የአጭር ልቦለድ ዐበይት ባሕርያት

Wednesday, 31 August 2016 12:45

 

በዘሪሁን አስፋው

 

 

አጭር ልቦለድ የራሱ ቅርጽና ይዘት ያለው፣ ለብቻው ተለይቶ ቢጠና፣ ቢመረመርና ቢተነተን ማኅበረሰባዊ ቁሶችን የማሳየት ዐቅም ያለው በራሱ የተሟላ ኪነጥበብ ነው። ማኅበረሰባዊ ዕውነታዎችን በማሳየት ረገድ ከሌሎቹ የሥነጽሑፍ ዘርፎች ማለትም ከሥነግጥም፣ ከተውኔትና ከረጅም ልቦለድ አንዳንድ ባሕርያትን ይጋራል። በኪነ ጥበባዊ ቅንብሩ ግን የራሱ መለያ መልኮች አሉት።

 

ይህ የሥነ ጽሑፍ ዘርፍ በባሕርዩ ቁጥብ ነው፣ ዓይነተኛና አይቀሬ ጉዳዮችን ብቻ መርጦ የሚይዝ። የሚጠቀሰው ሁሉ ተጎርዶ ቢቀር ያጐድላል። ቢጨመር ደግሞ ግብ ያስመታል። “በመልካም አጭር ልቦለድ አንድ መሥመር እንኳን ቢሆን ሳይፈልግ አይጻፍም የሚጠቀሰው ሁሉ አስፈላጊ ነው፣ እያንዳንዱ ጉዳይ አስቀድሞ ለታለመው የታሪኩ ግብ አንድ ነገር ያበረክታል።

 

የአጭር ልቦለድ ደራሲ “የመረጥኩት ማኅበራዊ ጉዳይ፣ የመረጥኩት ታሪክ፣ የፈጠርኳቸው ገፀ ባሕርያት ለአጭር ልቦለድ ቅርጽ የቱን ያህል ተገቢ ናቸው? በአጭር ልቦለድ መጠነ ይዘት ሊካተቱ ይችላሉ” የሚሉ ጥያቄዎችን በልቡ መያዝ ይኖርበታል። በአጭር ልቦለድ ቅርጻዊና ይዘታዊ ክልል ሊካተት የማይችል ነገር ማንሳት የኪነጥበቡን ቀለም ማደብዘዝ ይሆናል። ደራሲው ነገር፣ ገጸ ባሕርይና ታሪክ ሲመርጥ ተገቢነትን በሰላ አእምሮው እያሰበ ከከየነ ለዛ ያለው ሥራ ሊሠራ ይችላል።

በአጭር ልቦለድ ውስጥ ከዐቅሙ በላይ አያሌ ጉዳዮችን ካጨቁበት ያብጥና ይፈነዳል። ፈነዳ ማለት ደግሞ ቅርጽና ይዘቱ፣ ብትንትኑ ወጣ ማለት ነው። እንዲህ ሲሆን ደግሞ ኪነጥበባዊነቱ ይዘቅጣል። በረጅም ልቦለድ ቅርጽና ይዘት ለመከየን የሚበቃን ጉዳይ በአጭር ልቦለድ ለማሳየት መሞከር የአራት ዓመት ሕፃን የአባቱን ኮት ደርቦ በአደባባይ ሲታይ የሚፈጠረውን አይነት ስሜት ይከሰታል።

 

የአጭር ልቦለድ ደራሲው፣ ይህ ቃል ምን ትርጓሜ ያመጣል? ለሚፈለገው ግብ ብርቱ አስተዋጽኦ አለው? የተመረጡት ሐረጎችና የዐረፍተ ነገር ቅንብሮች በእርግጥ ግብ ይመታሉ? የሚገለጹት ድርጊቶች ታሪኩን ያራምዳሉ? ይህ ገጸ ባሕርይ የግድ መኖር አለበት? የሚገለጸው የገጸ ባሕርዩ የሰውነት እንቅስቃሴና አካላዊ መልክ፣ የንግግር ቅንብር ለዋናው ድርሰት ግብ መምታት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ?” እነዚህንና ሌሎች መሰል ጥያቄዎችን ሲመልስ ተገቢነትንና ቁጥብነትን አነሳ ማለት ነው። ይህን ተገንዝቦ የሚከሽን ደራሲ የአጭር ልቦለድ ድርሰቱን ተነባቢነት በልበሙሉነት ቢያስብ ዕውነት አለው።

 

ነጠላ ውጤት ከአጭር ልቦለድ ዋነኛ ባሕርያት መኻል ብዙ የጥበቡ አበጋዞች ተመሳሳይ ቃል የሰጡበትና ጀማሪ ደራስያንም ሊያስተውሉት የሚገባ ነው። ነጠላ ውጤት ታሪኩ ሊተረክ የበቃበት ዐቢይ ሰበብና ሄዶ ሄዶ እርፍ የሚልበት ብቸኛ ግብ ነው። ገና ከቀዳሚ ዐረፍተ ነገሩ ጀምሮ የደራሲው ጥድፊያ ወደተለመደው ግብ ለመድረስ መሆን አለበት። ከገጸ ባሕርያቱ ዕውቂያ እስከ ታሪካቸው ማለቂያ ድረስ የሚፈጸሙ ክንዋኔዎችና ሁነቶች የተተለመውን ግብ ተደራሽነት የማይቀይሩ፣ የታሪኩን ፈጣን ጉዞ የማይጎትቱ አንባቢው ለቅጽበት እንኳን ዐይኑን ከገጸ ባሕርያቱ ላይ እንዳያነሳ የሚያደርጉ ሊሆኑ ይገባል። የገጸ ባሕርያቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴና ሕልውና የታለመውን ነጠላ ውጤት ካስገኘ በኋላ ታሪኩ ይፈጸማል። ወደ እዚህ ታሪክ አጽናፍ ከተደረሰ በኋላ ትርፍ ነገር መጨመር አጭር ልቦለዱን ከቅርጽ ውጭ ማድረግ ይሆናል፣ ተጓዳኝ ግብ ብሎ ነገር በአጭር ልቦለድ ቦታ የለውም። የአጭር ልቦለድ ታሪክ የሚጓዝበት አንድ ተገቢ አቅጣጫ ይኖረዋል። ይህ ጉራንጉር የሌለው፣ ገጸ ባሕርያቱ እንደልባቸው ተጉዘው ታሪካቸውን የሚፈጽሙበት ቀጥተኛ ጎዳና ነው።

 

ታሪክ ለልቦለድ ዐቢይ ነገር ነው። ታሪክ የሌለው አጭር ልቦለድ ባዶ የቃላት ጥርቅም ብቻ ይሆናል። አብዛኛው አንባቢ አንድን አጭር ልቦለድ ለማንበብ ሲነሳ አስቀድሞ ታሪክን ያስባል። ስለዚህም ደራሲው ታሪክ መፍጠር አለበት። የሚፈጥረው ታሪክ ሰዋዊ ገጠመኞች ያሉበት፣ ሳቢነት፣ ሕያው ግጥምጥምነትና ዕውንነት ያለውና መንዛዛት የሌለበት መሆን ያሻዋል። በዚህ መልክ ከቀረበ ደግሞ የአንባቢውን ልቡና በመንካት የለዋጭነት ዐቅሙ ይልቃል። ከሰው ልጅ መሠረታዊ አርእስተ ነገሮች መሓል አንዱን ይዞ የተከየነ እንደሆነማ፣ ዘላቂነቱና የዕድሜ ባለፀጋነቱ አስተማመነ ማለት ነው። እንግዲህ እኒህን ያዋሐደ አጭር ልቦለድ ነው “ለካ ሕይወት እንዲህ ናት?” አሰኝቶ በአንባቢ ዘንድ የማይረሳ ትዝታ መፍጠር የሚችለው።

 

የአጭር ልቦለድ ታሪክ አቀራረብ የሰባኪነት፣ የደረቅ አስተማሪነትና የ“ስሙኝ! ልንገራችሁ!” አካሄድ እንዳይገኑበት መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ድርሰቱ የማይሰብክ፣ ግብረገብነት ባለው ዘዬ ለማስተማር የማይሞከር፣ ግን “ይኸውና! ዕውታው” እያለ የሚያሳይ፣ የሚጣለውን የሚጥል፣ የሚነሳውን የሚያነሳ፣ አንባቢን ማስገንዘብ የሚችል ቢሆን መልካም ነው። ለምሳሌ በሙርሲ ብሔረሰብ የጋብቻ ባህል ላይ ተመሥርቶ በተጻፈው “አንቻቦ” በተሰኘው የተስፋዬ ብርሃኑ አጭር ልቦለድ ውስጥ ደራሲው ያነሳው ዋና ማኅበረሰባዊ ጉዳይ “አጉልና ጎጂው የጋብቻ ባህሉ ገጽታ ይወገድ!” የሚል ነው። ደራሲው “ይህ የባህል ገጽታ መቅረት አለበት” እያለ አይሰብከንም ወይም አይነግረንም። ግን የዋና ገጸ ባሕርዩን የአንቻቦን የተቃውሞ ድርጊት በማቅረብ የጋብቻው ባህል ጎጂ ገጽታ መቅረት እንዳለበት ያስገነዝበናል። አንቻቦ “ዶንጋ” የተባለውን ለጋብቻ የደረሱ የሙርሲ ጎረምሶች ብቃት መፈተሻ ድብድብ ይጠላል። የደረሱ የሙርሲ ልጃገረዶች ደግሞ ከንፈራቸውን ማስተልተልና በሸክላ ማስወጠር፣ አንቻቦ ሲቃወም እናየዋለን። ጋዘር የተባለችው ልጃገረድ ከንፈሯን ስትተለተል የደረሰባትን ስቃይ እያሰበ ለባህሉ ያለውን ምሬት ይገልጻል። የብሔረሰቡን የጋብቻ ዋዜማ ልማድ በግልጽ ይቃወማል። በሚከተለው ሁኔታ፡-

 

“…ና - መሓል ግባና ታጠብ አንቻቦ ና - ይሉታል አባቱ ዘመድ አዝማድ ክብ ቀለበት ሠርቶ ሲዘፍን፣ እርሳቸው በደስታ ብዛት መሓሉን ቦታ ብቻቸውን ሞልተውት።

“ና ቶሎ እንጂ!” ደምና ፈርስ የተቀላቀለበትን ገበቴ ከትልቅ ወንድማቸው ለመቀበል እጃቸውን ዘረጉ። በጐሳው ልማድ መሠረት እርሱ የአባቱን ጠመንጃ ተቀብሎ በጉልበቱ ከተንበረከከ በኋላ በደምና በፈርሱ መታጠብ ነበረበት ጠመንጃውን በሁለት እጁ ይዞ እየፎከረ…

“አልቀበለውም!” አንቻቦ ፈርጠም ብሎ ምላሽ ሰጠ - ለአባቱ።

“ምኑን ነው የማትቀበለው?” አባቱ ቁጣቸውን ላለማሳየት - በለዘበ አንደበት ይጠይቁታል።

“በደምና በፈርስ መታጠቡንም ሆነ፣ የመረጣችሁልኝን ጋብቻ አልቀበለውም”

“እንዴት?”

“እንዲህ ነዋ!”

…….

“እኔ የምፈልገው ውበትን ነው። ያልተበላሸ ውበት! የፈለግሁትን ውበት አጥፍታችሁ የጠላሁትን እንድወድ ልታስገድዱኝ አትችሉም ጋዘርን የምወዳት በውበቷ ነው። የምወደውን ውበት አጥፍታችሁታል። ተልትላችሁታል። ስለዚህ ጋዘርን አላገባትም።”

 

በዚህ አጭር ልቦለድ የአንቻቦ አባት የብሔረሰባቸው ወግና ልማድ በሚፈቅደው መሠረት አስፈላጊውን በማድረግ ለልጃቸው፣ ጋዘር የተባለችውን ወጣት ያጩለታል። እንደባህላቸው ድግስ ደግሰው፣ ወዳጅ ዘመድ ጠርተው፣ ወጣቱ አንቻቦ ተገቢውን የቅድመ ጋብቻ ሥነ ሥርዓት እንዲፈጽም ይጠይቁታል። እሱ ግን የጋብቻው ባህል ጎጂና ኋላቀር መሆኑን በማመን ሥነ ሥርዓቱን ለመፈጸም ፈቃደኛ አለመሆኑንና የተመረጠችለትንም ልጃገረድ ማግባት እንደማይፈልግ በምሬት ይገልጻል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው የአባትና የልጅ ምልልስ ሁኔታ አንቻቦ በድርጊታዊ መልክ ያቀረበው ትውስታ ነው። ደራሲው በሙርሲ ብሔረሰብ የጋብቻ ባህል ላይ ሒስ የሰነዘረው ቀጥታ በመንገር ሳይሆን የገጸ ባሕርያቱን ድርጊት በተውኔታዊ አቀራረብ በማሳየት ነው።

 

አጭር ልቦለድ በአንድ ቦታ ጀምሮ ብዙ ቦታ ረግጦ፣ ሀገር ለአገር ዞሮ ለሚፈጸም፣ ረጅም ጊዜ ለሚወስድ ታሪክ ቦታ የለውም። ታሪኩ በአብዛኛው በአንድ በተወሰነ አካባቢ ተጀምሮ በዚያው ጠባብ ክልል ሲያልቅ ነው ድርሰቱ መልካም የሚሆነው። የጊዜ ክልሉም የተመጠነ ሲሆን በታሪክ ወቅት ረገድ የሚፈለገውን ቁጥብነት ያስገኛል። የጥቂት ሰዓታት ወይም ቀናት ታሪክ ነው - ደራሲው መፍጠር ያለበት።

 

“ሙሽራው” በሚል ርዕስ በ1979 በታተመው የአጭር ልቦለድ መድብል “ዱር ያበበ ፍቅር” የተሰኘው የንጉሴ አየለ ተካ ድርሰት በአጭር ልቦለድ የሚፈለገውን የቦታና የጊዜ ቁጥብነትና ጽምረት በመያዝ በምሳሌነት ሊጠቀሱ ከሚችሉት አንዱ ነው። ቦታው በመተከል ጉብላክ በተባለው ክልል በሚገኝ የጉሙዝ ብሔረሰብ መንደርና አካባቢ ሲሆን፤ ዋናዎቹ ገጸባሕርያት ያርሚያና ሽባቦ ትሪካቸውን የሠሩት በጥቂት ቀናትና በተወሰነ አካባቢ አከናውነውታል። በተጨማሪም “የእግር እሳት” በሚል ርዕስ በ…በታተመው የሰለሞን ለማ የአጭር ልቦለድ መጽሐፍ “ቤት ሲሞት” እና ሌሎቹን፣ በ…ከታተመው ከ“ጉዞው” የአውግቸው ተረፈን “እያስመዘገብኩ ነው”ን፣ ከሙሉጌታ ጉደታ ድርሰቶች “አጋጣሚ”ን፣ “የአራዳ ልጆች”ን ከአዳም ረታ “ማህሌት”ን “እብዱ ሽበሺን”ና “በዓለም ሕይወት አንድ ቀን”ንን እንዲሁም “ሕይወትና ሞት” ከተባለው የአበራ ለማ መጽሐፍ “ያራዳው ጐንጤ”ን መጥቀስ ይቻላል።

 

በአጭር ልቦለድ የተስፋፋ የገጸባሕርይ ሕይወት ታሪክ ሊካተት አይችልም። በታሪኩ መዋቅር ውስጥ የአንድ ሰው ታሪክ ከልደት እስከ ሞት አይቀርብም። በደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር” ውስጥ እንዳለው እንደበዛብህ ቦጋለ ታሪክ ዓይነት። በዚህ ድርሰት በዛብህ ሲወለድ፣ ሲያድግ፣ ሙሉ ሰው ሆኖ ሲኖር፣ በመጨረሻም ሲሞት እናያለን። እንዲያውም ከመወለዱ በፊት አባቱ ቦጋለ መብራቱና እናቱ ውድነሽ በጣሙ ትዳር ሲመሠርቱ እናውቃለን። እንዲህ ያለው ታሪክ ለረጅም ልቦለድ ቅርጽ ተገቢ ቢሆንም በአጭር ልቦለድ ቅርጽ ይህን መሳይ ታሪክ ለማቅረብ መሞከር ግን ለጥበቡ ባይተዋርነትን ያንፀባርቃል።

 

የአጭር ልቦለድ ገጸባሕርያት የራሱ ቅርጽና ይዘት በሚፈቅደው ሁኔታ መሳል አለባቸው፣ በዚህ የሥነ ጽሑፍ ዘርፍ መገኘት ያለባቸው ጥቂት ገጸ ባሕርያት መሆናቸውን ገና ከመነሻው ደራሲው መገንዘብ አለበት። ከአጭር ልቦለድ ባሕርያት አንዱ ቁጥብነት በገጸባሕርያት አሳሳልም ላይ መታየት ይኖርበታል። እኒህ ገጸ ባሕርያት ደምና ሥጋ ተላብሰው፣ ሲንቀሳቀሱ፣ ድርጊት ሲፈጽሙ፣ በአጠቃላይ ሕይወት ዘርተው በዕውኑ ዓለም ያሉ የምናውቃቸውን ሰዎች መስለው ሲሳሉ አጭር ልቦለዱ ተአማኒነትን ያገኛል። “የልቦለድ ገጸባሕርያት በሕይወት ውስጥ ከምናያቸው ሰዎች ጋር እጅግ የቀረበ አምሳያነት ሲኖራቸው ያሳምናሉ። ተአማኒነት ያላቸው ገጸ ባሕርያት ከአንባቢ ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዲፈጠር ያደርጋሉ። በዚህም አንባቢው የልቦለድ ሕይወታቸውን አጢኖና በተምሳሌትነት ወስዶ እንዲለወጥ ያነሳሱታል። የደራሲው ገጸ ባሕርያት በዕውኑ ሕይወት ያሉ ሰዎች ወኪሎች ናቸው። እነዚህን ገጸ ባሕርያት ደራሲው በሚቀርጽበት ጊዜ በማኅበረሰቡ ውስጥ ከተመለከታቸው ሰዎች ይነሳል። ደራሲው ገጸ ባሕርዩን ከብዙ ሰዎች ካጠራቀማቸው ልዩ ልዩ ባሕርያትና ሁኔታዎች በአንዱ ላይ በማከማቸት ስለሚቀደው አንዱን የልቦለድ ገጸባሕርይ ባለበት አቋምና መልክ፣ ቦታ የዕውቀት ደረጃ፣ እንዲሁም ባለበት ሥራና መደብ በዕውነታው ዓለም ማግኘት አይቻልም። ለምሳሌ በአንዱ ድርሰት ገበሬ ገጸ ባሕርይ ቢኖር ደራሲው በአንድ ቦታ ያለውን እከሌ የሚባል ገበሬ ሳይሆን ከተለያዩ አካባቢዎች ካያቸው ገበሬዎች ባሕርያት ጨምቆ የወሰደውን በፈጠረው ገበሬ ሰብእና ውስጥ በመከሰት ይስለዋል።

 

ደራሲው ገጸ ባሕርያት በሚቀርጽበት ጊዜ ለምሳሌ የአምሳ ወይም የመቶ ባለመደብሮችን፣ የቢሮ ሠራተኞችን ወይም ሌሎች ሠርቶ አደሮችን ዐበይት መደባዊ ገጽታዎች፣ ልማዶች፣ ዝንባሌዎች፣ እምነቶችና የአነጋገር ስልቶች ጨምቆ በአንድ ባለመደብር፣ የቢሮ ሠራተኛ ወይም ሌላ ሠርቶ አደር ገጸ ባሕርይ ሰብእና ውስጥ ያሳየ እንደሆነ ወኪል ገጸ ባሕርይ መፍጠር ቻለ ማለት ነው። ይህ ነው ደግሞ ኪነጥበብ የሚባለው።

 

 

በአጭር ልብወለድ ገፀባህርያት አጠቃላይ ሰብዕናና የባህርይ ሂደት እስከ ታሪኩ ፍጻሜ ዘላቂነት ሊኖረው ይገባል። ገጸባሕርያቱ እንደሰብእናቸው ተግባራትን ሲያከናውኑ መታየት አለባቸው። ያለምክንያት የሰብእና ለውጥ መደረግ የለበትም። ምናልባት በታሪኩ ሂደት ዋነኛ የባሕርይ ለውጥ ማድረግ ከተፈለገ ለለውጡ አሳማኝ ምክንያት መሰጠት ይኖርበታል። ለምሳሌ በአንድ አጭር ልቦለድ ውስጥ አንድ ግትር ጨቅጫቃ ግለሰብ ቢቀርብ፣ ይህ ባሕርዩ ጐልቶ እንዲታይና ክንዋኔዎቹ ሁሉ ይህንኑ ባሕርዩን የሚያንፀባርቁ እንዲሆኑ ያሻል። የግለሰቡ ባሕርይ ከዚህ የተቀየረ እንደሆነ ለውጡ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት መ ታወቅ አለበት። አጭር ልቦለድን መልካም ሊያሰኙት ከሚችሉት ነጥቦች አንዱ ገጸ ባሕርያትን በድርጊት ማሳየት ነው አንድ ወስላታ ገጸ ባሕርይ ወስላታነቱ ከነገረን፣ ሲወሰልት ብናየው ይበልጥ እናምናለን። ሌላዋ ገጸ ባሕርይ ደግሞ እጅግ ማዘኗን ከምንሰማ ስታዝን ብናያት የኀዘኗ ተካፋዮች እንሆናለን። የድርሰት ዓላማው የአንባቢውን የተመልካቹን ልብ ነክቶ አንዳች የባሕርይ ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ በመሆኑ ገፀ ባሕርያትን በድርጊታቸው የማሳየቱን ነገር ደራሲው ልብ ሊለው ይገባል።

 

ደራሲ በልቦለዱ ነፍስ ዘርተው እንዲንቀሳቀሱ የፈጠራቸውን ገጸ ባሕርያት ማወቅ ይኖርበታል። አውቋቸውም በልቦለድ ሕይወታቸው ውስጥ ያላቸውን አፍአዊና ኅሊናዊ መልክ የአጭር ልቦለድ ቅርጽ በሚፈቅደው መሠረት ማሳየት አለበት። የገጸ ባሕርያቱን አፍአዊና ኅሊናዊ መልክ ከሚኖሩበት የታሪክ ወቅትና አካባቢ ሳያርቅ እየተጠነቀቀ ያሳያል። ድርጊታቸው፣ አስተሳሰባቸውም ሆነ ቋንቋቸው ያሉበትን ማኅበረሰብ፣ ዘመንና አካባቢ አሻራ ከያዘ ተአማኒነታቸው ከፍ ይላል። በተጨማሪም የገጸባሕርያት አስተሳሰብ፣ ድርጊትና አነጋገር እንደ ዕድሜያቸው፣ እንደ ትምህርት ደረጃቸውና እንደመጡበት የማኅበረሰብ ክፍል መሆን ይኖርበታል። ለምሳሌ “ጅብ ነች” በተሰኘው አጭር ልቦለድ ታደሰ ሊበን ዋናውን ገጸ ባሕርይ በመጀመሪያው አንቀጽ፤

ቀኑ ቅዳሜ ነበር። አሰፋ የአዲስ አበባ ከፍተኛ ትምህርት ቤት ተማሪ እድሜው ሃያ ዓመት የሆነ፣ እናቱን ለመጠየቅ ከአዲስ አበባ 75 ኪሎ ሜትር በምሥራቅ በኩል ርቃ ከምትገኘው ከተማ ሸኖ ሄዶ፣ ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እናቱ ቤት ነበር። በማለት ያስተዋውቁናል።

 

በዚህ ዓይነት የተዋወቅነው አሰፋ በታሪኩ ውስጥ እንደ አዲስ አበባ ተማሪ፣ እንደከፍተኛ ትምህርት ቤት ተማሪ፣ እንደ ሃያ ዓመት ወጣት ሲያስብ ሲናገር፣ ሲመኝና ድርጊት ሲፈጽም ብናይ እናምነዋለን። አጭር ልቦለዱ የተጻፈበትን ዘመን ተመልክተን ደግሞ እንደዚያ ዘመን የአዲስ አበባ ወጣት፤ የከፍተኛ ትምህርት ቤት ተማሪ እንዲሆን እንፈልጋለን። በታሪኩ ሂደት አስፋ ከዚህ በራቀ መልክ ከቀረበልን አምነን መቀበሉ ስለሚከብደን - ገጸ ባሕርዩ በአግባቡ ያለመሳሉን እንገነዘባለን።

በዕውኑ ዓለም ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው በሚኖሯቸው የተለያየ ግንኙነቶች የተነሳ ልዩ ልዩ ቅራኔ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ቅራኔዎች ሲፈቱ ለውጥ ያስከትላሉ። ለውጡ የምርጫ፣ የምኞት፣ የዓላማ፣ የዐመል፣ የአስተሳሰብ፣ የእምነት፣ የኑሮ፣… ሊሆን ይችላል።

 

በዕውኑ ዓለም የሚታየው ቅራኔ በልቦለድ በአምሳያነት ይቀርባል። ለአጭር ልቦለድ ግጭት እንዲሰሙ ሳይሆን በተገላቢጦሽ “የጀርባ አጥንቱ” ነው ይባላል። እጅግ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ብቻ አይቀሬ ነው። ገጸባሕርያት በሁኔታ አስገዳጅነት ይጋጫሉ። በግጭቱ ለመሸናነፍ፣ በእምነታቸው ለመጽናት፣ የተመኙትን ለማግኘት፣ ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ፣ ፍላጐታቸውን ለማሟላት፣… ይፋለማሉ። ግጭቱም ይከራል። ከዚያ ይብሳል፣ ይመርራል። ወይም ግጭቱ የታሪኩ መዋቅር በሚፈቅደው ሁኔታ ይፈታል። ገጸባሕርያቱ ከግጭቱ ሲወጡ የወትሮዎቹ ሰዎች አይሆኑም። በሕይወታቸው ላይ አንድ ዓይነት ለውጥ ይከሰታል። በጎ ወይም ክፉ ነገር ያስከትላል። ይህ ለውጥ ሲታመን ተጋጮች ሲመጣጠኑ፣ የግጭቱ መነሻ ምክንያት ሲኖረውና ግጭቱ ታሪኩን በጥድፊያ ካራመደ “ደራሲው ተገቢ የአጭር ልቦለድ ግጭት ፈጥሯል” ማለት ነው።

በልቦለድ ሰው ከእምነቱ፣ ሰው ከሰው፣ ሰው ካለበት ማኅበረሰብና ከተፈጥሮ ሁኔታዎች ጋር ሊጋጭ ይችላል። ለምሳሌ “አንቻቦ” በተሰኘው ድርሰት አንቻቦ የብሔረሰቡን ወግኖ ልማድ “አልቀበልም!” ብሎ ሲያፈነግጥ ይታያል። ገጸባሕርዩ ከማኅበረሰቡ ጋር ተጋጨ ማለት ነው። በአበራ ለማ “ያራዳው ጎንጤ” ባልና ሚስቱ አቶ ጎንጤ ወ/ሮ አቻምየለሽ ተጋጭተዋል። የግጭቱ መነሻ (ምክንያት) የጎንጤ ሰካራምነት ነው። “ዳሮታ” በተሰኘው የወጋየሁ ተበጀ አጭር ልቦለድ ዋናው ገጸ ባሕርይ ዳሮታ ከራሱ ጋር መጋጨቱን (መቃረኑን) ወይም መጣላቱን እንገነዘባለን። በሙሉጌታ ጉደታ “የአራዳ ልጆች” በልሁን ከቤቱ የኮበለለው ከእናቱ ጋር በመጋጨቱ ነው። በስብሐት ገብረአግዚአብሔር “አምስት ስድስት ሰባት” ሰውና ተፈጥሮ ይጋጫሉ።

 

እስካሁን ከተነሱት ዋና ዋና ባሕርያት እንደተረዳነው የአጭር ልቦለድ ሕልውና በቋንቋ አማካይነት ይከሰታል።

 

አጭር ልቦለድ የሚቀርብበት ቋንቋ ምን ይምሰል?

 

የአጭር ልብወለድ ቋንቋ ግልጽና ከግብ የሚያደርስ መሆን አለበት። የልቦለዱን ቁጥብነትና ፈጣንነት የማያበላሽ፣ በጥንቃቄ የተመረጡ ቃላትና ዐረፍተ ነገሮች የሞሉበት መሆን ይኖርበታል። እነዚህ በደራሲው የቋንቋ ችሎታ የተመረጡና ቃላትና ዓረፍተ ነገሮች፣ የገጸባሕርያቱን ማንነት፣ ድርጊትና አስተሳሰብ ፍንትው አድርገው የማሳየት ዐቅም ካላቸው አጭር ልቦለዱ ከግብ የማድረሱ ነገር ይጐለምሳል። የአጭር ልቦለድ ቋንቋ ተደጋጋሚነትንና አሰልቺነትን፣ መንዛዛትንና መወሳሰብን አርቆ፣ በአንባቢ ኅሊና ውስጥ የትዝታን ምስል ፈጥሮ ታሪኩና የገጸባሕርያቱን ሕይወት ሁሉ ማስታወስ አለበት። ከአማርኛ አጭር ልቦለድ በቋንቋቸው ተገቢነትና ሥነጽሑፋዊነት ከሚጠቀሱት ሥራዎች መኻል የአዳም ረታን፣ የሰሎሞን ለማን፣ የስብሐት ገብረእግዚአብሔርንና የአበራ ለማን ድርሰቶች መጥቀስ ይቻላል።

ለአጭር ልቦለድ አበጋዞቹ ልዩ ልዩ መልኮችና አያሌ ፈርጆች ስለሚሰጡት ባሕርያቱ እስከ አሁን ያነሳናቸው ብቻ አይደሉም።

ምንጭ፤ የካቲት መጽሔት /መስከረም 1982 ዓ.ም¾

ይምረጡ
(9 ሰዎች መርጠዋል)
2016 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 801 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us