የታሪክ ወንጌል

Wednesday, 08 March 2017 12:07

 

በአሜን ተፈሪ

 

ባለፈው ዓመት ህዝባዊ ቁጣ አይተናል። ህዝባዊ ቁጣ ከድህነት ጋር ይያያዛል። ድህነት ደግሞ ከፖለቲካ መዋቅር ችግር ጋር የተያያዘ ነው። በመሆኑም ከድህነት ለመላቀቅ ፖለቲካዊ መዋቅር እንዲሻሻል ማድረግ ያስፈልጋል። ፖለቲካዊ መዋቅርን ለማሻሻል ደግሞ ሰፊ ህዝባዊ ንቅናቄ አስፈላጊ ነው። ግን ሁሉም ህዝባዊ ንቅናቄዎች የህዝብን ህይወት የማሻሻል ውጤት ፈጥረው አይጠናቀቁም። በመጀመሪያ፤ የአንድን ህብረተሰብ አደረጃጀት የሚቀይር የለውጥ እንቅስቃሴ ሲደረግ፤ ለውጥ ፈላጊዎች እና ነባሩ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ኃይሎች መኖራቸው የታወቀ ነው። የፖለቲካ ሥልጣኑን የያዙት እና የስርዓቱ ተጠቃሚ የሆኑት ወገኖች ለውጡን በመቃወም ይነሳሉ።
የሁሉንም የህብረተሰብ የለውጥ ሒደት የመመልከት ዕድል ያለው ታሪክ፤ እንደ ክርስቶስ በአጭር ቁመት - በጠባብ ደረት ተወስኖ በመካከላችን እየተመላለሰ ‹‹ህብረተሰባዊ ወንጌል›› (Social Gospel-ይህ ቃል ሌላ ፍቺ እንዳለው አውቃለሁ) ሊሰብክ እና ሊያስተምረን ቢመጣ፤ ‹‹ከኦሪት ዘፍጥረት›› እየጠቀሰ የሚነግረን፤ ህብረተሰብ ለውጥ ፈሪ መሆኑን ነው። በለውጥ ፈላጊው ሰፊ ህዝብ እና የፖለቲካ-ኢኮኖሚውን መዋቅር በፍላጎታቸው አምሳል ቀርጸው፤ ከመንበረ-ሥልጣን ተቀምጠው፤ በትረ-ሙሴን ጨብጠው፤ የሆነ ስርዓት አስፍነው ህዝብ በሚገዙ ወይም በሚያስተዳድሩ ልሂቃን በኩልም ሆነ በለውጥ ፈላጊ ህብረተሰብ ወገን በተደጋጋሚ የሚፈጸም የጅል ስህተት መኖሩን ይነግረን ነበር።


ህብረተሰባዊ ለውጥ ማምጣት ቀላል ነገር አይደለም። አሁን እንደቀላል ሊታዩ የሚችሉ፤ እንኳን በዕድሜ የበሰለ፤ በቀለም የተጠመቀ ሙሉ ሰው ቀርቶ፤ አፍ የፈቱ ህጻናት ጭምር የሚያውቁትን ነገር (ለምሣሌ መንግስት በህዝብ ምርጫ ሊቋቋም እንደሚችል ማሰብ) ለመረዳት እና ለመቀበል የማይቻልበት ዘመን አሳልፈናል። “ንጉሡ ከወረዱ ፀሐይ ትጠልቃለች” ሲሉ አምነን ተቀብለናል።


የአሁኑን ህገ መንግስታዊ ስርዓት ከማግኘታችን በፊት እንደአገር ተደጋጋሚ ስህተት ሰርተናል። ታሪክ በወንጌል ከሚነግረን እውነቶች መካከል ‹‹ህዝብ እና ገዢዎች ደጋግመው ካልተሳሳቱ በስተቀር የታሪክን ትምህርት አይረዱትም›› የሚል ቃል አንዱ ነው። ስለዚህ ሁሌም በለውጥ ፈላጊ ኃይል/ኃይሎች እና ነባሩ ስርዓት እንዲቀጥል በሚፈልጉ ወገኖች መካከል ፖለቲካዊ ግጭት ይኖራል።


ለውጡ አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት፤ ከለውጡ ቅኝት ጋር ተስማሚ የሚሆን አቋም በመያዝ፤ ለለውጥ ፈላጊው ህብረተሰብ ጥያቄ ምላሽ በሚሰጥ አኳኋን ራሳቸውን አስተካክለው በመሄድ፤ በፖለቲካዊ ግጭት ምክንያት ሊፈጠር የሚችልን አደጋ በማስቀረት፤ ለህዝብ ጥያቄ ትኩረት ሰጥተው፤ አጽንተው ያቆሙትን የህብረተሰብ አደረጃጀት አፈራርሰው፤ በአዲስ አደረጃጀት በመቀየር ለመጓዝ የሚችሉ ገዢዎች ብዙ ጊዜ አይገኙም። ብዙዎቹ ነባሩን ነገር አጥብቀው በመያዝ ድርቅ ብለው ይቆሙና በለውጡ ማዕበል ተጠራርገው ከፖለቲካው መድረክ ተወግደው፤ ቅርሳቸውን በታሪክ ግምጃ ቤት አኑረው ይጠፋሉ።


በሌላ በኩል፤ ለውጥ ፈላጊዎቹም የለውጥ ባለሟል የሆኑት ‹‹ህሊናዊ እና ነባራዊ›› ሁኔታዎች ቀስ በቀስ አድገው፤ ለአቅመ- ለውጥ እስኪደርሱ ድረስ፤ የታሪክ ስር - ሚዜዎች ከየቦታው ተሰባስበው፤ ተኳኩለው - አምረው ለአጀብ እስኪገኙ ድረስ፤ ብቅ ጥልቅ የሚሉ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን ተመልክተው የሚጎዱ ሰዎች ይኖራሉ። የለውጥ ንቅናቄ በአንድ ጀምበር ተጠንስሶ፣ ተሸፍሞ፣ ተብላልቶ፣ ፈልቶ፣ ጉሹ ጠርቶ እና ጠልሎ ለመጠጥ አይደርስም። በእርግጥ ጉሽ የለውጥ ጠላ ጠጥተው የሚሰክሩ ይኖራሉ። ሰክረውም ሊሳሳቱ ይችላሉ። የህዝብ የለውጥ ንቅናቄ እንደ ውቂያኖስ ለመምቴ ማዕበል እየሰገረ እና እየፎገላ መጥቶ፤ በግብታዊ ኃይል የስርዓቱን ዳር ዳር በእሣት ምላሱ እየላሰ ለወዲያው አስደንግጦ ይመለሳል።


እንደገና የወትሮውን ባህርይውን የያዘ መስሎ ተደላድሎ ይተኛል። የለውጥ ንቅናቄዎች ሁሉ ተፈላጊውን ለውጥ ወይም የብልጽግና ጎዳና በመክፈት አይጠናቀቁም። የለውጥ ንቅናቄዎች የለውጥ ኃይል ተሞልተው ይመጣሉ እንጂ፤ በፍጻሜው ግባቸውን ሊያሳኩ አሊያም ሊመክኑ ይችላሉ። በውድቀት ወይም በስኬት የመጠናቀቅ ዕድል ይዘው የሚጓዙ ናቸው። ስለዚህ ለውጥ ፈላጊዎች በታሪክ ፊት ደጋግመው ሲሳሳቱ የተመለከተ የታሪክ ‹‹ሊቀ ካህን›› በለውጥ ንቅናቄ የተነሳ ህዝብ አስተውሎ ሊሄድ እንደሚገባ ምክር መለገሱ አይቀርም።


የኢትዮጵያ ህዝብ በ 1966 ዓ.ም ያገኘውን ዕድል በሚያተርፍ ጎዳና ለመምራት አልቻለም። በ1966 ያገኘነውን የለውጥ ዕድል በጁንታዎች ተነጥቀን የመከራ ዘመን ጎትተናል። የግብጽ ህዝብም በቅርቡ ያገኘውን ዕድል የብዙዎችን ህይወት ሊቀይር በሚችል አግባብ ከዳር ሊያደርሰው አልቻለም። የግብጽ አብዮት አንድን ጨቋኝ የልሂቃን ቡድን፤ በሌላ ቡድን ከመተካት በቀር የሚሊዮኖችን ህዝብ ለመቀየር የሚያስችል ዕድል ይዞለት አልመጣም። አሁን ያለው ሁኔታ የእኛም ነገር ተመሳሳይ ዕድል እንዳይገጥመው በርትተን መስራት ይኖርብናል።

 

የተቋማት ምስጢር


እኛ አፍሪካውያን አንድ ችግር አለብን። በመልካም የለውጥ ዕድሎች በስፋትና በፍጥነት ተጠቃሚ ለመሆን ብዙ አንተጋም። በመጥፎ የለውጥ ወረርሽኝ፣ በስፋትና በፍጥነት ተጎጂ እንዳንሆንም በአስተዋይነት ጥፋትን አንከላከልም። ስለዚህ የታሪክ ፔንዱለም በአደገኛ ሁኔታ እንዲወናጨፍ እናደርገዋለን። እርግጥ አንዳንዴ አውሮፓና አሜሪካም በመጥፎ የለውጥ ወረርሽኞች ሳቢያ መጎዳታቸው አይቀርም። በዚህ ጊዜ ፔንዱለሙ በመጠኑ ይወናጨፋል። እንዲህ እንዳሁኑ በዶናልድ ትራምፕ አይነት መሪ አማካኝነት ፔንዱለሙን ያናውጡታል። የአውሮፓና የአሜሪካ መንግስታትም በፍትሕ መስፈን የረጋውን ፔንዱለም ሊያስቆጡት ይችላሉ። አሊያም በዓለም የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማዕከል የሚሰሩ ባለሟሎች ወይም ለነዚህ ተቋማት የተቀጠሩ ምሁራን በሚያመጡት የለውጥ ሐሳብ የታሪክን ፔንዱለም ክፉኛ ሊስቆጡት ይችላሉ።


ግን በአስተዋይ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች እና ዜጎች ጥረት ወረርሽኙን ለመከላከል፣ ለመመከትና ለመመለስ ይጣጣራሉ። በጥረታቸው በአገራቸው ለውጥ ለማምጣት ይችላሉ። በየጊዜው የሚነሳን ማህበራዊ ወይም ስርዓታዊ ወረርሽኝ ለመከላከል፣ ለመመከትና ለመመለስ ይችላሉ። እነዚህ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና ዜጎች ለውጥ ለማምጣት የሚችሉት፤ ችግር ሆኖ የታያቸውን ነገር ሁሉ ያለአንዳች ሰቀቀን ለመናገር የሚችሉ በመሆናቸው ነው። በሚናገሩት ነገር የተከፋ ሰው ወይም ቡድን ጥቃት ሊያደርስባቸው እንደማይችል ተማምነው የመናገር ድፍረት ስለሚኖራቸው ነው። ምናልባት ለማጥቃት የሚፈልግ ሰው ቢነሳ፤ እነሱን ከጥቃት ለመከላከል የሚችሉ የታመኑ ተቋማት ይኖራሉ። ስርዓት ለማጽናት ዋናው ጉዳይ የተቋማት ጉዳይ ነው። እንዲህ ያሉ ጠንካራ ተቋማት


(የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ…..) በሌሉበት አገር አስተዋይ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች ወይም ዜጎች ብዙ ለውጥ አያመጡም። የባህል፣ የእምነት እና የታሪክ ጉዳዮችም መሰናክል ሆነው ቀፍድደው ሊይዟቸው ይችላሉ። ደግ የለውጥ ዕድሎችን በትጋት ለመጠቀም እና ክፉ የለውጥ ወረርሽኞችን ለመከላከል›› የምንችለው ጠንካራ ተቋማት ሲኖሩን ነው። ‹‹Why Nations Fail›› የተሰኘ መጽሐፍ የጻፉት ምሁራን ‹‹አገራትን ድሃ ወይም ሐብታም የሚያደርጋቸው፤ የልዩነታቸው ምስጢር እና የመለያየታቸው መንስዔ፤ በነዚህ አገራት የሚገኙ ተቋማት ናቸው›› ይላሉ። ትንታኔያቸውን በዚህ ሐልዮት ላይ አቁመው ሐሳባቸውን ያስነበቡን እነዚህ ምሁራን፤ ባለጸጋዎቹ አገራት የብልጽግና ጉዞ ሲጀምሩ የስራቸው መነሻ ፖለቲካዊ ተቋማትን ማሻሻል መሆኑን ይጠቅሳሉ። የዓለምን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ታሪክ እየፈተሹ ዋቢ እየጠቀሱ ሐሳባቸውን ለማብራራት ይሞክራሉ።


በዚህ ትንታኔአቸው ወደ ኋላ አራት መቶ ዓመታት በመሄድ ይነሳሉ። ከቅርቡም ‹‹የአረብ ጸደይ››ን ጠቅሰው፤ ሆስኒ ሙባራክን ከስልጣን ያስወገደውን የግብፅ ህዝባዊ አመጽ ያጣቅሳሉ። በሚያቀርቡት ትንታኔ፤ የዓለምን ህዝቦች ህይወት እንዲሻሻል ያደረገ የፖለቲካዊ ተቋማት ለውጥ የተፈጠረው ሰፊ የህዝብ ተሳትፎ ባለው ህዝባዊ ንቅናቄ መሆኑን ያመለክታሉ። ህዝቦችን ለብልጽግና ህይወት የሚያበቃ እንዲህ ያለ ሥር ነቀል የፖለቲካ ተቋማት ለውጥ (transformations) የሚያስከትል የህዝብ ንቅናቄ መቼ እና ለምን እንደሚፈጠር ለማወቅ ከቻልን፤ ህዝባዊ ንቅናቄዎቹ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደታዩት ንቅናቄዎች ስኬት አልባ ጥረት እንደሚሆኑ ለመረዳት ወይም የሚሊዮኖችን ህይወት የሚያሻሻል ስኬታማ ጥረት መሆን ወይንም አለመሆናቸውን ለመመዘን ጥሩ አቋም ያስይዘናል።


የፖለቲካ ተቋማት ጉዳይ የተጻፈ ህገ መንግስትን እና የዴሞክራሲ ጎዳና የሚከተል ህብረተሰብ የመኖር እና ያለመኖር ጉዳይን ያካትታል እንጂ በእነሱ ብቻ ተወስኖ የሚያበቃ ጉዳይ አይደለም። Political institutions include but are not limited to written constitutions and to whether the society is a democracy. የፖለቲካ ተቋማት ጉዳይ፤ የመንግስት በስልጣን የመጠቀም አቅም እና ህብረተሰብን የማስተዳደር ብቃት የመያዝ ጉዳይ ነው። እንዲሁም፤ መንግስት ሁሉም ሰው ህግ አክባሪ ሆኖ ህይወቱን እንዲመራ ለመቆጣጠር የሚያስችል ብቃት የመገንባቱን ጉዳይ ይመለከታል።


ይኸ ብቻ አይደለም። ነገሩን ሰፋ አድርጎ በማየት፤ በህብረተሰቡ ውስጥ የፖለቲካ ሥልጣን የሚከፋፈልበትን አግባብ የሚወስኑ ጉዳዮችን፤ በተለይም የተለያዩ ቡድኖች ዓላማቸውን ለማሳካት ያላቸውን ችሎታ ወይም ከእነርሱ ዓላማ ተጻራሪ የሆነ ግብ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሌሎች ሰዎች የሚያደርጉትን አፍራሽ እንቅስቃሴ ለመግታት ያላቸውን ችሎታም ይመለከታል። የፖለቲካ ተቋማት ጉዳይ እነዚህን ነገሮች እንደሚያካትት መገንዘብ አስፈላጊ ነው።


የተቋማት ጉዳይ፤ በህብረተሰብ ተጨባጭ ህይወት ውስጥ ሰዎች የሚኖራቸውን ባህርይ እና የስራ ተነሳሽነታቸውንም የሚወስኑ በመሆናቸው፤ የአገራትን ስኬት ወይም ውድቀት የመወሰን ችሎታ ያላቸው ናቸው። በየትኛውም የህብረተሰብ እርከን የግለሰቦች የፈጻሚነት ችሎታ ወሳኝ ነው። ሆኖም፤ ይህ የፈጻሚነት ችሎታ አወንታዊ ኃይል ወደ መሆን መሸጋገር የሚችለው ጥሩ ተቋማዊ ማዕቀፍ ሲኖር ብቻ ነው።


ለምሣሌ፤ የማይክሮ ሶፍት ባለቤት ቢል ጌትስ፤ በመረጃ ቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንደ ተሰማሩ ሌሎች ሥመ ጥር ቱጃሮች (ፖል አለን፣ ስቲቭ ቦልመር፣ ስቲቭ ጆብስ፣ ላሪ ፔጅ፣ ስርጂ ብሪን እና ጄፍ ቤዞስ) እጅግ ከፍተኛ የፈጻሚነት ችሎታ እና ሥራ የመስራት ታላቅ መሻት ያላቸው ሰው ነበሩ። አሁንም ናቸው። ይህ እውነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ፤ ዞሮ ዞሮ የቢል ጌትስ የፈጻሚነት ችሎታ እውን መሆን የቻለው፤ በአካባቢያቸው አበረታች ሁኔታ በመኖሩ እና ያን ምቹ ሁኔታ እንደ መስፈንጠሪያ ተጠቅመው መሥራት በመቻላቸው ነው። የቢል ጌትስ እና የሌሎች መሰሎቻቸው እምቅ የፈጻሚነት ችሎታቸውን እውን ለማድረግ የሚያስችል ልዩ ልዩ እና ድንቅ ክህሎቶችን ማግኘት ያስቻላቸው የአሜሪካ የትምህርት ዘይቤ ነው። የአሜሪካ የኢኮኖሚ ተቋማት እነዚህ ሰዎች ከባድ እንቅፋት ሳይገጥማቸው በቀላሉ ኩባንያ መስርተው ሥራ መጀመር የሚችሉበትን ቀና መንገድ ከፍቶላቸዋል።


እነዚህ የኢኮኖሚ ተቋማት፤ እነ ቢል ጌትስ ያረቀቁት ፕሮጀክት በፋይናንስ እጦት ከንቱ ህልም ሆኖ እንዳይቀር ለማድረግ የሚያስችሉ ናቸው። የአሜሪካ የጉልበት ገበያም ቢል ጌትስ የሰለጠነ የሰው ኃይል በቀላሉ መቅጠር፣ እንዲሁም በአንጻራዊ ሚዛን ውድድር በሰፈነበት የገበያ ስርዓት ውስጥ ኩባንያቸውን በየጊዜው በማስፋፋት እና ምርታቸውን ለመሸጥ የሚያስችል ሁኔታ አመቻችቶላቸዋል። እነዚህ ሥራ ፈጣሪ ሰዎች ገና ከመነሻው ያለሙት ፕሮጀክት እውን እንደሚሆን መተማመንን አሳድረው የተነሱ ናቸው። በተቋማቱ ላይ እምነት አላቸው። ተቋማቱን መሠረት አድርጎ የቆመው የህግ የበላይነት መርህ አለኝታ ሆኖ ይታያቸዋል። ስለ ንብረት መብቶቻቸው መከበር ጭንቀት አያድርባቸውም። በመጨረሻም፤ የፖለቲካ ተቋማቱ ሰላም፣ መረጋጋት እና ቀጣይነትን ያረጋግጡላቸዋል።


አንድ አምባገነን ተነስቶ ሥልጣን መያዝ የሚችልበት ዕድል እንዳይኖር እና የጨዋታ ህጉን እንዳያፈራርሰው፣ ሐብታቸውን እንዳይወርሰው፣ እነሱንም ወህኒ እንዳይረውራቸው፣ ህይወታቸውን እና የኑሮ መሠረታቸውን እንዳይንደው፤ እንዲህ ያለ ሰው ሥልጣን ለመያዝ የሚችልበት ዕድል ዝግ እንዲሆን አድርገዋል። የተለየ ጥቅም ለማራመድ የተደራጁ ቡድኖች ኢኮኖሚውን ገደል ውስጥ በሚከት ጎዳና እንዲጓዝ ለማድረግ ተጽዕኖ በመንግስት ላይ ለማሳረፍ አይችሉም። ምክንያቱም፤ የፖለቲካ ስልጣን በህግ የተገደበ እና ሁነኛ በሆነ መጠን ለተለያዩ አካላት እንዲከፋፈል በመደረጉ፤ ለብልጽግና ለመሥራት ተነሳሽነት መፍጠር የሚችሉ ኢኮኖሚያዊ ተቋማት እንዳያብቡ አንቆ የሚይዝ ችግር አይገጥማቸውም። ስለዚህ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተቋማትን በማጠናከር ተሐድሶው ጥልቀት እንዲያገኝ በርትተን መስራት ይኖርብናል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
496 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 124 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us