ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት በሀላባ ብሔረሰብ

Wednesday, 07 June 2017 14:17

 

በደጀኔ ደንደና

 

 

ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሀገር እንደመሆኗ በብዙ ባህላዊ ዕሴቶቿ ትታወቃለች። ከነዚህ ባህላዊ ዕሴቶች መካከል ሀገረሰብ የዳኝነት ሥርዓቶች ረጅሙን ታሪካዊ ጉዞዎችን በማድረግና አስቸጋሪ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ ለዚህ ትውልድ መድረሱን ስንመለከት ባህላዊ ዕሴቶቻችን ምን ያህል ጠንካራ እንደነበሩና ዘመን ተሻጋሪነታቸው አግራሞትን የሚፈጥሩ ናቸው። የጥንካሬያቸውም ትልቁ ምስጢር ደግሞ በዋናነት ግንባር ቀደም ተጠቃሹ የባህሉ ባለቤት የሆነ ህዝብ ሲሆን፤ ለባህላዊ ዕሴቶቹ ያለው ፍቅር፣ ክብር፣ ታዛዥነት፣ ከታላላቆች መማር፣ የተማረውንም ለሌሎች ማስተላለፍ ወዘተ. በመሆኑ ከዘመን ዘመን ተሻግሮ ለዚህ ትውልድ እንደ ዱላ ቅብብሎሽ ማድረሱ የባህሉን ባለቤት ጠንካራነት የሚገልፅ ነው።

 

የሀገራችን ህዝቦች ባህላዊ ዕሴቶች ለአብሮ መኖር፣ ለሰላምና አንድነት፣ ለፍቅርና መቻቻል ከዚህ ባለፈ ለህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ስለመሆናቸው እሙን ነው። ከዚህ የተነሳ ሀገራችንን በሌሎች ሀገሮች ዘንድ በቱባ ባህላዊ ዕሴቶቿ እንድትታወቅ ከማድረጋቸው ሌላ ከመልካም ተምሳሌትነታቸውና ተሞክሮዎቻቸው ሌሎች እንዲማሩና እንዲወዱ በር የከፈተ መሆኑን እንረዳለን። በተለይ ባህላዊ የዕርቅ አስተዳደሮች መንግስት ለተለያዩ ፀጥታ ጉዳዮች የሚያውለውን የፋይናንስና የሰው ኃይል ከመቆጠባቸውና ከመቀነሳቸው ባለፈ በቱሪዝም ዘርፍም እያበረከቱ ያሉት አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ስለሆነም በዚህ አጭር ጥናታዊ ጽሁፍ የሀላባን ብሔረሰብ ባህላዊ ዳኝነትና የጥቁር ዕርድ ሥነ-ሥርዓት ያለውን አጭር ቅኝት ከብዙ በጥቂቱ እንመለከታለን።

 

በጥናቱ ሂደት መረጃዎች የተሰበሰቡት በመስክ ምልከታ (field observation)፣ በቃለ-መጠይቅ (Interview) እና በተመረጠ የቡድን ውይይት (Focus Group Discussion) ነው።

 

ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት በሀላባ ብሔረሰብ

ባህላዊ የዕርቅ ሂደቱ ከመጀመሩ በፊት ከተለያየ አቅጣጫ የመጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የጐሣ መሪዎች፣ የእምነት አባቶች እና ሌሎች ተሳታፊዎች የዕለቱን የዳኝነት ሥርዓት ለመጀመር ሁኔታዎች ምቹ መሆናቸውንና አለመሆናቸውን እርስ በርስ መረጃዎችን የሚለዋወጡበት ሥርዓት “ዱዱቦ” ተብሎ ይታወቃል። በዚህ የመረጃ ልውውጥ ሁሉም የሰማውን ያየውን ሁሉ ለዕርቅ ለተሰበሰበው ጉባኤ ተጨባጭና እውነትነት ያላቸውን መረጃዎችን ይሰጣል። በዚህ የመረጃ ልውውጥ እንደ ትልቅ ጉዳይ መነሳት ያለባቸው ለምሳሌ ስለ ሀገር ሰላምና ፀጥታ፣ የአየር ንብረት፣ የግብርና ሥራ፣ የቤተሰብ ሁኔታ፣ የጐሣዎች ጉዳይ፣ የሴቶች፣ የሕፃናትና የወጣቶች ጉዳይ፣ የአጐራባች ህዝቦችና ድንበር አካባቢ ያለው ወቅታዊ መረጃዎችና የመሳሰሉት ጉዳዮች ይነሳሉ።

 

በዚህ መልኩ መረጃዎችን ከተለዋወጡ በኋላ የዕለቱን የዳኝነት ሂደት ለመጀመር ምቹ ሁኔታ ካለ ይቀጥላል። ነገር ግን ከተሰጡት መረጃዎች ውስጥ የዕለቱን የኦገቴ ሴራ እንዳይቀጥልና የዳኝነት ሥርዓቱን አደጋ ውስጥ የሚከት መረጃ ከሆነ ወይም ሌላ ከዕለቱ አጀንዳ በላይ በጣም አስቸኳይና አንገብጋቢ ጉዳዮች አንዳንድ ጊዜ ስለሚፈጠሩ ሴራው የዕለቱን አጀንዳ ለሌላ ጊዜ ለማስተላለፍ ይገደዳል። በብሔረሰቡ ባህል መሠረት እንዲህ ዓይነቱ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ካየ በቀነ ቀጠሮ የዕለቱን አጀንዳ ያስተላልፉና እጅግ አጣዳፊና አንገብጋቢ የሆኑ ጉዳዮች በኦገቴ ሴራው መታየት ይጀምራሉ። ወይም ችግሮቹ ወደተከሰቱበት አካባቢ በመንቀሳቀስ የተፈጠረውን ጉዳይ በማጣራት ችግሮቹ ዕልባት እንዲያገኙ ይደረጋል።

 

በብሔረሰቡ ማንም ግለሰብ ትንሽ ወይም ትልቅ ጥፋት ካጠፋ በኮርማ ይቀጣል። ኮርማ መጥራት የብሔረሰቡ ወግና ልማድ ነው። ይህ “ዎርጃሞ” ተብሎ ይታወቃል። የኮርማ መቀጮ በብሔረሰቡ ባህል ቋሚ እንስሳ ወይም ጥሬ ገንዘብ ሊሆን ይችላል። በአጠቃላይ ዎርጃሞ መቀጮ ወይም የኮርማ ቅጣት እንደ ማለት ነው። በብሔረሰቡ በኮርማ መቀጣት ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ የተለመደና አሁንም እየተሰራበት ያለ ጠንካራ ባህል ነው። ማንም በጥፋተኝነት የተፈረጀ ሁሉ ኮርማ ይቀጣል። በዳይ ወይም ጥፋተኛ ግለሰብ ኦገቴ ፊት ቀርቦ ስለጥፋቱ ያምናል። ለዕርቅ የተሰበሰበው ዕድምተኛ ይህ ግለሰብ ጥፋት አጥፍቶ ይኸው በከበረው ኦገቴ ፊት ቀርቧልና ምን ይደረግ? ተብሎ ሲጠየቅ ተሰብሳቢው በአንድ ድምፅ ይቀጣ ይላል። የኦገቴ መሪው ምን ይቀጣ ብሎ ተሰብሳቢውን ይጠይቃል። በመቀጠል ተሰብሳቢው ጥፋተኛው በመጀመሪያ ዋስ ይጥራ ይላል። ጥፋተኛው ግለሰብ ለዕርቅ ከተሰበሰቡት ውስጥ ለዋስትና ይሆነኛል ብሎ ያመነበትን አንዱን ግለሰብ ይጠቁማል። ለዋስትና የተጠራው ግለሰብም ዋስትናውን መቀበል አለመቀበሉን ይጠየቃል። መቀበሉን ሲያረጋግጡ ጥፋተኛው ግለሰብ ኮርማ እንዲቀጣና ቅጣቱን ካልከፈለ ግን ዋሱ እንደሚከፍል ካሳሰቡ በኋላ ወደ ዋናው ጉዳይ በማለፍ ስለ ተከሰተው ግጭትና ስለደረሰው ጥፋት መመልከት ይጀምራሉ። የጥፋት አይነቶቹ ቀላል ይሁኑ ከባድ ሁሉም የዕርቅ ሂደቶች የሚጀመሩት በዚህ መልኩ ይሆናል።

 

በኮርማ ላይ የሚጨመር ሌላ ተጨማሪ መቀጮ በባህሉ ይኖራል። ይህ “ወደፋ” በመባል ይታወቃል። ይህም የማር ቅጣት ነው። በብሔረሰቡ አንዳንድ ቀለል ያሉ የጥፋት አይነቶች በማር ክፍያ የሚያልቁ ናቸው። ለምሳሌ በቤተሰብና በጐረቤት አካባቢ የሚነሱ ተራ አለመግባባቶች፣ የሴቶችና ህፃናት ግጭቶችና ታላላቅ አባቶችን አለማክበርና የመሳሰሉት ግጭቶችን የአካባቢው ሽማግሌዎች ጉዳዩን አቅልለው በመፍታት ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ግለሰብ ማር እንዲቀጣ ያደርጋሉ። የማር ቅጣቱም አንድ ሙሉ እንስራ ሆኖ ግማሹን በብርዝ መልክ ጥፋተኛው ግለሰብ ለዕርቅ ሥርዓቱ የወጡትን ሽማግሌዎችና የተበዳይ ቤተሰብን በማጠጣት የሚቀጣበት ሂደት ይሆናል። በመጨረሻም ሽማግሌዎቹ በሁለቱ ወገኖች በበዳይና በተበዳይ ላይ ከዋንጫ ብርዝ እየተጎነጩ እንትፍ እያሉ ይመርቋቸዋል።

 

በብሔረሰቡ የወንጀል ድርጊት በፈፀመ ግለሰብ ላይ ባህላዊ የጥፋተኝነት ውሳኔዎች ከመተላለፋቸው በፊት ጥፋተኛው ግለሰብ ዋስ እንደሚጠራ የታወቀ ሲሆን ይህ የዕርቅ ሂደት በብሔረሰቡ ዘንድ “ሩበቴ” ተብሎ ይታወቃል። ይህም የሆነበት ምክንያት ለግለሰቡ ለማናቸውም ጉዳዮች ጥፋተኛውን በሚመለከት ኃላፊነትን የሚወስድ ሰው የግድ ስለሚያስፈልግ ነው። ወንጀል ፈፃሚው ካመለጠ ወይም የተላለፈውን የቅጣት አይነት በጊዜና በሰዓቱ የማይከፍልና የማይፈጽም ከሆነ በቀላሉ ዋሱ ስለሚጠየቅ ነው። ጥፋተኛውም ግለሰብ ዋስ (ሩበቴ) የሆነለትን ግለሰብና ቤተሰቡን ችግር ውስጥ ላለመክተት ብሎ ለባህላዊ የዕርቅ ውሳኔዎች ሁሉ ተገዥና ታዛዥ ይሆናል።

 

በቤተሰብ፣ በቤተዘመድ፣ በጎረቤት፣ ጐሣ ከጐሣ፣ አንድ ጎሣ ከሌላ ጎሣ እንዲሁም ከአጐራባች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር ድንገት ሳይታሰብና በስህተት የተፈጠረ የግድያ ድርጊትን በብሔረሰቡ በባህላዊ የዳኝነት ሥርዓቱ /ኦገቴ/ የሚፈታበት የዕርቅ ሂደት “ጉዳ” ይባላል። በዚህ በጉዳ ሥርዓት ከገዳይ የጥቁር ዕርድ ብቻ ይጠበቅበታል።

 

“ጉማ” አንድ ግለሰብ ሆን ብሎ አስቦበትና አቅዶ በቂም በቀል የግድያ ድርጊትን ከፈፀመ በኦገቴ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት አንድ መቶ (100) የቁም ከብቶች የሚቀጣበት የባህላዊ የፍርድ ሂደት ነው። ምንም እንኳን አንድ መቶ የቁም ከብቶች ለአንድ ሰው ከአቅም በላይ የሚሆንበት ጊዜ ቢኖርም የገዳዩ የቅርብ ቤተዘመድና ጐሣ የቁም ከብቶችን በማዋጣት ይተባበሩታል። ምክንያቱም ገዳዩ ችግር ውስጥ ሳይገባ በፊት ለሌሎች ችግር የደረሰ በመሆኑ ዛሬ እንዲህ ያለ ችግር ውስጥ ገብቶ እንዴት ዝም እንላለን የሚል የመተባበርና የመተጋገዝ ባህሉ በብሔረሰቡ ዘንድ የነበረና ያለ ስለሆነ የተላለፈበት የቅጣት ውሳኔ በዚህ መልኩ ይከፍላል። ከብቶቹ በዋናነት ጊደሮችና ላሞች ይሆናሉ። ምክንያቱም የደረሰው በደል አስከፊ በመሆኑ ላሞችና ጊደሮች ወላድና የሚራቡ በመሆናቸው የሟች ቤተሰብን ሞራል ይጠብቃል፤ ሊካሱ ይችላሉ ተብሎ ስለሚታመን ቅጣቱ በዚህ መልክ ይወሰናል። በሌላ መልኩ በባህሉ እንደ ጥፋቱ ቅለትና ክብደት አንድ ጥፋተኛ ግማሽ ጉማ ወይም ሩብ ጉማ የሚከፍልበት ሁኔታ ይኖራል።

 

ሆን ተብሎ በቂም በቀል፣ ድንገትና በስህተት /ጉማና ጉዳ/ ለሚፈፀሙ የግድያ ድርጊቶች ሁሉ ለዕርቅ ሂደቱ የጥቁር ዕርድ ሥርዓት ይፈፀማል። ጥቁር መልክ ያለው እንስሳ የሚመረጥበት ዋናው ምክንያት በሟች ቤተሰብም ይሁን በገዳይ ቤተሰብ በኩል የደረሰው ነገር እጅግ መራራ፣ የከፋ፣ ጨለማና መሪር ሐዘን መድረሱን ያመላክታል። ይህ የዕርድ ሥነ-ሥርዓት ከጠንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መኖሩን የሀገር ሽማግሌዎች ይናገራሉ። ከሚታረዱት እንስሳት መካከል በጎችና የቀንድ ከብቶች ይጠቀሳሉ። ፍየል ጭራዋ አጭርና የተገለበጠ በመሆኑ በማናቸውም የዕርቅ ሥርዓቶች ላይ ለእርድ አትመረጥም።

 

የደረሰው የግድያ ሁኔታ በነዚህ ጥቁር መልክ ባላቸው እንስሳት ደም መፍሰስ ሁለቱም ቤተሰቦች ላይ የደረሰው ችግር፣ መከራና ስቃይ ጨለማ ስለ ነበር ይህ ድቅድቅ ጨለማ ተገፎ ወደ ብርሃን የሚቀየረው ጥቁር መልክ ያለው እንስሳ ሲታረድ ብቻ ነው ተብሎ ስለሚታመን ነው። ግድያው ከተፈፀመበት ዕለት ጀምሮ ሁለቱም ቤተሰቦች ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የጋራ መስተጋብሮች በእጅጉ ተለያይተው የቆዩ በመሆናቸው በመጨረሻዋ የዕርቅ ዕለት በሆነው የጥቁር እርድ ሥነ-ሥርዓት በኋላ የሚተያዩ ይሆናል። የዕርቅ ዕለት የገዳይ ቤተሰቦች ያመጡትን ጥቁር መልክ ያለው በግ፣ ላም፣ ወይፈን ወይም ጊደር ታርዶ ደም እስኪፈስ ድረስ ሁለቱም ወገኖች አይተያዩም። በዕርቅ ስፍራው ሁለቱም ቤተሰቦች ፊታቸውን አዙረውና ጀርባቸውን ተሰጣጥተው ይቆማሉ።

 

የታረደው እንስሳ ደም ከፈሰሰ በኋላ ፊታቸውን ያዞራሉ። ወዲያው ከታረደ እንስሳ ሆድ ዕቃዎች ውስጥ ሳንባ አውጥቶ በታረደው እንስሳ ላይ ያስቀምጡና የገዳይ ቤተሰቦች በሙሉ ሳንባውን በጣታቸው ነካ አድርገው ቅንድቦቻቸውን በማስነካት በፈሰሰው ደም ላይ እየተሻገሩ ወደ ሟች ቤተሰብ ይቀላቀላሉ። ይህም ማለት ሁለቱም ወገኖች ከግድያው ዕለት ጀምሮ እርስ በርስ ያለመተያየታቸውን ሲያመለክት፤ ነገር ግን ከዛሬ ጀምሮ በፍቅር ዓይን እንተያያለን፤ እርም ወጥቷል የሚል ባህላዊ ትርጉም ያለው ሥነ-ሥርዓት ነው። በተጨማሪም የታረደውን እንስሳ ቆዳ በአምባር መልክ አዘጋጅተው የሁለቱ ወገኖች እንዲያጠልቁ ይደረጋል። ይህ የቆዳ አምባር “ሜንጥቻ” የባላል። ቆዳ የማሰሩ ትርጉም ዕርቅ መውረዱንና ሁለቱም ቤተሰቦች አንድ መሆናቸውን ያመለክታል። የታረደው እንስሳ ሥጋ በክትፎ መልክ ይዘጋጅና በገዳይ መዳፍ ላይ በማኖር ቀድሞ እንዲቀምስና ለሟች ቤተሰብ ተወካይ ከመዳፉ እንዲያቀምስ ይደረጋል። ይህም ሥርዓት ከዚህ በኋላ ሁለቱም ቤተሰብ ከቂም በቀል ነፃ መሆናቸውንና ዕርቅና ሰላም መውረዱን ያሳያል።

 

በመጨረሻው የዕርቅ ዕለት ከጥቁር ዕርድ ሥነ-ሥርዓት ጐን ለጐን ከሚካሄዱት ባህላዊ የዕርቅ ሥርዓቶች መካከል ሌላው ቁልፍ ተግባር የማርና የኮሶ መርጨት ሥነ-ሥርዓት ነው። ይህ ሥነ-ሥርዓት የሚከናወነው የገዳይ ቤተሰብ ለዕርቅ ቀን ከጥቁር ዕርድ ጋር ኮሶ ያዘጋጃሉ። የመርጨቱን ተግባር የሚያከናውኑት የገዳይ እህት ወይም አክስት ሲሆኑ ሁለቱም ከሌሉና የማይገኙ ከሆነ ግን ከገዳይ ቤተሰብ በኩል ሌላ ሴት ልትሆን ትችላለች።

 

ኮሶ የመርጨቱ ጉዳይ የደረሰው የግድያ ሁኔታ ልክ እንደ ኮሳ የመረረ መሆኑንና ከዕርቁ በኋላ ይህ መራራ ነገር መውጣቱን አመላካች ሲሆን፣ የማር መርጨቱ ሥነ-ሥርዓት ደግሞ በሟች ቤተሰብ በኩል ይፈፀማል። የምትረጨው ማንም ሴት ስትሆን በእርግጥብ ግራዋ ቅጠል ተነክሮ ይሆናል። ይህም በሟች ቤተሰብ በኩል የሚከናወነው መራራ ሐዘን ወጥቶ ጣፋጭና ፍቅር ይግባ የሚል መልዕክት ያለው ባህላዊ አንድምታ አለው። በሟች ቤተሰብ በኩል ከማር ሌላ ወተትም ሊረጭ ይችላል። ይህም ፍፁም ሰላም መውረዱን ያመለክታል። ለሀገር ሽማግሌዎችም በዋንጫ ማርና ወተት ተሞልቶ ይሰጥና በሁለቱም ቤተሰቦች ላይ እየተጐነጩ እንትፍ እያሉ ይመርቋቸዋል።

 

በመቀጠል በገዳይ ቤተሰብ በኩል የመጣውን ጋቢ /ቡሉኮ/ እንደ ድንኳን ተዘርግቶ ሁለቱም ቤተሰብ በስሩ እነዲሰበሰቡና ምርቃት እንዲቀበሉ ይደረጋል። ይህም ከዚህ በኋላ አንድ ቤተሰብ ሆነናል፣ የተፈጠረው ችግር ተፈትቷል፣ ዕርቅ ወርዷል፣ ወደ ቀድሟችን የርስ በርስ ፍቅርና ሰላም ተመልሰናል ለማለት ነው። በመጨረሻም የተዘጋጁትን ባህላዊ ምግቦች ከአንድ ገበታ ይበላሉ። ባህላዊ መጠጦችም ከአንድ ዋንጫ ይጠጣሉ፤ ተመራርቀው ይሸኛኛሉ። አልፎ አልፎ አሁንም በብሔረሰቡ ቀለል ያሉና ድንገት በስህተት የተፈፀሙ የወንጀል ድርጊቶች በማር መርጨት ብቻ እንደሚያልቁ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። በዚህ መልኩ ዕርቅ ከወረደ በኋላ ገዳይም ይሁን ቤተሰቦቹ ያለ ምንም ስጋት ከሟች ቤተሰብ ጋር በሰላምና በፍቅር እንደ ቀድሟቸው በባህላዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አብሮ መኖር ይጀምራሉ። ከዚህ ባለፈ ደግሞ በሁለቱም ቤተሰቦች መካከል የበለጠ ወዳጅነትና ዝምድና እንዲኖርና እንዲጠናከር በቅርብ በደም የማይገናኙ ከሆነ ለአቅመ ሔዋን የደረሱ ልጆች ካሏቸው በጋብቻ ይተሳሰራሉ።

 

ማጠቃለያ

ባህላዊ የዕርቅ ሥርዓቱ በአሁኑ ወቅት በብሔረሰቡ በሰፊው እየተተገበረ የሚገኝ ሲሆን፤ ከዘመናዊ ዘዴ ይልቅ ተመራጭነቱም ከፍተኛ እንደሆነ መረጃ የሰጡ ግለሰቦች ይመሰክራሉ። በተለይ ከቂም በቀል የነፃ ዕርቅ ከማውረዱ፤ ከወጪ ቆጣቢነቱና ቤተሰብ እንዳይበታተን ከማድረጉ አንፃር ህዝቡ ባህላዊውን በመምረጥ በማንኛውም ሁኔታ የሚከሰቱትን ግጭቶችን ለመፍታት እንደ ብቸኛ አማራጭ አድርገው ህዝቡ በመገልገል ላይ የሚገኝ ባህላዊ ዕሴት ነው። ባህላዊ ዕርቁ ዘመናዊውን ዘዴ ሙሉ በሙሉ ሳይቃረንና ሳይቃወም ጎን ለጎን መንግስት ለእርቅ ስርዓቶች በማለት የሚያወጣቸውን የሀብት ብክነትን ከመቆጠብ ባለፈ ወደ ማስቀረት ደረጃም የደረሰበት ሁኔታ እንዳለ እንዲሁም ለሰላም፣ አብሮ ለመኖር፣ ለመቻቻልና ለልማት እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን መረጃ የሰጡ ግለሰቦች ይናገራሉ። በመሆኑም በብሔረሰቡ ባህላዊውም ይሁን ዘመናዊው የዕርቅ ስርዓቶች ለህዝብ ጥቅም ጎን ለዕን በመሆን ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን በጥናት ወቅት ለመመልከት ተችሏል። ይህ መልካም ተሞክሮ መቀጠል አለበት።

    

ምንጭ፡- ቅርስ መፅሔት

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
222 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 119 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us