መለስን በጨረፍታ ከዲፕሎማሲው አምባ

Wednesday, 16 August 2017 12:39

 


(የዲፕሎማቶቹ ምስክርነት)

ከአዶናይ

 

ስለታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ማንነት፤ ባህሪይ፤ የአገርና የህዝብ ፍቅር፤ አንባቢነት፤ የስራ ወዳድነትና ታታሪነት፤ ወዘተ… ከመሳሰሉ ተነግረው ከማያልቁና ትውልዱ ሊማርባቸው ከሚገቡ በርካታ ቁም ነገሮች ውስጥ እጅግ በጥቂቱ፤ ለዚያውም ከህልፈቱ በኋላ መስማትና ማንበብ ችለናል። ስለመለስ ከተለያዩ ፅሁፎችና ሚዲያዎች፤ ከቅርብ ጓደኞቹ፤ የስራ ባልደረቦቹ፤ የመንግስት ባለስልጣናት፤ የውጪ ሙሁራንና ፖለቲከኞች በጨረፍታ ብናነብም ሆነ ብንሰማም እነዚህ በጥቂቱ የተነገሩ እውነታዎችም ሳይቀር በአንዳንድ ወገኖች የአንድ ወገን ምስክርነት ተደርገው የሚታዩበት ሁኔታ ይታያል። ያም ሆነ ይህ ጥሩ የሰራ ሰው የሰራው ጥሩ ስራ ለዘለአለም ከመቃብር በላይ ሆኖ ታሪክ ሲዘክረው የሚኖር በመሆኑ ወደፊትም ስለ መለስ ዜናዊ ገና ያልሰማናቸውን፤ ያላነበብናቸውንና ያላወቅናቸውን ተነግረው የማያልቁ ጥንካሬዎቹንና ብቃቶቹን እየሰማንና እያነበብን ለራሳችን ከመማር አልፈን ትውልድንም እየቀረፅን እናልፋለን የሚል እምነት አለኝ።


ለአሁኑ ፅሁፌ መነሻ የሆነኝ ስትራቴጂክ ቲንኪንግ ኦን ኢስት አፍሪካ የተባለ ድረገፅ ኢድቶሪያል ቦርድ እ.ኤ.አ ኤፕሪል 14/2016 ስለመለስ ዜናዊ ለንባብ ያበቃውን ፅሁፍ ሳነብ ከብልህ ፖለቲከኛነቱና መሪነቱ ባሻገር እዚህ ግቢ ተብላ ከምንም ትቆጠር ካልነበረች ከአንዲት ደሀ አገር ተፈጥሮና የዚህች ደሀ አገር መሪ ሆኖ በአለም አቀፉ የዲፕሎማሲ መድረክ ለአገሩ ጥቅም ብርቱ ጠበቃ መሆን የቻለ ነበር፡፡ ከዚህም ከመሆን አልፎ በነበረው ጥልቅ ሁለንተናዊ አቅምና ብቃት ኃያላን ለሚባሉቱ መንግስታት ከፍተኛ የዲፕሎማቲክ ወኪሎች ሳይቀር ምክሩን በመለገስ ጭምር የነበረው በሳል የዲፕሎማሲ ብቃትና በራስ መተማመን የተሞላበት የተደራዳሪነት አቅም ስላስደመመኝ፤ እንዲሁም ከጓደኞቹ፤ ከትግል አጋሮቹና ወገንተኛ ተብለው በጭፍኑ ከሚተቹ ፀሀፍት ውጪ ስለመለስ የሌሎች አገር ሰዎችና ዲፕሎማቶች ምን አስተያየት አላቸው? እንዴትስ ይረዱት ነበር? በሚለው ጉዳይ ላይ ከዚሁ ድረ-ገፅ ፅሁፍ እኔ ለማወቅ የቻልኩትን ለአንባቢዎችም ማካፈል አለብኝ የሚል ስሜት ውስጤን ፈንቅሎት በመውጣቱ የእንግሊዘኛ ፅሁፉን እንደሚስማማ አድርጌ በአማርኛ በመተርጎም እነሆ ለማለት ተገደድኩ።


የአሜሪካ መንግስት የውጪ ጉዳይ መስሪያቤት የሚስጥራዊ ቴሌግራም መልእክት ሰነዶች ግምጃ ቤት በመባል የሚታወቀውና የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤቱን የቴሌግራም መልእክቶችን በማነፍነፍ ይፋ በሚያደርገው ዊኪሊክ ድረ-ገፅ የአሜሪካውያኑ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ብቻ ሳይሆን የአለም መሪዎችና የየአገራቱ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች ከአሜሪካ ዲፕሎማቶች ጋር የሚያደርጓቸው ጥልቅ ውይይቶች፤ በጊዜውና በወቅቱ ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚያነሷቸው ሀሳቦችና የመልእክት ልውውጦች፤ አንዳንድ ጊዜም ከነዚህ ውይይቶችና ሀሳቦች ጀርባ ያሉ ግለሰቦች ጭምር ሳይቀሩ እየታደኑ በጨረፍታም ቢሆን ይፋ ይደረጋሉ።


በየመገናኛ ብዙሀኑ ከሚነገሩ ለዛቢስና አሰልቺ አገላለፆች ባለፈ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለአገሩ፤ ለምስራቅ አፍሪካ እንዲሁም ለራሷ ለአሜሪካ ፖለቲካ ስለነበረው ራእይና እውቀት የውጪው አለም ያለውና የነበረው ግንዛቤ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በየሚዲያዎቹ ሪፖርቶች ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚገለፀውና የሚታየው አገሪቷን ያለተቀናቃኝ በጠንካራ መዳፉ በብቸኝነት እየመራ ያለ፤ ግትር፤ የሰውን ሀሳብ ብቻ ከመቅዳት ባለፈ የራሱን ሀሳብ ማፍለቅ የማይችል (stereotypical) እና ነገሮችን በአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚያይ የአፍሪካ ትልቁ ሰው /Big Man/ እንደሆነ ተደርጎ ነው። ነገር ግን እውነታው ይህ ሳይሆን መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያም ሆነ የአፍሪካ እምቅ አቅም፤ የእድገት ተስፋ እንዲሁም ኢትዮጵያም ሆነች አፍሪካ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ክብ ጠረጴዛ እኩል ቦታ እንደሚኖራቸው አስቀድሞ የታየው ብልህ ሰው ነበር። እናም መለስ ዜናዊ ይህንን ሊሆንና ሊታመን የማይችል የኢትዮጵያና የአፍሪካ ታሪክ በአስደናቂ ሁኔታ መቀየር የቻለ ታላቅ ሰው ነው።


ከአራት አመታት በፊት በአሳዛኝ ሁኔታ በድንገት ስለተለየን የኢትዮጵያው የቀድሞ ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ በራሳቸው በኢትዮጵያውያን ፍላጎት ላይ የተመሰረተውን አዲስ ራእዩንና ይህን ራእዩን በራሱ መንገድ የከፍታው ጫፍ ላይ እንዴት እንዳደረሰው የዊኪሊክ የቴሌግራም መልእክቶች (cabeles) በጥቂቱ ጨልፈው ያሳዩናል።


በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር በነበሩት ዶናልድ ያማማቶና ምክትሉ ቪኪ ሁደልሰን አማካኝነት በተለያዩ ጊዜያት ለአሜሪካን የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት የተላኩት አብዛኞቹ የቴሌግራም መልእክቶች በአሜሪካውያኑ ዲፕሎማቶችና በኢትዮጵያው መሪ መካከል ሲደረጉ የነበሩ ውይይቶች ግልፅነት የሚንፀባረቅባቸውና አንዳንዴም ለዲፕሎማቶቹ በመጠኑ ምቾት በማይሰጡ ሁኔታዎች የተከተቡ እንደነበሩ ይጠቁማሉ። በጠቅላይ ሚኒስትሩና በዲፕሎማቶቹ መካካል የተደረጉ የውይይት አርእስቶች በአብዛኛው በኤርትራ፤ በኢሳያስ አፈወርቂ፤ በሶማሊያ፤ በሱዳን፤ በኬንያና በራሷ በኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ነበሩ።


የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር የአገሩን ጥቅም በላቀና በተሻለ ሁኔታ ለማስጠበቅ በሚከተላቸው ስትራቴጂዎችና ታክቲኮች ላይ የአሜሪካውያኑ ዲፕሎማቶች ብዙውን ጊዜ ባይስማሙም ለነዚህ ስትራቴጂዎችና ታክቲኮች መነሻ በሆኑት የመለስ ትንታኔዎች ላይ ያለምንም ማቅማማት በእርግጠኝነት ይስማሙ ነበር። መለስ ዜናዊ በመሬት ላይ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ያለውን ሰፊና ጥልቅ ግንዛቤ፤ ሁለገብ ምሁራዊ አቅምና ብቃት፤ በተግባራዊ እውነታ ላይ የተመሰረተ/pragmatic/ በሳል የፖለቲካ ክህሎት ከወቅትና ከጊዜ ጋር አጣምሮ በተግባር ማሳየት የቻለ ሰው ነው።


ከዚህም በተጨማሪ መለስ ከተለመደውና ፊትለፊት ከሚታየው ነባራዊ ሁኔታ ባሻገር ሁኔታዎችን ለማየትና ውጤታቸውን ለመተንበይ የሚያስችል እጅግ የተለየ የፖለቲካ አስተውሎትና እይታ የተቸረው መሪ ነበር።

መለስ በኤርትራ ላይ
በጉዳዩ ላይ በመገናኛ ብዙሃን ሲነገሩ ከነበሩ ዘገባዎች በተቃራኒው በአሜሪካን መንግስት ባለስልጣናትና በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መካከል የተደረጉ በርካታ ስብሰባዎችና ውይይቶችን በሚመለከት ለአሜሪካን የውጪ ጉዳይ መስሪያቤት ከተላኩ የቴሌግራም ልውውጦች ውስጥ በርካቶቹ በዊኪሊክ ድረ-ገፅ ላይ ይፋ ተደርገዋል። የአሜሪካ መንግስት አምባሳደሮች፤ ሌሎች ዲፕሎማቶችና የኮንግረስ አባላት ከመለስ ዜናዊ ጋር ሁለቱን አገራት በማያግባቡና በሚያለያዩ ጉዳዩች ጭምር ሳይቀር ለበርካታ ጊዜያት ረጅም ጊዜ የወሰዱ ውይይቶችና የሀሳብ ክርክሮች ሲደረጉ እነዚህ በሁለቱ መንግስታት መካከል የነበሩ ውይይቶችና ክርክሮች እጅግ ግለሰባዊ ወዳጅነት በተሞላበት፣ ተከታታይና ጠንካራ ግንኙነት ላይ የተመሰረቱ ነበሩ።


ከነዚህ በርካታ ውይይቶችና የሀሳብ ልውውጦች ውስጥ መለስ ዜናዊ የመንግስቱ ሀይለማርያምን አገዛዝ ለመጣል በተደረገው የትጥቅ ትግል አጋሩ ስለነበረው የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አስተሳሰብ ያለው የጠለቀ እውቀትና ከዚህ በመነሳትም ለአሜሪካኖቹ የሰጠው ኢንፎርሜሽንና ምክር ለአሜሪካን መንግስት ትልቅ ትርጉምና ዋጋ ነበረው። ምንም እንኳን በኤርትራውያኑ ፖለቲከኞች ያረጀ ያፈጀ የበላይነት አስተሳሰብና እምነት በተወሰነ ደረጃ ኢሳያስ የመለስ አለቃ ተደርጎ የሚቆጠር ቢሆንም፤ የኤርትራውያን መሪዎች ራሳቸው ከዚህ ምሁር መሪ እጅግ በርካታ ነገሮችን ተምረዋል ቢባል ለብዙዎቹ ማመን ቀላል አይሆንላቸውም። ሁለቱ ሰዎች (መለስና ኢሳያስ) እርስ በእርሳቸው በደንብ የሚተዋወቁ ናቸው።


በአንድ ወቅት የኤርትራ መንግስት ሽብርተኝነትን እንደሚደግፍና ኤርትራ ሽብርተኝነትን ከሚደግፉ መንግስታት ዝርዝር ውስጥ የመግባቷን ሁኔታ የአሜሪካ መንግስት እያጤነ የመሆኑን ዜና የአሜሪካኑ አምባሳደር ያማማቶ ለመለስ ሲያቀብሉ መለስ በበኩሉ ይህ ከመሆኑ በፊት በቅድሚያ አምባሳደሩ የኢሳያስን ስነልቦናዊ ባህሪይ በሚገባ መረዳት እንዳለባቸውና ሁኔታው በአሜሪካ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ስጋት በጥንቃቄ ማጥናት እንደሚገባቸው ለአምባሳደሩ ምክር ለግሷቸው ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይ መለስ “ጠመንጃ የምትጠቀም ከሆነ በውስጡ ጥይት ያለው መሆኑን እርግጠኛ መሆን ይኖርብሃል” ብሎ ነግሯቸው እንደነበርና መለስ ይህንን ለማለት የፈለገበት ምክንያትን አሜሪካን ሽብርተኝነትን በሚረዱ መንግስታት ዝርዝር ውስጥ የኤርትራን መንግስት ለማስገባት እያጤነች የመሆኑን መግለጫ ለመስጠት ካሰበች ሁኔታውን በደንብ መከታተል እንዳለባትና ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን ለኢሳያስ ታላቅ ድል እንደሚሆን ለማመልከት እንደሆነ የአሜሪካው አምባሳደር ያማማቶ ይገልፃሉ።


አምባሳደር ያማማቶ ኢሳያስ አፈወርቂ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ኤርትራን ተፅእኖ ፈጣሪ፤ ራሱን ደግሞ በአካባቢው ተፈላጊና ከፍተኛ ዋጋ ያለው መሪ የማድረግ ህልምና ፍላጎት ስላለው ይህንን ህልሙንና አላማውን ለማሳካት እጅግ አደገኛ፤ ሁከተኛና በጥባጭ፤ ጨካኝ እንደሆነ መለስና በመለስ ዜናዊ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ያምናሉ ሲሉ ይገልፃሉ። አምባሳደሩ በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸውን አስተያየት በመቀጠል ኢሳያስና የኢሳያስ አመራር ይህንን የአካባቢው የበላይ የመሆን ህልሙን እውን ለማድረግና ለማረጋገጥ የኤርትራ ህዝብ ሊቋቋመው ከማይችለው የኢኮኖሚ ድቀት ጀምሮ ሳይወድ በግድም ቢሆን እስከ ሞት መስዋእት ለማድረግ ወደኋላ እንደማይል ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በእርግጠኝነት እንደሚያምን ይገልፃሉ። እንደ አምባሳደሩ አገላለፅ ኢሳያስ በወታደራዊ አቅሙ በኢትዮጵያ ላይ ምንም የማድረግ አቅም እንዳሌለው ጠንቅቆ ያውቃል ብሎ መለስ እንዳስረዳቸውና ሀሳቡንም በመቀጠል የኢሳያስ ስትራቴጂ በቀጥታ ከኢትዮጵያ ጋር ከመዋጋት ይልቅ በተዘዋዋሪ መንገድ የጦርነት አባዜውን ወደ ሶማሊያና ሱዳን በመውሰድ የጦርነት አድማሱን በሌላ መንገድ ማስፋት እንደሆነና ይህንን ለማድረግም ሶማልያን በማተራመስ፤ የኢትዮጵያን ምእራባዊ ክፍል ለማጥቃት ሱድንን በመጠቀም በኢትዮጵያና ጅቡቲ መካከል ውጥረትና ግጭት እንዲፈጠር በማድረግ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ውስጣዊ ልዩነቶችን ለማባባስ የሚያስችል ድጋፍ በማድረግ፤ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችን በሽብርተኝነት በማሰልጠንና በማሰማራትና የአለም አቀፍ ማህበረሰቡ በኢትዮጵያ ላይ ትኩረቱን በማድረግ ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ የምትሰነዝረውን ክስ አሳንሶ እንዲያይ ማድረጉን የሚቀጥል መሆኑና ይህ ማለት ደግሞ የኤርትራ መንግስት በሌሎች መንገዶችና ዘዴዎች በኢትዮጵያ ላይ የሚከተለው የጦርነት ስትራቴጂ ያለ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያምን አምባሳደሩ ያስረዳሉ።


አምባሳደሩ ኢሳያስን በአለማቀፍ መድረኮች ያለማሳተፍና ኤርትራን መነጠል የኤርትራን ሰርጎገቦች ለመገደብ ተመራጩ ስትራቴጂ እንደሆነና ኢሳያስና የኤርትራ መንግስት ከኢትዮጵያ በላይ ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት የበለጠ አደጋ ናቸው ብሎ ስለሚያምን በሶማሊያ ያሉ ለሶማሊያ መረጋጋት አደገኛ የሆኑ አክራሪ ቡድኖችን በማዳከም በሞቃዲሾ ተቀባይነት ያለው ጠንካራ መንግስት በመመስረት ሶማሊያን ማረጋጋት በጣም አስፈላጊው ጉዳይ እንደሆነ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ያምናል ሲሉ ይገልፃሉ።


ዲፕሎማቶቹ አስተያየታቸውን በመቀጠል ስለመለስ እንዲህ ይነግሩናል። እ.ኤ.አ. ከ1998 ቀደም ብሎ የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት በይፋ ከመጀመሩ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለአሜሪካን መንግስት የኤርትራው መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ሚዛናዊ ውሳኔ ሰጪ ያለመሆኑንና የመንግስት አስተዳደር ህግና ስርአቶችን በሚገባ የማይረዳ ሰው እንደሆነ አሳውቆ የነበረ መሆኑንና ኢሳያስ ለነባራዊ እውነታ ያለው አረዳደድ መለስና እሱ ከሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት አረዳድ በእጅጉ የተለየ መሆኑን አጠንክሮ ይከራከር እንደነበር ይገልፃሉ።


በመሬት ላይ ካሉ ተጨባጭ ነባራዊ እውነታዎች በመነሳት መለስ አሜሪካ በኢትዮጵያና ኤርትራ ላይ የምታራምደው ፖሊሲ ወደኤርትራ ያደላ እንደሆነ ስለሚያምን አሜሪካን ለበርካታ አመታት ኢትዮጵያንና ኤርትራን በአንድ ሚዛን የምታይበትን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ አለማዊ እይታና ከኢትዮጵያ ይልቅ ለኤርትራ የነበራትን የተዛባ ሚዛንና አቋም አጥብቆ ይቃወም ነበር። በዚህ ብቻ ሳያበቃ ኤርትራ ምንም ታደርግ ምን በጭፍን ለኤርትራ መንግስት የሚያዳሉና የኢትዮጵያን ጥቅም የሚፃረሩ በርካታ የአሜሪካ መንግስት ባለስልጣናት እንዳሉ የኢትዮጵያ መንግስት ያምን ነበር። ለምሳሌ በኤርትራ መንግስት የአየር ድብደባ መቀሌ ላይ ለተገደሉ ንፁሀን ህፃናት ደንታ ሳይሰጠው፤ በዛላንበሳ ላይ በኤርትራ ሀይሎች ለደረሰው ውድመትና በዚህ ሳቢያም እስከ 170,000 የሚጠጉ የትግራይ አርሶ አደሮች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ለችግር መዳረጋቸው ሳያሳስበው ኢትዮጵያ ለአገር ደህንነት ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ ብላ ያሰበቻቸውን ኤርትራውያንን ከሀገሯ ስታስወጣ የአሜሪካን መንግስት ድርጊቱን የሚያወግዝ ጠንካራ መግለጫ ነበር ይፋ ያደረገው። ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ይህ መግለጫ ፍትሀዊና ሚዛናዊ ያልሆነ መግለጫ እንደነበር ስለሚያምን በጉዳዩ ላይ አጥብቆ ይከራከር ነበር።


ከዚህ በተጨማሪም መለስ የአሜሪካ መንግስት ለኤርትራ መንግስት ባለው የተሳሳተ አመለካከትና አቋም ምክንያት ጦርነቱን ለማስቀረት የሚያስችል ሚናውን እንኳን አልተጫወተም ብሎ ያምናል። ይህን አቋሙንም ለአሜሪካኖቹ በግልፅ በማሳወቅና አቋማቸውን እንዲያስተካክሉ ለማደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አሜሪካኖቹ በኢሳያስ ወረራ ያላቸውን ተቃውሞ ለራሱ ለኢሳያስ በግልፅ እንዲያሳውቁት የሚከተለውን አገላለፅ አዘጋጅቶ ሰጥቷቸው እንደነበር በወቅቱ የነበረው አሜሪካው ምክትል አንባሳደር ይገልፃል። መለስ አዘጋጅቶ አሜሪካኖቹ ለኢሳያስ እንዲያሳውቁት የሰጣቸው መልእክት እንዲህ ይነበባል። “ኢሳያስ ይህ የአንተ ጥፋት ነው። ባድመን ለቀህ መውጣትህ የተወሰነ የፖለቲካ ዋጋ ሊያስከፍልህ ይችል ይሆናል። ይህን ሳታደርግ ብትቀር ጦርነቱን ለማስቀረት ላንተ ከምናደርገው ድጋፍና ኢትዮጵያ ላይ ከምናደርገው ግፊት ውጪ ሃላፊነቱ የራስህ ነው።” የሚል እንደነበር ምክትል አንባሳደሩ ይገልፃል። (እዚህ ላይ በመለስ ተፅፎ ለአሜሪካኖቹ የተሰጠውን የእንግሊዘኛ ፅሁፍ ሳይሸራረፍ እንዳለ ለአንባቢዎች አቅርቤዋለሁ)


“Isayas, this is your mess, you may pay some political costs by withdrawing from Badme, but if you do not, you are on your own, without our support and without our pressure on Ethiopia to avoid the war”


መለስ በወቅቱ በኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ ላይ አሜሪካኖቹ ሲያራምዱት የነበረውን ፖሊሲ በመቃወም አሜሪካን ነገሮች እየሄዱ ባሉበት መንገድ እና እየተባባሱ እንዲሄዱ በመፍቀዷ ምክንያት ጭምር ኢሳያስ ባድመን በፍቃደኝነት መልቀቅ ካልቻለ ኢትዮጵያ ኢሳያስን ሳይወድ በግድ ከባድመ ለማስወጣት የሚገድባት አንዳችም ነገር እንደማይኖር የአሜሪካ መንግስት ማወቅ እንዳለበት ግልፅ አድርጎላቸው እንደነበር አምባሳደሮቹ በቴሌግራም መልእክቶቻቸው ለመንግስታቸው ማሳወቃቸውን በመግለፅ ፅሁፉ የክፍል አንድ ሀሳቡን ይቋጫል። እኔም ድረ-ገፁ በክፍል አንድ ያሰፈረውን ሀሳብ በማጠቃለል በቀጣዩ ጊዜ በክፍል ሁለት የፃፈውን ይዤላችሁ እመለሳለሁ።
ቸር ይግጠመን!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
154 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 153 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us