ኢህአዴግ ዕድሉን ባያባክነው

Wednesday, 15 February 2017 13:32

 

በያሬድ አውግቸው

ዲሞክራሲያዊ መብቶች የተከበሩባቸው ሀገሮች የሚኖሩ ህዝቦች ፍላጎቶቻቸውን በመደበኛነት በሚከናወኑ ሃገራዊና አካባቢያዊ ምርጫዎች በማስጠበቅ ይታወቃሉ። ጥሩ ለሰራው ድምጻቸውን በመስጠት ላልሰራው ደግሞ በመከልከል። በነዚህ ሀገሮች መንግስታት በኩል የሚተገበሩ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶችም ዜጋቸውን ፍላጎት መሰረት ማድረግ ግድ ስለሚላቸው በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚታቀዱና የሚተገበሩ ናቸው። በሌላ በኩል በተቃራኒው ወገን የሚገኙ ሃገራት መንግስታት የሚተገብሩዋቸው የፖለቲካም ሆነ ሌሎች ፕሮግራሞች ከጥናት ይልቅ የመሪዎቻቸውን ፍላጎት መሰረት በማድረግ የሚታቀዱ በመሆኑ የቀጣይነት፣የአዋጭነት እና የአንገብጋቢነት ችግር ይስተዋልባቸዋል። ልምዳችን እንደሚያሳየው ቀጣይነት፣ አዋጭነት እና አንገብጋቢነትን ያላገናዘቡ ፖሊሲዎችም ሆነ ተግባራት ህዝቦችን ለከፍተኛ የኢኮኖሚ፤ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ኪሳራዎች ሲዳርጉ ቆይተዋል፤ እየዳረጉም ይገኛሉ።

የዚህ ጽሁፍ አላማ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን መገንባት በቀጣይነት እንዲኖር ለምንፈልገው ጠያቂና ምክንያታዊ ማህበረሰብ እና የተዋጣለት መንግስት ያለውን ሚና ማሳየት ነው። ዘርዘር ስናደርገው ሃገሩን የሚወድ ጠያቂና ምክንያታዊ ዜጋ እንዲፈጠር እንዲሁም የሚተራረሙና የሚጠባበቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲኖሩ የሚያደርጉ እርምጃዎችን ተከትሎ የሚመጣን ዘላቂና የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት ፍሬዎች በማሳየት፤ ባለመኖሩ የሚከሰቱ የጎንዮሽ ጉዳቶች ማስታወስ ይሆናል።

የአለማችንን የፖለቲካ ምህዳር ስናይ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት የሰፈነባቸው ሁሉም ሃገሮች በሰላም፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፍ የተሻለ የተጓዙ ወይም መንገጫገጭ በሌለው ሁኔታ ወደዚያው የሚገሰግሱ ሆነው ይገኛሉ። መድብለ ፓርቲ ስርዓትን ስናስብ ደግሞ የዴሞከራሲያዊ ስርኣት መገለጫ የሆኑ ነጻነቶች አስፈጻሚውን ወደማይፈለጉ ባህሪያት እንዳያዘነብል ለማስጠንቀቅ አለፍ ሲልም ለመጠየቅ ያግዛሉ የሚለውን እውነታ እናገኛለን። በሌላ አነጋገር አስፈጻሚው ራሱን 24/7 እንዲመለከት እድል ይሰጣሉ። 

ወደ ሃገራችን ስንመጣ ምንም እንኳን የዲሞክራሲያዊ ስርኣት ተቋማትን የሚያበረታታ ህገመንግስት ያለን ቢሆንም በተግባር ግን የዴሞክራሲ ኤለመንቶች የሚጨቆኑበትና ዋጋ የሚከፈልበት ሁኔታ ይስተዋላል። የገዥው ፓርቲ አባላት ታማኝነታቸውን ለማሳየት በሚወስዷቸው የማዋከብ እርምጃዎች የሲቪክ ማህበራትና አማራጭ የፖለቲካ ኃይሎች /ተቃዋሚ ተብለው የሚጠሩ ኃይሎች/    ቀጭጨዋል፤ ህብረተሰቡ በሃገሩ ጉዳይ የሚያደርገው ተሳትፎም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ ይገኛል። በብዙ ታክሲዎች ውስጥ ተለጥፎ የማየው “መብትዎ ታክሲ ውስጥ ብቻ አይታይዎ” የሚለው ቧልት አዘል ጥቅስ የጠያቂነት ባህል ቦታ እንደሌለው ከሚያሳዩ ምሳሌዎች አንዱ ነው።

የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ በመበርታቱ ህዝቡ ከፖለቲካው መድረክ እራሱን እንዲቆጥብና እንዲሸማቀቅ አድርጎአል። በዚህ የተነሳም ተስፋ መቁረጥ በብዙዎች አዕምሮ እንዲሰርጽ አድርጎአል። ይህም በአደረጃጀትና በፕሮግራም የተልፈሰፈሱ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲኖሩን ሚናውን አበርክቷል። ፓርቲዎቹ በውስጥ ችግሮቻቸው መታመሳቸውም የዚህ አብይ ማስረጃ ይመስለኛል። ይህም ህብረተሰቡ በሃይሎቹ ላይ እምነት እንዲያጣ አድርጓል። ገዥው ፓርቲ ከነድክመቱም ቢሆን ይቆይልን የሚለው የህብረተሰቡ ዝንባሌም የዚሁ አካል እንደሆነ ይሰማኛል። ይህ ዝንባሌ ጤናማ ቢመስልም እርካታን ግን አያመለክትም።  ምክንያቱም እውነተኛ የህዝብ እርካታ የሚመነጨው ከአንድ በላይ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለስልጣን ማወዳደር የሚስችል አቅም በእጁ መሆኑን ሲያረጋግጥ በመሆኑ ነው።

ከላይ እንዳየነው የአለማችን ተሞክሮ የሚያቀርብልን ምርጫዎች ሁለት ናቸው። አንደኛው የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት የሃገሪቱ ህዝቦች ያለተጽዕኖ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ስጦታዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ይሆናል። ይህም ገዥውም ሆነ አማራጭ የፖለቲካ ኃይሎች ለጎንዮሽ /Horizontal/ እና ቀጥተኛ /Vertical/ ተጠያቂነትና ምዘና እንዲጋለጡ ያስችላል። ይህ መጋለጥ ገዥው ፓርቲም ይሁን ወደ ስልጣን የሚወጡ ፓርቲዎች በተወሰኑ ዓመታት ልዩነት እንታደሳለን አይነት መሃላ ሳያስፈልጋቸው በእጃቸው ያለን እድል ላለማባከን በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው ንቁ እንዲሆኑ ያግዛል። ሁለተኛው ምርጫ ገዥው ፓርቲ እራሱን ሊያሳዩትና ሊጠይቁት የሚችሉ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት እንዲጠናከሩ ባለመስራቱ በፓርቲው ውስጥና በመንግስታዊ መዋቅሩ በሚከሰት ዝቅጠት እንደተለመደው መመታት ይሆናል። ይህም ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት መከላከልን ሳይሆን ከተከሰቱ በኋላ በእሳት ማጥፋት መሰል እርምጃዎች ህይወትሀብትና ጊዜያችንን እንድናቃጥል፤ ሲብስም ሃገራችንን እንድናጣ ያደርገናል።

ለማጠቃለል የሲቪክ ማህበራትና አማራጭ የፖለቲካ ኃይሎች መጠናከር ለተጠያቂነት ስርዓት መዳበር መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች መሆናቸውን አይተናል። ለዚህም የዳበረ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ያላቸውንም ሆነ ሂደቱን በቁርጠኝነት የጀመሩ ሃገሮች ተሞክሮ መመልከት ይቻላል። በፖለቲካው ሳይንስም ሆነ በኔ እምነት ሃገሪቷ ለተሟላ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንድትጋለጥ የሚያግዙ ተቋማትን (አማራጭ የፖለቲካ ኃይሎችየሲቪክ ማህበራት እና ሌሎችም) በማጠናከር እርስ በእርሱ የሚተራረምና የሚጠባበቅ ስርዓት መፍጠር ይቻላል።  ሳይንሱንም ሆነ ያለፍንባቸውን ተሞክሮዎች በማየት ገዥው ፓርቲ ከአማራጭ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ለመጀመር ያሰበውን ውይይት በብስለትና በጥንቃቄ ያስኬደዋል የሚለው ተስፋዬ የጠነከረ ነው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
383 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 128 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us