የባህረ ሰላጤው የፖለቲካ ትኩሳትና የኢትዮጵያ አቋም

Wednesday, 05 July 2017 12:09

 

ከዘአማን በላይ

 

የባህረ ሰላጤው ሀገራት በፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ናቸው። እስካሁን ድረስ ሰባት ሀገራትን ያቀፈውና በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ቡድን በአንድ ጎራ፤ ኳታር ለብቻዋ ሆነው አንደኛው ሌላኛውን አሸባሪዎችን በመርዳት ይወነጅላል። ሳዑዲ አረቢያን፣ ግብፅን፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስን፣ ባህሬንን፣ ሊቢያን፣ የመንንና ማልዲቪስ ደሴትን ያካተተው ቡድን፤ በነዳጅ ሃብት የበለፀገችውን ኳታር “ሙስሊም ወንድማማቾችን፣ አይ ኤስ እና ሃማስን የተሰኙ የሽብር ቡድኖችን ትደግፋለች እንዲሁም ኢራን ለምትደግፋቸው አሸባሪዎችም የገንዘብ ድጋፍ ታደርጋለች” በማለት ከሀገሪቱ ጋር የነበራቸውን ማናቸውንም ምጣኔ ሃብታዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን አቋርጠዋል። የኳታር መንግስት በበኩሉ፤ ውንጀላው ተጨባጭ አለመሆኑን በመግለፅ፤ ‘ማን አሸባሪዎችን እንደሚረዳ እናውቃለን፤ ያም ሆኖ ከሀገራቱ ጋር መደራደር እንፈልጋለን’ ብሏል። የባህረ ሰላጤው አካል የሆነችው ኩዌት አሚር ጃበር አል አህመድ አል ሳባህ ሰባቱን ሀገራትና ኳታርን ለማደራደር የዲፕሎማሲ ጥረት ጀምረዋል።


ይህ አሰጥ-አገባ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከሰባቱ ሀገራትም ይሁን ከኳታር ጋር ግንኙነት ያላቸውን የዓለም ሀገራትን ትኩረት ስቧል። በኳታር ግዙፍ የጦር ሰፈር ያላት አሜሪካ በፕሬዚዳንቷ ዶናልድ ትራምፕ አማካኝነት ችግሩ በድርድር እልባት እንዲያገኝ ያሳሰበች ሲሆን፤ ምክንያቷም በባህር ሰላጤው ሀገራት ሽኩቻ አሸባሪዎች ጡንቻቸው ይፈረጥማል ከሚል የመነጨ መሆኑን አስታውቃለች። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሳዑዲው ንጉስ ጋር በስልክ ባደረጉት ውይይት “ችግራችሁን በጠረጴዛ ዙሪያ ፍቱ” ማለታቸውን ዘገባዎች ያስረዳሉ።


ቱርክ በበኩሏ፤ ዶሃን በማግለል ሽብርተኝነትን መፋለም እንደማይቻል ገልፃለች—የኳታርን መንግስት የ“እንደራደር” አቋምን እንደምትደግፍ በማስታወቅ። ፈረንሳይም “የባህረ ሰላጤውን ሀገራትን ችግር ለመፍታት ዝግጁ ነኝ” ብላለች። የኳታር ግዙፍ የነዳጅ ምርት ተቀባይ የሆኑት ቻይና፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያና ህንድ ደግሞ ምናልባት ችግሩ በጠረጴዛ ዙሪያ የማይፈታ ከሆነ፤ የሳዑዲ መራሹ ቡድን ርምጃ ጥቅማቸውን እንደማይጎዳ ማረጋገጫ እንፈልጋለን ሲሉ ተደምጠዋል። የባህረ ሰላጤው የፖለቲካ ትኩሳት በዲፕሎማሲ አቅጣጫም እየታየ ነው። የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከሰላጤው ሀገሮችና ህዝቦች ጋር ያላቸው ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ታሪካዊና ስነ-ልቦናዊ ግንኙነቶች ከውዝግቡ ውጭ ሊሆኑ እንደማይችሉ ተንታኞች እየገለፁ ነው። ለዚህም በሳዑዲ የሚመራው ቡድንና ኳታር በየፊናቸው በምስራቅ አፍሪካ ውስጥ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን እያደረጉ መሆናቸውን መግለፅ የሚቻል ይመስለኛል።


በቅርቡ የኳታር ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሱልጣን ቢን ሳድ አል ሙራክሂን አዲስ አበባ በመገኘት ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ተወያይተዋል። የኳታር ኤሚር ሼህ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የላኩትን መልዕክትም አቅርበዋል። ሚኒስትር ዴኤታው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የባህረ ሰላጤውን ቀውስ በማስረዳት ኢትዮጵያ ከኳታር ጎን እንድትቆም ጠይቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በሀገራቱ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በውይይት እንዲፈታ ከፖሊሲዋ የመነጨ አቋም እንዳላት ነግረዋቸዋል።


በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ቡድን አባል የሆነችው የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ሚስ ሪም አል ሀሺሚም ሰሞኑን አዲስ አበባ ተገኝተው ከኢፌዴሪ የውጭ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ጋር ተወያይተዋል። ሚኒስትር ዴኤታዋ በወቅቱ ስለ ባህረ ሰላጤው ሀገራት ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ገለፃ አድርገዋል። ዶክተር ወርቅነህ በበኩላቸው፤ ሀገራቸው በባህረ ሰላጤው ሀገራት መካከል የተፈጠረውን ችግር በዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲፈታ ጥረት እንደምታደርግና የኩዌቱን አሚር ጃበር አል አህመድ አል ሳባህ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ትደግፋለች ብለዋል። በስተመጨረሻም የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወቅታዊውን የባህረ ሰላጤ ሀገራት የፖለቲካ ትኩሳት አስመልክቶ፤ “ኢትዮጵያ በባህረ ሰላጤው ሀገራት መካከል የተፈጠረው ውዝግብ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ የበኩሏን ድጋፍ ታደርጋለች” በማለት የአቋም መግለጫ አውጥቷል።


ርግጥ ማንኛውም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ በባህረ ሰላጤው ሀገራት ጉዳይ ሀገራችን ያላትን አቋም በሚገባ ይገነዘባል ብዬ አስባለሁ። አዎ! ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ ላይም ልክ በሌላዎቹ የውጭ ጉዳይ ተግባሮቿ ሁሉ በዚህ ክስተት ላይም የገለልተኝነት አቋምን ማራመዷ ግልፅ ነው። ኢትዮጵያ በየትኛውም ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አትገባም። ለሰላም ካላት ቀናዒ ፍላጎት በመነሳት ሀገራቱ ችግራቸውን በውይይትና በድርድር እንዲፈቱ የምትሻ ሀገር ናት። ለዚህም ነው—የባህረ ሰላጤውን ሀገራት ችግር ለመፍታት የኩዌቱ አሚር እየከወኑ ያሉትን የዲፕሎማሲያዊ ጥረት ትደግፋለች በማለት አቋሟን የገለፀችው።


ይህ የሀገራችን አቋም የፖሊሲ ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ ግጭቶችን በማስወገድ ላይ የተመሰረተ፣ በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ አኳኋን የሚመራና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ነው። ይህም ሀገራችን በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ የገለልተኝነት መርህን (The principle of Neutrality) እንደምትከተል የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ፤ መርሁ እንደ ሀገር የሚተገበር እንጂ ለባህረ ሰላጤው ሀገራት ሲባል የተተገበረ አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።
ርግጥ ላለፉት 26 ዓመታት የሀገራችን የገለልተኝነት መርህ አቋም የተገለፁበትን በርካታ ዕውነታዎች ማንሳት የሚቻል ቢሆንም፤ ለአንባቢያን ግንዛቤ ይረዳ ዘንድ አንድ ሃቅ ብቻ ላንሳ—የሱዳንና የደቡብ ሱዳንን ችግር ከመፍታት አኳያ የተጫወተችውንና እየተጫወተች ያለችውን ሚና። ለየትኛውም ወገን ያልወገነው የኢትዮጵያ በገለልተኝነት ላይ የተመሰረተው የሰላም ዲፕሎማሲ መርህ በተለይ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል የነበረው የረጅም ጦርነት ታሪክ እንዲያበቃ ወሳኝ ምዕራፍን የከፈተና እልባት የሰጠ ነው።


እንደሚታወቀው በምስራቅ አፍሪካ ቀጣናው ያንዣበበው ከባድ የጦርነት አደጋ የሁለቱንም ሱዳን ህዝቦች የሰላም ተስፋ ያሟጠጠ ነበር። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ቢሆን በሱዳን ጉዳይ ያን ያህል እምነት እንዳያሳድር ምክንያት መሆኑም እንዲሁ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የኢፌዴሪ መንግስት የሁለቱን ሱዳኖች ሰቆቃ ያጠላበት ረጅም ጦርነት እንዲቆም ብርቱ ጥረት አድርጓል—ለየትኛውም ወገን ያልወገነ ገለልተኛ መንገድን በመከተል። ይህም በሁለቱ ሱዳኖች መካከል ዘላቂ የሰላም መፍትሔ ማምጣት ችሏል።


ደቡብ ሱዳን እንደ ሀገር ከተመሰረተች ወዲህም ሁለቱን ሱዳኖች ሲያጨቃጭቅ በነበረው የአብዬ ግዛት ውስጥ በሰላም አስከባሪነት በመሰማራት በዚያ አካባቢ ሊከሰት የነበረውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራን ማዳን የቻለች ሀገር ናት። እዚህ ላይ ሳልጠቅሰው የማላልፈው ነገር ቢኖር፤ ኢትዮጵያ በአብዬ ግዛት የሰላም አስከባሪነት ስትመረጥ ምናልባትም በዓለም አቀፉ የሰላም ማስጠበቅ ታሪክ ብቸኛው ሊሆን የሚችለውን ጉዳይ ነው—ኢትዮጵያን ሁለቱ ሱዳኖችና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአንድ ድምፅ ለሰላም አስከባሪነት መምረጣቸውን።


አዎ! በመንግስታቱ ድርጅት ታሪክ ውስጥ ጎረቤት ሀገር ሆና፣ በሁለት ተቀናቃኝ ወገኖች ‘ሰላማችንን ትጠብቅልን’ የተባለችና ይህም አቋም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሙሉ ድጋፍ ያስገኘላት ሀገር ኢትዮጵያ ለመሆኗ በርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ታዲያ እዚህ ላይ ሀገራችን በሶስቱም አካላት ተመራጭ የሆነችበት ምክንያትን ልብ ይሏል! ይኽውም በየትኛውም ሀገር ላይ የምትከተለው የገለልተኝነት አቋም፣ ለሰላም ያላት ቁርጠኝነትና የምትመራበት የህዝባዊነት መርህ ነው።


ደቡብ ሱዳን ነፃ ሀገርነቷን ካወጀች ካለፈው በጣት የሚቆጠር ዓመት ወዲህ ቢሆንም በቀጣናው የተጠበቀው ሰላምና መረጋጋት ሊፈጠር አልቻለም። በአዲሲቷ ሀገር ውስጥ አዲስ የጦርነት አደጋ ሊያንዣብብና የቀጣናው ሰላምም ለዳግመኛ ችግር ሊጋለጥ ችሏል—በሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫኪርና በተቀናቃኛቸው ዶክተር ሪክ ማቻር አማካኝነት ባገረሸው አዲስ የርስ በርስ ጦርነት ሳቢያ። ታዲያ ይህን ችግር ለመፍታት ኢትዮጵያ የአደራዳሪነት ሚና ተጫውታለች። በቀድሞው የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ስዩም መስፍን የተመራው አደራዳሪ ቡድንም ለየትኛውም የደቡብ ሱዳን ኃይል ባልወገነ መልኩ በገለልተኝነት የሰላም ስምምነት እንዲፈረም የማድረግ ስራዎችን በብቃት አከናውኗል።


በኢጋድ አማካኝነትም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጁባ ድረስ በመመላለስ ሁለቱ የሀገሪቱ ተቀናቃኝ ወገኖች ችግራቸውን በሰለጠነ መንገድ እንዲፈቱ ጥረት አድርገዋል። ይህ ጥረታቸውም ኋላ ላይ “ኢጋድ ፕላስ” በተሰኘው ቡድን አማካኝነት በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲትና በዶክተር ሪክ ማቻር አማካኝነት የሰላም ስምምነት እንዲፈረም ምክንያት ሆኗል። ምንም እንኳን የሰላም ስምምነቱ እስካሁን ድረስ የተጨበጠ ለውጥ ሊያመጣ ባይችልም፤ ኢትዮጵያ ነገም ቢሆን ይህን የገለልተኝነት መርህዋን ከኢጋድና ከሌሎች ሰላም ወዳድ ኃይሎች ጋር በመሆን አጠናክራ መቀጠሏ አይቀሬ ነው—በገለልተኝነት ላይ የተመሰረተ የሰላም መርህዋ ሁሌም የሚቀጥል ነውና።


ታዲያ በሰባቱ የባህረ ሰላጤው ሀገራትና በኳታር መካከል የተፈጠረው የፖለቲካ ትኩሳትም በተመሳሳይ ሁኔታ የሚታይ ይመስለኛል። በኢትዮጵያ በኩል ቋሚ መርህ ተጥሶ ከዚህ በተለየ መንገድ ምላሽ የሚሰጠው አይመስለኝም። ሀገራችን ከሁሉም የባህረ ሰላጤው ሀገራት ጋር ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ያላት በመሆኗ ከዚህ መርህዋ ውጭ ልትከተል አትችልም። እናም በዚህ አጋጣሚ መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ እየተከተለ ያለውን በሳል አካሄድ ለማድነቅ እወዳለሁ። በቀጣይም ጉዳዩን በቅርበት በመከታተል የገለልተኝነት መርሁን ተመርኩዞ ለሰላምና ለሁለትዮሽ ዘላቂ የጋራ ተጠቃሚነት በማሰብ አስፈላጊውን ሀገራዊ ውሳኔ እንደሚኖረውም አልጠራጠርም።¾

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
155 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 107 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us