ከ11ዱ የሀገር አቀፍ ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

Wednesday, 06 December 2017 13:22

ከ11ዱ የሀገር አቀፍ ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ

የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

ድርድር ለሰላማዊ ትግል ቀዳሚ መሳሪያ ነው!!

አማራጭ የህዝብ ድምጾች የሚሰሙበት መድረክ እንዲመቻች ለማድረግና ህዝብ ስልጣን ባለቤት እንዲሆን የሚያስችል የህግ ማእቀፍ መኖር የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት አሁን እየታዬ ያለውን የፖለቲካ ትኩሳት በማርገብ በቂምና በጥላቻ የተሞላው የአገሪቱ ፖለቲካ ተቀርፎ በምትኩ መቻቻልና መልካም ፉክክር ያለበት የፖለቲካ ምህዳር እንዲኖር ማስቻል ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ስለዚህ እኛ    11ዱ የሀገር አቀፍ ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመደራጀት መብት ከወረቀት ባለፈ ለስልጡን የፖለቲካ ስርዓት ግንባታ ሒደት መሰረት ለመጣልና ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋትና ሰብአዊ መብት እንዲከበር ማድረግ ቀዳሚ ተግባር መሆን እንዳለበት ይታመናል።

የፖለቲካ ድርድር ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደትን ለማሳለጥ ጠቃሚ መሳሪያ በመሆኑ ድርድሩ በአግባቡ እንዲካሄድ የሁሉንም ባለድርሻ አካላትን ድጋፍ የሚጠይቅ ታላቅ ተግባር ነው። ከገዥው ፖርቲ ኢህአዴግ ጋር የጀመርነው ድርድር የሃገራችንን ውስብስብ የፖለቲካ ችግር ለመፍታት ያስችላል ብለን በማሰብ ለአለፉት 11 ወራት የድርድር መተዳደሪያ ደንብን ከማዘጋጀትና ማፅደቅ ጀመሮ 12 የድርድር አጀንዳዎች በጋራ በመለየት በቀዳሚዎቹ ሶስት የምርጫ ህጎች አጀንዳዎች ላይ ድርድር አድርገናል።

በመጀመሪያው አጀንዳ ማለትም በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ 573/2000 ላይ የነበረን የድርድር ሁኔታ አሁን በምንገኝበት ስብስብ ደረጃ ሳይሆን ፓርቲዎች በተናጠልና በተወሰነ ምልኩም ቢሆን በቡድን የተደራደርን ቢሆንም በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በርካታ የድርድር ሃሳቦች ቀርበዋል። ይሁን እንጂ በወቅቱ ተደራዳሪ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቁጥር 16 ስንሆን የነበረን የድርድር ሁኔታ በተናጠል በመሆኑና እርስ በርስ ተናበን ገዢውን ፓርቲ መገዳደር ባለመቻሉ ከድርድር ይልቅ ውይይት በሚመስል መልክ የተጠናቀቀ አጀንዳ ነበር። በዚህ ሁኔታም ቢሆን በአዋጁ ውስጥ የፖለቲካ ምህዳሩን ያሰፋሉ የተባሉና የመድብለ ፓርቲ ስርአቱን ያጠናክራሉ ያልናቸውን ድንጋጌዎች እንዲሻሻሉ ተደራድረናል።  በአንፃሩ ገዢው ፓርቲ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ከቀረቡት የድርድር ሃሳቦች ውስጥ ሰፊ ክርክር ተደርጎባቸው ስምምነት ካልደረሰባቸው ማሻሻያዎች ውስጥ  ለፖለቲካ ፓርቲዎች የዳኝነት ችሎት አሰያየምና በዋናነት የአቃቤ ህግና የፕሬዝዳንቱን ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት መታገድ ዋና ዋናዎቹ ነበሩ።

ይሁን እንጂ በመጀመሪያው የድርድር አጀንዳ የነበረውን ሂደት በመገምገም ከተደራዳሪ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል አስራ አንዳችን የድርድር ሃሳቦቻችንን በጋራ በማደራጀት ከሁለተኛው አጀንዳ ማለትም ከምርጫ ህጉ አዋጅ ቁጥር 532/1999 ጀምሮ ጠንክረን እየተደራደርን እነገኛለን። እኛ የ11 ዱ ሀገር አቀፍ ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁንም በኢትዮጵያ ምርጫዎች በተሟላ ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆኑ ነጻና ሚዛናዊ ምርጫዎች እንዲካሄዱ ወሳኝ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው ብለን እናምናለን። በአገራችን የዜሮ ድምር ፖለቲካን በማስወገድ በፖለቲካ ኃይሎች መግባባትና ትብብር ላይ የተመሰረተ የተረጋጋ ፖለቲካዊ ሥርዓትን ለመፍጠር የበለጠ ወደ ሚያግዝ አማራጭ ከመቀየር አንስቶ የህግ ማእቀፉን በማሻሻል ለነጻና ሚዛናዊ ምርጫ እንቅፋት ሆነው የሚገኙ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ሁኔታዎች መሻሻል እንዳለባቸው አጠንክረን ተደራድረናል። በድርደሩም ውጤት ለማስመዝገብ ጠንክረን እየሰራን ነው።

ሁለተኛው አጀንዳ የተሻሻለው የምርጫ ህግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 ሲሆን በ2002 እና በ2007 ዓ.ም በተደረጉት የምርጫ ሂደቶች ከታዩት ጉድለቶች አንጻር በኢትዮጵያ በቀጣይነት የሚደረጉ ምርጫዎች የበለጠ ዴሞክራሲያዊና ነጻና ሚዛናዊ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የምርጫ ህግ፣ የምርጫ ስነ-ምግባር ኮዱንና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምዝገባ አዋጅን ማጣጣም አስፈላጊ የሚያደርጉ ሁኔታዎችን በመረዳት በምርጫ ህጉ ላይ መደረግ አለባቸው ብለን ያመንባቸውን የማሻሻያ ሀሳቦች በማቅረብና በመደራደር ከአለም አቀፍ የምርጫ ህግ መስፈርት፤ የተባበሩት መንግስታትንና የአፍሪቃ ህብረትን የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታና የሰብአዊ መብት አከባበር ድንጋጌዎች ስምምነት ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ለማድረግ ተደራድረናል።

በዚህም መሰረት የምርጫ አመራር አካል አደረጃጀት የአለም አቀፍ ተሞክሮዎችንና ሞዴሎችን በማቀረብ ከኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ለማጣጣም የድርድር ሀሳብ አቅርበናል። ሆኖም ግን ገዥው ፓርቲ የምርጫ አመራር አካል ባለበት ሁኔታ እንዲቆይ በመፈለጉ እኛ 11 ዱ ሀገር አቀፍ ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ ባለመስማማት ድርድሩ የተሟላ ሳይሆን ቀርቶ የምርጫ አዋጅ 532/99 በከፊል ተቋርጧል። በድርድር መርህ መሰረት የተቋረጠው ድርድር እንደገና ማየት የሚቻለበት አግባብ በገዢው ፓርቲ በኩል እንደሚኖር የተገለፀ በመሆኑ ድርድሩ ከእኛ ጋር ስለሚቀጥልበት ሁኔታ እየተነጋገርን እንገኛለን።

ነገር ግን የምርጫ ስርዓቱን በተመለከተ አሁን የምንከተለውን የአብላጫ ድምጽ የምርጫ ስርአት ወደ ተመጣጣኝ የምርጫ ስርዓት እንዲቀየር የመደራደሪያ ሐሳብ አቅርበን ነበር። የአሰራር ሂደቱንና ህጉን ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማዛመድ የመድበለ ፓርቲ ስርአት ግንባታውን የሚያጠናክርና የተሳትፎ ፖለቲካ እንዲኖር በሚያስችል መልኩ የሌሎች አገሮችንም ተሞክሮ ግምት ውስጥ በማስገባት ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦችን ከአለም አቀፍ ተሞክሮዎች ጋር በማገናዝብ ለመደራደር ችለናል።የነበረውን የምርጫ ስርዓት በምርጫ አብዛኛው ሕዝብ የመረጠው ሳይሆን አብላጫ ድምጽ ያገኘው ብቻ ሁሉንም ጠቅልሎ የሚወስድና በፖለቲካ ኃይሎች መካከል መቻቻልንና መግባባትን እያሳደጉ ከመጓዝ አንጻር አብላጫውን ድምጽ ላገኘው ፓርቲ የሚያጎናጽፈው የላቀ መብት የሌሎች ፓርቲዎችን ተሳታፊነት ስለሚያሳንስ በኛ በኩል ይህ የጠቅላይነት ባህሪ ያለው የምርጫ ስርዓት ቀርቶ ተመጣጣኝ ውክልና ስርዓት እንዲሆን ተደራድረናል።

በአገራችን የተጀመረው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እየተጠናከረ እንዲሄድ አሁን ካለበት አንድ ፓርቲ ሙሉ በሙሉ የበላይነትና ቁጥጥር ወደ ሁሉም ፖለቲካ ኃይሎች ትብብር ወደ ተመሰረተበት ደረጃ ማሸጋገር የግድ ይላል። ሥርዓቱ በሁሉም ፖለቲካዊ ኃይሎች ተሳትፎና ትብብር ላይ የተመሰረተ ከማድረግ ባሻገር በምርጫ ሂደት የሕዝባችን ተሳትፎ ተጽዕኖ ያለው እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በማመን፣ እኛ 11 ዱ የሀገር አቀፍ ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ አሁን በሥራ ላይ ያለው የአገራችን የምርጫ ሥርዓትን በመቀየር በአገር ግንባታ ሂደት በተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ሊኖር የሚገባውን ትብብር የሚያጎለብትና ለኢትዮጵያ ዴሞክርሲ ዕድገት አስተዋጽዖ የሚያደርግ የምርጫ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ የአብላጫ ድምጽ ስርዓትን ወደ ቅይጥ ትይዩ የምርጫ ሥርዓት (mixed parallel electoral system) ለመቀየር ከገዥው ፓርቲ ጋር ስምምነት ላይ ደርሰናል።

ቅይጥ ትይዩ የምርጫ ስርአት በኛ በ11 ዱ ተደራዳሪ ፓርቲዎች በኩል የባከኑ ድምጾች በመቶኛ ስሌት ለተመጣጣኝ ውክልና እና ለአብላጫ ድምጽ ይሁን የሚለው ቀመር ላይ ለበርካታ የድርድር መድረኮች ከተደራደርን በኋላ  ለተመጣጣኝ ውክልና 20% ለአብላጫ ድምጽ 80% የውክልና ድምጽ አሰራር እንዲኖር በመስማማት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ አሁን ካለው ተጨማሪ 110 ወንበሮችን በማካተት ወደ 660 መቀመጫዎች እንዲያድግ ስምምነት ላይ ተደርሱዋል። በእኛ እምነት ይህ የባከኑ ድምጾች ወደ ፓርላማ ወንበር እንዲቀየሩ ማደረግ የፖለቲካ ተሳትፎን በመጠኑም ቢሆን እንደሚያሻሽል እናምናለን።

በሦስተኛ ደረጃ የተደራደርንበት አጀንዳ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 662/2002  ሲሆን እኛ 11ዱ የሀገር አቀፍ ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ በአዋጁ ውስጥ የተካተቱ የህግ ድንጋጌዎችን ከህገመንግስቱና ከአለምአቀፍ የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች ጋር በማነጻጸር የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተሳትፎን ይገድባሉ ብለን ያልናቸውን አንቀጾች እና መጨመር አለባቸው ያልናቸውን ሐሳቦች ከነማሻሻያቸው ለይተን በማቀረብ ተደራድረናል። በአዋጁ ውስጥ ከተካተቱት አንቀጾች ውስጥ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ የሚገድቡና ጥንካሬያቸውንም የሚፈታተኑ ናቸው ያልናቸውን 10 አንቀጾች እንዲሻሻሉ፣ 4 አንቀጾች እንዲሰረዙ፣ 2 አንቀጾች እንዲጨመሩ በማቀረብ ሁሉንም በሚባል ደረጃ ገዥው ፓርቲ ተስማምቷል። ነገር ግን የጋራ ምክር ቤት ተቋማዊ ይዘትና ክትትል ከፌደራል እስከ ወረዳ ድረስ የሚደራጁትን የጋራ ምክር ቤቶች የምርጫ ኮሚሽን እንዲያቋቁማቸውና እንዲከታተላቸው ሐሳብ አቅርበን ገዥው ፓርቲ አልተስማማም። ነገር ግን የጋራ ምክር ቤቶች በተዋረድ ባሉት ምክር ቤቶች  ስር እንዲሆኑ በቀረበው የመደራደሪያ ሐሳብ በመጽናቱ ከስምምነት ላይ አልተደረሰም።

 

እኛ 11ዱ የሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች፡-

1.       እየተደመረ የሚቀጥል ዘላቂ ለውጥን በተቻለ ፍጥነት ማረጋገጥ ከሚያስችሉ አማራጮች መካከል አንደኛው ለአገራችን ዲሞክራሲ መጎልበት ገንቢ የሆኑ ሀሳቦችን በመተማመን ደረጃ በደረጃ ተቋማዊ እየሆኑ እንዲያድጉ የሚያስችሉ ስምምነቶችን መፍጠር ነው ብለን ስለምናምን ገንቢ ሀሳቦችንና ስምምነቶችን መፍጠርያ የሆኑ ውይይቶቸንና ድርድሮችን ማድረግ እንደ ወሳኝ የትግል ስልት አድርገን ድርድሩን ወደፊት ማስቀጠል፣

2.       የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን ያለው የአገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አንጻር አስፈላጊ በሆኑ የሀገር ጉዳዮችና በአገር ግንባታ ሂደት በተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ሊኖር የሚገባውን ትብብር ለማምጣት፣ ገዥው ፓርቲ ሙሉ በሙሉ በብቸኝነት እየተቆጣጠረው እንዳይሄድ የሚያስችል ፖለቲካዊ ተፅእኖ በመፍጠር፣ ለብሔራዊ መግባባት፣ ፖለቲካዊ መቻቻልና አንድነት እንቅፋት የሆኑ ህጎችና ፖሊሲዎችን በማሻሻል ህዝቡ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሚያደርገውን ተሳትፎ ለማጎልበት በቁርጠኝነት እየታገልን የህዝቡን ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ለለውጥ እንሰራለን።

3.       በአገራችን የተጀመረው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እየተጠናከረ እንዲሄድ አሁን ካለበት የአንድ ፓርቲ የበላይነትና ቁጥጥር ተላቆ በሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ትብብር የሚመሰረትበት ምእራፍ ማሸጋገር የግድ ስለሚጠይቅ፣ መቻቻልና መግባባት እየሰፈነና እየሰረጸ ቀስ በቀስ አገራችን ከዜሮ ድምር ፖለቲካ እንድትላቀቅ  ማስቻል ነው። የፖለቲካ ሥርዓቱን በሁሉም ፖለቲካዊ ኃይሎች ተሳትፎና ትብብር ላይ የተመሰረተ ከማድረግ ባሻገር ዜጎች በምርጫ የሚፈልጉትን ወደስልጣን ለማምጣት የማይፈልጉትን ለማውረድ የሚችሉበትን ስርአት በማምጣት የዜጎችን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተሳትፎ ጠንካራ እንዲሆን ለማድረግ በትጋትና በቁርጠኝነት እንሰራለን።

4.       በዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የመገናኛ ብዙሃንና ፀሃፊዎች የማተካ ሚና አላቸው። በመሆኑም የድረድሩን ሂደት በቅርብ በመከታተል ለህዝቡ መረጃ ተደራሽ በማድረግ የህዝቡን ተሳትፎ ከፍ እንዲልና በፖለቲካው ወሳኝ ሚናውን እንዲጫወት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

5.       ድርድር የሃሳብ ትግልን ማእከል ያደረገ የህዝብን ፍላጎት በመወከል የሚደረግ የፖለቲከኞች ሰላማዊ መድረክ ነው። አሁን ከገዢው ፓርቲ ጋር እያደረግን ያለው ድርድር በህዝብ ጥያቄና ተፅእኖ እንጂ በፓርቲዎች የልየነት አጀንዳ ተፅእኖ የተፈጠረ ክስተት አይደለም።በመሆኑም በተለይ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚታየው ተገቢ ያልሆነ የጥላቻና የፍረጃ ፓሮፓጋንዳ የአንድ ፓርቲ አገዛዝን ከማራዘም በስተቀር የፈየደው ነገር ስለሌለ በመካከላችን ተከባብረን የውድድር ሜዳውን በማስተካከል ሁላችንም በህዝብ ድምፅ ለመዳኘት ዝግጁ መሆን ይጠበቅብናል።

6.       በመጨረሻም ከዚህ ድርድር የሀገሪቱ ህዝቦች በፖለቲካው ምህዳር መጥበብ ምክንያት ያጡትን የተሳትፎ መብት ለማግኘት ያስችላል ብለን ስለምናምን፣ የፖሊተካ ፓርቲዎችን፣ የብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮችንና በአጠቃላይ የዜጎችን የተለያዩ አስተሳሰቦች ወደመድረክ ሊያመጣ ይችላል ብለን ስለምናስብ የድርድሩን ሂደት የባለድረሻ አካላት ድጋፍ እንዳይለየን በዚህ አጋጣሚ ጥሪ እናስተላለፋለን።

የ 11ዱ የሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ

1.       የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ደርጅት (መኢአድ)

2.       የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(መኢዴፓ)

3.       ቅንጅት ለአንድነትና ለፍትህ (ቅንጅት)

4.       የኢትዮጵያውያን ዴሞክረሳያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)

5.       አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ (አንድነት)

6.       የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ(አብአፓ)

7.       የኢትዮጵያ ዴሞክራሲዊ ህብረት(ኢድህ)

8.       የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ(ኢዴአን)

9.       አዲስ ትውልድ ፓርቲ(አትፓ)

10.     የኢትዮጵያ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(አሰዴፓ)

11.የወለኔ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርተ(ወህዴፓ)

ህዳር 2010

አዲስ አበባ¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
96 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 121 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us