ፓርላማው እርጥብ ብርድ ልብስ አያስፈልገውም!

Wednesday, 21 December 2016 14:28

 

ሰንደቅ ጋዜጣ 12ኛ ዓመት ቁጥር 586 ረቡዕ ህዳር 21 ቀን 2009 ዓ.ም ዕትም ‘’የኔ ሐሳብ’’ በሚለው ዓምድ ስር ገፅ በ16 እና 19 ላይ ‘’የፓርላማው ገመና ሲዳሰስ’’ በሚል ርዕስ ሁለመናዬ አካሉ የተባሉ አስተያየት ሰጪ የምክር ቤቱና ፅ/ቤቱ ውስንነቶችና ዕጥረቶች ያሏቸውን ነጥቦች አንስተዋል፤ መፍትሔ እንዲበጅላቸውም ጠቁመዋል።

ችግሩ ግለሰቡ በፅሁፋቸው ምክር ቤቱንና ፅ/ቤቱን ባስነበቡት ፅሁፍ ለመዳሰስ መፈለጋቸው አይደለም።የግል አስተያየትን መግለፅ ህገ-መንግሰታዊ መብታቸው ብቻም ሳይሆን ጠቃሚና ገንቢ ከሆነ የሚበረታታና እሰዮ፤ በርቺ/ታ የሚያሰብል ነው። ቅቡልነቱም አጠያያቂ አይሆንም። ነገር ግን መፃፍ መፈለግ ብቻ በቂ አይደለም። ስለሚፃፈው ጉዳይ በቂ መረጃ መያዝ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር  ነው። ይህ ካልሆነ ግን ፅሁፉ ለመፃፍ ብቻ የተፃፈ ይሆንና  ከመንደር ወሬ የዘለለ ረብ አይኖረውም። ከዚህ አንፃር አስተያየት ሰጪው በምክር ቤቱ በተለይ በፅ/ቤቱ ላይ የሰነዘሩት ትችት በተራ አሉ ባልታ ላይ የተመሰረተ ውሃ የማይቋጥር መሆኑን የፃፉት ፅሁፍ ያሳብቃል።

ፀሃፊው አንዱ ያነሱት ጉዳይ በፓርላማው  የአንድ ፓርቲ ውክልና ብቻ በመኖሩ ህይወት ያለው ክርክር አይካሄድም የሚል ነው። እንደሚታወቀው አገራችን የምትከተለው የምርጫ ስርዓት  በዴሞክራሲ ባህል የዳበሩ በርካታ የዓለም አገራት የሚከተሉት ዓይነት ነው። በዚህ የምርጫ ስርዓት  እስካሁን አምስት አገራዊና ክልላዊ ምርጫዎች የተካሄዱ ሲሆን፤ በርከት ያሉ የፓርላማ መቀመጫዎች በተቃዋሚ ፓርቲዎች የተያዙበት የምክር ቤት ዘመናት ተስተውለዋል። በተካሄዱ ነፃና ፍህታዊ ምርጫዎች በተለይ ከአንደኛው ምክር ቤት ጀምሮ እስከ ሶስተኛው ምክር ቤት በርካታ የተቃዋሚ አባላት  ፓርላማ ገብተዋል።

ሆኖም  በሂደት ኢህአዴግ የሚከተለው ፖሊሲና ፕሮግራም ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ትክክለኛ የልማት አቅጣጫ ሆኖ በህዝብ ዘንድ አመኔታን በማሳደሩ እና በተግባርም ህዝቡ የልማት ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ በ2007 ዓ∙ም በተካሄደ ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የተለያዩ  የፖለቲካ ፓርቲዎች ፖሊሲና ፕሮግራሞቻቸውን በተለያየ መንገድ ለህዝብ አቅርበው ኢህአዴግ ያቀረባቸው እጩዎች በነፃና ፍትሃዊ ምርጫ አሸናፊ በመሆናቸው  ወደ ምክር ቤት ገብተዋል። ይህ በመሆኑም አሁን በምንገኝበት አምስተኛው ምክር ቤት ሁሉም መቀመጫዎች  በኢህአዴግና አጋሮቹ ተይዘዋል። ለዚህ ውጤት ዋነኛውና ወሳኙ ጉዳይ በአገሪቱ የምርጫ ህጎች መሰረት ሁሉም ወገኖች ተስማምተው በተካሄደው ምርጫ የተገኘ የህዝብ ውሳኔ በመሆኑ  ከዴሞክራሲ መርህ አንፃር ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው።

 ይህ ሁኔታ ፀሃፊው እንደሚሉት በፓርላማው ምንም ተቃዋሚ ስለሌለ ህይወት ያለው ክርክር አይደረግም ማለት አይደለም። ምንም እንኳ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በፓርላማ መኖር ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ  አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የሚታመን ቢሆንም፤ የአንድ ፓርላማ ዴሞክራሲያዊነትና ውጤታማነት መመዘኛው የተቃዋሚ ፓርቲ በፓርላማ ውስጥ መኖር ውይም ባለመኖር ብቻ የሚገለፅ አይደለም።

በዚህ ዙርያ ሁለመናዬ አካሉና  ሌሎች መሰል  ግለሰቦች ሊረዱት የሚገባው ጉዳይ የምክር ቤት አባላቱ ከአንድ ፓርቲ የመጡ ቢሆንም በፖሊሲና እቅድ አፈፃፀም፤ በወጡ ህጎች አፈፃፀም ላይ ጠንካራ ክርክር ከማድረግ የሚከለክላቸው አሰራር የለም። የምክር ቤቱ የክትትልና የቁጥጥር ስራም የሚያተኩረው በአፈፃፀም ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ነቅሶ አውጥቶ እንዲታረሙና እንዲከታተሉ ክትትል ማድረግ ነው። ለህዝብ ቅሬታ ምላሽ እንዲሰጥ ድጋፍና ክትትል ከማድረግ ባለፈ ድክመቱን በማያርምና በማያስተካክል አስፈፃሚ አካል ላይ ምክር ቤቱ እርምጃ የመውሰድ ስልጣንና አሰራር አለው።

 ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ የኢህአዴግ አባላት በፓርላማ ውስጥ በፖሊሲና ፕሮግራም ልዩነት ፈጥረው መወያየት አይችሉም። ምክንያቱም ከመነሻው የፓርቲ አባለቱ የፓርቲውን ፖሊስና ፕሮግራም አምነው ተቀብለው ነው ፓርቲውን ወክለው በእጩነት የቀረቡት፤ ህዝቡም የመረጣቸው በፓርቲው ፖሊሲና ፕሮግራም ላይ አመኔታ ስላደረበት ነው። አሁን ያሉት የምክር ቤቱ አባላት የተጣለባቸውን የህዝብ ውክልና ኃላፊነት በጥራት እየተወጡ አይደሉም ማለት የሚቻለውም ህዝቡ የመረጠውን ፖሊስና ፕሮግራም እናስፈፅማለን ብለው ከተመረጡ በኋላ ተፃራሪ ውሳኔ ሲያስተላልፉ ቢስተዋል ነው። ከዚህ ውጭ ምክር ቤቱ የአፈፃፀም  ጉድለቶችን መሰረት በማድረግና በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙረያ ገደብ የለሽ ክርክር ማካሄድ ይችላል፤ እያካሄደም ይገኛል።

ምክር ቤቱ በ2008 በጀት ዓመት ያከናወናቸው ተግባራት የህዝብ ውክልናንም መወጣት መቻላቸውን የሚያሳይ ነው ። ጥቂት ማሳያዎችንም ማቅረብ ይቻላል።

የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮግራም ጉብኝትን ማንሳት ይቻላል። ጉብኝት የወጣው የምክር ቤቱ ሱፐር ቪዥን ቡድን ስለስራው ለምክር ቤቱ ሪፖርት አቅርቦ በርካታ  ችግሮች ታውቀው እንዲፈቱ አድርጓል። ከዚህ ባለፈ ያልተገነቡ ሕንፃዎች መኖራቸውን በሪፖርቱ አሳይቶ በአስተዳደሩ በኩል በመጀመሪያ  ‘’የአረገም የሰመጠም ሕንፃ የለም‘’ ተባለ። ጥያቄው ሲጠናከር ሕንፃዎቹ ከቦታው ችግሮች አኳያ ከታሰቡበት ቦታ ፈቀቅ ተደርገው እንደተገነቡ ተገለፀ። በመጨረሻ ግን ያልተገነቡ ሕንፃዎች መኖራቸው ታመነ። ቁጥራቸውም ከሰማኒያ አካባቢ እጅግ የበለጠ እንደሆነ ተጠቁሞ ውል ያተገባባቸውና ክፍያም ያልተፈፀመባቸው እንደሆኑ ተገለፀ። ቤቶቹ ለተጠቃሚ እንዲተላለፍ ዕጣ ሲወጣ በቀረቡ ሪፖርቶች እነዚህ ጉዳዮች በዝምታ የታለፉ ነበር።

የስኳር ፕሮጀክቶችንም በፕሮጀክቶቹ መዘገየት  ዙርያ የታሰበው ጥቅም ያለመገኘቱና የገንዘብ ብክነት ማስከተሉ ምክር ቤቱ በግልፅ ገምግሞታል። መንግስትም በድፍረት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ችግር እንደገጠማቸውና ከልምዱ በተወሰደው ትምህርት ስራዎቹ ስለሚጠናቀቁበት ሁኔታ መግለጫ እያቀረበ ይገኛል።

ከዋናው ኦዲተር የፋይናንስና የክዋኔ ኦዲት ግኝት መነሻ በማድረግ በባለ በጀት መስሪያ ቤቶች እየተጠሩ ሙሉ ቀን የፈጀ ግምገማ ሲካሄድ ነበር። የምክር ቤቱ የአሰራር ደንብ ማሻሻያ ተደርጎበት የአስፈፃሚ ሪፖርት አጠራጣሪ ሲሆን ሪፖርቱ ውድቅ የሚደረግበት ስርዓት ተዘርግቶ የሞቀ ግምገማ ተካሂዷል። በመብራት፣ በመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች እና በመሳሰሉት ጉዳዮች ዙሪያ የነበሩ ግምገማዎች ህዝቡን ተጠቃሚ አድርገዋል። የህዝብ የውክልና ስራም ናቸው።

ፀሀፊው ሌላው ያነሱት ጉዳይ“ በኢትዮዽያ ፓርላማ የተወከሉ የምክር ቤት አባላት ሁሉን አውቀው፤ በበቂ መረጃ ላይ ተመስርተው ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ የዳበረ ልምድና የተሻሻለ አሰራርን በመተግበር ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል” የሚል ማሳሰቢያ ነው። በሌላ መለኩ ደግሞ በአምስት የምክር ቤት ዘመናት ያለማቋረጥ የተወከሉ አባለት በምክር ቤቱ መኖራቸውን ፀሃፊው ይቃወማሉ። ፀኃፊው በአንድ በኩል የምክር ቤቱ አባላት የዳበረ ልምድ እድሚያስፈልጋቸው ያነሳሉ። የምክር ቤቱ አባላት የዳበረ ልምድ እንዲኖራቸው ከተፈለገ በተደጋጋሚ መመረጣቸው አስተያየት ሰጭው ካነሱት ሃሳብ አንፃር በአዎንታዊ የሚነሳ እንጂ መኮነን የሚገባው አይመስለንም። አስተያየት ሰጪው ፓርላማውን የመተቸት አባዜ ወስጥ ገብተው ነው እንጂ፤ በተደጋጋሚ የተመረጡ የምክር ቤት አባላት ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ይህ አልበቃ ብሏቸው“ እኔንና የሥላሴ ቤተክርስቲያንን ከአራት ኪሎ የሚነቅለን የለም፤ በማለት በኩራት የሚገልፁ  አሉ” የሚል የመንደር ወሬ አሉባልታ አስፍረዋል በፅሁፋቸው።

በመሰረቱ ፀሃፊው  የፌደራሉ መንግስት ትልቁ የሰልጣውን አካል የሆነውን ምክር ቤት  እጥረትና ውስንነት በመተንተን መፍትሄ ማስቀመጥ ከፈለጉ መጀመሪያ ከአሉባልታና ከግብታዊነት ርቀው በመረጃ የተደገፈ ጽሁፍ ሊያስነብቡን ይገባል፤ በአምስት የምክር ቤት ዘመናት ምክር ቤቱ የፓርላማ ዴሞክራሲን በመተግበር ያሳየውን እድገትና ለውጥ በፅሁፋቸው አንድ ቦታ እንኳ ለመግለፅ  አለመሞኮር  ሚዛናዊ ፀሃፊ አለመሆናቸው  በቂ ማስረጃ ነው ማለት ይቻላል ።

ምክር ቤቱ የተሻሻለ አሰራርን መተግበር እንዳለበት አስተያየት ሰጪው አንስተዋል። ፀሃፊው ዘንግተወት አልያም የመረጃ  ክፍተት ኖሮባቸው ይሆናል እንጂ የምክር ቤቱ አንዱ መገለጫ እኮ  ከአስፈፃሚ መንግስት አካላት አደረጃጀትና ነባራዊ ለውጦች አንፃር መሻሻሎች እያደረገ መምጣቱ ነው /adjusting to changing reality/። በ5ኛው ምክር ቤት አንደኛ አመት የስራ ዘመንም የምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት የስነ ምግባር ደንብ የአስፈፃሚ አካላት ተጠያቂነትን የበለጠ በሚያጠናክርና የምክር ቤቱን ውጤታማነት በሚያጎለብት አግባብ ተሻሽሏል። በምክር ቤቱ አካላት አደረጃጀት ላይም  መሻሻሎች ተደርጓል።

 የፀሃፊው ድፍረት የተሞላበት አስተያየት የአባላቱ አቅም፣ብቃትና ችሎታ ውስንነት አለበት የሚለው ነው። ፀሃፊው ይህን ድምዳሜ ለመስጠት ማስረጃቸው ምንድነው? ቢባል በመረጃ የተደገፍ ሳይሆን በስሜት ተነድተው የሰጡት ድምዳሜ ነው ብንል ማጋነን አይሆንብንም። የአባለቱ አጠቃላይ መረጃ የሚያሳየው /profile/ በተለይ የአምስተኛው ምክር ቤት አባላት የትምህርት ዝግጅታቸውም ከፍተኛ የሚባል ነው፤ በፖለቲካ አመራር ብቃታቸው ደግሞ ከወረዳ ጀምሮ በዞንና በክልል በተለያዩ አመራር ቦታዎች ያገለገሉና ከፍተኛ ልምድ ያካባቱ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ የምክር ቤቱ አባላት የህዝብ ውክልና ኃላፊነትንና የክትትልና የቁጥጥር ተግባርን በአግባቡ ለመወጣትና በጥራት ለመፈፀም ያግዛቸው ዘንድ እንደየአስፈላጊነቱ የአቅም ግንባታ መድረክ በከፍተኛ አመራሩ ይመቻቻል።

በተሻሻለው የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የአሰራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ፣  በGTP I አፈፃፀምና በGTP II ረቂቅ ዕቅድ ላይ ውይይቶች ተካሂደዋል። እንደዚሁም በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት መሰረታዊ ጽንሰ ሀሳቦችና ባህሪያት፣ በሕገ መንግስታዊ ስርዓት ግንባታ ም/ቤቱና አባላቱ ስለሚኖራቸው ሚና፣ የፍትሕ ዘርፍ ሚናና ተግዳሮቶች፣ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ምንነትና ፋይዳው፣ በመሬት ስነ-ምህዳር መዋቅር፣ በህዳሴ ግድብ እና በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ዙሪያ የተካሄዱ ውይይቶች ለአባላቱ ሰፊ ግንዛቤ ያስጨበጡ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ስለለውጥ መሣሪያዎች ይዘት፣ ስለዕቅድ አዘገጃጀት፣ ስለሪፖርት ግምገማና ግብረ መልስ አሰጣጥ የተሰጡ ስልጠናዎች አባላቱን በመገንባትና ለቀጣይ ስራ በማዘጋጀት በኩል ጠቃሚ እንደነበሩ ታይቷል። በጠቅላይ አቃቢ ህግ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ የተዘጋጀው ሥልጠና በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሥርዓቱ ዙሪያ ያሉ አጠቃላይ ሁኔታዎችና ቀጣይ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በተመለከተ አባላቱ ሰፊ ግንዛቤ እንዲይዙ አስችሏል። የተሰጡ ስልጠናዎች በእውቀት ላይ የተመሰረተ ሃላፊነትን የምክር ቤቱ አባላት እንዲወጡ የሚያግዙ ናችው።

የምክር ቤቱ አባላት በፓርላማው የሚያካሂዷቸው ውይይቶችም በየጊዜው   ብስለት እየታየባቸው፤ ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ መስጠት ላይ ያተኮሩ ናቸው። በተለይ በአምስተኛው ምክር ቤት አንደኛ ዓመት የስራ ዘመን የህዝብ ጥያቄዎችን  አደራጅተው ለሚመለከትው አስፈፃሚ አካል እያቀረቡ መስተካከል በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ በህዝብና በአገር ወገንተኝነት ስሜት የመወያየትና የመከራከር ሁኔታ በሰፊው ተስተውሏል።

ከዚህ አንፃር የምክር ቤቱ ዓባላት የአቅም ውስንነት አለባቸው የሚለው የፀኃፊው የድምዳሜ መነሻው ምንድ ነው ብንል? ከግብታዊነት የመነጫ፤ ውሃ የማይቋጥር፤ ተራ አሉባልታ ነው ማለት ይቻላል። ፀሃፊው ሊስተካከሉና ሊታረሙ ይገባል። በመረጃ ያልተደገፈና ሚዛናዊ ያልሆነ ፅሁፍ መፃፍ ለራስም ሆነ ለአገር አይጠቅምም፤ለዳቦም ብቻ ሲሉ መፃፍም ብዙ ርቀት አያራምድም።

ፀኃፊው በአጠቃላይ በምክር ቤቱ ላይ ባነሷቸው ነጥቦች ዝርዝር መረጃ ከፈለጉ በፓርላማ መፅሔት ቅፅ 21 ነሐሴ 2009 ዓ∙ም ዕትም ከመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ከተከበሩ አቶ አስመላሽ ወ/ሥላሴ ጋር የተደረገውን ሰፊ ቃለ ምልልስ እንዲመለከቱ እንጠቁማለን።

ፀኃፊው የምክር ቤቱ ፅ/ቤቱ መሰረታዊ  ችግር አለበት ሲሉም ተችተዋል።

 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፅ/ቤት ለምክር ቤቱና አካላቱ ሙያዊ ድጋፍና አስተዳደራዊ አገልገሎት ለመስጠት በአዋጅ የተቋቋመ ነው ፅ/ቤት የሚሰጠው ሙያዊና አስተዳደራዊ አገልግሎት ለአገራችን የፓርላማ ዴሞክራሲ ስርዓት እድገት  የራሱ ዓይነተኛ አስተዋፅኦ ያለው በመሆኑ፤ የሰራተኛውን የአገልገሎት አሰጣጥ አቅም  ለማጎልበት የአጭር፣ መካከለኛና ረጅም ጊዜ ስልጠናዎች የሚሰጡበትን አግባብ  ለመፍጠር  በአገር ወስጥ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ባሻገር ከአቻ አገራት ፓርላማዎች ጋር ትስስር በመፍጠርና ለምድ በመቀመር ለምክር ቤቱና አካላቱ የሚሰጠውን ሙያዊና አስተዳደራዊ አገልገሎት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። ፅ/ቤቱ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችለው በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በመደገፍ ወረቀት አልባ ምክር ቤት /paper less Assembly/ ለመፍጠር እና በሰው ኃይል፣ በአደረጃጀትና በመግባት አቅርቦት ዙርያ ያሉበትን ውስንነቶች ለመፍታት በአሁን ወቅት ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

  ፅ/ቤቱ  የተጣለበትን ከባድ ኃላፊነት  እንዲወጣ በአግባቡ  ተደራጅቷል ወይ? የሚል ቅሬታ አንስተዋል። በቅርብ ከስልጣን እና ተግባር አንፃር ውስንነቶችን ለመፈታት ታልሞ ፅ/ቤቱ በዋና ጸሐፊና መክትል ጸሐፊ እንዲመራና በስሩም ቁጥራቸው እንደ የአስፈላጊነቱ የሚወሰን መምሪያ ኃላፊዎች እንዲኖሩት በአዋጅ የተደረገውን መሻሻል በራሱ የግልፅነትና የተጠያቂነት ችግር አለበት ብሎ መናገር ትልቅ የአመክነዮ ስህተት ነው። በአዋጅ ተደንግጎ ምክር ቤቱ ተወያይቶበትና አምኖበት ያፀደቀውን የፅ/ቤቱን አደረጃጀት ግልፅነት የለውም በሎ መፈረጅ እውነት ያላዋቂ ሳሚ አያስብልምን?

“በእውቀትና በክህሎት አለመመራት፤ ከብቃት ይልቅ ትውውቅና የጥቅም ግንኙነት የነገሰበት አሰራር …” በፅ/ቤቱ እንዳለም ፀኃፊው ያነሳሉ።

በመሰረቱ የጽ/ቤቱ አመራሮች ምደባ በሹመት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አንድ ዳይሬክተር አንድ ክፍልን እንዲመራ ሲሾም የትምህርት ዝግጅቱና የስራ ልምዱ ከሚመራው ክፍል ጋር ተቀራራቢነቱና አግባብነቱ እንዲሁም የመምራት ቁርጠኝነቱ ታይቶ ነው የሚመደበው እንጂ አስተያየት ሰጪው እንደሚሉት በትውውቅና በጥቅም ግንኙነት አይደለም። ከተመደበ በኋላም በስራው ውጤታማ ሆኖ ካልተገኘ ፈጥኖ የሚነሳበትና በተሻለ ሰው የሚተካበት  አሰራር ነው ያለው። ስራውን በአግባቡ ያልመራ ተሿሚ ከቦታው በሾመው አካል ይነሳል። ይህም እየተደረገ ነው።

የሰራተኛውን ብቃት በተመለከተ ምክር ቤቱ ቀጥሮ እያሰራ ያለው የሀገሪቱ ዪኒቨርስቲዎች የሚያፈልቋቸውን ባለሙያዎች እንደማንኛውም የመንግስት ተቋማት በሲቪል ሰርቪሱ መመሪያና ደንብ በመሰረት ነው። ሆኖም ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው  የአመራሩንና የሰራተኛውን እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት እንዲሁም የአገልጋይነት መንፈስ ለማሳደግ ፅ/ቤቱ አያደረገ ያለው ጥረት ከፍተኛ የሚባል ነው።

 ይህ ሲባል ግን ፅ/ቤቱ ከባለሙያ አንፃር ችግር የለበትም ማለት አይደለም፤ የሰራተኛ ፍልሰት እንማንኛውም የመንግስት ተቋማት ይስተዋላል። ዋነኛው መክንያት ደግሞ የተሻለ ክፍያ ፍለጋ ነው፤ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ሰራተኛ ለማቆየት  በፅ/ቤቱ በኩል ጥረት እየተደረገ ነው።

የቀድሞ ምክር ቤት አባላት  በምክር ቤቱ ፅ/ቤት መመደብ እንደችግር ተነስቷል። የቀድሞ የምክር ቤት አባለት ከዚህ ቀደም አልፎ አልፎ ይመደቡ የነበረ ቢሆንም፤ በአሁን ወቅት ተፈፃሚ እየሆነ አይደለም፤ ይደረግ የነበረው ምደባውም ካላቸው ልምድ አንፃር ለፅ/ቤቱ እድገት አስተዋፅኦ ይኖረዋል በሚል እሳቤ እንጅ ለመጦር አይደለም። በመሰረቱ ህዝብን ያገለገሉ የምክር ቤት አባላት በፅ/ቤቱ መመደባቸው እንደ ትልቅ ጥቅም ታይቶ መነሳት አልነበረበትም። የእኛ አገር የእድገት ሁኔታ ስለ ሚገድብ እንጂ  የቀድሞ የምክር ቤት አባላት ሲሰናበቱ እንኳ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅማ ጥቅም እግኝተው አይደለም። እነሱም ቢሆን ማግኘት የሚገባንን ጥቅማጥቅም አላገኘነም ብለው ቅሬታ ሲያሰሙ ብዙም አይስተዋሉም።

ከጥቅማ ጥቅም ጋር በተያያዘ  በግልፅነትና በውድድር ላይ ተመስርቶ ነው የሚሰራው። የትምህርት ዕድልም ሲመጣ ሰራተኛው እንዲወዳደር መስፈርቱ በውስጥ ማስታወቂያ ይገለፃል። ዕድገትም በውድድር ነው። ቅጥርም እንደዚሁ። አዲስ የተቀጠሩ ሰራተኞች በአንድ ወቅት በስብሰባ ላይ ስለአሰራሩ ምስጋና ያቀረቡበት ወቅትም ነበር።

ሌላው ከንብረት ብክነት ጋር የሚያያዝ ሀሳብ ነው የተነሳው። በንብረት አያያዝም የተሻሻሉ አሰራሮች እንዲተገበሩ እየተሰራ ነው።

በውጭ አገር ጉዞ ስም ለፅ/ቤት ሰራተኞች የሚባክን ገንዘብ የለም። ለአጫጭር ስልጠናዎችና ለልምድ ልውውጦች የሚሆኑ የውጭ ጉዞዎች በዓመት አንድ ጊዜ እንኳን አያጋጥሙም። ይህም ቢሆን በጋባዥ አገር ወጪ የሚሸፈን ነው። የፅ/ቤቱ ኃላፊ ከዓለም ፓርላማ ህብረት ስብሰባ ጎን ለጎን ለሚካሄደው የምክር ቤቶች ፅ/ቤቶች በጸሐፊዎች መድረክ ለመገኘት የሚያደርጉት የውጭ ጉዞም በፕሮግራም የታወቀ ስለሆነ ለውጭ ጉዞ የሚባክን ገንዘብ የለም። የምክር ቤት አባላት ጉዞም ቢሆን ለአገሪቱ ከሚያስገኘው ጥቅም አንፃር እየተመዘነ የሚፈቀድ ነው። 

በግብዣና በድግስም ብክነት እንዳለም ተነስቷል። የምክር ቤቱ እንግዶች የሆኑ ከውጭ አገር ሲመጡ መስተግዶ ይደረግላቸዋል። መስተንግዶ ህጋዊ ነው። ምክር ቤቱ ከህዝብ ጋር የሚገናኝባቸው በርካታ መድረኮች አሉ። ምክር ቤቱ ለስራ ለጠራቸው እንግዶች ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ዝግጅቶችን ያደርጋል። ምክር ቤቱ ሰኔ መጨረሻ ሲዘጋ ይህን ምክንያት አድርጎ ለምክር ቤት አባላትና ለሰራተኛው በአፈ ጉባኤው ስም ዝግጅት ይኖራል። እነዚህ አስፈላጊነታቸው ታምኖ በበላይ አመራር ተወስኖ የሚደረግ ስለሆነ ሰራተኛው በድግስ ተንበሽብሾ እንደሚኖር አስመሰሎ መፃፍ  የተሳሳተ መረጃ ማስተላለፍና ውዥንብር መፍጠር ነው። መታረም አለበት።

የመኪና ግዢም እንደብክነት ተወስዷል። እንደማንኛውም መንግስት ተቋማት ለአመራሮች እንደሚደረገው ሁሉ አቅምን ባገናዘበ መለኩ ሊፋን መኪናዎች ለቋሚ ኮሚቴ አመራሮችና ዳይሬክተሮች ተገዝቷል። ግዥው በመንግስት ግዥ ማዕቀፍ የተፈፀመ ነው። የተለየ ነገር እንደተደረገላቸው  አጋኖና አጩሆ መፃፍ ሚዛናዊነትና አስተዋይነት የጎደለው ነው።

መኪናው የተሰጣቸው ሰዎችም ስልጠና ተሰጥቷቸው መንጃ ፈቃድ ወስደው መኪናውን እያሽከረከሩ ይገኛሉ። መኪናዎቹ የመድን ሽፋን የተገባላቸው ስለሆነ ተገቢውን ዕውቀት ያልያዘ ሰው እንዲያሽከረክር አይፈቀድም።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለሁለት ምርጫዎች በራሳቸው የትራንስፖርት ወጪ የምክር ቤቱን ስራ ሲሰሩ ነበር። በ3ኛው ምክር ቤት ደግሞ ለመደበኛ ስብሰባ ቀን ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ አውቶቡስ ሊገኝ ችሏል። ከ4ኛው ምክር ቤት ጀምሮ የመኪና ሰርቪስ አገልግሎት ከሰኞ እሰከ ዓርብ ሊሆን ችሏል። አሁን ደግሞ ለቋሚ ኮሚቴ አመራር ልፋን ደርሷል። ወደፊትም አገራችን ከምታስመዘግበው እድገት አንፃር እየተገመገመ የአመራሩም ሆነ የሰራተኛው ጥቅማ ጥቅም እንደሚሻሻል ነው የሚጠበቀው።

የመኪና ግጭት በአዲስ አበባ አገራዊ ችግር ሆኖ ሳለ የምክር ቤት አባላት የስራ መኪና ያዙ ተብሎ የአገሩን ችግር በነሱ ላይ ብቻ ለመጫን መሞከር አግባብ አይደለም። በየገደላገደሉ እየዞሩ መቀደስ የተኛውን ሰይጣን መቀስቀስ እንዲሉ አስተያየት ሰጪው እዚም እዛም እየረገጡ ህዝብን ከማሳሳት ቢቆጠቡ መልካም ነው እንላለን።

ሌላው የፓርላማ ካፍቴሪያ ጉዳይ ነው። የስራ አስኪያጁ አመጣጥ አይታወቅም የሚለው ስህተት ነው። ሁለት ጊዜ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ወጥቶ እና በብሔራዊ ሬዲዮ ማስታወቂያ ተነግሮ በተደረገ ምዝገባ በአስፈታኝ ድርጅት ከሌሎች ጋር ተወዳድሮና አሸናፊ ሆኖ ነው  ቅጥሩ የተፈጸመው። ቅጥሩም ግልጽና የሚታወቅ ነው።

የቦርድ አባላት የተሰየሙት ሁለቱ አፈ ጉባኤዎች ካፍቴሪያውን ለማስተዳደር ባወጡት መመሪያ መሰረት ነው። ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3 አባላትና ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ደግሞ 2 አባላት ያሉትና የሁለቱ ፅ/ቤቶች የሰው ሀብት አስተዳደር ኃላፊዎች የተወከሉበት ቦርድ ነው። ለአገልግሎታቸው እንደማንኛውም የመንግስት ቦርድ አባል በየወሩ የሚከፈል አበል አለ። የስራ ዘመናቸውም አምስት ዓመት ነው። ዕድሜ ልክ አይደለም። ተመራጮቹ በምርጫው ካልቀጠሉ በአዲስ አባል ይተካሉ። የሚቀጥሎም ሆነ የአፈ ጉባኤዎቹ ይሁንታ ያስፈልጋል፤ አሰራሩ ይህ ነው።

ገቢ ወጪውም ሆነ ንብረቱ በውስጥ ኦዲተር ቁጥጥር ይደረግበታል። 2007፣ 2005 እና 2003 ዓ.ም ኦዲት ተደርጓል። ከትርፍ ገንዘቡም ከሠራተኛው ፍቃድ ውጭ የህዳሴ ግድብ ቦንድ አልተገዛም። ሰራተኛው መዝናናቱ ቀርቶብኝ የካፍቴሪያው አመታዊ ትርፍ ለህዳሴ ግድብ ይዋል ማለቱ ጥፋቱ ምኑ ላይ ነው?  ፀሃፊው ስንት አስተማሪ ነገሮችን መፃፍ እየቻሉ፤ መሰረት የለሽ በሬ ወለደ ወሬ ላይ ጊዜያቸውን ማባከን መፈለጋቸው ከንቱ ጉንጭ አልፋነት ነው።

ምክር ቤቱ ሌላውን እየተቆጣጠረ የጓዳው ነገር እንዴት ይዟል ነው የሚል ሀሳብም ተነስቷል። ፅ/ቤቱ በምክር ቤቱ ቁጥጥር ይደረግበታል። ከምክር ቤቱ ኮሚቴዎች አንዱ የሆነው የምክር ቤት ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ ይከታተለዋል። የምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት የስነ ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀፅ 153 ንዑስ አንቀፅ 4 ስለኮሚቴው ስልጣንና ተግባር ሲደነግግ “የምክር ቤቱን የሰው ሃይል፣ የፋይናንስ እና የንብረት አስተዳደር ይከታተላል፤ ይቆጣጠራል፤ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘውም በአፈ ጉባኤው በኩል ተገቢ እርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫ ያስቀምጣል” በማለት ነው።

ከዚህ ባለፈ የምክር ቤቱ አባላትም አገልግሎት አሰጣጡን አስመልክተው እንደባለ ድርሻ የምክር ቤቱን ፅ/ቤት ይገመግማሉ። ቋሚ ኮሚዎቴችም ከሚሰጧቸው አገልግሎት አንፃር የምክር ቤቱን ፅ/ቤት ይገመግማሉ። እነዚህ ሁኔታዎች ተዳምረው ነው አሁን እየታየ ያለው ለውጥ የመጣው። የምክር ቤቱ ፅ/ቤት የራሱ ራዕይ አለው። ይህን ለማሳካትም አሁንም ብዙ ስራዎችን በማከናወን ላይ የሚገኝ ነው።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽ/ቤት 

የኢንፎርሜሸን ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
432 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1037 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us