አል-አሙዲ ወልድያ ላይ ታሪክ ሰሩ

Wednesday, 01 February 2017 14:11

በማዕረጉ በዛብህ

እያንዳንዱ አካባቢ፣ ገጠር፣ ከተማም ሆነ ጠቅላላው አገር በደስታም ሆነ በሐዘን የሚያስታውሳቸው ታሪካዊ ዕለታት አሉት። የ232 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ ለሆነችው ወልድያ ጥር 6 ቀን 2009 ዓ.ም አዲስ የታሪክ ሐውልት የተገነባበት ቀን ነው ሊባል ይችላል። መላው የወልድያና የአካባቢው ሕዝብ በታላቅ ጉጉት ይጠብቀው የነበረው የ“ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ስታድየምና ሁለገብ የስፖርት ማዕከል” እጅግ በጣም በደመቀ ሥነ-ሥርዓት ተመርቆ ለባለቤቱ ለወልድያ ከተማ ሕዝብ የተበረከተበት ዕለት ጥር 6 ቀን 2009 ዓ.ም ነው። ይህንን የስታዲየሙን ምርቃትና ርክክብ በዓል ታሪካዊ የሚያደርጉት ምክንያቶች ብዙ ናቸው።

ከታሪክ አንፃር ሲታይ ከጥቂት አስርት ዓመታት በፊት በዚህችው ከተማ በጨርቅ ኳስ ይጫወቱ በነበሩት የዛሬው ብቸኛ ኢትዮጵያዊ ቢሊየነር በሆኑት በሼህ አል-አሙዲና በአብሮአደግ ጓደኛቸው በዶ/ር አረጋ ይርዳው የገንዘብና የዕውቀት ቅንጅት የተሰራው ዘመናዊ ስታዲየም ለወልድያ ከተማ መሰጠቱ የከተማውን ሁለተኛ የዕድገት ታሪክ ምዕራፍ የከፈተ ዕለት ሆኖ መታየት አለበት፤ ምክንያቱም የስታዲየሙ መኖር ሌሎች ዘመናዊ የዕድገት ተቋማት እንዲቋቋሙ የሚገፋፋ ነው። ስታዲየሙ ካለው ተጨባጭ የአገልግሎት ጠቀሜታ በላይ መጭውን ብሩህ የዕድገት ተስፋ ዘመን የሚያንፀባርቅ ነው።

ስታዲየሙ ከሚገኝበት አካባቢ አንፃር ንብረትነቱ የወልድያ ከተማ ቢሆንም ጠቃሚነቱ በአጠቃላይ ለአገሪትዋና ከዚያም አልፎ ለቅርብ የጐረቤት አገሮችም አገልግሎት ሊሰጥ ይችላል። ስታዲየሙን በሚገባ በጥቅም ላይ ለማዋል የአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ውድድሮችንም የሚያስተናግድ መሆን አለበት። ያ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ወልድያን ከአዲስ አበባና ከሌሎች የቅርብ ጐረቤት አገሮች ጋር የሚያገናኛቸው የአውሮፕላን ማረፊያና በቂ ዘመናዊ ሆቴሎች ሲኖሩዋት ነው። ስለሆነም የሚቀጥለው የወልድያ ልጆች፣ የክልሉ የአስተዳደሩ አመራር አባሎችና በተለይም የከተዋ ነዋሪዎች የቤት ስራ እነኚህን ዕቅዶች የሚያካትት መሆን ይኖርበታል።

ለምረቃው በዓል በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ የተዘጋጀው መጽሔት እንደገለፀው ወልድያ የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያላት ከመሆንዋም በላይ “ሰፋፊ ኢንዱስትሪዎችን ሊያንቀሳቀስ የሚችል” ኃይልና የ24 ሰዓት የውሃ አገልግሎት እንደምታገኝ ታውቋል። የእነኚህ አገልግሎቶች መኖር ከተማዋ ብዙ ተጨማሪ የእድገት ስራዎችን ልታስተናግድ መቻልዋን የሚያመለክት ነው።

በሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ሙሉ ወጪ የተገነባው የወልድያው ስታዲየምና የስፖርት ማዕከል 567,890,000 ብር የወጣበት ሲሆን፤ ከፊፋ የሚጠበቁትን አገልግሎቶች ሁሉ ያካተተ ነው። ስታዲየሙ 25,000 ተመልካቾችን በአንድ ጊዜ ሊያስተናግድ የሚችል፣ የውጤት መግለጫ ቦርዶች፣ የኦድዮ መሣሪያዎችና ዙሪያውን ከዝናብና ከፀሐይ ሙቀት መከላከያ ክፈፎች የተገጠሙለት፣ በዘመናዊነቱ በአገራችን ተወዳዳሪ የሌለው፣ በውበቱ ተመልካችን የሚያስደምም ነው።

የስፖርት ማዕከሉን ዝርዝር መግለጫ በተመለከተ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ያዘጋጀው መጽሐፍ-አከል መጽሔት እንደገለፀው፤ ስታዲየሙ ከፍተኛ ኃይል ያላቸው መብራቶች የተገጠሙለት፣ ቀንና ማታ፣ በጋና ክረምት ሊያጫውት የሚችል፣ ለክብር እንግዶች የመዝናኛ፣ ለስፖርት ጋዜጠኞች ዜና ማስተላለፊያ ቢሮዎችና የተሟላ የኢንተርኔት አገለግሎት ያለው ነው። ከዚያም በላይ አራት ቡድኖች በአንድ ጊዜ የሚስተናገድበት የገላ መታጠቢያና፣ የመፀዳጃ ክፍሎች፣ የህክምና፣ የአስተዳደር ቢሮዎችና የመሰብሰቢያ አዳራሽ የያዘ ነው። በአጠቃላይ የስፖርት መወዳደሪያ ተቋማትን በተመለከተ፣ እጅግ የተዋበ የቴኒስ ሜዳና የመዋኛ ገንዳ፣ የቅርጫት፣ የመረብና የዕጅ ኳስ መጫወቻዎች፣ የመብራት፣ የውሃና የቴሌፎን ሲስተሞች የተዘረጉበት በጣም ዘመናዊ ተቋም ነው።

ሌላው የስታዲየሙን ምረቃ በዓል ታሪካዊ ያደረገው ምክንያት የምረቃው ሥነ-ሥርዓት በአገሪትዋ ጠቅላይ ሚኒስትር መከናወኑ ሲሆን፤ ድርጊቱ ኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ ከፍተኛ መዋዕለንዋይ በመመደብ የአገራቸውን ልማት በመደገፍ ላይ የሚገኙትን ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲን ለማመስገንና ለማክበር መልካም አጋጣሚ ከመሆኑም በላይ ስታዲየሙ በአጠቃላይ ለአገሪቱ የሚኖረውን ጠቀሜታም የሚጠቁም ነው።

ስታዲየሙ ከምኞት ወደ ተጨባጭ የአንድ የታሪክ ወቅት ትልቅ የድርጊት አሻራ ሆኖ መቻሬ ሜዳ ላይ ሊሰራ የቻለው የግንባታውን 600 ሚሊዮን የሚጠጋውን ወጭ መጠነ-ሰፊ በሆነው ደግነታቸው በለገሱት በሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ልግስናና ስራውን ከጽንሰ ሃሳብነት እስከ ፍፃሜው ድረስ ሙያዊ እውቀት ከተላበሰ አመራር እስከ ዝርዝር የሥራ ተሳትፎና ቁጥጥር ድረስ በቆራጥነት በመከታተል ኃላፊነታቸውን በተወጡት በዶ/ር አረጋ ይርዳው ነው። የእነኝህ ወልድያ ከተማ ላይ በአንድ ትምህርት ቤት በራድ ሻይና ፓስቲ እየተካፈሉ ያደጉ ሁለት ሰዎች ዛሬ በመቶ ሚሊዮኖች የሚካሄዱ ስራዎችን አብረው በመስራት ያስመዘገቡዋቸው የስራ ውጤቶችና የመተማመን ባህሪ ለሌሎች ትምህርት የሚሆን ነው። አንደኛው ለሌላው ያለውን ፍቅርና አክብሮት እንደሚከተለው ሲገልፁት ይሰማል።

“ይህን ስታዲየም ተገንብቶ በማየቴ ከልቤ ተደስቻለሁ። ስታዲየሙን በዚህ መልክ ሳይ በርግጥም ግንባታውን እንዲያስፈጽም ኃላፊነት የሰጠሁት ጓደኛዬና አብሮ አደጌ ዶ/ር አረጋ ይርዳውን ኮርቼበታለሁ”

ሼህ አል-አሙዲ [የሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ስጦታ ላሳደገች እናት አገር]

ከሚለው መጽሔት።

 

የወልድያ ሕዝብ ደግሞ ያለችውን ጥሪት አሟጦ ሁለገብ የስፖርት ማዕከሉን ለማስገንባት ዘራ፣ የዘራውን ዘር ፍሬ አፍርቶ ማየት ናፈቀ። በዚህ ጊዜ ነበር የቁርጥ ቀን ልጅ ያስፈለጉት። ምን ጊዜም ቃልህን የማታጥፈው ወንድሜ ሼህ መሐመድ እንዲገነባ በማድረግ ኮርቼብሃለሁ

ዶ/ር አረጋ ይርዳው፤ [ከላይ ከተጠቀሰው መጽሔት]

 

ሌላው ሁለቱ የወልድያ ልጆች አንድ የሚያደርጋቸው ለዚያች ዕድለኛ ከተማ ያላቸው የፍቅር ትዝታ ነው።

“በወልድያ ከተማ በስሜ የሚጠራው ስታዲየም ለኔ ልዩ ትርጉም አለው። ወልድያ ያደኩባት፣ የተማርኩባት፣ የምወዳቸውን ጓደኞቼን ያፈራሁባት፣ በኢትዮጵያዊነት ባህልና ወግ የታነጽኩባት፣ የልጅነቴ አሻራ ያረፈባት፣ ምንጊዜም ልረሳት፣ ልዘነጋት የማልችል ከተማ ነች።”

ሼህ አል-አሙዲ አሁንም [የሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ስጦታ ላሳደገች እናት አገር]

ከሚለው መጽሔት።

 

ዶ/ር አረጋ ደግሞ እንዲህ ይላሉ፤ “ወልድያ ሕዝቦችን ሊያስተሳስር የሚችል ልዩ ባህል የሚነደፍባት፣ ፍቅር ሆና ፍቅርን የምታካፍል የቆነጃጅት ከተማ ነች። በአጭሩ ወልድያ ለእኔ ፍቅር ናት።”

(ተምሳሌት ልዩ እትም፣ 2009)

 

የስታዲየሙን ግንባታ ተደናቂ ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ ከአንዳንድ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት እንደ መብራት፣ የመሮጫ ወለል፣ የሳውንድ ሲስተም በስተቀር በአጠቃላይ አገር ውስጥ በተመረቱና በሚገኙ የግንባታ ዕቃዎችና በኢትዮጵያውያን መሐንዲሶችና የግንባታ ጠበብት ባለሙያዎች መሠራቱ ነው። የግንባታውን ሥራ በኅብረት ያከናወኑት ሁዳ ሪል ስቴት፣ ኮምቦልቻ የብረታ ብረት ምርቶች ኢንዱስትሪ፣ ዘመናዊ የሕንፃ ኢንዱስትሪ፣ አዲስ ጋዝና ፕላስቲክ ፋብሪካ፣ ዋንዛ ፈርኒሺንግ ኢንዱስትሪ፣ ቪዥን አልሙኒየም ማኑፋክቸሪንግ፣ አደጐ ሚድሮክ ትሬዲንግ፣ ሚድሮክ ሲኢኦ ማኔጅመንት እና አመራር አገልግሎት፣ ዩናይትድ የአውቶሞቢል ጥገና አገልግሎትና ሚድሮክ ጂኢኦ እና ኤክስፕሎሬሽን አገልግሎት የተባሉት የሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ንብረት የሆነው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች ናቸው። ለስራው ከፍተኛ አመራር በመስጠትና የቅርብ ቁጥጥር በማድረግ ለስኬት ያበቁት ዶ/ር አረጋ ይርዳው፣ የሚድሮክ የቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚና የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ናቸው።

ስታዲየሙ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች መሠራቱ የኢትዮጵያን የግንባታ ምሕንድስና ጥበብ ስራና ልምድ ዕድገት የሚያበስር ሲሆን፤ ለወደፊት ለሚሰሩ ተመሣሣይ የግንባታ ሥራዎች አገሪትዋ የራስዋን አስተማማኝ ባለሙያዎች ያፈራች መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

“የሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ስታዲየም እና የስፖርት ማዕከል” ምረቃ በዓል የሎጅስቲኩ ዝግጅትና ስፋት በጣም የሚደነቅ ድርጊት ነበር። ለበዓሉ የተጋበዘው እንግዳ በተወሰነ ቁጥር የተያዘ ሰው ሳይሆን ሕዝብ ነበር ማለት ይቀላል። ለአምስትና ለአራት ቀናት ያን ሁሉ ሕዝብ ቁርስ፣ ምሳ፣ ራት አብልቶና አጠጥቶ፣ ለእያንዳንዱ ሰው የስፖንጅ ፍራሽና የአየር አልጋ ሰጥቶ፣ መፀዳጃ ቤት አዘጋጅቶ ማስተናገድ ምን ያህል ወጭ እንደሚጠይቅና ሥራው ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ፍርድ ለአንባቢ የሚተው ነው።

“የልማት አርበኛ” በተባለው መጽሔት እንደተገለፀው ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ በእናት አገራቸው በኢትዮጵያ ባፈሰሱት መጠነ ሰፊ መዋዕለንዋይ ከ70 በላይ ድርጅቶችን በማቋቋም እስከ 40ሺህ ለሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። በመቀሌና ለቀምት ለሚገኙት ስታዲየሞች ግንባታ ከፍተኛ ገንዘብ ከመለገሳቸው በላይ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር 274 ሚሊዮን ብር፣ በሰሜን አሜሪካ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ረድተዋል። (የልማት አርበኛ 2006)

ይህችን አጭር የትዝታ ማስታወሻ ጽሁፍ ዶ/ር አረጋ ሼህ አል-አሙዲንን በመረቁበት የወሎ ባህላዊ የአነጋገር ዘይቤ እደመድማለሁ። “አቦ ይባርክህ!!”¾

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
526 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 129 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us