የችግሮቻችን መነሻና መድረሻ የሆነው የከረረ “ዲሞክራሲዊ ማዕከላዊነት”

Wednesday, 07 June 2017 14:21

 

በያሬድ አውግቸው

ኢህአዴግ የሃሳብ ብዙህነትን የሚያስተናግድ ስርዓት አስፈላጊነት ላይ  ቁርጠኝነት  እንዳለው ሲነግረን የአንድ ጎረምሳ እድሜ አስቆጥሮአል። ሆኖም ተጨባጩ ነባራዊ ሁኔታ እንደሚያሳየን ይህ  ብዙ  የሚባልለት  ብዙሀነት በኢህአዴግ ድርጅታዊ  ህገ ደንቦችና አሰራሮች ሲታፈንና ሲጨቆን ይታያል። ካለቦታቸው በመተግበር የዲሞክራሲ ህልማችንን ካጨነገፉ የፓርቲው የአመራር ፍልስፍናዎች መካከል ደግሞ  “ዴሞክራሲዊ ማእከላዊነት” በመባል የሚታወቀው የአመራር ፍልስፍና አንዱ ነው። ይህ የእምነትን ያክል ጥልቀትና ስፋት የደደረውና ከሶሻሊስታዊ ርዕዮተ ዓለም የተቀዳው የአመራር ባህል  ፓርቲውንና  ሃገራችንን  ህይወት  አልባ አድርጎአቸዋል።

እስቲ አንዳንድ ማሳያዎችን እንይ። እንደ ብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን የቅርብ ግዜ   ጥናታዊ ሪፖርት  ከሆነ ህግ አውጪ  የሆነው የተወካዮች ምክር ቤት በአስፈጻሚው አካል ተጽህኖ ስር  ወድቆ ይገኛል። በተገለጸው ጥልቀትና መጠን ተጽህኖ ስር የወደቀ ህግ አውጪ  ደግሞ በአስፈጻሚው የሚቀርቡ  ረቂቅ ህጎች፤ ተቋማዊ አደረጃጀቶች እና  ህገወጥ አሰራሮችን ፈትሾ እርማት እንዲደረግባቸው አምርሮ ይሰራል ተብሎ አይጠበቅም። የአለማችን ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየንም ህግ ተርጓሚና ህግ አውጪ ተቋማት አስፈጻሚውን ወደ መስመር የማያስገቡ ከሆነ በስልጣን መባለግ፤ አድርባይነት፤ መሞዳሞድ፤ ደንታቢስነት እና የሃብት ብክነት  የአስፈጻሚው መገለጫ ባህርያት መሆናቸው አይቀሬ ነው። ከምስራቅ አውሮፓ ሃገራት ተሞክሮ እንደምናየው ከልክ ያለፈ ዲሞክራሲያዊ ማእከላዊነት መገለጫ  የሆነባቸው ገዢ ፓርቲዎች ከላይ የተገለጹ  ባህርያት ወደ ውድቀት መርቶአቸዋል።

ሌላው የሃገራችን ከልክ ያለፈ ዲሞክራሲያዊ ማእከላዊነት ጣጣ ደግሞ የመንግስት ሃላፊዎች የተመደቡባቸውን ተቋማት በሙሉ አቅማቸው እንዳይመሩ ማድረጉ ነው። ሃላፊዎቹ በሃገሪቱ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ተመርኩዘው ወደ  ውሳኔ መድረስ ሲገባቸው የዲሞክራሲ ማእከላዊነት ባህልን ላለመጋፋት ሲሉ ደህንነታቸውን በሚያስጠብቀውና ምናልባትም እንደ ሃገር አክሳሪ መንገዶችን ብቻ እንዲመርጡ  አድርጎአቸዋል።  ይህ ልምድ ለየት ያለ ውሳኔ ለመወሰን የበላይ አካል መመሪያ ጥበቃ  በሚያንጋጥጥ የበታች አመራር የተሞላ የሲቪል ሰርቪስ መዋቅር እንዲኖረን ዋናውን  ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ለምሳሌነት መረጃ በመስጠት በኩል የአገራችን ተቋማት ሃላፊዎች ውስጥ ያሉ ችግሮችን ማንሳት ይቻላል። በመጀመሪያ የበታች አመራሮች ቁንጮ የፓርቲና የሃገር አመራሮች ለቃለመጠይቅ ከሚመርጡዋቸው የተወሰኑ  ሚዲያዎች ውጪ  መግለጫ መስጠት ዋጋ ያስከፍላል ብለው  ስለሚያምኑ በራቸውን   ይዘጋሉ። በመቀጠል መግለጫ የሚሰጡባቸው ጉዳዮችም ቀደም ብሎ በከፍተኛ  በሃላፊዎቹ  ይፋ የወጡ ጉዳዮች ላይ  ብቻ እንዲያጠነጥን ይጠነቀቃሉ። እነዚህ  የገደል ማሚቶ መሰል መግለጫዎች የሃገራችን የመንግስት ተቋማት መገለጫዎች ሆነው ቀጥለዋል። 

ሌላውና በገዥው ፓርቲ ውስጥ ከሚንሸራሸሩ የፖለቲካ ባህሎችና ፍልስፍናዎች  መካከል በጭፍን በሚያምን አመራር ሃገሪቱ እንድትሞላ ያደረጋት ደግሞ “ከእኔ የፖለቲካ ፍልስፍና ውጪ  የሆነ አመለካከትም ሆነ ድርጊት ለሃገሪቱ አጥፊ ነው” መሰል  አመለካከት ሲልም ይፋ የወጣ ተግባር ነው። ይህ  አስተሳሰብ ወደ ዲሞክራሲ እየተጓዝኩ ነው ከሚል ፓርቲ የሚጠበቅ አልነበረም። ሂውማን ራይት ዎች፤ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል፤ ለጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች እና  መሰል ተቋማትን  የሊበራል ዲሞክራሲ ርእዮተ አለም መሳሪያዎች ናቸው  ብሎ የመፈረጅ ባህል በምሳሌነት ይጠቀሳል። የሚገርመው ለሃገራችን ግንባር ቀደም እርዳታና ብድር አቅራቢ ሃገራት እነዚህ ተቋማት አላማውን ያራምዱለታል የሚባለው የሊበራል ዲሞክራሲ ጎራ መሆኑ ነው። እንግሊዝና ዩ ኤስ አሜሪካን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። እዚህ ላይ መገለጽ ያለበት በፓርቲው ውስጥ የሰፈነው የጠነከረ የዲሞክራሲዊ ማእከላዊነት አስተሳሰብ በዚህ ምክንያታዊነት ገዥ በሆነበት ዘመን እንኳን ፓርቲው እራሱን ብቻ አንዲያዳምጥ ጠፍሮ ይዞታል። በእኔ እምነት ድርጅቱ ለውስጣዊ ትግል እራሱን ክፍት ቢያደርግ ወደ ዘመኑ አስተሳሰብ  እየተገፋም ቢሆን ይቀላቀል ነበር የሚል ጽኑ እምነት አለኝ።

በአጠቃላይ የዲሞክራሲዊ ማእከላዊነት መዘዝ በፓርቲ መዋቅር ላይ ብቻ የሚቆም አይደለም። በመንግስት ሶስቱም ክንፎች፤ በመንግስት በጀት በሚተዳደሩ የዲሞክራሲ ተቋማት እና  በሲቪክ ማህበራት ዙሪያ በሚወጡ ህጎች ላይ መንጸባረቁ  አይቀሬ ነው። አስተሳሰቡ ግትርና ለለውጥ እድል የማይሰጥ በመሆኑ ህብረተሰቡን በቀላሉ ከሚቀርጹት በተቃራኒ ጎራ ካሉ ጉልበታም አስተሳሰቦችና ፍልስፍናዎች ጋር  ታግሎ የመዝለቅ እድሉ እጅግ የመነመነ ነው። ስለዚህ ገዥው ፓርቲ በአዲስ ተካሁባቸው ከሚላቸው አመራሮች ጋር ግትር የሆኑና ለመሻሻል እድል የማይሰጡ አስተሳሰቦች  እና የፖለቲካ  ፍልስፍናዎችን ጡረታ ሊያወጣ ይገባል እላለሁ።¾

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
331 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 96 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us