የፓርላማው ገመና ሲዳሰስ

Thursday, 01 December 2016 15:08

 

-    ከመስከረም ወዲህ ስንቴ ተሰበሰበ?

ሁለመናዬ አካሉ (ከግንፍሌ)

 

 

ፓርላመንታዊ ሥርዓት በሚከተሉ አገራት የሚታየው ፓርላመንታዊ አሰራርና ሂደት በአብዛኛው የየአገራቱን ፖለቲካዊ ሥርዓት፣ ሕገ-መንግስት ወይም የፓርላማ ባህል መሠረት ያደርጋል። በእነዚህ አገራት በሚገኙ ፓርላማዎች (ምክር ቤቶች) ውስጥ ያለው የአባላት ውክልናም እንደየሀገራቱ ሕግ የተለያየ ነው። የውይይት የክርክሩ ሂደትም የየራሱ ባህሪና መገለጫ አለው። በዚህ ረገድ የተወሰኑ አገራት ፓርላማዎችን መጥቀስ ይቻላል። የአንዳንድ አገራት ፓርላማዎች የምክር ቤት ውሎና አባላት በሚያካሂዱት ስብሰባ ያለው ውዝግብና አለመግባባት ቡጢ እስከመሰናዘር የሚዘልቅ መሆኑ ተስተውሏል። ከውይይት ይልቅ ዱላ ቀረሽ በሆነ ንትርክና ጭቅጭቅ በሚታይባቸው በእነዚህ ፓርላማዎች አዳራሹ በመነታረኪያ መድረክነቱ እምቢባይነትና ስሜታዊነት በርትቶ በጩኸት የሚጠናቀቅበት ሂደት የተለመደ ነው። በዚህ ረገድ በዩክሬንና በቱርክ ፓርላማዎች የታየው ድብድብ እና በደቡብ አፍሪካ ፓርላማ የሚታየው ጭቅጭቅና ጩኸት ይጠቀሳል። በእነዚህ ፓርላማዎች ውስጥ የሚታየው ጭቅጭቅና ንትርክ ባለመደማመጥና ባለመግባባት ሰፊ ጊዜ የሚባክንበት ከመሆኑም በላይ ጉባዔው ሳይቋጭ የሚቋረጥበትና የሚበተንበት አጋጣሚ ይበዛል። በተለይ በደቡብ አፍሪካ በጩኸትና በንትርክ የሚተራመሰውን ፓርላማ ለማረጋጋትና ኹከት ፈጣሪዎቹ እንዲወጡ ለማድረግ የምክር ቤቱ አፈጉባዔ የፀጥታ አስከባሪዎች ወደ ፓርላማው እንዲገቡ ለማዘዝ የሚገደዱበትም ሁኔታ አለ። ይባስ ብሎ አንዳንድ የምክር ቤት አባላት የምክርቤቱን አፈጉባዔ በማጥላላትና በመዝለፍ ጭምር ከወንበራቸው እንዲወርዱ እስከማስገደድና በጩኸት ፓርላማውን በማደበላለቅ ለድብድብ የሚጋበዙ መሆናቸው ተስተውሏል።

 

በአንፃሩ የእንግሊዝና የካናዳ ፓርላማዎች የጉባዔ ሂደት ከዚህ የተለየ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። በእነዚህ አገሮች ከገዥው ፓርቲ ውጭ የተወከሉ የምክር ቤት አባላት በውይይቱ ሂደት የሚያነሱት ሀሳብና ተቃውሞአቸውን የሚገልፁበት መንገድ ፍፁም ሥርዓት የተላበሰ ከመሆኑም በላይ ለጥቂት ሰከንዶች ከሚገለፅ ማጉረምረምና ማጨብጨብ አይዘልቅም። የስብሰባው ሂደትም ሲቋረጥ አይስተዋልም። አስተያየታቸው ስነስርዓት ያለው በጉባዔው ጥልቅ ውይይት የሚያካሂዱበት በመሆኑም በፓርላመንታዊ አሰራር በአርአያነት ይጠቀሳሉ። ከሁሉም በላይ አፈጉባኤው ያለው ተቀባይነት በሁሉም ዘንድ የተከበረ መሆኑና ተደማጭነቱ የላቀ በመሆኑ ጉባዔውን ህይወት ይዘራበታል። የምክር ቤቱ አባላትም የተጣለባቸውን ኃላፊነት ህዝባዊ ውክልና በአግባቡ በመወጣትና በጥራት በመፈፀም ረገድ በቂ እውቀትና አቅም እንዳላቸው ስራቸው ምስክር ነው። በመረጣቸው ህዝብም እምነት ተጥሎባቸዋል፣ ሰፊ የሀሳብ መንሸራሸር በሚካሄድባቸው በእነዚህ ፓርላማዎች ውስጥ ማረጋገጥ የሚቻለው የዳበረ ፓርላመንታዊ አሰራር በመተግበር ዴሞክራሲያዊ ባህሪ የተላበሱ መሆናቸው ነው።

 

ሌላው በአንድ ፓርቲ ውክልና የታጠሩ የአንዳንድ አገራት ፓርላማዎች ናቸው። በእነዚህ ምክር ቤቶች የሚታየው ፓርላመንታዊ ገፅታን በሚመለከት ህይወት ያለው ክርክር የማይካሄድበት፣ አጀንዳዎች ሁሌም ያለተቃውሞ፣ በተባበረ ድምፅ (በሙሉ ድምፅ) ወይም በአብላጫ ድምፅ የሚፀድቁበት ሂደት ማየት የተለመደ ነው። የዴሞክራሲ ገፅታን ባልተላበሱ በእነዚህ ምክር ቤቶች የተሟሟቀ ውይይት አይጠበቅም። በፓርላመንታዊ አሰራርም በርካታ ውስንነቶችና እጥረቶች ይታያል። በአጠቃላይ በዓለማችን ፓርላማዎች ያለው አሰራር የማይመሳሰል፣ በየምክርቤቶቹ የሚካሄዱ ውይይቶችና የውይይት ሂደቶች ያላቸው ልዩነት ሰፊ መሆኑን መረዳት ይቻላል። በዚህ መነሻ የአገራችንን ፓርላመንታዊ አሰራር በዝርዝር በመቃኘት ያለውን እጥረትና ውስንነት በሚገባ በመተንተን በችግሮቹ ዙሪያ መፍትሄ መፈለግ ግድ ይላል።

 

አሁን ባለው እውነታ በአገራችን ሁለቱም ምክርቤቶች (ፓርላማዎች) ምንም ተቀናቃኝ (ተቃዋሚ) የለም፤ የአንድ ፓርቲ ብቻ ውክልና በመኖሩ በፓርላማው ህይወት ያለው ክርክር እንዳይካሄድ አድርጓል። በውሳኔ አሰጣጥ ላይ ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይንፀባረቅ ያለአንዳች ክርክር ውሳኔ የሚተላለፍበት አሰራር መኖሩ የእኛን ፓርላማ የተለየ ያደርገዋል። በድርጅታዊ አሰራር አጀንዳዎች ተዘጋጅተውና ተቆጥረው የሚቀርቡበት ሂደት የድርጅትን እንጂ የህዝብ ውክልናን ለመፈፀም አያስችልም። በዚህም ፓርላማው በሚያካሂደው ጉባዔ ባለቀ ጉዳይ እጅ በማውጣት ውሳኔ ማሳለፉ ለመራጩ ህዝብ ተገዥነታቸውን የሚፃረር ነው። አሁን ያሉት የምክርቤት አባላት የተጣለባቸውን ኃላፊነትና ህዝባዊ ውክልና በአግባቡ ለመወጣትና በጥራት ለመፈፀም ያላቸው ዝግጁነት፣ በቂ አቅምና እውቀት ያላቸው መሆን አለመሆኑን ከሚካሄዱት (የተካሄዱት) የፓርላማ ውሎዎች መረዳት ይቻላል። በኢትዮጵያ ፓርላማ የተወከሉ የምክርቤት አባላት ሁሉን አውቀው፣ በበቂ መረጃ ላይ ተመስርተው ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ የዳበረ ልምድና የተሻሻለ አሰራርን በመተግበር ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል። ይህንን ጉዳይ ከሌሎች አገራት ፓርላማዎች የምክርቤት አባላት አቅምና ብቃት አንፃር በሚገባ መፈተሽ ያስፈልጋል። በእኛ ሕገ-መንግስት የምክር ቤቱ አባላት ተገዥነታቸው ለሕገ-መንግስቱ ለህዝቡና ለህሊናቸው መሆኑ ተደንግጓል። ይህን ሕገ-መንግስታዊ ድንጋጌ የምክርቤት አባላት ሁሌም እንደፀሎት ሊደጋግሙት ይገባል እላለሁ።

 

በኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት ምዕራፍ አንድ አንቀፅ አንድ የኢትዮጵያ መንግስት ስያሜ “የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ” መሆኑን ሲደነግግ፤ ምዕራፍ አራት የመንግስት አወቃቀርን በተመለከተም ስርዓተ መንግስቱ “ፓርላመንታዊ” መሆኑ ተደንግጓል። የኢትዮጵያ ፓርላማ ባለሁለት ቤት (Bicameral) በመሆኑ ሁለት ምክርቤቶች አሉት። እነዚህም የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት እና የፌዴሬሽን ምክርቤት ናቸው። የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ወደ 547 መቀመጫዎች ሲኖሩት ከእነዚህ ውስጥ 501 መቀመጫዎች በኢሕአዴግ፣ 46ቱ ደግሞ በአጋር ድርጅቶች ተይዘዋል። የፌዴሬሽን ምክርቤት ደግሞ ከየክልሉ ምክርቤቶች የሚወከሉ 153 አባላትን ይዟል። ሁለቱም ምክር ቤቶች ከ1988 ዓ.ም እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ ባሉት አምስት የምርጫ ጊዜያት 22 ዓመታትን አስቆጥረዋል። አምስቱንም የፓርላማ ዘመን ያለማቋረጥ በምክርቤት አባልነት የተወከሉ መኖራቸው ይታወቃል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ አንዳንድ የምክርቤት አባላት አንዴ የፌዴሬሽን ምክርቤት አባል በመሆን በሌላ አምስት ዓመት ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባል በመሆን የተወከሉም አሉ። በእነዚህ ፓርላማውን በ“ርስትነት” ከያዙት የምክርቤት አባላት መካከል ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን በሕዝብ ተወካይነት የሚገኙት ደግሞ “እኔንና የስላሴ ቤተክርስቲያንን ከአራት ኪሎ የሚነቅለን የለም!” በማለት ሲገልፁ በኩራት ነው። ለመሆኑ ካለ እነሱ ሰው የለም እንዴ? ኢህአዴግ ምነው ሰው አጣ? የሚሉም በርካቶች ናቸው። አራት የፓርላማ የሥራ ዘመናት (ሃያ ዓመታት) ተጠናቀው አምስተኛው የፓርላማ ዘመን ከተጀመረ አንድ ዓመት ተጠናቆ ሁለተኛውም ሁለት ወራትን አስቆጥሯል። ከእነዚህ የፓርላማ የሥራ (የስልጣን) ዘመናት ውስጥ በተለይ የሚጠቀሰው ሦስተኛው (ከ1998-2002 ዓ.ም) የፓርላማ የስራ ዘመን ነው። በዚህ ወቅት በፓርላማው ህይወት ያለው ክርክር የታየበትና ሰፊ የሀሳብ መንሸራሸር የተደረገበት በመሆኑ ብዙዎቹ በአድናቆት ያስታውሱታል። ዛሬስ? ቢባል ምላሹን ካለው እውነታ መረዳት አያዳግትም። በዚህ ዙሪያ የተወሰኑ ጉዳዮችን በማንሳት እውነታውን ማመላከት ይቻላል። አሁን ባለው እውነታ ፓርላማችን ያሉበትን እጥረቶችና ውስንነቶች በዝርዝር በመመርመር (በመፈተሽ) አፈጉባዔው ወይም የሚመለከተው አካል ትኩረት ቢሰጡትና መፍትሄ ቢፈልጉለት መልካም ነው። ፓርላማው ህይወት ያለው ክርክር እንዲያካሂድ (ህይወት እንዲዘራ) ለማድረግና በተሻለ አሰራር እንዲንቀሳቀስ ያሉትን ክፍተቶችና ችግሮች በመፈተሽ ጥልቅ “ተሀድሶ” ማድረግ ይጠበቅበታል።

እንደመነሻ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በተመለከተ በፓርላማችን (በሁለቱም ምክርቤቶች) የአባላት ውክልና ጉዳይ የቋሚ ኮሚቴዎች አደረጃጀትና የኮሚቴው አባላት ድልድል (አደላደል) ፍትሐዊነቱ ከአድልዎ የነፃና በአቅምና በችሎታ ላይ መሠረት በማድረግ መካሄዱ እንደገና መታየት ይኖርበታል። ከዚህ በመነሳት ሌሎች ችግሮችን ማጥራትና በቀሪዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ የተሻለ መስራትና ውጤታማ መሆን ጠቀሜታው ቀላል አይደለም።

 

አምስተኛው የፓርላማ ዘመን ሁለተኛ ዓመት የሥራ ጊዜ የተጀመረው ሁለቱ ምክርቤቶች መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም ባካሄዱት የጋራ መክፈቻ ጉባዔ ነው። በዚህ የጋራ ጉባዔ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በርካታ ጉዳዮችን አንስተው መንግስት በዚህ ዓመት በትኩረት ሊሰራባቸው የሚገባውን ዋና ዋና ተግባራት በማመላከት አቅጣጫ አስቀምጠዋል። የፕሬዚደንቱ ንግግር በብዙዎቹ ዘንድ አድናቆት ተችሮታል። በሌላ በኩል “እውነት ተግባራዊ ይደረጋል?” በሚል ጥርጣሬ የሚገልፁት በርካቶች ናቸው። ከፕሬዚደንቱ ንግግር “የአብላጫ ድምፅና የተመጣጣኝ ውክልናን የሚያጣምር የምርጫ ሕግ መቅረፅ ይገባል” በሚል የተገለፀው ከአራት ዓመታት በኋላ የሚጠበቀውን ለማየት ጉጉት የሚያሳድርብን ነው።

 

ፓርላማ መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም ስራውን በይፋ ቢጀምርም ማክሰኞ ጥቅምት 1 ቀን 2009 ዓ.ም ደግሞ በፓርላማው ታሪክ አጭር ስብሰባ (ለ20 ደቂቃ ብቻ) የተካሄደበት መሆኑ ተጠቅሷል። ባለፈው ዓመት (2008 ዓ.ም) 42 መደበኛ እና 6 ልዩ ስብሰባዎች ያካሄደው ፓርላማችን 68 አዋጆችን አጽድቋል። ይህ የባለ ሙሉ ድምፅ ምክርቤት በስድስተኛው የምርጫ ዘመን (ከአራት ዓመት በኋላ) በሚኖረው ዕጣ ፈንታ ላይ መተንበይ ባይቻልም፤ የምርጫ ሕጉ እንደተባለው ከተሻሻለ ተመጣጣኝ (Proportional) በሚባለው የምርጫ ሥርዓት አምስት በመቶ ደምፅ ያገኙ የህዝብ ወኪሎች ወደ ምክርቤት በመግባት ብዙ ድምጾች የሚወከሉበት ፓርላማ ስለሚሆን ህይወት ያለው ክርክር የሚካሄድበት ፓርላማ፤ እንደሚሆን ተስፋ አለን። የጀመርነው አዲስ ዓመት (2009 ዓ.ም) “የመታደስ ዓመት” ለዚያውም በጥልቅ የመታደስ ጉዳይ በተግባር ከታየ ፓርላማውም ዲሞክራሲን ማዕከል ባደረገ ተሀድሶ የተሻለ ሆኖ መገኘት ይኖርበታል። በዚህ ረገድ የሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበራቸውን በማረጋገጥ ሕገ-መንግስቱ እንዲከበር ኃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል።

 

በፓርላማው ያለፉት ዓመታት እንቅስቃሴዎችና ውጤታማነት ዙሪያ በርካታ ጉዳዮችን በመዘርዘር መግለፅ ይቻላል። የአባላቱ አቅም ብቃትና ችሎታ የራሱ ውስንነቶች ያሉት ቢሆንም፤ ይህንን በተሻለ የትምህርት ተሳትፎ መለወጥ እንደሚቻል ሁሉ ለመለወጥ ራሳቸውን ያላዘጋጁና ካላቸው የኋላ የትምህርት ደረጃ አንፃር ዝግጁነታቸው ለውጤት እንዲበቃ ጥረት ማድረግ ግድ ይላል። የፓርላማው ህንፃ የዕድሜ ጉዳይ ከሌሎች አገራት ፓርላማ አንፃር ለውጥ የሚያስፈልገው ቢሆንም፤ ችግሩን በመፍታት ረገድ የመንግስት ትኩረት ወሳኝ መሆኑ የማይካድ ነው።

 

ሌላው የሁለቱም ፓርላማዎች መሠረታዊ ችግር የጽ/ቤቶቻቸው ጉዳይ ነው። ሁለቱ የፓርላማ ጽ/ቤቶች ለምክርቤቱ፤ ለአባላትና አካላት ሙያዊ ድጋፍና አስተዳደራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ በአዋጅ መቋቋማቸው ይታወቃል። ይህ ሆኖ ሳለ ጽ/ቤቶቹ ተልዕኮአቸውንና ኃላፊነታቸውን በሚገባ መወጣታቸውን በሚገባ መፈተሽ ያስፈልጋል። እነዚህ ጽ/ቤቶች የነበረባቸውን ውስንነቶች ለማስወገድ በሚል የተሻለ አደረጃጀት ተጠንቶ እንደገና የማደራጀት፣ የማዋቀር ስራ ተሰርቶ ይሆናል። ይህ ጥናት በራሱ የግልፅነትና የተጠያቂነት ችግር እንደነበረበት፣ ለጽ/ቤቶቹ በፀሐፊነት (በኃላፊነት)፣ በዳይሬክተርነት፣ የሚሰየሙ (የሚሾሙ) ግለሰቦች በራሳቸው ልክ (Tailor made) ፈረንጆቹ Tailored እንደሚሉት በተጠና አደረጃጀት ሥራ ላይ የዋለው አሰራር እንደገና መፈተሽ ይኖርበታል። የፓርላማ ጽ/ቤት ለምክርቤቱ የጀርባ አጥንት ወይም ዋናው ሞተር መሆኑ ይታወቃል። በዚህ መሠረት ጽ/ቤቱ የተጣለበትን ከባድ ኃላፊነት እንዲወጣ በአግባቡ ተደራጅቷል ወይ? የአመራሩ የሰራተኛው ዕውቀት ክህሎትና አመለካከት ምን ይመስላል? ብቃት ያላቸው፣ በሙያው የበሰሉና ባላቸው ችሎታ የተመደቡ ስንት ናቸው? ቀደም ሲል የምክር ቤት አባል የነበሩትን በምርጫ ሳይመረጡ ሲቀሩ በጽ/ቤቱ በመመደብ (በመሰግሰግ) በዘፈቀደ የተሰራው ስራ በሙያው የሰለጠነ ሰው መመደብ ሲገባው በአባልነት የተደረገው ምደባና ባልሰለጠኑበት በማያውቁት ዘርፍ ተደልድለው፣ ከብቃት ይልቅ በትውውቅና በጥቅም ግንኙነት የተሰራው ስራ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የጐደለው መሆኑን መረዳት ይቻላል። በዚህ ረገድ በዕውቀትና በክህሎት ያለመመራት፣ ከብቃት ይልቅ ትውውቅና የጥቅም ግንኙነት የነገሰበት አሰራር ከላይ እስከታች መፈተሽ ይኖርበታል።

 

በሁለቱም ምክርቤቶች ጽ/ቤቶች የሚታየው በቅጥር፣ በምደባ፣ በሹመት በዝውውር በትምህርት ዕድልና በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች የተንሰራፋው አድሎአዊነት ሌሎችም ችግሮች በሚገባ ተፈትሸው ሠራተኛውም በግልፅ ተወያይቶበት መፍትሄ መፈለግ ያስፈልጋል። የፓርላማው ጽ/ቤት ጉዳይ በተለይም በንብረት አያያዝ በግዥ በውጭ ጉዞ የሚባክነው የህዝብ ገንዘብ በግብዣና በድግስ የሚወጣው ወጭ በዚህም ተጠቃሚ የሆኑትን በመለየት እርምጃ ጭምር መውሰድ ያስፈልጋል። የፓርላማ ተሽከርካሪዎች አጠቃቀምና አሁን ያለው እውነታ ደግሞ እጅግ አሳዛኝ ነው። የአገሪቱ ሀብት እንዴት እንደሚባክን ለማየት የፓርላማ መኪኖች ትልቅ ማሳያ ናቸው። ለፓርላማው አገልግሎት በሚል ቀደም ሲል ከነበሩት ተሽከርካሪዎች በተጨማሪ ከ44 በላይ አውቶሞቢሎች ተገዝተው ለቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና ምክትሎች፣ ለዳይሬክተሮች ተሰጥተዋል። ከማን ተገዙ? እንዴት ተገዙ? የሚለውን ጥያቄ አውቶሞቢሎቹን በማየት ብቻ መግለፅ ይቻላል። መኪኖቹን የተረከቡት የምክርቤት አባላትና ዳይሬክተሮች እንደራሳቸው ንብረት የሰጡት ትኩረት፣ ስለተሽከርካሪዎቹ ያላቸው እውቀት፣ መንጃ ፈቃድ ያወጡበት ሂደት፣ የመንዳት ችሎታና ብቃታቸው ለመኪኖቹ ደህንነት ብቻ ሳይሆን ለራሳቸውም ጭምር ያለውን ድርሻ ባለመረዳት በአሁን ሰዓት አንዳንድ አውቶሞቢሎች ተጋጭተውና ተበላሽተው ለወጭ መዳረግ ባልተከሰተ ነበር። የአገርና የህዝብ ሀብት እንዲህ ሲባክን በማየት ዝምታን የመረጡ የምክርቤቱ አባላት ችግሩን አያውቁት ይሆን? በማለት የሚጠይቁ ሠራተኞችም በራሳቸው በመድረክ ማንሳት ይኖርባቸዋል። ፓርላማው ሌላውን አስፈፃሚ አካል እየጠራና በቦታውም ተገኝቶ ቁጥጥር ካካሄደ የራሱን የውስጥ ጉዳዮችም ትኩረት በመስጠት መፍትሄ ሊፈልጉለት ይገባል። በፓርላማው ውስጥ ያለውን የአሰራር ችግርና የንብረት አያያዝ ጉዳይ በሚመለከት የምክርቤት አባላት እስከዛሬ ምን አደረጉ? እንደሌላው የሚኒስቴር መ/ቤት ጽ/ቤቶቻቸውንም ቢቆጣጠሩ ጥሩ ይመስለኛል። ከላይ ካለው መነሻ በተጨማሪ ሌሎች ጉዳዮችንም ማንሳት ይቻላል። በተለይም ማንም ትኩረት የማይሰጠውን ግን ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ በስራ ላይ የሚገኘውን የፓርላማውን ካፍቴሪያ፣ በሚመለከት የምክርቤቱን ክብርና ሞገስ በጠበቀ አሰራር እንዲንቀሳቀስ አለመደረጉና ወጭና ገቢውን አገልግሎቱን የማሻሻል ንረት ሲታይ ባለቤት የሌለው መምሰሉ ያሳሳባል። ይህ በቦርድ የሚተዳደረው የምክር ቤቱ ካፍቴሪያ ለቦርድ አባላት በየወሩ የሚከፍለው ገንዘብ ወርሃዊ ክፍያ (ደመወዝ) እንደገናም የቦርድ አባላቱ በካፍቴሪያው የሚደረግላቸው ልዩ መስተንግዶ (አገልግሎት) የግል ተጠቃሚ መሆናቸው ጭምር፣ ወሰን የለሽ የአገልግሎት ጊዜያቸውና በሌላ የማይተካበት ምክንያት መታየት ይኖርበታል። የካፊቴሪያው ስራ አስኪያጅ የተመረጠበት መስፈርትና ግልፅነት መኖሩ ጭምር ሊታይ ይገባዋል። በካፊቴሪያው ዓመታዊ ትርፍ ቀደም ሲል ሠራተኛው በዓመት አንዴ እንዲዝናና ይደረግ ነበር። አሁን ትርፉ “ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ” መሰጠቱ ሲገለፅ ይህ በመገናኛ ብዙሃን በይፋ እንዲነገር ማድረግና ለሠራተኛውም ሊገለፅለት ለምን አልተፈለገም? የካፊቴሪያው ገቢና ወጭ በኦዲተር ተጣርቶ እንዲገለፅ አለመደረጉና ከሙስና እና ከተጠያቂነት አንፃር ያለው ክፍተት ሁሉ እንዲታረም ማድረግ ያስፈልጋል።

 

ፓርላማው እንደ መንግስት “መታደስ” ስላለበት ሁሉንም ችግሮቹን በሚገባ ነቅሶ በመፈተሽ ሠራተኛውን ጭምር በማወያየት በጥልቅ መታደስ ይኖርበታል። የፓርላማው እጥረቶችና ውስንነቶች በዝርዝር ተለይተው መፍትሄ በመፈለግ በተሻለ አሰራር መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። የምክርቤቱን ራዕይ በማሳካት ሂደት የሠራተኛው ድርሻ የላቀ መሆኑ ይታወቃል። በጽ/ቤት ደረጃ ከሚታዩ በርካታ ችግሮችና ጉዳዮች መካከል ጥቂቶቹን ብቻ በመምዘዝ ለመግለፅ ተሞክሯል። ሁሉንም ጉዳዮች የጽ/ቤቱ ሠራተኞች የሚያውቁት ቢሆንም፤ በየኮሪደሩ ከማጉረምረምና በአለፍ ገደም ከመውቀስ በዘለቀ በሚዘጋጁ መድረኮች ማጋለጥ ይገባል። በጣም በርካታ ጉዳዮች እዚህ እንዳልተጠቀሱ ይታወቃል። ይህ እንደመነሻ የቀረበ ነው። ከዚህ በበለጠ መረጃ እና ማስረጃ ያላቸው በርካቶች መኖራቸው እውነት ነው። እውነታውን ይፋ በማውጣት እርምት እንዲደረግ ቢገልፁት ፓርላማው ችግሮቹን አስወግዶ በተሻለ አሰራር ለውጤት እንደሚበቃ ጥርጥር የለውም። እነዚህ ጉዳዮች በመገለፃቸው “ለምን ተነካሁ!” በሚል የምክርቤቱ ሕዝብ ግንኙነት አካባቢ ዘራፍ በማለት እንደተለመደው “አላዋቂ ሳሚ….” የሚል ምላሽ ከሰጠ ለመለወጥ ዝግጁነት የለም ማለት ነው። ይህ አስተያየት የቀረበው የአገራችን ፓርላማ በተሻለ አቅም እንደሌሎች አገራት ህዝባዊ ውክልናውን በብቃት እንዲወጣ በሚል በጐ አመለካከት ነው። ከዚህ ባለፈ ለአስተያየቱ የማይሆን ምላሽ በመስጠት የሌለ ታሪክ መዘብዘብ “እሽ! አትበሉኝ የሹም ዶሮ ነኝ!” ያስብላል። ይህም ለመለወጥ ዝግጁነት የለም ማለት ነው። የተጠቀሱትን ችግሮችም ማዳፈን ይሆናል። ከዚህ ሁሉ ያሉትን ችግሮች በሂደት ለማስወገድ መዘጋጀት ይገባል። እንደውም ከአራት ዓመት በኋላ እንደተባለው ፓርላማችን “የአብላጫ ድምፅና የተመጣጣኝ ውክልናን የሚያጣምር” ከሆነ ይህን የማይቀር እውነት ለመቀበል መዘጋጀትና እስከዚያው የተሻለ በመስራት የሕዝቡን አመኔታ ማጐልበት ይገባል። እኔ እንደዜጋ ይህንን አቅርቤያለሁ። ፓርላማው በተሻለ አሰራር ተለውጦ ማየትን ሁሉም ይመኛልና የዚያ ሰው ይበለን። ሠላም ሁኑ!¾   

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
446 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1029 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us