ሕፃናት እንዲያነቡ የወላጆች የቤት ሥራ

Wednesday, 18 January 2017 10:39

መ.ተ

 

በኋላ ሕይወታቸው አንባቢዎች እንዲሆኑልን የምንመኝላቸውን ሕፃናት የንባብ ፍቅር እንዲያድርባቸው ማድረግ የምንችለው በማለዳ የቤት ሥራችንን ሥንሠራና ከጨቅላ እድሜአቸው ማስጀመር ስንችል ነው። ለልጆቻችን ምግብ፣ ልብስ፣ መኖርያ ቤት በማሰናዳት  ለአካላዊ ዕድገታቸው እንጥራለን። ለአዕምሯዊ ዕድገታቸው የምንሰራ ከሆነ ደግሞ አዕምሮአቸውን ለማበልጸግ መፃሕፍት እንዲያነቡ ማድረግ አለብን።

አዕምሮን ለማበልጸግ ፕሌይ ስቴሽን፣ ሌሎች ጫወታዎች ማጫወት እና መጫወቻ ሽጉጥን የመሳሰሉ ቁሳቁስ ለልጆቻችን የምንሰጥ ወላጆች በርካታ ነን። ቴሌቪዥን እንዲመለከቱም የምናደርግም አለን። ነገር ግን እነ ፕሌይ ስቴሽን በበዙ ቁጥር የማንበብ ፍላጎትን በእጅጉ እንደሚቀንሱ በጥናት የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። አርተፊሻል ሽጉጥ በሕፃንነቱ የሰጠነው ሕፃንም ምናልባት አነጣጥሮ ተኳሽ እንጂ ጥሩ አንባቢ ላይሆን ይችላል።

ልጆችን ጥሩ አንባቢ ለማድረግ ወላጆች የቤት ሥራቸውን መጀመር ያለባቸው ግን ከራሳቸው ከወላጆች ነው። ወላጆች ራሳቸው ማንበብ ይኖርባቸዋል። ልጆች ወላጆቻቸውን የሚመስሉት በመልክ ብቻ ሳይሆን ከወላጆቻቸው በሚማሯቸውም ነገሮች ነው። ማንኛውም ለልጁ ቅን አሳቢ ወላጅ ልጁ “እናቴን አይቼ ነው መጠጥ የጀመርኩት፣ አባቴ ይጠጣ ስለነበር እኔም ጠጪ ሆንኩኝ” ከሚል ይልቅ “እማዬ ስታነብ አይቼ ነው፣ አባቴ ሲያነብ አይቼ ነው ማንበብ የጀመርኩት” ቢል ይመርጣል። አንዳንድ ወላጆች ግን በእኩልነት ሰበብ፣ በማዝናናት ሰበብ ልጆቻቸውን መጠጥ ቤት በመውሰድ ለራሳቸው አልኮል መጠጥ ሲጠጡ ለልጆቻቸው ለስላሳ ሲገዙ እና “እስቲ ቅመስ ምን ምን ይላል” ሲሉ ይስተዋላል። ይህንን በዐይን አይቶ ማረጋገጥ የሚፈልግ በካዛንቺስ፣ በፒያሳ እና በአራት ኪሎ አልፎ አልፎም በሌሎች ከተሞች አንዳንድ መጠጥ ቤቶች መቃኘት በቂው ነው።

ወላጆች ይህን ከማድረግ ተቆጥበው ልጆቻቸው ከንባብ ጋር ፍቅር የሚወድቁበትን ሌሎች ዘዴዎች ቢቀይሱ ለራሳቸውም ለወላጆቻቸውም ለሀገርም የሚጠቅሙ አንባቢ ዜጎች ማፍራት ይቻላል። ይህን ከማድረጊያ ዘዴዎች አንዱ ልጆቻችን በሚገኙባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ለእነሱ የሚሆኑ መጻሕፍት አስቀምጠን እንዲያነቡ ማበረታታት ነው። መፃሕፍቱን በመኝታ ቤታቸው፣ በመኪና ውስጥ፣ በመኖርያ ቤት ሳሎን፣ በሕፃናት ማቆያዎች እና መዝናኛዎች ወዘተ መሆን ይችላሉ።

ለልጆች የንባብ ባሕል መዳበር ወላጆች ኃላፊነቱን ለመምህራን ብቻ መተውም የለባቸውም። ወላጆችም መምህራንም ያልተናነሰ ሚና አላቸው።

ከሦሥት ዐሠርት ዓመታት በፊት በነበረ የትምህርት አሰጣጥ የቋንቋ መምህራን ማንበብ የሚችሉ ጎበዝ ተማሪዎችን ብቻ ሲያስነብቡ እንደነበር የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከራሱ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ያስታውሳል። ይህ ግን በፍጹም ትክክል አይመስልም። ምክንያቱም ውጤታማ የሚደርገው እና አንባቢ እንዲሆኑ የሚገፋፋው ጥቂት ተማሪዎችን ብቻ ነውና።

እዚህጋ መምህራኑም ሆኑ ወላጆች ብዙ ወላጆች ልጆች እርስ በርስ እንዲያነቡ ዕድሉን ማመቻቸት ይኖርባቸዋል። ይህ በትምህርት ቤት አካባቢ ብቻ የሚከናወን አይደለም። ወላጆች በራሳቸው ጊዜ ልጆቻቸውን እና የጎረቤቶቻቸውን ልጆች በጋራ እንዲያነቡ ማድረጋቸው ተገቢ ነው።

እነዚሁ ወላጆች የልጆቻቸውን ልደት ሲዘክሩ ከሚገዙዋቸው ቸኮሌት፣ ከረሜላ፣ ሙዝ፣ ብርትኳን … ጋር መጽሐፍ በመግዛት ለልጃቸው ስጦታ ቢሰጡም የሚደገፍ ተግባር ነው። ከዚህም ሌላ ለልደት የተጠሩትን ልጆችም ሆነ ሌሎች የሰፈር ልጆችን በንባብ አወዳድሮ የተሻለ ውጤት ለሚያመጡት መፃሕፍት ቢሸልሙ ሌሎቹንም ያላሰለሰ ድጋፍ ቢያደርጉላቸው ለነገ አንባቢ ትውልድ መፈጠር ዛሬ መሠረት እየጣሉ መሆኑን ሊረሱት አይገባም።

የመሠረት መጣሉ ሥራም በዚህ ብቻ የሚበቃም አይደለም። በመኝታ ሰዓት ተረት ይነግራሉ ተብለው የሚጠበቁ እነዚሁ ወላጆች ለልጆቻቸው መጽሐፍ ማንበብ፣ ልጆቹን ማስነበብ እና ከልጆቻቸው ጋር አብረው ማንበብም ይችላሉ። አብሮ ማንበብ ለወላጅ ልጅ ፍቅር ይበልጥ መዳበርም ያግዛል ይባላል።

ከአብሮ ማንበብ ሌላ አብሮ ሽርሽርም ሆነ አያት ጥየቃ በሚኬድበት አጋጣሚ ሁሉ ልጆችን ከንባብ ጋር የማቆራኘቱ የቤት ሥራ በወላጆች ትከሻ ላይ የተንጠለጠለ ነው። እርስዎ እንደ ወላጅ ልጆችዎን አያትጋ መውሰድ ብቻ አይበቃዎትም። ስለ ወላጆችዎ ማለትም ሥለ ልጆችዎ አያቶች የተጻፉ ነገሮችን ለልጆችዎ አዕምሮ በሚስማማ መልኩ ማንበብ ቢችሉም ይመረጣል። የሚነበበው ነገር የግድ በመጽሐፍ መልክ የተቀናበረ ወይም በታዋቂ ደራሲ የተጻፈ መሆን አይጠበቅበትም። እርስዎ ራሶ መጠነኛ ጽሑፍ ማዘጋጀት ይችላሉ።

ልጆቼ እንዲያነቡ ምን አድርጌአለሁ ብለው ዘወትር ራስዎን በመጠየቅ የወላጅነት ወይም የአሳዳጊነት ሚናዎን መወጣት እንዳለቦት አይዘንጉ። እርሶ ትልቁን ሚና ይወጡ እንጂ መንግሥትም የተቀረውም ማኅበረሰብ ሚና እንዳለውም ያስታውሱ።

ሌላም እርስዎ ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር አለ። ልጆችዎን በእረፍት ሰዓታቸው ቤተመጻሕፍት ይውሰዷቸውና እንዲያነቡ መንገዱን ይክፈቱላቸው። በአብያተ መጻሕፍት የታሪክ፣ የምግብ አሰራር፣ የፍልስፍና፣ የሥነ ሕይወት፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የምህንድስና፣ የሃይማኖት፣ የልቦለድ፣ ሌሎችም መጻሕፍት እና ሌሎች ጥራዞች ለልጆች እንዲሆኑ ጭምር ሆነው የተዘጋጁ ስላሉ እነዚህንም ልጆችዎ እንዲያነቡ ያበረታቱዋቸው። ምንጊዜም ግን መርሳት የሌለቦት በቤተመጻሕፍቱም ሆነ በሌላ የማንበቢያ ሥፍራ ልጅዎ የመረጠችውን/ የመረጠውን እንዲያነብ/ እንድታነብ ምርጫውን ለእነሱ መስጠት ብልህነት ነው።

አብረው ማንበብ በሚኖርቦትም ጊዜ የልጅዎ ምርጫ እንደተጠበቀ ነው። ከዓሥር ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት በብዛት ማንበብ ያለባቸው ጎላ ጎላ ባሉ ሆሄያት የተጻፉ ጽሑፎች ሥዕል በርከት ያለበት መጽሐፍ መሆን እንዳለበትም በዘርፉ በማስተማር እና በመመራመር የተሰማሩ ምሁራን ይመክራሉ። ምክሩን መቀበልዎ እንደተጠበቀ ሆኖ በጋራ ከልጅዎ ጋር በሚያነቡበት ጊዜ መጽሐፉ ሥዕላዊ ከሆነ ልጅዎ ስለ ሥዕሉ እንዲናገር ሥለ ጽሑፉም ምን እንደተረዳ መጠያየቁ ለወደፊት የሚያነበውን መጽሐፍ በበለጠ ጉጉት እንዲያነብ ይጋብዘዋል።

የልጅዎ የንባብ ጉጉት የሚቀንሰው ግን ማድረግ ያለብዎትን ሳያደርጉ ሲቀሩ እና ልጅዎ በቴሌቪዥን ፊልሞች እና በቪዲዮ ጌሞች ተጠምዶ እንዲውል የለቀቁት ጊዜ ነው። ቴሌቪዥን መመልከት፣ ኮምፒዩተር ላይ መጫወት፣ የቪዲዮ ጌም መጫወት እና ሰፈር ውስጥ ኳስ መጫወት የየራሳቸው ጠቀሜታ ቢኖራቸውም የልጅዎን አዕምሮ ሙሉ በሙሉ እስኪቆጣጠሩ ግን መጠበቅ አይኖርበትም። ሁሉም ነገር በልኩ ሲሆን ያምራልና። እርስዎ የቤት ሥራዎን በአግባቡ ከሠሩ ሁሉንም ነገሮች ከልጅዎ ጋር በመመካከር በመርሐግብር በማከናነወን የቤት ሥራዎን መሥራት አያቅቶትም።

ሁል ጊዜም ግን ማስታወስ ያለብዎት ልጅዎ ራሱን ችሎ ቢማርም በራሱ አይማርም። ብዙውን ነገር ከርስዎ ከአባቱ ከእርሶ ከእናቱ ነው የሚማረው። ሲወለድም አዕምሮው እንደ  ነጭ ሰሌዳ ሆኖ ነው። ነጭ ሰሌዳ የጻፉበትን ይጽፋል። ልጅዎም እንደዚያው ነው። በልጅዎ ነጭ ሰሌዳ ላይ በጎውንም መጥፎውንም፣ ስኬቱንም ውድቀቱንም መጻፍ የሚጀምሩት እርስዎ ወላጅ ወይም አሳዳጊው ነዎት። የቤት ሥራዎን በአግባባ ከሰሩ ልጅዎ አንባቢ ሆኖ ያድጋል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
453 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 123 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us