የጋምቤላ የእርሻ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክንያት ለከፍተኛ ኪሳራ እየተዳረግን ነው አሉ

Wednesday, 21 June 2017 14:03

 

በጋምቤላ ክልል በእርሻ ኢንቨስትመነት ተሰማርተን የምንገኝ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር በመውሰድ የልማት እንቅስቃሴ ስናደርግ ቆይተናል። በክልሉ ስራ ከጀመርንበት ወቅት አንስቶም በተለያየ መልኩ ሃገራችንና ህዝባችንን እየጠቀምን እንገኛለን። የተለያዩ የግብርና ስራዎችን በማስተዋወቅ፣ ለህብረተሰቡ የስራ እድል በመፍጠር፣ በአካባቢው የስራ ባህል እንዲዳብር በማገዝ፣ የተለያዩ የመሰረተ ልማት አውታሮችን በመዘርጋት፣ ማህበራዊ ኃላፊነታችንን በመወጣት፣ እንዲሁም ምርቶቻችንን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድ የሃገራችንን ልማት በማፋጠን ረገድ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እያደረገን ነው።

ሆኖም መንግስትና ከግብርና ኢንቨስትመንት ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላት ሁሉ በማንኛውም ጊዜ የሃገር ውስጥ ባለሀብቶችን እንቅስቃሴ በተለያየ መልኩ በማገዝ አቅማቸውን መገንባትና ማበረታታት ሲገባቸው፣ ነገሮች በዚህ መልኩ እየተካሄዱ አይደሉም። በተለይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶችንና አምራቾችን አቅም፣ ልምድና ጥንካሬን ከግምት ባለማስገባት ጥረታችንን በሚያዳክም መልኩ እየሰራ ይገኛል። እናም በጋምቤላ ክልል እየሰራን የምንገኝ ባለሃብቶች እያጋጠሙን ያሉ ችግሮች እየተባባሱ በመሄዳቸው ስራችንን አደጋ ላይ ጥለውታል። የልማት ባንኩም ይህን ችግር በመፍታት ረገድ የሚያደርገው ጥረት አሉታዊ ሆኗል።

በዚህ ማመልከቻ ጉዳዩን ለሚዲያ እና ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ይፋ ለማድረግ ከመገደዳችን በፊት በመልካም አስተዳደር ጉድለት ምክንያት በኢትዮጵያ ልማት ባንክ እያጋጠሙን ያሉት ችግሮች የልማት ስራዎቻችንን በአግባቡ እንዳናከናውን እያደረጉን ስለመሆናቸው ለባንኩ ዋና መስሪያ ቤትና ለቅርጫፎቹ በተለያዩ አጋጣሚዎች ስንገልፅና አቤቱታችንን በተከታታይ ስናሰማ ቆይተናል።

በማህበራችን አማካኝነት ይህን ስናደርግ የቆየነው በልማት ባንክ ሲታዩ የነበሩት ችግሮች ወደ ባሰ ደረጃ ሳይሸጋገሩ በጊዜ ቢፈቱ ውጤቱ ለእኛ ለባለሃብቶቹ ብቻ ሳይሆን ለሃገሪቱ እድገትም ሚናው የላቀ መሆኑን በመገንዘብ ነው። ይንን ታሳቢ በማድረግ የማህበሩ አባላት ከዋናው መስሪያ ቤት ኃላፊዎችና ከባንኩ ዲስትሪክት ማኔጀሮች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች ብናደርግም ሰሚ ማግኘት አልቻልንም።

ባንኩ አሰራሮችን ፈትሾና መርምሮ ድጋፍ ማድረግ፣ እንዲሁም የኛንም ጉድለቶች በመፈተሽ አቅማችንን በሚያጎለብትና ስራችንን በሚያቀላጥፍ መልኩ ማገዝ ሲገባው፣ በጊዜ ማከናወን የነበረበትን ስራ ዘንግቶ አሁን ከ110 የእርሻ ፕሮጀክቶቻችንን በላይ ወደ ታማሚ ምድብ ወይም NPL ጎራ እንዲገቡ አድርጓቸዋል።

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብልሹ አሰራር ምክንያት እና አጠቃላይ በክልሉ ባሉት ተጨባጭ ሁኔታዎች ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ያጋጠሙንና በግልፅ ያስተዋልናቸው ችግሮች የሚከተሉት ናቸው።

1.  የባንኩ አገልግሎት አሰጣጥ እና አሰራሮች በፍፁም የማያሰሩ እና ለውድቀት የሚዳርጉ ናቸው።

2.  በመንግስት የእርሻ ኢንቨስትመንት መመሪያና ህግ መሰረት እያንዳንዱ ብድር ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት የእፎይታ ጊዜ /grace period/ መሰጠት ሲገባው፣ ባንኩ የእፎይታ ጊዜ እንዳይኖረን በማድረግ ፕሮጀክቶቻችን በውድቀት አፋፍ ላይ እንዲያርፉ/ በከፍተኛ ሪስክ ውስጥ እንዲወድቁ አድርጓል።

3.  የእርሻ የኢንቨስትምንት ስራ ከፍተኛ የመንግስት ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ይታወቃል። ሆኖም ግን ባለፉት ዓመታት መንግስት በጋምቤላ የሚካሄዱት የእርሻ ኢንቨስትመንቶች ምንም ዓይነት የምርጥ ዘር፣ የኬሚካል አቅርቦት፣ የገበያ. . . ወዘተ ድጋፎች ባለማድረጉ ኢንቨስተመንቱ በከፍተኛ ደረጃ ሲጎዳ በመቆየቱ፤

4.  በጋምቤላ ክልልና አካባቢው በተደጋጋሚ የሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች ባለሀብቱ ተረጋግቶ እንዳይሰራ በማድረግ ረገድ የጎላ ድርሻ ነበራቸው፤

5.  በ2006 እስከ 2008 ዓ.ም ተፈጥሮ የነበረው የመሬት መደራረብ ለመፍታት ብዙ ጊዜ በመውሰዱ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ባለሃብቶች በቂ የዝግጅት እና የማምረቻ ጊዜ አላገኙም።

6.  በክልሉ 2007/2008 ዓ.ም ተከስቶ በነበረው ሰፊ ቦታ የሸፈነ ድርቅ ምክንያት የዝናብ እጥረት በማጋጠሙ፣ ባሀብቶች ከእርሻ ልማታቸው በቂ ምርት አላገኙም።

7.  በክልሉ ውስጥ ተከስተዋል ተብሎ በተወራው መጠነ ሰፊ ችግሮች ለመፍታት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በተዋቀረ አጣሪ ቡድን አማካኝነት ከአንድ ዓመት በላይ የፈጀ ጥናት ሲካሄድ የባከነው ጊዜ ትልቅ ነበር። ይህም የእርሻ ስራውን ከማስቆም በላይ ባለሀብቱ ተረጋግቶ እንዳይሰራ አድርጎታል።

8.  በተለያዩ ጊዜያት በሚታየው ያልተረጋጋ የሃገር ውስጥና የውጭ ገበያ ምክንያት ባለሃብቱ ምርቱን በኪሳራ ሲሸጥ ቆይቷል። ይህም ሄዶ ሄዶ ለኪሳራ ዳርጎታል።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱት ባለሀብቶች ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች እየተጋፈጡ እንደ ዜጎች ለሃገር ልማት የበኩላቸውን ለማበርከት ሲጥሩ ቆይተዋል። ሆኖም ችግሮቹ አብዛኞቹን የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናክረው እንዳይጥሉ በማድረግ ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገቡ አድርገዋቸዋል። የኢትዮጵያ መንግስት እንዲህ አይነት ችግሮችን ከግምት በማስገባት ባለሀብቶችን እንደሚያበረታታ እናውቃለን። ሃገራዊ ኃላፊነት የሚሰማው ማንኛውም አካልም የባለሃብቶችን እንቅስቃሴ ሲያስብ ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች ከግምት እንደሚያስገባ ግልፅ ነው።

ሆኖም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከሃገራዊ አሰራርና ኃላፊነት ውጪ በመሄድ፣ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች አቅማቸው እንዳልዳበረ እያወቀ፣ ከውጪዎቹ ባለሀብቶች በተለየ መንገድ ሃገራዊ ባለሃብቶችን የመደገፍ ኃላፊነት እንዳለበትም እየታወቀ፣ ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች ከግምት ማስገባት ሲገባው፣ ሀገርና ህዝብን በሚጎዳ መልኩ በማን አለብኝነት ጥረታችንን ለማልማት ህልማችንን ለማምከን ቆርጦ ተነስቷል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ሀገር የሚያለሙትን ዜጎች ከማቀጨጭና ከጨዋታ ውጪ እንዲሆኑ ከማድረግ ይልቅ፣ ጥረታቸውን ከግምት አስገብቶ የተለየ ድጋፍ፣ ማበረታቻና እገዛ መስጠት በተገባ ነበር። በዓለም ላይ ከሃገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ ውጭ ያደገ ሃገር እንደሌለ ልብ ይሏል።

ባንኩ እያደረሰብን ባለው የመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት ከስረን ከጨዋታ ውጭ ብንሆን ጉዳቱ ከኛና ከቤተሰቦቻችን አልፎ፣ በስራችን የሚተዳደሩ ሰራተኞች፣ የክልሉ ህዝብና መንግስት እንዲሁም የሀገሪቱ ጉዳት እንደሚሆን ማንም ኃላፊነት የሚሰማው አካል ይገነዘበዋል።

ባለሀብቶቹ ብድር ከወሰዱ ገና ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ብቻ ነው ያስቆጠሩት። እላይ በተጠቀሱት ችግሮች ውስጥ ሆነው በመስራት በመንግስት ድጋፍ በሚቀጥሉት ተከታታይ ዓመታት ብድሮቻቸውን እየመለሱ ውጤታማ ስራ እንደሚያከናውኑ ይጠበቅ ነበር። ሆኖም ባለሃብቶቹ ብድር ከወሰዱ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ምንም አይነት ድጋፍ ሳይደረግላቸው፣ የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ከግንዛቤ ሳይገቡ፣ በመንግስት መመሪያ የተፈቀደው የእፎይታ ጊዜ ተከልክለው፣ የተሰጣቸውን መሬት በወጉ አጥንተውና አልምተው ሳይጨርሱ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባለሃብቶቹ የያዙዋቸውን ፕሮጀክቶች ወደ ታማሚ ጎራ በማስገባት በሃራጅ እንዲሸጡ እስከማመቻቸት መድረሱ ተገቢነት የለውም። ይህ ኃላፊነት ከሚሰማው የመንግስት ተቋም የሚጠበቅ ተግባር አይደለም።

የባንኩ አመራሮች ችግሮቹን በመገንዘብ ፕሮጀክቶቹ ወደ ታማሚ ጎራ ከመግባታቸው በፊት አስቸኳይ የማስተካከያ ውሳኔ እንዲሰጡን በተደጋጋሚ ብንጠይቅም እስካሁን ድረስ ትርጉም ያለው መፍትሄ ሊሰጡን አልቻሉም። በዚህ ምክንያት በአሁኑ ወቅት በጋምቤላ ክልል በእርሻ ኢንቨስትመንት ተሰማርተው ብድር ከወሰዱ 194 የአገር ውስጥ ባለሀብቶች መካከል ከ110 በላየ ፕሮጀክቶች በታማማ /NPL/ ጎራ ገብተው ይገኛሉ። ይህን ሁኔታ በፅኑ እንቃወማለን። መንግስት ባለበት ሀገር ውስጥ እንዲህ አይነት ተግባር መፈፀም እንደሌለበትም እናምናለን።

ስለሆነም እኛ በጋምቤላ ክልል በእርሻ ኢንቨስትመንት ስራ የተሰማራን ባለሀብቶች የሚዲያ ተቋማችሁ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ እየደረሰብን ያለውን የመልካም አስተዳደር በደል በአግባቡ ተገንዝቦ እና ሁኔታውን በጥልቀት ፈትሾ የሚከተሉትን መልዕክቶች በዜናና ፕሮግራም እንዲያስተላልፍልን በአክብሮት እንጠይቃለን።

1.  ባንኩ በስራዎቻችን መሃል በተደጋጋሚ እያጋጠሙን የቆዩትን ችግሮች በጥልቀት ገምግሞ የብድሮቻችን የመመለሻ የጊዜ ገደብ እንዲያራዝምልን፤

2.  እስካሁን ድረስ በተለያዩ ጥቃቅን ምክንያቶች ከሁለት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ /200,000,000/ የስራ ማስኬጃ ገንዘብ የተያዘባቸውን ፕሮጀክቶች ችግር በመፍታት ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲመለሱ ውሳኔ እንዲሰጠን፤

3.  በተለያዩ ምክንያቶች የስራ ማስኬጃ እጥረት ያጋጠማቸው ድርጅቶች ተጨማሪ የስራ ማስኬጃ ብድር እንዲፈቀድላቸው፤

4.  በመንግስት የኢንቨስትመንት መመሪያ መሰረት ለባለሀብቶች የተቀመጠው የእፎይታ ጊዜ በእኛ ማህበር ስር ላሉት ባለሃብቶችም ተግባራዊ እንዲደረግ፤

5.  በባንኩ ችግር ምክንያት ከቀን ወደ ቀን እየተዳከሙ ወደ ታማሚ ጎራ /NPL/ እና ወደ ሐራጅ እየገቡ ያሉ ፕሮጀክቶች ችግር በመፍታት በዚህ ክረምት ስራ እንዲያስጀምራቸው፤

6.  መንግስትም ችግራችንን በጥልቀት በመረዳት የዘር ወቅት ሳያልፍ አስቸኳይ የማስተካከያ መፍትሄ እንዲወሰድ እንጠይቃለን።    

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
170 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1017 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us