“ሰሞኑን የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ እና ማዕከላዊ ም/ቤት የሰጡት መግለጫዎች ሕዝቡ ለሚያነሳቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች መልስ የሰጡ አይደሉም!!”

Wednesday, 31 August 2016 12:40

 

(ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ)

 

በመላው ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተፋፋመ ስለሚገኘው ሕዝባዊ ተቃውሞ እና በተለይ ደግሞ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተከሰቱትን መጠነ ሰፊ የተቃውሞ ሰልፎች እና ሰልፎቹን ተከትሎ የደረሰውን የሰው ሕይወት እልቂትና የንብረት ውድመት መሠረት በማድረግ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ እና የማዕከላዊ ም/ቤት ሰሞኑን መግለጫ ማውጣታቸው ይታወሳል። ከመግለጫቸው ውስጥ እጅግ የሚያስገርመውና ሰዎቹ ማሰብ ተስኗቸው በቅዥት ዓለም ውስጥ እየኖሩ መሆናቸውን የሚያጋልጣቸው፣ የሕዝቡን በከፍተኛ መስዋዕትነት እየታጀበ በመካሄድ ላይ ያለውን የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች “ልማታችን ያስከተለው ነው” ማለታቸው ነው። በዚህ ረገድ የፊውዳሉ ስርዓት ታጋዩን የዩኒቨርስቲ ተማሪ “ምቾት በዝቶበት ነው፣ ስርዓቱ ላይ ተቃውሞ የሚያሰማው” ይል የነበረውን ያስታውሰናል። ይህ በእንዲህ እንዳለ መግለጫው በሌላ በኩል የፓርቲው አባላት የመንግሥትን ሥልጣን በመጠቀም ለመክበር በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሕዝቡን በማስመረር ለፈጠሩት ችግር ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸውና በአዲሱ ዓመት ተጨባጭ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ሲገልጽ፣ በሌላው አንፃር ደግሞ ለጥፋቶቹ ሌላ ማመሃኛ በመፈለግ በሕዝቡ እንቅስቃሴ “የጥፋት ኃይሎች” የሚላቸው እጅ እንዳለበት ይከሳል። ሕዝቡ ይዞ የተነሳውንም ጥያቄዎች በፓርቲው ውስጥ፣ በተለይም በከፍተኛውና በመካከለኛው አመራር በሚያደርጉት ብርቱ ግምገማዎችና ለበታች ካድሬዎችም በሚደረጉ ኮንፈረንሶች አማካይነት እንደሚፈታቸው በአፅንኦት ገልጿል። ይህም ስልት ገዢው ፓርቲ ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ሲያደርግ ከነበረው የካድሬ ሹመኞቹ ግምገማና አስመሳይ ብወዛ የተለየ እርምጃ እንደማይሆን ይታወቃል። በዚህ አቋሙም ህዝባችን መብቱንና ነፃነቱን ለማስከበር ከጽንፍ ጽንፍ በመንቀሳቀስ አምባገነን ስርዓቱን ለመቃወም መነሳቱን ኢሕአዴግ ያለመገንዘቡ በእጅጉ መድረክን አስገርሟል።

 

ኢሕአዴግ መልዓተ-ሕዝቡ ያነሳቸውን ጥያቄዎች እንደ ወትሮው አድበስብሶ ለማለፍ እየሞከረ መሆኑ የተለመደ ስልቱ መሆኑ ይታወቃል። ለአብነትም ባለፈው ዓመት ባደረጋቸው የአባል ድርጅቶቹ ጉባዔዎች በርካታ የሙስናና የአስተዳደር ብልሹነት ጥያቄዎች ተነሥተው መፍትሔ ያገኙ ዘንድ፣ የየአባል ድርጅቶቹ አባላት ግምገማዎችና የሕዝብ ስብሰባዎች እንዲያካሂዱ ወስኖ፣ በውሣኔው መሠረትም ዓመቱን በሙሉ ሕዝቡንና የየድርጅቱን አባላት በሚያሰለች ሁኔታ የማያባሩ ስብሰባዎች ተካሂደዋል። ሆኖም ለሕዝቡ ጥያቄዎች መፍትሔ አላስገኙም። ይባስ ብሎ የሕዝቡ ተቃውሞ ስፋትና ጥልቀት ጨምሮ በዋናነት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች፣ እንዲሁም በተወሰነ ደረጃም በደቡብና በትግራይ ክልሎች ይኼው የሚታዩ መጠነ ሰፊ ሕዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ተከስተዋል። በዚህም ኢሕአዴግ ያስቀመጣቸው የመፍትሔ አቅጣጫዎች ሕዝቡ ለሚያነሳቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች የሚመጥኑ አለመሆናቸው በተጨባጭ ተረጋግጧል። ስለሆነም የሕዝቡ ትግል አሁን ወደደረሰበት ከፍተኛ ሰላማዊ እምቢታ ደረጃ ተሸጋግሯል። ይህንንም እንቅስቃሴ ለማክሸፍ መንግሥት በሚወስደው የኃይል እርምጃዎች በዓመቱ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተገድለዋል። ሺዎችም ከሕግ አግባብ ውጭ ታስረዋል፤ እጅግ በርካታ ንብረት ወድሟል፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ተስተጓጉለዋል፣ በኢንቬስትመንትና በቱሪዝም እንቅስቃሴዎችም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል።

 

በእነዚህ ሕዝቡ ባካሄዳቸው ተቃውሞ ሰልፎች መጀመሪያ ላይ የአዲስ አበባን ክልል የማስፋፋቱ ዕቅድ እንዲሰረዝ፣ የወልቃይትና የቅማንት ሕዝቦች የማንነት ጉዳይ በአፋጣኝ እንዲወሰን ወዘተ የሚሉ ቀላል ጥያቄዎች ይነሱ ነበር። ቀስ በቀስ ደግሞ በመንግሥትና በገዢው ፓርቲ ባለሥልጣናት እየተፈፀሙ ያሉት የመሬትና የንብረት ዝርፊያዎች እንዲቆሙና ብልሹ አስተዳደር እንዲወገድበ የሚሉ ጥያቄዎች ቀረቡ። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ጥያቄዎቹ ጥልቀት እያገኙ በመሄድ፤ በሰልፈኞቹ እየተነሱ ያሉት፣ ባልመረጥናቸው አስተዳዳሪዎች አንገዛም፤ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችን ይከበሩ፤ ነፃነታችን ታፍኗል፤ ፍትህ እንፈልጋለን፤ የሚሉ የመሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ጥያቄዎች ሆነዋል።

 

እነዚህ ሕዝቡ በአሁኑ ጊዜ በእንቅስቃሴ ማዕቀብ ተጽዕኖ ሥር የሚማቅቁትን የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር ሳይጠብቅ በራሱ ተነሳሽነት፣ በነቂስ በመውጣት እያቀረቡ ያሉት ጥያቄዎች በአሁኑ ወቅት ስፋት ቢያኙም፤ ላለፉት በርካታ ዓመታት በተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በሲቪል ማኅበረሰብ፣ በሚዲያ ሰዎች፣ በምሁራንና በበርካታ ዜጎች ሲቀርቡ የነበሩ ናቸው። ሆኖም ኢሕአዴግ “ጆሮ ዳባ ልበስ” ብሎ በማንአለብኝነት ሲደፍቃቸው ኖሯል። አሁንም ቢሆን የሕዝቡን ጥያቄዎችና እንቅስቃሴዎች በተለመደው አግባብ “ትምክህተኞች፣ ጠባቦች፣ ሻዕቢያዎች፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች፣ በአጠቃላይ የጥፋት ኃይሎች እየፈጠሯቸው ያሉ ችግሮች ናቸው” በማለት ራሱ የፈጠራቸውን ችግሮች በሌሎች ለማላከክ እየሞከረ ነው። ይህ አገላለጽ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞችና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው የራሳቸው ግንዛቤ እንደሌላቸውና በሌሎች እንደሚታለሉ አድርጎ ስለሚቆጥር በሕዝቡ ላይ ያለውን ንቀት የሚያንፀባርቅ ነው። የውጭ ጠላቶች ኢትዮጵያ እንድትዳከም ፍላጎት ቢኖራቸውም ይህን ሚሊዮኖች በሥርዓቱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ የገለጹበትን ታሪካዊ ሰልፍ የፈጠሩት የውጭ ኃይሎች ናቸው ማለቱ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም።

 

ኢሕአዴግ የተከሰተውን ሥር የሰደደ የአገራችንን ፖለቲካዊ ቀውስ ብቻውን በግምገማዎችና በካድሬ ስብሰባዎች እፈታዋለሁ ማለቱ የባሰ ችግር ከመፍጠር የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው መድረክ ባወጣቸው አያሌ፤ መግለጫዎች ሲያሳስብ ቆይቷል። የተነሱት የሕዝብ ጥያቄዎችም፤ ለችግሮቹ ፈጣሪ በሆነው ኢሕአዴግ መፍትሄ ያገኛሉ ብሎ መድረክ ጭራሽ አያምንም። በሕዝቡ እንቅስቃሴ የተፈጠረውን ያለመረጋጋት በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው ደግሞ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ሲረጋገጥ፤ ነፃ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ ምርጫ ሲካሄድ፣ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ሲከበሩ፣ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ሲኖር እና በአገራችን ያሉ ባለድርሻ አካላት ሁሉ በሂደቱ ተሳትፎ ሲኖራቸው ብቻ ነው።

 

ስለሆነም፤ በገዢው ፓርቲ ብቻ በሚደረግ ግምገማና አሰልቺ የካድሬዎች ስብሰባ ለህዝባችን መሠረታዋ ጥያቄዎች መፍትሄ ይገኛል ብሎ ማሰብ የሁኔታውን ክብደትና አሳሳቢነት መሳት በመሆኑ፣

1.  በሺዎች የታሰሩት ዜጎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ እና ሕዝቡም ላይ እየደረሰ ያለው ወከባ ባስቸኳይ ቁሞ፣ የሕዝባችን በሰላማዊ ሰልፍ ኢሕአዴግ ላይ ያለውን ተቃውሞ የማሰማት ሕገ-መንግስታዊ መብቱ እንዲከበር እንጠይቃለን።

 

2.  በአሁኑ ጊዜ ለተፈጠረው የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ተጠያቂ እንደመሆኑ መንግሥት ካሣ እንዲከፍልና ሕዝቡ ላይ የደረሰውን ጉዳት መጠን የሚያጣራ ገለልተኛ ዓለም አቀፋዊ አካል እንዲቋቋም መድረክ በድጋሚ ይጠይቃል።

 

3.  የችግሩ ምንጭ የገዢው ፓርቲ ፀረ-ሕዝብ ፖሊሲዎችና አምባገነን ፀረ-ዴሞክራሲ የፖለቲካ አቅጣጫዎች እንጂ “የውጭ ኃይሎችና የተቃዋሚዎች ሤራ ነው” ብሎ መድረክ አያምንም። ስለሆነም የችግሩን መንስኤ ወደ ሌሎች አካላት የማላከኩ ፕሮፓጋንዳ በአስቸኳይ ቁሞ፣ ኢሕአዴግ ኃላፊነቱን እንዲወስድና ሀገራችን እየገባች ካለችበት ቀውስ ለመታደግ ሕዝባዊና ሀገራዊ መፍትሄ ላይ ከሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ጋር እንዲሠራ አበክረን እንጠይቃለን።

 

4.  ለዘለቄታው በአገራችን ዴሞክራሲ፣ ሰላምና መረጋጋት ይሰፍን ዘንድ፣ ኢሕአዴግ ከመድረክና ሌሎች ሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር መሠረታዊውን የፖለቲካ ምህዳር በማደላደሉና ለወቅቱ የሕዝብ ጥያቄዎች መፍትሔ በመሻቱ ቁም ነገሮች ላይ ባስቸከይ ድርድር ውስጥ እንዲገባ መድረክ አበክሮ ይጠይቃል።

5.  ይኼንን ኢሕአዴግ ያሰፈነውን ሀገራዊ ቀውስ ለማስወገድና በሀገራችን ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ መላው ሕዝባችን ዛሬም እንደ ወትሮው ከሰላማዊ ትግላችን ጐን እንዲሰለፍ ጥሪ እናቀርባለን።

 

ዘላለማዊ ክብር በግፍ ለተገደሉት ወገኖቻችን!

ድል ለሰላማዊ ትግላችን!

ነሐሴ 23 ቀን 2008 ዓ.ም

አዲስ አበባ¾

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
386 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 833 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us