የሐብት ምዝገባ ተከናውኗል፣ ማሳወቁስ?

Wednesday, 01 February 2017 14:10

 

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የሀገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች ሥር ነቀል በሆነ ሁኔታ በመቀየር መልካም አስተዳደር የተረጋገጠበት፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት መንገሥታዊ ሰራርን ለመዘርጋት አስተዋጽኦ ያላቸው በርካታ እርምጃዎችን እንደወሰደና አሁንም በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። ከእነዚህም መካከል የመንግስት አሠራርን በግልጽነትና በተጠያቂነት ላይ ለመመስረት፣ ሙስና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ እንዲሁም የመንግስት የሥራ ኃላፊነት እና የግል ጥቅሞች ሳይቀላቀሉ በየራሳቸው መንገድ የሚመሩበትን ግልጽ ሥርዓት በመዘርጋት ሊፈጠር የሚችለውን የጥቅም ግጭት ለማስወገድ የሀብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ አዋጅ ቁጥር 668/2002 ሚያዚያ 2002 ዓ.ም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁ ተጠቃሽ ነው።

አዋጁ የፌዴራል የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የተሿሚዎችን፣ የተመራጮችንና የመንግሥት ሠራተኞችን ሃብት እንዲመዘግብ፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘውም የምዝገባውን በሙሉ ወይም በከፊል የስነ-ምግባር መከታተያ ክፍሎችን በመወከል ሊያከናውን እንደሚችል፣ የሀብት ምዝገባ ሰነዶች ጠባቂ ሆኖ እንደሚያገለግል፣ ሃብታቸውን ላስመዘገቡ ተሿሚዎች፣ ተመራጮችና የመንግሥት ሠራተኞች የምዝገባ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንደሚሰጥ እና በአጠቃላይ ስላከናወነው የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ መረጃ በየሁለት ዓመቱ በሪፖርት መልክ ማውጣት እንደሚጠበቅበት ይደነግጋል።

በዚሁ መሠረት ኮሚሽኑ በመጀመሪያው ዙር (2003-2004) የተካሄደውን የተሿሚዎች፣ የተመራጮችና የመንግሥት ሠራተኞች የሃብት ማሳወቅና ምዝገባ አጠቃላይ የሁለት ዓመት የአፈፃፀም ሪፖርት አዘጋጅቷል። በሪፖርቱም የሀብት ማሳወቅና ምዝገባን አጠቃላይ ምንነትና ጠቀሜታ፣ የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ በኢትዮጵያ፣ የኮሚሽኑን የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ዳይሬክቶሬት አመሰራረትና አደረጃጀት፣ የሀብት ማሳወቅና ምዝገባን የሁለት ዓመት የተጠቃለለ የሥራ እንቅስቃሴ፣ በእስከአሁኑ የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ወቅት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና መፍትሄዎች፣ በቀጣይ ከሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ሥራ አንፃር ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እና አጠቀላይ የሀብት ምዝገባ መረጃዎች እንዲካተቱ ተደርጓል።

የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ አጠቃላይ ምንነት፣ የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮና ጠቀሜታ

 የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ አጠቃላይ ምንነት

ሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ማለት የአንድን ሀገር መንግስታዊ አሠራር በግልጽነትና በተጠያቂነት ላይ ለመመስረት፣ ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እንዲሁም የመንግስት የሥራ ኃላፊነት እና የግል ጥቅም ሳይቀላቀሉ በየራሳቸው መንገድ የሚመሩበት ግልጽ ሥርዓት በመዘርጋት ሊፈጠር የሚችለውን የጥቅም ግጭት ለመከላከልና ለማስወገድ እንደየሀገሩ ተጨባጭ ሁኔታ በሚደነገግ ሕግ መሰረት የህዝብ ተመራጮች፣ ተሿሚዎች እና/ ወይም የመንግስት ሠራተኞች የሀብትና የገንዘብ ጥቅሞቻቸውን (financial interest) የሚያሳውቁበትና የሚያስመዘግቡበት ሥርዓት ነው።

የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ሥርዓት እንደየሀገሩ ተጨባጭ ሁኔታ ምዝገባው በተወሰነ ጊዜ ወቅቱን ጠብቆ ዕድሳት የሚካሄድበት ሲሆን፣ ሀብታቸውን እንዲያሳውቁና እንዲያስመዘግቡ ግዴታ የሚጣልባቸው ሰዎችም የተለያዩ ናቸው። በምዝገባው የሚካተቱት የሀብት ዓይነቶች እና የገቢ ምንጮችም የየሀገራቱን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የሚከናወኑ በመሆኑ የተለያዩ ናቸው።

ሀብት ማሳወቅና ምዝገባ የተለያዩ ሀገራት ልምድ

በዓለማችን ቁጥራቸው ከ149 በላይ የሚሆኑ ሀገራት እንደየሀጋቸው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጨባጭ ሁኔታ የሀብት ማሳወቅና ምዝገባን በሕግ ደረጃ ደንግገውና የአፈፃፀም መመሪያ አውጥተው ህጉን ተግባራዊ በማድረግ የሥነ ምግባርና የፀረ-ሙስና ትግሉን የሚያግዝ አንድ ቁልፍ ተግባር አድርገውታል። እነዚህ ሀገራት በተለያዩ እርከን ላይ በሚገኙ የመንግስታዊና የህዝባዊ ድርጅቶች ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይ በማተኮር የሀብት ማሳወቅና ምዝገባን ያከናውናሉ። የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ አፈፃፀማቸውንም እንደየራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ በተለያየ መንገድ የሚያከናውኑ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ተሞክሮ የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ተግባር በአራት ዋና ዋና ዘዴዎች ሊከናወን እንደሚችል ያሳያል።

እነዚህም፡-

$1·         የመንግስት ባለሥልጣናትን ሀብት ብቻ የመመዝገብ ዘዴ፣

$1·         የመንግስት ባለሥልጣናትን እና ሁሉንም የመንግስት ሠራተኞች ሀብት የመመዝገብ ዘዴ፣

$1·         የመንግስት ባለሥልጣናትን፣ የመንግስት ሠራተኞችን እና የእነዚህን ቤተሰብ፣ የቅርብ ዘመዶችና ወዳጆች ሀብት የመመዝገብ ዘዴ እና

$1·         የሁሉንም ዜጎች ሃብት የመመዝገብ ዘዴ ናቸው።

የመንግስት ባለሥልጣናትን ሀብት ብቻ የመመዝገብ ዘዴ

የዚህ የምዝገባ ዘዴ መነሻው ከፍተኛና ወሳኝ የሆነ ውሳኔ የሚሰጠው የመንግስት ባለሥልጣን ስለሆነ መመዝገብ ያለበት የባለሥልጣን ሀብት እንጂ በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት አነስተኛ ወይም ምንም ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የማይችሉ ሌሎች ሠራተኞች ሀብት መሆን የለበትም በሚለው የመከራከሪያ ሃሳብ ላይ የተመሠረሰተ ነው። የዚህ ዘዴ ጠንካራ ጎኑ ምዝገባው ቁልፍ በሆኑ ውስን ሰዎች ላይ ብቻ የሚያተኩር በመሆኑ ከአሰራርም ሆነ ከውጪ አንፃር ተፈፃሚነቱ በአንፃራዊነት የተሻለ (manageable) መሆኑ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በመንግስት ባለሥልጣናት ላይ ብቻ የሚያተኩርና ሌላውን የመንግስት ሠራተኛ የሚያካትት የሀብት ምዝገባ ዘዴ መሆኑ በውሳኔ አሰጣጥ ረገድ ቀላል የማይባል ሚና ያላቸውንና በየደረጃው የሚገኙ ሠራተኞችን አለመሸፈኑ የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ዓላማዎችን ከማሳካት አንፃር ክፍተት እንዳለበት ይገልጻል። የዚህ ዓይነቱ የምዝገባ ዘዴ እንደ ጃፓን፣ ኒውዚላንድ እና አውስትራያ ባሉ ሀገራት ሥራ ላይ መዋሉ ዘዴው ያገኘውን ተቀባይነት መገመት የሚያስችል ነው።

የመንግስት ባለሥልጣናትን እና ሁሉንም የመንግስት ሠራተኞች ሀብት የመመዝገብ ዘዴ

ይህ ዓይነቱ የምዝገባ ዘዴ ሁሉም የመንግስት ባለሥልጣናት እና የመንግስት ሠራተኞች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ግዴታ የሚጥል ሲሆን መነሻውም ከላይ እስከታች የሚገኙት የመንግስት ባለሥልጣነትም ሆኑ የመንግስት ሠራተኞች ይነስም ይብዛ በመንግስት ሥልጣን የመጠቀም አጋጣሚ ስላላቸው ሁሉም ሀብታቸውን የማሳወቅና የማስመዝገብ ግዴታ ሊጣልባቸው ይገባል የሚል ነው።

የዚህ የአመዘጋገብ ዘዴ ጠንካራ ጎን ሁሉንም የመንግስት ባለሥልጣት እና የመንግስት ሠራተኞች የሚያጠቃልል ከመሆኑ አንጻር ሰፊ ሽፋን ያለው መሆን ሲሆን፣ ደካማ ጎኑ ደግሞ ምዝገባውና የመረጃ አያያዙ ሥራ ሰፊና አድካሚ፣ ከገንዘብና ከሰው ኃይል አንፃርም ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ እና ጊዜ ወሳጅ መሆኑ ነው። ይህ የምግዘባ ዘዴ በጥቂት አገሮች ለምሳሌ በፊሊፒንስና በላቲቪያ ስኬታማ ቢሆንም በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ግን ተሞክሮ ውጤታማ መሆን ያልቻለ ነው።

የመንግስት ባለሥልጣናትን፣ የመንግስት ሠራተኞችን እና የእነዚህን ቤተሰብ፣ የቅርብ ዘመዶችና ወዳጆች ሀብት የመመዝገብ ዘዴ

ይህ የምዝገባ ዘዴ በከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናትና የመንግስት ሠራተኞች ላይ ብቻ ሳይወሰን የእነሱ ቤተሰቦች፣ ዘመዶችና ወዳጆ ጭምር ሀብታቸውን የሚያስመዘግቡበት ነው። የዚህ ዘዴ ጠንካራ ጎኑ ምዝገባው በከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናትና የመንግስት ሠራተኞች ላይ ብቻ ሳይወሰን የእነሱ ቤተሰቦች፣ ዘመዶችና ወዳጆች ጭምር ሀብታቸውን የሚያስመዘግቡበት እንደመሆኑ ከቀደሙት ዘዴዎች ጋር ሲነፃፀር የተሻለና ሰፊ ሽፋን ያለው መሆኑ ነው። የዘዴውን ደካማ ጎን ስንመለከት ደግሞ የዘመድ አዝማድና የወዳጆችን ንብረት ሁሉ እንዲመዘገብ ማስገደድ የግል ነፃነትን የሚጋፉ ነው የሚል ክርክር የሚቀርብበት መሆኑ ነው። የመንግስት ባለሥልጣናትና ሠራተኞች ወዳጆችና ዘመዶች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ የሚጠየቁት ከባለስልጣቱ እና ከሠራተኞቹ ጋር ዝምድናና ወዳጅነት ስላላቸው እንደሆነ ግልፅ ነው። ይህንን ዝምድናና ወዳጅነት ብቻ መሰረት በማድረግ ይህን መሰሉን ግዴታ በሌሎች ወገኖች ላይ መጣል የለበትም የሚለው ክርክር ጠንካራ ነው። በተጨማሪም ዘዴው ከላይ ከተጠቀሱት ሁለት የምዝገባ ስልቶች የበለጠ ወጪ፣ ጊዜና አቅም የሚጠይቅ ነው። ይሁንና ከእነችግሩም ቢሆን እንደነፔሩ ያሉ የላቲን አሜሪካ ሀገራት ጥቅም ላይ እያዋሉት ይገኛል።

የሁሉንም ዜጋ ሃብት የመመዝገብ ዘዴ

የሁሉንም ዜጋ ሀብት የመመዝገብ ዘዴ ከዚህ በላይ ከተገለፁት ሶስት የምዝገባ ዘዴዎች አንፃር የላቀ ሽፋን የሚሰጥ ከመሆኑ አንፃር የሀብት ምዝገባን ዓላማ ለማሳካት የተሻለ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል። ይሁንና በመንግስታዊ ኃላፊነት ወይም ተቋም በምርጫ፤ በሹመት ወይም በቅጥር ላይ የማይገኙ ሰዎችን ሀብት ሁሉ ለመመዝገብ የሚሞክር ዘዴ እንደመሆኑ ምክንያታዊነቱ የላላ፣ ምዝገባው በፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ የመፈፀም ዕድሉ ጠባብ እንዲሁም አድካሚና አስተዳደራዊ ወጪውም ከፍተኛ መሆን የዚህ የምዝገባ ዘዴ ደካማ ጎኖች ተደርገው ይወሰዳሉ።

የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ጥቅሞች

የሀብት ማሳወቅና ማስመዝገብ ጥቅሞችን ከሚከተሉት ሶስት ዋና ዋና ሁኔታዎች አንጻር መመልከት ይቻላል፡-

$11.  ሙስናን አስቀድሞ ለመከላከል (preventive function)

$12.  የሙስና ወንጀልን ምርመራ ለማቀላጠፍ (investigative function)

$13.  የህዝብ አመኔታን ለመፍጠርና ለማጠናከር (Trust building functions) ናቸው።

ከላይ ከተቀመጡት ሶስት ዋና ዋና ጥቅሞች ባሻገር ሌሎች ዝርዝር ጥቅሞችንም ማየት ይቻላል። እነሱም፡-

$1·         ዜጎች የመንግስት ኃላፊዎችና ሠራተኞች ያላቸውን ሀብት ለማወቅ ስለሚያስችላቸው፣ በመንግስት አስተዳደር ላይ ያላቸው እምነት ይበልጥ ከፍ ይላል፣ ዜጎች በመንግስት ኃላፊዎችና ሠራተኞች የሀብትና የንብረት ይዞታ ላይ ሊያነሱ የሚችሉትን በማስረጃ ላይ ያልተደገፈ ጥርጣሬና ሃሜት ይቀንሳል፣ በዚህም የመንግስታዊ አገልግሎት ሰጪ አካላት ውጤታማነት እንዲጨምር ያግዛል፣

$1·         መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የራሱን አስተዋፅኦ ያደርጋል፣ ዜጎችና መንግስት በልማትና በሌሎች የመንግስት እቅዶችና ፕሮግራሞች ላይ የሚያደርጉትን ርብርብ በአንድ ልብ እንዲያከናውኑ አስተዋፅኦ ያደርጋል፤

$1·         ሙስናን ለመከላከልና ለመዋጋት በሚደረገው ርብርብ የማስረጃ ማሰባሰቡን ሂደት ለማቃለል ያግዛል፣

$1·         የፀረ-ሙስና ትግሉን ይበልጥ ለማጠናከር ይረዳል።

የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ በኢትዮጵያ

 የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የሀገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎችን ሥር ነቀል በሆነ ሁኔታ በመቀየር መልካም አስተዳደር የተረጋገጠበት እና ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት መንግስታዊ አሠራርን ለመዘርጋት የየራሳቸው አስተዋፅኦ ያላቸው በርካታ እርምጃዎችን እንደወሰደና አሁንም በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። ከእነዚህም መካከል የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮራሞችና የዚሁ አካል የሆኑ ንዑስ ፕሮግራም አንዱ ሲሆን በዚህ ንዑስ ፕሮግራም አማካኝነት ሀገራችን የተያያዘችው የልማት፣ የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ሥርዓደት ግንባታ በሙስናና በብልሹ አሰራር እንዳይደናቀፍ የፀረ-ሙስና ትግሉን በግንባር ቀደምትነት የሚያስተባብሩና የሚመሩ የፌዴራል እና የክልል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና አካላት መቋቋማቸው፣ ሙስናን በወንጀልነት የሚፈርጁ ህግጋት በወንጀል ሕጉ መደንገጋቸው እና የሙስና ልዩ ባህሪያትን መሰረት ያደረገ የፀረ-ሙስና ልዩ የሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ህግ መውጣቱ ከላይ የተጠቀሱት የማሻሻያ ፕሮግራሞች አካልና ውጤት ተደርገው ሊወሰዱ የሚችሉ ናቸው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀረ-ሙስና እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት የፀረ ሙስና መከላከያና መዋጊያ ስምምነቶች መጽደቅ ከላይ የተመለከቱት ጠንካራ የመንግስት አቋምና እርምጃዎች ተጨማሪ ማሳያዎች ናቸው።

መንግስት ከላይ በተዘረዘሩት ጥረቶቹ ብቻ ሳይወሰን የመንግስት አሠራርን በግልጽነትና በተጠያቂነት ላይ ለመመስረት፣ ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ እንዲሁም የመንግስት የሥራ ኃላፊነት እና የግል ጥቅሞች ሳይቀላቀሉ በየራሳቸው መንገድ የሚመሩበትን ግልጽ ሥርዓት በመዘርጋት ሊፈጠር የሚችለውን የጥቅም ግጭት ለማስወገድ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞድራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 55(1) መሠረት የሀብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ አዋጅ ቁጥር 668/2002 ሆኖ ሚያዚያ 4 ቀን 2002 ዓ.ም አውጥቷል።

የሀገራችን የሀብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ ሕግ የተዘጋውም ከላይ በዝርዝር ያየናቸውን የሌሎች አገሮች የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ተሞክሮዎች እንዲሁም የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ በማገናዘብ ነው። ሕጉ የተሟላ ይሆን ዘንድም በዝግጅት ወቅት የውጪ አማካሪዎች በጥናት እንዲሳተፉ ከመደረጉም በላይ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲተችና እንዲዳብር ተደርጓል።

የሀገራችን የሀብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ አዋጅ ሕጋዊ መሰረቶች

 በአገራችን የተደነገገውን የሀብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ አዋጅ ቁጥር 668/2002 ከሕግ አንፃር ያሉትን ሕጋዊ መሰረቶች ስንመለከት በዋነኛነት ተጠቃሽ የሚሆኑት፡-

$1·         በ1987 የወጣው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 12

$1·         በ1997 የተሻሻለው የፌዴራል የስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 433/1997፤

$1·         ኢትዮጵያ ተቀብላ ያፀደቀቻቸው የተባበሩት መንግስታት የፀረ-ሙስና ኮንቬንሽን እና የአፍሪካ ሕብረት የሙስና መከላከያና መዋጊያ ኮንቬንሽን እና

$1·         በ1996 ዓ.ም የወጣው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ሕግ ናቸው።

እነዚህን ዘርዘር አድርገን ስንመለከትም፡-

$11.  የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግስት አንቀጽ 12 የመንግሥት አሰራር ግልጽነትና ተጠያቂነትን በሚመለከት እንደመርህ የሚወሰድ ድንጋጌ ነው። መርሁ ግልጽነትና ተጠያቂነትን የሚያካትት ሲሆን የመልካም አስተዳደርም የማዕዘን ድንጋይ ነው። የግልጽነትና የተጠያቂነት አሠራር የመንግስት ሥራ በግልጽ ሕግ እና የአሰራር ሥርዓት ላይ ተመሥርቶ ማከናወንን፤ የግል ጥቅምን ከሕዝብ ጥቅም ጋር አለማደባለቅን፤ በህጋዊ ሥልጣ ብቻ መገልገልን እና እናዚህ በተጓደሉ ጊዜ ተጠያቂነት ማስከተሉን ይጨምራል። በዚህ መሰረት የመንግስት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት የሚለው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 12(1) አንዱ የሀብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ አዋጅ ሕጋዊ መሰረት ነው።

$12.  በተሻሻለው የፌዴራል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 433/1997 አንቀጽ 7(7) የመንግስት ባለሥልጣናትና በሕግ ሀብታቸውንና የገንዘብ ጥቅሞቻቸውን እንዲያስመዘግቡ ግዴታ የተጣለባቸውን የመንግስት ሠራተኞች ሀብትና የገንዘብ ጥቅሞች መዝግቦ የመያዝ ወይም ተመዝግበው እንዲያዙ የማድረግ ኃላፊነት ለኮሚሽኑ ተሰጥቶታል። ይህም ለአዋጁ መውጣት ሌላው ሕጋዊ መሰረት ነው።

$13.  አገራችን ያጸደቀቻቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀረ-ሙስና ኮንቬንሽን እና የአፍሪካ ሕብረት የሙስና መከላከያና መዋጊያ ኮንቬንሽኖችም እንደ ቅድም ተከተላቸው በአንቀጽ 8 እና 7 አባል ሀገራት በአገሮቻቸው ሕግ መሠረት የመንግስት ባለሥልጣናትን የሀብትና የገንዘብ ጥቅም ምዝገባ እንዲያከናውን ደንግገዋል። በተጨማሪ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 9(4) መሠረት ኢትዮጵያ የጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምነቶች የኢትዮጵያ ህግ አካል እንደመሆናቸው ሀገሪቱ ከላይ የተጠቀሱትን የፀረ-ሙስና ስምምነቶች ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል። ሀገራችን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እና የአፍሪካ ሕብረት ግንባር ቀደም መሥራችና መቀመጫ እንደመሆኗ እንደ አባል አገር በግል ድንጋጌዎቹን ሥራ ላይ ከማዋል በተጨማሪ ኮንቬንሽኖቹን በመተግበር በኩል ከፍተኛ የአርአያነት ሚና መጫወት ይጠበቅባታል።

$14.  ሌላው ለሀብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ አዋጅ ሕጋዊ መሰረት የሚሆነው በ1996 ዓ.ም ተሻሽሎ የወጣው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ ውስጥ የተካተቱት ድንጋጌዎች ሲሆኑ እነሱም፡-

$1-    ሀብትና ንብረቱን የማስመዝገብ ኃላፊነት ያለበት ሰው ንብረቱን፣ የፋይናንስ አቋሙን ወይም ስጦታ መቀበሉን ሳያስመዘግብ ቢቀር እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ቅጣት እንደሚቀጣ በወንጀል ሕጋችን አንቀጽ 417/2/ መደንገጉ፤

$1-    ገንዘቡን ወይም ሀብቱን ያገኘው በህጋዊ መንገድ መሆኑን ማስረዳት ያልቻለ የንብረቱ መወረስ እንደተጠበቀ ሆኖ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚቀጣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 419 መደንገጉ፤

$1-    ንብረቱን እንዲያስመዘግብ በሕግ ግዴታ የተጣለበት ሰው ንብረቱን በሌላ ሰው ስም ማለትም በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይን ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ቢያቀርብ ደግሞ በወንጀል ህጋችን አንቀጽ 684 መሠረት እንደሚቀጣ መደንገጉ ናቸው።

ምዝገባ የሚመለከተው ሰው ሀብቱን በሌላ ሰው ስም ሲያስመዘግብ ወይም በተለያዩ ምክንያቶች ላያስመዘግብ የሚችልባቸውን አጋሚዎች በማሰብ የህጉን ውጤታማነት የሚጠራጠሩ ወገኖች አሉ። እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው ነገር ማንኛውም ወንጀል ተፈፅሞ ወንጀሉ መፈፀሙ ሳይታወቅ ወይም ወንጀሉ መፈጸሙ ታውቆም ወንጀለኛው ሳይታወቅ በተለያዩ ምክንያቶች የሚቀርበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። በተመሳሳይ ሁኔታ ሀብት የማሳወቅና የማስመዝገብ ግዴታ የተጣለበት ሰውም ሀብቱንና የገቢ ምንጮቹን ሳያስመዘግብ የሚቀርበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። ይሁንና መታየት ያበት ዋናው ነገር የህግ ማዕቀፍ መፈጠሩ፣ የሥርዓቱ መዘርጋትና አብዛኛው ሰው ወደ ሥርዓቱ የሚገባበት ሁኔታ መመቻቸቱ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በአፈፃፀም ረገድ የሚታዩ ተግዳሮቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀረፉ እንደሚሄዱ እና አፈፃፀሙን የሚፈታተኑ ወገኖች ቢኖሩ እንኳን ቁጥራቸው እየተመናመነ እንደሚሄድ ታሳቢ ማድረግ ተገቢ ነው።

በአጠቃላይ የህጉ መውጣት ከላይ የተዘረዘሩት የተመቻቹ ሕጋዊ መሰረቶች ስላሉት ሀብታቸውን ማስመዝገብ የሚገባቸው ሰዎች ሳያስመዘግቡ ሊቀሩ የሚችሉበት ዕድል መኖር የህጉን መውጣት አስፈላጊነት የሚቀንሰው አይሆንም።

የኢትዮጵያ የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ሕግ አዘገጃጀት

በቀዳሚዎቹ ክፍሎች በአገራችን የሀብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ ሕግን ለመደንገግ ሕጋዊ መሰረቶች መኖራቸውን፣ ሕጉም ሙስናን አስቀድሞ ለመከላከል፣ የሙስና ወንጀል ምርመራን ለማቀላጠፍና የህዝብ አመኔታን እንደሁኔታው ለመፍጠርና ለማጠናከር እንደሚረዳ እንዲሁም እያንዳንዱ አገር ከራሱ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ይበልጥ ዓላማዬን ያሳካልኛል ያለውን የሀብት ማሳወቂያና ማስመዝቢያ ዘዴ እየመረጠ ተግባራዊ በማድረግ ዓለም አቀፍና አካባቢያዊ ስምምነቶችን ሥራ ላይ ለማዋል ጠቀሜታ እንዳለው ለማብራራት ተሞክሯል። ከዚህ አንፃር ለሀገራችን የተሻለው የሀብት ምዝገባ ዘዴ የትኛው ነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በቅድመ ዝግጅት ወቅት ስለተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትና በፖሊሲ አቅጣጫዎች ላይ አጠር ያለ ማብራሪያ መስጠቱ ተገቢ ይሆናል።

ሕጉ ከመርቀቁ በፊት የሌሎች ሀገሮችን ተሞክሮ መሠረት በማድረግና የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት የምዝባው ህግና የሚዘረጋው ሥርዓት የሚመሰረትበትን የፖሊሲ አቅጣጫ በግልጽ ለማወቅ ቀደም ሲል የተጠቀሱት አማራጮች በኮሚሽኑ አማካኝነት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እንዲቀርቡ ተደርጓል። የእያንዳንዱን አማራጭ ጠንካራና ደካማ ጎኖች፣ የተሻለ የተባውን አማራጭ ጭምር በያዘው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ቀጥሎ የተመለከተው የፖሊዲ አቅጣጫ የተሰጠ ሲሆን ውሳኔው የሚረቀቀውን ህግ ይዘት በመወሰን ረገድ ጉልህ ድርሻ ነበረው።

$1·         መንግስት የህዝብ ተመራጮችና የመንግሥት ተሿሚዎች ሁሉ ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ፤ በዚህም የግልጸኝነት እና የተጠያቂነት አሰራር እንዲኖር፣ ለዚህም የሚረዳ ሥርዓት እንዲዘረጋ የማያወላውል ቁርጠኛ አቋም ያለው መሆኑ፣

$1·         የሚዘረጋው የሀብት ምዝገባ ሥርዓት ሙስናን በመከላከል ረገድ ሊያበረክት የሚችለው የመንግስት ሠራተኛውንም ጭምር የሚያካትትበት አግባብ እንዲኖር፣

$1·         የህዝቡን ተሳታፊነትና ባለቤትነት ለማረጋገጥ የሀብት ማሳወቅ እና ምዝገባ መረጃ ያለአንዳች ገደብ ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን መፈለጉ ናቸው።

የሀገራችን የሀብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ ሕግ ሲቀረጽ ከላይ በተዘረዘሩት የፖሊሲ አቅጣጫዎች ላይ በመመስረት ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ለማጣጣም ጥረት ተደርጓል። እያንዳንዱ አገር እንደየራሱ ሁኔታ ችግሬን ይበልጥ ይፈታልኛል በሚለው የራሱ መንገድ የሀብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ ሕግ ተግባራዊ የሚያደርግ ቢሆንም በበርካታ አገሮች ያለው የሀብት ምዝገባ ለሚከተሉት ዋና ዋና ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ይሞክራል። በሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ረገድ አንዱ አገር ከሌላው አገር የሚመሳሰልበት ወይም የሚለይበት ምክንያትም በአንድ መልኩ ወይም በሌላ ለእነዚህ ጥያቄዎች በሚሰጥ መልስ ላይ የተመሠረተ ነው። ይህም፡-

$1·         ሀብታቸውን ማሳወቅና ማስመዝገብ ያለባቸው እነማን ናቸው?

$1·         የሚመዘገበው ሀብት የትኛው ነው?

$1·         በመዝገብ የተያዘው መረጃ ለሕዝብ በምን ዓይነት ሁኔታ ይገለፃል?

$1·         ምዝገባ መካሄድ ያለበት መቼና በምን ያህል ድግግሞሽ ነው?

$1·         ሀብትን ያለማስመዝገብ ምን ምን ቅጣቶችን ያስከትላል?

የመጀመሪያው የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ረቂቅ ሕግ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ከመላክ በፊት በተለያዩ መድረኮች ለመንግስት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ተወካዮች፣ ለክልል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ተወካዮች፣ ለወጣቶችና ለሴቶች ተወካዮች፣ ለሚዲያ ተቋማሰት፣ ለሲቪል ማህበረሰብና ለሃይማኖት ተቋማሰት ተወካዮች ረቂቅ ሕጉ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ከየመድረኮቹ በተገኙ ግብዓቶችም ረቂቅ ሕጉን ይበልጥ ለማዳበር ተችሏል። ረቂቅ ሕጉ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተደግፎ ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከቀረበ በኋላም ምክር ቤቱ በጠራው የህዝብ ማሳተፊያ መድረክ /Public Hearing/ ላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ያነሷቸው በርካታ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ረቂቁን ይበልጥ በማዳበር ረገድ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል።

­­

የኢትዮጵያ ሀብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ አዋጅ ይዘት

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዚያ 4 ቀን 2002 ዓ.ም ያፀደቀው የሀብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ አዋጅ ቁጥር 668/2002 በአራት ክፍሎች፣ በ25 አንቀጾችና በ50 ንዑስ አንቀጾች የተደራጀ ነው። ይኸውም፡-

መግቢያው ሀብትን ለማሳወቅና ለማስመዝገብ የወጣው አዋጅ ሊያስፈፅም የፈለገውን ዓላማና የሕገ መንግስቱን አንቀጽ 55(1) መሠረት በማድረግ መታወጁን ይገልጻል።

ክፍል አንድ፡-

ጠቅላላ ድንጋጌዎችን ያቀፈ ሆኖ የአዋጁን አጭር ርዕስ፣ በአዋጁ ውስጥ ጥቅም ላይ ከዋሉት ውስጥ አሻሚ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የተለዩ ቃላት ትርጓሜንና የአዋጁን የተፈፃሚነት ወሰን ይዟል።

$1·         የተፈፃሚነት ወሰንን በሚመለከት አዋጁ በፌዴራል መንግሥት፣ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች አስተዳደር ተሿሚዎች፣ ተመራጮችና የመንግስት ሠራተኞች ላይ ተፈፃሚ የሚሆን ነው፤

$1·         አዋጁ ትርጓሜ በሚለው አንቀጽ 2/4/ በተሿሚነት የዘረዘራቸው፤

$1-    የሪፐብሊኩን ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ ሚኒስትሮችን፣ ሚኒስትር ዴኤታዎችን፣ ምክትል ሚኒስትሮችን፣ ኮሚሽነሮችን፣ ምክትል ኮሚሽነሮችን፣ ዋና ዳይሬክተሮችንና ምክትል ዋና ዳይሬክተሮችን፣

$1-    የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞች አስተዳደሮች ከንቲባዎችንና ሌሎች ተሿሚዎችን፣

$1-    የመደበኛና የከተማ ነክ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንቶችን፣ ምክትል ፕሬዝዳንቶችንና ዳኞችን፤

$1-    የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ ተሿሚዎችን፤

$1-    አምባሳደሮችን፣ የቆንስላዎችና የሌሎች የዲፕሎማቲክ ሚሲዮን ኃላፊዎችን፤

$1-    ዋና ኦዲተርንና ምክትል ዋና ኦዲተርን፤

$1-    የብሔራዊ ባንክ ገዥና ምክትል ገዢን፤

$1-    የመንግሥት የልማት ድርጅት የሥራ አመራር ቦርድ አባላትን፣ ሥራ አስኪያጆችንና ምክትል ሥራ አስኪያጆችን፤

$1-    የመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች ፕሬዝዳንቶችንና ምክትል ፕሬዝዳቶች ናቸው።

የአዋጁን አንቀጽ 2/4/ /ለ/ እና /መ/ን በቅርበት ስናነብ የተሿሚዎች ዝርዝር በዚህ ሳይወሰን የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከንቲባዎችና ሌሎች ተሿሚዎች፣ እደዚሁም የመከላከያና የፖሊስ ተሿሚዎችን ይጨምራል። ይሁንና አዋጁ የድሬዳዋና የአዲስ አበባ ሌሎች ተሿሚዎች እነማን እንደሆኑ ያልዘረዘረ ወይም ያላመለከተ ሲሆን የመከላከያና የፖሊስ ተሿሚዎችንም በተመሳሳይ መንገድ ሳይዘረዝር ቀርቷል። ታዲያ አዋጁ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ፣ የመከላከያና የፖሊስ ተሿሚዎችን በዝርዝር ባለማመልከቱ እነዚህ ተሿሚዎች እነማን እንደሆኑ በምን ዓይነት መንገድ መለየት ይቻላል?

የሀብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ ሕግ ረቂቅ ላይ ግብዓት ለማሰባሰብ በተጠሩ መድረኮችና አዋጁ ከጸደቀ በኋላ አዋጁን ለማስረጽ በተዘጋጁ የውይይት መድረኮች ተመሳሳይ ጥያቄዎች ተነስተው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል። እጅግ ጠቃሚ ግባቶችም ተገኝተዋል። ተሿሚዎችንና ተሿሚ ያልሆኑትን ለመለየት ከሚያስችሉተ መስፈርቶች ቀዳሚ የሚሆነው የፌዴራል መንግስት ተሿሚዎችን ከሌሎች ተሿሚዎች ለመለየት የተደነገገ የህግ ማዕቀፍ መኖር ነው። ይሁንና ይህ ሕግ በተሟላ ሁኔታ ስለሌለ ይህ የመፍትሄ አቅጣጫ በራሱ ምሉዕ ሊሆን አልቻለም። በዚህም ምክንያት ክፍተቱን ለሙላት የአዲስ አበባና የድሬዳዋ አስተዳደሮች በራሳቸው ሕግ ወይም አሠራር በተሿሚነት የለዩአቸውን መውሰድ የተሻለው አማራጭ ሆኗል። የመከላከያንና የፖሊስ ተሿሚዎችንም በተመሳሳይ መንገድ የየተቋማቱን ደንብ፣ መመሪያ ወይም አሰራር እንደመነሻ በመውሰድ ተሿሚዎችን ተሿሚ ካልሆኑት ለመለየት ይቻላል። ስለዚህ የሀብት ማሳወቅደና ምዝገባ አዋጅ በትርጉም ክፍሉ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን እንደዚሁም የመከላከያና የፖሊስ ተሿሚዎችን ለመለየት የማይቻል አላደረገውም።

የመንግስት ሠራተኞችን በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 668/2002 አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 6 ከ‘ሀ’ - ‘ሐ’ የተጠቀሱት በግልጽ የተመላከቱ በመሆናቸው እንዳለ ተወስደዋል። ነገር ግን ኮሚሽኑ ሌሎች ሀብት የሚያስመዘግቡ ሰራተኞችን እንዲለይ በሚፈቅደው በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 6/‘መ’ መሰረት ቀጥታ ውሳኔ የሚሰጡ፤ በውሳኔ ላይ ተፅዕኖ ማሳረፍ የሚችሉ ወይም ውሳኔ የማይሰጡ ቢሆንም ከሥራቸው ወይም ከሙያቸው አንጻር ለጥቅም ግጭት በሚያጋልጥ የሥራ መስክ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች በሀብት አስመዝጋቢዎች ዝርዝር ውስጥ እንዲካተቱ ተደርጓል።

ክፍል ሁለት፣

ይህ ክፍል የአዋጁን ዋና ዋና ጉዳዮች አካቶ የያዘ ሲሆን በዝርዝር ሲታይ የሀብት ምዝገባው የሚመለከተው ማንን እንደሆነ፤ ምዝገባው የሚያካትተውን ሀብት፣ ምዝገባውን ስለሚያስፈፅመው የመንግስ አካል፣ ስለምዝገባ ወቅት፣ በምዝገባ ሥርዓት ውስጥ የገባ አስመዝጋቢ ግዴታዎች፣ የምዝገባን ትክክለኛነት ስለማረጋገጥ፣ ስለምዝገባ መረጃ ተደራሽነትና ሀብትን አለማስመዝገብ የሚያስከትለውን ተጠያቂነት የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን ይዟል።

ክፍል ሶስት፤

የጥቅም ግጭትን ስለማሳወቅ የተደነገጉ ድንጋጌዎችን የያዘ ሲሆን ስጦታን፣ መስተንግዶንና የጉዞ ግብዣን የሚመለከቱ ሁኔታዎችን፣ የጥቅም ግጭትን ለማስወገድ መውሰድ ስላለበት እርምጃ፣ የጥቅም ግጭት ከተከሰተ በኋላ ስለሚወሰድ እርምጃና የጥቅም ግጭትን ያለማሳወቅ ስለሚያስከትለው ውጤት የሚዘረዝር ነው።

ክፍል አራት፤

ይህ የአዋጁ የመጨረሻ ክፍል ሲሆን ጥቆማን፣ የአዋጁን ተፈፃሚነት ማረጋገጥን፣ ቅጣትን፣ ተፈፃሚነት የማይኖራቸው ሕጎችን፣ ደንብና መመሪያ የማውጣት ስልጣንና አዋጁ የሚፀናበትን ጊዜ የተመለከቱ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን የያዘ ነው።  

ምንጭ፡- የፌዴራል የስነምግባርና የጸረ ሙስና ኮምሽን

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
522 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 123 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us