በቃና ቴሌቪዥን የሚቀረጹ ትውልዶች እና ቀጣዩ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ጫናዎቹ እንዴት ይታያሉ

Wednesday, 01 February 2017 14:08

የትኛውም ሀገር የራሱን ታሪክ ማንነት የመተረክ መብቱ የተጠበቀ ነው። ራስን መሆን፣ በራስ እሴቶች መቆም ማመን የሚመከር ነው። በተለይ የራስ ማንነትን ታሪክን ለማሳወቅ ብዙ መንገዶች አሉ። አንዱ ፊልም ነው። ፊልም በሲኒማ ማሳያ ቤቶች የሚቀርብ ወይም በቴሌቪዥን ተከታታይ ፕሮግራሞች የሚቀርብ ነው።

ብዙውን ጊዜ ፊልም የሚቀርብበት ፎርም ሳይሆን ይዘቱ አጨቃጫቂ ነው። አሉታዊ ወይም አዎንታዊ ገፅታዎችም አሉት። ፊልም ለመዝናናት የሚተወነ፣ በቀላሉ በምስል ተደግፎ የሚቀርብ ድርጊት በመሆኑ ተፅዕኖው ተደራሽነቱ ከፍተኛ ነው። በአንድ ጊዜ የተፈለገን መረጃ ወይም ጭብጥ ለብዙ ተመልካች ማቅረብ ማድረስ የሚያስችል ቀላል ዘዴ ነው። በፊልም የሚተላለፉት መልዕክቶች ተደራሽ እንዲሆኑ የሚመረጥበት መንገድ አደገኛ እና እጅግ አጨቃጫቂ ነው። ይኸውም፣ በወንጀል በግድያ በዝሙት በኃይል ላይ መሰረት ያደረጉ በመሆናቸው ነው።

በተለይ በሁከት፣ በጠብ እና በሃይለኝነት ላይ የተመሰረቱ ፊልሞች በሕፃናት እና በወጣቶች ባህሪ ላይ ያላቸው ሚና አሉታዊ ነው። በሌላ መልኩ ከፊልም ጋር ተያይዘው የሚቀርቡ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ምርጫዎች፣ የፖለቲካ ስልቶች፣ የፖለቲካ ፍላጎት ማስፈጸሚያ መንገዶች በርካታ ናቸው። በሀገራችንም በቴሌቪዥን በተከታታይ የሚሰራጩ የተለያዩ የፊልም ጭብጦች መኖራቸው ይታወቃል። ከሁሉም በላይ ግን በቃና ቴሌቪዥን እየተላለፉ የሚገኙ ፊልሞች ይዘታቸው በሁከት በጠብ በሃይል ላይ ያተኮሩ መሆናቸው በሕፃናት እና በአዋቂዎች ቀጣይ ባሕሪ ላይ ያላቸው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው። አሉታዊ ተፅዕኖውም ያመዝናል። በቀጣይም ከፖለቲካ ጋር የተያያዙ ጭብጣቸው በተወሰኑ ሃይሎች ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ መቅረባቸው አይቀሬ ነው።

በዚህ ጹሁፍ በወፍ በረር ለማቅረብ የተሞከረው ፊልም ባሕሪን ከመለወጥ እና የተለያዩ የፖለቲካ ፍላጎቶች ማስተላለፊያ መንገድ መሆኑን ለማመላከት ነው። እንዲሁም ከፖለቲካ ፍላጎቶች አንፃር ፊልም ያለውን ሚና እና ተፅዕኖ አመላካች ነገሮች ለማቅረብ ነው። በአሜሪካ ሀገር የተሰሩ በርካታ ጥናቶች ቢኖሩም ለማሳያነት አንድ ሁለቱን መመልከቱ አይጎዳም።      

በሀገረ አሜሪካ በአማካኝ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ከታቀፉ ልጆች መካከል፣ 8ሺ የግድያ እና 100ሺ የሁከት የወንጀል ፊልሞችን ለማየት የተጋለጡ ናቸው። እድሚያቸው አስራ ስምንት ዓመት ሲሞላቸው ቀደም ብሎ ከሰፈረውን አሃዝ በእጥፍ የመጋለጥ እድላቸውን የሰፋ ነው።

በዚህ መልክ ተጋላጭ የሚሆኑ ልጆች ባሕሪያቸው ተገማች ነው። የአመጸኝነት የሃይለኛነት ባሕሪ እና በቴሌቪዥን የሚቀርቡ ፊልሞች ቀጥተኛ ተያያዥነት አላቸው። በአሜሪካ የብሔራዊ የአእምሮ ጤና ተቋም ሪፖርት "Television and Behavior: Ten Years of Scientific Progress and Implications for the Eighties." እንደሚያሳየው፣ በመጫወቻ ቦታዎች እና በጎዳናዎች ላይ በቴሌቪዥን በሚሰራጩ የግድያ የአመጽ ፊልሞች መነሻ ሁከት፣ ብጥብጥ፣ ሃይል የተቀላቀለበት ድርጊት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አረጋግጠዋል። በአምስት አመታት ውስጥ በ732 ልጆች ላይ በተደረገው ጥናት፤ የተለያዩ ጠብ የሚጭሩ ባሕሪዎች ተስተውለዋል። ከወላጆች ጋር ግጭት መፍጠር፤ ግጭት እና ወንጀል መፍጠር፤ እነዚህ ባሕሪዎች ቴሌቪዥን ከሚመለከቱ ሰዎች ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት እንዳላቸው አረጋግጠዋል።

በረጅም ጊዜ የተደረገው ጥናት ደግሞ በጣም የሚረብሽ ነው። በአሜሪካ በሚገኘው የኢሊኖይ ዩኒቨርስቲ ሳይኮሎጂስት የሆኑት ሌዎናርዶ አሮን፣ ልጆች በስምንት አመታቸው እና በድጋሚ የአስራ ስምንት አመት ወጣቶች ሲሆኑ ባጠኑት ጥናት እንዳሰፈሩት፣ ልጆች በስምንት ዓመት እድሚያቸው አካባቢ ቴሌቪዥን ማየት ልምድ ያደርጋሉ። ስለዚህም ከስምንት ዓመት እድሜያቸው ጀምሮ የኃይለኝነት ባሕሪ ይጫናቸዋል። በጣም የሁከት የብጥብጥ ፊልሞችን ከሶስተኛ ክፍል ጀምሮ ምርጫቸው ያደርጋሉ። ባሕሪያቸውም በጣም ኃይለኛ፤ ለጠብ የቀረቡ ይሆናሉ። ኤሮን ያስቀመጡት ማጠቃለያ፣ በቴሌቪዥን የሚተላለፉ የሁከት የብጥብጥ ፊልሞች በልጆች ላይ የሚያስከትሉት ውጤት ወይም ተፅዕኖ ተደማሪ ነው።

ኤሮን እና ሮዌል ከሃያ ዓመታት በኋላ በጥናታቸው ያገኙት፣ ስርዓተ ጥለቱ እንደቀጠለ (pattern) ነው። በጥናታቸው ያገኙት፣ በስምንት ዓመታቸው ጀምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው የሁከት የብጥብጥ ፊልሞችን የተመለከቱ ልጆች፤ ወንጀል የመፈጸም፤ ሕፃናትን ማወክ፤ ፍቅረኛቸውን የማወክ እድላቸው እስከ ሰላሳ ዓመት እድሚያቸው የሚቀጥል ነው። የጥናታቸው መደምደሚያም እንደሚያሳየው፤ በከፍተኛ ሁኔታ ለሁከት ለብጥብጥ ፊልሞች ተጋላጭ መሆን፤ ለሃይለኝትን ባሕሪ መንስኤ ነው። የቴሌቪዥን ሁከት ብጥብጥ የሚጎዳው፤ በወጣትነት እድሜ የሚገኙትን ወንዶችንም ሴቶቹንም፣ በተለያዩ በማሕበራዊ-ምጣኔ እና በሁሉም የማሳብ ደረጃ የሚገኙትን ወጣቶችን ያካትታል።

ከፖለቲካ ኢኮኖሚ ጫናዎች አንፃር

ዳግላስ ኬለነር “Film, Politics, and Ideology: Reflections on Hollywood Film in the Age of Reagan*” በሚል ርዕስ ባሰፈሩት ጹሁፍ፣ ከቀደም ብለው በጻፉት መጽሃፍ ላይ “Politics and Ideology in Contemporary Hollywood Film (1988),” ያሰፈሩትን ፍሬ ነገር ጠቅለል አድርገው አቅርበውታል። ይኸውም፣ “ማይክል ራያን እና እኔ (ዳግላስ ኬለነር) የሆለዉድ ፊልሞች ከ60ዎቹ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከፖለቲካ ንቅናቄዎች እና ከተለያዩ ትግሎች ከተፈጸመባቸው ታሪካዊ ወቅቶች ጋር የተያያዙ ናቸው ብለን እንሞግታለን። የእኛ የትርካ ታሪክ ካርታ፣ በ60ዎቹ የሥርነቀል ለውጥ አራማጆች የመውጣትና የማዘቅዘቅ፣ በ70ዎቹ የሊብራሊዝም ውድቀት እና የአዲስ ቀኝ ሃይሎች ማበብ እና በ80ዎቹ የቀኝ ሃይሎች አሸናፊነት እና ዓብይ የፖሊካ ኢኮኖሚ አስተሳሰብ መሆኑ የሚያሳዩ ናቸው። አረዳዳችን፣ አብዛኞቹ የ60ዎቹ ፊልሞች ሃተታ ፀረ-ጦርነት፣ አዲስ ግራ ዘመም እንቅቃሴዎች እና ፌሚኒዝም፣ ብላክ ፓዎር፣ ተቃርኖያዊ የባህል ንቅናቄ እና በማህበራዊ ሁኔተዎች ላይ አዲስ ጠንካራ ትችት ማፍለቅ ላይ ያተኮሩ ናቸው።” ብለዋል።

በዚህ ጹሁፋቸው በሀገራችን የፊልም አፍቃሪዎች ዘንድ ከፍተኛ አድናቂዎች ያላቸው ሮኪ እና ራምቦ የሰሯቸውን ፊልሞች በማሳያነት አቅርበዋል። ይኸውም፣ “The Rocky-Rambo syndrome” በሚል ማቀፊያ አስቀምጠውታል። ሮኪ እና ራምቦ የሚሰሯቸው ፊልሞች በማይታመኑ ድርጊቶች እና ብቃቶች የሚፈጸሙ ገድሎች ናቸው። ፀሐፊውም የሚሉት፣ ከሮኪና ከራምቦ ፊልሞች የዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ የሚያገኘው ወይም የሚረዳው፣ “እውቅና እና ራስን ለማረጋገጥ የሚቻለው በሃይል እና ራስን የማይቀመሱ ተጋፊ አድርጎ በማቅረብ ነው።” በራምቦ ፊልሞች ማብቂያ ላይ አሳዛኝ የፍቅር ፍላጎቶች የሚንንጸባረቁት፣ ማኅበረሰብ በቂ በሆነ ሁኔታ መዋቅራዊ የጋራ ድጋፍ በግለሰቦች መካከል ለሚፈጠር ጤናማ ግንኙነት ማቅረብ እንደማይችል ነው። እንዲሁም የስታሎን ፊልሞች ጡንቸኝነት እና በወታደራዊ የበላይነት ራስን የማረጋገጥ ሁኔታዎችን የሚያወድሱ ናቸው።

ከላይ እንደማሳያ የቀረቡ ሁለት ሃተታዎች ፊልም ከባሕሪ እና ከፖለቲካዊ ተልዕኮው አንፃር እንድንመለከተው የሚያመላክቱ ናቸው። በሕፃናትና በወጣቶች ላይ የሚፈጠሩ አሉታዊ የባሕሪ ለውጦች ማሕራዊ ቀውስ ማስከተላቸው አይቀርም። ያስከትላሉም። እያስከተሉም ነው። ከፖለቲካ አንፃርም ስንወስደው የበለጸጉ ሀገሮች ወይም ዓለም ዓቀፉ የኮርፖሬት መዋቅር የሚፈልጉትን የፖለቲካ አስተሳሰቦች በሕዝብ ላይ የሚጭኑበት መንገድ ነው። የእነዚህን ውጤቶች ለመገንዘብ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚሆን አይደለም። አደጋቸው ተደማሪ በመሆኑ፣ ነገን ዛሬ ላይ ሆኖ መመልከት የሚችል አቅም ያስፈልጋል። አንዳንድ በዚህ የፊልም ኢንዱስትሪ የተሰማሩ ሰዎች በፊልም ዙሪያ የሚቀርቡ አስተያየቶችን ከኢኮኖሚ ጠቀሜታ አንፃር በማንሳት ሊያከሽፉት ሲራወጡ ማየት የተለመደ ነው።

ለምሳሌ በሀገራችን በቃና ቴሌቪዥን የሚተላለፉ ፊልሞች ከዘጠና አምስት በመቶ በላይ በሕፃናት ባሕሪ ላይ የሚያስከትሉት አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው። የቤተሰብ ጊዜ የሚባል በተለይ ከሥራ በኋላ የሚሰባሰበው ቤተሰብ ጊዜውን በፊልም ብቻ እንዲያጠፋ የውዴታ አስገዳጅነት ላይ ጥለውታል። ሕፃናት ነገን የሚያስታውሱት የሚናፍቁት፣ ቀጣዩን የፊልም ክፍል ነው። ትምህርት ቤት ውስጥ የሚያወሩት ያለፈውን የፊልም ታሪክ ነው።

በተለይ የፊልሞቹ ይዘት በጠብ በተንኮል በሃይል ላይ ያመዘኑ መሆናቸው የወጣቶችን አይምሮ የመዝረፍ እድላቸው ከፍተኛ ነው። የፊልሞቹ የመልዕክታቸው ይዘት እና የፊልሙ አተራረክና ድርጊት በራሱ ብቻ በአንድ ሰው ባሕሪ ላይ የሚያስከትለው ጫና በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም። በፊልሞቹ ላይ አንዳንድ የቃላት አጠቃቀምና አመጣጠን ወላጅ ከልጆቹ ጋር በጋራ ሊያዳምጣቸው የሚገቡ አይደሉም። ልጆችንም አለእድሚያቸው ለወሲብ እንዲነሳሱ የሚጋብዙ ናቸው።

የፊልሞቹ ዘውግ አመራረጥ በራሱ ከተራ የኢኮኖሚ ትርፍ ተጠቃሚነት የዘለሉ አይደለም። አንድ ፊልም የሚሰራው በአብዛኛው ከአንድ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ነው። በሌሎች ሀገሮች ልክ የሆኑ እሴቶች፣ በዚህ ሀገር ውስጥ ተቀባይነት የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚህ በፊት የተለያዩ ፊልሞች ሲታዩ ያልቀረቡ ስጋቶች ለምን በቃና የቴሌቪዥን ተከታታይ ፊልሞች ላይ መሰንዘር አስፈለገ? የሚል ጥያቄ ማቅረብ አስፈላጊ ነው። ምላሹም፣ የቃና ፊልሞች ተደራሽነት ከፍተኛ በመሆኑ ነው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በሀገሪቷ የሥራ ቋንቋ ተተርጉሞ መቅረቡ ነው።

ቃና ወደፊት የሚያስከትለውን የማሕበራዊ ቀውስ በአስተማማኝ ሁኔታ ማስቀረት የሚችሉት፣ ወላጆች ብቻ ናቸው። የመንግስት ኃላፊነት የሚሆነው የፖሊሲ ማስተካከያዎችን ማስቀመጥ ነው። ምን አይነት ማስተካከያዎች፣ በጥናት የሚመለሱ ናቸው የሚሆኑት።

የቃና ኃላፊነት የሚሆነው፣ በማሕበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ ሕዝብ አሳታፊ የሆኑ ዘገባዎች እና ውይይቶች ማቅረብ ነው። በጋዜጠኞች እየተዘጋጁ የሚቀርቡ ሃሽ ታግ ምንድን ነው? የሚሉ ፕሮግራሞች በአዎንታዊ መልኩ የሚወሰዱ ናቸው።

እንደመውጫ ግን፣ ዛሬ ላይ ሆኖ ነገን መመልከት የሚችል የማሕበራዊ ጥናት ባለሙያ ወይም የመንግስት ኃላፊ ቃና ስለሚፈጥራቸው ቀጣይ ትውልዶች መመካከር ያለብን ይመስላል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
529 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 131 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us