በብሉምበርግ ዘገባ የኦሮሚያ ክልል ምላሽ

Wednesday, 28 June 2017 11:52

 

ብሉምበርግ የተሰኘው ሚዲያ በኢትዮጵያ በሲሚንቶ ማምረቻ የኢንቨስትመንት ሥራ ላይ ተሠማርቶ የነበረው ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ በጫና ምክንያት ሊዘጋ እንደሚችል ማስጠንቀቁን የሚመለከት ዜና ሰሞኑን ይዞ ወጥቷል።


ዜናው መሠረት ያደረገው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በቅርቡ በክልሉ ከሚገኙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች አመራሮች ጋር በመወያየት ኩባንያዎች ጠቅልለው ይዘውት የነበረውን የሲሚንቶ ጥሬ ዕቃ የማውጣት ሥራ ለክልሉ ወጣቶች እንዲለቁ ማድረጉን ተከትሎ ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ቅሬታ ስለገባው መሆኑ ተመልክቷል።
የኦሮሚያ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ዜናው ከተሰማ በኋላ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ የሚከተለው ምላሽ አስፍረዋል።

 

*** *** ***

 

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የስራ አጥነት ችግርን ለመፍታት ዘርፈ ብዙ ስራዎች በማከናወን ላይ ይገኛል። በክልሉ ለወጣቶች የስራ ዕድል ሊፈጥሩ የሚችሉ ዘርፎችን በመለየት ወደ ተጨባጭ ተግባርም ገብቷል። ከዚህም ዉስጥ ለሲሚንቶ ግብዓት የሚዉሉ ማዕድናት ለወጣቶች የስራ ዕድል እንዲዉል ማድረግ አንዱ ነዉ። የማዕድን ቦታዎችን በተመለከተ የክልሉ መንግስት ሁለት መሰረታዊ እርምጃዎችን ወስዷል። አንደኛዉ እርምጃ የሲሚንቶ ማምረቻ ፋብሪካ ሳይኖራቸዉ የማዕድን ቦታዎችን በተለያየ መንገድ ይዘዉ ምንም እሴት ሳይጨምሩ አሸዋ እና ፑሚስ እያፈሱ ሲሸጡ የነበሩ "ባለሀብቶች" ላይ የተወሰደ እርምጃ ነዉ። እነዚህ "ባለሀብቶች" ከዚህ ዘርፍ እንዲወጡ እና የማዕድን ቦታዉ ለስራ አጥ ወጣቶች እንዲተላለፍ መደረጉን መግለጻችን ይታወሳል።


ሁለተኛዉ እርምጃ በክልላችን የሚገኙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በሲሚንቶ ምርት የዕሴት ሰንሰለት ለሲሚንቶ ግብዓት የሚዉለዉን የማዕድን ጥሬ ዕቃ ከማዉጣት ጀምሮ ያለዉን ሁሉንም ስራ ራሳቸዉ ኩባንያዎች ጠቅልለዉ ይሰሩ ስለነበረ፣ ከዕሴት ሰንሰለቱ ዉስጥ ማዕድን የማዉጣቱን ስራ ለተደራጁ ወጣቶች እንዲለቁ (outsource) እንዲያደርጉ ማድረግ ነዉ። በዚህም መሰረት ከሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ ባለሀብቶችና የማኔጅመንት አካላት ጋር በተደረገ ዉይይት የሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ ከዕሴት ሰንሰለቱ ዉስጥ ጥሬ ዕቃን የማቅረብ ጉዳይ ለወጣቶቹ በመልቀቅ የስራ ዕድል እንዲፈጠርላቸዉ በመስማማት፣ ወጣቶቹ የሚያመርቱተን ጥሬ ዕቃም ገዝተዉ ለመጠቀም ተስማምተዉ በይፋ ዉል ተፈራርመዉ ወደ ተግባር ገብተዋል። በዉላቸዉ መሰረትም ያለምንም የስራ መስተጓጎል በመገበያየት ላይ ይገኛሉ። በዚህ ዘርፍም በሺህዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።


የሲሚንቶ ምርት ግብዓት ማዕድናትን ማምረት ኩባንያዎች ለስራ አጥ ወጣቶች ጥቅም እንዲዉል የማድረጉ ጉዳይ ከሲሚንቶ አምራች ኩባንያዎች ጋር በተደረገ መቀራረብ እና ሰፋ ያለ ዉይይት ኩባንያዎቹ ፈቃደኛ ሆነዉ የተፈጸመ ነዉ። ይህ ስምምነት ለሲሚንቶ አምራች ኩባንያዎች አስተማማኝ እና ዘላቂነት ያለዉ ግብዓት እንዲያገኙ በማድረግ ምርታማነታቸዉ እንዲያድግ የሚያግዝ ነዉ። በተጨማሪ በሲሚንቶ የዕሴት ሰንሰለት በግብዓት አቅርቦት የወጣቶቻችንን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑ የታመነበት ነዉ።


የሲሚንቶ ግብዓት ማዕድናትን በተመለከተ የተደረሰዉ ስምምነት እና አፈጻጻሙ ከላይ ተገለጸዉ ሆኖ ሳለ ብሉምበርግ የተባለ ሚዲያ ጁን 22/2017 " ከማዕድን ማዉጫ ዉዝግብ ጋር በተያያዘ ዳንጎቴ የኢትዮጵያ ፋብሪካዉን ሊዘጋ ነዉ " የሚል ዘገባ አውጥቷል። ይህ ዘገባ ዉሸት እና መሰረተ ቢስ ነዉ። ከዳንጎቴም ሆነ ከሌሎች የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጋር ከላይ በተጠቀሱት መሰረታዊ ሀሳቦች ላይ መግባባት ተደርሶ ወደ ተግባር ከተገባ በኋላ ምንም የተነሳ ዉዝግብ የለም። በዳንጎቴም ይሁን በሌሎች የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የቀረበ ቅሬታም የለም። ዳንጎቴም ሆነ ሌሎቹ የሲምንቶ ፋብሪካዎች ፍጹም በተረጋጋ ሁኔታ ስራቸዉን በማከናወን ላይ ናቸዉ።


ከዚህ በተጨማሪ የብሉምበርግ ኮሬስፖንደንት በዚህ ዙሪያ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በኩል ጉዳዩ የሚመለከታቸዉን አካላት አላነጋገረም። በዘገባዉ ስማቸዉ የተጠቀሰዉ የኦሮሚያ የትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ታከለ ኡማ ሲሆን ጋዜጠኛዉ ከእርሳቸዉ ጋር ስለ ኦሮሚያ ኦይል ካምፓኒ ምስረታ እንጂ በማዕድን ጉዳይ ምንም ሀሳብ እንዳልተለዋወጡ ታዉቋል። በመሆኑም ዘገባዉ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትን አቋም የሚገልጽ ሀሳብ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸዉ የክልሉ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ሀሳብ ያልተካተተበት ነዉ። ይህ ደግሞ ዘገባዉ መሰረታዊ የጋዜጠኝነት የስነ ምግባርን ያልተከተለ የክልሉን መንግስት መልካም ስም ለማጉደፍ ሆን ተብሎ የተሰራ ተራ ፕሮፓጋንዳ ስለመሆኑ ማስረጃ ነዉ።


የዚህ አይነት ፕሮፓጋንዳ ዋነኛ ዓላማ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ኢንቨስትመንትን በአግባቡ የማያስተናግድ አስመስሎ በማቅረብ የክልሉ መንግስት የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር እና ሌሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እያደረገ ያለዉን ጥረት ማደናቀፍ ነዉ። የክልሉን መንግስት መልካም ስም በማበላሸት በጥርጣሬ እንዲታይ ማድረግ ነዉ። የዚህ ዓይነት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎች ከዚህ በፊት በሀገር ዉስጥ የተለያዩ ሚዲያዎች ተሞክረዉ ስለተጋለጡ ግባቸዉን ሳይመቱ ቀርተዋል። የክልሉ መንግስት የሚወስናቸዉ ዉሳኔዎች እና የሚሰራቸዉ ስራዎች ሕገ መንግስቱን መሰረት ያደረጉ እና ከምንም በላይ የህዝቡን ተጠቃሚነት ከግምት ያስገቡ ናቸዉ። በመሆኑም በየትኛዉም ሚዲያ ፕሮፓጋንዳ ሚደናቀፉ እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል። በመሆኑም ከዚህ በፊት በሀገር ዉስጥ ሚዲያዎች ተሞክሮ ያልተሳካን የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በዉጭ ሀገር ሚዲያዎች ለማሳካት መሞከር ተቀባይነት የለዉም።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
218 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 136 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us