የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኃላፊነቱን በሚገባ እየተወጣ ነውን?!

Wednesday, 14 September 2016 14:59

- ፌዴሬሽኑ የአትሌቲክስ ቤተ መዘክር /Museum/ ሊያቋቁም ይገባዋል!

በተረፈ ወርቁ

 

ከሁለት ሳምንት በፊት በተወዳጁ በደራው ጨዋታ የሬዲዮ ዝግጅት ጋዜጠኛ ደረጄ ሀይሌ ከሥራ ባልደረባው አዜብ ወርቁ ጋር በመሆን በስደት በካናዳ አገር የሚኖረውንና በአሁን ሰዓት ደግሞ በጽኑ ሕመም ላይ ሆኖ ሆስፒታል ተኝቶ እየታከመ የሚገኘውን አፍሪካዊውን፣ ኢትዮጵያዊውን ጀግና አትሌት ምሩፅ ይፈጠርን በተመለከተ እጅግ የሚያሳዝንና በራሳችን እንድናፍር የሚያደርግ፣ በጣሙን የሚያስቆጭ፣ ልብ የሚነካና ለመሆኑ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንስ የት ነው ያለው፣ ሓላፊነቱንና ሥራውንስ በሚገባ እየተወጣ ነው ወይ ብለን ለመጠየቅ የተገደድንበት አንድ ድንቅ የሆነ ዝግጅት አቅርቦ ነበር።


የደራው ጨዋታ ስለ ጀግናው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ካቀረበው ዝግጅት በኋላ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ሆነ ሌሎች በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚኖሩ አገር ወዳድና ተቆርቋሪ ኢትዮጵያውያን እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንዳሉ ከመገናኛ ብዙሃን እየሰማን ነው። ጋዜጠኛ ደረጄና አዜብ ይህን የአገራችንን፣ የአፍሪካ ፈርጥና ስመ ጥር ጀግና አትሌት ካለበት፣ ከተሰደደበት ሀገረ ካናዳ ፈልገውና አፈላልገው ላቀረቡት ምርጥ ዝግጅት በእውነት ምስጋና ይገባቸዋል።


ከምስጋናዬ ባሻገር ግን ለአትሌቲክስ ፌዴሬሽን አንዳንድ ጥያቄዎችን ማንሳት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ይሄውም ይህ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ኩራት የሆነ ጀግና አትሌት ለዚህን ያህል ጊዜ ሲንገላታ፣ ውለታው ተዘንግቶ በባዕድ አገር ተሰዶ ተንከራታች ሲሆን፣ ይህ ታላቅ ጀግና የአገሩን ሰንደቀ ዓላማ በኦሎምፒክ መድረክ ከፍ እንዲል አድርጎ ሁላችንንም እንዳላኮራን ሁሉ ከአገሩ፣ ከምድሩ፣ ከሕዝቡ መካከል ምርር ብሎት ወጥቶ ሲሰደድ ለመሆኑ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሆነ መንግሥት ምን ያደረገው ነገር ነበር?! ይህ ታላቅ ባለ ታሪክ በምን ሁናቴ እንዳለስ ያውቅ ነበርን ...?!


እንደው የሆነስ ሆነና የደራው ጨዋታ ይህን አፍሪካዊ ጀግና ባያስታውሰው ኖሮ ምሩፅ ይፈጠር አገሩ/እናት ምድሩ በዓይኑ እንደዞረች፣ ሕዝቡን እንደናፈቀ፣ በቁጭት፣ በንዴት እንደተበሰለሰለ በዛው በስደት አገር እንዳለ ተረስቶ ሊቀር ነበር ማለት ነው?! ጀግናው አትሌት ምሩፅ ከበሽታው ጋር እየታገለ፣ በሚያቃስትና አንጀትን በሚያልውስ ድምፅ አገሬንና ሕዝቤን እንደናፈኩ በዚህ መቅረቴ ይሆን በማለት ... በስልክ ከጋዜጠኛ ደረጄ ጋር ያደረገው ቆይታ ልብን የሚሰብርና በጣሙን የሚያስቆጭ ነበር። በእውነት ጀግኖቻችንን ለማክበር፣ ባለውለታዎቻንን ለመዘከር ለሰነፍን፣ ለደከምን ለእኛ ይህን መራር የሆነ ሐቅ መስማት የሚያስቆጭ፣ በንዴት የሚያበግን ነው። ለአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ደግሞ ማፈርን የሚያውቅ ከሆነ ደግሞ እጅጉን ሊያፍርበት፣ ሊቆጭበት፣ ራሱን ሊወቅስበት የሚገባ አሳዛኝ ጉዳይ ነው።


በዛ ሕመምና ስቃይ ውስጥ ሆኖ አትሌት ምሩፅ ይፈጠር የተሸለመውን የወርቅ ጫማ እንደ ሌሎቹ የዓለማችን የስፖርቱ ዓለም ዝነኞችና ምርጦች ለጨረታ አቅርቦ ለመጠቀም ለምን እንዳላሰበ ሲጠይቅ እንኳን በቁጣና በአንዳች የቁጭት ስሜት ውስጥ ሆኖ "እንዴ ይህ ሽልማት እኮ የእኔ ሀብት አይደለም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት ነው ሲል ነበር።" ለአገሩ ታሪክ በመቆርቆርና ለሕዝቡ ክብር በመቆጨት ይህን የተናገረው ... ይህ ታላቅ ሰው ከራሱ፣ ከሕይወቱ በፊት የአገሩንና የሕዝቡን ታሪክና ክብር ያስቀደመ- የኢትዮጵያዊነት ሀያል ፍቅርና ብሔራዊ ኩራት ዛሬም ድረስ በልቡ ውስጥ እንደ እሳት እየተንቀለቀለ ያለ ጀግና ሰው ነው። ግን ደግሞ በሚያሳዝን ሁናቴ ላለፉት በርካታ ዓመታት ይህ የአገር፣ የሕዝብ ባለውለታ ውለታው ተዘንግቶ እኛ፣ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ሆነ መንግሥት ዘንግተነው በመከራ፣ በችግር የኖረና ... በኋላም ደግሞ በብስጭት የተነሳ ለስደት የተዳረገ ሰው ነው።


ጋዜጠኛ ደረጄ ሀይሌ ምሩፅ ያለበትን አሳዛኝ ሁኔታ በደራው ጨዋታ የሬዲዮ ዝግጅት እስኪያቀርበው ድረስ ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ሆነ ከመንግሥት በኩል ስለዚህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ፣ አፍሪካዊ ጀግና ምንም ያሉትም ሆነ የሰማነው ነገር አልነበረም። ይህ እጅግ የሚያሳፍርና የሚያሳዝን ነው።


አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለእነዚህ የአገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም መድረክ ከፍ ላደረጉ፣ ለሕዝባቸው ክብርና ኩራት የሆኑትን የቀደሙም ሆነ አሁን በውድድር ዓለም ያሉ ጀግኖች አትሌቶቻችን የትና በምን ሁናቴ ላይ እንዳሉስ በቅጡ ያውቅ ይሆን ...?! ፌዴሬሽኑ አትሌቶቻችን በአገር፣ በአህጉርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ የውድድር መድረኮች ያስመዘገቡትን ድላቸውን፣ አኩሪ ታሪካቸውንና ታላላቅ ገድሎቻቸውን በሚገባ ሰንዶ የሚያስቀምጥበት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የተደራጀ ቤተ መዛግብት፣ የታሪክና የመረጃ ሰነድ ክፍል ይኖረው ይሆን ...?! ለመሆኑ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለራሱ ለፌዴሬሽኑም ሆነ በአጠቃላይም ደግሞ ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ታላቅ ክብርና ጌጥ ለሆኑት ለጀግኖቻችን፣ ለዕንቁዎቻችን፣ ለአትሌቶቻችን ምን ያህል እውቅና እና ክብር ይሰጣል ወይም አለው?! የሚሉ መሰል ጥያቄዎችን ብናነሳ ምላሹና በፌዴሬሽኑ ውስጥ ያለው እውነታ አንገት ሊያስደፋ የሚችል እንደሆነ እገምታለሁ።


ለአብነትም ይሄው የዚህ ሰሞኑ በአትሌቲክስ ፌዴሬሽንና በአትሌቶቻችን መካከል እየሰማን የሚገኘው እሰጥ አገባ፣ ዱላ ቀረሽ ንትርክ የሚነግረን እውነታ ቢኖር ፌዴሬሽኑ እንኳን የቀደሙትን ጀግኖቻችንን ቀርቶ በደጁ፣ በእጁ ውስጥ የሚገኙትን የትናንትናዎቹን፣ የቅርቦቹን ጀግኖቻችንን እንኳን እህ ብሎ ለመስማትም ሆነ የሚገባቸውን ክብር በመስጠት ረገድ ምን ያህል ጥያቄ ውስጥ የወደቀ ያለ እንደሆነ እየታዘብን ነው።


መቼም ምንም ይሁን ምንም ዓለም ስማቸውንና ታሪካቸውን በወርቅ ቀለም የጻፈላቸው፣ በታላቅ ስስትና ጉጉት የሚመለከታቸውንና የሚያከብራቸውን እንደ እነ ሻለቃ አትሌት ሀይሌ ገ/ሥላሴ፣ እንደነ የመጀመሪያቱ አፍሪካዊት የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ኮ/ል ደራርቱ ቱሉ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ስለሺ ስህን፣ ገ/እግዚአብሔር፣ መሠረት ደፋር፣ ዓለም የዲባባ ልጆች በማለት የሚያደንቃቸው እነ ወርቅነሽ፣ እጅጋየሁና ገንዘቤ ... የመሳሰሉትን አትሌቶቻችንን ፌዴሬሽኑ አቅርቦና አክብሮ እህ ብሎ ሊሰማቸውና ሊያስተናግዳቸው ዳገትን የመወጣት ያህል የሚከብደው ከሆነ በአጭር ቃል ማለት የሚቻለው ቢኖር ህልውናውም ሆነ ሥራው በትልቅ ጥያቄ ውስጥ የወደቀ መሆኑን ነው።


የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለአገር፣ ለሕዝብ ክብር የሚቆረቆር ከሆነ ለእነዚህ ጀግኖቻችን መጀመሪያ ራሱ አክብሮ ሊያስከብሯቸው ይገባል። ይሄው ዛሬ ዛሬ እንደምንታዘበው ፌዴሬሽኑ ፍቅርና ክብር የነፈጋቸው አትሌቶቻችን ዜግነታቸውን ቀይረው ለሌላ አገር እየሮጡ እንደሆኑ እያየን ነው። የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑን ደጋግሞ ስሙ በሚነሳበት የአሠራር ክፍተት፣ ለአትሌቲክሱ ዘርፍ የራሱ የሆነ በአትሌቶቻችንም ሆነ በሕዝብ የታመነባቸው የባለሙያዎች አመራር አለመኖር/Luck of Professional Athletics Management Committee፣ ሙሰኝነትና ንቅዘት፣ ጎሰኝነትና ፖለቲካዊ ስሜት የተጫነው ... አካሄዱና በውስጥና በውጭ ፌዴሬሽኑን ሰንገው በያዙት ችግሮቹን በተመለከተ በአትሌቶቻችን የሚነሳው ብሶትና ሮሮ፣ ቁጭትና መንገብገብ እጅግ እየበዛ እየሄደ ነው።


የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከወዲሁ ከአትሌቶቻችን፣ ከባለሙያዎችና ከሕዝብ ጋር ተመካክሮ አንዳች መፍትሔ መፈለግ ካልተቻለ በዓለም መድረክ በብቸኝነት በክብር የምንጠራበት ተስፋችን የሆነው የረጅም ርቀት ሩጫ በታሪክ ብቻ በነበር የምናስታውሰው እንዳይሆን ያስፈራል፤ ያሰጋልም። ፌዴሬሽኑ ብቻ ሳይሆን መንግሥትም ሆነ በአትሌቶቻችን ያለበትን የአመራር ክፍተት፣ የተዝረከረከ የአሠራር ሂደት ከመፍታት ጎን ለጎንም በበኩሌ አንድ አጥብቆ ሊያስብበት የሚገባው ጉዳይ አለ እላለሁ። ይሄውም የኢትዮጵያ፣ የአፍሪካና ብሎም የዓለም ሀብት የሆኑትን የጀግኖች አትሌቶቻችንን አኩሪ ታሪካቸውንና ገድላቸውን ለትውልድ ትውልድ፣ ለአፍሪካና ለዓለም ሕዝብ ሁሉ በክብር ጠብቆ ሊያስተላልፍ የሚችልበት አንድ ደረጃውን የጠበቀ የአትሌቲክስ ቤተ-መዘክር/Museum እና የአትሌቶቻችን ታሪክ በሚገባ ጠብቆ የሚይዝበት የታሪክ ክፍል ወይም ቤተ መዛግብት ሊያቋቁም ያስፈልገዋል።


በባዶ እግሩ በሮም የኦሎምፒክ አደባባይ ማራቶንን ሮጦ ዓለምን ጉድ ከሰኘውና ካስደነቀው ከጀግናው ከአበበ በቂላ ጀምሮ ዓለም ማርሽ ቀይሪ በሚል ቅጽል የሚጠራውና በአትሌቲክስ ብቸኛው አፍሪካዊው የወርቅ ጫማ ተሸላሚ የሆነውን ምሩፅ ይፍጠረን፣ ማሞ ወልዴ፣ ዓለም ሁሉ በአንድ ድምፅ ዕፁብና ድንቅ የሆነ የዓለማችን የሁልጊዜም ምርጥ አትሌት የሚል ክብርን የተጎናጸፈውን የሻለቃ ሀይሌ ገ/ሥላሴ፣ የኮ/ል ደራርቱ፣ የፋጡማ ሮባ፣ የብርሃኔ አደሬ፣ የመሰረት ደፋር፣ የዲባባ ልጆችን ... በአጠቃላይ ትናንትና የነበሩ ዛሬም ያሉትንና ወደፊትም የሚመጡትን አትሌቶቻችንን ታሪካቸውን፣ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሮጠው አንፀባራቂ ድል ያስመዘገቡበትን ጫማዎቻቸውን፣ ማሊያዎቻቸውን፣ ሜዳሊያዎቻቸውንና የተለያዩ ሽልማቶቻቸውን፣ አኩሪ ታሪካቸውን በክብር ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍና ዓለም እንዲያየው፣ እንዲጎበኘው ለማድረግ እንዲቻል የአትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ሆነ መንግሥት ቤተ መዘክር/ሙዚየም ማቋቋም በእጅጉ አስፈላጊ ይመስለኛል።


በዓለም የኦሎምፒክ መድረክ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በረጅም ሩጫና በማራቶን ዓለም ሁሉ እጅግ የተደነቀባቸውን የጀግኖች አትሌቶቻችን ታሪክና ገድላቸውን በአንድነት ተሰብስቦና በክብር ተቀምጦ የምናይበት አንድ ትልቅ ማዕከል ያስፈልገናል። ይህ ዓይነቱ ተቋም ለአገራችን የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገትና በተጨማሪም ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጪ ጎብኝዎች /tourists ሌላ አዲስ መዳረሻ፣ ለአትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ክብር እንደሆነ አስባለሁ። በመጨረሻም የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስለ ጀግናው አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር መልካም የሆነ ዜናን እንደሚያሰማን ተስፋ እናደርጋለን። አበቃሁ!


ሰላም!! 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
556 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1030 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us