ምስክርነት ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ

Wednesday, 12 April 2017 12:25

 

በዮሴፍ አለሙ

 

ኢትዮጵያ ከ10 አመት በላይ በየአመቱ ከ8 በመቶ እስከ 11 በመቶ ፈጣን የሚባል  ኢኮኖሚያዊ እድገት እያስመዘገበች  መሆኗን ድረ-ገፁ CIA WORLD FACTBOOk  ያለፈው ጥር 12 ቀን 2017 በፈረንጆች አቆጣጠር ትኩስ መረጃውን እንካችሁ ይለናል። በሚገርም  ሁኔታ ከ188ቱ የIMF አባል አገሮች መካከል  ፈጣን  ኢኮኖሚያዊ እድገት በማስመዝጋብ ኢትዮጵያችን በ5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ይህ ፈጣን  ኢኮኖሚያዊ እድገትም አስተማማኝና ቀጣይነት አለው ከሚባለው የግብርና እና የአገልግሎት ዘርፍ የመጣ መሆኑን ድረ-ገፁ ይገልፃል።


ነገር ግን ፍትሀዊ ነው ከሚባለው ከእስካንድኒቪያን ሀገሮች ኢኮኖሚ አንፃር ሲታይ  ይህ የኢትዮጵያ ፈጣን የሚባለው ኢኮኖሚያዊ እድገት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ  ያማከለ ወይንም ያዳረሰ ባለመሆኑ ምክንያት  ኢትዮጵያችን በኢኮኖሚ ዕድገት ከአፍሪካ  በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡  ይህ ማለት በኢኮኖሚስቶቹ ቋንቋ ኢትዮጵያ አንፃራዊ አይደለም፡፡ ፍፁም ያልተመጣጠነ ኢኮኖሚያዊ እድገት ያላት አገር ሲል  ዝቅ አድርጎ አስቀምጧታል - ይህ በቁጥር  ሲገለፅ   ኢትዮጵያ 33 በመቶ ያልተመጣጠነ የሀብት ክፍፍል  የታየባት ሀገር ሲል በ173ኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል በ2011ዱ ጥናት መሰረት ። ሆኖም ግን  ኢትዮጵያችን ድህነትን ታግላ ለመጣል፥ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ደፋ ቀና እያለች መሆኗንን  ድረ-ገፁ  CIA  ባይክድም  እውነታው ግን ኢትዮጵያችን ካላት ፈጣን የሆነ የህዝብ እድገትና የአጭር ጊዜ የእድገት ጅማሮ ምክንያት በፕላኔታችን ላይ አሁንም ድረስ  ድሀ ከሚባሉት ተርታ መሆኗን ይገልፃል።


ሌላኛው  ተጨማሪ እንቅፋት ከዓለም የአየር ንብረት ጋር ተያይዞ  ዝናብ ወቅቱን  ጠብቆ ባለመዝነቡ ምክንያት ከ30 ዓመት በኋላ ድጋሚ በ2015/2016 የተከሰተው ድርቅ ብዙ ሚሊዮን ኢትዮጲያዊውያንን ለረሀብ   አጋልጧል። ለዚህ ደግሞ ትልቁ ምክንያት 80 በመቶ ኢትዮጵያዊ በግብርና የሚተዳደር መሆኑ ነው። ነገር ግን በዚሁ አጋጣሚ የአገልግሎት  ዘርፉ ደግሞ ግብርናውን በመከተል  ለአገሪቱ  GDP ዕድገት ከፍተኛ ድርሻ እያደረገ ይገኛል።


የመሬት ባለቤትነትን በተመለከተ፦  መንግስትም  ሆነ  ግለሰቡ መሬት ላይ የጋራ የሆነ የባለቤትነት መብት እንዳላቸው   በህገ-መንግስቱ  ላይ የተብራራ  ቢሆንም  ነገር ግን የግለሰቡ  መብት መሬቱን ተከራይቶ ወይም ተኮናትሮ  ለ99 አመት  የመጠቀም መብት እንጂ  መሬቱን የመሸጥም ሆነ የግሉ የማድረግ እንዲሁም በመሬቱ ዋስትና ላይ ተመስርቶ ገንዘብ የመበደር  መብት እንደሌለው  ይጠቅሳል።


በህገ-መንግስቱ መሰረት ግለ-ሰቡ መሬቱን ተከራይቶ የመጠቀም  መብት ይኑረው እንጅ  በአጠቃላይ መሬቱን  በበላይነት የመቆጣጠር ስልጣን ያለው መንግስት ነው እንደ ሲ.አይ.ኤ ዎርልድ ፋክት ቡክ /CIA world  FACTBOOk/ ተጨማሪ መረጃ፡፡ ነገር ግን እንደሚታወቀው ይህ 80 በመቶ በግብርና የሚተዳደረው ገበሬ የረጅም ጊዜ የኪራይ /lease/ መብት  እንዲኖረው በሰነድ የተደገፈ ህጋዊ የማረጋገጫ ደብተር  ተሰጥቶታል።
እንደሚታወቀው በፈረንጆች ከ2005  ጀምሮ መንግስት መሬትን አስመልክቶ አዲስ ስርዓትን በመዘርጋት ማንኛውም የድሮ  የመሬት ባለይዞታዎች ሁሉ ሰነድ ላይ  እንዲመዘገቡ በማድረግ  እያንዳንዱ ገበሬ የረጅም ጊዜ የሊዝ መብት እንዲኖረው  የማረጋገጫ ደብተር ሰጥቶታል ሲል ሲ.አይ.ኤ  ህገ-መንግስቱን  መሰረት አድርጎ አስቀምጦታል። በመጀመሪያው የመሬት ጥናት መሰረት ይህ በሰነድ የታቀፈ የይዞታ  ማረጋገጫ ደብተር እያንዳንዱ አርሶ አደር  መሬቱን  ለማልማት በየትኛውም የልማት አማራጭ ያለውን ሀይል መሬቱ ላይ በማፈሰስ ከእርከን እስከ መስኖ ልማት ድረስ እንዲያለማ መልካም  የሚባል መነሳሳትን ፈጥሮለታል ይለናል  ድረ-ገፁ CIA።


ነገር  ግን እንደ ድረ-ገፁ ዘገባ ይህ የመሬት የይዞታ መብት በአዲስ አበባ ፍትሀዊነት በጎደለው አካሄድ ማለትም  ለሙስናና ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ በመሆኑ ምክንያት አፈፃፀሙ ዝቅተኛ በሚባል ደረጃ እየተፈፀመ መሆኑን በጥናት ደርሼበታለው ሲል CIA  አስረግጦ ይናገራል። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ‘በትሬዲግኢኮኖሚክስ' ጥናት መሰረት 32 በመቶ ሙስና የተጠናወታት ሀገር መሆኗንና  በደረጃ  ሰንጠረዥ ደግሞ  108ኛ ላይ መቀመጧ ሀገሪቷ ኪራይ ሰብሳቢዎችና ሙሰኞች የበዙባት ሀገር ለመሆኗ ጥሩ ማስረጃ ነው ለማለት ያስደፍራል።


ሌላው ይህ ድረ-ገፅ  ኢትዮጵያ  ከውጭ ገበያ የምታገኘው የምንዛሪ ገቢ በይበልጥ  እያቀረበችው ካለው የአገልግሎት ዘርፍ የመነጨ  ነው ይለናል። ለዚህ የአገልግሎት ዘርፍ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ  ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸውን የግብርና ምርቶችን ቡናን ጨምሮ  በማስከተል ቀዳሚ  ተምሳሌት ነው ይለናል። ቡናን ካነሳን ደግሞ ቡና ለኢትዮጵያችን  የውጭ ምንዛሬ  በማስገኘቱ ረገድ ከፍ ያለ ቦታ ቢኖረውም ሌሎች ምርቶች ማለትም ወርቅ፣ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች፣ ጫት፥ ከብቶችን፥ እንዲሁም የአበባ ምርትን ጨምሮ ጠቃሚ በሚባል ደረጃ ለውጭ ገበያ እያቀረበች መሆኑን የCIA  ጥናታዊ ዘገባ ያስረዳል። በሀገሪቱ ነገር ግን   ለውጭ ምንዛሪ ከምትልካቸው አጠቃላይ ምርቶች መካከል የፋብሪካ ውጤቶች ከ8 በመቶ በታች መሆናቸውን መረጃው ይጠቁማል። ኢትዮጵያ በውጭ ገበያ ላይ ምርቶችን በማቅረቡም ሆነ በመግዛቱ በኩል አሁንም ድረስ ኢትዮጵያ  ያልተሻገረቻቸው ገና ብዙ ሰንሰለታማ ችግሮች  እንዳሉባት ጠቅላይ ሚኒስተሩ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሳይቀር በቅርቡ ማብራሪያ  የሰጡበት ጉዳይ ነው፡፡


የመዋእለ ሀብት ፍሰትን/ኢንቬስትመንትን/ በተመለከተ፦ በባንክና የኢንሹራንስ አገልግሎት   ዘርፍ ላይ የመዋእለ ንዋይ ፍሰት፥ በቴሌኮሙኒኬሼን እንዲሁም በጥቃቅንና  አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ኢንቬስትመንት ላይ  ለሀገር ውስጥ ኢንቬስተሮች ብቻ የተፈቀደ  ሲሆን በጨርቃ ጨርቅና በቆዳ ውጤቶች  ላይ፥ በግብርናው መስክ  በተለይም ለኢንዱስትሪው የሚበጁ ጥሬ እቃ ምርቶችን በማምረቱ ረገድ እንዲሁም መብራትንና የመብራት ግብዐት የሆኑ መሳሪያዎችን  በማምረቱ በኩል ደግሞ የውጭ ባለሀብቶች ይበልጥ እንዲሳተፉበት እየተደረገ ነው።


ሌላው CIA world  ማወቅ አለባችሁ የሚለን እውነታ  ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ በእቅድ ላይ የተመሰረተ /planned/ መሆኑን ነው። ለዚህ ደግሞ ባለፈው በፈርንጆች 2015 ማብቂያ ላይ መንግስት ከ2016-2020፤   2ኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሺን /GTP II/ ዘመን አስመልክቶ የ5 አመት እቅድ ይፋ ማድረጉ  ኢትዮጵያ በእቅድ የምትመራ ኢኮኖሚ እየተገበረች መሆኗን  ጥሩ ማሳያ ነው ይለናል ድረ -ገፁ።


በዚህ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሺን አቅድ  ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ ትሰራለች የሚለን ድረ ገፁ በተለይም በጨርቃጨርቅና በቆዳ ምርቶች እንዲሁም  በኢንዱስትሪው ውስጥ አልፈው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶችን ጭምር  ለውጭ ምንዛሪ ብታቀርብ የተሻለ አማራጭ ሊኖራት እንደሚችል በዚህ በሁለተኛው የ5 አመቱ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ አቅዳ ደፋ-ቀና እያለች መሆኗን መረጃው ይጠቁማል።


በተጨማሪም የሀይል ግንባታና ስርጭትን አስመልክቶ፣ የመንገድ ግንባታ የባቡር ሀዲድን ጨምሮ እንዲሁም ኤርፖርቶችንና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባትና በማስፋፋቱ በኩል  ኢትዮጵያ   በአዲሱ የመሰረተ-ልማት ግንባታ  ውስጥ  አቅዳ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች።


በኢንዱስትሪው ዘርፍ በኩል ደግሞ  የነበረውን 16 በመቶ የኢንዱስትሪ ጉዞ  ከግብርናው እና ከአገልግሎት ዘርፉ ጎን ተራምዶ   ለአገሪቱ የGDP እድገት  ከፍተኛ ሚና እንዲጫወት ለማድረግ ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪውን ሊደግፉላት  የሚችሉ ከህዳሴው ግድብ በተጨማሪ ሶስት ታላላቅ  የሀይል ምንጭ ግድቦችን በመገንባትና እንዲሁም ሌሎች ሊተኩ የሚችሉ  የተፈጥሮ የሀይል አማራጮችን ጭምር  ተጠቅማ  ወደ 10320 ሜጋ ዋት  ከፍ በማድረግ አስተማማኝ የሀይል ክምችትን ለመገንባት አቅዳለች ይለናል  ድረ -ገፁ   CIA።


ድረ-ገፁ ኢትዮጵያ ከሁሉም  ጎረቤቶቿ ጋር መልካም የሚባል የንግድ ትስስር ለመፍጠር  በመስመር ግንባታው ዘርፍ  ማለትም ኢሌክትሪካል ሲስተም የተገጠመለት የባቡር ሀዲድ መስመርን በመገንባት ባለችበት የቀጠናው ዞን ተስፋ የሚጣልበት ኢኮኖሚያዊ አማራጭ ሊፈጥርላት ይችላል ሲል ይጠቅሳል።  ለዚህ ደግሞ በመጠናቀቅ ላይ ያለው ኢትዮ-ጅቡቲ  የባቡር ሀዲድ ኢትዮጵያ በባቡር መስመር ግንባታ ላይ  ያላትን  ቁርጠኝነት በደንብ ያሳያል የሚለን ድረ-ገፁ እናም ኢትዮጵያ ከሁሉም ጎረቤቶቿ  ጋር ለመገናኘት ወደ ፊት ወደ ጎረቤቶቿ የምትገነባቸው የባቡር መስመሮችም ከዚሁ ከኢትዮ-ጅቡቲ መስመር ጋር  እንዲጣመሩ በማድረግ  በቀጠናው ዞን የረባ የገበያ ትስስር በመፍጠር የንግድ ግንኙነቱን ማሳለጥ ብቻም ሳይሆን ማህበራዊ መስተጋብርን  የባህል ልውውጥን ጨምሮ ጥሩ የሚባል ቅርርብና ትውውቅን ይፈጥራል ሲል ያስቀምጣል ድረ ገፁ።


ኢትዮጵያ በኤርፖርት ግንባታና የማስፋፋት ስራዎችም ላይ እቅዷን ለመተግበር ከፍተኛ ትግል እያደረገች መሆኗን ድረ-ገፁ በአይኔ በብረቱ  አረጋግጫለሁ ይለናል። ለምሳሌ   በአመት እስከ 25 ሚሊዮን ደንበኞችን እንዲያስተናገድ በአዲስ አበባ ኤርፖርት እየተገነባ ያለው  ተጨማሪ  የማስፋፊያ ተርሚናል በዚሁ አመት በ2017 ተጠናቆ ደንበኞቹን ለማስተናገድ ክፍት ይሆናል የሚለን ድረ-ገፁ በተጨማሪም ሀገሪቷ  ሌሎች ተጨማሪ 19 የአየር  ጣቢያዎችን /terminals/ በመገንባት የነበረውን 49 የመዳረሻ ክልል   ወደ  68  ከፍ በማድረግ ለመኪና መዳረሻ ምቹ ያልሆኑ ተራራማና በረሀማ ቦታዎች ላይ ጭምር አዳዲስ የሀገር ውስጥ የመዳረሻ ተርሚናሎችን ለመገንባት በአምስት አመቱ እቅዷ መሰረት እየተንቀሳቀሰች ለመሆኗ  ምስክር ነኝ ይለናል ።


እንደሚታወቀው  ኢትዮጵያ ሰንሰለታማ ኮረብታዎች የሚጎረብጧት አገር ብትሆንም  ነገር ግን እስከ አሁን በ100ሺ ኪ.ሜ የሚሰፈሩ መንገዶችን በመገንባት ከዚህ ቀደም በመንገድ ችግር ከእያንዳንዱ የሀገሪቱ የግንኙነት  መረብ  ተነጥለው ለነበሩ ቦታዎች ሀገራዊ ትስስር እንዲኖራቸው መልካም የሚባል  እድሎችን ፈጥራለች።  ሌላው  ኢትዮጵያ  ፍፁም አዲስ የሆነ አለምአቀፋዊ  ኢርፖርት በፈረንጅ በ2025ቱ የአምስት አመት እቅዷ ላይ ይፋ በማድረግ  ግንባታውን ትጅምራለች ሲል CIA በተስፋ ጠብቁ ይለናል።


በዚሁ በያዝነው  ወር አጋማሺ፦ መጋቢት 14/2017 ላይ ደግሞ  https፡//en.m.Wikipedia.org  ድረ-ገፅ CIA WORLD FACTBOOk ን ምንጭ አድርጎ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በየደረጃው፣ በአይነት በአይነቱ በቁጥር አሰላስሎ  በድረ-ገፁ ላይ እንደሚከተለው አቅርቦታል።
ኢትዮጵያ  በ2016   ወደ 67 ነጥብ 43 ቢልዮን ዶላር ጠቅላላ /ኖሚኒያል/ GDP በማስመዝገብ 70ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። በ2014  የ10 ነጥብ 2 በመቶ፥ በ2016 ደግሞ የ6 ነጥብ 5 በመቶ የGDP እድገት እንዲሁም በ2015 ጥናት መሰረት ደግሞ የ10 ነጥብ 1 በመቶ የዋጋ ግዥፈት ተመዝግቦባታል። ሌላኛው  IMF በ2016 ባጠናው መሰረት ይህ አመታዊ GDP  ለ99 ነጥብ 4  ሚልዮን ህዝብ  አመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ሆኖ  ሲሰራ 739 ነጥብ 4 ዶላር ወይም  ብር 16 ሺ 266 ብር ከ8 ሳንቲም ይደርሰዋል ይለናል፡፡፡


የአገሪቱ አመታዊ  የGDP እድገት  በየዘርፉ ሲፈተሽ፦   ግብርናው 40 ነጥብ 5 በመቶ በመሸፈን ከፍተኛ ድርሻ ቢኖረውም የአገልግሎት ዘርፉ ደግሞ ከግብርናው በላይ ተራምዶ  43 ነጥብ 3  በመቶ በመሸፈን ለኢኮኖሚው እድገት  ዎሳኝ ሚና ማስመዝገቡን የ2015 ጥናት ያሳያል ። ኢንዱስትሪውም ቢሆን  16 ነጥብ 2 በመቶ በመሸፈን  ጅምሩ ጥሩ በሚባል ደረጃ ተመዝግቧል።
ነገር  ግን በ2014 ጥናት መሰረት 29 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆነው  ኢትዮጵያዊ በቀን 1 ነጥብ 90 ዶላር  ወይም  በብር  41 ነጥብ 80 በማግኘት ከድህነት ወለል በታች ኑሮውን የሚገፋ ነው ሲል ጥናቱ ያሳያል።


በ2016 ጥናት መሰረት በሰው ሀይል አቅርቦት ኢትዮጵያችን 50 ነጥብ 97 ሚልዮን በመሽፈን 14ኛ ደረጃ ላይ  ተመዝግባለች። ነገር ግን በስራ  አጥ ቁጥር 17 ነጥብ 50 በመቶ  /እንደ 2012 ጥናት/  በመሸፈን 163ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። በተጨማሪም በ2016 ጥናት መሰረት  ኢትዮጵያ ውስጥ  ስራ /business/  ለመስራት ባለው ምቹ ያልሆነ  የቢሮክራሲ  ውጣ ውረድ ውጥንቅጥ ምክኒያት ሀገሪቱን በ159ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል።


ኢትዮጵያ  የ3 ነጥብ 163  ዶላር ቢልዮን ዶላር  ምርቶቿን፦ቡናን፥ ጫትን፥ ወርቅን፥ የቆዳ  ውጤቶችን፥ ከብቶችን እና የቅባት ምርቶችን  በውጭ ገበያ ትሸጣለች። በተቃራኒው ደግሞ አይሮፕላንና ማሺኖችን፣ ብረታብረቶችን፥ የኤሌክትሪክ ግብአቶችን፥ ነዳጅና ተሽከርካሪዎችን ኬሚካልና የማዳበሪያ ምርቶችን ጭምር  በ15 ነጥብ 87 ቢልዮን ዶላር ከውጭ ገበያ  ትገዛለች።


የኢትዮጵያን ምርቶች በመግዛቱ በኩል  ሲዉትዘርላንድ  14 በመቶ፥ ቻይና 11.7 በመቶ በመሸፈን ቀዳሚ ሲሆኑ አሜሪካ 9 ነጥብ 5 በመቶ ኔዘርላንድ  8 ነጥብ 8 በመቶ ሳውዲአረቢያ 5 ነጥብ 9 በመቶ እና  ጀርመን (2015 ጥናት መሰረት) 5 ነጥብ 7 በመቶ በመሸፈን ከ3 እስከ 6 ያለውን ደረጃ ይዘዋል።


በሌላ በኩል  ደግም ለኢትዮጵያ ምርቶቻቼውን  በማቅረቡ ረገድ  ቻይና 20 ነጥብ 4 በመቶ በመሸፈን በቀዳሚነት ደረጃ ምርቶቿን ለኢትዮጵያ ታቀብላለች። አሜሪካ 9 ነጥብ 2  በመቶ፥ ሳውዲአረቢያ 6 ነጥብ 5 በመቶ እና በ2015 ጥናት መሰረት  ህንድ 4 ነጥብ 5 በመቶ በመሸፈን ከ2 እስከ 4 ያለውን ደረጃ በመሸፈን ተቀምጠዋል።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
346 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 109 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us