የኢትዮጵያ ጎዳናዎች ከልመና ነፃ የሚሆኑት መቼ ነው?

Wednesday, 17 May 2017 12:57

 


በዮሴፍ አለሙ

 

ኢትዮጵያ ላለፉት አስርት አመታት እያንዳንዳቸው 30 ሚልዮን ዶላር ያስመዘገቡ 30 አዳዲስ ባለሀብቶች የተፈጠሩባት ሀገር ሲል አስቀምጧታል። በሁለት አሀዝ ኢኮኖሚያዊ እድገትም ወደፊት እየተራመደች ለመሆኗ በደንብ ተመስክሮላታል።


ነገር ግን በሌላ በኩል ደግሞ ከ29 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ህዝብ ከድህነት ወለል በታች ማለትም በከፋ ድህነት ውስጥ ነው ይለናል አለም ባንክ በ2015 ጥናት። ከዚህ ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት በ2011 አጠናሁ ብሎ ባወጣው ሪፖርት መሰረት "በድፍን" አገሪቱ ከ150ሺ እስከ 200ሺ የሚሆኑት ዜጎች በጎዳና ላይ ሕይወታቸውን የሚገፉ ወጣቶች ናቸው፡፡ በልመና የሚተዳደሩ የእኔ ቢጤ ደካሞችን ሳይጨምር። በተጨማሪም በዚሁ ጥናት መሰረት በመዲናችን አዲስ አበባ ብቻ ከ50 ሺ እስከ 60ሺ የሚደርሱ የጎዳና ልጆችን ቆጥሬአለሁ ሲል መንግስት በራሱ ሰነድ ላይ አስቀምጦታል።


ነገር ግን የተባበሩት መንግስታት የአለም ዩኒሴፍ በ2011፦ ሀገራችን ኢትዮጵያ አቅመ ደካሞችን ሳይጨምር ከ600ሺ በላይ የሚሆኑት የጎዳና ልጆቿ "መንገድ አዳሪ" መሆናቸውን በጥናት አረጋግጫለሁ ይለናል። በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ደግሞ ከ100ሺ በላይ የሚሆኑት አሳዳጊ አልባ ልጆች መንገድ ላይ በችጋር አለም ህይወትን የሚገፋ ናቸው፤ በዩኒሴፍ ጥናት መሰረት። ምክኒያቱ ደግሞ ወላጆቻቼው ደካሞችና በሽተኞች ፥አለዛም ደግሞ የመተዳደሪያ ገቢያቸው በጣም ዝቅተኛ የሚባል በመሆኑ ወይ' ደግሞ ወላጆቻቸው ከእነ አካቴው በሞት የተለዩአቸው በመሆናቸው ምክንያት ይህን አሰልቺ የጎዳና ህይወት ሊገፉት ተገደዋል ሲል ዩኒሴፍ ይገልፃል።


አስኪ አንድ ነገር በጨረፍታ ታዝብን እንቀጥል፦ ከላይ በሀገራችንም ሆነ በከተማችን አዲስ አበባ የሚኖሩ ጎዳኒስት ልጆችን አስመልክቶ በመንግስት በኩል የተቀመጠው የቁጥር መረጃ ከዩኒሴፍ ጥናታዊ መረጃ ጋር ሲነፃፀር ለምን ያን' ያክል ሰፊ የቁጥር ልዩነት ተፈጠረ? ደ'ሞስ ለመረጃ ያክል የትኛውን ማመን ይቀላል? መገመት የምንችል ይመስለኛል፦ በእኔ ሀሳብ መንግስት ገመናውን በትክክል አደባባ ላይ ያወጣል የሚል ግምት የለኝም። በዩኒሴፍ በኩል ደግሞ የገመና ጉዳይ ሳይሆን የሚያስጨንቀው ጎዳና ላይ ቁርና ፀሀይ ለሚያሳቅቃቼው ልጆች ህይወት መስጠቱ ላይ ነው። ዓላማውም ዘመድ አልባ ለሆኑ ታዳጊ ልጆች ዘመድ መሆን ነው። ታዲያማ በዩኒሴፍ በኩል የተቀመጠው የቁጥር መረጃ ተቀባይነት ያለው አይመስላችሁም? ያም ሆነ ይህ ትዝብት ለመውሰድ ያክል አነሰውት እንጅ ጉዳያችን የቁጥር መሸዋወዱ ላይ አይደለም።


ይልቅ ዋናው ትኩረታችን መሆን ያለበት፦ መች ነው በኢትዮጵያ ምድር የልመና ስራና ልማድ የሚወገደው? መች ነው የከተሞቻችን ጎዳናዎች ከልመና መድረክ ነፃ የሚሆኑት? መቼ ነው በየስርቻው ወድቀው ለሚያጣጥሩ ሰዎች ዘላቂ መፍትሄ የሚፈየድላቸው? መንግስትስ በቅርቡ ምን አቅዶ ይሆን? የሚለው ላይ ነው።

 

ኤልሻዳይ /አዲስ እራይ ማሰልጠኛ ተቋም/


እንደሚታወቀው ከዚህ ቀደም መንግስት ለታዳጊ የጎዳና ተዳዳሪ ወጣቶች በኤልሻዳይ ማሰልጠኛ ተቋም በተደጋጋሚ የስልጠና እድል አመቻችቶ እንደነበር የሚካድ አይደለም። መልካም ከሚባሉት የቅርብ ጊዜ ትውስታዎች መካከል አንዱ ነው ለማለት ያስደፍራል። ምክኒያቱም በዚህ ተቋም ውስጥ የትምህርት እድል ያላገኙ ወጣቶች በሚፈልጉት ሙያ፥ የሙያና የአቅም ግንባታ ስልጠና ስነ ልቦናዊ ትምህርትን ጨምሮ ጥሩ እድል አግኝተው እንዲሁም ከስልጠና መልስ በሰለጠኑበት የሙያ መስክ በልዩ ልዩ ተቋማት ተመድበው እራሳቸውንም ሀገርንም እንዲጠቅሙ መደረጉ ድንቅ ጅማሮ ነበረ።


እናም ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በተመደቡበት ቦታ ስራቸውን አክብረው ታግለው በመስራት ጥሩ ደረጃ ላይ የደረሱ ጥቂት የማይባሉ የጎዳና ወጣቶችን በብዙ ድርጅቶች ውስጥ መታዘብ ችለናል፦ በደብረዘይት ኢንጅነሪንግ ብረታ ብረት ፋብሪካ፣ በወንጂ ስኳር ፉብሪካ፥ በደብረ ብርሀን ማሺኒግ ፋብሪካ፥ በጣና በለስ፥ በህዳሴው ግድብ እና በአጠቃላይ በሀገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ልዩ ልዩ ድርጅቶች ውስጥ ብዙ የኤልሻዳይ ፍሬዎች ይገኛሉ። ኤልሻዳይ ከጎዳና ላይ አንስቶ ዶዘር፣ ግሬደር፣ ትርክተር፣ ክሬን የሚያንቀሳቅሱ ኦፕሬተሮችን፥ የገልባጭ መኪና ሹፌሮችን ጨምሮ እንዲሁም ልዩ ልዩ ቴክኒሻኖችን በማፍራት የብዙ ታዳጊ ወጣቶችን ህይወት በመለወጥ መልካም የሚባል ጅማሮ እያደረገ ይገኛል።


ነገር ግን ይህ የምስጉኖቹ የሙያ ቤት ኤልሻዳይ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ወጣቶችን ከወደቁበት ጎዳና አንስቶ አፋር-አዋሽ 40 ድረስ ወስዶ የሀገር ሀብት በጀት ተደርጎበት፣ በስንት ድካም ካሰለጠነ በኋላ ከጥቂቶቹ በቀር ብዙዎቹ ሰልጣኝ ወጣቶች በተሰማሩበት ቦታ ብዙም የረባ ስራ ሳይሰሩ፥ ራሳቸውንም ሳይጠቅሙ ከምድብ ቦታቸው ጠፍተው ተመልሰው ወደ ነበሩበት የጎዳና ሕይወት ተመልሰዋል፡፡ ይህ ወጣቶቹ በቂ የሆነ የስነልቦና ዝግጅት ሳይኖራቸው ወደአዲስ ሕይወት እንዲገቡ መደረጉን አመልካች ሲሆን በአብዛኛው በመንገዶች ድልድይ ስር ተዝረክርከው የምናያቸው የጉዳና ልጆች በመንግስት ክትትልና ድጋፍ ማነስ ኤልሻዳይ ያመቻቸላቸውን መልካም እድል ረግጠው የመጡ ለመሆናቸው ከራሳቸው ከልጆቹ አንደበት ሰምተን እርግጠኛ መሆን እንችላለን።


በከተማችን አዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ በተለይ ደግሞ ቦሌ መድሃኒያለም ዙርያ እና አድዋ ፓርክ አካባቢ የሚኖሩ የጎዳና ወጣቶች በኤልሻዳይ "አዲስ እራይ ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ" ሰልጥነው በተለያየ የሙያ ዘርፍ ሙያ ያላቸውና አልፎ አልፎም አንዳንዶቹ ባለማወቅ ስልጠና አቋርጠው የወጡ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ በቅርፃቅርፅ አንዳንዶቹ ደግሞ በሹፍርና፥ በኦፕሬተር፣ በቴክኒሻን አውቶ እንዲሁም በስኳር ፋብሪካ ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ፥ ሌላኛዎቹ ደግሞ በልዩ ልዩ የጥገና መስክ እና በሌሎችም ሙያዎች ተክነው በስራ ቦታ ተሰማርተው የነበሩ ናቸው። ነገር ግን ለምን ወደ ጎዳና ህይወት እንደተመለሱ ስጠይቃቸው አብዛኛዎቹ ከስልጠና መልስ መንግስት ወደ ስራ ሲያሰማራቸው የምድብ ቦታቸውን ባለመውደድ ምክንያት፥ የቅጥር ደመወዛቸው ከድርጅት ድርጅት፥ ከቦታ ቦታ ሰፊ የሆነ ልዩነት መኖሩ ፍትሀዊ ያልሆነ የደመወዝ አከፋፈል ስርዓት በሚል ሰበብና ጭራሽ አንዳንድ የምድብ ቦታዎች ላይ በጣም አነስተኛ ደመወዝ ይከፈላቸው ስለነበር እንደሆነ ይናገራሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ በሰለጠኑበት ሙያ ቀርቶ በሌላ ባለመዱት የሙያ ዘርፍ ሲመድቧቸው ምድባቸውን ባለመቀበል ወደ ጎዳና የተመለሱ ናቸው።


የተወሰኑት ደግሞ ሩቅ ማየት ባለመቻላቸው ምክንያት የስልጠና ቦታቸውን/አፋር አዋሽ-40 አሚባራ ወረዳ/ከመጀመሪያው ባለመውደድ ስልጠናውን አቋርጠው ጠፍተው የወጡ መሆናቸውን ያስረዳሉ። በተለይም በስራ መስክ ሲሰማሩ ደግሞ በምድብ ቦታቸው ላይ የመንግስት ክትትልና ድጋፍ ባለመኖሩ ምክንያት ሀሳባቸውን ሊረዳ የሚችል፥ ስነ-ልቦናቸውን ሊጠብቅ የሚችል መሪ ባለመኖሩ ምክንያት ድጋሚ ጎዳናን እንድንመርጥ ተገደናል ይላሉ።


ያም ሆነ ይህ፥አሁን ይህ የጎዳና ህይወት በጣም አንገሽግሾናል፥ እጅጉን አንገላቶናል፤ ባለማወቅ ነው እንጅ በኤልሻዳይ መኖር መልካም ነበረ፤ ባለመረዳት ህይወታችንን አበላሽተናል፤ ያን መልካም አጋጣሚ ማበላሸት አልነበረብንም። መንግስት ድጋሚ ይህንን የኤልሻዳይ የትምህርትና የሙያ እድል ለአራተኛ ጊዜ ቢያመቻችልን አሁንም በተስፋ አራተኛውን ዙር እየጠበቅን ነው። መንግስት ይህን እድል በድጋሚ ቢያመቻችልን የትም ቦታ በየትኛውም ደመወዝ በተመደብንበት ቦታ በቀጥታ በሙያችን ለመስራት ፈቃደኞች ነን ሲሉ ያነጋገርኩዋቸው የጎዳና ልጆች ቁጭታቸውን ይናገራሉ።
በተጨማሪም መስራት ለማይችሉት አቅመ ደካማ በልመና ለሚተዳደሩ ሰዎች ደግሞ በየዘርፉ እየስሩ ካሉ መንግስታዊ ያልሆኑ ሀገር በቀል እና ኢ-አገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር መንግስት ከጎናቸው በመቆም ይበልጥ አጠናክሮ በመስራት እና ራሱም መንግስት የአንበሳውን ድርሻ ወስዶ የደካሞች መጦሪያ ተቋማትን እንደ ሰለጠኑት አለማት በመክፈት አቅመ ደካሞች ቀሪ ሕይወታቸውን በሠላም ኖረው፣ ሲያልፉም ጧሪ ቀባሪ እንዲያገኙ በማድረጉ በኩል መንግስት የማያወላዳ ኃላፊነት አለበት።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
308 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 102 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us