የ2ሺህ 200 ማስታወሻ

Wednesday, 08 February 2017 15:10

በይርጋ አበበ

ኢትዮጵያ ረጅም ዘመን የተሻገረ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ረጅም ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የመሬት ስፋት ያላት ግዙፍ እና ባለክብር አገር ነች። ይህች የአፍሪካ ኩራት የሆነች አገር ፈጣሪ ካጎናጸፋት የመሬት ስፋት በተጨማሪ ቁጥር ስፍር የሌላቸው የተፈጥሮ ሀብቶችና መስህቦችን አድሏታል። የዜና ዘጋቢዎች ሁለት የተለያዩ ሀሳቦችን በአንድ ላይ አጋብተው ሊዘግቡ ሲያምራቸው “በሌላ ዜና” ብለው ከመጀመሪያው ተቃራኒ የሆነ ሃሳብ ይዘግባሉ። እኔም የሙያ አጋሮቼን ባህሪ ተጋርቼ ቀደም ሲል ከገለጽኩት የተለየ ሀሳብ ላቅርብ። ኢትዮጵያ ፈጣሪ ከማያልቅበት በረከቱ ካደላት የተፈጥሮ ሃብትና የመሬት ስፋት እንዲሁም ጸጋዎች በተቃራኒ ተዘርዝሮ የማያልቅ ወንፊት ሙሉ ችግር የተከናነበች አገርም ናት።

በ2007 ዓ.ም ከህንድ ውቅያኖስ የሚነሳው እርጥበት አዘል ንፋስ ለኢትዮጵያ የሚለግሰውን ዝናብ በወቅቱ ሊለግስ ባለመቻሉ በአገሪቱ በርከት ያሉ አካባቢዎች ድርቅ ጠንከር ብሎባቸው ቆይቷል። የ2007 ዓ.ም ድርቅ (የኤልኒኖ ክስተት) ከተከሰተባቸው አካባቢዎች መካከል አንዳንዶቹ ከደዌያቸው ሲፈወሱ፤ አንዳንዶቹ አገግመው እንደገና ሲያገረሽባቸው (በኢንፌክሽን ሲጋለጡ)፤ አንዳንዶቹ ደግሞ የኤልኒኖው ጉዳት ይበልጥ በርትቶባቸዋል። በሶስት ደረጃ የተከፈሉትን የድርቁ ተጠቂዎች የመጎብኘት እድል ገጠሞኝ ነበር። በዛሬ የጉዞ ማስታወሻ የምንመለከተውም 18 የጋዜጠኞች ቡድን በተዘዋወረባቸው አካባቢዎች የታዘብኳቸውን አብይ ክስተቶችና ገጠመኞች ይሆናል።

መነሻችንን አዲስ አበባ አድርገን ወደ ምንጃር ሸንኮራ በማቅናት የጉብኝታችንን የመጀመሪያ ምዕራፍ ስናደርግ የትግራይዋ ዛላንበሳ ደግሞ የጉብኝቱ የመጨረሻ ከተማ ነበረች። ከአዲስ አበባ በሞጆ ምንጃር ሸንኮራ፣ መጥተህ ብላ (ቡልጋ)፣ ሽዋሮቢት፣ ጉባ ላፍቶ፣ አላማጣ፣ እንዳምሆኒ፣ ሀውዜን እያለ ዛላንበሳ ድረስ ያደረግነው የጉብኝት ጉዞ 2200 ኪሎ ሜትር የሸፈነ በመሆኑ የጽሁፉን ርዕስ “የ2200 ማስታወሻ” ተብሎ እንዲጠራ የተደረገው በዚህ ምክንያት መሆኑን አስቀድሞ መጠቆምን ወድጃለሁ።

 

 

ተስፋ ያጣችው የተስፋ አገር

ለሁለት ቀናት ቆይታ ያደረግንባት የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ዋና ከተማ አረርቲም ሆነች አርሶ አደሮቹን የጎበኘናቸው የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ለማስታወሻ የሚሆን ብዙም ቁም ነገሮችን ማየት አልቻልንም ነበር። በመሆኑም በዚህ የጉዞ ማስታወሻ ላይ የመጀመሪያ ምዕራፍ የሚከፈተው በቡልጋ ይሆናል። ዳሩ ቡልጋ የኢትዮጵያዊያን የቀለም አባት የሆነው ተስፋ ገብረሥላሴን የፈጠረች አይደለች!! የኢትዮጵያ ምሁራንን በር ከፋቹ ተስፋ የተወለዱባት ቡልጋ የዚህ ጸሁፍ በር ከፋች ሆናለች።

ኔልሰን ማንዴላ በይቅርባይነታቸውና በነጻነት ታጋይነታቸው የዓለም ህዝብ ከክብር ጋር አድናቆቱን ይለግሳቸዋል። ጥቁሩ የነጻነት ታጋይ ከተናገሯቸው ህልቆ መሳፍርት ገንቢ ንግግሮቻቸው መካከል “ዓለምን ለመለወጥ ብቸኛው መሳሪያ ትምህርት ነው” የምትለዋ መፈክራቸው በተለይም እንደ አፍሪካ ባሉ ድሃና መሃይምነት በሰፈነባቸው አካባቢዎች በከፍተኛ ደረጃ ትነሳለች። ኔልሰን ይህችን መፈክር የተናገሯት በ1990ዎቹ ቢሆንም ኢትዮጵያዊው የቀለም አባት ተስፋ ገብረሥላሴ ግን ገና በ1910 ገደማ “መሃይምነት ይጥፋ እውቀት ይስፋፋ፣ ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ” ሲሉ ኢትዮጵያ ለእድገትና ለስልጣኔ የምታደርገው ጉዞ ሊሳካ የሚችለው በትምህርት ብቻ መሆኑን ተናገረዋል።

እንዳለመታደል ሆኖ ተስፋ “ድንቁርና ይጥፋ” ብለው የመከሩት ምክር ተቀባይነት አላገኘ ወይም ደግሞ እሳቸው የተናገሩትን ገንቢ ቃል (powerful word) እንደ ራሳችን ወስደን አላከበርናቸው ስለ ትምህርት አስፈላጊነት ለመናገር አፋችንን ስንከፍት ቶሎ የምንጠቀማቸው መፈክሮች “የበላና የተማረ ወድቆ አይወድቁም” የሚለውን ሆድ አደር አገርኛ አባባልና ቀደም ሲል የተጠቀሰውን የኔልሰን ማንዴላ መፈክር ብቻ እንጂ “ድንቁርና ይጥፋ እውቀት ይስፋፋ ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ” የሚለውን ዘመን ተሻጋሪ አባባል አይደለም። በጣም የሚገርመው ደግሞ በተስፋ ገብረሥላሴ ፊደል ገበታ የተማረው ሁሉ ባለውለታውን ረስቶ የሩቅ አገሩን የማንዴላን ንግግር መናገሩ ነው። ለዚህ ይሆን “አባቱን ሳያውቅ አያቱን ይናፍቃል” የሚባለው?

የተስፋ ገብረሥላሴ አገር በቀድሞው ቡልጋ አውራጃ ሲሆን አሁን ስሙ ተቀይሮ “በረኸት ወረዳ” ተብሏል። የተስፋ ትውልድ መንደር ደግሞ ከምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ዋና ከተማ አረርቲ ወደ ደብረ ብርሃን በሚወስደው መንገድ ከ28 ኪሎ ሜትር በኋላ ወደ መጥተህ ብላ ከተማ (የበረኸት ወረዳ ዋና ከተማ ነች መጥተህ ብላ) በሚወስደው መንገድ በግምት 15 ኪሎ ሜትር ከዋናው አስፋልት ርቃ ትገኛለች። በዚህች የገጠር ቀበሌ በታህሳስ 24 ቀን 1895 ዓ.ም የተወለዱት ተስፋ ገብረሥላሴ ዘ ብሔረ ቡልጋ የእውቀት አባትና የኢትዮጵያዊያን ምሁራን ብርሃን ፈንጣቂ ናቸው ድንቁርና ይጥፋ እውቀት ይስፋፋ ሲሉ የተናገሩት። ፊደልን ከቆዳ ላይ ጽፈው ማቲዎችን ሰብስበው ያስተምሩበት የነበረው የተስፋ ትምህርት ቤት (ትልቅ ዛፍ) ዛሬም በህይወት ተገኛለች። እዛች ቦታ ላይ ደግሞ ተስፋን የማይመጥን መታሰቢያ ሀውልት ቆሞላቸዋል።

የተስፋ አገር (በአሁኑ አጠራር በርኸት ወረዳ) ከባህር ጠለል በላይ ከ750 እስከ 850 ሜትር ከፍታ ያላትና የአየር ንብረቷም 80 በመቶ ያህሉ ቆላማ፣ 17 በመቶ ወይና ደጋ እና ሶስት በመቶ ደግሞ ደጋማ ነው። 42 ሺህ ከሚሆነው የወረዳው አጠቃላይ ህዝብ ውስጥ 18 በመቶ ማለትም 7500 ያህሉ የአርጎባ ብሔረሰብ ሲሆን ቀሪው አማራ ነው። ከዘመናት በፊት ድንቁርና ይጥፋ ሲሉ የተናገሩት ተስፋ ገብረሥላሴ ዛሬ አገራቸው (አጠቃላይ ኢትዮጵያ በተለይም ቡልጋ) ድህነት ቤቱን ሰርቶባታል። በተለይ ቡልጋ ወረዳ በአገሪቱ ከሚገኙ የድህነት መንደሮች ቀዳሚዋ ሳትሆን አትቀርም። ከ42 ሺህ ህዝቧ መካከል ባለፈው ዓመት 37 ሺህ በዚህ ዓመት ደግሞ 27 ሺህ የሚሆነው በከፋ ድህነት ውስጥ እንደሚገኝ ከወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመልክቷል። በጉብኝት ወቅት የታዘብነውም “መጥተህ ብላ” የሚባለው የወረዳው ከተማ “መጥተህ ብላ ከምትባል መጥተህ ጹም” ተብላ ብተጠራ የተሻለ ይሆናል። ምክንያቱም ከተማዋ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት በስራ አጥነት ምክንያት በየቡና ቤቱ እና በየመንገዱ ጫት ሲቅሙ እና አርሶ አደሮቹም ቢሆኑ ለሰው እና ለእንስሳት መጠጥ ወሃ ፍለጋ ከሶስት እስከ አምስት ሰዓት በእግር መጓዝ ግዴታ ሆኖባቸው አይተናል። የተስፋ አገርም “ተስፋዋ” ደብዝዞ ስመለከት ተስፋ እንኳንም በዚህ ዘመን አልኖሩ ስል በሞታቸው ተጽናናሁ።

 

 

ውሃ የጠማቸው ወንዞች

ደራሲና ገጣሚ በእውቀቱ ስዩም “በገጠር ወንዙ ብቻ ሳይሆን ድልድዩም የእግዜር ስራ ነው” ሲል በአንድ ወቅት ተናግሮ ነበር። 2200 ኪሎ ሜትር በሸፈነው የድርቅ ምልከታ ጉዞዬ የታዘብኩት ግን በየመንገዱ የማገኛቸው ወንዞች የእግዜር ስራ የሆነው ውሃው ደርቆ የሰው ስራ የሆነው ድልድዮች ግን አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ነው። ሁሉም በሚያስብል መልኩ ወንዞቹ ውሃ ሳይኖራቸው ድልድይ ታቅፈው መኪና እና የቁም እንስሳት ሲተላለፉባቸው ይውላሉ። ወንዞቹ ለምን ውሃ ጠማቸው? የሚል ጥያቄ በአእምሮዬ አቃጭሎብኝ ነበር።

ለዚህ ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ እንዲሰጠኝ የጠየኩት ሰው ባይኖርም በድርቅ ወደ ተጎዱት አርሶ አደሮች በተጓዝኩበት ጊዜ የታዘብኩት በአገሪቱ የደረሰው ድርቅ እንስሳቱንና ማሳውን ብቻ ሳይሆን ወንዞችንም ለውሃ ጥም እንደዳረጋቸው ነው። በአንድ ወቅት በተፈጠረ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለዓመታት መሬቱም ብቻ ሳይሆን እንስሳቱ እና ወንዞቹ ውሃ ሲጠማቸው ቆሞ የሚያይ ደካማ የአካባቢ ጥበቃ እና ስንኩል ኢኮኖሚ በአገሬ መገንባቱን ስታዘብ እነዛ ወንዞች በቀጣይም በውሃ ጥም የሚሰቃዩበት ጊዜ ላለመኖሩ ዋስትና የለኝም።

 

 

የአገሬ አምሳያ የሆኑት እንስሳት

ሀበሻ ሲተርት “ለላም ቀንዷ አይከብዳትም” ይላል። እኔ የቀንዱን ክብደትና የላሟን ስሜት ባላውቅም “እንደሚከብዳት” ግን እገምታለሁ። ለምን እንዲህ አልክ? ካላችሁኝ መልሴን ከዚህ እንደሚከተለው ሳላንዛዛ ረዘም አድርጌ አቀርባለሁ።

በውሃ ጥምና በምግብ እጥረት ስጋቸው አልቆ ቆዳቸው የሰፋቸው የቀንድ እንስሳት ምስራቅ አፍሪካ ድረስ የቴሌቪዥን ፐሮግራም መሳብ የሚችል አንቴና የሚመስል ቀንድ ተሸከመው ሲሄዱ ስመለከት ቀንዳቸው እንደከበዳቸው ገምቻለሁ። አውቃለሁ ቀንድ ጠላትን ለመመከት የሚያገለግል የእንስሳት የጦር መሳሪያ ነው። አውቃለሁ ቀንድ እንስሳት የሆነ ነገር ሲነካቸው ለማከክ የሚያገለግላቸው የእንስሳት ጥፍር ነው። እንዲሁም ቀንድ ለእነሱ ጌጣቸው ነው። ግን ሲበዛስ? ያኔ ሸክም አይሆንም ትላላችሁ?

ቀንድ ያላቸው እንስሳት ቀንድ ከሌላቸው ተመሳሳይ እንስሳት ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ በቀንዳሞቹ አሸናፊነት እንደሚጠናቀቅ ግልጽ ነው። አገርም እንዲሁ ነች። ከውጭ ወራሪ ጠላት ለመድፈር ይነሳል። ያኔ ጠንካራ መንግስት ህዝቡን አስተባብሮ ጠላትን ድባቅ ይመታና አገሩንም ራሱንም ያስከብራል። ነገር ግን የላሟ ቀንድ ከስጋዋ ከገዘፈ ቀንዱ ራሱ ጠላት እንደሚሆናት ሁሉ መንግስት በሙስና እና በአምባገነንነት ራሱን ከአገሩ በላይ የሚያገዝፍ ከሆነ አገርም እንዲሁ ናት። በቡልጋ፣ በምንጃር ሸንኮራ፣ በሽዋሮት፣ በራያ አላማጣ፣ በወሎ እና ሌሎችም አካባቢዎች ስዘዋወር የተመለከትኳቸው ቀንዳም ከብቶች ቀንዳቸው ውበታቸው ሳይሆን ሸክማቸው መሆኑን ተገንዝቤያለሁ። እነሱን ስመለከት አገሬን አሰብኳት።

 

 

የተኮነነችው የጻድቃን አገር

ኤርትራን ከኢትዮጵያ ገንጥሎ የወሰደው ሻዕቢያ በ1990 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ፈጸመ። ወረራውን መክቶ የሻዕቢያን እብሪት ለማስተንፈስ የአገሪቱ ህዝብ እንደ አንድ ሰው ሆኖ በመነሳት ሻዕቢያን ድል ነስቶ ሻዕቢያ አቅሙን እንዲያውቅ አደረገ። በዚያ የጦርነት ወቅት በኢትዮጵያ በኩል ጦሩን ከሚመሩ ጀኔራሎች መካከል አንዱ በትውልድ ዛላንበሳ በእድገት ማይጨው መሆናቸው የሚነገርላቸው ሜጄር ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳዔ ናቸው። ጄኔራሉ ጦሩን ከመሩባቸው ግንባሮች መካከል በተለይም በዘመቻ ጸሀይ ግባት ላይ የፈጸሙት የአመራር ብቃት በቀድሞ አለቆቻቸው ውዳሴን አትርፎላቸው ነበር ዳሩ ሲያልቅ አያምር ሆኖ በጠብ ቢለያዩም ከቀድሞ አለቆቻቸው ጋር።

በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን በጎበኘንባቸው ወቅት የመጨረሻው የጉዞ መዳረሻ የነበረው የኢትዮጵያና የኤርትራ ወታደሮች በቅርብ ርቀት እንከካስላንትያ የሚገጥሙባት ዛላንበሳ ከተማ ነች። በዛላንበሳ ጉዟችን ወቅት ለጋዜጠኞች ቡድን ማብራሪያ የሚሰጡ የአካባቢው የመንግስት ኃላፊዎች ነበሩ። በዚህም ወቅት ታዲያ አንድ አነስተኛ መንደር በእጃቸው እያመለከቱ “ያ ቤት የጄኔራል ጻድቃን አባት ቤት ነው” አሉን። ማመልከቻ ጣታቸውን (ጂ ፒኤሳቸውን) ወደ ሌላኛው አቅጣጫ አዙረው “ያ ደግሞ የዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ወላጆች ቤት ነው” ሲሉ ገለጹልን።

የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ለመሆን በምርጫ እየተወዳደሩ ያሉት ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም እና የራያ ቢራ አክሲዮን ማህበር መስራቹ ጄኔራል ጻድቃን ገብረ ትንሳዔ ዛላንበሳ ተወልደዋል። ወይም ዛላንበሳ እነዚያን የመሰሉ ጎምቱ ሰዎች ከአብራኳ ወጥተዋል። በአሁኑ ወቅት ከ12 ሺህ የማያንስ ህዝብ እንዳላት የተነገረልን ዛላንበሳ 10 ሺህ የሚሆነው ህዝቧ የእለት ምግብ እርዳታ ፈላጊ ነው። የሁለቱ ጎረቤት አገሮች መጣላታቸውን ተከትሎ ወደ ኤርትራ የሚሄደውም ሆነ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው የንግድ እንቅስቃሴ በመቋረጡ ከተማዋ እንቅስቃሴ አልባ ሆናለች። ቀደም ሲል የነበረው ዱቄት ፋብሪካ ጨምሮ ሌሎች በርካታ የንግድ ተቋማትን የሚያስተዳድሩ ህንጻዎች በሙሉ በጦርነቱ እንደቆሰሉ ሳይታከሙ ሞታቸው ደርሶ አንቀላፍተዋል። (ነብሰ ሔር)

ድርቅ ደጋግሞ የሚያጠቃት ዛላንበሳ ጦርነቱ ተጨምሮ ፈተናዋን አብዝቶባት የኩነኔ ምድር ወይም አኬል ዳማ ሆና ሳያት ጻድቃንን እንዳልወለደች ኩነኔዋ ከየት እንደመጣ ባስብም መልስ ላገኝ ባለመቻሌ ማሰቤን ትቼ ጉዞዬን ወደ አዲግራት አደረኩ። ወደ አዲግራት ስንጓዝ በርቀት አንድ ገደላማ መንደር ውስጥ ከተሰገሰጉ የገጠር መንደሮች ውስጥ ሻምበል ምሩጽ ይፍጠር የተወለደው እዚያ መሆኑን ነገሩን። የምሩጽን ትውልድ መንደር በርቀት በሚያሳዩኝ ዕለት የምሩጽ ይፍጠር አስከሬን በአዲስ አበባው ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በክብር እያረፈ ነበር።

 

 

አንዳንድ አመሎች

የመኪናውን አሽከርካሪ ጨምሮ 18 አባላትን ከያዘው የጉዞ ቡድን ውስጥ አንዳንዱ የተለመደ ባህሪ ሲኖረው ሌላው ደግሞ ወጣ ያለ ባህሪ ይኖረዋል። በዚያ ጉዞ የተመለከኩትም እንደ ሙሴ አይነቱ የቆሎ ምርኮኛ፣ የየኔአሁ ላይቭ ዘገባ እና የዚህ ጸሁፍ አዘጋጅ የቡና ፍቅርም የጉዞው አባላት የማይዘነጋው ገጠመኝ ነው። ዝርዝሩን ከዚህ በታች!!

ሙሴ የአንድ መንግስታዊ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኛ ሲሆን ከተጓዡ ሁሉ ለየት ያለ ባህሪ አለው። ከአደርንበት ሆቴል ወጥተን መኪና ውስጥ እንደገባን ሁላችንም ሰላምታ ስንለዋወጥ ሙሴ ወሬውን የሚጀምረው “ቆሎ የለም እንዴ?” ብሎ በመጠየቅ ነው(የጋዜጠኛው ቡድን በዝግመተ ለውጥ ከፈረስ የመጣ ይመስል አንድ ኩንታል ቆሎ እና ከ300 ሊትር የማያንስ ውሃ ተይዞለት ነበር)። የገብስ ቆሎ የደም ዝውውሩን እንደሚቆጣጠርለት ሁሉ ሙሴ ቆሎ ሳይበላ ሌላ ስራ መስራት አይችልም። የጉዞውን አባላት ፈገግታ በመለገስ አሰልቺውን ጉዞ ያስረሳን ባለውለታችን ሙሴ ከቆሎ በተጨማሪ ሚሪንዳ በመጠጣት ተስተካካይ አልነበረውም። አባቱ የቀድሞው የኒያላ ግብ ጠባቂ እንደሆነ የነገረን ሙሴ “ኢትዮጵያ ቡና” ለሚባለው የአገራችን ክለብ ያለው ፍቅር ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ “በቡና የሚመጣበትን በቆሎ ለመመከት” ታጥቆ የተነሳ ይመስለኝ ነበር።

አብዛኛው የጋዜጠኛ ቡድን ከኤሌክትሮኒክስ በተለይም ከማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች የመጣ በመሆኑ በየጉዞው መሀል ሾፌሩ መኪና እንዲያቆምለት የሚያቀርበው ምክንያት “ላይቭ” ልገባ ነው” በማለት ነው። በዚህም የተነሳ መኪና በሚቆምበት ወቅት “ማን ላይቭ ገባ” ይባላል። ከጋዜጠኞች “ላይቭ ልገባ ነው” በኋላ አንደኛው አባላችን አቶ ትዕግስቱ (ስሙ የተቀየረ) ለቁርስ ወይም ለምሳ አለዚያም ለሻሂ ረፍት መኪና ሲቆም ሲጋራ ለማጨስ ከቡድኑ ለየት ብለው ይቆማሉ። “የት እየሄድክ ነው” ተብለው ሲጠየቁ “ላይቭ ልገባ ስለሆነ እንዳትረብሹኝ ብዬ ነው” በማለት ራቅ ብለው አመላቸውን በመወጣት (ሲጋራቸውን አቡንነው) በመመለስ የጓደኞቻቸውን ምቾት ይጠብቃሉ።

ሌላው የጉዞው ልዩ ገጠመኝ አንዱ አባላችን (የዚህ ጸሁፍ አቅራቢ) ለቡና ካለው ፍቅር የተነሳ መኪና በቆመበት አጋጣሚ ሁሉ የሚሮጠው የጀበና ቡና ወደሚያፈሉ ቤቶች ነው። በዚህ ተደጋጋሚ ድርጊቱ አንዳንዶቹ በተለይም ሾፌሩ ቴዲ ሲበሳጭበት ቀሪዎቹ ግን “ተውት ይጠጣ አለበለዚያ ጉዞው አይገፋለትም” ሲሉ ይከላከሉለታል። በአንድ አጋጣሚ ግን አንዱ ጋዜጠኛ “ይርጋ ለምርጫ ተወዳደር ምልክትህን ግን ጀበና አድርግ” ሲል እንደ ዋዛ የጣላት ቀልድ ውላ እያደረች ቅጽል ስሙ ልትሆን ምንም አልቀራትም ነበር።

ስለሾፌራችን ካነሳን አይቀር የተወሰኑ ነጥቦችን ላክልና ላብቃ (ለነገሩ 17 መስመሮችን እንጂ 26 መስመሮችን አልጽፍ)። የመሪነትን ሀይል ያየሁት በዚያ ሾፌር ነው። ከተጓዝንበት 2200 ኪሎ ሜትር ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው እጅግ አስቸጋሪ መልክዓ ምድር እና የመንገድ መሰረተ ልማት ያልተሟላለት ወይም መሰረተ ልማቱ እንደ ባልቴት ጥርስ የወላለቀ በመሆኑ ለመኪና ጉዞ እጅግ አስቸጋሪ ነው። በተለይማ ከአረርቲ ደብረ ብርሃን የሚያገናኘው መንገድ በ2001 ዓ.ም የአስፋልት መንገድ ግንባታው የተጀመረ ቢሆንም ኮንትራክተሩ (አኬር ኮንስትራክሽን) ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆነውን መንገድ ሳይገነባ ጥሎት በመጥፋቱ መንገዱ ለመኪና አስቸጋሪ ነው። ከአንዳንድ ቧልቶ አዳሪዎች “በዚያ መንገድ እንኳን መኪና ውሃ ራሱ አቋርጦ ለማለፍ ይሰጋል” ሲሉ ምሬታቸውን በቀልድ እያዋዙ እንደሚኖሩ ነግረውኛል።

ያን የመሰለውን ለመኪናም ሆነ ለፈረሰኛ ፈታኝ መንገድ ያለፍነው ከፈጣሪ ረዳትነት ቀጥሎ በሾፌራችን ጠንካራ ስነ ልቦና እና ብቃት አማካኝነት ነው። የዚያን ሾፌር መሪ አጠቃቀም ብቃት ስመለከት አሁንም አገሬ ድቅን አለችብኝ። አስቸጋሪ መንገድ ሳይኖራት በደካማ ሾፌር መሪዋ ባለመስተካከሉ ጉዞዋ ወደ ገደል ሲሆን እያየሁ ዝም ማለት ባይኖርብኝም “ዝም” አልኩ።¾  

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
506 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 132 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us