ሙስናን መዋጋት የህዝቧን ፍላጎት የምታሟላ አገር የመፍጠር ጉዳይ ነው

Wednesday, 09 August 2017 12:57

 

 

ብ. ነጋሽ

 

ሙስና ዓለም አቀፍ ችግር ነው። እ.ኤ.አ. በ1993 ዓ/ም የተመሰረተው መቀመጫውን ጀርመን በርሊን ያደረገው በሙስናና ከሙስና ድርጊት የሚመነጩ የወንጀል ድርጊቶችን በመከላከል ተግባር ላይ የተሰማራው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሙስናን፣ ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም ለግል ጥቅም የማዋል ድርጊት ሲል ይፈታዋል። ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ሙስናን፣ በሚመዘበረው ገንዘብ መጠንና በሚከሰትበት ዘርፍ ከፍተኛ፣ ቀላልና ፖለቲካዊ በሚል ይመድበዋል።


ከፍተኛ ሙስና፣ በፖለቲካ ተሿሚዎች የሚፈጸም እንደሆነ ነው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የሚገልጸው። ከፍተኛ ሙስና፣ ፖሊሲዎችን ወይም የመንግስትን ዋና አሠራር በማዛባት ከፍተኛ ባለስልጣናት በህዝቡ መስዋዕትነት ራሳቸውን የሚጠቅሙበት ሁኔታ ነው። ቀላል ሙስና በመካከለኛና ዝቅተኛ የስራ ኃላፊዎች የሚፈጸም ነው። በዚህ ደረጃ የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች በሆስፒታሎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በፖሊስ ጣቢያና በመሳሰሉ ተቋማት መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችንና አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚያደረገውን ጥረት እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመው የራሳቸውን ጥቅም የሚያስጠብቁበት ሁኔታ ነው። ፖለቲካዊ ሙስና ከሃብትና ከበጀት ምደባ ጋር በተያያዘ ፖሊሲዎችንና የአሰራር ሥርዓትን በማዛባት ሥልጣንንና የግል ሃብትን ለማስጠበቅ በፖለቲካ ውሳኔ ሰጪዎች የሚከናወን ድርጊት ነው።


ሙስና ደረጃው ቢለያይም፣ ከበለጸጉ እስከደሃ ባሉ ሁሉም ሃገራት የሚታይ ችግር ነው። ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በየዓመቱ የሃገራትን የሙስና ደረጃ የሚያሳይ ሰንጠረዥ ያወጣል። ተቋሙ ይፋ ባደረገው በ2016 ዓ/ም የዓለም ሃገራት የሙስና ደረጃ ዴንማርክ፣ ኒው ዚላንድና ፊኒላንድ በዝቅተኛ ሙስና በቅደም ተከተል ከ1 እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። በኢኮኖሚ አቅም የዓለም ቀዳሚዋ ሃገር አሜሪካ 10ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ፣ ሁለተኛዋ የዓለማችን ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ቻይና 79ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ከአፍሪካ የተሻለ የሙስና ደረጃ ላይ የምትገኘው ሩዋንዳ ስትሆን፣ በ50ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ኢትዮጵያና ግብጽ እኩል 108ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በሙስና የመጨረሻውን ደረጃ የያዘችው ሃገር አፍሪካዊቷ ሶማሊያ ስትሆን 176ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ደቡብ ሱዳን ከሶማሊያ ከፍ ብላ 175ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።


በትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የሙስና ኢንዴክስ 108ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ሃገራችን ኢትዮጵያ አደገኛ ደረጃ ላይ ነች ብሎ መውሰድ ይቻላል። ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያን በ2014 ዓ/ም 110ኛ፣ በ2015 ዓ/ም 103ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል። ይህ ደረጃ ባለፉት ሶስት ዓመታት የኢትዮጵያ ሙስና ተሻሸሏል ወይም ዝቅ ብሏል ማለት አያስችልም። የደረጃ መሻሻል ወይም ማሽቆልቆል የሚያመለክተው አሃዝ ከኢትዮጵያ የሙስና ደረጃ መሻሻል ወይም ማሽቆልቆል የመነጨ ከመሆን ይልቅ፣ ከሌሎች ሃገራት ደረጃ መዋዠቅ ጋር የተያያዘ ወደመሆኑ ያዘነብላል።


ከትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የደረጃ ምዘና ወጣ ብለን በሃገሪቱ የነበረውንና ያለውን የሙስና ሁኔታ ስናስተውል ግን ሙስና ቀንሷል ማለት ባያስደፍርም፣ ቢያንስ ማህበረሰቡ ሙሰናን እንደጸያፍ ድርጊት የሚያይበት ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያመለክቱ ሁኔታዎችን እናስተውላለን። በዘውዳዊው ሥርዓት ሙስና ለወጉ ያህል የተከለከለ ድርጊት ነው ቢባልም፣ በአዋጅ የተፈቀደ ያህል በይፋ የሚፈጸምና የስልጣን ማሳያ ነበረ። ሙስና ነውር አልነበረም። ባለርስቱ ግብር እንዲሰበስቡ ከሚያሰማራቸው ጭቃ ሹምና መልከኛ ጀምሮ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ከወረዳ እስከ ጠቅላይ ግዛት፣ ከጠቅላይ ግዛት እስከቤተ መንግስት ሙስና ነውር ሳይሆን የባለስልጣንነት ወግ ነበር፤ ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል።


በወታደራዊው ደርግ ሥርዓት፣ መንግስት የሃገሪቱን ኢኮኖሚ፤ የማምረት፣ የወጪና የገቢ፣ የችርቻሮና የጅምላ ንግድ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ስለነበረ በየደረጃው ያሉ በዚህ የንግድና የምርት ዝውውር ውስጥ ያሉ ባለሥልጣናት፣ ሞያተኞችና ተራ ሠራተኞች ጭምር ዝውውሩን በማጥበቅ የይለፍ እጅ መንሻ ይቀበሉ ነበር። የጉምሩክና የፋይናንስ ፖሊስ ደግሞ የሙስና መናኸሪያዎች ነበሩ። ከዚያ ቀደም በነበሩት ሥርዓቶች ፈጽሞ ያልነበረ ልዩ ሙስናም ነበር፤ በወታደራዊው ደርግ ሥርዓት። ይህም ከብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ጋር የተገናኘ ነበር። በግዳጅ ለብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት የሚመለመሉ ወጣቶችን ከአገልግሎቱ ለማስቀረት ወላጆች ለአብዮት ጠባቂ ሊቀመንበሮችና በየደረጃው ለነበሩ ወታደራዊ ኮሚሳሮችና አዛዦች በሺህ የሚቆጠር ገንዘብ ጉቦ ይከፍሉ ነበር። በጉቦ ተለቅቀው ከኮታው በጎደሉ ወጣቶች ምትክ ወገንና ገንዘብ የሌላቸው የደሃ ልጆች ከተገኙበት ተይዘው ማሟያ ይደረጋሉ።


በወታደራዊው ደርግ የስልጣን ዘመን የኢኮኖሚው እንቅሰቃሴ እጅግ ደካማ ስለነበረ በሙስና የሚከፈለውና ከቀበሌ ጀምሮ ባሉ የመንግስት ተቋማት፣ መንግስታዊ የንግድና የማምረቻ ድርጅቶች የሚመዘበረው ገንዘብ በሺሆች የሚቆጠር ነበር። ይህ የወታደራዊውን ደርግ ሙስና ከአሁን ጋር ሲነጻጸር ቀላል ቢያስመስለውም፣ በቁጥጥር ሥርዓትና ድርጊቱን እንደጸያፍ በመመልከት ደረጃ ግን አሁን የተሻለ ሁኔታ መታየቱ እውነት ነው። እርግጥ አሁን የሃገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ በማደጉና የቢሊየን ኢኮኖሚ ላይ በመደረሱ፣ በመንግስት የሚከናወኑት የልማት ፕሮጀክቶችም በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ የሚደረግባቸው ግዙፍ በመሆናቸው በሙስና ቅብብልና ምዝበራ ላይ ያለው ገንዘብ በመቶ ሚሊየኖች የሚቆጠር ለመሆን በቅቷል።


የኢፌዴሪ መንግስት ሙስና ሃገሪቱ የተያያዘችውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ የለውጥ ሂደት ሊያደናቅፍ የሚችል አደጋ መሆኑን የተገነዘበው ገና ከጠዋቱ ነበር። የፌደራል የስነምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን በ1993 ዓ/ም መቋቋሙ ይህን ያመለክታል። በሙሰኞች ላይ እርምጃ የመውሰዱ እንቅስቃሴ ግን ከዚያ ቀደም ነበር የተጀመረው። በ1989 ዓ/ም በወቅቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ነጋዴዎችና አቀባባዮች ላይ የተወሰደው እርምጃ፣ እንዲሁም በ1993 ዓ/ም በሽግግር መንግስቱ ወቅት የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዬ አብረሃና አባሪዎቻቸው ላይ የተወሰደውን የህግ እርምጃ ለዚህ ማሳያነት መጥቀስ ይቻላል። የሥነምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ከተቋቋመም በኋላ በገቢዎችና ጉምሩክ ከፍተኛ አመራሮች፣ ነጋዴዎችና አቀባባዮች ላይ እርምጃ ተወስዷል።


የሥነምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ከተቋቋመ በኋላ የሙስና ወንጀል ጥቆማዎችን ተቀብሎ በመመርመር ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ በመመስረት እንዲቀጡ ከማድረግ በተጨማሪ፣ በተለያየ መንገድ ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ ለመፍጠር የአመለካከት ለውጥ ሥራ ተከናውኗል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጭምር በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው እንዲቀጡ በማድረግ ረገድ ጉልህ ስራዎች ተከናውነዋል። ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን በሙስና እንዲጠየቁ በማድረግ ረገድ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በቀዳሚነት ደረጃ ላይ የምትገኝ ይመስለኛል። እነዚህ ሁኔታዎች አሁን ሙስናን ቢያንስ እንደጸያፍ ድርጊት የሚቆጥር ትውልድ መፍጠር አስችለዋል የሚል ግምት አለኝ። አሁን ሙስና የሥልጣን ማሳያና ጀብድ ሳይሆን ነውር ነው። ይህ ቀደም ሲል ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲታይ ሙስናን የማቃለሉ ሂደት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ያመለክታል።


ሰሞኑንም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ ነጋዴዎችና ደላሎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋሉት የሙስና ተጠርጣሪዎች 51 ደርሷል። ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ዋናና ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች፣ የመንግስታዊ የልማት ተቋማት ስራ አስኪያጆች፣ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ይገኙበታል። አነዚህ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ወይም ባለስልጣናት ናቸው።


እንግዲህ፣ ባለፉት ዓመታት ሙሰና የሃገሪቱ መሰረታዊ ችግር መሆኑ ሲገለጽ መቆየቱ ይታወቃል። ይህም በየደረጃው ባሉ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና በፍትህ ተቋማት የመልካም አስተዳደር መጓደል፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ አፈፃፀም መጓተትና ከተያዘላቸው በጀት እጥፍና ከዚያ በላይ ወጪ መጠናቀቅ፣ አንዳንዶቹም ተቋርጦ መቅረት ወዘተ ተገልጿል። ይህ ሁኔታ መንግስትን አሳስቦታል ህዝብንም አስቆጥቷል። ባለፈው ዓመት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የታየው የህዝብ ቁጣ ከሙስና/ኪራይ ሰብሳቢነትና ካስከተለው የመልካም አስተዳደር መጓደል የመነጨ ነው።


ይህን ተከትሎ የፌደራልና የክልል መንግስታት እርምጃ ለመውሰድ ቃል ገብተው ነበር። ከያዝነው ዓመት ጀምሮ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች በተለያየ ደረጃ በሙስናና በመልካም አስተዳደር ማጓደል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ እንደተገኘባቸው የማስረጃ ደረጃ አስተዳደራዊ እርምጃና የፍርድ ቤት ክስ ሲመሰረትባቸው ቆይቷል። የሰሞኑ በጠቅላይ አቃቤ ህግ የተወሰደ እርምጃ ዓመቱን ሙሉ በምስጢር መረጃና ማስረጃ ሲሰባሰብበት ቆይቶ የተወሰደ ነው። የሰሞኑ የሙስና ተጠርጣሪዎች ለተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ለመጠየቅ ፍርድ ቤት ቀርበው የጊዜ ቀጠሮ ተይዞባቸዋል። የክሱን ሂደትና የሚቀርበውን ማስረጃ ወቅቱ ሲደርስ የምንመለከተው ይሆናል።


በአጠቃላይ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት የሙስና ሁኔታ አደገኛ ነው። ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ የባለፉት አንድ ተኩል አስርት ዓመታት የኢኮኖሚ እድገት፣ እስካሁን በዘለቀበት ፍጥነት በማስቀጠል መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት በ2017 መካከለኛ ገቢ ደረጃ ላይ ያለች ሃገር የመፍጠሩ ጉዳይ ጉልህ ፈተና የሚገጥመው መሆኑ አይቀሬ ነው። በመሆኑም፣ መንግስትና በኢኮኖሚ እደገቱ ኑሮው እንዲሻሻል የሚጠብቀው ህዝብ በጋራ በሙሰኞች ላይ ምህረት የለሽ እርምጃ ለመውሰድ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል። ሙስናን መዋጋት ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በቀጣይ ዓመታት የህዝቧን ፍላጎት ማሟላት የሚችል የኢኮኖሚ አቅም ያላት ሃገር የመፍጠር ያለመፍጠር ጉዳይ መሆኑ መታወቅ አለበት።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
172 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1049 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us