የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስን ሕልዉና በመፈታተን ሕዝቡን ከዓላማዉ ማስቆም አይቻልም

Wednesday, 10 May 2017 13:33

 

ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ/ኦፌኮ የተሰጠ መግለጫ

ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸዉ ሰዎች ተሰባስበዉ የሚከተሉትን አመለካከት ለማራመድ ፓርቲ ማቋቋቸዉ ኦፌኮ የመጀመሪያም አልነበረም፤ የመጨረሻም አይሆንም። የኦሮሞ ሕዝብን ብቻ ሳይሆን ተመሳሳይ፣ መሠረታዊ ዓላማና ፍላጎትያላቸዉን ለመደገፍ በተለያየና በተራራቀ አከባቢ የምንኖርዜጎች የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ሕገ መንግስት በሚፈቅደዉ መሠረት በኦፌኮ ሥር ተሰባስበን የቆምንለትን የሕዝብ ዓላማ በሠላማዊ መንገድ በማራመድ ላይ እንገኛለን። በኦሮሚያ ክልል ብቻም ሳንወሰን ሕዝባዊ ዓላማዉ ከሚያስተሳስረን ከሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፓርቲዎች ጋር በመሰባሰብም፤ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ በመመስረት መሠረተ ሰፊ ለሆነዉ ሕዝባዊ ዓላማ በመታገል ላይ እንገኛለን። ትግላችንና ዓላማችን ሕዝባዊ አድርገን በመታገላችን ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ድጋፍ ተችረናል።

እያራመድነዉ ያለዉ ዓላማ ሕዝባዊ በመሆኑ ብቻ እየተጓዝንበት ያለዉ ጎዳና ሁሉ አልጋ በአልጋና የተለሳለሰ እንዳልሆነ እናዉቃለን። የጎዳናዉ መሻከር ምክንያቱ ብዙም የተወሳሰበ ሳይሆን የሕዝብን ጥያቄና ዓላማ አንግበን በመጮሃችን ለኢህአዴግ አልተመቸዉም።

ይህንን መግለጫ እንድናወጣ የተገደድነዉ ማንንም ለመክሰስ ወይም ለመወንጀል ሳይሆን መላዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፤ በተለይም የኦሮሞ ሕዝብ በኦፌኮ ላይ የደረሰዉንና ሊደርስበትም ይችላል ብለን ሥጋት የሆነን ሕዝባችን እዉነታዉን እንዲያዉቅ ለማድረግ ነዉ።

በኢትዮጵያ ምርጫ ሕግ መሠረት በየአምስት ዓመቱ የሚካሄደዉ የምርጫ ዉጤት የታሰበዉ ሳይሆን ቀርቶ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚታገሉ ዜጎች የሚደበደቡበት፣ አካላቸዉ የሚጎድልበት፣ መኖሪያ ቤታቸዉ ከሕግ አግባብ ዉጭ የሚደፈርበት፣ ዜጎች ከመኖሪያ ቄያቸዉ የሚሰደዱበትና የሚንገላቱበት የሚታሰሩበት በግፍ የሚገደሉበት አዉድማ ሆኗል። የዚህ ገፈት ቀማሾች ከሆኑት ዉስጥ ደግሞ የኦፌኮ አባላትና ደጋፊዎች ሁሉ የዚህ ግፍ ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸዉ። የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ የተሻሉ ዕጩዎችን አቅርቦ እያለ ዕጩዎቻችን አልተመረጣችሁም መባላቸዉ ብቻ ሳይሆን፤ ከምርጫዉ በኋላም ኢህአዴግን ለምን ተቃወምክ በሚል ሰበብ በየዞኑ የሚገኙ የኢህአዴግ ካድሬዎችና ካቢኔዎች በአባሎቻችን ላይ ዘግናኝና አሰቃይ ዕርምጃ ወስደዋል፤ የኦፌኮ ቢሮዎችን በመስበር ሰነዶችንና ገንዘብ ዘርፈዋል።

የኢህአዴግ ሰዎች በሕዝብና በተቃዋሚ ፓርቲዎች አቋም ላይ በነበራቸዉ የተሳሳተ እይታ ኦፌኮን ጨምሮ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሕልዉና አጥፍተናል ብለዉ በማመናቸዉ፤ ሰብአዊ መብትን በመድፈር፣ የሕግ የበላይነትን በማጥፋት መልካም አስተዳደር ማጉደላቸዉን፣ ኪራይ ሰብሳቢነታቸዉን፣ ሙሰኛነታቸዉንና የመሬት ቅርሚትን በስፋት ቀጠሉበት። እንደአሰቡት ሳይሆን ሕዝባዊ መነሳሳት አጋጠማቸዉ።

ሕዝባዊ መነሳሳቱ ያሰጋቸዉ የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሳይቀሩ እየሆነ የነበረዉ ዝርፊያና ጉድለቶች በመንግስት ሌቦች መፈጸሙን አደባባይ ወጥተዉ ቢናገሩም በጣም የዘገየ ከመሆኑ የተነሳ ሕዝቡ ጆሮ ሰጥቶ ሊያዳምጣቸዉ አልፈለገም። ከፍተኛ የኢህአዴግ ባለሥልጣናቱም ቢሆኑ ላደረሱት ጥፋት በትክክል ይቅርታ ለመጠየቅ ሳይሆን የሥልጣን ዕድሜያቸዉን ለማራዘም ስለሆነ፤ ሕዝቡ ሠላማዊና ሕጋዊ ጥያቄዎችን በመያዝ አደባባይ ከመዉጣቱ አስቀድሞ፤ ኦፌኮም በበኩሉ ወደፊት ሊደርስ የሚችለዉን ችግርና አደጋ በመረዳት ከወዲሁ ተገቢ የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ አገሪቷን ለሚያስተዳድረዉ ፓርቲና መንግስት አሳዉቆ ነበር።

ነገር ግን ጩኸታችን ሰሚ ጆሮ አላገኘም። ይሁን እንጂ መንግስትና ገዥዉ ፓርቲ ያደረጉት ነገር ቢኖር የሕዝብን ጥያቄ ወደጎን በመተዉ አመራርን በመቀየርና ካቢኔዎችን በማዘዋወር ጥልቅ ተሃድሶ አደረጋለሁ በማለት አሁን አገሪቷን የገጠማት የመልካም አስተዳደር ጉድለት፣ ሙስና፣ የመሬት ቅርምት፣ የወጣት ሥራ አጥነት ነዉ ብሎ የማዘናጊያ ሐሳቦችን በመከተል ጉዞዉን ቀጠለ። ይህ በኛ እምነት የተያዘዉ አካሄድ አሁን አገራችንን የገጠማትን ችግር ይፈታል ብለን አላመንም።

በሠላማዊ መንገድ መብቱን ለማስጠበቅ በወጣዉ ሕዝብ ላይ ታጣቂ ኃይል በማሰማራት መፈክር ብቻ ይዞ ባዶ እጁን በወጣዉ ሕዝብ ላይ በማስተኮስ የሕዝብን ጥያቄ ለማፈን ሙከራ አድርጓል። እነሆ በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች እንዲሞቱ፣ እንዲቆስሉ፣ እንዲሰደዱና እንድንገላቱ ተደርገዋል። ይህ እንዳለ ሆኖ ይህንን ሁሉ ጥፋት በሕዝብ ላይ የፈጸሙና ያስፈጸሙ ሰዎች ላይ የተወሰደ አንዳች ዕርምጃ የለም። እንዲያዉም የተወሰደዉ ዕርምጃ ትክክልና ተመጣጣኝ መሆኑ ለሕዝባችን ተገልጿል። በግልባጩ የሆነዉ ግን አብዛኛዉ የኦፌኮ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች፣ የሌሎች ፓርቲዎች አባላትና ንፁሐን ዜጎች በተገኙበት ቦታ ተይዘዉ ዘብጥያ እንዲወርዱ ተደርገዋል። በቆላማ ሥፍራዎች ላይ የሹፈት ሥልጠና እንዲወስዱ ተደርገዋል። በነዚያ የማጎርያ ቦታዎች ላይ ሕይወታቸዉ ያለፈ ስለመኖራቸዉ ሕግና ታሪክ ያወጣል ብለን እንጠብቃለን። የተደረጉትን ሕገ ወጥ ተግባሮችን ሕጋዊ ለማሰኘት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አዉጆ ኢዴሞክራሲያዊ አገዛዙን ለመቀጠል እያመቻቸ ነዉ።

ከኢህአዴግ ኢዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የተነሳ ሊመጣ የሚችለዉን አስቀድሞ የተነበየዉ ኦፌኮ፣ አመራሩና አባላቱ ሕዝባዊ መነሳሳቱን እንደአባባሰ ተቆጥሮ የኢህአዴግ መንግስት አንዱ አካል በሆነዉ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት ቀርቧል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም እንደተለመደዉ የቀረበዉን ሐሳብ በመደገፍና በማፅደቅ በዚህ ጉዳይ ላይ የሰጠዉ ዉሳኔም እጅግ አድርጎ አሳዝኖናል። በሪፖርቱ ዉስጥ፤

$11.  ተጠያቂ ይሆናሉ የተባሉት የመንግስት ተቋማትና መሪዎቻቸዉ በስም ተለይተዉ አልተጠቀሱም። ይህ ባልሆነበት የመንግስት ተቋማትና መሪዎቻቸዉ ተጠያቂ የሚሆኑበት ምንም ስልት የለም።

$12.  የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ራሱ የመንግስት አንዱ አካል ስለሆነ በሪፖርቱ ገለልተኛነት ላይ እምነትየለንም።

$13.  ገለልተኛ ነኝ የሚለዉ ኮሚሽን ኦፌኮን በሕግ ፊት ተጠያቂ ለማድረግ ሲያመቻች፤ ኦፌኮ ራሱን እንዲከላከልም ሆነ ንፅህናዉን እንዲያስረዳ ጥያቄም ሆነ ሁኔታዉን የመግለፅ ዕድልአልተሰጠዉም። ሪፖርቱ የቀረበለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ይህንን አንስቶ አልጠየቀም። የአንድ አካል ገለልተኛነት ዝቅተኛ መለኪያ በጠያቂነትም ሆነ በተጠያቂነት የሚገኙ አካላትን ማነጋገር ይሆናል። ስለሆነም የኮሚሽኑን ገለልተኛነትና የምክር ቤቱን ኃላፊነት ጥያቄ ዉስጥ የሚከት ሆኖ አግኝተናል። የሰብአዊ መብት ኮሚሽኑ ሪፖርቱን የሠራዉ በሰብአዊ መብት ኮሚሽንነቱ ሳይሆን በኢህአዴግ ባለሥልጣንነቱ እንደሆነ ያሳብቅበታል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንደሚለዉ ሳይሆን ኦፌኮ ሕዝባዊ መነሳሳቱን አላባባሰም። ኦፌኮ ያንን የሕዝብ ማዕበል በዚያ ዓይነት ሁኔታ ለማንቀሳቀስ አቅሙን የለዉም። ኦፌኮ ያደረገዉና ወደፊትም ሕልዉናዉ ተጠብቆ የሚቆይ ከሆነ የሚያደርገዉ ነገር ቢኖር ማንም አካል ከሕገ መንግስታዊ አግባብ ዉጭ ሥልጣን መያዝም ሆነ ሥልጣን ላይ መቆየትንፈፅሞ የማይፈቅድና ሕገ መንግስታዊ አግባብን ረግጦ የሚመጣ አካል ካለም ሕዝባችን ለመሸከም የማይሻ መሆኑን አስምረን እየገለፅን በጀመርነዉ ሠላማዊ የትግል ጉዞየምንቀጥል መሆኑን እንገልፃለን። አባባላችንና አካሄዳችን ጠመንጃ ለለመዱት ቀላል ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ሕዝባችን በጦርነት የተሰላቸ ስለሆነ ከሠላማዊ ትግላችን ጎን ይቆማል ብለን እናምናለን። ይህ ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር ሳይሳካ ቢቀርና ሕዝባዊ አመፁ ወደአፈሙዝ የሚዞር ከሆነ፤ ዲሞክራሲያዊ አካሄድን ያልተቀበለዉ ኢህአዴግ ተጠያቂ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በእሬቻ በዓል ላይ ሰዎች ገደል ገብተዉ ሞቱ ብሎ አሳዛኝ ሪፖርት ጨምሮ አቅርቧል። ሰዎች ተራ እንስሳ ባለመሆናቸዉ ካልተገደዱ በስተቀር በተለይም ለዓመታዊ ክብረ በዓላቸዉ ተሞሽረዉ በሄዱበት አካባቢ ገደል አይገቡም። ገደል መግባት ካስፈለጋቸዉ ደግሞ ከመላ ኦሮሚያ ተሰባስበዉ ቢሾፍቱ ድረስ መምጣት አያስፈልጋቸዉም። የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ/ኦፌኮ ይህ በዓል ሠላማዊ የሕዝብ በዓል ስለሆነ፤ ፖለቲካዊ ገፅታ ማላበስ አሰፈላጊ አለመሆኑን አስቀድሞ አስጠንቀቆ እያለ፤ የኢህአዴግ መንግስት በሠላም በዓሉን ለማክበር የወጣዉን ሕዝብ ከሰማይና ከምድር በሰራዊት ማስከበብና ያን የሚያህል ጉዳት ማድረስን ማዉገዝ ሲገባዉ፤ የኮሚሽኑ የሰጠዉ እማኝነት ወገናዊነቱ ለማን እንደሆነ ግልፅ አድርጓል።

ኢህአዴግ፤ ዛሬም ሥር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንደመፍታት፣ የመብት ጥሰቶችን እንደማስቆም፣ በመንግስት ኃይሎች ለተጎዱ ዜጎች ካሳ እንደመክፈል፣ የታሰሩ ዜጎችን እንደመፍታት፣ ሙሰኞችንና ኪራይ ሰብሳቢዎችን ለሕግ እንደማቅረብ፣ ካድሬዎቹን አደብ እንዲገዙ እንደማድረግ፣ የፍትህ አካላትን ከሥራ አስፈፃሚ ተፅዕኖ ሥር ነፃ እንደማድረግለዲሞክራሲያዊ አሰራር እንደመዘጋጀት፣ የሕግ የበላይነትን እንደማክበር፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንደማንሳት፣ የመሳሰሉትን ከመፈጸምችግሮችን በተቃዋሚ ፓርቲዎች (ኦፌኮ፣ ሰማያዊና የጌድኦ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት) ላይ ማላከክን መርጧል።

የሕዝቦችን ድህነት ለማጥፋትና ዘላቂ የሆነ ልማት ለማካሄድ የሚቻለዉ የሰዎች ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሲከበሩ፣ የሕግ የበላይነት ሲሰፍን፣ ሁሉን አሳተፊ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ምክክሮችና ድርድሮች ሲካሄዱ፣ የዜጎች ነፃነት ሲከበርና የሕዝብ ጥያቄ በአግባቡ ሲፈታ ነዉ።

የኢህአዴግ መንግስት ኦፌኮ ላይ አነጣጥሮ እንደነበረ የሚያስረዱት ገና በየዞኑና በየወረዳዉ የሚገኙትን የፓርቲ ጽህፈት ቤቶቻችን በመንግስት ኃይሎች ሲዘጉ፣ ሲዘረፉ ከሁሉም ደግሞ የኦፌኮ መሪዎች ከያሉበት እየተለቀሙ ሲታሰሩ፣ ኦፌኮ ላይ ከየአቅጣጫዉ ዛቻ ሲዘነዘር፤ የኦፌኮን ሕልዉና እየተፈታተኑ መሆኑን ተረድተናል። ሕዝቡም ይህ ሥጋት እንደሚኖርና እንድንጠነቀቅ አሳዉቆናል። ነገር ግን የኦፌኮን ሕልዉና መፈታተን ሕዝባዊ ትግሉን ሊቀለብስ እንደማይችል አስቀድመን ስንናገር የነበረ ስለሆነ በሕዝባዊ ኃላፊነት ከማሰብ በስተቀር ብዙም አላስጨነቀንም።

ምክንያቱም የኦፌኮን አመራር ከሊቀመንበሩ ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ ያሉትን ወደእስር ቤት የጎተተ ሥርአት ለራሱ ፖለቲካ ጥቅም ካልሆነ በስተቀር ለኦፌኮ ሕልዉና ይጨነቃል የሚል እምነት አልነበረንም። ከዚህ በፊትም ስናደርግ እንደነበረዉ ሁሉ የኦፌኮ ሕልዉና አደጋ ላይ ቢወድቅ እንኳን ይግባኝ የምንለዉ ለሕዝባችን ነዉ። የተገደሉ፣ የታሰሩና የተንገላቱ ወገኖቻችን የሕዝባችንን ፍላጎት ለጠባብ የግል ጥቅም እንዳልሰጡ ሁሉ ቀሪዎችም ይህንን ለማድረግ ቃላችንን ደግመን እናድሳለን። ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የዉሳኔ ሐሳብና ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዉሳኔ አንፃር የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ/ኦፌኮ ሕልዉና አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ግልፅ ማድረግን እንወዳለን። ነገር ግንየኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ/ኦፌኮ ሕልዉናን በመፈታተን ሕዝቡን ከዓላማዉ ማስቆም እንደማይቻል ለሚመለከታቸዉ ሁሉ በአጽንኦት እናስገነዝባለን።

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ

ፊንፊኔ፣ ሚያዚያ 30 ቀን 2009

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
219 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 84 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us