በተሻሻለው የገጠር መሬት አዋጅ በመሬት የመጠቀም መብትን ለብድር ዋስትና ማስያዝ እና የአርሶ አደሩ ፈተና!

Wednesday, 15 November 2017 12:54

 

በፍቃዱ አንዳርጌ መኮንን (www.abyssinialaw.com)

ከመሬት ጋር ሕይወቱ የተሳሰረዉ አርሶ አደር ከመሬት ተዝቆ የማያልቅ ሃብት እንዳለ ያምናል። በመሬቱ ያለዉ መብት ቀጣይነት ያለዉና በእርግጠኛነት ስርዓት ላይ የተመሰረተም እንዲሆን ይፈልጋል። መሬቱን ተጠቅሞ መክበር ሆነ መከበር ይፈልጋል። መሬቱን ሆነ ጥርኝ አፈሩን በዋዛ ፈዛዛ አሳልፎ መስጠት አይፈልግም። ጥግ ድረስ ቢርበዉና ቢቸግረዉ በሬዎቹን ከነበሬ ዕቃ (ሞፈርና ቀንብር) መሸጥ የማይፈልገዉ አርሶ አደር መሬቱን እንዲሁ በቀላል አሳልፎ ይሰጣል ማለት አይቻልም። አርሶ አደሩ ሁሌም በመሬቱ የሰፋ መብት እና ነፃነት እንዲኖረዉም ይፈልጋል። በመሬት ላይ የሚወጡ ሕጎችም ከሌሎች ሕጎች በተለዬ መልኩ ትኩረት የሚፈልጉት ሰፊ ማዕቀፍ ባላቸዉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተፈፃሚ ስለሚሆኑ እና ቀላል የማይባል ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተፅኖኖ ስለሚኖራቸዉ ነዉ። 
አብዛኛዉን ጊዜ በመሬት ላይ የሚዘጋጁ ሕጎች በወጡ ቁጥር አከራካሪ መሆናቸዉ የተለመደ እየሆነ መጥቷል። ቀደም ሲል በገጠር መሬት ላይ የወጡ ሕጎች የአማራ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 133/1998 ጨምሮ አርሶ አደሩ በመሬቱ ላይ ያለዉን መብት በተመለከተ ሰፊ የሆነ መብት አልሰጡም በማለት ሲተቹ ቆይተዋል። የተሻሻለዉ የአማራ ክልል ገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 252/2009 በተደጋጋሚ ሲነሱ ለነበሩ ችግሮች መልስ በሰጠ መልኩ እንደተዘጋጀ በመግለጽ በአዲስ መልኩ ፀድቋል። አዋጁም እንደገና ሊወጣ የቻለዉ አርሶ አደሩ በመሬቱ ላይ ያለዉን መብት ለማስፋት እንደሆነም በመግቢያዉ ላይ ያትታል። ይህ ሕግ ቀደም ሲል በነበሩ ሕግ ያልታቀፉ መብቶች ዉስጥ አዲስ ነገር ይዞ የመጣ ሲሆን በገጠር መሬት ላይ ያለን የመጠቀም መብት በዋስትና ማስያዝ እንደሚቻልም በአዲስ መልኩ ደንግጓል።


በአዋጅ ቁጥር 252/2009 አንቀፅ 19(1) በገጠር መሬት ላይ ያለን የመጠቀም መብት ለዕዳ በዋስትና ማስያዝ እንደሚቻል መግለፁ አርሶ አደሩ በመሬቱ ላይ ያለዉን መብት ሊያሰፋ የሚያስችልና ተጨማሪ የኢኮኖሚ አማራጭ መሆኑ በበጎነት የሚነሳ ነዉ። ሆኖም በዚህ አዋጅ አንድ አርሶ አደር የመጠቀም መብቱን ለዕዳ በዋስትና ማስያዝ የሚችለዉ በብሔራዉ ባንክ እዉቅና ለተሰጠዉ የገንዘብ ተቋም ብቻ እንደሆነ ገደብ አስቀምጧል። ይህ ማለት ደግሞ አርሶ አደሩ በመሬቱ ላይ ያለዉን የመጠቀም መብት ለዕዳ ዋስትና ማድረግ የሚችለዉ በሕጉ በተቀመጠዉ አበዳሪ ተቋም ብቻ ነዉ ማለት ነዉ። አርሶ አደሩ እስካሁን በመሬቱ ላይ ከነበረዉ መብት የሰፋ መብት በአዲሱ አዋጅ ቢሰጠዉም አሁንም አዋጁ ከትችት አልዳነም። የመጠቀም መብትን በዋስትና ማስያዝ ጋር በተገናኘ አዋጁ ካለበት ክፍተት እና ወደፊት ሕጉ ተግባራዊ ሲሆን ስጋት የሚሆኑ ጉዳዮችን መመልከቱ ችግሩን ከስሩ መረዳት የሚያስችል ነዉ።

ግለሰብ አበዳሪዎችን ያገለለዉ አዋጅ፡- ለምን?


በተሻሻለዉ የገጠር መሬት አዋጅ አንድ አርሶ አደር የመጠቀም መብቱን ለዕዳ ዋስትና ማስያዝ ቢችልም አበዳሪዉን ለመምረጥ መብት አልተሰጠዉም። ብደር ሊወስድም የሚችለዉ ብሔራዊ ባንክ እዉቅና ከሰጣቸዉ ተቋም ብቻ ነዉ። የአበዳሪዉን ተቋም በሕግ አዉጭዉ መወሰኑ አርሶ አደሩ በቀላሉ ያለቢሮክራሲ ብድር ሊበደር የሚችልበትን ሁኔታ የሚያጠብ እንደሆነም ይነገራል። የፌደራል የገጠር መሬት አዋጅ ቁጥር 456/97 ለማሻሻል በረቂቅ ደረጃ ያለ ሕግ እና የአዋጁ ሐተታ ዘምክንያት የመጠቀም መብትን በዕዳ ዋስትና ማስያዝ ከግለሰቦች ለሚበደሩ አርሶ አደሮች የተፈቀደ ሊሆን የሚገባዉ የገንዘብ ተቋማት ተደራሽነታቸዉ ዉስን ስለሆነ ነዉ በማለት ምክንያቱን ያስቀምጣል።


ከዚህ ሐተታ ዘምክንያት መረዳት እንደሚቻለዉ የሕጉ መሻሻል አርሶ አደሩ በመሬቱ ላይ ያለዉን የመጠቀም መብት ለማስፋት ከሆነ በገጠር መሬት ላይ ያለን የመጠበቅ መብት በዋስትና ማስያዝ የሚያስችል ሁኔታ አብሮ ሊዘረጋ እንደሚገባ ነዉ። የገንዘብ ተቋሞች ዉስንነት እንዳለ ሆኖ አርሶ አደሩ ከግለሰቦች ብድር እንዳይወስዱ ክልከላ የተደረገበት ምክንያት ከምን ዓላማ እንደሆነ ግልፅ አይደለም። ከግለሰቦች ብድር መከልከሉ ተገቢ ነዉ በማለት የሚከራከሩ አካሎች ሕግ አዉጭዉ አራጣን ከመከላከል አንፃር የግለሰብ አበዳሪዎችን እንዳገለለ በመግለፅ ይከራከራሉ። ከግለሰቦች የሚበደሩ አርሶ አደሮችን ከመብቱ ማግለል ያስፈለገዉ አራጣን ከመከላከል አንፃር መሆኑ መከራከሪያ ቢቀርብም የብድር ዉሉ በሕጉ በተቀመጠዉ ወለድ መጠን ስለመደረጉ መቆጣጠር ስለሚቻል አራጣ ስጋት ሊሆን እንደማይችል መከራከሪያም ይቀርባል።


የተሻሻለዉ አዋጅ ለምን አበዳሪ ፋይናንስ ተቋሞችን ብቻ ለመምረጥ እንደፈለገ ግልፅ ነገር ባይሆንም በክልሉ በስፋት ለአርሶ አደሩ የብድር አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘዉ የአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም (አበቁተ) ከዚህ አዋጅ ጋር አብሮ እየተነሳ ይገኛል። የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ በተሳተፈበት እና በተሻሻለዉ አዋጅ ዙሪያ በተዘጋጄ አንድ ወርክ ሾፕ አብዛኛዉ የሕግ ባለሙያ(ዳኞች) አዋጁ አርሶ አደሩ የመጠቀም መብቱን ዋስትና አድርጎ ከግለሰቦች እንዳይበደር መከልከሉ በአሁኑ ሰዓት በክልሉ ሰፊ የብድር ሽፋን እየሰጠ የሚገኘዉን አበቁተ ተቋም ከመጥቀም የዘለለ ዓላማ እንደሌለዉ ሲገልፁ እንደነበር መታዘብ ችሏል። 

ከፍተኛ የዕዳ ወለድ ተጋላጭነት፡- 


ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የሚነሳዉ ሌላዉ ስጋት ለከፍተኛ የዕዳ ወለድ ተጋላጭነት ነዉ። ይህ የከፍተኛ ዕዳ ተጋላጭነት ስጋትም በፌደራል የገጠር መሬት አዋጅ ማሻሻያ ሐተታ ዘምክንያት ተነስቷል። እንደሚታወቀዉ በፍትሐ ብሔር ሕግ የብድር ወለድ መጠን ከዘጠኝ እስከ አስራ ሁለት በመቶ ሲሆን ይህ የወለድ መጠን ከግለሰብ ለተወሰደ ብድር ተፈፃሚም ይሆናል። ሆኖም የገንዘብ ተቋሞች ከፍትሐ ብሔር ሕጉ የተለዬ ወይም ከፍ ባለ ወለድ እንዲያበድሩ ተፈቅዶላቸዉ እየሰሩ ይገኛል። ለምሳሌ የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም(አበቁተ) ብድር ሲሰጥ እስከ 18 በመቶ ወለድ እንደሚያስብ ይታወቃል። በግልጽ መረዳት እንደሚቻለዉ አንድ አርሶ አደር ከአንድ ገንዘብ ተቋም በ18 በመቶ ወለድ ብድር ከሚወስድ ከግለሰብ እስከ 12 በመቶ ወለድ ብድር ቢወስድ ተጠቃሚ ይሆናል። ከተሻሻለዉ የገጠር መሬት አዋጅ ጋርም ተያይዞ የሚነሰዉ ስጋት አርሶ አደሩን ከገንዘብ ተቋሞች ብቻ እንዲበደር ማድረግ ለከፍተኛ ወለድ ማጋለጥ እና መጉዳት ይሆናል የሚለዉ ይገኝበታል። መብቱን መፈቀድ አስፈላጊ መሆኑ እስከታመነ ድረስ አርሶ አደሩ በዝቅተኛ ወለድ ብድር ሊወስድበት የሚችለዉ ሥርዓት መዘጋት ወይም መገደብ የፍትሐዊነት ጥያቄ ያስነሳል።


የተጓዳኝ ግዴታዎች ፈተና፡-


የፌደራል ገጠር መሬት አዋጅ ማሻሻያ ሐተታ ዘምክንያት ከግለሰብ አበዳሪዎችም መበደር የግድ ያስፈልጋል ከሚልባቸዉ ምክንያቶች ዉስጥ የገንዘብ ተቋሞች ከብድሩ በተጨማሪ ተጓዳኝ ግደታዎችን ስለሚያስቀምጡ አርሶ አደሩን በመብቱ በሙሉ ተጠቃሚ እንዳይሆን ያደርገዋል የሚል ነዉ። እንደሚታወቀዉ የገንዘብ ተቋሞች በተለይም በክልሎች ያሉ እና ለአርሶ አደሩ የብድር አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ተቋሞች ብድር የሚሰጡት በቡድን ሲሆን ተበዳሪዎች ከብድሩ ማግስት ጀምሮ በየወሩ እንዲቆጥቡ ግዴታ ይጣልባቸዋል። ከብድር ማግስት በየወሩ የሚቆጠበዉ ገንዘብ ዕዳዉ ተከፍሎ ሲያልቅ ለተበዳሪዉ የሚመለስ ቢሆንም ተደራቢ ግዴታ በመሆን ተበዳሪዉን የሚያጨናንቅ ነዉ። በተጨማሪም በግል መበደር የማይችሉ ሰዎች በቡድን በማይነጣጠል ሃላፊነት ብድር እንዲወስዱ የሚደረግ በመሆኑ ተጓዳኝ የቡድን አባል ካለማግኘት ጀምሮ በቀላሉ ብድሩ እንዳይገኝ ፈተና ይሆናል። በአንጻሩ ከግለሰብ የሚወሰደዉ ብድር በየጊዜዉ ብድሩን ከመመለስ ዉጪ ሌላ ተጓዳኝ ግዴታ የማይጭን በመሆኑና መያዣ የሚሆነዉ ነገር እስካለ ድረስ ሌላ የተለዬ መስፈርት ስለማይጠይቅ የብድሩን ሂደት ቀላል ያደረግዋል። ከገንዘብ ተቋሞች ብቻ ብድር ሊወሰድ ይገባል በማለት በገደብ ማስቀመጡ ለሌሎች ተጓዳኝ ግዴታዎች የሚያጋልጥና ብድር የማግኘቱን ሂደት አስቸጋሪ የሚያደረገዉ ስለሆነ ሕግ አዉጭዉ ጉዳዩን ከአርሶ አደሩ ጥቅም አንጻር ተመልክቶታል የሚለዉን አከራካሪ ያደርገዋል።

 

የፌደራል አዋጅ አስፍቶ የሰጠዉን መብት ክልሎች መገደብ ይችላሉ?


በኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 52(2)(መ) እና በፌደራል የገጠር መሬት አዋጅ ቁጥር 456/97 አንቀጽ 17(1) መሰረት ክልሎች የገጠር መሬትን በተመለከተ ለማስተዳደር እና አጠቃቀሙን ለመወሰን ህግ ሊያወጡ እንደሚችሉ ይናገራል። በዋናነት ክልሎች ያለዉን ክልላዊ ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ዉስጥ በማስገባት ስለገጠር መሬት አጠቃቀም ሕግ ማዉጣት ቢችሉም መሰረታዊ በሚባሉ ጉዳዮች ከፌደራል የመሬት አዋጅና ከሕገ መንግስቱ በተለዬ መልኩ ሕግ ማዉጣት ስልጣን አልተሰጣቸዉም። በገጠር መሬት ያለን የመጠቀም መብት ለዕዳ ዋስትና ማስያዝ በፌደራል ሆነ በክልሉ የገጠር መሬት አዋጅ በዝምታ ታልፎ እንደነበር ግልጽ ነዉ። በረቂቅ ደረጃ ቢሆንም የፌደራል የገጠር መሬት አዋጅ በዝምታ ያለፈዉን መብት በግልጽ አርሶ አደሩ የመጠቀም መብቱን መያዣ በማድረግ ከግለሰቦች ሆነ ከገንዘብ ተቋሞች ብድር ሊወስድ እንደሚችል አስቀምጧል። ይህ መብት ቀደም ሲል በግልፅ ያልተሰጠ አዲስ መብት እንደመሆኑ ክልሎችም ይህንን መብት ከፌደራል ሕጉ ጋር አጣጥመዉ ማዉጣት ይጠበቅባቸዋል። የፌደራል አዋጁ በረቂቅ ደረጃ ያለ ገና ያልፀደቀ በመሆኑ የክልሉ ከፌደራሉ አዋጅ በተለዬ የአርሶ አደሩን የመጠቀም መብት በዋስትና ማስያዝ ላይ አጥቦ ደንግጓል ለማለት መደምደም ባይቻልም በምክንያታዊ መመዘኛ አርሶ አደሩ ከግለሰቦች እንዳይበደር መከልከሉ ፍትሐዊ አይመስልም።
በተሻሻለዉ አዋጅ ቁጥር 252/2009 አንቀፅ 24(1) አንድ ኢንቨስተር በሊዝ የወሰደዉ የገጠር መሬት ላይ ያለን የመጠቀም መብቱን መያዣ አድርጎ ሲበደር ከግለሰብ ብድር እንዳይወስድ ገደብ አልተደረገበትም። ለአርሶ አደሩ ሲሆን ብድር መወሰድ የሚችለዉ ከገንዘብ ተቋማት ብቻ ሲሆን መሬትን በሊዝ ለያዘ ኢንቨስተር ግን ብድር የሚወስድበት አካል ላይ ገደብ አለመደረጉ ሕጉ ሊያሳካዉ የፈለገዉ ዓላማ ግልጽነት እንዲጎድለዉ አድርጎታል። ችግሩ ያለዉ ከግለሰብ አበዳሪዎች ከሆነ ኢንቨስተሩም ከግለሰቦች የመጠቀም መብቱን ዋስትና በማድረግ ብድር እንዳይወስድ እንደ አርሶ አደሩ መከልከል ነበረበት ወደሚል ስሌት ያስገባናል። ሆኖም ከግለሰቦች ብድር የተከለከለበት ገፊ ምክንያት ስላልተገለፀ ስሌታችን ዋጋ አልባ ያደርገዋል። ሕይወቱ ከገጠር መሬት ጋር በጥብቅ የተሳሰረዉ አርሶ አደር አንድ መሬት በሊዝ ከወሰደ ኢንቨስተር የሰፋ መብት እና ነፃነት በመሬቱ ላይ እንዲኖረዉ ይፈልጋል፤ያስፈልገዋልም። በዚህ ረገድም ሕግ አዉጭዉ ጥንቃቄ ማድረግ ነበረበት።


በአጠቃላይ የተሻሻለዉ የአማራ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ አርሶ አደሩ በመሬቱ ላይ ያለዉ ተጠቃሚነት እንዲሰፋና አማራጭ የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲኖረዉ ለማድረግ የመጠቀም መብቱን ለእዳ ዋስትና ማስያዝ እንደሚችል መፍቀዱ ተገቢነት ያለዉ ቢሆንም መብቱ ተፈፃሚ የሚሆነዉ ከገንዘብ ተቋሞች ብቻ ብድር ሲወሰድ ነዉ በማለት ጥብቅ ገደብ ማስቀመጡ ሕጉ የተሻሻለበትን ዓላማ እንዳያሳካ የሚጎትት ነዉ። በሌላ አገላለጽ ሥጋ ሰጥቶ ቢለዋ እንደመንሳት ነዉ። የገንዘብ ተቋማት ካላቸዉ ተደራሽነት እና ከሚያስቀምጡት ጥብቅ የብድር ሂደት፣ ለብድር ከሚያስቡት ከፍተኛ የወለድ መጠን እንዲሁም ከብድር በኋላ በሚያስቀምጡት ተጓዳኝ ግዴታዎች አንፃር የተሻለ የብድር አማራጭ ሊሆን የሚችለዉን ከግለሰቦች መበደር ክልከላ ማድረጉ አጠያያቂ ነዉ። ሕጎች ሲወጡ በሕጉ መብት የተሰጣቸዉ አካሎች መብታቸዉን ተግባራዊ የሚያደርጉበት ምቹ ሥርዓት አብሮ መፍጠር እንዳለበት ይታመናል። አርሶ አደሩ በመሬቱ ላይ ያለዉን የመጠቀም መብት ለእዳ መያዣነት ሲፈቀድለትም በተጓዳኝ መብቱ ተፈፃሚ የሚሆንበትን የሰፋ ዕድል እና ምቹ ሁኔታ መፈጠር እያለበት መብቱን ተፈጻሚ የሚያደርግበት ሥርዓት አጥቦ መደንገጉ ተገቢነት አልነበረዉም። ሕግ አዉጭዉ አካልም ጉዳዩን እንደገና ተመልክቶ አርሶ አደሩ በመሬቱ ላይ ያለዉን የመጠቀም መብት ለብድር የሚስያይዝበትን ስርዓት ሊያሰፋ በሚችል መልኩ ማሻሻያ ሊያደርግ ይገባዋል።

ይምረጡ
(9 ሰዎች መርጠዋል)
944 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 96 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us