መልካም አስተዳደር ይስፈን እንጂ፤ ጨርሶ ይወገድ አልተባለም!!!

Thursday, 13 July 2017 14:55

 

ከዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዎ ግንባር (ዎሕዴግ)

የተሰጠ መግለጫ

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ እየገዘፈ በመሄድ ላይ ያለው የመልካም አስተዳደር እጦት ለማናቸውም በበጎነት ለሚታሰቡ አገራዊና ሕዝባዊ ጉዳዮች አፈፃፀም ከፍተኛ እንቅፋት በመሆን ላይ እንደሆነ፣ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ባሉ አካላት ሳይቀር እየተገለፀ ያለ ሐቅ ሆኗል።

ስለአንድ ጉዳይ ተፈጥሮአዊ ባህሪንም ሆነ፣ ተፈፃሚነቱ ሊያስከትል የሚችለውን ጥቅምና ጉዳት ጠንቅቆ ለመረዳት ችላ ማለት፣ ተረድተውም ቢሆን፣ ለሕልውና ዳኝነት ቅድሚያ መስጠትን በመዝለል፣ በጉልበት የመጠቀም ሙከራ በማድረግም ሆነ፣ በሌላ ዓይነት ስሜት በመገፋፋት የሚሰጥ ሚዛናዊነት የጎደለው አስተያየት ውሳኔና ሌሎችም ድርጊቶች የመልካም አስተዳደር እጦት ምንጮች እንደሆኑ አጠያያቂ አይሆንም።

አንድ ዜጋ በግለሰብ ደረጃም ሆነ፣ ሕዝቦች በጋራ ለሚያደርጉት ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊም ሆነ፣ ፖለቲካዊ ቀና እንቅስቃሴ መሰናከል ከመሆን ይልቅ ጥሩ አጋዥ መሆን የመልካም አስተዳደር ዓይነተኛ ምንጭ ሊሆን ይችላል። የዚህ ዓይነት ተግባር ፈፃሚው ራሱ እንደ አንድ ዜጋ ወይም እንደ አንድ የተቀባይ ማኅበረሰብ አባል የበጎ እገዛው ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

የአስተሳሰብ ቀናነትና ለራስ ዋሽቶ አለመገኘት ለፍትሐዊነት መስፈን ቁልፍ መሠረት መሆኑ መዘንጋት አይገባም። ለሁሉም ጉዳዮች መመሰቃቀል ምንጩ  የአስተሳሰብ መዛባት መሆኑ መካድ የለበትም። ግለሰቦችን ከግለሰቦች፣ ሕዝቦችን ከሕዝቦች፣ ሕዝቦችን ከመንግሥት ጋር የማቀያየም ተግባር የሚመነጨውም ከአስተሳሰብ ቀናነት መጓደል ነው ማለት ይቻላል።

በቀና ዕይታ በቀላል ጥረት አስተካክሎ ወደር የማይገኝለት ጥቅምን በየተስለፈበት መስክ ማግኘት ወይም ማስገኘት እየተቻለ በጥንቃቄ ጉድለት ወይም ከገዛ ሕልውና ጋር ባመግባባት በሚፈፅመው ተቃራኒ ድርጊት ወደር ለማይገኝለት ጉዳት ምክንያት መሆን ሲቻል ይታያል።

ጉዳዩ የሕዝባዊነት ባህሪ ያለው ሲሆን ጥቅሙም ሆነ፣ ጉዳቱ ያህንን ያህል የገዘፈ ይሆናል። ሕዝባዊነት ባሕሪ ባለው ጉዳይ ላይ የሚሰጥ ውሳኔ ቸልተኝነት የተቀላቀለበት  መሆን አይገባም።

በአሁኑ ጊዜ በዎላይታ ዞን ውስጥ በኃላፊዎች ሊፈፀም ነው የተባለ አንድ አስገራሚ ነገር እንዳለ ይገለፃል።

ጮካሬ የሚባል ከ8 ያላነሱ መንደሮች ያሉበት የዎላይታ ይዞታ አካል የሆነ፣ መሬትን በአጎራባች ሲዳማ ዞን ለማስረከብ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። ይህ ቦታ ቀደም ሲል የዎላይታ መሬት፣ መሬትን የሕዝብ ካደረገ ከ1967 ዓ.ም አዋጅ በኋላም የዎላይታ ይዞታ እንደሆነ የማኅበረሰቡ የዕድገት ታሪክ ያረጋግጣል።

ጮካሬ በዎላይታ ይዞታነት የሚገኝ  መሬት አካል ሊሆን የቻለውም፣ በጦርነት ወይም በድንበር መግፋት ሳይሆን ሰላማዊ በሆነ ጥንታዊ የሕዝቦች የአሰፋፈር ሂደትን በጠበቀ ሁኔታ ነው። ይህንን ሁኔታ የዕድሜ ባለፀጋ የሆኑ የሲዳማ አዛውንቶችም አሳምረው ይመሰክራሉ።

የዎላይታ ዞንና የሚመለከተው ወረዳ አስተዳዳሪዎች ጉዳዩን እንዴት አድርገው ከላይ እንደተባለው እየተገለፀ ባለው ሁኔታ ተፈፃሚ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ግራ ይገባል። ምን ዓይነት አስጨናቂ ሁኔታ ገጥሟቸው እየተቸገሩ እንደሆኑም የሚታወቅ ነገር የለም። የጉዳዩ ምስጢር ምንም ይሁን ምን አንተን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል ብለው የማሉለትን ሕዝብ መብት የሚረግጥ ድርጊታት ፈፅመው መገኘት አይጠበቅባቸውም።

ዎላይታ ካለበት የመሬት ጥበት የተነሳ ቁጥሩ በፍጥነት እየጨመረ በመሄድ ላይ የሚገኘውን ሕዝብ መሸከም የሚችል የግብርና ኢኮኖሚን ለማዳበር አልቻለም። ኢኮኖሚው ሕዝቡን መሸከም ላለመቻሉ ማሳያውም የዎላይታ ወጣቶች በአሁኑ ጊዜ ከቀያቸው ተፈናቅለው ትምህርት በመቅሰሚያ አፍላ ጊዜያቸው በአገሪቱ በተለያዩ ስፍራዎች ሁነው ከእጅ ወደ አፍ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ተጠምደው ዕድሜያቸውን እየገፉ መገኘታቸው ነው።

ይሁን እንጂ፣ ይህ ችግር ስለአለ ብሎ የዎላይታ ሕዝብ ከአጎራባች ዞን ወይም ከአጎራባች ክልል መስተዳደር መሬት ተቆርሶ ይሰጠኝ አላለም። ያለውን ያህል ብቻ አሟጦ በመጠቀም ችግሩን ለመቋቋም ብርቱ ጥረት ያደርጋል እንጂ፤ ታዲያ ይህ ሕዝብ፣ ካለበት ችግር ተላቆ የለማ ሕይወት የሚመራበትን መንገድ እየቀየሱና እየተገበሩ ማገዝ እንጂ፣ ተቃራኒውን ለመፈጸም እንዴት ይታሰባል? እውነትን ረግጦ ሊጠቅመው የታሰበለት ወገንም ቢሆን፣ ጊዜያዊ የሆነ፣ ከአንገት በላይ ምስጋና ቢቸር እንጂ፣ ከውስጡ አያመሰግንም። ይልቅስ ሊታዘበው ይችላል።

የሲዳማ ሕዝብ የተፈለገው ያህል ግፊት ይደረግ እንጂ፣ ከበቂ በላይ የሆነ የለማ መሬት ስላለው አግባብነት በሌለው መንገድ ከዎላይታ መሬት ተቆርሶ ይሰጠኝ አይልም። ከፊል አርብቶ አደር የሆኑ ሲዳማዎች በግጦሽ ፍለጋ ጮከሬን ብቻ ሳይሆን ሌላም የዎላይታ ይዞታ የሆነ መሬት አቋርጦ እስከ ጋሞ ጎፋ ቦሮዳ ወረዳ ድረስ ቢሄዱም ለምን አደረጋችሁ? ተብለው አያውቁም። በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለ የመቻቻልና የመተሳሰብ መንፈስ በዚህና በመሳሰሉ መልካም ተግባሮች ሲገለፅ ቆይቷል።

የሲዳማ ሕዝብ በግጦሽ ፍለጋ ወቅት ሲንቀሳቀስ የእንስሳት ኮቴ ያረፈበት መሬት ሁሉ ይዞታቱም ወደ እኔ ካልዞረ፣ ለዎላይታ ሕዝብ ለግብርና ተግባሩ መሆን የሚገባ የግሉ የሆነ ለም መሬትም ተነጥቆ ካልተሰጠኝ ይላል ተብሎም አይታሰብም። ህዝቡ ከምንም በላይ ሰላምንና ወንድማማችነትን የሚወድ አርቆ አሳቢ ሕዝብ ነውና።

ለምዕተ ዓመታት ፀንቶ የቆየ የዎላይታ እና የሲዳማ ህዝቦች የመግባባት እና የመተጋገዝ ስሜት ከአስር ወይም ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት ባልተጠበቀ ሁኔታ በተከሰተ ችግር ምክንያት እንዲሸረሸር ሁለቱም ወገኖች እንደማይፈቅዱ ሙሉ እምነት አለን። የአካባቢ ባለስልጣትም ቢሆኑ ጮካሬን ለሆነ ኢንቨስትመንት ፈልገውም ከሆነ፣ በዎላይታ ይዞታነት ሆኖ እያለ ተፈፃሚ ከማድረግ የሚያግድ ኃይል ያለ አይመስለንም።

ስለሆነም፡-

1.  በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለ የቆየና የዳበረ የወንድማማችነት አቋም ይበልጥ ተጠናክሮና ተከብሮ እንዲቀጥል ጥሪ እያደረግን፣

2.  የሁለቱም ዞኖች ነባር ድንበር ላይሸራረፍ እንዲከበር፣ አለ የተባለ ችግርም ፍትሐዊነትን በጠበቀ ሁኔታ ተፈቶ በአካባቢው የተሟላ የመልካም አስተዳደር መስፈን በክልሉ ባለስልጣናት በኩል እንዲረጋገጥ፣

3.  የዎላይታ ዞን አስተዳዳሪዎችና በተዛማጅነት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሌሎች ኃላፊዎችም ይህ ሁኔታ ሊያስከትል ከሚችለው ከሕሊናና ከታሪክ ወቀሳ ራሳቸውን የማዳኑ ሁኔታ አንድ ጉዳይ ሆኖ፣ የተነሳውን ሃሳብ በተባለው ዓይነት ከመፈፀም በመቆጠብ የዎላይታ ሕዝብ ሰብዓዊና ብሔራዊ መብት እንዳይገፋ እንዲያደርጉ እናሳስባለን።

የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዎሕዴግ)

ሰኔ 3 ቀን 2009 ዓ.ም

አዲስ አበባ

  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
191 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 91 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us