮች መጠቃለላቸውን ሰነዶቹ አክለው ገልፀዋል።

የሰሜኑ ንጉሥ /ሩስያ/ እና የደቡብ ንጉሥ ግብፅና አፍሪካውያን አረቦች በተነሱበት ዘመን የምስራቅ ንጉሥ የሚባል ኃያል መንግሥት እንደፈሚነሳ በመፅሐፍ ቅዱስ ተገልጧል። ሐገራችንም የዛሬን አያድርገውና በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ጠረፋማው አካባቢ በሰሜን የቀይ ባህርን ጨምራና እስከ ምስራቅ ጫፍ ድረስ የምትወከልብዙ የአረብ መሬቶችም በባለቤት የመራች ጠንካራ ሐገር ነበረች። መሬቷ አንሶ አንሶ ተቀናንሶ ሰዉ ተበታትኖ ነበር ብቻ ሆኖ ቀረ እንጅ።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
802 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1052 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us