“በአንድ ጠጠር….”

Wednesday, 03 May 2017 12:34

 

በደረጀ ባልቻ

መግቢያ

መንፈሳዊ ጉዞ ወደ …የሚል ጽሑፍ ያለባቸውና በብሔራዊው ሠንደቅ ዓላማችን አሸብርቀው መንፈሳዊ መዝሙር እያሰሙ የሚጓዙ አውቶቡሶችና ሚኒባሶች ስመለከት ብዙ ጊዜዬ ነው። የተለያዩ በዓላት ለምሳሌ እንደ ግሸን ማርያም፣ አክሱም ጽዮን፣ ሳማ ሰንበት፣ ዝቋላ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ፣ ቁልቢ ገብርኤል፣ ወዘተ ሲቃረቡ ይህ ሁኔታ በብዛት ይስተዋላል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በየሳምንታቱ የመጨረሻ ቀናት (ዓርብ ቅዳሜና ዕሁድ) ተመሳሳይ ሁኔታ ማየት የተለመደ እየሆነ መጥቷል።

ስለነዚህ መንፈሳዊ ጉዞዎች ብዙ ስሰማ ከቆየሁ በኋላ አንድ በቅርብ የማውቃት የሥራ ባልደረባዬ ስለ ዘብር ገብርኤል አወጋችኝ። የሰማሁት ነገር በጣም አስደነቀኝ፤ በጆሮዬ የሰማሁትን በዐይኔ የማየት ፍላጎትም አደረብኝ። ይህም ፍላጎቴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሲመጣ፤ ዛሬ ነገ ስል ጥቂት ጊዜ ከቆየሁ በኋላ እግዚአብሔር ሲፈቅድ ተሟላልኝ። መጋቢት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. መንፈሳዊ ጉዞ ወደ ዘብር ገብርኤል።

ከጉዞው አስተባባሪ ከወጣት ሔኖክ ጥላዬ በተሰጠኝ መረጃ መሠረት ለሦስት ቀናት ጉዞ የሚጠቅሙኝ ያልኳቸውን የቀንና የማታ አልባሳት፣ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ሸካክፌ ከጠዋቱ 12 ዓት ከ30 ደቂቃ እንድገኝ ከተነገረኝ ቦታ  ደረስኩ። በነገራችን ላይ አስተባባሪውን ወጣት ሳውቀው ጥቂት ጊዜ የቆየሁ ቢሆንም፤ መጀመሪያ የተዋወቅሁት አቡ በሚል ስሙ ነበር። በጉዞዋችንም ላይ ግማሹ አቡሌላው አቡላ ደግሞም ሌላው አቡዬ እያሉ ሲጠሩት ነበር የምሰማው። እኔም ከነዚህ በአንዱ ወይም በሌላው ስጠራው ከቆየሁ በኋላ፤ ይህን ጽሑፍ ሳዘጋጅ ነው ትክክለኛ ስሙን ለመፈለግ የተገደድኩት። ይህ የዓለም ስሙ ሲሆን፤ በጎበኘናቸው የተለያዩ ገዳማት እና አብያተክርስቲያናት ያሉትና ልክ እንደ ልጃቸው የሚያዩት አባቶች በክርስትና ስሙ ኃይለ ኢየሱስ እያሉ ነበር የሚጠሩት።

ወደ ጉዞው!

ደረጃ 1 የሆነው አውቶቡስ ከተነገረኝ ሰዓት 40 ደቂቃ ያህል ዘግይቶ ከተባለው ስፍራ ደረሰ። የዘገየበትን ምክንያት እረዳለሁና አልተበሳጨሁም። በቁጥር 60 የምንደርሰውን ተጓዦች አማካይ አማካይ ከሆኑ ቦታዎች አሰባስቦ ለመጓዝ ለዚያውም ካለው የከተማው የመጓጓዣ ችግር አንጻር፣ መዘግየት ቢፈጠር የሚያወቃቅስ አይደለም። ሁሉም ለበጎ ነው ብሎ ማለፍ።

ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ከሠላሳ ደቂቃ አውቶቡሱ ሲንቀሳቀስ፤ አስተባባሪው ስለጉዞው ማብራሪያ ሰጠ። ማብራሪያውም የጉዞውን ዓላማ፣ መዳረሻዎቹን፣ እንዲሁም በጉብኝቱ ወቅት ትኩረት የሚያሻቸውን ነጥቦች ያካተተ ነበር። የተከተለው መንፈሳዊ መዝሙርና ከተጓዦች መካከል በአንድ ወንድም የተሰጠ ትምህርት ሲሆን፤ በመቀጠልም ለምንጎበኛቸው ገዳማት እና አብያተክርስቲያናት መጠነኛ ድጋፍ ሊሰጥ የሚችል መባዕ ማሰባሰብ ነበር። ተጓዡን በማያጨናንቅ መልክ ፌስታል እንደ ሙዳየ ምጽዋት እየዞረ ጥቂት ገንዘብ ተሰባሰበ። ጉዞው ቀጠለ።

የመጀመሪያው መዳረሻ ከመነሻችን 130 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የሚገኘው ደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተክርስቲያን ነበር። ቤተክርስቲያኑን ከተሳለምንና ለምንሄድባቸው ገዳማት እና አብያተክርስቲያናት አገልግሎት የሚውሉ አንዳንድ ቁሳቁስ (እጣን፣ ጥላ (ድባብ)፣ ጧፍ፣ ዘቢብ፣ አትሮኖስ) የመሳሰሉት ከተገዙ (በግልም በአስተባባሪዎቹም)  በኋላ ጉዞው ቀጠለ። 180 ኪ.ሜ ላይ አስፋልት ደህና ሰንብት ብለን ከጣርማ በር ወደ ቀኝ ታጥፈን ፒስታውን መንገድ በመንፈሳዊ መዝሙር ታጅበን ነካነው። ሰዓቱ አምስት ሰዓት ከሠላሳ ይላል። ዕለቱ ዓርብ ነው። የምንሄድበት ዘብር ገብርኤልም ጸበል መጠመቅ ይጠብቀን ስለነበረ የምሳ ነገር አልተነሳም።

መንገዱ ወጣ ገባ፣ ጠመዝማዛና ፒስታ መሆኑ (የመኪናውን ፍጥነት ስለሚቀንሰው) ተፈጥሮን ለማድነቅና የሕዝቡን አሠፋፈር ለመታዘብ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል። አካባቢው በአብዛኛው ተራራማና ገደላገደል የበዛበት ነው። ያንን ሳይ በአንድ ወቅት ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የተጓዘ ጓደኛዬ የተናገረው ትዝ አለኝ። የአካባቢውን መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ ሲገልጽ ተራሮች ስብሰባ ተጠርተው የተቀመጡ ይመስላል ነበር ያለው። የሰሜን ሸዋውም ወደዚያው ይቀርባል። በመንገዳችን ላይ ካየናቸው ከተሞች ጎላ ብለው የሚታዩት መዘዞ እና ሞላሌ ናቸው። የቀሩት መንደሮች ወይም ደረቅ ጣቢያ የሚባሉ ዓይነት ናቸው። የገጠሩም ሕዝብ አሠፋፈር እጅግ የተበታተነ ሲሆን፤ ጥቂት የቆርቆሮ ክዳን ቤቶች በየተራራው ጥግ ተለጣጥፈው ይታያሉ። በዚህ ሁኔታ ነዋሪው በምን መልክ የመሠረተ ልማትና የዘመናዊው ሥልጣኔ ትሩፋት ተቋዳሽ ሊሆን እንደሚችል ግራ ይገባል።

ይህንኑ እያሰላሰልኩና በመንፈሳዊ መዝሙር እየተበረታታሁ፤ ሰዓቴ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ከሀያ ደቂቃ ሲያሳይ፤ ወገሬ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ደረስን። ከአውቶብስ ወርደን የጸበሉን አቅጣጫ ይዘን በእግራችን ነካነው። አንድ ሁለት መቶ ሜትር እንደተጓዝን የአካል ጥንካሬንና የዓላማ ጽናትን የሚፈትን ሁኔታ ገጠመን። ጫማ ማውለቅ፤ ከዚያም በግምት ወደ ሦስት መቶ ሜትር በላይ የሚሆን ርቀት ድንጋዩ ባፈጠጠ ገደላማ መንገድ በመጓዝ ጸበሉ ዘንድ መድረስና ወረፋ ጠብቆ መጠመቅ። የመልሱ ጉዞም የዚያኑ ያህል ከባድ ነበር።

በጽሑፍ ባላገኝም፤ ከአስተባባሪው ወጣት እንደተረዳሁት ዘብር ማለት መልስ ( ይጠብቃል) ማለት ነው። ወገሬ ቅዱስ ገብርኤል የተሰረቀ ወይም የጠፋ ንብረትን/ሀብትን ያስመልሳል። የታጣ ጤናን ይመልሳል ተብሎ ይታመናል። ይህም የሚሆነው እምነትን መሠረት ባደረገ ሁኔታ ነው። እንግዲህ ከላይ የተጠቀሰው መስዋዕትነት የሚከፈለው ይህንን በረከት ለማግኘት ነው። የተሳካላቸው ሰዎች እንደሚመሰክሩት መስዋዕትነቱ ቢያንስ እንጂ የሚበዛ አይደለም።

ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ፤ ምሳ ከቀኑ አስር ሰዓት ከሩብ ላይ ተበላ። በነገራችን ላይ፤ የመጀመሪያውን ቀን (ዓርብ መጋቢት 22 ቀን) ቀለባችንን (ምሳና እራት) ተጓዦች ለየራሳችን ቋጥረን የወጣን ሲሆን፤ የሁለቱን ቀናት፣ ማለትም ቅዳሜና ዕሁድ፣ ቀለባችንን የቻሉን የጎበኘናቸው ገዳማት እና አብያተክርስቲያናት አባቶች ናቸው። አይ ሲጥም! የመጣሙ ምክንያት ቅመማ ቅመሙ አይደለም። ወይንም በልማድ እንደሚባለው ምግብን የሚያጣፍጠው ረሀብ በመሆኑም አይደለም። የአባቶቹ ትህትና፣ መጥረብረብና ሰው በልቶ የሚጠግብ የማይመስላቸው ሁኔታ የምግብ ፍላጎትን ይከፍታል፤ ጣዕሙንም ያሳምረዋል።

ዘብር ገብርኤል ጸበላችንን ከተጠመቅንና ቤተክርስቲያኑን ከተሳለምን በኋላ፤ በማግስቱ እንደምንመለስ ቀጠሮ ይዘን እዚያው አቅራቢያ የሚገኘውን አቡነ ሀብተማርያም ቤተክርስቲያን ተሳልመን ከቀኑ በአስራ አንድ ሰዓት ለማደሪያችን ወደ ተዘጋጀው ወደ አቡነገብረመንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን አመራን። ከሠላሳ አምስት ደቂቃ ጉዞ በኋላ ቤተክርስቲያኑ ስንደርስ፤ አባቶች የመኝታ አዳራሾቻችንን አዘጋጅተው ይጠብቁን ነበር። ጓዛችንን ከመኪና አውርደን መኝታችንን ከዘረጋጋን በኋላ ቤተክርስቲያኑን ተሳልመንና መንፈሳዊ ትምህርት ተከታትለን፤ ከምሳ ያስተረፍነውን ቀማምሰን፤ የማግስቱ መርሐግብር ተነግሮን፤ ወደ መኝታ!!

በማግስቱ ቅዳሜ፣ መጋቢት 23 ቀን፣ በሌሊት መነሳት ነበረብን። ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ከሠላሳ ደቂቃ ተነስተን ኪዳን ካደረስን በኋላ፤ በአስራ አንድ ሰዓት ገደማ (11፡10) ወደ ወይን አምባ ቅዱስ ገብርኤል ተንቀሳቀስን። ከአርባ አምስት ደቂቃ ጉዞ በኋላ ከንጋቱ አስራ ሁለት ሰዓት ገደማ (11፡55) ወይን አምባ ቅዱስ ገብርኤል ደረስን። ሲነገር እንደሰማነው፣ ወይን አምባ ቅዱስ ገብርኤል ፈጣን ሰሚ ነው ይባላል። እንደ አባባልም ዘብር በዓመት ወይን አምባ በዕለት ይባላል። ወይን አምባ ኪዳን ካደረስንና ከተጸለየልን በኋላ ወደ ወገሬ ዘብር ቅዱስ ገብርኤል ተመለስን። በገዳሙ አባቶች ተጸልዮልን ከቀኑ አምስት ሰዓት ከሀምሳ ደቂቃ ከዘብር ተንቀሳቅሰን ከአስር ደቂቃ ጉዞ በኋላ እረትመት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ደረስን። እዚያም አጭር ጸሎት አድርሰን እንደገና ከሃያ ደቂቃ ጉዞ በኋላ ዳስአምባ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ደረስን። ኪዳን አድርሰን ተጸለየልንና ምሳ እዚያው በልተን ወደ ዳስአምባ ቅዱስ ጊዩርጊስ ገዳም  አቀናን።

ዳስአምባ ቅዱስ ጊዩርጊስ ገዳም እንደደረስን በተዘጋጁልን አዳራሾች መኝታችንን ዘርግተን ጥቂት ካረፍን በኋላ ወደ መንበረ ጽዮን ሰቅላዬ ቅድስት ማርያም ገዳም አቀናን። ጉዞው በመኪና ሳይሆን በእግር ነበር። አስተባባሪው በረከት እንድታገኙ አስቤ ነው ብሎታል። ጉዞው በእግር በመሆኑ ብቻ አይደለም። ሲኬድ ቀጥ ያለ ዳግትና በመልሱ ጉዞ ደግሞ መንፏቀቅ ይቀላል ( ይጠብቃል) የሚያሰኝ ቁልቁለት ነበረው። ይሁን፤ ለበርከት ነው።

ሰቅላዬ ማርያም አንድ ድንቅ ሥራ አየን። በአንድ ሰው (አባ ለአከ ማርያም በሚባሉ አባት) ጉልበት ብቻ በእጅ (በመሮና መዶሻ) የተፈለፈለ ዋሻ አየን። የዋሻው መግቢያ በጣም አጭርና ጠባብ ሲሆን፤ በእንብርክክ አልያም በደረት በመሳብ ካልሆነ ጎንበስ ብሎ ለመግባት ወገብን ይፈትናል። እኔ ሞክሬው ጭንቅላቴን ቧጦኛል። ስወጣ እንደ ሕፃናት ተንበርክኬ ዘለቅሁት። የመንግሥተ ሰማያት ተምሳሌት ነው ብለዋል አባ ለአከ ማርያም። አንዴ ከተገባ ውስጥ ለውስጥ ያሉት ክፍሎች አያስቸግሩም፤ ሳያጎነብሱ መንቀሳቀስ ይቻላል። እዚያ ውስጥ አጭር ጸሎት አድርገን ወደ ዳስአምባ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም ተመለስን።

በመጨረሻው ቀን (መጋቢት 24 ቀን) ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ተነስተን በዳስ አምባ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም እና እዚያው አጠገብ በሚገኘው የአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ቤተክርስቲያን ኪዳን አደረስን። ከዚያም በሐዋርያት ቤተክርስቲያን ጸሎት ከተደረገልን በኋላ የመስቀል ዳሰሳና ቅብዐ ቅዱስ የመቀባት መርሐግብር ተከተለ። በመስቀል ዳሰሳው ወቅት እርኩስ መንፈስ ያለበት ሰው ይለፈልፋል፣ ይወራጫል። የዚህ ዓይነቱ ሰው ፈውስ እንዲያገኝ በአባቶች ይረዳል። ከእኛ መሀልም ጥቂት ሰዎች ይህ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል። ቅብዐ ቅዱሱም ችግር አለብን ብለን ባመለከትነው የሰውነት ክፍሎቻችን ላይ ተቀብቶልናል።

ይህ ከሆነ በኋላ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ከሃያ ደቂቃ ተንቀሳቅሰን ሁለት ሰዓት ገደማ (1፡55) ግንድአጥሚት (ይጠብቃል) ማርያም ገዳም ደረስን። ስለ ስሟ ከተሰጠን ማብራሪያ እንደተረዳነው፣ ከገዳሟ ሕንጻ አጠገብ የበቀለ አንድ ዛፍ ሕንጻው ጣሪያ ላይ ጉዳት ያደርሳል ብለው ስለገመቱ፤ በወቅቱ የነበሩት ኃላፊዎች ዛፉ እንዲቆረጥ ይወስናሉ። ይህ በሆነ በማግስቱ ጠዋት ሲታይ ዛፉ ከሕንጻው ጣሪያ ላይ ወደውጭ ተጣምሞ ተገኘ። ከዚያን ጊዜ (1886 ዓ.ም) ጀምሮ ዛፉ ዛሬም ተጣምሞ ይታያል። ተዓምር ነው!

በዚያው ገዳም ከተጓዦች መካከል አንዱ ወንድም ለምእመናን ትምህርት ከሰጠና ለእኛም በአባቶች ከተጸለየልን በኋላ ደጀሰላም ገብተን ቁርሳችንን (ዳቦና ጠላ) አድርገን በመዝሙር አመሰገንን። ከሰማኋቸው መዝሙሮች ቀለል ያለችኝና የያዝኳት ይህቺው መዝሙር ነበረች።


2 ጊዜ

 

በላይነ ጸገብነ          

ሰተይነ ለወይን

ንሴብሆ ንሴብሆ  

ለእግዚአብሔር

ኧኸ

ንሴብሆ ንሴብሆ

ለእግዚአብሔር

በአማርኛ

2 ጊዜ

 

በላን ጠገብን

ጠጣን እረካን

እናመስግን እናመስግን

እግዚአብሔርን

ኧኸ

እናመስግን እናመስግን

እግዚአብሔርን

ይህ ከሆነ በኋላ በሦስት ሰዓት ከአርባ አምስት ደቂቃ ከግንድ አጥሚት ማርያም ተንቀሳቅሰን በአምስት ሰዓት ምስካበ ቅዱሳን አርብአሐራ መድሃኔዓለም ገዳም ደረስን። ይህ ገዳም የሚገኘው በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት፣ በመንዝ ማማ ምድር ወረዳ፣ ልዩ ስሙ ይገም ተብሎ በሚጠራ ቦታ ነው። ከአዲስ አበባ 246 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ይገኛል። የገዳሙ ታሪክ እንደሚያስረዳው ምስካበ ቅዱሳን ማለት የቅዱሳን ማረፊያ ማለት ሲሆን፤ አርብአሐራ ማለት ደግሞ አርብአ አርባ (ቁጥርን) ሐራ ወታደር ማለት ነው። ይህም ስለሃይማኖታቸው የተሰዉትን ቅዱሳን እና ሰማዕታት ተጋድሎ ለማመልከት የተሰጠ ስም ነው። በስፍራው በርካታ የቅዱሳን ዐፅሞች ይገኛሉ። ገዳሙ ብዙ ገድል አለው። የገዳሙን አጭር ታሪክና ግብረ ተዐምራት የያዘውን መጽሐፍ እንዲያነቡ እጋብዛለሁ።

ከይገም ምሳችንን በልተን በሰባት ሰዓት ከሃያአምስት ደቂቃ ተንቀሳቀስን። ከሁለት ሰዓት ጉዞ በኋላ ጣርማ በር ስንደርስ፤ ከሁለት ቀናት በፊት ትተነው የሄድነው አስፋልት እንደተዘረጋ ጠበቀን። ጉዞው ቀጠለ፤ ወደ አዲስ አበባ። በመጨረሻም ከቀኑ አስራሁለት ሰዓት ገደማ (11፡55) አሌልቱ ቅዱስ ገብርኤል ደርሰን ከተሳለምን በኋላ ጉዞው ቀጥሎ፤ ተጓዡ በየአድራሻው መውረድ ሲጀምር፤ እኔም ከልጄ ጋር ተቀጣጥረን ይጠብቀኝ እነበረበት ካራ አካባቢ ከአውቶቡሱ ተሰናብቼ ወረድኩ።

መዝጊያ

በደረስንባቸው ገዳማትና አብያተክርስቲያናት በሙሉ የሰማናቸው ተመሳሳይ ችግሮች ናቸው። ገዳመቱና አብያተክርስቲያናቱ ለምእመናን አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ከፍተኛ ችግሮችን ተቋቁመው ነው። ብዙ ነገሮች አልተሟሉላቸውም። ካህናቱ አገልግሎት የሚሰጡት በግብርና ሥራቸው ላይ ደርበው ነው። መተዳደሪያ ደመወዝ የላቸውማ! ስለዚህ አልፎ አልፎ ግዴታና ጫና እንደሚታከልበትም ተረድተናል።

አስተባባሪው የዚህ ዓይነት ጉዞ ባዘጋጀ ቁጥር ከተጓዦች የሚሰበስበው ገንዘብ ለነዚህ ገዳማትና አብያተክርስቲያናት መደጎሚያ የሚውል ነው። እኛም ያዋጣነው ገንዘብ ለዚሁ ተግባር ሲውል ተመልክተናል። በየቦታው ጉብኝታችንን ስናበቃና ተመራርቀን  ልንለያይ ሲሆን ስጦታው ይበረከታል። እንደታዘብኩት ያዋጣነው ገንዘብ ለእኛ በተናጠል ምንም ማለት ላይሆን ይችላል። ለእነርሱ ግን ትልቅ ትርጉም አለው። አንድ የችግር ቀዳዳ ይደፍናል። ለሚሰጡት አገልግሎትና ለሚያደርጉት ተጋድሎ የሞራል ስንቅ ይሆናቸዋል። በእርግጥ ሊረዱ ይገባል! የሰው ብቻ በቂ ሊሆን ስለማይችል እግዚያብሔር ይርዳቸው!

ጉዞው አስደሳች፣ አስተማሪና አነቃቂ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በአንድ ጉዞ ከአስር በላይ ገዳማትን እና አብያተክርስቲያናትን መጎብኘት ቀላል ነገር አይደለም። በልማድ በአንድ ጠጠር ሁለት ወፍ ይባላል። እርግጥ ነው፤ ወፎቹ ባያልቁ ጥሩ ነበር። ምሳሌው ግን ለዚህ ዓይነቱ ጉዞ በጣም ይረዳል። ጉዞውን ያስተባበረውን ወጣት ከልብ አደንቃለሁ፤ አመሰግናለሁ። ወጣት ነው። እንደ አንዳንድ የዕድሜ ጓደኞቹ ከተማ ላውደልድል አላለም። የተለያዩ ሱሶች ተገዢ ሆኖ እራሱን ፋይዳቢስ አላደረገም። አግባብ ባልሆነ መንገድ በመገለባበጥ በረከት የሌለው ጥቅምና ሀብት ላጋብስ አላለም። ለጋ ዕድሜውን ሌሎችን በመርዳት ለበጎ ተግባር አውሎታል። ዕድሜና ጤና ይስጠው!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
453 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 86 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us