"ዕድሜዋን ሙሉ ለጠፋሁት ልጇ ላለቀሰችልኝ እናቴ የሚፈሰውን የዛሬውን የአንድ ቀን እንባዬን ከንቱ አታድርጉብኝ እባካችሁ ...?!"

Wednesday, 03 May 2017 12:37

 

በተረፈ ወርቁ
[የሂፖው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ አውግስጢኖስ]

 

ብፁዕ አባታችን የላኩልኝን የመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን የኖረችውን የኢትዮጵያዊቷን የቅድስት ኤፍጄኒያን ታሪክ ሳነብ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሥነ መለኮት ዩኒቨርሲቲ የሚማር አንድ ጓደኛዬ በአንድ ወቅት በስጦታ ያበረከተልኝ መጽሐፍ ውስጥ ያነበብኩት አንድ ድንቅ የሆነ ታሪክ ትዝ አለኝ። በምሥራቅውያን እና በምዕራባውያን ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያት አባቶች/አበው ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለውና የቅድስና ማዕረግ የተሰጠው የ፬ኛው መቶ ክ/ዘመን እውቅ የሥነ መለኮት ሊቅ፣ ፈላስፋ፣ ታላቅ ሰባኪ፣ አስተዳዳሪ፣ ጸሓፊ፣ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ተሟጋችና የመናፍቃን መዶሻ "Apologetics Father" በመባል የሚታወቀው ቅዱስ አውግስጢኖስ የተጻፈው "the Conefession" የሚለው መጽሐፍ ነው።


ይህ "ኑዛዜ" በሚል ቅዱስ አውግስጢኖስ ስለ ራሱ የጻፈው መጽሐፍ በተለይ በምዕራብ ዓለም ባሉ የሥነ መለኮት ምሁራንና ክርስቲያኖች ዘንድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ በስፋት የተነበበና በብዙ ቋንቋዎች የተተረጎመ መጽሐፍ ነው። ቅዱስ አውግስጢኖስ "the Conefession" ከሚለው እውቅ መጽሐፉ በተጨማሪ በክርስትናው ዓለም የሚታወቅበት ሌላኛው ድንቅ መጽሐፉ ደግሞ "the City of God" በሚል የጻፈው መጽሐፍ ነው።


ይህ ፈላስፋ፣ የንግግር አስተማሪ፣ ጸሐፊ፣ በሮማ፣ በግሪክና በሰሜን አፍሪካ በነበሩ ታላላቅ ትምህርት ቤቶች ውስጥ መምህር የነበረው አውግስጢኖስ የክርስትና ሃይማኖትን አስተምህሮ የሚነቀፍና በክርስቲያኖች ላይ አብዝቶ የሚሳለቅ ሰው ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ አጥባቂ የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ የነበረችው እናቱ ቅድስት ሞኒካ ልጇ፣ አውግስጢኖስ ክርስቲያን እንዲሆንላት በብዙ እምባ፣ ለቅሶና ተማሕፅኖ፣ በጸሎት ሰትተጋ የነበረች ሴት ነበረች። ይህች ሴት በተደጋጋሚ የሮማ ሊቀ ጳጳስ ወደሆነው ወደ ቅዱስ አምብሮስ በመሄድ እንባውን እያዘራችና ደረቷን እየደቃች ልጇን አውግስጢኖስ ክርስቲያን እንዲያደርግላት ትማጸነው ነበር።


ለበርካታ ጊዜያት በተደጋጋሚ ወደ እርሱ እየመጣች በእንባዋን እያጎረፈች ልጇ የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ እንዲሆን ስታለቅስለት፣ ስትማፀንለት ለነበረችው ለቅድስት ሞኒካ ቅዱስ አምብሮስም:- "አንቺ ሴት ይህን ያህል እንባ ያፈሰስሽለት፣ በጸሎት የተማፀንሽለት ልጅ ጠፍቶ የሚቀር ይመስልሻልን ... በፍጹም ... አመፀኛው ልጅሽ አንድ ቀን በእግዚአብሔር ፍቅር ልቡ ተሸንፎ - እውነት፣ ሕይወትና መንገድ ወደሆነው ወደ ጌታችንና መድኋኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይመጣል ...።" በሎአት ነበር። ቅድስት ሞኒካም በዚህ በሊቀ ጳጳሱ በቅዱስ አምብሮስ ቃል በመጽናናት፣ አንድ ቀን ልጇ ወደ ክርስትና ሃይማኖት እንደሚመጣ ተስፋ በማድረግ በፍቅር እንባ ዘወትር ጠዋት ማታ አንድ ልጇ ከዓመፃ መንገዱ ተመልሶ ክርስቲያን ይሆንላት ዘንድ አምላኳን ትማፀን ነበር።


ቅድስት ሞኒካ በአንድ ሌሊትም በመኝታዋ ላይ ሳለች ያያችውን ሕልም እጅግ ለምታፈቅረው ለልጇ እንዲህ ስትል ነገረቸው፤ "ልጄ ሆይ ዛሬ ሌሊት በታላቅ ባሕር ላይ ሆነን ይመስለኛል፣ ታዲያ በዛ ባሕር ላይ እኔና አንተ ተለያይተን በተሳፈርንበት መርከብ ላይ በመካከላችን በተዘረጋው ረጅም መሸጋገሪያ ድልድል ላይ በርጋታ እየተራመድክ እኔ ወዳለሁበት መርከብ ላይ ስትመጣ አየሁ። ልጄ ሆይ ክርስቲያን ልትሆንልኝ ነው መሰል ብላ አለችው። አውግስጢኖም:- "እናቴ ሆይ ይህ ፈጽሞ ሊሆን አይችልም። ምናልባት አንቺ እኔ ወዳለሁበት መርከብ ትመጪ እንደሆነ ነው እንጂ ... እኔ ለዘላለም አንቺ ወዳለሽበት መርከብ ወይም አንቺ እንደምትይው ወደ ክርስትና ሃይማኖት  በፍጹም ልመጣ አልችልም አላት።"


ይህን ተስፋውን የሚንድ፣ እምነቷን የሚፈታተንና የእናትነት ፍቅሯን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ የሚመስል ምላሽን ከልጇ የሰማችው ቅድስት ሞኒካም ... የልጇን እጅ አጥብቃ ይዛ እንባዋ እየጎረፈ፣ በፍቅር ቃል "አምላኬ አደራህን ልጄን ተስፋው አንተ ብቻ ነህ፣ እኔ በአንተ ጥበብ ወለድኩት፣ አንተ ግን ሥጋህን ቆርሰህ፣ ደምህን በመስቀል ላይ አፍስሰህ ቤዛ ሆንከው ... በዘላለም ፍቅርህም ወደድከው ..." በማለት እንደተናገረች አውግስጢኖስ የሕይወት ታሪኩን በጻፈበት "the Conefession" መጽሐፉ ውስጥ ገልጾታል።


ቅዱስ አውግስጢኖስ በእናቱ ጸሎት፣ እንባ በእግዚአብሔር ፍቅር ወደ ክርስትና ሃይማኖት ከመጣ በኋላም ... የሂፖ በአሁኑ የዓለም ካርታ የሰሜን አፍሪካ/የአልጄሪያ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ነበር። ልጇ አውግስጢኖስ ወደ ክርስትና ሃይማኖት መምጣቱን ያየችው ቅድስት ሞኒካ እንዲህ ስትል ጸለየች፣ " ... አምላኬ፣ መድኋኒቴና ተስፋዬ ሆይ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ በዚህ ምድር ላይ ለመኖር እፈልግ የነበረው ልጄ የአንተ ደቀ መዝሙር/ክርስቲያን ሆኖ ለማየት ነበር። ይህን ደግሞ ለሀጢአተኞች ባለ ፍቅርህ ለልጄ ምሕረትን ይቅርታን አደረገህለት። ልጄ የአንተ ሆኗል ... አሁን በዚህ ምድር ላይ ለመኖር የሚያጓጓኝ አንዳች ነገር የለምና ጌታዬ፣ አምላኬ ሆይ ባሪያህን ወደ አንተ ወሰደኝ፤" ብላ ጸለየች።


ቅድስት ሞኒካም ከጥቂት ሕመም በኋላ በ56 ዓመቷ በሰላም አረፈች። ከትውልድ ሀገሯ ርቃ በንዳድ ሕመም በመኝታዋ ላይ ተኝታ ለነበረችው እመቤት ሞኒካን የአውግስጢኖስ ወዳጆች፣ እንዴት ከአገሯ ርቃ በዚህ ሥፍራ የመሞቷ ነገር እንደማያስጨንቃት ጠይቋት እርሷም ... እንዲህ በማለት መለሰችላቸው:- "ለእግዚአብሔር ሩቅ የሆነ ምንም የለም፣ በዓለም ፍጻሜ ከየት ሥፍራ ያስነሳኝ ይሆን ወይ ብዬ ቅንጣት ታህል አልፈራም።" ይህንም ብላ አንቀላፋች።


ቅድስት ሞኒካ ባረፈችበት ጊዜም የአውግስጢኖስ ወዳጅ የሆነው ሰባኪውና ሮማዊው ባለ ቅኔ ኢቮዲዩስ የፍቅር እንባውን እያፈሰሰ በገናውን አንስቶ ከመዝሙረ ዳዊት:- "አቤቱ ጌታ ምሕረትንና ፍርድን አቀኝልሃለሁ።" የሚለውን ዜማ አዜመ። በዛ ያሉትም ሁሉ ይህን መዝሙር አብረውት በአንድነት አዜሙ። ቅዱስ አውግስጢኖስ እናቱ በሞት፣ በአካል በእርሱ የተለየችበትን ቀን የተሰማውን የሐዘን ስሜት በተመለከተ "the Confession" በሚለው መጽሐፉ እንዲህ ሲል ገልጾታል።


እናቴ የመጨረሻ እስትንፋሷን ተንፍሳ ዓይኖቿን ስትከድን ... ጥልቅ የሆነ ሐዘን ልቤን ሰንጥቆ ገባ፣ ወደ እንባም ተለወጠ። በተመሳሳይ ጊዜ የዓይኖቼን እንባ ልቦናዬ ሲገታና የጎረፈውን እንባዬን መልሼ ስውጥ፣ ስቃይ እንዴት እንዴት ተናንቆኝ እንደነበር! ነገር ግን እናቴ የመጨረሻ እስትንፋሷ እንደወጣች ልጄ አድኦዳቱስ እሪታውን መቆጣጠር አቅቶት ነበር። ግን ሁላችንም ስናጽናናው በጥቂቱ ተረጋጋ።


ቀስ በቀስም አገልጋይህ ለአንተ ራሷን በመስጠት ታደርግ የነበረው የፍቅር አገልግሎት፣ ለእኛ የነበራት ፍቅርና እንክብካቤ በማስታወስ ወደ ቀደመ ትዝታዬ መመለስ ጀመርኩ። ጌታዬ ኢየሱስ ሆይ ... ለራሴና ለእርሷ በአንተ ፊት ማልቀስ ለእኔ እጅግ ጣፋጭ ነበር። አግቼው የነበረውን እንባዬን እንደፈቀደው እንዲወርድ፣ ከልቤ ጥልቀት እንዲወጣ፣ እንዲፈስ ትውኩት። በእነርሱም ዕረፍትን አገኙ። የእንባ ዘለላ በፊቴ ያለማንበባቸው ትርጉሙ ለነቀፋ እንዳበቃቸው እንደነዚያ ሰዎች ሳይሆን የአንተ ጆሮዎች ለእኔ ቅርብ ነበሩና። ነገር ግን አሁን በዚህ መጽሐፌ ለአንተ እናዘዛለሁ። አቤቱ ጌታዬ! የፈቀደ ያንበበው፣ የፈቀደም እንደፈለገ ይተርጉመው።


ለጥቂት ጊዜ ለዓይናቼ ዛሬ ሞታ ያየኋት ያቺ እምዬ፣ በአንተ ፊት እንድኖር፣ ለብዙ ዓመታት በፍቅር ለእኔ ያነባችልኝ፣ ለእናቴ ያለቀስኩበት ሰዓት ጥቂት ሆኖ ታይቶት ሀጢአት እንደሠራሁ ሆኜ ቢያገኘኝ አይሳለቅብኝ ... ይልቁንስ በክርስቶስ ወንድሞች ሁሉ አባት፣ በአንተ ላይ ስለፈጸምኩት ሀጢአት ግን ያልቅስልኝ ... እናም ዕድሜዋን ሙሉ ለጠፋሁት ልጇ ላለቀሰችልኝ እናቴ የዛሬውን የአንድ ቀን እንባዬን ከንቱ አታድርጉብኝ እባካችሁ ...?!"


የሂፖው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ አውግስጢኖስ በክርስትናው ዓለም በእነዚህ ጥልቅ መንፈሳዊ አባባሎቹ/ንግግሮቹ  ይታወቃል፤ እነሆ በጥቂቱ፤
"ጌታ ሆይ፣ ለአንተ ፈጠረኸናልና፣ ልባችንም በአንተ እስክታርፍ ድረስ እረፍትን አታገኝም፤"
"... ጌታዬ ሆይ ይህ ኑዛዜዬ እርግጠኛ ባልሆነ ሕሊና ሳይሆን፣ እንደሚያፈቅርህ እርግጠኛ በሆነ ሕሊና ነው። ልቤን በቅዱስ ቃልህ ሰይፍ ወጋኻት እኔም አፈቀርኩህ። ሰማይም፣ ምድርም፣ በውስጣቸው ያሉ ሁሉ እነሆ ላፈቅርህ እንደሚገባ ይነግሩኛል። ሰዎች የሚያመካኙትን እንዲያጡ ለሁሉም ከመናገር አይቆጠቡም ... ነገር ግን ከሁሉ በላይ በዘላለማዊ ፍቅርህና በማያመረመረው ምሕረትህ የምትምረውን ሁሉ ልትምረው፣ የምትራራለትንም ሁሉ ልትራራለት ትፈቅዳለህ ...።"


ለማውጫ ያህል የፍቅር፣ የእንባ ሴት ስለሆነችው የቅዱስ አውግስጢኖስን እናት ቅድስት ሞኒካ መሠረት አድርገን ስለ እንባና የእንባ ሰዎች ስለሆኑ ቅዱሳን ጥቂት ነገር ላንሳ። እማሆይ ማዘር ተሬዛ እንዲህ ይላሉ፣ "የፍቅር ሰዎች የእንባ ሰዎች ናቸው።" የቤተ ክርስቲያናችን መጽሐፈ መነኮሳት፣ ማር ይስሐቅ ... በወንጌሉ እንደተጻፈላት የጌታዋን እግር በእንባዋ እንዳጠበችው ማርያም በፍቅር እንባቸው የሚታወቁ በርካታ ቅዱሳን አባቶችና እናቶች እንዳሉን ይነግረናል። በቤተ ክርስቲያናችን መጽሐፈ መነኮሳት አስተምህሮ መሠረትም ከዐሥሩ ማእረጋት መካከል እንባ አንዱ የፍቅር ስጦታ እንደሆነ ይነግረናል።


በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ልበ አምላክ ንጉሥ ዳዊት፣ አይሁዳዊው ነቢዩ  ኤርምያስ፣ (ነቢዩ ኤርምያስ ስለ ኢየሩሳሌምና ሕዝቡ ጥፋት - ምነው ዓይኖቼ የእንባ ምንጭ በሆኑልኝ ሲል የጸለየና በመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ዘንድ "የእንባ፣ የሐዘን፣ የሰቆቃ ሰው፣ አልቃሻው ነቢይ" በሚል ቅጽል ስያሜ ይታወቃል።) ነቢዩ ዳንኤል፣ ሊቀ ነቢያት ሙሴ፣ ፍቁረ እግዚእ ቅዱስ ዮሐንስ፣ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ... የእንባ ሰዎች ነበሩ። ዛሬ በአብዛኞቻችን የደረት  ኪስና በእህቶቻችን ቦርሳ ውስጥ የማይጠፋውን ውዳሴ ማርያምን የደረሰውና ዛሬ በእርስ በርስ ጦርነት የፈራረሰችው፣ ዜጐቿ በምድር ሁሉ በስደት የተበተኑባት፣ ሕፃናቷ በራብ አለንጋ የሚገረፉባት ሀገረ ሶርያ፣ የሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም እጅግ የእንባ ሰው ነበር። የሕይወት ታሪኩን የጻፈለት የቤ/ክ አባት ስለ ታላቁ አባት ቅዱስ ኤፍሬም እንባ ሲናገር:-


"... When I start to remember his floods of tears I myself begin to weep, for it is almost impossible to pass dry eyed through the ocean of his tears. There was never a day or night ... when his vigliant eyes didn't appeared bathed in tears ..."


እመቤታችን፣ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከላይ በምሳሌነት ከጠቀስናቸው የእግዚአብሔር ሰዎች ሁሉ በተለየ ዘመኗን ሁሉ በፍቅር እንባ ስለ ሰው ልጆች ሁሉ ምሕረት ስታነባ፣ ስታለቅስ የኖረች ቅድስት፣ ክብርት ሴት፣ ዘላለማዊ ድንግል ናት።  


አምላካችን፣ ጌታችንና መድኋኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋዕለ ስብከቱ ለቅድስቲቱ ከተማ ለኢየሩሳሌም እንባውን ማፍሰሱን፣ ማልቀሱን ወንጌላዊው ሉቃስ እንዲህ ጽፎታል።
"... ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት፥ እንዲህ እያለ። ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል ...።"


ብርሃነ ዓለም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በእስያ የነበረውን የሦስት ዓመት የወንጌል አገልግሎት ፈጽሞ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ በተዘጋጀበት ጊዜ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችንና ቀሳውስትን አስጠርቶ በፍቅርና በእንባ እንዲህ አላቸው:-
"እኔ ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ አውቃለሁ። ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሠጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ። አሁንም ለእግዚአብሔርና ያንጻችሁ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ መካከል ርስትን ይሰጣችሁ ዘንድ ለሚችል ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋለሁ።" [ሐዋ. 20፥17-38።]
ሰላም! ሻሎም!

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
272 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 87 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us