የኢሕአዴግ “ጥልቅ ተሃድሶ” የዜጎችን ችግር በጥልቀት እያባባሰው መጣ እንጂ ለመሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄ መልስ አልሰጠም!

Wednesday, 05 July 2017 12:46

 

(ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የተሰጠ መግለጫ)

ኢሕአዴግ በየጊዜው በሀገራችን ላይ እያስከተለ ያለው ዘርፈ ብዙ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ ከመሄድ አልፈው ባለፉት ሁለት ዓመታት እጅግ አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሳቸውና በብዙዎች ግምት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወት እንዲቀጠፍ፣ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለእስርና እንግልት ሲዳረጉ፡- በቢሊዮን ብሮች የሚቆጠር ንብረት እንዲወድምና የብዙሃኑ ኑሮ እንዲመሰቃቀል ምክንያት ሆኗል።

ይህ ሁሉ ጥፋት ሊደርስ የቻለው ኢሕአዴግ የሚነገረውንና የሚመከረውን አልሰማ በማለት የዜጎችን ጥያቄ በጥሞና አዳምጦና አጢኖ ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ጥያቄዎችን በኃይል አፍኜ እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ በሚለው የአምባገነንነት ተግባሩ ምክንያት ነው።

መድረክ በየጊዜው በሚነሱ ሕዝባዊ ጥያቄዎች ላይ መነጋገር፣ መወያየትና የጋራ  መፍትሔ መሻት አማራጭ የሌለው የሰላም መገኛና በሀገራዊና ሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ መተማመኛ  መንገድ መሆኑን መግለጫዎችን በማውጣት በየጊዜው ሲያሳስብና ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቷል። የሕዝቡን ተገቢና ህጋዊ ጥያቄዎች ላለማዳመጥ ቆርጦ ጆሮ ዳባ ልበስ ያለው ኢሕአዴግ ግን በግትር አቋሙ በመቀጠሉ፤ መጠነ ሰፊ የሆነውን ሀገራዊ አቀፍ ሕዝባዊ ተቃውሞ ተቀስቅሷል። ይህንንም ተቃውሞ በመደበኛ የፀጥታ ማስከበር ሥርዓቱ መወጣት ባለመቻሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ተገዷል። ለ6 ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አውጆ ሁኔታው እርሱ እንደፈለገው ሳይሆን ሲቀር የአዋጁን ጊዜ አራዝሞ እነሆ ዛሬም ሀገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር እንደወደቀች ትገኛለች። ከዚህም በተጨማሪ በማን አለብኝነት ጉልበት ተጠቅሞ በሀገራችን ላይ የጫነው “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ያመጣውን ሁለንተናዊ ቀውስ በግለሰብ ሹመኞች ላይ ማላከክ መፍትሔ ይሰጥ ይመስል፣ የባለሥልጣናት ብወዛ እርምጃዎችን ከሚኒስትሮች ጀምሮ በመውሰድ፣ የሕዝባችንንና የዓለም ማህበረሰብን ትኩረት ከመሠረታዊው የሕዝባችን የሥልጣን ጥያቄ ለማዘናጋት ከፍተኛ ድራማ መሥራት መያያዙን በትዝብት እያየነው ነው።

ኢሕአዴግ በየጊዜው ከሚገባባቸው የፖለቲካ ቅርቃሮች ለመውጣት የአገዛዙን ይዘት ለውጥ የማያመጡ መፈክሮች በመቀያየር የህዝቤን ቁጣ ለማብረድ የተለመደውን የፕሮፓጋንዳ ሥራ መሥራቱ የተለመደ ሲሆን፣ የወቅቱ መፈክሩ ደግሞ “ጥልቅ ተሃድሶ” አደርጋለሁኝ የሚል ሆኗል። በቀደምቱ ዓመታት አደረኩ ይል የነበረው “ተሃድሶ” ውጤት አልባ በመሆኑና አንድ ለአምስት ያደራጃቸውን ህዋስ አባላቱንም አስከድቶ፣ ካድሬዎቹን ጭምር ያሸፈተው ሕዝባዊ ማዕከል ክፉኛ እንዳስደነገጠው የሚታወስ ነው። ከዚህም የተነሳ የሕዝቡን በሥርዓቱ ላይ ያነጣጠረውን ቁጣና የእምቢተኛነት ስሜት ለማርገብ በማለም “በጥልቀት እታደሳለሁ” የሚል መፈክር በማንገብ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ የካድሬዎችንና የአባላቱን ስብሰባዎች በማካሄድ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የሕዝብ ገንዘብ በማባከን እርባናቢስ ተግባር እየፈፀመ ነው። በዚህ ተግባሩም የመንግሥት ሠራተኛውንና ሌላውንም አምራች ኃይል ሥራ እያስፈታ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትንና ተማሪዎችን ክቡር ጊዜ እያባከነ፣ ሀገራችንን በሁለንተናዊ መልኩ እየጎዳት ይገኛል።

በዚህ ወደ 8 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በተራበበትና በተራቆተበት ሀገር ገዥው ቡድን በዚህ ዓይነቱ የሀብት ብክነት ላይ ተሰማርቶ መገኘቱ፣ የ“አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ርዕዮተ ዓለማዊ ቀኖናውን ከውድቀት መከላከልን ዋነኛ ተግባሩ አድርጎ መያዙን ያሳያል። ይህ ተግባሩም ኢሕአዴግ ለሕዝብና ለሀገር የማይበጅ የጠባብ ቡድን ዓላማና ጥቅም የሚያራምድ መሆኑን ያጋልጠዋል። ስለሆነም ዛሬም የሕግ የበላይነት ሊሰፍን ባለመቻሉ ዜጎች ይዋከባሉ፣ ያለምንም የኢኮኖሚ አማራጭ ምንም የሌለውን አርሶ አደር ከይዞታው ያፈናቅላሉ፣ ወዘተ። ለዚህም የሚከተሉት ለአብነት የሚጠቀሱ ይሆናሉ፡-

ሀ. በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል

1.  በጋሞ ጎፋ ዞን ጨንቻ ላይ የአቶ ተመስገን ያንቾ የዞኑ የመድረክ ሥ/አ/ኮ/አባል ከሕግ አግባብ ውጭ ታፍኖ መታሰር፣

2.  አሁንም በዚሁ ክልልና ዞን የመድረክ ሥ/አ/ኮ/አባል የሆኑት የአቶ ወንድሙ ዑዱ በኢሕአዴግ ታጣቂዎች በዱላ ተደብድበው ለሕይወታቸው አስጊ ሁኔታ ውስጥ መሆን፤

3.  በዚሁ ክልል በካንባታ ጠንባሮ ዞን የመብት ጥያቄ ያነሱ የሰባት መምህራን መታሰርና የሌሎች ከሥራ መታገድ፣ እንዲሁም ደሞዛቸው ከሕግ አግባብ ውጪ መቆረጥ፣

4.  በሀዲያ ዞን በምስ/ባደዋች ወረዳ “የሪፎርም ከተማ” በሚል ሰበብ፣ ብቸኛ መተዳደሪያው እርሻ የሆነውን አርሶ አደር፣ የመሬት ይዞታውን የከተማ ክልል ነው በማለት፣ ያለምንም ካሣ ክፍያ በማፈናቀል፣ ማሳቸው ውስጥ ገብተው ቅየሳ እያካሄዱ ሁከት እየፈጠሩ መሆኑ፣

ለ/ በትግራይ ክልል

1.  የዓረና ሊቀመንበር የሆኑት የአቶ አብርሃ ደስታ በመቀሌ ከተማ ባልታወቁ ሰዎች መደብደብና የአካል ጉዳት መድረስ፣

2.  የእነ አቶ ፍስሃጽዮን ተክለሃይማኖት (10 የመድረክ አባሎች) በፖለቲካ አቋማቸው መንስዔነት፣ ከሕግ አግባብ ውጪ ከ1-7 ዓመት ተፈርዶባቸው ወህኒ መወርወር፣

3.  ለችግረኛ የዓረና አባላት የነፍስ አድን እርዳታና የሴፍቲኔት ዕድል መከልከል፣

ሐ/ በኦሮሚያ ክልል

1.  በምዕራብ ሸዋ ዞን የሁለት ወጣት ተማሪዎች በግፍ መገደል፣ ከእነርሱ ውስጥ አለምነህ እተቻ የሚባል የ11ኛ ክፍል ተማሪ ከወላጆቹ ቤት ተጠርቶ በመንግሥት ኃይሎች ተደብድቦ መገደሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፊት በነበረው የሕዝባዊ እንቅስቃሴ ወቅት በዜጎችና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት ለአልኩ ባይነት አጣራለሁ ያለው የኢሕአዴግ የቀኝ እጁ የሆነው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርትም አንድ ሰሞን ለጋሽ አገሮች መንግስት በፈፀመው መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ መብት ረገጣ ላይ ይሰነዝሩት የነበረውን ወቀሳ ለማለዘብ በመሣሪያነት ከመገልገል ዓላማ ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው እያየነው ነው።

ሌላው የሚያስገርመው የኢሕአዴግ ድራማ፣ መፈናፈኛ ያሳጣውን ሕዝቤ ያነሳውን፣ በነፃ ፍትሃዊና ተዓማኒ ምርጫ እውን እንዳይሆን ያፈነውን የሥልጣን ጥያቄ ለማዳፈን፣ ከሀገር አቀፍ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመነጋገር ስብሰባ ጠራሁ ማለቱ ነው። ይህንን ጥሪ ተቀብለን ግንኙነቱን መፍጠራችን፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማደላደል ሊያደርስ ወደሚያስችለው ድርድር ደረጃ ከፍ ለማድረግ በነበረን ዓላማ ቢሆንም፣ ለተደረገው ጥረት ኢሕአዴግ ያሳየው እምቢተኛነት፣ ቁም ነገር ላለው ድርድር እቅድ እንደሌለው በዚህ አቋሙ አስገንዝቦናል። መሠረታዊ ችግሩ ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳራ ላይ የመጣ ተግዳሮት የለብኝም በማለት በቅዠት ዓለም ውስጥ በመሆን፣ ሁኔታዎች ወደ ቀድሞ ይመለሳሉ በማለት ተስፋ ማድረጉ ነው። ስለሆነም በፖለቲካ ምህዳር ላይ የተከሰተውን መሠረታዊ ለውጥ እንኳን ማጤን ያላስቻላቸው “ጥልቅ ተሃድሶ” ከቃላት ጨዋታ ያለፈ በሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ላይ ለውጥ የሚያመጣ ፋይዳ እንደሌለው መረዳት ችለናል።

በመሆኑም ይህ የኢሕአዴግ አካሄድ ዛሬም ካለፈው ሁኔታና ጥፋት አለመማርን የሚያሳይ ስለሆነ፣ ጉዳዩ እንደገና በውል ተጢኖ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በአግባቡ ያሳተፈ ሀገራዊ ችግር መፍትሔ ፍለጋ ተግባር ላይ ትኩረት እንዲደረግ መድረክ ወትሮም እንደሚያደርገው ሁሉ ሕዝባዊ ጥሪውን አበክሮ ያቀርባል።

መላው የሀገራችን ዜጎችም በያሉበት ሆነው የሚመለከቱት የEBC አሰልቺ የስኬትና በሁሉም ጉዳዮች ላይ በሀገሪቱ ብሔራዊ መግባባት የተደረሰበት የማስመሰል ዘገባዎች፣ የኢሕአዴግ የጊዜ መግዣና የማታለያ ድርጊቶች መሆናቸውን ተገንዝበው ተገቢውን ተፅዕኖ ሁሉ በሰላማዊ አግባብ ከመድረክ ጎን በመሆን እንዲያሳርፉ ጥሪ እናስተላልፋለን።

            ድል ለሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ትግላችን!

         ሰኔ 23 ቀን 2009 ዓ.ም

         አዲስ አበባ (መሀታም አለው)   

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
160 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 970 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us