የኘራይቬታይዜሽን ሂደት በኢትዮጵያ

Wednesday, 29 March 2017 12:19

 

ኘራይቬታይዜሽን በሕዝብ ወይም በመንግሥት ይተዳደሩ የነበሩ አገልግሎቶችን ወደ ግል ባለሀብቶች የማዛወር ሂደት ነው። ሂደቱ በመንግሥት ስር የነበሩ የልማት ድርጅቶችን የማምረት አቅም በመገንባት እና ድርጅቶች በመንግሥት ላይ የሚያሳርፉትን የበጀት ጫና በመቀነስ መንግሥት በአገልግሎት ሰጭው ዘርፍ ማለትም በጤና፣ በትምህርት እና በመሠረተ ልማት ግንባታዎች ላይ እንዲያተኩር ያደርጋል። ይህን በማድረግም የግል ባለሀብቶች በኢኮኖሚ ግንባታው እንዲሳተፉ እና ሕዝቡም በገበያው ተሣታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን ያበረታታል። በተጨማሪም ገበያ መር የኢኮኖሚ ስርዓት እንዲፈጠር፣ ሀገራዊ ኢኮኖሚ እንዲዳብርና የተወዳዳሪነት አቅም እንዲገነባ ያስችላል።

ኘራይቬታይዜሽን በጥንታዊ ግሪክ እንደተጀመረ ይነገራል። በሮማ ሪፐብሊክ ተግባራዊ ሲደረግ እንደነበርም መዛግብት ያሳያሉ። ከነዚህ በተጨማሪ በቻይና ወርቃማ ዘመን በሚባለው በሀን ስርዎ መንግሥትም በተሻለ መልኩ ይተገበር እንደነበር ይታወቃል። በስፋትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ኖሮት ተግባራዊ የሆነው ግን በእንግሊዟ መሪ በማርጋሪት ታቸርና በአሜሪካው መሪ በሮላልድ ሬገን ዘመን እንደነበር ይገለጻል። ከነዚህ ሀገራት በመቀጠልም በላቲን አሜሪካ፣ በምስራቅ እና በመካከለኛው አውሮፓ ሀገሮች እና በቀድሞዋ የሶቪየት ሕብረት ተግባራዊ ተደርጓል። 
እነዚህ ዘመናት በኢትዮጵያ ኘራይቬታይዜሽን ተግባራዊ ከሆነበት ዘመን ጋር ተቀራራቢ ናቸው። በኢትዮጵያ የኘራይቬታይዜሽን ኘሮግራም አፈጻጸም ቅድመ ዝግጅት ከተደረገ በኋላ ኘሮግራሙ ተግባራዊ የሆነው በ1987 ዓ.ም ነው። ይህ ዓመት ደግሞ እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ እና እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ ከተካሄዱት የአውሮፓ ሀገራት የኘራይቬታይዜሽን ሂደቶች የተቀራረበ ነው። ጃፓንን ከመሰሉ አገሮች ጋር ሲነጻፀር ደግሞ በአተገባበሩ ቀዳሚ እንደሚባል አንዳንድ ሰነዶች ይገልጻሉ።
በእንግሊዝ ሀገር የመጨረሻ የሚባለው የኘራይቬታይዜሽን ሂደት እ.ኤ.አ በ1985 ዓ.ም ወይም በ1977 ዓ.ም እንደተከናወነ የሚገልጹ ሰነዶች አሉ። ይህ ዓመት ከኢትዮጵያ የፕራይቬታይዜሽን አተገባበር ጋር የተቀራረበ ነው። በመሆኑም በኢትዮጵያ ተግበራዊ በሚደረግበት ወቅት ከሌሎች ሀገራት ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ልማድ በመነሳት ኘራይቬታይዜሽንን ተግባራዊ ለማድረግ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ከኘራይቬታይዜሽን አፈጻጸም ጋር የሚገናኙ ቅድመ ሁኔታዎችን እንዲሁም የኘራይቬታይዜሽንን ሀገራዊ ጠቀሜታ ከመለየትና ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር ሰፊ ጥናትንና የአተገባበር ጥንቃቄንም የሚጠይቅ ነበር።
ኘራይቬታይዜሽን በኢትዮጵያ እንዲካሔድ ያስፈለገው ለምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ለዚህ ጥያቄ ደግሞ አጠቃላይ የዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን እና የወቅቱን የሀገሪቱን ሁኔታ በማየት መልስ ሊሰጥ ይቻላል።
 ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን በመተው በወቅቱ ሀገሪቱ የነበረችበትን ሁኔታ በጥቂቱ ማየቱ ተመራጭ ነው። የኘራይቬታይዜሽን ኘሮግራም በኢትዮጵያ ተግባራዊ እንዲደረግ መሠረት የሆነው የደርግ የዕዝ ኢኮኖሚ ስርዓት በነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ስርዓት መተካት ነው። በሌላ አገላለጽ የደርግ ሥርዓት ለውጥን ተከትሎ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት የፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ለውጥ መደረግ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ስለነበረ ነው። ይህም ከ1983 ዓ.ም በፊት የነበረው የዕዝ ኢኮኖሚ ስርዓት ያስከተላቸውን የኢኮኖሚ ውድቀቶች ለመቀየር የሚደረግ ነው።
ከ1983 ዓ.ም በፊት በነበሩ ዓመታት የሀገሪቱ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ የምርት መጠን (GDP) 1.5% ነበር። ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ የምርት መጠን አንጻር የመንግሥት ወጪ 30.8% ደርሶ ነበር። በ1980/81 ዓ.ም አጠቃላይ ገቢ ከሚፈለገው ወይም ከሚጠበቀው በ17.1% ያነሰ ነበር።
በአጠቃላይ የውጭ ንግድ ዝቅተኛ የሆነበት፣ የመንግሥት ወጪም ከገቢው ጋር ያልተጣጣመበት እና ሀገራዊ ዕድገት ዝቅተኛ የነበረበትን ሁኔታ ያሳያል። የመንግሥት የልማት ድርጅቶችም በድጐማ የሚንቀሳቀሱ ሲሆን የአቅም አጠቃቀማቸውና ትራፋማነታቸው ዝቅተኛ ነው። ድርጅቶቹ መሸከም ከሚችሉት በላይ የሆነ የሠራተኛ መጠን ይዘው ነበር። ከፍተኛ የፖሊቲካ ጫና ያለባቸው ሲሆን በተወዳዳሪነትና ትርፋማነት መርህ መስራት አይችሉም። ይህ ደግሞ ለመንግሥት ከሚፈጥሩት የኢኮኖሚ አቅም ይልቅ ከፍተኛ ድጐማ በመቀበል አቅሙ እንዲዳከም ያደርገዋል።
እነዚህን ሁኔታዎች በማሻሻልም መሠረተ ልማቶችን እንዲስፋፉ፣ የአገልግሎት ሠጪ ዘርፎች አቅም እንዲያድግ እና አጠቃላይ ሀገራዊ ኢኮኖሚ አቅም እንዲጐለብት ማድረግ ያስፈልጋል። 
ይህን ለማድረግ ደግሞ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ኘሮግራም መቅረጹ ተገቢ ነበር። ከዚህ ጋር በተያዘም የኘራይቬታይዜሽን ኘሮግራም ተገቢነት አጠያያቂ አይሆንም።ሀገሪቱ የነበረችበትን መጠነ ሰፊ ችግር ቀርፎ የዕድገት አቅጣጫን እንድትከተል ማድረግ አስፈላጊ ነበር።በመሆኑም የኘራይቬታይዜሽን ኘሮግራም ተፈጻሚ መሆን ጀመረ። ከኘሮግራሙ ተግባራዊነት በፊት በመንግሥት ሥር የነበሩ የልማት ድርጅቶች በኮርፖሬሽኖች ተደራጅተው ነበር።
ስለሆነም የልማት ድርጅቶቹ ሕጋዊ ሰውነት እንዲኖራቸውና የተወዳዳሪነትና የትርፋማነት መርህን ተከትለው እንዲሰሩ ማድረግ አስፈላጊ ነበር። በዚህ መሠረትም የኮርፖሬሽን አደረጃጀቶች ፈርሰው በአዲስ መልክ እንዲደራጁ ተደረገ። ይህ ደግሞ ድርጅቶች ወደግል ባለሀብቶች የሚዛወሩበትን ሁኔታ እንዲመቻች የሚያደርግ ነበር። የልማት ድርጅቶቹን ለመምራት እንዲሁም ወደ ግል ባለሀብቶች ለማስተላለፍ የሚያስችሉ አሰራሮችም በአንድ ተቋም እንዲተገበሩ ተደረገ። ይህን ተግባር ለማከናወን የኢትዮጵያ ኘራይቬታይዜሽን ኤጀንሲና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 412/96 አንድ እንዲሆኑ ተደረገ።
 ለኘራይቬታይዜሽን ኘሮግራም ተግባራዊነት ምቹ የሆኑ ተግባሮችም ተከናወኑ። ከእነዚህ መካከል የባንክ ወለድ መጠንና የብር ምንዛሪ መጠንን ማስተካከል፣ የልማት ድርጅቶች እራሳቸውን ችለው እንዲቋቋሙ ማድረግ እና አዲስ የኢንቨስትመንት አዋጅን ተግባራዊ ማድረግ ተጠቃሽ ናቸው።የእነዚህ ሁኔታዎች መመቻቸት በአንድ ሀገር የኘራይቬታይዜሽን ተፈጻሚነትን ውጤታማ ያደርጋል። ነገር ግን የኘራይቬታይዜሽን ስኬት እንደየ ሀገሮች ነባራዊ ሁኔታ ሊወሰን ይችላል። ሀገራዊ ልዩነቶች እንዳሉ ሆነው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ኘሮግራሞች መደረግና ተፈጻሚነታቸው፣ የገበያ ተወዳዳሪነት ብቃት እና ተወዳዳሪ የሆኑ የንግድ ተቋማትን የመገንባት ሂደቶች ለኘራይቬታይዜሽን ውጤታማነት ወሳኝ ናቸው። ለዚህም ነው ለኘራይቬታይዜሽን ትግበራ ቅድመ ሁኔታዎች የተመቻቹት። እነዚህና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች ከተመቻቹ በኋላ በ1987 ዓ.ም ድርጅቶችን ወደግል ባለሀብቶች የማሸጋገር ተግባር ተከናወነ።
የኘራይቬታይዜሽን ሂደት ተግባራዊ በተደረገበት ወቅት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች 234 ሲሆኑ ብር 593 ሚሊዮን አጠቃላይ ሀብት ነበራቸው። በስራቸውም 210,949 የሚሆን የሰው ኃይል ይዘው ነበር። አንድ መንግሥት የልማት ድርጅቶችን የሚያቋቁምበት ዓላማ ይኖረዋል። ከነዚህ ዓላማዎች መካከልም የፖለቲካ የበላይነትን ለመያዝ፣ ወሳኝ የልማት መስኮችን ለመቆጣጠር፣ በሀገር ውስጥ በቂ የግል ባለሀብት አለመኖርና ሀገር በቀል ባለሀብቶች አለመበራከት የሚሉት ምክንያቶች ተጠቃሽ ናቸው።
እነዚህ ምክንያቶች ከ1983 ዓ.ም በፊት ከተቋቋሙ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አመሠራረት ጋር ተገናኝተው ሊታሰቡ ይችላሉ። በተለይም በደርግ ዘመን የግል ንብረቶችን በመውረስ የተቋቋሙ ድርጅቶችን ዓላማ መገመት አያስቸግርም። ነገር ግን እነዚህ የልማት ድርጅቶች ከመንግሥት ከፍተኛ ድጐማ ይቀበሉ ነበር። የመንግሥትን እንቅስቃሴ ከበጀት አንጻር ሊደግፉ የሚችሉ አልነበሩም። የአገርን ኢኮኖሚ ከማጐልበት አንጻርም ዝቅተኛ ሚና ነበራቸው። መንግሥት የበጀት ነፃነት ኖሮት ወደ ልማት እንዲያተኩር አያደርጉም። 
በመሆኑም ድርጅቶቹ ከመንግሥት ድጐማ ተላቀው ኢኮኖሚውን ለመገንባት የሚችሉት በኘራይቬታይዜሽን ሂደቱ ነበር። ድርጅቶችን እንደገና የማደራጀት ሥራ ከተከናወነ በኋላ ከ1987 ዓ.ም እስከ 2005 ዓ.ም በተደረጉ ድርጅቶችን ወደግል የማዛወር ሂደት 318 ድርጅቶችና ቅርንጫፎች በቀጥታ ሽያጭ፣ 5 ድርጅቶች በሊዝ እንዲሁም 9 ድርጅቶችን ደግሞ በጋራ ልማት ወደ ግል ባለሀብቶች ተዛውረዋል። ከነዚህ ድርጅቶች ሽያጭ መንግሥት ከብር 13 ቢሊዮን በላይ አስገብቷል።
የልማት ድርጅቶች እንደገና ከተደራጁ እና መንቀሳቀስ ከጀመሩ ጀምሮ እስከ 1997 ዓ.ም ባሉ ዓመታት ምርታማነታቸው ጨምሯል። በነዚህ ዓመታት ድርጅቶች በዓመት በአማካኝ እስከ ብር 13.2 ቢሊዮን የሚያወጡ ንብረቶችን አንቀሳቅሰዋል። ከዚህ እንቅስቃሴም ብር 11 ቢሊዮን የሚያወጡ ምርቶችና አገልግሎቶችን ለሽያጭ አቅርበዋል። በመሆኑም ከነዚህ ምርቶችና አገልግሎት ሽያጭ በዓመት በአማካኝ የብር 1 ቢሊዮን ትርፍ ተገኝቷል። ለ170,000 ዜጐች የሥራ እድል ተፈጥሯል። በ1997 ዓ.ም ቀረጥን ሳይጨምር በዲቪደንድ የብር 800 ሚሊዮን ፈሰስ አድርገዋል። ከ1998 ዓ.ም እስከ 2005 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ደግሞ በአማካኝ በዓመት የብር 25 ቢሊዮን በላይ የሚገመት ንብረት አንቀሳቅሰዋል። ከዚህም በዓመት በአማካኝ የብር 1.6 ቢሊዮን ትርፍ ገቢ አስገኝተዋል።
ከኢኮኖሚ ማሻሻያ ኘሮግራሙ በፊት የነበሩ 234 ድርጅቶች አጠቃላይ ሀብት ብር 593 ሚሊዮን ነበር። ከማሻሻያ በኋላ ግን ለምሳሌ እስከ 1997 ዓ.ም በዓመት በአማካኝ ሲንቀሳቀስ የነበረው የድርጅቶች የምርትና አገልግሎት ሀብት ከማሻሻያው በፊት የነበረውን የልማት ድርጅቶች አጠቃላይ ሀብት 20 እጥፍ የሚበልጥ ነው። ከ1998 ዓ.ም እስከ 2005 ዓ.ም የነበሩት የልማት ድርጅቶች ደግሞ ከማሻሻያ ኘሮግራሙ በፊት ከነበረው የድርጅቶች አጠቃላይ ሀብት በ40 እጥፍ የሚበልጥ የምርትና አገልግሎት ሀብት ያንቀሳቅሱ ነበር። በአማካኝ በዓመት ይገኝ የነበረው ትርፍ እንኳን ከማሻሻያው በፊት የነበረን የድርጅቶች አጠቃላይ ሀብት ይበልጣል።ከላይ የተገለጹት ዓመታዊ ትርፎችና የሀብት እንቅስቃሴዎች የተሸጡ ድርጅቶችን የሽያጭ ዋጋ አያጠቃልሉም። ይህ ሁኔታ ምን ያህል የኘራይቬታይዜሽን ሂደቱ መንግሥትን እያገዘ እንደነበር ያስረዳል።
ይህን ሁኔታም ከኢኮኖሚ ማሻሻያ በፊት ከነበረው የሀገራዊ ዕድገት ጋር አገናኝቶ ማሰቡ ከኘራይቬታይዜሽን ኘሮግራሙ ተግባራዊነት ጋር የተገናኙ ዕድገቶችን ለማጤን ያስችላል።
በኘራይቬታይዜሽን ሂደቱ ያላቸውን ስጋት የሚገልጹ ወገኖች አሉ። ከስጋታቸው በመነሳት የኘራይቬታይዜሽን ሂደቱ ምን ይመስላል? የሚለውን ማየት እነዚህን ስጋቶች ለመቅረፍ የተሻለ ነው። የኘራይቬታይዜሽን ኘሮግራም ተግባራዊ ከተደረገበት ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ለአስራ ሰባት ዓመታት ታላላቅ ድርጊቶች ተከናውነዋል። ኘሮግራሙ በሀገሪቱ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊትም በርካታ ጥናቶች ተደርገዋል። ኘሮግራሙ ተግባራዊ ሲደረግም በመጀመሪያ አነስተኛ የሆኑ ኢንተርኘራይዞች ወደግል እንዲዛወር ተደርጓል። በነዚህ ሂደቶች የድርጅቶች ዋጋ ትመናን፣ የሠራተኞችን ጉዳይ፣ የድርጅቶች የዝውውር ስልትን የመሳሰሉ ወሳኝ ሁኔታዎችን በተመለከተ በጥናትና በተግባር ከሚታዩ ልምዶች በመነሳት ዝግጅት ተደርጓል።
ወደግል በሚዛወሩ ድርጅቶች የሚገኙ ሠራተኞች በሀገሪቱ የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ መሠረት ድርጅቶችን የሚገዙ ባለሀብቶች እንዲያስተዳድሯቸው የሚያስችሉ እና የቋሚ ሠራተኞችና የኮንትራት ሠራተኞች ሕጋዊ መብቶች እንዲጠበቁ የሚያደርጉ ሥራዎች ተሠርተዋል። በጡረታ የሚገለሉ ሠራተኞች መብትም በሕግ መሠረት እንዲከበር የማድረግ ሥራዎች ተከናውነዋል። ከነዚህ በተጨማሪ መንግሥት በሴፈትኔት እንዲታቀፉ የፈቀዱ ሠራተኞችን መብትም እንዲከበር አድርጓል። የኘራይቬታይዜሽን ሂደቱ እንደተጀመረ በኢትዮጵያ ችርቻሮ ንግድ ኮርፖሬሽን፣ በኢትዮጵያ ቤቶችና የቢሮ ዕቃዎች ኢንተርኘራይዝ እና በጊዜው በተላለፉ ሆቴሎች ከሚገኙ 4,364 ሠራተኞች መካከል 1,454 የሚሆኑት ሴፍትኔት ኘሮግራሙን መርጠው እንደነበር የሚታወስ ነው። በዚህ መሠረትም ኤጀንሲው 39 ሱቆችና መጋዘኖች፣ 4 ሆቴሎች፣ 1 የቴክኒክ ሱቅ እና 1 የቴክኒክ አገልግሎት መስጫ ማዕከልን ለነዚህ ሠራተኞች እንዲተላለፍ አድርጓል። 
በጨረታ ውድድር በማሸነፍ ድርጅቶችን ሊገዙ ሲችሉ ሠራተኞች ይቀነሱልን የሚል ቅድመ ሁኔታ ያቀረቡ ባለሀብቶች ተቀባይነት አጥተው ኤጀንሲው ጨረታ የሠረዘበት አጋጣሚም አለ። ለዚህ እንደምሳሌ መጥቀስ ካስፈለገ በ2001 ዓ.ም. በጨረታ ቁጥር 001/2009-2010 ለሽያጭ ቀርቦ የነበረው የቃሊቲ ምግብ አ.ማ ነው። በዚህ ጨረታ ተሳተፎ ከጠቋሚ ዋጋ በላይ ከፍተኛ ገንዘብ የሰጠ የግል ድርጅት የሠራተኛ ይቀነስልኝ ቅድመ ሁኔታውን ሊያነሳ ባለመቻሉ ኤጀንሲው ጨረታውን ሠርዟል። በቀጣይ በ2002 ዓ.ም. በጨረታ ቁጥር 002/2009-2010 ይኸው አክሲዮን ማኅበር በድጋሜ ለሽያጭ ቀርቦ ሠራተኞቹንም ሙሉ በሙሉ በመረከብ በፊት ከተሰጠው ዋጋ በላይ ለሰጠውና አሁን እያስተዳደረው ላለው የግል ድርጅት ሊሸጥ ችሏል።
ከንብረት አተማመን አንጻርም እንደዚሁ ስጋቶች ሲነሱ ይታያል። ጽሑፉ የኘራይቬታይዜሽን ሂደቱ ያለ አንዳች ውጣውረድ የተሳካ ነው የሚል ሀሳብ የለውም። ምክንያቱም ማናቸውም የሚከናወኑ ተግባራት ይነስም ይብዛ በሂደት የሚገጥሟቸው ፈታኝ ሁኔታዎች ይኖራሉ። እነዚያን ለማለፍ በሚደረግ ጥረት የራሳቸው ጠንካራና ደካማ ጎኖች መታየታቸው አይቀርም። የኘራይቬታይዜሽን ጽንሰ ሀሣብ አዲስ በመሆኑ አተገባበሩ ላይም ልምድና ተሞክሮዎችን መያዝ አስፈላጊ ነበር። ከአጀማመሩ ላይ እንዚህን ሁኔታዎች ለመቅረፍም ከውጭ በመጡ አማካሪዎችና በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች አማካኝነት ሠፊ ጥናቶች ተደርገዋል። 
በዚህ መሠረትም ከአጀማመሩ የነበሩ የዋጋ ትመና ሂደቶች ላይ /Indiscriminative/ አለመሆን የኢንተርኘራይዞች የሀብት አያያዝ ደካማ መሆን፣ አላስፈላጊ እና ጥቅም የሌላቸው እቃዎችን የማጠራቀም ሁኔታ፣ ለድርጅቶች ሽያጭ ምቹ ያልሆነ ገበያ፣ በኢንተርኘራይዞቹ ሕጋዊ የሆነ የንብረት አመዘጋገብ ሁኔታ አለመኖር፣ የወጪና የገቢ አመዘጋገብ ስርዓት የጠበቀ አለመሆን ወዘተ የሚሉ ሁኔታዎች ተለይተዋል። እነዚህም በዋጋ ትመና ሂደቱ ላይ ጫና ነበራቸው። ከዚህ በተጨማሪ በሀገር ውስጥ በዋጋ ትመና የሰለጠኑ ባለሙያዎች እጥረት መኖሩ ለዚህ ችግር አስተዋጽኦ ነበረው። የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችን በዋጋ ትመና በማሰልጠን ማሰራት ከመጀመሩ በፊት ችግሩን ለመቅረፍ በውጭ ሀገር ባለሙያዎች መጠቀም ተጀምሮ ነበር።
ከነዚህ የዋጋ ትመና ችግሮች በመነሣትም የድርጅቶች ዋጋ ትመና ሂደቶች እንዲስተካከሉ ተደርጓል። በዚህ ሂደት የልማት ድርጅቶችን የኦዲት ሁኔታ በየጊዜው ከማስተካከል ጀምሮ የተለያዩ ተግባሮች ተከናውነዋል።በመሆኑም የትመና ሂደቶች ገበያውን መሠረት ያደረጉ ከመሆናቸው በተጨማሪ ለአትራፊና ከሳሪ ድርጅቶች በሚል የተለያዩ የዋጋ ትመና ሂደቶች ከግምት ውስጥ ይገባሉ። ስለዚህ የድርጅቶች የዋጋ ትመና ሁኔታ በጥንቃቄና የመንግሥትን ጥቅም በሚያስከብር መንገድ ተፈጻሚ ሲሆን ቆይቷል። ድርጅቶችን ወደግል ለማዘዋወር የሚያስችሉ የማዛወሪያ ስልቶችም የግል ባለሀብቱን በሚያበረታታና የመንግሥትን ጥቅም በሚያስከብር መንገድ ተከናውነዋል። አሁንም እየተከናወኑ ይገኛል። በዚህ ሒደትም ሕጋዊ የሆኑ ሁኔታዎችን የሚፈታተኑና ግልጽነትና ተጠያቂነት የጐደላቸው አካሔዶች አልተፈጠሩም።
ድርጅቶች ለሽያጭ የሚቀርቡበት ሒደትም ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና የሕግ የበላይነትን በተከተሉ ይፋዊ ጨረታዎች ተፈጻሚ ሲሆን ቆይቷል። አሁንም በዚህ መልኩ ተፈጻሚ እየተደረጉ ይገኛሉ። በግልጽ ጨረታ በተደረጉ ውድድሮች አማካይነት ከተሸጡ ድርጅቶች 85% የሚሆኑት ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተላልፈዋል።
ይህ ደግሞ የሀገር ውስጥ ባለሀብቱን አቅም ከመገንባትና በኢኮኖሚው ግንባታ ሂደት ወሳኝ ሚና እንዲጫወት ከማድረግ አንጻር አበረታች ነው። በእነዚህ ግልጽ ጨረታዎች በሚወዳደሩ ባለሀቶች መካከል የሚደረገው ውድድር ግልጽና ተጠያቂነት የተሞላበት ነው። በመሆኑም ከዚህ አንጻር የቀረቡ ቅሬታዎች አላጋጠሙም። የድርጅቶችን የሽያጭ ገቢ ከመሰብሰብ አንጻርም በአብዛኛው ጊዜያቸውን ጠብቀው የተከናወኑ ነበሩ። አልፎ አልፎ የሚታዩ የክፍያ መዘግየቶችንም ሕጋዊ በሆነ አግባብ እንዲመለሱ የማድረግ ሥራዎች ተከናውነዋል። በመሆኑም የድርጅቶች አተማመንና የሽያጭ ክፍያ አሰባሰብ ላይ የሚነሱ ስጋቶች ከስጋት አንጻር ተገቢ ቢሆኑም እውነታን የተከተሉ ባለመሆናቸው ክብደት ሊሰጣቸው አይገባም። አንዳንዶቹ አስተያየቶች ደግሞ በኘራይቬታይዜሽን ኘሮግራሙ ያልታቀፉና ንብረትነታቸው የማን እንደሆኑ ከማያውቋቸው ድርጅቶች በመነሳት ሂደቱን የሚወቅሱ አሉ።
የኘራይቬታይዜሽን ሂደቱን ከኢትዮጵያ አንጻር ማየት ከተፈለገ ግን እንደሌሎች የዓለም ሀገራት በተለይም ያደጉ ከተባሉት አንጻር ውጤታማ ነው ለማለት የሚቻል ሂደት ነው። መንግሥት የነበረበትን የበጀት ችግር የቀረፈ፣ የሥራ ዕድል የፈጠረ፣ ባለሀብቶችን በተለይም የሀገር በቀል ባለሀብቶችን በኢኮኖሚው ግንባታ ያሳተፈ፣ የሀገር ውስጥ ገበያ ውድድር እንዲጠናከር ያደረገ ነው ማለት ይቻላል። 
በመንግሥት እጅ የሚገኙ የልማት ድርጅቶችም ትርፋማ ከመሆን በዘለለ አዳዲስ የማምረቻ ማሽኖችን እንዲገዙ፣ የማስፋፊያ ኘሮጀክት ነድፈው ተወዳዳሪነታቸውን እንዲያሳድጉ አድርጓል። የውጭ ምንዛሬ ከማፍራት አንጻርም ሰፊ ስራን እንዲሰሩ አድርጓል። 
ኤጀንሲው ድርጅቶችን ወደግል ካስተላለፋቸው በኋላም በሚሰጣቸው ድጋፍ ለኢኮኖሚው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አስችሏል። ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ያላትን ሀገር ተከታታይና ፈጣን የሚባል የኢኮኖሚ ዕድገት እንድታስመዘግብ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ይገኛል። የመሠረተ ልማት ግንባታዎች የሚፋጠኑበትን ሁኔታ አመቻችቷል። ከዚህ ጐን ለጐን የልማት ድርጅቶች በአቅራቢያቸው ላለው ማሕበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ያስቻለ ውጤታማ ተግባር አከናውኗል።
ምንጭ፡- የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
320 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 100 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us