ሥራ ፈጣሪዎች የሚገኙበት ቁመና በህብረ ቀለማዊ አይኖች ሲታይ

Wednesday, 21 December 2016 14:28

 

በሸዋፈራው ሽታሁን

በኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ዜጋ ቁጥር በመካከለኛው ስሌት 53 በመቶ እጅ ኢንተርፕረነርሺፕ (የሚሆኑት በራስ ሥራ ፈጠራ) ችሎታን የጨበጡ ናቸው ሲል የሚተርከው በፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንትና ከእድሜያቸው ዘለግ ላለ ጊዜ በልማት ኢኮኖሚክስ ላይ ጥናት በማድረግ ስም ያላቸው ዶክተር ወልዳይ አምሀ በጋራ ካጠኑት የጥናት ፍሬአቸውን ካሳተሙት መጽሔት ላይ ሰፍሯል። ሁለቱ የምጣኔ ሀብት ሳይንስ ቀንዲሎች ግኝታቸውን እንዲህ ይደረድራሉ። ፈጠራ ተኮር የሥራ እድል ምጣኔ (65%)፣ ከቁስ መር ኢኮኖሚ (63%) በአማካኝ ሲበልጥ ፈጠራን መሬት ላይ የማዋል ችሎታ ምጣኔ (69%)፣ ከቁስ መር ኢኮኖሚ (62%) በአማካኝ ያንሳል። በተጨማሪም እድሜ፣ የትምህርት ደረጃ፣ በሥራ ፈጠራ ላይ ያለ የማህበረሰብ አቋም እና ማህበራዊ ድርን የመሳሰሉ የስነ ሕዝብ ምንዝሮች የኢትዮጵያ እምቅ የኢንተርፕሪነርሺፕ አቅምና በእሱም ላይ የመሰማራት ዝንባሌን የሚወስኑ መስመሮች ናቸው።

የከተማ ጐልማሶች በገጠር ከሚኖሩት ይልቅ ፈጥነው በቀደመው ሥራ ፈጠራዊ ንቅናቄዎች ላይ የመሰማራታቸው ነገር በግልጽ ይታያል። የገጠሩ አካባቢ ሰዎች “የእወድቃለሁ ፍራቻ” ከልካይ እንደሆነባቸው ጥናቱ በአሀዝ ተንትኖ ያስረዳል።

ምርምሩ የእነዚህን ስንክሳር ቀስ በቀስ ለማንሳት በከፊልም ቢሆን የኢንተርፕሪነርሺፕ የተለያዩ መልኮች መግቢያና መውጫውን ፍራቻ ማስወገጃ ሥልቶችን ወደ አንጐል የሚያሰርጽ ትምህርት ሥርአት ውስጥ የማካተት ሐሳብን ያጋራል። ትምህርቱን የቀመሰው ሕብረተሰብ በማህበራዊ ድር ውስጥ አንዳቸው ለአንዳቸው እያካፈሉ በማዳረስ በውጤቱም የአመለካከት ለውጥን ልናይ እንችላለን ይላል። ከዚህ ጐን ለጐን ወጥ የኢንተርፕሪነርሽፕ ስትራቴጂ በማውጣት በፖኬጅ ወይም በክላስተር አሰራር የኢንተርፕሪነርሽፕ ኤክስቴንሽን ሰራተኞችን በማሰማራት ብዛትና ጥራት ያለው ድጋፈ ማድረግ እንደ የማያቋርጥ ስልጠናና ክትትል፣ የምርትና የገበያ ትስስር አገልግሎት የመሰረት ልማት አቅርቦት ሙሌት በስልጠናው ውሃ ልክ የተስተካከለ መሆንን፣ የኋላና የፊት የገበያ ቅንብር፣ ብድርና፣ ተስማሚ ወቅታዊ የስትራተጂና ፖሊስ እጅ እንዳይለያቸው ማድረግ ለአዲስ ጀማሪዎች ቢደረግ ሲል ጥናቱ ምክር የሰጠበት ሲሆን ለተጀመሩ አነስተኛና መለስተኛ ኢንተርፕራይዞች ደግሞ አይናችንን ሳንነቅል የማይቆም ድጋፍ እንዲኖር ማስቻል ነው ይላል። ጥናቱ በማጠቃለያው ላይ አስታውሶ ያለፈው የኢንተርፕርነርሺፕ መዋቅር ስእል ከከተማ ገጠር፣ ከክልል ክልል ስለሚለያዩ “ክልል ተኮር የኢንተርፕሪነርሽፕ እቅድ” ያስፈልጋል ሲል ይደመድማል።

ሕግና ኢንተርፕርነርሺፕ

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 40 ንኡስ አንቀጽ 1 ላይ የንብረት መብትን በተመለከተ የሚከተለውን ይላል። “ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ  የግል ንብረት ባለቤት መሆኑ/መሆኗ ይከበርለታል /ይከበርላታል። ይኸ መብት የሕዝብ ጥቅም በመጠበቅ በሌላ ሁኔታ በሕግ እስካልተወሰነ ድረስ ንብረት የመያዝና በንብረት የመጠቀም ወይም የሌሎችን ዜጐች መብቶች እስካልተቃረነ ድረስ ንብረትን የመሸጥ፣ የማውረስ ወይም በሌላ መንገድ የማስተላለፍ መብቶችን ያካትታል። ወረድ ብሎ ይኸንኑ አንቀጽ ሲያጠናክር በአንቀጽ 41 ንኡስ አንቀጽ 1 ላይ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባሕል መብቶች ሥር “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመስማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመስራት መብት አለው” ሲል ያክልበታል። ያልተገደበ መብት፣ መብት አይባልም የተሰኝ የሕዝብና መንግሥት ልሒቃን አስተምሕሮት ያስታውሰናል። ዘንጋችንን ማወዛወዝ የምንችለው የሰው አፍንጫ እስካልነካን ድረስ ነው። የሌሎችን ሰላም፣ ሐይማኖት፣ ክብርና ማንነት እስካላጓደልን ድረስ አዲስ አበባ ላይ ይሁን ድሬዳዋ፣ ኦሮሚያ ይሁን ትግራይ ባሻው ሥፍራ ሄዶ አንዳች ጥቅም አገኝበታለሁ በሚለውና በወደደው የንግድ መስክ ይሁን በሌላ ሥራ ፈጠራና ተዛማጅ ሥራ መሰማራት እንደሚቻል የመብት ድንበሩን ያለብዥታ ያሳያል።

ታላቁ ሕግ /ሕገ መንግሥት/ ይኸንን በማያወላዳ አኳኋን ቢያስቀምጠውም በመሬት ላይ ያለው እውነት  ግን ከሕጉ መንፈስ በአብዛኛው ሊባል በሚችል ሁናቴ ራቅ ብሎ ይታያል። ይኸ የሆነው የሥራ ፈፃሚ የመንግሥት ወኪሎች ሥለ ሥራ ፈጠራ ያላቸው አስተሳሰብና አፈፃፀም መጓደል ታላቁን ሕግ /Grand Law/ የወረቀት ላይ ነብር አድርጐ ያስቀረዋል። ለዚህ ማስረጃ የሚሆነን ከወር በፊት የታየውን ግርግር መጥቀስ በቂ ነው።

የወረዳና የመዘጋጃ ቤት የቢሮ አለቆች የፕሮጀክት ግብአት ሳይሟላ ተደራጅቶ ሥራ እንዲፈጥር ወጣቱን ይሰብኩታል። ወጣቶቹም ቃላቸውን በማመን ወደ ቢሮአቸው ይነጉዳል። የአንድ ሳምንት ሥልጠና ይወስዳሉ። ሥራ ይጀመራል፤ ከወራት በኋላ የቢሮ አለቆች ከእነሱ ጐን አይገኙም። የአለቆች ካላንደራቸው ሲታይ በሚጠቅምና በማይጠቅም የፖለቲካ ጉዳይ ስብሰባ የታፈነ ነው። ወጣቶቹ ደጋፊ አጥተው ይበተናሉ። በራሳቸው ልምድና እውቀት የቆሙት ስላይደሉ። ቆመው ይሄዱ የነበሩት ኢንተርፕራይዞች መንገዳገድ ይጀምራሉ። በሂደትም ሲሟሙ አይተናል። በባሕር ዳር ዙሪያ ብሎኬትና ቢም ማምረት ላይ ተሰማርተው የነበሩ ወጣቶች ይኸንን መሰል እጣ ተጐንጭተውታል። ከአሥሩ የኢንተርፕርነርሺፕ ክህሎት መመዘኛ ሜትሮች ውስጥ ሁለቱ የወርቅ ደረጃ ያላቸው ናቸው። “ፈጣን፣ የተሻለ ርካሽ” እና “የተጠና ኃላፊነት  መውሰድ” የተሰኙት ናቸው። እነዚህ ሜትሮች በሁለቱም ወገን በሥራ ፈፃሚው የመንግሥት ወኪልና በወጣት ሥራ ፈጠራ ተሰማሪዎች ላይ ባልተሟላ አኳኂን የሚገኙ እንደሆነ ይስተዋላል። የሕግ ተርጓሚው አካል የሁከት ይወገድልኝ ጥያቄን ወይም የንብረት ጥበቃን ጥያቄ  ሳያስታምም የሕግ መስመሩን ተከትሎ እራሱን ለሕግና ሞራል አስገዝቶ ሊከውነው የተገባ ነው። ሰሞኑን ለሥራ ጉዳይ ወደ ባሕር ዳር ስንጓዝ እግረ መንገዳችንን ፍቼ ላይ ወርደን ሻይ ቡና እያልን ከተማዋን ዞርናት። አንድ አነስተኛ ሱቅ ያለውን ወጣት ፍቼ እንዴት ናት ስንል ጠየቅነው። “ዛሬ ዛሬ ትሻላለች፣ ሌቦች ባይጠፉበትም” አለ። እናንተስ በስብሰባዎቻቸው ሁሉ እየተሳተፋችሁ አታጋልጧቸውም ብለን ጥያቄአችንን አስከተልን። እነሱ ስብሰባ የሚጠሩት አምሳያዎቻቸውን ነው። ይቃወሙናል ብለው የሚጠረጥሩአቸውን አያሳትፉም፣ አይጠሩም” አለ። ታዲያ ባይጠሩአችሁም መሰብሰብ መብታችሁ አይደለም እንዴ አልነው “ከመሞት መሰንበት ይሻላል” ብሎን ወደ ጓዳው ገባ።

የሕብረተሰብና መንግሥት መሐል ክፍተት የፈጠረው የዝቅተኛና የመካከለኛ አመራር ንቅዘት እንደሆነና መንግሥትም ይኸንኑ ማመኑን ልብ ይሏል። በወረቀት ላይ ያሉ መተዳደሪያ ሕጐች ሥራ ላይ የሚያውላቸው በቀጥታ ከታችኛው ሕብረተሰብ ጋር የሚገናኙት እነሱ ስለሆኑ ነው። ተጠያቂነቱን ትከሻቸው ላይ የምንጥለው።

ዲሞክራሲና ኢንተርፕርነርሺፕ

ከምርጫ 97 በኋላ እንደ አ.አ 2002 ዓ.ም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ስለ ልማታዊ መንግሥት ጽፈው ውይይት ሳይደረግበት በቀጥታ ሥራ ላይ እንዲውል አዘዙ። መለስ ዜናዊ- ነፍስ ይማር!!። የደቡብ ኮሪያ ታይዋን የሩቅ ምሥራቅ ኤስያ ሀገራትን ልምድን በመውሰድ ብዝሀነት በሞላባት ኢትዮጵያን በመሰል ሀገር ዲሞክራሲን ሰርዞ ልማታዊነትን ብቻ የማቀንቀን ውጤት ከ150 በላይ  ፋብሪካዎች በወጣቱ አመጽ ለቃጠሎ መዳረግ ሆኗል። የልማታዊ መንግሥትነት ያስገኘውን ስኬት ወደ ኋላ ስንቃኝ ቀዝቃዛ ጦርነት የበላይነት በያዘበት ከ50ዎቹ እስከ 80ዎቹ አመተ ምህረታት ጊዜ በካፒታሊዝም ጐራ ውስጥ የነበሩት እንደ ደቡብ ኮሪያ ያለው አገር ከሰሜን ኮሪያ ኮምዩኒዝም ለመታደግ አሜሪካ የዶላር ዝናብ ለወቅቱ የደቡብ ኮሪያው አምባገነን መሪ ጀነራል ፖርክ ታዘንብላት ስለነበረ የኢኮኖሚ እድገት በሀገሪቱ መጥቷል። ግን ዛሬ ትናንት አይደለም። ቀዝቃዛው ጦርነት በሶቭየት ህብረት መፈራረስ ምክንያት አክትሟል። በኢትዮጵያ ዲሞክራሲን ቦታ ነፍጐ የሚወጣ ፖሊሲ የመንግሥት ደጋፊ ያልሆኑትን የሕብረተሰብ አካላት በተለይም ምሁራን ከሲስተም ውጭ ያደርጋቸዋል። ስለሆነም ኢንተርፕሪነርሺፕ ቀጭጮ የሚፈስ መዋዕለ ንዋይ እጥረትን ያስከትላል። የሥራ እድል ይመነምናል። የዚህ መሆን ውጤቱ ከላይ የተጠቀሰው ይሆናል።

በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ስለመኖሩ የማይካድ ነው። እድገት ሲመጣ የመጀመሪያ ተጠቃሚዎቹ ካፒታልና እውቀት ያላቸው የመጀመሪያ ረድፍ የፍሬው ተቋዳሾች ናቸው። ይኸ በሌሎች አገሮችም እድገትን ሲጀምሩት የታየ እንጂ በኢትዮጵያ በልዩ ሁኔታ የሚታይ አይደለም። እድገቱ ወደ ደሀው እስኪወርድ ጊዜ ይወስዳል። እስከዚያው ድህነቱን እየተካፈለ ይኖራል። የደሀና የሀብታም የገቢ ልዩነት ይሰፋል፣ መጥበብ የሚችለው የኢኮኖሚ እድገቱ ወደ ኢኮኖሚ ልማት ሲሸጋገር ነው። እድገት የቁጥር ጭማሪን የሚያሳይ ሲሆን ልማት ደግሞ የአይነትና ጥራት እድገትን የሚያሳይ ነው። ይኸንን የኢኮኖሚ እድገት ጠባይ ለህብረተሰብ ግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ፣ የመንግሥት የሥራ ድርሻ ይመስላል። በገቢ ልዩነት ምክንያት ተደጋጋሚ አመጽና ብጥብጥ እንዳይከሰትና ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዳይቀዘቀዝ አንድ  አይነት አስተዋጽኦን ሊያበረክት ይችላልና።

ዲሞክራሲን ቸል ያለ እድገት ሌላም ጣጣን ያስከትላል። የሀገሪቷ ሀብት በጥቂት ቡድኖች ቁጥጥር ሥር በመዋል በግብጽና በቱኒዚያ እንደተፈጠረው አይነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ አሊገርኪ ለመፍጠር አይሳነውም። ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰብ ባለበት፣ ልዩ ልዩ ባሕል ባለበት፣ የማንነት ጥያቄዎች ጊዜ እየጠበቁ ብቅ በሚሉበት አገር ሥራ ፈጠራ፣ ልማት፣ እድገት ያለ ዲሞክራሲ ከፎርሙላ ውጪ ይሆናል።

አሜሪካዉው የኢኮኖሚክስ ሊቅ አማርትያ ሰን በ1998 እንደ እ.ኤ.አ. የኢኮኖሚክስ ኖቤል ሽልማት ያገኘበት ሃሳብ ይኸው ነበር። ዌልፌር ኢኮኖሚክስ ምንጩ የሰዎች መሰረታዊ ፍላጐት መሟላት፣ ከማናቸውም ባርነት ነፃ መውጣት፣ በመረጡት የሕይወት መንገድ ሲኖሩና የመረጡትንም ሲያገኙ ነው ይላል። የአለም ባንክ የዚህን ሊቅ ሰው ሐሳብ በመዋስ የሀገራትን እድገት የሚተልምበት መለኪያ አድርጐ እየተጠቀመበት ነው። መለኪያው የመልካም አስተዳደር ጠቋሚዎች /Good governance indicator/ ይሰኛል። ስለሆነም ዲሞክራሲ አማራጭ ሳይሆን ግዴታ ነው።

የሕዝብ ቁጥር እድገትና ኢንተርፕርነርሺፕ

ከዛሬ 20 አመት በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 150 ሚሊየን እንደሚደርስ ይገመታል። ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲወዳደር ቁጥሩ ከፍተኛ ነው። በበጐ አይን ስናየው ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ፀጋ ነው። ለጐረቤት ሀገራትና በዙሪያቸው ላሉት አፍሪካውያን የገበያ እድል ያስገኛል። በጐ ባልሆነ አይን ሲታይ ደግሞ የኢኮኖሚ እድገታችን  የሕዝብ ቁጥሩን ካልበጠ እዳ  ይሆናል። አሊያም እድገቱና ሕዝበ ምጣኔው ጋር እኩል መሆን አለበት። ሁለቱም ካልተሳኩ ግን በፈተና ጐዳና ላይ እናዘግማለን።

በ20ኛው ከፍለ ዘመን ሁለተኛው አጋማሽ ላይ በተለይም በ1950ዎቹ ሕንድ በረሐብ ወረርሽኝ ስትመታ የዛሬን አያርገውና ኢትዮጵያ ምግብና ጥራጥሬ ለሕንድ ልካ ነበር። የጠኔ ጊዜያቸው ጋብ ሲልላቸው በ1960ዎቹ ከምግብ እጥረት አርነት ያወጣቸውን “የአረንጓዴው አብዮት” ነጋሪትን ጐሰሙ። ሰሩም። ዛሬ ሕንድ በምግብ እራስዋን ከመቻልዋም በላይ ልዩ ልዩ ምርቶችን ለአለም ገበያ የምታቀርብ ባለፀጋ ሀገር ሆናለች።

ኢትዮጵያም ከሕንድ ልምድ በመውሰድ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ኢንተርፕርነርሺፕ ሥራ ላይ ብታውል እንደሚበጃት ይታመናል። ለሥራ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ የመጡ የገጠር ኗሪዎች የእግረኛ መንገዶችን  አጨናንቀው ይታያል። የቁጥሩ መብዛት በአካባቢ የተፈጥሮ ሀብት ላይ፣ በትራንስፖርትና የመብራት ሀይል አቅርቦት ላይ ጫና ያሳድራል። ወጣትና ጐልማሶቹ አዲስ አበባን ሌሎች አብይ ከተሞችን ከሚያጥለቀልቁ ይልቅ በየቀዬአቸው መሬት ያላቸው ከመሬታቸው ላይ፣ የሌላቸው ከወላጆቻቸው መሬት ተካፍለው፣ ወላጆች ፈቃደኛ ካልሆኑ ያልታረሰ መሬት እየመነጠሩ የአካባቢ ሀብትን ለብክለትና ምክነት ሳይዳርጉ በጥንቃቄ የሚያበጁበት መሆን ይኖርበታል። ልምድና እውቀት እንደአቅማቸው የሙያ ችሎታ ያላቸው ከፋብሪካዎች ጋር ለማስተሳሰር የሚሞክርበት የፋብሪካን ምርት ለጅምላ ሻጭ ብቻ ከሚሸጥ ይልቅ ወጣቶች ብድር እየተሰጣቸው በቀጥታ ከፋብሪካው ምርትን እየገዙ ለህብረተሰቡ በየመንደሩ እንዲያከፋፍሉ የሚያስችል በዚህም የደላላና ልዩ ልዩ ወጪዎችን በማስቀረት በኢንተርፕርነርሺፕ ዘዴ ቁጥሩ ከፍ ያለ ወጣትን ወደ ሥራ የሚያሰማራ ፖሊሲና ስትራተጂ ያስፈልገናል።

በጥቅሉ የዲሞክራሲ፣ የሚዲያና የሲቪል ማህበራት ተናቦ የመስራት ጥምረት ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ አጣዳፊ ሥራ ነው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
536 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 420 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us