በቤት ውስጥ ኮምፒዩተር የመጠቀም ተጽእኖ በልጆች

Wednesday, 08 March 2017 12:13

 

መ.ተ

በሀገራችን ኮምፒዩተርን ለተማሪዎች ለማዳረስ የተወጠነ ዕቅድ እንዳለ ብዙዎቻችን እናውቃለን። እንዲያውም አንድ ላፕቶፕ ለአንድ ልጅ የሚል መርሐግብር ተዘርግቶ መተግበርም ጀምሮ እንደነበር እናስታውሳለን። ደቡብ ኮርያ ደግሞ በትምህርት ቤት የወረቀት ደብተርን ለማስቀረት ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ደፋ ቀና እያለች ትገኛለች። እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴ የጠቀሜታውን ያህል አላስፈላጊ ተጽእኖም እንዳለው ነው በዓለማችን ዙርያ የተደረጉ ጥቂት ጥናቶች እያሳዩ ያሉት። ከነዚህ ጥናቶች አንዱን ለዚህ ገጽ እንዲሆን አድርገን በማሳጠር እንዲህ ተርጉመነዋል። መልካም ንባብ።

በመኖርያ ቤት እና ትምህርት ቤት የተማሪዎች ኮምፒዩተር አጠቃቀም በጣም እያደገ መምጣት ጥያቄዎች እያስነሳ ነው። ጥያቄዎቹም የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ እንዴት አኗኗራቸውን ይቀይራል በሚል ፍሬሐሳብ ዙርያ ያጠነጥናሉ። የቤት ሥራቸውን ለመሥራት እንዴት ይጠቀሙበት? ድብርትንስ እንዴት በዚህ መከላከል ይቻላል? ነውጠኛ ባሕርይንስ ለመከላከል እንዴት ጥቅም ላይ ይውላል? የሚሉ ይሆናሉ። ይህ ጽሑፍ  በቤት ውስጥ ኮምፒዩተር አጠቃቀም ዙርያ የተደረገውን ውስን ጥናት እና በልጆች አካላዊ፣ አዕምሮአዊ እና ማኅበራዊ ዕድገት ላይ ያለውን ተጽዕኖ በመጠኑ ያስቃኛል።

በዚህ ጥናት ከተካተቱ ተማሪዎች አንዱ 16 ዓመት የሆነው ወጣት የኢንተርኔት አቅርቦት እስካለ እና ድመቴን ይዤ እስከሔድኩ ድረስ ወደ አንታርክቲካ መሔድ እፈልጋለሁ ብሏል። ይህ የሆነው የዛሬ15 ዓመት አካባቢ ነው። ዛሬም ቢሆን ነገሮች ብዙም የተለወጡ አይመስልም።

በዚህ ዙርያ የተካሔደው መነሻ ጥናት የኮምፒዩተር በቅርበት መኖር ልጆቹ ቴሌቪዥን እና ኮምፒተር ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ በመጨመር ሌሎች ተግባራት የሚያከናውኑበትን ጊዜ ከመቀነሱም ሌላ ላልተፈለገ ውፍረት እንደሚያጋልጣቸው ጠቁሟል። በተመሳሳይ መልኩ የአዕምሮ እድገትን አስመልክቶ በተደረገው ጥናት የኮምፒዩተር ጌሞች የኮምፒዩተር ዕውቀትን የሚጨምሩ ሲሆን በዚያውም የማንበብ እና ሥዕሎችን በሦሥት ማዕዘን የማየት ዐቅማቸውን እንደሚያሳድጉ ጠቁሟል።

የተገኘው ውስን መረጃ እንደሚያመለክተው የኮምፒዩተር አጠቃቀም የትምህርት ውጤትን በመጠኑ እንደሚያሻሽል ነው። ይሁን እና የልጆቹን ማኅበራዊ ዕድገት አስመልክቶ የጥናቱ ውጤት ይበልጥ የተቀላቀለ ነው። ከምክንያታዊ የኮምፒዩተር አጠቃቀም እስከ ጌም (ጨዋታ) መጫወት በልጆቹ የጓደኝነት እና ቤተሰባዊ ሕይወት ላይ አፍራሽ ተጽእኖ እንዳለው የተባለው ጥቂት ቢሆንም ከዚያ ወዲህ በተደረጉ የዳሰሳ ጥናቶች ግን የተራዘመ የኢንተርኔት አጠቃቀም ወደ ብቸኝነት እና ድብርት እንደሚያመራ አሳይቷል። ከነዚህ ውስጥ በጣም አሳሳቢው ኃይል የተቀላቀለበት የኮምፒዩተር ላይ ጨዋታ የልጆቹን ጀብደኝነት በመጨመር ነውጠኛ አድርጎ ልጆቹን ለስቃይ ማጋለጡ ነው። እውነተኛ ሕይወትን ከቁም ቅዠት እንዳይለዩም ይጋርዳቸዋል ተብሏል። የዳሰሳ ጥናት አጥኚዎቹ በመደምደሚያቸው የኮፒዩተር አጠቃቀም በልጆች ላይ የሚያመጣውን ተጽእኖ በመቀነስ እና ልጆች የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ተጨማሪ እና የተጠናከረ ጥናት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በቤት ውስጥ ኮምፒውተር መጠቀም በልጆች ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ የማጥኛው ጊዜ አሁን ነው። በሀገራችን የተደረጉ መሰል ጥናቶች መኖራቸው ለጊዜው መረጃ ባይኖረንም በአሜሪካ አብዛኞቹ ልጆች በመኖርያ ቤታቸው ውስጥ ኮምፒዩተር እንዳላቸው  ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጥናት ገልጧል።

ኮምፒዩተሮቻቸውንም ከትምህርት ቤት የተሠጣቸውን የቤት ሥራ ከመስራት እስከ ጓደኞቻቸው ጋር በኢሜይልና በመሰል መገናኛ እስከ መጨዋወት ይጠቀሙባቸዋል። እ.አ.አ በ1999 ልጆች ካሉዋቸው የሀገሪቱ ቤተሰቦች 67% የኮምፒዩተር ጌሞች ነበሩዋቸው። 60% በቤት ውስጥ ኮምፒዩተር፣ 37% ደግሞ ከኢንተርኔት የሚያገናኙ ኮምፒዩተሮች ነበሩዋቸው። የኢንተርኔት ተጠቃሚዎቹ በ1996 ማለትም ከሦሥት ዓመት በፊት ከነበረው በእጥፍ ያደገ ነበር። ምንም እንኳ ልጆቹ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ኮምፒዩተር ከመጠቀም ይልቅ ቴሌቪዢን በመመልከት ቢያውሉትም በረሀ የሚገኝ ደሴት ላይ ብትሔዱ ምን ይዛችሁ ትሔዳላችሁ ተብለው ከተጠየቁ ዕድሜአቸው ከ8 ዓመት እስከ 18 ዓመት ካሉ ልጆች ውስጥ ኢንተርኔት ያለው ኮምፒዩተር እንደሚመርጡ ነው የተናገሩት።

ስለ ልጆቻቸው በ1999እ.አ.አ ከተጠየቁ ወላጆች በተገኘው መረጃ መሠረትም በጥናቱ የተካተቱ ልጆች በቀን 4ሰዓት ከ48ደቂቃ ቴሌቪዥን ወይም ኮምፒዩተር ላይ አፍጠው ይውላሉ።

ይህ አይነት አካሔድ በአዕምሮ ላይ ከሚያመጣው ተጽዕኖ በተጨማሪ በአካልም ላይ ተጽእኖ አለው ነው የሚሉት አጥኚዎቹ። በዚህ ከሚመጡ ጉዳቶች አንዱ ከመጠን ያለፈ ውፍረት የማስከተል ዕድሉ የሰፋ መሆኑ ነው። የልብ ምት መጠንንም ያዘበራርቃል ይላሉ አጥኚዎች። በእጅ ላይም ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፤ የልጆች አብዝቶ ከኮምፒዩተር ጋር መቆራኘት።

የተሟላ ጥናት በመስኩ እስካሁን አልተካሔደም ነው የሚሉት ይህን መነሻ ጥናት ያጠኑት አጥኚዎች። ስለዚህ በቤት ውስጥ ኮምፒዩተር መጠቀም የልጆችን የትምህርት ተሳትፎ ያሳድጋል መባሉም ሆነ የአካል እና የአዕምሮ ጉዳት ያስከትላል መባሉን ደምድሞ መናገር አይቻልም። ስለዚህ በቤት ውስጥ ኮምፒዩተር ያለን ወላጆች ልጆቻችን ኮምፒዩተር እንዲጠቀሙ ከመፍቀዳችን እና ከመከልከላችን በፊት ደጋግመን ልናስብብት ይገባል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
494 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 97 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us