አኰቴት ዘለማ መገርሳ

Wednesday, 15 November 2017 12:59

                

በአንድነት ቶኩማ

 

 

“ሰሞኑን ምን ይሰማል ጃል?” ማለት እወዳለሁ። ጋዜጠኛ አሊያም ጦማሪ ስለሆንኩ አይደለም። የወሬ ሱስ ያለብኝም አይመስለኝም። የአገሬ ጉዳይ ስለሚያሳስበኝ እንጂ። ደግሞስ “እረኛ ምን አለ?” ይሉ አልነበር ኢትዮጵያውያን አያቶቼ። ልክ ነበሩ። ዜና ወይም ወሬ ፈልገው ነበር እንዲህ ይሉ የነበሩት። የተሰማውን ወሬ አድምጦና አብላልቶ አቋምን ለማስተካከል። አሊያም ይህን የሚሉት ስሜትን ለመቃኘትስ ቢሆን ምኑ ከፋ?

ታዲያ ሰሞኑን ሁነኛ ወዳጆቼን “ጆሮ ሰጥቼ” ሳዳምጥ ስለአንድ ሰሞነኛ (የቤተክህነቱ ሳይሆን የፖለቲካ) ሰው ሰማሁ። መጀመሪያ ስሰማ ተራ አሉባልታ ወይም ሐሳዊ ተክለሰብዕና ግንባታ መሰለኝና መሐል ሰፋሪ ሆኜ ማዳመጥ ጀመርኩ። ምን አለፋችሁ በየጋዜጣው፣ በዩቲዩብ፣ በፌስቡክና በሌሎች ሚዲያዎች ሁሉ በስፋት እየተደመጠ ያለ ዜና ስለኒህ ግለሰብ ሆነ። ይኼ ነገር ምንድን ነው? በማለት ከመንታ ልብነት ወደ አንድ ውሣኔ መጣሁ። ከሰማሁት ተነስቼ ለማሞካሸት። ብዙም ይኼ ነገር ባይሳካልኝም። የግለሰቡ ሥረ ነገር ወይም ተልዕኮ ምንም ይሁን ምን ሐሣቡን ወደድኩት። የሚናገሩትንና የሚያስተላልፉትን ሐሳብ የምጋራው በመሆኑ ተቀበልኩትና ይህን “አኮቴት ዘለማ መገርሳ” ለመጻፍ ወሰንኩ።

እንደሰማሁት እና በተለያየ ጽሁፍ ሰፍሮ እንዳየሁት ወጉን ላውጋችሁ። “ኢትዮጵያውያን ተዋልደዋል”፣ “አንድነት እንጂ መለያየት ለማንም አይጠቅምም”፣ “ማንም በተሾምንበት ቦታ ያለ አግባብ ሊያዘን የሚችል የለም”፣ “የኦሮሞ ሕዝብ መብት ይከበር”፣ “የኢትዮጵያ አንድነት ይጠበቅ”፣ “አማራና ኦሮሞ የተጋባ ሕዝብ ነው” እና የመሳሰሉ ነገሮችን መናገራቸውን በወፍ በረር ጭምር ሰማሁ። ሲደጋገምብኝ እንዴት እኒህ ሰው በዚህ አቋማቸው ጸንተው እንዳሉ ተረዳሁ። አፈወርቅ ገብረኢየሱስ ስለ አዲስ አበባ አመሠራረት እና ዝና መውጣት ሲናገሩ “ግሩም ነው። የግሩም ግሩም” እንዳሉት ሆነብኝ። ገርሞኝ ነው። ባለፉት ዓመታት የሰማነውን ሳስታውስ ነው ይህ ግርምት የመጣብኝ። ከዚያ በፊት የነበሩት አያቶቻችንማ ይኼ የአቶ ለማ መገርሳ ንግግር መጀመሪያቸው ነበር። ይህን በማለቴ እሳቸውም እንደማይታዘቡኝ ተስፋ አደርጋለሁ። አዲስ አይደለም ስል ነው። በቅዱስ ቃሉ “የሰማነውን ማን አምኗል” የተባለውስ በዚህ አይነት ትንግርት መካከል የመጣ መልካም ዜና ነብዩ በመናገሩ አይደለምን? ይህ ነው የመገርሳን ልጅ ለማን ያደመቃቸው!!!

“በባለፈው ትርክት መነታረክ ይቅር” ዓይነት ነገር ብለዋልም ሲባል ሰምቻለሁ። እውነት ከሆነ ደስ ይላል። ተገኝቶ ነው!! “ወደኋላ እያየን ወደፊት መጓዝ አንችልም” ሲሉ ምልከታቸውን ሰንዝረዋል። ግሩም ነው። የግሩም ግሩም። የኋላዬን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ እንዳለው ሐዋርያው ጳውሎስ። አትደነቁ!

“ምን ያለች አገር ናት የተክለፈለፈች

ቅድም በኋላዬ አሁን ባይኔ መጣች” (ዮፍታህ ንጉሴ) እንዲሉ ሆኖባቸው ነው።

ለእኚህ ግለሰብ የኢትዮጵያ ዕምብርት የሆነውን የጀግንነት፣ የአንድነት፣ በራስ የመተማመንና የመስዋዕትነት መንፈስ የቸራቸው አለ። ይህ መንፈስ ባይኖራቸው እንዲህ ጠንክረው ይወጣሉን? አይመስለኝም። የኋላ ስንቃቸው ጠንካራ ነው። ያልተበረዘ፣ ያልተከለሰ፣ ያልከሰለ ‹‹ኢትዮጵያዊነት ወ ኦሮሞነት›› ይታይባቸዋል። ደግሜ እላለሁ ግሩም ነው የግሩም ግሩም!!!

እስኪ ልጠይቃችሁ። ይህን መንፈስ ከየት አገኙት? ከአያቶቻቸው ነዋ! አቡነ ጴጥሮስ መክኖ ይቀራል እንዴ? ቴዎድሮስስ፣ አብዲሳ አጋስ ደማቸውን በከንቱ አፈሰሱ ብላችሁ ነው? ለማን ለማልማት ነው እኮ! በቀለ ወያ ትዝ ብሏቸው ነው። ገረሱ ዱኪ፣ ባልቻ አባነፍሶ፣ አሞራው ውብ ነህ፣ አበበ አረጋይ፣ በላይ ዘለቀ፣ ጃገማ ኬሎ፣ ኃይለማርያም ማሞ፣ አሉላ አባነጋ፣ ኃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ ኧረ ምኑ ቅጡ በዐይነ ሕሊናቸው መጥቶባቸው መሰለኝ። ይህ ስንቅ አንድ ሊባል ይችላል። የአያቶች ያውም ስመጥር አርበኞች ታሪክ ትውስታ። ለማንኛውም ለማ ይልማ!!!

አንተ ወንድማችን እልፍ አእላፋት ሁን፣ ዘርህም የጠላቶችን መንደር ይውረስ። ወይም ኦሮሞዎች እንዲሉ እንደ ምድር ሰርዶ እንደሰማይ ጉም ሁን! (አንቱታውን  ለምረቃ ስላልተመቸኝ ነው ያስቀረሁት።)

አድምጡኝማ! የአቶ ለማ መገርሳ ሌላው ስንቃቸው ኢትዮጵያዊ በዘር ድብልቅልቁን የወጣ መሆኑን ተረድተው መሰለኝ። ቀይና ነጭ ጤፍን መለየት እንደማይቻል ገብቷቸው ነው። “ኢትዮጵያዊነት ሰርገኛ ጤፍ ነው ብለናል። አብሮ የሚበጠር፣ አብሮ የሚፈጭ፣ አብሮ የሚበላ ነው።” የጃገማ አጎት አባ ዶዬም ይህን ነበር ያሉት። የዚህ ምስጢራዊ ሕዝብ ውስብስብ ዝርያ ታይቷቸው ነው። ይህ ለማንም ጎጠኛ አይገለጥም። የአባቱን ስም ጠርቶ የአያቶቹን ሲደግም አንድ ዘር ብቻ ሊኖረው እንደማይቻል ገብቶት ነጻ ካልወጣው በቀር። ሌላውማ በተረት ተሞልቶ ተበክሎ በካይ ሆኖ የለ? አንዱ በአንድ ቦታ ዘርህ ምንድን ነው ሲባል “አላውቀውም ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የወታደር አገር ናት። በመሆኗም  በሴት አያቴ በር ያለፈው የትኛው ዘር  እንደሆነ አላውቅም ወይም አልተነገረኝም” ሲል አሻፈረኝ አለ አሉ። የደሬሳ ልጅ ነው እንዲህ አለ የሚባለው። የደሬሳ ልጅ “የእኔን ዘር ሴት አያቴ እና እግዚአብሔር ብቻ ነው የሚያውቀው” ሲል ይሞግታል። የታምሩ ልጅ አለቃ ይህን ብለው ነበር ሲባልም ሰምቻለሁ።

ማንም በኢትዮጵያ ምድር ላይ ተቀምጦ ያልተቀየጠ የለም። ቅይጣዊ መሆናችን አጥንተው መሰለኝ ለማም ይህን ሐሳብ የተጋሩት። ለዚህ  መሰለኝ አንድነቱን በልዩነት፣ ልዩነትን በአንድነት ያስተጋቡት። ያልተቀየጠ ምን ነገር አለ? ባህላችንም ተቀይጧል፤ ታሪካችንም ቢሆን እንደዚያው። እሳቸው አሉ እንደተባሉት “ኢትዮጵያዊነት ከደም አልፎ በልብ ውስጥ የተቀመጠ የተከበረ ማንነት ነው። ሞክሬው ባላውቅም “…..ሱስ” ነው። ኢትዮጵያዊነት ምን እንደሆነ ዛሬ ባየነው ትእይንት … ትርጉም ገብቶኛል። ኢትዮጵያዊነት ልዩ ነው። ከደም አልፎ ልቡ ውስጥ እንዳለ ዛሬ አይተነዋል። እውነትም ኢትዮያዊነት በልብ ነው።”

ቋንቋችንም ቢሆን እንደዚያው። ብቻ አንዱ በተወለደበት አካባቢ የሚናገረውን ቋንቋ ተገን አድርጐ የዚህ ዘር ወይም የዚህ ብሔር ነኝ ይላል። ሞኝነት ነው። የባህል ቅይጡ አንድ ጽሑፍ አስታወሰኝ። “… በታላቅ ዛፍ ስር ይሰባሰባሉ። (ስለ ኦሮሞዎች ነው የሚናገረው) ይኸ ታላቅ ዛፍ ያልተገለጸ ምስጢር አላት። አማሮች ቤተክርስቲያን ሲሠሩት በዛፍ ስር ነው አጸድ ይሉታል፣ ይሳለሙታል፣ ፈትልም ያስሩለታል። ይኸ ሕግ ከኦሮሞ ይሁን ከአማራ የመጣ አይታወቅም። ስለዚህ ኦሮሞዎች የቤተክርስቲያን አጸድ እስከ ዛሬ አልቆረጡም። ቢደርቅም አያነዱትም ያከብሩታል። ይፈሩታልም።”ይላል በአንድ ቦታ።

እኒህ ሰው በእውነት ምጡቅ የኢትዮጵያ ልጅ ናቸው። እውነተኛ ሰው በጭንቅ ቀን ይበቅላል። “አቤቱ ከተንኮል፣ ከሸማቂ፣ እንዲሁም እንዲህ ዓይነቱን ሰው ከሚያጠፋው ሰይጣናዊ ምክር ጠብቃቸው” ብንልስ? ቀድሞ አሜን ያለ ደግሞ አሜን ይበል። አሜን ያላለ አሜን ይበል። የመድኃኒት ሐሣብ ቀርቧልና። ፍቅር ነው መድኃኒቱ።

ሌላው የአቶ ለማ ልዩ ስንቃቸው የግሎባላይዜሽን ሥርዓተ ማኀበር አመሠራረትን በጥልቅ ተረድተው መሰለኝ። ከጥልቅ ተሃድሶ ይልቅ ጥልቅ እውቀት ውስጥ መግባት። ገደብ አልባ ሥርዓተ ማኀበር፣ መስመር የለሽና በቅብብሎሽ ደማቅ የሆነውን የባህል መስተጋብር በጭንቅላታቸው አጢነው መሰለኝ። ይኽ ነው የኛ ዘመን መልኩ። በተለያዩ አገሮች በተፈለገው መጠን ተንደላቆ መኖር እየተቻለ በኛ በራሣችን አገር አብሮ አለመኖር ወይም መኖር አለመቻል ድንቁርና መሆኑን ተገልጾላቸው ነው። አዋቂነት ነው። ማወቅ ማለት ይህን አስቀድሞ መገንዘብ ነው። ማወቃቸው በዚህ ታውቋል። መለያየት አያዋጣም። መለያየትም አይቻልም። ዓለም መንደር እየሆነች ባለችበት ዘመን መንደሮች ዓለም ለመሆንና ለመበጣጠስ መሞከራቸው ልክነቱ አልታያቸውም። ጥሩ እይታ ነው። መለያየት እንደ አተያይ አልሆነላቸውም። ወጥ አቋም ያዙ እንጂ። በፍቅር የሆነ አንድነትን ነው የተመኙት!!!

በጎጥ አመለካከት የወደቁ ዐይኖች ከወደቁበት ጥፋት ለአንድነት ሲነሱ የሚመጣ አመለካከት ነው። ይህ አሻግሮ ማየት ነው። ለቆሙለት ለኢትዮጵያና ለኦሮም ሕዝብ ማሰብ ነው። በርግጥ ክቡር ሆይ ታይቶዎታል። ማየት የተሳናቸው በቅርብ ያለውን የከርስ ጉዳይ ሲያዩ እርስዎ ግን አሻግረው አይተዋል። ሀገር አዩ። ማዶ ያለውን ተረድተውታል። ማየት ይህ ካልሆነ ምን ሊሆን ይችላል? ባለ ርዕይ ማለት ይኼ ነው። ዐይኑ ገዳይ ሳይሆን ዐይኑ አዳኝ ይሉ ነገር።

ወዲህ በሉኝማ። አቶ ለማ መገርሳ ሌላው ስንቃቸው የተቀዳው የሕዝቡን ድምፅ ከመስማት ነው። ወይም የሕዝብን ፍላጐት ከማወቅ የመነጨ ነው። “ጆሮ ያለው ይስማ!” የሚለውን እየሰሙ ነዋ ያደጉት። እንቅጩን እንናገርና  እሳቸውን ያደነቅነው መስማት የተሳነው ሰው ባለመሆናቸው ነው። “ሕዝቡ ምን ይላል?” “ሰው ምን አለ?” “ጎንደር ምን ይላል?” “ኦሮሞ ምን አለ?” “ወይም “አማራ ምን አለ?”፣ “ትግራይ ምን ፈለገ?” “ጉራጌ ምን አለ?” ወይም “በአንድነት ምን አሉ?” ብሎ መጠየቅና ማደመጥ ስንቃቸው ሳይሆን አልቀረም። የሕዝቡን ኑሮ ሰምተውታል። የታላቅነት ደረጃ ነው። የአገልጋይነት መንፈስ ነው። የሕዝብም ኑሮውን ማደመጥ፣ ወጉን መስማት፣ ባህሉን ትውፊቱን ማጥናት፣ ፍላጐቱን መረዳት ወዙን ማሽተት የብልህነት መንገድ ነው። እንደሰማሁት ለአማራው  ለኦሮሞው፣ ለትግራይና ለደቡቡ ይዘውት የመጡት አጀንዳም መልካም ተስፋ ነው። ንግግራቸው ለሁሉ ተስፋ ነው ሲባል እየሰማሁ ነው። እንተማመን ያሉ ይመስላል። እሱማ “እምነት፣ ተስፋና ፍቅር ጸንተው ይኖራሉ” ይል የለም ቃሉ።

ሌላውን ስንቅ ያገኙት ከሚያምኑበት አንዱ መስመር የተነሣ ነው። ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር አይመስለኝም። እሱንማ ስንቱ ካድሬ ውጦ መቼ ለኢትዮጵያ አሰበ። ለጎጡ ጎብጦ ቀረ እንጂ። ድፍረት አይሁንብኝ እንጂ እርስዎ የአዲሱ ትውልድ ተስፋ ስለሆኑ የሚያውቁትን ነው እየተናገሩ ያሉት። የተጋባ እና በአንድነት የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦችን እንጂ ድርጅታቸው ወደኋላ እየጎተተ የሚያመጣው ተረት በውስጣቸው ሰርጾ የገባ አይመስልም። የኢትዮጵያ ተስፋ እሳቸው ይሁኑ ወይስ ሌላ እንጠብቅ? ዮሐንስ መጥምቁ እስር ቤት ሆኖ ነጻ አውጭ ሲጠብቅ ክርስቶስን እርሱ እንደጠበቀው አላገኘውምና “የምትመጣው አንተ ነህ ወይስ ሌላ አንጠብቅ” ሲል ላከበት። ክርስቶስም “ሂዱና ዕውሮች ያይሉ፣ ዲዳዎች ያይናገራሉ፣ ሽባዎች ይተረተራሉ” ብላችሁ ንገሩት አለ። እኔንም አንዳንድ ሰዎች የሚመጣው አቶ ለማ ናቸው ወይስ ሌላ እንጠብቅ ብለው ይጠይቁኛል።

የእሳቸው መልስ ምን ይሆን? ስገምት “ሂዱና የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ነው፣ የኦሮሞ ሕዝብ መብት ይከበር፣ ኢትዮጵያ የሰነበተች ጥንታዊት አገር ናት፣ ኦሮሞና አማራ አንድ ነው፣ ወዘተ …” እያለ ይናገራል ብላችሁ ንገሩ እንደሚሉ። ወይም እንደተማሩትና ተኮትኩተው እንዳደጉበት የእምነት አስተምህሮ አምላክዎትን መስለው “ባሪያ የለም፣ ጨዋ የለም፣ አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፣ ሁሉም በክርስቶስ አንድ ነው” የሚለውን ያንፀባረቁ ይሆን? በርግጥ ግሪካዊ አለ። አይሁዳዊም አለ። በክርስቶስ ግን ወንድማማች ናቸው። ወይም አንድ ናቸው። ሁሉም በኢትዮጵያ አንድ ነው ሲባል ብሔር የለም ማለት እንዳይደለ ወይም አለመሆኑን እናውቃለን። በኢትዮጵያ ግን አንድ ነን።

ይቅርታ አድርጉልኝ እንጂ የታላቁ መምህር የክርስቶስ ባርያ ናቸው! ለቆሙለት አላማ የቆሙ “ሞ አንበሳ ዘምነገደ ኢትዮጵያ” ብያቸዋለሁ። የእኔ ብቻ ጀግና አይደሉም። ታሪክ የሚያስታውሳቸው የታሪክ ጀግና እንጂ። ከተሰነጣጠቀው የመበታተን ማማ ላይ በቅለው እልቂትን የገሰፁ ማኀተመ ሥላሴ ብያቸዋለሁ። አንድነቱን በሦስትነት የገለፀውን ምስጢረ ሥላሴን የተረዱ በዚያም የታተሙ። በአካል ሦስት በመለኮት አንድ የሚለውን የተቀበሉ። ትርጓሜው በቋንቋ ብዙ በኢትዮጵያዊነት አንድ። በባህል በቋንቋ ልዩ ልዩ (መወራረሱ ሳይረሳ) በመንፈስ በልብ እና በደም አንድ ሕዝብ። ይስበኩ አንድነትን፤ ኩራት ነጻነትን። ልክ ነዎት። አንድ አምላክ በሦስትነት የሚኖር ተብሎ ይሰበክ የለም ወይ?

በጨለማው ብርሃን ይብራ ያለው እግዚአብሔር የተነፈሰብዎት የብርሃን ልጅ ብርሃን ናቸው። ባጭር ቃል የጣይቱ ብጡል መንፈስ አለባቸው። “ብርሃን ዘኢትዮጵያ” ቢባሉ የሚከፋው ያለ አይመስለኝም። ይልማ ደሬሳ “ባቲ” ወይም ጫጉላ ጨረቃ” ያለው የእሳቸውን ጨረቃ (ባቲ) ማለትም ሱስ የሆነችባቸውን ኢትዮጵያን መስሎ ተሰማኝ። የአልጎሪካል አተረጓጎም ዘዴን ተጠቅሜ ነው ይህን የምለው። ጻሕፍት፣ ባለቅኔዎች፣ ኢትዮጵያዊ ሆሜሮች የሚመኟትን የጊዳዳ ልጅ ጉንጉን አበባ ናት ያሏትን ኢትዮጵያ። ሚስትህ፣ እናትህ እና ሃይማኖትህ ናት ያሏትን ኢትዮጵያ። እስክንድር የተከተላት፣ መንግሥቱ ከአለቃ ለማ አገር ምናልባትም ከወደ አንኮበር የፈለጋት፣ ዮሐንስ አድማሱ ነይ የሚላት፣ ገብረክርስቶስ ደስታ ከሃሮ ማያ የናፈቃት፣ ተስፋዬ ገሰሰ ከወደ ሃረር ወዴት ነሽ ያላት፣ ዳኛቸው ወርቁ ከይፋት የተመኛት። አይ ኢትዮጵያ እንዲህ ለሁሉ ሱስ ሆነሽ ትዘልቂ! እሰይ፣ እሰይ ወይም አሹ!!!!!!!!!

እሱማ እውነት እንነጋገር ከተባለ የሎሬት ፀጋዬ “ኢልመ ገልማ አባ ገዳ” ያሏቸው የኦሮሞው (የቦረናው) አንደበተ ርቱዕ አባ ገዳ መንፈስም ያለባቸው ይመስላል። አንደበተ ርቱዕ ናቸዋ! ይኼ ነው እንግዲህ ምክንያቱ የፀጋዬ ገብረመድህን ግጥም ለእርሳቸው ይገባቸዋል የምለው። “ከመድረኩ “የለማ መገርሳ የአንድነትና የፍቅር ስብከት ይጠበቃል። ሰውዬው ሲናገር ያምርበታል። አንደበቱ ይጣፍጣል። ለነገሩ ፍቅርና አንድነትን የሚሰብክ ላይጣፍጥ አይችልም” ተብሎ ተጽፎ አንብቤ ተደነቅሁ። (ምንጭ አዲስ አድማስ ጥቅምት 25 ቀን 2ዐ1ዐ ዓ.ም)።

‹‹ሰው ስንፈልግ ባጀን›› ያለው ሙሉጌታ ሉሌ እሳቸውን ስላላየ ቢሆንስ? ወይም ለማ ራሳቸው የሙሉጌታን ጩኸት ሰምተው መልስ ሰጥተው ቢሆንስ? “ማን ይላክልኛል? ማንንስ እልካለሁ …?” ያለው የትንቢተ ኢሳይያስ መልእክት አነቃቅቷቸው ቢሆንስ? ኢትዮጵያ ሀገራችን ራሷ “ማን ይሄድልኛል ማንንስ እልካለሁ” ባለችበት ጊዜ ፈጥነው መልስ የሰጡት በዚህ ምክንያት ቢሆንስ? ዮሐንስ አድማሱ ተወርዋሪ ኮከብ ያለው እርሳቸውን መሰለኝ።

“ተወርዋሪ ኮከብ የደረሰው ቦታው የጨለመ ምድር

      አይታይም ነበር።

      ጨለማ አካል ገዝቶ

      ይዳሰስ ነበረ በየቦታው ገብቶ።…

ተወርዋሪ ኮከብ በራሱ ነበልባል በራሱ ነዲድ ተቃጥሎ [ያልጠፋ]

ተወርዋሪ ኮከብ በምናውቀው ሰማይ [በኢትዮጵያ ምድር አለልን በይፋ]

[ተወርዋሪው ኮኮብ በማናውቀው ጨፌ በራልን በተስፋ]

[ብጥስጣሹን አካል፣ ብትንትኑን መንደር ጣጥፎ ሊሰፋ]

(ድቅል ግጥም ከዮሐንስ አድማሱ ጋር)።

አቶ ለማ “የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ያስተሳሰረው የደም ሐረግ ብርቱ ነው። ድልድያችን ሻማ፣ ከዘራችን ቄጤማ አይደለም፣ ዘመን ባስቆጠረ አብሮነታችን ወደ ላቀ ደረጃ እንደምንሸጋገር እናምናለን” ብለዋላ!!!። ታዲያ ይህ አይወደድምን?

ያም ሆነ ይህ አቶ ለማን ብዙ ሰው ወዷቸዋል። ጠርጣሮች እንዳሉ ሆነው። ይሁን እንጂ ንግግራቸው የኢትዮጵያ የግብረ ገብ (የሞራል) መሪ አድርጎቸዋል። ሞራል ወይም ግብረ ገብነትስ ቢሆን መች ከአጀንዳቸው ጠፋ። “ትውልድ ለመቅረፅ ደግሞ ቅድሚያ የሚወስደው ቤተሰብ ነው። በመቀጠል ማኀበረሰብ፣ ስለሆነም ለሥነ ምግባር ጉዳይ ቅድሚያ ልንሰጥ ይገባል። አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ስነ - ምግባርን በተመለከተ ትኩረት ልትሰጡት ይገባል” ያሉት እኮ እሳቸው ናቸው። ይህ ምን ክፋት አለው?

ለነገሩ ከእሳቸው ጋር አብረው የቆሙት ዶ/ር አብይ አህመድስ ቢሆኑ መች አወቅናቸው? ለሀገራችን አብይ መሪ ናቸውሳ! እሳቸውም ፍቅርን አስቀደሙ እኮ። የፍቅር ስብከት እንዴት ደስ ይላል። የፍቅር ትዕዛዝ ታላቅ ናት። በርግጥ የፍቅር ትዕዛዝ ሐዋርያው ዮሐንስ እንዳለው አዲስ ትዕዛዝ አይደለችም። ብዙ ጊዜ የተነገረች ናት። ለኢትዮጵያም አዲስ አይደለችም። ቀደም ሲሉ ሰብከዋታል። ኖረውባታልም። ይሁን እንጂ በአዲስ መልክ በዶ/ር አብይ በኩል ተሰበከቻ! ዮሐንስም ያለው ይኼንኑ ነው። የሰማነውን አስታወሱን። ያወቅነውን አሳወቁን። እንዲህ ሲሉ “ሐረርጌ የፍቅር ሀገር ናት። ፍቅር ከዚህ ኤክስፖርት ሊደረግ ይገባል። ዓለምና ኢትዮጵያ በፍቅር እጦት በሚሰቃዩበት በዚህ ጊዜ እናንተ ፍቅርን የምታካፍሉን ከሆነ እየበላን እንራባለን…” ጎሽ የአንበሳ ልጆች አንበሶች። ኦቦ ሌንጮ ብየዎታለሁ። የአንበሳ ጌታ ለማለት ነው። ሁለተኛው ሞአ አንበሳ ዘም ነገደ ፍቅር።

አቶ ለማ መገርሳ እንዳለፈው ትውልድ ጀግና ፍለጋ ወደ ውጭ ሄደው አልማሰኑም። ምን በወጣቸውና። የአገራቸው ጀግና ሞልቶ ተርፎ። ማኦ፣ ማርክስ እና ቼ ጉቬራ ሲሉ አልደከሙም። የሀገራችን ስመጥር ታጋዮችን ነው መሠረት ያደረጉት። “ለዚች ሀገር ሕይወቱን አሳልፎ የሰጠው ይህ ሕዝብ ለሀገር፣ ለአንድነቱ ነው። ትናንት በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ደሙን የገበረው ለኢትዮጵያ ነው።” ብለዋላ!። እኒህ ባለስልጣን የራሣቸውን አልናቁም። የሌሎች አገር ጀግኖች ለራሣቸው ሠርተዋል። በዚህ ይደነቃሉ። የኛዎቹን አስደናቂ ጀግኖች ደም ገብረው አገር ማቆየታቸውን አልካዱም። በእኔ እምነት “ይኼ የማነው የኮራ የደራ” የተባለው ለእርሳቸው ነው። “ፍቅር ያሸንፋል” እውነት ነው። ማንም ሊለያየን አይችልም። ፍቅር ይልቃል!!! እነዚህ ሰዎች የዘራነውን ሳናጭድ የደረሱልን ኮከቦች ናቸው። የጥላቻ እንክርዳድ ፍሬ (እብቅ) ሳያጎሞራ ሊያመክኑ ቆርጠው የተነሱ።

“ጠላት በዋናው ላይ ትርፍ አገኛለሁ ሲል፣

እኛስ ዋናችንን ስለምን እናጉድል” እንዳሉት ዮፍታሄ ንጉሴ ለምን ፍቅርን፣ አንድነትን፣ አብሮነትን እናጉድል?

ሰሞኑን እነ አቶ ለማ የዮፍታዬ መንፈስ አርፎባቸዋል መሰለኝ። በቅኔያቸው ደምቀው በሀገር ፍቅር ነደው አገራቸውን አስተባብረው ትንሳኤዋን ለማምጣት ተነስተዋል። የፍቅርና የአንድነት ትንሣኤን ማምጣት ነው ግባቸው። የመቆራቆዝ መንፈስን ለማቆርቆዝ መሰለኝ አላማቸው። ወፌ ቆመች ቢባሉስ!

ታዲያ እነ አቶ ለማ መገርሳ እስከዛሬ የት ነበሩ? የሚሉ አሉ። ትልቅ ጥያቄ ነው። በመጀመርያ እነ አቶ ለማ መገርሳ በነቁበት ጊዜ መንቃታቸው ያስመሰግናቸዋል። እኔ ግን መጀመርያውንም የተኙ አልመሰለኝም። ንግግራቸው ተኝቶ የነቃ ሰው አይመስልማ!። ለጊዜው ዝም ብለው እንጂ። “ዝምታ ወርቅ ነው” የሚል ብሂልን የተቀበሉ አልመሰለኝም። አንደበተ ርቱዕ ናቸዋ! ታዲያ ለምን ዝም ብለው ቆዩ? ዮፍታሄ ንጉሴ ያለው ሆኖባቸው ነው።

“ሲመቸኝ ዝም ብል፣ ዝም ያልሁ መስሎታል፤

ሲታሰብ ነው እንጂ ዝም ማለት የታል” ያለውን።

የአገር ልጆች ተሰብሰቡ አገር አቅኑ። አራሙቻውን ንቀሉ። ወይም እንቦጩን ንቀሉ። ጥላቻና መከፋፈልን አስወግዱ። የልዩነትን ‹‹ዛር›› አባሩ። በአንድነታችን ክበሩ። ፍቅር ስትሉ ዘምሩ፣ አትፍሩ እሱን አውሩ። አንድነትን ዘምሩ። ፍቅርን አብስሩ። እባካችሁ መዝሙረ ሐዋዝ አሰሙን። ለኛም ይባቤ ይሁንልን። ይህን እየሰበካችሁ ብትሞቱስ ሞታችሁ ይባላልን? አይመስለኝም። በዚህ አቋማችሁ ምክንያት ከሞታችሁ ደግሞ

“ለምን ሞተ ቢሉ

ንገሩ ለሁሉ

ሳትደብቁ ከቶ፤

“ከዘመን ተኳርፎ

ከዘመን ተጣልቶ።” በማለት የባለቅኔዎችን ቅኔ ተውሰን እናበረክትልዎታለን። ወይም ዮፍታሄ ንጉሴ እንዳለው

“ከአገሬ ዕድሜ ተርፎ የሚቀረው ዕድሜ፣

ሞተ ነፍስ ይባላል ልናገር ደግሜ፣” ነው በማለት “ሞተ ነፍስ እንዳይባሉ” እናነቃቃቸዋለን። አሊያማ የቁም ሞት ሊሞቱ ነዋ! እሱስ ይቅርባቸው!!!! እንዲህ አይነትስ “ሱስ” አይያዛቸው። አይመጥናቸውም።

Last modified on Wednesday, 15 November 2017 13:09
ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
269 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 930 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us