ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት ያላቸው ደረጃ

Wednesday, 29 March 2017 12:23

 

ኦስማን መሐመድ (www.abyssinialaw.com)

ካለፈው የቀጠለ

ሁለተኛው አመለካከት ተቃራኒ አቋምን የያዘ ነው። ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት መጽደቅ ብቻ ስምምነቶቹ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ሕጋዊ ውጤት እንዲኖራቸው ያስችላል የሚል ነው። አቋማቸውንም ለማጠናከር እንዲረዳቸው በማሰብ የዚህ አመለካከት አራማጆች የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥትን አንቀጽ 9 (4) በዋቢነት ይጠቅሳሉ። የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 9 (4) እንዲህ ይነበባል፦

“ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሐገሪቱ ሕግ አካል ናቸው” ተብሎ ተደንግጓል።   

በእነዚህ ሕግ ባለሙያዎች የሚቀርበው ክርክር ዓለም አቀፍ ስምምነት የኢትዮጵያ ሕግ አካል የሚሆነው ስምምነቱ እንደጸደቀ ወዲያውኑ ነው። ሕገ-መንግሥታዊው ድንጋጌው በኢትዮጵያ የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሐገሪቱ ብሔራዊ ሕግ አካል ለማድረግ በነጋሪት ጋዜጣ መታወጅን እንደቅድመ ሁኔታ አያስቀምጥም የሚል መከራከሪያ አላቸው። እነዚህ የሕግ ባለሙያዎች የዓለም አቀፍ ስምምነቱ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ መውጣት ወይም አለመውጣቱ በመጽደቅ ተግባር አስቀድሞ ሕጋዊ እንዲሆን ለተደረገው ዓለም አቀፍ ስምምነት ሕጋዊነትን የሚጨምር ወይም የሚቀንስ አይሆንም የሚለውን የመከራከሪያ ሃሳብ የሚያራምዱ ናቸው። በመሆኑም የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በነጋሪት ጋዜጣ ታውጀው ባይወጡም የማክበርና ተፈፃሚ የማድረግ ግዴታና ኃላፊነት አለባቸው የሚለውን መከራከሪያ ያቀርባሉ። የዚህ ጽሑፍ ጸሃፊ፣ በሚከተሉት ዋና ዋና ምክንያቶች፣ ከሁለተኛው አመለካከት ጋር ይስማማል።

የኢትዮጵያ መንግሥት አንድን ዓለም አቀፍ ስምምነት ሲያፀድቅ ስምምነቱ ውስጥ የተቀመጠውን ግዴታና ኃላፊነት ለመፈፀም ፈቅዶና በስምምነቱ ድንጋጌዎች እንደሚገደድ ተገንዝቦ ነው። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሐገሪቱ የበላይና የመጨረሻ ፍርድ ቤት ሲሆን ኢትዮጵያ ያጸደቀቸውን የዓለም አቀፍ ስምምነት ድንጋጌዎች በዋቢነት በመጥቀስ የሰጣቸውን ውሣኔዎችና የሕግ ትርጉሞች በመመርመር፣ የጸደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጻሚ የሚሆነው በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ሲታወጅ ነው ወይስ አይደለም? ለሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት እንችላለን። ለምሳሌ፦    

ጉዳይ-1(Case-1)የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በአመልካች ወ/ት ፀዳለ ደምሴ እና በተጠሪ አቶ ክፍሌ ደምሴ መካከል በሰበር መ/ቁ/ 23632 ለነበረው ክርክር ዓለም አቀፍ የሕፃናት መብት ኮንቬንሽንን (The Child Rights Convention) በመጥቀስ ጥቅምት 26 ቀን 2000 ዓ.ም ውሣኔ ሰጥቷል። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት፣ የበታች ፍርድ ቤቶች የሠጡትን ውሣኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት አለበት በማለት የሻረው ሲሆን ጉዳዩን «ኢትዮጵያ ካፀደቀቻቸው የዓለም አቀፍ ስምምነቶች መካከል የሕፃናትን መብት በሚመለከት 1984 ዓ.ም የፀደቀውን እና በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 9(4) መሠረት የሀገሪቱ የሕግ አካል የሆነው የሕፃናት መብት ኮንቬንሽን አንቀጽ 3(1)»መሠረት በማድረግ ከመረመረ በኃላ ፍርድ ቤቶችም ሆኑ ሌሎች አካላት ሕፃናትን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ውሣኔ ሲሰጡ የሕፃናቱን ጥቅምና ደህንነት በዋነኛነት ማስቀደም እንዳለባቸውና የሕፃኑ ጥቅምና ደህንነት (The Best Intereset of the Child) የሚጠበቀው በአመልካች በኩል መሆኑን በመተንተን የአሁኗ አመልካች ወ/ሪት ፀዳለ ደምሴ የሕፃን ቢንያም ክፍሌ ሞግዚትና አስተዳዳሪ ሆና ሕፃኑን በመልካም አስተዳደግና ደህንነነት ተንከባክባ እንድታሣድገው ተሹማለች በማለት ወስኗል፡፡

ጉዳይ-2(Case-2)የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በአመልካች ተስፋዬ ጡምሮ እና በተጠሪ የፌዴራል የሥነ-ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን-ዐቃቤ ሕግ መካከል በሰበር መ/ቁጥር 73514 በነበረው የወንጀል ክርክር የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነትን (International Covenant on Civil and Poltical Rights) በመጥቀስ ህዳር 6 ቀን 2005 ዓ.ም ውሣኔ ሰጥቷል። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በፍርድ ሐተታው ላይ የኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ የኢፌዴሪ የወንጀል ሕጉ ከመፅናቱ በፊት የመንግሥት ሥራውን ለቅቆ በንግድ ሥራ መሰማራቱ በተረጋገጠው አመልካች ላይ ምንጩ ያልታወቀ ሐብት ይዞ በመገኘት የሙስና ወንጀል ያቀረበበት ክስ ማንኛውም ሰው የወንጀል ክስ ሲቀርብበት የተከሰሰበት ድርጊት በተፈፀመበት ጊዜ ድርጊቱን መፈፀም ወይም አለመፈፀም ወንጀል መሆኑ ካልተደነገገ በስተቀር ሊቀጣ እንደማይችልና ወንጀሉ በተፈፀመ ጊዜ ተፈፃሚ ከነበረው የቅጣት ጣሪያ በላይ ሊቀጣ እንደማይችል ከደነገገው የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 22 (1) እና አገራችን ባፀደቀቸው የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት አንቀጽ 15 (1)«No one shall be held guility of any criminal offince on account of any act or omission which did not constitute a criminal offince under national or international law, at the time which the criminal offince was committed»በሚል የተደነገገውን የወንጀል ሕግ መርህ የሚጥስና የአመልካችን መብት የሚያጣብብ ነው። የበታች ፍርድ ቤቶች ከላይ የተገለጸውን ዓለም አቀፋዊ መሠረታዊ መርህ በማስፈፀም የዐቃቤ ሕጉን የወንጀል ክስ ውድቅ ማድረግ ሲገባቸው አመልካች ምንጩ ያልታወቀ ሐብት ይዞ በመገኘት የሙስና ወንጀል የፈፀመ ጥፋተኛ ነው በማለት የሰጡት የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሣኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ አመልካች በነፃ እንዲሰናበት ሲል ወስኗል።

ጉዳይ-3(Case-3)የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በአመልካች አለማየሁ ኦላና እና በተጠሪ በተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (United Nations Development Program) መካከል በሰበር መ/ቁጥር 98541 በነበረው የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ክርክር አመልካች የተለያዩ ክፍያዎች በተጠሪ እንዲከፈላቸው በወረዳው ፍርድ ቤት በተወሰነው ውሣኔ መሠረት የአፈፃፀም መዝገብ ከፍተው ክርክሩ በመታየት ላይ እያለ ተጠሪ የመከሰስ መብት የለውም ተብሎ የአፃፀም መዝገቡ በሁሉም የበታች ፍርድ ቤቶች መዘጋቱ ተገቢ መሆን፣ ያለመሆኑን ለመመርመር ሲባል ያስቀርባል ከተባለ በኃላ፣ ተጠሪ የተባበሩት መንግሥታት አካል ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ጥቅምና የተለየ ከለላን በተመለከተ በተደነገገ ስምምነትም በማንኛውም መንግሥት ፍርድ ቤቶች ተከሶ መቅረብ የሌለበት መሆኑን በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር አንቀጽ 105 እንዲሁም ከተባበሩት መንግሥታት ጥቅምና የተለየ ከለላን በተመለከተ በተደነገገው ስምምነት አንቀጽ 2(2) እና 3 ሥር በግልጽ ተመልክቷል። በመሆኑም ከመነሻውም ኢትዮጵያ በፈረመችው ዓለም አቀፍ ስምምነት መሠረት፣ ተጠሪ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ላለመዳኘት በሕግ የተጠበቀለት የከለላ መብትና ጥቅም እያለው፣ የወረዳው ፍርድ ቤት በሌለው ሥልጣን የሰጠው ውሣኔ እንዲፈጽም ማድረግ፣ በዲፕሎማቲክ ግንኙነቱ ላይ አሉታዊ ውጤት የሚያስከትል በመሆኑ የአመልካችን የአፈፃፀም አቤቱታ አልተቀበልነውም፣ የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሣኔ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ሥህተት የለበትም በማለት ወስኗል።        

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሕፃናት መብት ኮንቬንሽን እና የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አጸድቃለች። ዓለም አቀፍ የሕፃናት መብት ኮንቬንሽን መጽደቁን ብቻ የሚያመለክት እና የስምምነቱን አንቀጾች ሙሉ ቃል ሳይዝ ወጥቷል። የጸደቀው ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ አልወጣም። ሌላው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ከመሰረቱ አባል ሐገራት አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን ማቋቋሚያ ቻርተሩን ፈርማ አጽድቃለች። የተባበሩት መንግሥታትና በሥሩ የሚገኙ ድርጅቶች እንደአባል መንግሥታት ሉዓላዊ አካል ለመሆናቸው በቻርተሩ አንቀጽ 2(1) ላይ የተደነገገ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታትና በሥሩ የሚገኙ ድርጅቶች እንድሁም የድርጅቶቹ አመራሮች ከሥራቸው ጋር በተያያዘ ጉዳይ፣ በአባል ሐገራት ፍርድ ቤቶች ያለመከሰስ የሕግ ከለላ፣ በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር (Charter of the United Nations) አንቀጽ105 (1)ና (2) ተሰጥቷቸዋል። ይሄው የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (United Nations Development Program) በተከሣሽነት ቀርቦ ጉዳዩ ከታየ በኋላ፣ የያቤሎ ወረዳ ፍርድ ቤት ተከሣሽ የተለያዩ ክፍያዎችን ለከሣሽ እንዲከፍል ሲል ውሣኔ ሰጥቷል። የወረዳው ፍርድ ቤት ውሣኔ በይግባኝ ያልታረመ ቢሆንም እንኳ ሥልጣን ሳይኖረው፣ ያለመከሰስ የሕግ ከለላ ባለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላይ የሰጠው ውሣኔ ሊፈፀም የማይችል ነው ተብሎ የአፈፃፀም አቤቱታው ወድቅ ሆኗል።

ከላይ በግልጽ ባየናቸው ሦስት-ጉዳዩች፣ በኢትዮጵያ የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ዝርዝር ድንጋጌዎች የእንግሊዝኛው ሙሉ ቃል ከአማርኛ ትርጓሜው ጋር በነጋሪት ጋዜጣታውጆ ስላልወጣ ዜጎች፣ ዳኞችና የፍትህ አካላት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በቀላሉ ሥለ ስምምነቶቹ ይዘት ማወቅ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል።በተለይ የተባበሩት መንግሥታት ቻርተርና የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ባልወጣበት ሁኔታ፤ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የእነዚህን ዓለም አቀፍ ስምምነት ድንጋጌዎች በፍርዱ ላይ በመጥቀስ፣ በመተርጎምና ተፈጻሚ በማድረግ የሰጠው ውሣኔ የሚያስተላለፈው መልዕክት ወይም የሚኖረው የሕግ ውጤት፤ በሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታውጀው ባይወጡም በሁሉም ደረጃ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች የማከበርና በፍርዶቻቸው ውስጥ ተፈፃሚ የማድረግ ግዴታና ኃላፊነት እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ ነው። በመሆኑም በኢትዮጵያ የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሐገሪቱ ብሔራዊ ሕግ አካል ለማድረግ በነጋሪት ጋዜጣ ማወጅ አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ አይደለም።  

በዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት መካከል ስላለው ደረጃ(Hierarchy of Treaties/Convention Verses the FDRE Constitution)

ሕጎች በባህሪያቸው፣ በተፈጥሮቸው፣ በአደረጃጀታቸው፣ ሊያስከብሩት በፈለጉት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አላማዎች ክብደት፣ በሚያወጧቸው አካላት የፖለቲካ ሥልጣን ክብደት ወ.ዘ.ተ የተለያዩ ናቸው። ታዲያ እነዚህ ሁሉ ልዩነቶች እያሉ የሕጎች ሁሉ ደረጃ እኩል ነው ቢባል የሚያስኬድ አይደለም። ሥለዚህ በተለያዩ የሕግ አይነቶች መካከል አንዱ ከሌላው የበላይ ወይም አንዱ ከሌላው የበታች የመሆን ባህሪ በመደበኛ አጠራሩ የሕጎች ደረጃ (Hierarchy of Laws) እየተባለ የሚጠራው ነው። የሕጎች ደረጃ በሕጎች መካከል የሚኖረውን የከፍና ዝቅ፣ በሕጎች መካከል ያለውን ተዋረድና የበላይና የበታችነት (Superior-Inferior relation) ግንኙነትየሚመለከት ነው። ይህም ማለት ሕጎች በሙሉ በእኩልነት ደረጃ የሚታዩ ሳይሆኑ አንዱ ከሌላው የመብለጥ ወይም የማነስ ደረጃ አላቸው። የዳኝነት ሥርዓቱ በአንድ አከራካሪ ጉዳይ ላይ ለመወሰን ሲሞክር በሕጎች መካከል አለመግባባት፣ ግጭትና ተቃርኖ ማጋጠሙ የተለመደ ነው። የዳኝነት አካሉም አንዱን ሕግ መርጦ ለጉዳዩ እልባት መስጠት አለበት። ምርጫውን ለማካሄድና አለመግባባቱን ለመፍታት በጣም የተሻለው መንገድ የሕጎችን ደረጃ ማወቅ ነው። በዚሁ መሠረት የበታች ሕጎች የበላይ ሕጎችን በምንም አይነት መቃረን አይችሉም። ተቃርነው ቢገኙ የበታች ሕጎች ውድቅ ሆነው የበላይ ሕጎች ተፈፃሚነት ይኖራቸዋል። ሥለሆነም የአስተዳደር መመሪያዎችና ደንቦች በምንም መልኩ አዋጆችን፤ አዋጆች ደግሞ ሕገ-መንግሥትን ሊቃረኑ አይገባም፣ ሆኖም ከተገኘም የበላይ የሆነውን ሕግ በመምረጥ ለጉዳዮች እልባት እንሰጣለን። ስለ ሕጎች ደረጃ ለመግቢያ ያህል ይህን ካልኩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት ያላቸውን ደረጃ እንመልከት።

በኢትዮጵያ የሕጎች የበላይና የበታች አሠላለፍ ላይ የዓለም አቀፍ ስምምነቶች ትክክለኛ ቦታ ወይም ደረጃ የት እንደሆነ ባለመታወቁ በሕግ ምሁራኖች መካከል ብዙ ክርክሮችን እየጋበዘ ያለ አጀንዳ ነው። የፀደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት ከአንድ ሐገር ሕገ-መንግሥት ጋር ሊጋጭ ይችላል። በዚህ ጊዜ ዓለም አቀፍ ስምምነት ከሕገ-መንግሥቱ የበላይ የሆነ ደረጃ ሊሰጠው፣ ከሕገ-መንግሥቱ ጋር በእኩል ደረጃ ሊገኝ፣ ወይም ከሕገ-መንግሥቱ የበታች የሆነ ደረጃ ሊያገኝ ይችላል። በዚህ ጉዳይ ላይ በሁሉም ሐገሮች ተመሳሳይና አንድ ወጥ የሆነ የሕግ ማዕቀፍና አሰራር የለም።

በኔዘርላንድ እና በስዊስ ሕግ መሠረት የጸደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት ከሕገ-መንግሥቱ ጋር ከተቃረነ ዓለም አቀፍ ስምምነቱ የበላይነት አለው። በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስምምነት ከሕገ-መንግሥቱ የበላይ ነው የሚል መከራከሪያ አለ።ለዚህ አመለካከት አንደኛው ምክንያት፣ ዓለም አቀፍ ሕግ በአባል መንግሥታት ላይ አስገዳጅነት አለው፣ ሐገሮች ዓለም አቀፍ ሕግን በግዛታቸው ውስጥ እንዲከበር የማያደርጉ ከሆነ የሕግ ኃላፊነትን ያስከትልባቸዋል የሚለው ነው። በዚህ አመለካከት መሠረት አባል መንግሥታት ከዓለም አቀፍ ግዴታዎቻቸው እራሳቸውን ለማሸሽ ሲሉ በሕገ-መንግሥቶቻቸው ሊመኩ አይችሉም። ዓለም አቀፍ ሕግ ከሕገ-መንግሥቱ የበላይነት እንዳለው የቬና ዓለም አቀፍ ስምምነት ላይ እንደተጠቀሰው የአንድ የዓለም አቀፍ ስምምነት አባል መንግሥት የሆነ ስምምነቱን ተፈፃሚ ላለማድረግ በማሰብ ሕገ-መንግሥቱን መጥቀስ አይችልም በማለት ይደነግጋል። ይህንን ድንጋጌ መሠረት በማድረግ የዓለም አቀፍ ሕግ ምሁራን የዓለም አቀፍ ሕግን የበላይነት በመደገፍ ይከራከራሉ።  

ሁለተኛ ምክንያት ሆኖ የሚቀርበውበሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 13(2) «በምዕራፍ ሦስት የተዘረዘሩት መሠረታዊ የመብቶችና የነፃነቶች ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግጋት፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች እና ዓለም አቀፍ ሠነዶች መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ ይተረጎማሉ»ከሚለው የድንጋጌው ይዘት በሚሰጠው ትርጉም የሚወሰን ነው። ዓለም አቀፍ ስምምነት ከሕገ-መንግሥቱ ምዕራፍ ሦስት ድንጋጌዎች የበላይ ሊያደርገው የሚችል ሁኔታ ያለ መስሎ የሚታየው በአንቀጽ 13(2) ሥር ያለውን«በተጣጣመ መንገድ ይተረጎማሉ»የሚለውን ሐረግ ስናጤነው ነው። ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከሕገ-መንግሥቱ ጋር ተጣጥመው ይተረጓማሉ ሣይሆን የሚለው የምዕራፍ ሦስት የሕገ-መንግሥቱ አንቀጾች ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር ተጣጥመው መተርጎም አለባቸው ስለሚል ነው። በአንድ በኩል የሕገ-መንግሥቱ ምዕራፍ ሦስት ድንጋጌዎችን በዓለም አቀፍ ስምምነቶች ላይ ጥገኛ የሚያደርግ ይመስላል። በሌላ በኩል ሕገ-መንግሥቱ ከዓለም አቀፍ ስምምነት ጋር ተጣጥሞ ይተርጎም ሲባል ከፍ ያለ ደረጃ የተሰጠው ለዓለም አቀፍ ስምምነቱ ይመስላል፤ ለዚሁ ክፍል ከፍ ያለ ደረጃ ከተሰጠው ደግሞ ሁለቱ በተቃረኑ ጊዜ የዓለም አቀፍ ስምምነቱ የበላይ ሆኖ ተፈፃሚ ይሆናል ማለት ነው።

በአንቀጽ 13(2) ላይ ትኩረት ያደረጉ ምሁራን ሰብዓዊ መብቶችን እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የተመለከቱት የሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች ሲተረጎሙ እጅግ ዘመናዊ፣ ጥልቀትና ምጥቀት ባለው መንገድ ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ከሚያደርጉት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎችና ሥነዶች ጋር ተጣጥመው ይተርጎሙ መባሉ ቢያንስ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በተመለከተ ያሉት የሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች ለዓለም አቀፍ ስምምነቶች ተገዥና የበታች መሆናቸውን ያመለክታል ባይ ናቸው። ዛሬ ለሰው ልጆች የሰብዓዊ መብቶች የሚደረገው ጥበቃ መነሻው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት አድርጎ በፍጥነት እየሠፋና እየጠለቀ በመሄድ ላይ ነው። ሥለዚህ በሕገ-መንግሥቱ ምዕራፍ ሦስት ውስጥ የተካተቱት መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች በፍጥነት እያደገ ከሚሄደው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ጋር ተጣጥመው ቢተረጎሙ የተሻለ ነው በማለት ክርክራቸውን ያጠናክራሉ። ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ የቆመ የፍትህ ሥርዓት ሰብዓዊ መብቶችን የበለጠ ለሚንከባከብ ዓለም አቀፋዊ ሰነዶች የበላይነት መስጠቱ ምን ላይ ነው ችግሩ ሲሉ በአፅንኦት ይጠይቃሉ።በዚህ ወገን ያሉት ምሁራኖች ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ከሕገ-መንግሥቱ በላይ ናቸው የሚል የፀና አቋም አላቸው።

በሌላ በኩል ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከሕገ-መንግሥቱ ጋር እኩል የሆነ ደረጃ የሚሰጥባቸው ሐገሮች አሉ። ለምሳሌ በዩናይትድ ስቴትስ የፀደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከዩናይትድ ስቴትስ ሕገ-መንግሥት ጋር በእኩል ደረጃ ይታያሉ። በአሜሪካ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 4 ፓራግራፍ 2 በግልጽ እንደተደነገገው ሕገ-መንግሥቱን እስካልተቃረነ ድረስ የዓለም አቀፍ ስምምነቶች ልክ እንደ ሕገ-መንግሥቱ የሐገሪቱ የበላይ ሕጎች ናቸው። በአሜሪካ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከሕገ-መንግሥቱ ጋር እኩል የሆነ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል ማለት ይቻላል። በተመሳሳይ በእኛም ሐገር በንጉሱ ጊዜ የነበረው የ1955ቱ የተሻሻለው ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 122 በግልጽ እንደተመለከተው፣ የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከሕገ-መንግሥቱ ጋር እኩል ደረጃ የተሰጣቸው መሆኑን ይገልፃል።

ሌሎች ሐገሮች ለዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከሕገ-መንግሥቶቻቸው ያነሰ ደረጃን ይሰጣሉ። በእነዚህ ሐገሮች ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ሕገ-መንግሥቱን ከተቃረኑ ተፈጻሚነትን አያገኙም። ለምሳሌ በፖርቱጋል እና በግሪክ፣ ሕገ-መንግሥት ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች የበለጠ ደረጃ አለው። በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥቱ ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች የበላይነት አለው የሚሉት ወገኖች የሚከተሉትን የመከራከሪያ ድንጋጌዎች በዋቢነት ያነሳሉ። የመጀመሪያው በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 9(4) መሠረት የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሐገሪቱ ሕግ አካል ናቸው። በመቀጠል ሕገ-መንግሥቱ በአንቀጽ 55(12) መሠረት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዓለም አቀፍ ስምምነቶችን እንዲያጸድቅ ሥልጣን ስለተሰጠው እነዚህ ስምምነቶች ከአዋጅ ጋር በእኩል ደረጃ እንዲገኙ ያደርጋቸዋል ይላሉ። ሕገ-መንግሥቱ በኢትዮጵያ የበላይነቱን የሚደነግገው በግልጽና በማያሻማ አኳኃን ነው። ይኸውም በአንቀጽ 9(1) «ሕገ-መንግሥቱ የሐገሪቱ የበላይ ሕግ ነው» ብሎ ከደነገገ በኃላ የዚህ ውጤት ምን እንደሆነ ሲደነግግ «ማንኛውም ሕግ (የጸደቀ የዓለም አቀፍ ስምምነትን ይጨምራል)፣ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለስልጣን ውሣኔ ከዚህ ሕገ-መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም» በማለት ይደመድማል። ሕገ-መንግሥት የሐገሪቱ ሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ እንደመሆኑ መጠን ለዓለም አቀፍ ስምምነቶችም የበላይ የሆናል። ይህ የክርክር መስመር እንደሚያሳየው የዓለም አቀፍ ስምምነቶች ትክክለኛ ደረጃ ከሕገ-መንግሥቱ በታች ከአዋጅ ጋር እኩል የሚል ነው። ሆኖም የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 13(2) ከሕገ-መንግሥቱ ውስጥ የተካተቱት ሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ ካጸደቀቻቸው የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ጋር ተጣጥመው ይተርጎሙ ማለቱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እንደማገናዘቢያነት የሚያገለግሉ መሆናቸውን ለማሳየት ተፈልጎ ነው ባይ ናቸው። ወደነዚህ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የምናመራው በምዕራፍ ሦስት ያሉት ድንጋጌዎች ግልፅነት ሲጎላቸው፣ አሻሚና አጠርጣሪ ሲሆኑ ብቻ ነው። በዚህም ለትርጉምና ለማገናዘቢያ ብቻ ዋጋ ያላቸው መሆኑን የሚጠቁም አንቀጽ እንጂ ሕገ-መንግሥቱን የበታች ለማድረግ የተደነገገ አይደለም ይላሉ።    

ሌላኛው መከራከሪያቸው የብሄራዊ ሉአላዊነት (National Sovereignty)ፅንሰ ሃሳብ ነው። የኢትዮጵያ  ሕዝቦች ሉአላዊነት የሚገለጽበትን ሕገ-መንግሥት ለዓለም አቀፍ ስምምነቶች ተገዥ ይሁን የሚባል ከሆነ መንግሥት በውሣኔ ሰጭነት ያለውን ሚና ያዳከማል፤ ሕጎችን ከብሄራዊና ሕዝባዊ ጥቅም አኳያ ለመቅረጽ ሙሉ ሥልጣኑን መጠቀም አይችልም፤ በአጠቃላይ የሐገር ሉአላዊነት የሚባለው ጉዳይ ትርጉም የለሽ ይሆናል በማለት ይከራከራሉ። በመጨረሻ የሚያነሱት መከራከሪያ የሕገ-መንግሥቱ አርቃቂዎች ያላቸውን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ነው። ከተለያዩ ምንጮች ማረጋገጥ እንደተቻለው በሕገ-መንግሥቱ ረቂቅ ውይይት ወቅት በዓለም አቀፍ ስምምነቶችና በሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች መካከል ግጭት ቢፈጠር እንዲት መፈታት ይቻላል በሚል ለተነሳው ጥያቄ የተደረሰው መደምደሚያ ለሕገ-መንግሥቱ ቅድሚያና የበላይነት መሰጠት እንዳለበት ነው።    

በዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና በአዋጅ መካከል ስላለው ደረጃ(Hierarchy of Treaties/Convention Verses National Legislation)   

በአሁኑ ወቅት በበርካታ ሐገሮች እንደ አዋጅ ያሉት የመጀመሪያ ደረጃ ሕጎች የሚወጡት በሕገ-መንግሥት የሕግ  አውጪነት እውቅና በተሰጠውና ከሕዝብ በቀጥታ በተመረጡ አባላት በተዋቀረው የሕግ አውጪ ምክር ቤት አማካኝነት ነው። ይህ ሕግ አውጪ አካል በተለያዩ ሐገሮች የተለያየ ስም፣ ሥልጣን እና አወቃቀር አለው። ለምሳሌ ዱማ በሩሲያ፣ ኮንግረስ በአሜሪካ፣ ፓርላማ በእንግሊዝ፣ መጅሊስ በኢራን፣ ቡንዲስታግ በጀርመን እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ በመባል ይታወቃሉ። አዋጅ በተወካዩች ምክር ቤት የሚወጣ ሕግ ሲሆን በደረጃው ከሕገ-መንግሥቱ በታች የሚገኝ እና አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ከሚያወጣቸው ደንቦች የበላይ ነው። ከዚህ መሠረተ ሃሳብ በመነሳትበኢትዮጵያ የፀደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት በደረጃው ከሕገ-መንግሥቱ በታች የሚገኝ ሲሆን በሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ከሚወጣ አዋጅ ጋር እኩል ወይም ተመሳሳይ ደረጃ አለው የሚል አተያይና አረዳድ አለ።  

በፀደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነትና በአዋጅ መካከል ግጭት በሚፈጠርበት ጊዜ ስምምነቱ ከአዋጅ የበላይነት ያለው ወይም የሌለው ስለመሆኑ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት የሚናገረው ነገር የለም። በመሆኑም በዓለም አቀፍ ስምምነትና በአዋጅ መካከል የተፈጠረ ግጭት እኩል ደረጃ ባላቸው ሁለት ብሔራዊ ሕጎች መካከል እንደተፈጠረ ግጭት ይቆጠራል። ሁለት የእኩልነት ደረጃ (ማዕረግ) ባላቸው ሕጎች መካከል ተቃርኖ ወይም ግጭት ሲፈጠር ይህን ተቃርኖ ወይም ግጭት ለመፍታት የምንጠቀመው የአተረጓጎም ሥልት፣ በኋላ የወጡ ሕጎች ቀድመው የወጡትን ሕጎች ይሽሯቸዋል(the latter prevails over the former, i.e. repeal of a legislation by latter legislation of equal status) የሚል ነው። ቅድሚያ የምንሰጠው ለኃለኞቹ ሕጎች ነው። ከዚህ መሠረተ-ሀሳብ በመነሳት«በኃላ የፀደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት ቀደም ሲል ከወጣ አዋጅ የበላይነት እንዳለው፤ በኃላ የወጣ አዋጅ ቀደም ሲል ከፀደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት የበላይነት አለው»የሚለውን የመከራከሪያ ሀሳብ የሚያቀርቡ የሕግ ባለሙያዎች ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ነው።

በእኔ በኩል «የፀደቀዓለም አቀፍ ስምምነት ከአዋጅ ጋር እኩል ወይም ተመሳሳይ ደረጃ አለው እንዲሁምበኃላ የወጣ አዋጅ ቀደም ሲል የፀደቀን ዓለም አቀፍ ስምምነት ይሽረዋል»የሚለውን የመከራከሪያ ሀሳብ የማልስማማበትን እና እሳቤው የዓለም አቀፍ ሕግን የቃረናል የምልበትን ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ከዚህ በታች አቀርባለሁ።

አንደኛው ምክንያት፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት የቃል ኪዳን ሰነዶች፣ አባል መንግሥታት የፈረሟቸውን  ስምምነቶች የማክበር፣ የማስከበር፣ የማሟላት እና የማቀላጠፍ ግዴታ ይጥልባቸዋል። አባል መንግሥታት በዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት የቃል ኪዳን ስምምነት ዕውቅና እና ጥበቃ የተሰጣቸውን መብቶችና ሕግጋት ከመጣስ በመታቀብ ሰብአዊ መብቶችን የማክበር ግዴታ አለባቸው። በመሆኑም አባል ሐገራት ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች ጋር የሚቃረን አዋጅ በግዛታቸው ተፈፃሚ  ባለማድረግ የተጣለባቸውን ሰብአዊ መብቶች የማክበር ግዴታ መውጣት አለባቸው። በሰብዓዊ መብት የቃል ኪዳን ስምምነቶች የተደነገጉትን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች አባል መንግሥታት ማክበር አለባቸው። መንግሥት ሰብአዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር ግዴታውን የሚወጣው አስፈላጊውን የሕግ አስተዳደርና ሌሎች እርምጃዎች በመውሰድ እንደሆነ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች ተደንግጓል። ነገር ግን አባል መንግሥታት ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች ጋር የሚቃረን አዋጅ ተፈፃሚ በማደረግ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎቹን እና ስምምነቶቹን ቀሪ ማድረጋቸው ወይም መሻራቸው የተጣለባቸውን ሰብአዊ መብቶች የማክበርና የማስከበር ግዴታና ኃላፊነት እንደጣሱ የሚያስቆጥር እና ዓለም አቀፍ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ተግባር ስለሆነ ከመነሻው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግጋትና ስምምነቶች የሚሽር ሕግ ማውጣት አይችሉም።   

ሁለተኛው ምክንያት፣ ማንኛውም ዓለም ዓቀፍ ስምምነት አስገዳጅ ከመሆኑ በፊት በአባል መንግሥታት ፈቃደኝነት መሟላት ያለበት ሥርዓትና ሂደት በቬና የዓለም አቀፍ ስምምነት ሕግ (The Venna Convention on the Law of Treaties) ላይ የተመለከተ ሲሆንይሄውም መንግሥታት በመጀመሪያ ዓለም አቀፍ አጀንዳ በሆነው ጉዳይ ላይ መደራደርን (Negotiation)፣ ሰነዱ ላይ መፈረምን (Signature)፣ በምክር ቤቶቻቸው ማፅደቅን (Ratification) እና ቀደም ሲል እውቅና ያገኘ ዓለም አቀፍ ስምምነት ሲሆን በመጨመር (Accession) ለዓለም አቀፍ ሕግ ተገዥ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው። ይህን ዓለም አቀፋዊ ሕግና ሥርዓት ተከትለውዓለም ዓቀፍ ስምምነቱን የሐገራቸው የሕግ አካል ያደረጉ አባል መንግሥታት ለሕጉ ተገዥ የመሆን ግዴታ አለባቸው። ስለዚህ ዓለም አቀፍ ስምምነት የአባል መንግሥታት ፍቃድ የተገለፀበት ተግባር ብቻ ሳይሆን ከበስተጀርባው ለአፈፃፀሙ ዓለም አቀፍ ሕግ ዋስትና የሚሰጠው ስምምነት ነው። አንድን ዓለም አቀፍ ስምምነት የፈረመና ያፀደቀ ሐገር ከጊዜ በኃላ በሚያወጣው አዋጅ ዓለም አቀፍ ስምምነቱን መሻር አይችልም። በኢትዮጵያ የፀደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት ከአዋጅ ጋር እኩል ደረጃ አለው፣በኃላ የወጣ አዋጅ ቀደም ሲል ከፀደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት የላቀደረጃ አለው በማለት የሚቀርበው መከራከሪያ፣ የቬና ዓለም አቀፍ የስምምነት ሕግን የሚቃረን አተያይና አረዳድ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም የሚል እምነት አለኝ። ዓለም አቀፍ ሕግጋትና ስምምነቶች በአንድ ሐገር ምክር ቤት ፀድቀው የሕግ አካል ሆኑ ማለት ዓለም አቀፍ ባህሪያቸውን ይለቃሉ ማለት አይደለም። አንድ አባል ሐገር በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ምክንያቶች የገባበትን ዓለም አቀፍ ስምምነት ቀሪ ስለሚያደርግበት፣ ስለሚያቋርጥበት እና ከስምምነቱ ስለሚወጣበት ሂደት የሚመለከቱ ድንጋጌዎች በቬና ዓለም አቀፍ የስምምነት ሕግ ላይ በግልጽ ተደንግጓል። አንድ አባል ሐገር የዓለም አቀፍ ሕግና ሥርዓት በሚፈቅደው መሠረት ዓለም አቀፍ ስምምነቱን ቀሪ በማድረግ አባል ከሆነበት ዓለም አቀፍ ስምምነት መውጣት ይችላል። ከዚህ ውጭ ዓለም አቀፍ ሕግጋትና ስምምነቶች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመፀድቃቸው ብቻ ከአዋጅ ጋር እኩል ደረጃ አላቸው፣በኋላ የወጣ አዋጅ ቀደም ሲል ከፀደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት የበላይነትአለው በሚል የሚቀርበው መከራከሪያ ከላይ በዘረዘርኳቸወ መሰረታዊ የሕግ ምክንያቶች ስህተት አለበት እላለሁ። በመሆኑም በእኔ እምነት በኢትዮጵያ የጸደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት ከአዋጅ የላቀ ወይም የበለጠ ደረጃ ያለው ይመስለኛል።

ማጠቃለያና የመፍትሄ ሀሳቦች

1.ዓለም አቀፍ ስምምነት ሉአላዊ ሐገሮች የተሰማሙበት አንድ ወይም ከዚያ በላይ የሆነ ሕጋዊ የጽሑፍ ሰነድ ሲሆን የሚመራው በዓለም አቀፍ ሕግ ነው። ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሉአላዊ አገሮች አሁን አሁን ደግሞ ዓለም አቀፍ ሕጋዊ ስውነት ያላቸው ድርጅቶች በዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና አካባቢያዊ /ክልላዊ/ ጉዳዩችን መሠረት በማድረግ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ባሕላዊ ርዕሶች ዙሪያ አስገዳጅ የሆኑ ደንቦችን እና መርሆችን በመንደፍ ተግባራዊ ለማድረግ ቃል የሚገቡባቸው አስገዳጅ ስምምነቶች ናቸው።

2.በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 9(4) በግልጽ እንደተደነገገው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሕገ-መንግሥቱን መስፈርቶች አሟልተው እስከተገኙ ድረስ በኢትዮጵያ ላይ ዓለም አቀፍ አስገዳጅነት አላቸው። ነገር ግን የስምምነቶቹ ድንጋጌዎች በሐገሪቱ ተፈፃሚነትን እንዲያገኙ፣ በነጋሪት ጋዜጣ ተዘጋጅተው እንዲወጡ ማድረግ አስገዳጅ አይደለም።

3.   በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት አንድ ሐገር አንድን ዓለም አቀፍ ስምምነት አፀደቀ ማለት ራሱን ለዓለም አቀፍ ሕብረተሰብ አስገዝቶ ለስምምነቱ እንደቆመ ያመለክታል። በቃል- መታሰር /Pacta Sunt Servanda/በቬና ዓለም አቀፍ የስምምነት ሕግ አንቀጽ 26 ላይ ሰፍሯል፤ አንድ ሐገር ግዴታውን ለመወጣት ስምምነት በሚያደርግበት ወቅት በቅን ልቦና ግዴታውን እንደሚወጣ ያመለክታል። ይህ መርህ ሀገሮች ለፀደቁ ስምምነቶች ከፍተኛ ቦታ እንዲሰጡ ይጠይቃል።  

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
571 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1072 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us