“ወንድማማችነትና አንድነት እንዳይሻክር ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል”

Wednesday, 22 November 2017 12:39

 

ከዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዎሕዴግ)

የተሰጠ መግለጫ

 

አገራችን ኢትዮጵያ በቁጥር ከ80 በላይ የሆኑ ብሔርና ብሔረሰቦች ያሏት አገር መሆንዋ ይታወቃል።

እነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች በቁጥራቸው ልክ የሆኑ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ታሪኮችና ሌሎችም የማንነታቸው መገለጫ እሴቶች አሏቸው።

ሁሉም አንዱ የሌላውን በማክበር፣ እርስ በርስ በመግባባትና በመተሳሰብ ኖረዋል። እየኖሩም ነው።

 

በአስከፊ ሥርዓቶች የሰፈነባቸውን ብሔራዊ ጭቆና ለማስወገድም አብረው ታግለዋል። አሽቀንጥረው የጣሉት ያ ሥርዓት ዳግም እንዳይመጣ፣ ፍጹም የሆነ እኩልነት፣ ሰላምና ፍትህ የሠፈነበት ሥርዓት እንዲገነባ ለማድረግ አሁንም አንድ ላይ ሁነው ባልተቋረጠ ሰላማዊ የትግል እንቅስቃሴ ላይ ናቸው።

 

ይሁን እንጂ፣ አልፎ አልፎ ከአነዚህ በተመሳሳይ የትግል ሰልፍ ላይ ከሚገኙ ሕዝቦች ውስጥ በአንዳንዶቹ ዘንድ ተከስቶ የሚገኝ አንዳንድ አስከፊ ተግባር ሲታይ ያስገርማል። ያሳዝናልም። ወደጎን የሚካሄድ ትግልም አለ እንዴ? ያሰኛል።

 

ህዳር 4 ቀን 2010 ዓ.ም በዝዋይ ውስጥ በዎላይታና በኦሮሞ ብሔረሰቦች መካከል ተፈጠረ በተባለው አለመግባባት ምክንያት የበርካታ የዎላይታ ወገኖቻችን ሕይወት ሊጠፋ ችሏል። በርካቶችም ቆስለው ሆስፒታል ገብተዋል፤ ያልቆሰሉት ተሰብስበው፣ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሲባል በአንድ ካምፕ ውስጥ እንዲቆለፍባቸው ተደርጓል። የአንዳንድ ዎላይታ ተወላጆች ቤት ንብረት እንዲቃጠል መደረጉንም ለማወቅ ተችሏል። በጭራሽ በሁለቱ ብሔረሰቦች መካከል ይፈጠራል ተብሎ የማይታሰብ ድርጊት ሆኖ ተገኝቷል።

 

የፀቡ መነሻም በአንድ የኦሮሞ ተወላጅና በአንድ የዎላይታ ተወላጅ መካከል ከተፈጠረ አለመግባባት ጋር በተያያዘ ሁኔታ እንደሆነ ይገለጻል። በተባለው ዓይነት ሂደት የተፈጠረ አለመግባባት ባለድርሻ በሆነ የኦሮሞ ተወላጅ ላይ ደርሷል የተባለ ከፍተኛ ጉዳት በከፍተኛ ደረጃ አሳዝኖናል። እናወግዛለንም።

 

ፀቡ የተከሰተው የዎላይታ ሕዝብ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ካለው የጥላቻ ስሜት እንዳልሆነ፣ እንደይደለ፣ የማንም ሕሊና አሳምሮ ይረዳዋል። የዎላይታ ሕዝብ የኦሮሞ ሕዝብን በአገሪቱ ለመልካም ሥርዓት ግንባታ በተመሳሳይ የትግል ሜዳ ላይ የተሠለፈ የትግል አጋሩ አድርጎ ያስባል እንጂ ሌላ እምነት የለውም።

 

በዚህ ዓይነት ሁኔታ በሚታዩ ሕዝቦች መካከል አልፎ አልፎ በቤተሰብ መካከል የሚከሰት ዓይነት ችግር ቢከሰትም፤ መጠኑ የከፋ ከሆነ፣ ለፍርድ አቅርቦ፣ ተመጣጣኝ ቅጣት ማስወሰን፤ መለስተኛ ከሆነም፤ በግልፅና በመለስተኛ እርምጃ ለማቃለል መሞከር ይገባ ነበር። ሳይሆን ቀርቶ ከላይ እስከተጠቀሰ ደረጃ መድረስ አሳዝኖናል።

 

በማኅበራዊም ሆነ፣ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች በተወሰኑ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች አባላት በሆኑ ግለሰቦች መካከል የሚፈጠር አለመግባባት በሁለቱ ሕዝቦች መካከል እንደተፈጠረ ችግር በማስመሰል መንቀሳቀስ የሂደቱን ሁኔታ ግራ ከማጋባት በስተቀር ሌላ ትርጉም ሊኖረው አይችልም። የኦሮሞ ሕዝብም በዎላይታ ሕዝብ ላይ በዚሁ ዓይነት ሂደት ያምፅበታል ተብሎ አይታሰብም።

 

በኦሮሞ ብሔረሰብ አባላት መካከል ተቀላቅለው የሚገኙ የዎላይታ ብሔረሰብ አባላት፣ ልክ በዎላይታ ውስጥ እንደሚገኙ የኦሮሞ ተወላጆች የሚያደርጉት ዓይነት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ አድርገው የሚጠበቅባቸውን ከመፈፀም ሌላ ጎጂ ነገር እንደማያስቡ፣ አስበውም እንደማያውቁ እየታወቀ፤ የብዙ ዎላይታዎች ሕይወት እንደጠፋና ቀሪዎችም አካባቢውን ለቀው እንደሄዱ ማድረግና የመሳሰሉ ተግባሮች ጨርሶ የማይመጥኑ እርምጃዎች መሆናቸው መታመን አለበት።

 

ሕዝብ እንደ ሕዝብ ሊጠይቅባቸው የሚገቡ ጉዳዮችም ሆኑ፣ ጥፋቶች በሕዝቡ በራሱ የተፈጸሙ ብቻ ሆነው መገኘት አለባቸው። የግለሰቦችን ጥፋት የህዝብ እያስመሰሉ የከፋ ጉዳት በሕዝብ ላይ እንዲደርስ ማድረግ ተገቢ አይደለም።

 

በመሆኑም፡-

1.  በቅንነት በዕለታዊ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ተሰልፈው ሠላማዊ ተግባር በሚፈጽም በዎላይታ ሕዝብ ላይ የደረሰውን አስከፊ ጥቃት አጥብቀን አንቃወማለን።

2.  በተከሰተው ችግርና አለመግባባት ምክንያት ሕይወታቸውን ላጡ ለሁለቱም ብሔረሰቦች አባላት የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን እንገልጻለን።

3.  በወገኖቻችን ላይ ግድያ የፈጸሙ ግለሰቦች ጉዳይ እየተጣራ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንዲደረግ አበክረን እንጠይቃለን።

4.  በዎላይታና በኦሮሞ ሕዝቦች መካከል ያለ ለዘመናት የዘለቀ ወንድማዊ አንድነት በዚህና በመሳሰሉ ትርጉመ-ቢስ በሆኑ ደካማ ምክንያቶች እንዳይሸራረፍ ሁለቱም ህዝቦች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እናሳስባለን።

 

ከዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዎሕዴግ)

ህዳር 6 ቀን 2010 ዓ.ም

አዲስ አበባ¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
85 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 106 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us