የህዳሴ ክትባቶች

Wednesday, 13 December 2017 12:58

ዳደ ደስታ

 

1) የከረረን ማክረር


አትሌቶች ወደ ሩጫ ውድድር ሲገቡ በቡድንም በግልም ይዘዋቸው የሚገቡ የተለያዩ የማሸነፊያ ዕቅዶችና ስልቶች ይኖራሉ። “ዙሩን ማክረር” አንዱ ሊሆን ይችላል። ሰሙኑን ከዓባይ ውኃ ጋር በተገናኘ ከወደ ግብጽ የሚሰሙ ድምጾችና ቅኝቶችም ዙሩን ለማክረር ያለሙ ይመስላሉ። “ከዓባይ አንዲት ጭልፋ ውኃ አትቀነስም” ሲሉን ከረሙ። ድርድሩ ቅርቃር ሲገባ እንዲህ ዓይነት ኃይለ ቃሎች ከዓባይ ወንድሞቻችን ሁሌ የምንሰማው የተለመደ ነገር ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ዘላቂ መፍትሄ እሚሻ ትልቁና ቀዳሚው የኢትዮጵያ አንገብጋቢ አጀንዳ እንደመሆኑ በሳል አያያዝ ይጠይቃል።


አንዳንዱ አጥር (ችግር) አርቀህ ወደፊት ብትገፈትረውም እንደገና እዛው ስትደርስ ተገትሮ ይጠብቅሃል። ትርፉ ሁለተኛና ቀጣይ ድካም ነው። እማያዳግም ሥራ ይጠይቃል፤ ወደ ጎን በማሽቀንጠር አለያም በብልሃት አልፎ በመሻገር መገላገልን ይጠይቃል። ደግሞ አንዳንድ ተላላፊ በሽታዎች አሉ፣ መድሀኒታቸው በሽታው ራሱ ነው። መከላከያ ክትባቱ እሚቀመመው ከራሱ ከበሽታው ስለመሆኑ ልብ ሳትሉ አልቀራቹሁም።


ኢትዮጵያ በ‹እገድባለሁ አትገድቢም› ዘላለሟን ከግብጽ ጋር ስትጣላ አትኖርም። መፍትሄውም፣


‹አንድ ቀን ይረዱን ይሆናል› በሚል ተስፋ ብቻ ግድቦችን ለሌላ ጊዜ እያቆዩ ከግብፆች ጋር መደራደር አይደለም። ይልቁንም ግድቦቹን እየገነቡ መደራደር ነው። ከግብጾች ጋር ያለን ግድብ-ወለድ ጸብ ማርከሻው ራሱ ግድብ በመሆኑ ግድብ ገንብቶ መገኘት እንጂ ምክንያታዊነት አይሆንም።


የኢትዮጵያውያን ደማቅ ታሪክና ስልጣኔ ከወረቀትና ብራና በፊት ድንጋዮች ላይ ተጽፏል። አሁን ደግሞ ዘመኑ ደርሶ በውኃ ላይ እየተጻፈ ነው። የህዳሴው ግድብ ልኬት ከዚህ አያንስም። በአሁኑ ወቅት የህዳሴው ግድብ የናይል ዲፕሎማሲ ማእከላዊ ስበት ሆኗል። ከግብጽ ጋር በስውርም በገሃድም እማያቋርጥ ግብግብ ዉስጥ ነን ብለናል። በዚያ ሁሉ የዘመናት ስውርና ግልጽ ውግያ ኢትዮጵያ ሁለቴ ከማሸንፏ በቀር ድሉ የግብጽ ሆኖ ዘልቋል። ግን ደግሞ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ሶስተኛው ድል ተደርጎ ሊቆጠር እሚገባው ነው። ያውም የቀደምቶቹ የጦርነት ድሎች የአንድን ጊዜ ክስተት መደምደሚያ ብቻ ነበሩ። ይህ ግን ለቀጣይ ሌሎች ብዙ ድሎች ምቹ ንጣፍ እሚፈጥር የልማት ድል ነው።


ስለ ህዳሴው ግድብ ብዙ ጊዜ ብዙ ነገር ብያለሁ። ይሀኛውም የመጨረሻ አይሆንም። ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ አገራዊ ዕጣ ፈንታ በእንደዚህ ዓይነት ሚዛን በአንዲት ፕሮጀክት ስኬትና ውድቀት ላይ ተንጠልጥሎ አይቼ አላውቅም። ያም ማለት፣ የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያን ጂኦፖለቲካዊ የከፍታ ሽግግር እውን ለማድረግ ስትራተጂካዊ ሚና የመጫወቱን ያህል፣ በግንባታው ዘመን የአገራችን ተጋላጭነትንም በዚያው ልክ ከፍ አድርጎታል። በአንዳንድ ገፅታው፣ የግድቡ የግንባታ ሂደት ስኬት ከግድቡ አገልግሎት መጀመርና መስጠት በላይ ስትራተጂክ ሆኖ ታይቷል። ለዚህም ነዉ አንዳንድ ጉዳዮችና ማሳሰቢያዎች ተደጋግመው መነገር እሚኖርባቸው።


የህዳሴን ግድብ ገንብቶ መጨረስ ማለት ኃይል ማመንጨት መቻል ማለት ብቻ አይደለም። የግብጽን ድንበር ዘለል አፍራሽ እጆችንም ከኢትዮጵያ ጉዳዮች እንዲገደቡ ማድረግ ማለት ነው። ይህ የመጀመርያው ውጤት ሲሆን የኋላኋላ የኢትዮጵያና የግብጽ እጆች በወዳጅነትነት እየተጨባበጡ እንዲዘልቁ ማድረጊያም ነው። ወደ ፊት ኢትዮጵያ፣ የግብጽ ድጋፍና አጋርነት ሳትጠይቅ የምታገኘው ገጸ-በረከት ይሆናል። የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን መጎሰ-ቦታ ለአንዴና ለመጨረሻ በአዎንታዊ መልኩ ይቀይረዋል። እንግዲህ ኢትዮጵያ በዚህ ትልቅ ድል አፋፍ ላይ እንደመሆኗ ሁኔታውን የሚመጥን ጥንቃቄ የግድ ይላል።


ግድቡ ኃይልና ጉልበት ነው። ጉልበት ነው፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ በሚገባት ጂኦፖለቲካዊ ማማ ላይ በማስቀመጥ ገንቢ ተጽእኖዋ ለማሳረፍ የሚያስችላት ትክክለኛ ቦታዋን ስለሚያሰጣት። ግድቡ ኃይል ነው፤ ምክንያቱም አሁን የሚመነጨውን ድምር ኃይል ካለበት 3 እጥፍ ከፍ እንዲል ስለሚያደርገው። ስለዚህ ግድቡ የጉልበት (የተጽእኖ) እና የኃይል (ኤሌክትሪሲቲ) ፋይዳ ነው ያለው። ይህ ግድብ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የላቀ ቢባልም ከዚያ በላይ ግን ዓይነተኛ መለያው ጂኦፖለቲካዊ ጥቅሙ ስለመሆኑ አያከራክርም።


በህዳሴው ግድብ ዙርያ ካሉት ገጽታዎች፣ ጂኦፖለቲካዊ ፋይዳው የፕሮጅክቱ ዋነኛ የስህበት ማዕከል መሆኑን ያሳያል። እርግጥ ኃይል በማመንጨት ለአገሪቷ ዕድገት የሚጫወተው ሚናም ቀላል አይሆንም ብለናል። እሱኛውን ግን በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ነው። ከዚህ ግዙፍ ግድብ መገንባት ጋር በሶስተኛ ደረጃ የሚታዩ ገጽታዎችም ይኖራሉ። ለምሳሌ ከተፈጥሮ መነካካት ጋር የሚያያዙ አካባቢያዊና ከርሰ-ምድራዊ ሁነቶች። በጥቅሉ “የጋራ” በሚል ሊገለጹ ይችላሉ። በግድቡ ዙርያ ከታች ግርጌ ተፋሰስ ሃገሮች፣ ከግብጽና ሱዳን ጋር የሚደረጉ ድርድሮች እነዚህን ሶስት ገጽታዎች ለየብቻ ለይተው በመፈረጅ እንደየአንገብጋቢነታቸው ለኢትዮጵያ ካላቸው ትርጉም መዝነው የሚያዩ መሆን ይገባል። ይህም በድርድር ሂደትና ጥበብ አዋቂዎች እንደሚጠሩት፡ “ለድርድር የማይቀርብ/ የማይሸጋሸግ ዋና ጉዳይ”፣ “ሁለተኛው ዋና ጉዳይ” እና “የማያወዛግብ ጉዳይ” ማለትም (Competitive Needs, Redressable Needs, Mutual Needs) የሚባልቱ ዓይነት መሆኑ ነው።

 

2) ጂኦ ፖለቲካዊ…


አሁን ጥያቄው ከህዳሴው ግድብ ገጽታዎች ውስጥ በቀጥታ የኢትዮጵያ አገራዊ ጂኦፖለቲካዊ ፋይዳዎች ከተባሉት ጋር የተቆራኙ፣ እናም በፍጹም ለድርድር መቅረብ የሌለባቸው የትኞቹ ሁኔታዎች ናቸው የሚለውን ነው። የዚህ ጥያቄ መልስ ግን ቀላል ነው። ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር ላላትና ተያያዥ ግንኙነቶች የተጽዕኖ ጉልበት የሚያጎናጽፏት የግድቡ ባህርያት ለይቶ መገንዘብን ይጠይቃል። ይህ ግብጽ አጥብቃና በቅድሚያ የምታቀርባቸው የድርድር ጥያቄዎች ራሳቸው ወደ ተባሉት ሁኔታዎች ይጠቁማሉ። ለማሳያ ያህል አይነኬ ያልናቸውን ጉዳዮች እንነካካ። አብዛኛው ጊዜ ድርድሮቹ የጦዘ መካረር ውስጥ የሚገቡት በወሳኝና ተነጣጣቂ (competitive) ባህርያት ባላቸው ነጥበ-ውዝግቦች ዙርያ ነው። ወሳኝ ፍልሚያ የሚካሄደውም በነዛ ጉድዮች ላይ ነው። አንዳንዴ ለማለዘቢያ ወይም እንደግርዶሽ እንዲያገለግሉ በማስላት ለመስማማት አስቸጋሪ የማይመስሉ ጥያቄዎች ተጃምለው የሚቀርቡ ቢመስሉም ዋናው ግብግብ ግን ወሳኞቹ አጀንዳዎች ላይ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት እንደመቆናጠጫ እንዲያገለግሉ ታስበው ነው። እንጂማ ወሳኞቹ አጀንዳዎች ላይ ያለበቂ ፍልሚያ የሚሸነፍ ወይም የመጀመርያ አቋሙን የሚለቅ ተደራደሪ የለም።


ግብጽና ኢትዮጵያም ግድቡን ወይም በአጠቃላይ የናይልን ውኃ በተመለከተ የሚጠብቃቸው የድርድር ትንቅንቅ ኢትዮጵያ በወንዙ ላይ ያላት የቁጥጥር ጉልበትና ድርሻ ለማረጋገጥ፣ ግብጽ ደግሞ ይህ እውን እንዳይሆን በሙሉ ዓቅምና ጥበብ መታገል ነው። በዚህኛው የሞት-ሽረት አጀንዳ ላይ አሸንፎ መውጣት ለሁለቱም ያለው ትርጉም ሰፊ ነው። ግብጽ ከሞላ ጎደል ለዘመናት የቆየውን የውኃው ብቸኛ ተጠቃሚነት በአንድ እጅ፣ እንዲሁም በሌላው እጅ፣ የኢትዮጵያን የመጠቀም ፍላጎትና አቅም እንደነበረው ማስቀጠል ሲሆን ኢትዮጵያ ደግሞ ይህንን አስተሳሰብና ሁኔታ እሰከ ወዲያኛው ማስቀየር ነው። በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ አሻጥር፣አለያም በደህንነታዊ ሴራዎችና ወታደራዊ ዛቻዎች፣ ካልሆነም በየድርድሩ ፍልሚያ በተናጠል ወይም በጣምራ የሚገለጽ ይሁን እንጂ የትግሉ ማዕከላዊ ግብ እሚሽከረከረው አሁን በጠቀስኩት ጭብጥ ዙርያ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያን በዓባይ ውኃዊ ሃብቷ ላይ የማዘዝ ዓቅሟንና መብቷን በማኮላሸትና በማቃናት መካከል አገራዊ ወሳኝ ጥቅሞቻችን በውስብስብ የድርድር ሂደቶች በሚሰነቀሩ የተንኮል ቀዳዳዎች ሾልከው እንዳይጠፉብን መድረኮቹን የሚመጥን ዝርዝር እውቀትና የሃሳብ ልዕልና ታጥቀን መቅረብ አለብን።


ይህን አይነኬ ያልነው አጀንዳ ወሳኝ የትግል ነጥብ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ልብ ለማሸነፍ ብቻ የሚሰሩበት ግንባር ነው። እዚህኛው አጀንዳ ላይ ከግብጽ ወንድሞቻችን ጋር እምንጋራው ድል የለም። እያንዳንዷ የግድቡ ስኬት ለኢትዮጵያውያን ፍስሃ የመሆኗን ያህል ለግብጾች ሌላ ስሜት ናት። ይህ ግን ይህንን ወሳኝ የግንባታ ም ዕራፍ ሙሉ በሙሉ እስኪታለፍ ነው። ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያና ግብጽ በግድቡ ምክንያት ከሚፋጠጡ ይልቅ ይቀራረባሉ። አንዱ ሌላውን ከሚጠራጠረው ይልቅ መናበብና መደጋገፍ ገዢ የግንኙነት መገለጫ ይሆናል። ስለዚህ የዚህ ዓይነት ቁልፍ ባህርይ ይዘዋል እምንላቸው የግድቡ ገጽታዎች ምን ምን እንደሆኑ ለይቶ መመርመር ይገባል።


ለምሳሌ የኢትዮጵያ ጂኦፖለቲካዊ ወሳኝ ጥቅም ከሚገለጽባቸው የግድቡ ገጽታዎች ሁለቱን ለማየት እንሞክር። አንዱ የግድቡ ግንባታ ፍጥነት ነው። ግንባታው ‹መች ተጀምሮ መች ያልቃል› የሚለው ጉዳይ የኢትዮጵያውያንም የግብጻውያንም ስሜት ከተቃራኒ ምክንያት እኩል ወጥሮ የያዘ ጉዳይ ነው። ይህ ሲጀመር ጀምሮ ከግንባታው ዕድገት ጋር እየጦዘ የተጓዘ ስሜት ነው። የጡዘቱ ንረት ከግንባታው ልዩ ልዩ እርከኖች ጋር ከፍና ለጠቅ ሲል ተስተውሏል። የግድቡ ስራ ሲጀመር ግብጽ ውስጣዊ የፖለቲካ ትርምስ እያስተናገደች ነበረ። በዚያን ጊዜ የነበረውን የግብጽ የሽግግር ፓርላማ ህዝባዊ ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያ ድረስ ልኮ ያቀረባቸው ሁለት ጥያቄዎች ነበሩ። ልዑካኑም አገራችን እየታመሰችና ሽግግር ስለሆነ እስክትረጋጋና ቋሚ መንግስት እስክታገኝ በሚል ነበር ጥያቄዎቹን ያቀረቡዋቸው። አንደኛው የኢትዮጵያ መንግስት ተቀብሎት ግን ገና በፓርላማ ጸድቆ ህግ እንዲሆን በአጀንዳ ተይዞ የነብረውን የኢንቴቤው ትብብራዊ ማዕቀፍ ሳያጸድቅ ግብጽ እስክትሸጋገር ድረስ ፓርላማው እንዲታገስ የሚል ሲሆን በተመሳሳይ ምክንያትም የተጀመረው የግድቡ ግንባታም ለተመሳሳይ ጊዜ የግንባታው ሂደት እንዲቆም ነበር። የኢትዮጵያ መንግስት ህጉን የማቆየት ጥያቄ ሲቀበለው ግንባታውን የማቆየት ጥያቄው ግን ውድቅ አደረገው። ያም ትክክለኛ ውሳኔ ነበር።


ግብጽ በተለያዩ ሰበቦች የግድቡ ግንባታ ለአፍታ ያህል ቆም እንዲልላት ያልጠየቀችው ጊዜ የለም። አሁንም ድረስ ግድቡ በአካባቢያዊ ተፈጥሮና የሰዎች ደህንነት ላይ የሚኖረው ተጽእኖ በምልአት ተጠንቶ እስኪታወቅ ድረስ “ግንባታውን ቆም አድርጉት” የሚል ውትወታ በየስብሰባ መድረኩና በግብጽ የሚድያ አውታሮች ያለመታከት የሚቀርብ ፈተና ነው። ሆኖም እሰከ አሁን የግድቡን የተፋጠነና ያልተቋረጠ ግንባታ ወደ መጨረሻው የጂኦፖለቲካዊ ልዕና የሚያደርስ ሂደት በመሆኑ በዚህ የተዘናጋ አልነበረም። እርግጥ በገንዝብ ምክንያትና በሌሎች ተጨባጭ ከዓቅም በላይ የሆኑ ችግሮች ሊኖር የሚችለውን መጓተት ሌላ ጉዳይ ነው። የግድቡ ግንባታ ዘገየ ማለት ግን ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር ባላት ግንኙነትና ተዛማጅ ሁኔታዎች አንጻር ወደ አዲስ ምዕራፍ የምትሸጋገርበትን ፍጥነት ማዘግየት ማለት እንደሚሆን ሙሉ ግንዛቤ ማግኘት አለበት።


ሁለተኛው ከዚህ የጂኦፖለቲካዊ ቁምነገር አንጻር አያይዘን የምናየው ነጥብ የግድቡ አጠቃላይ ዓቅመ-ስፋትና ትልቀት ነው። ይህም ቅድም በአንደኛ ደረጃ የጠቀስነውን የግድቡ ጂኦፖለቲካዊ ቁመናን ይመለከታል። በዚህ ላይም ቢሆን አንዳች ድርድር ሊፈቀድ አይገባም። ግብጾች ሁሌም የግድቡን መጠን አሳንሱት የሚል መደራደርያ ይዘው ይቀርባሉ። በትልቁና 6250MW የማመንጨት ዓቅም ባለው ግዙፍ ታላቁ የህዳሴ ግድብ መጀመር ቁልፍ ምርጫ የሚሆንበትም አንዱ ምክንያት ከተባለው ጂኦፖለቲካዊ ጉልበት አኳያ ሲመዘን ነው። ለምሳሌ ግብጾች እንደ አማራጭ አቅርበውታል ተብሎ የሰማነው አንዱ የመደራደርያ ነጥብ የግድቡ መጠን አሁን ካለው ዕቅድ ዝቅ ብሎ በዚያ ምክንያት ኢትዮጵያ የምታጣውን የኃይል (power) መጠን በገንዘብ ተተምኖ ለኢትዮጵያ ማካካሻ እንዲሰጣት የሚያግባባና ሌሎች ትንንሽ ብዙ ግድቦች እንዲገነቡ የሚል እንደነበር ነው። ብልጥ አቀራረቦች የሚከሰቱት በተለያየ ብልሃት ነው። አላማና ግባቸው ግን ሁሌም ከላይ ባነሳነው ቁምነገር ዙርያ እሚሽከረከር ነው። ግብጽ በዚህ አቀራረቧ ተሳክቶላት ተቀባይ ብታገኝ ለኢትዮጵያ እምትከፍለው ማካካሻ ክፍያ ኢኮኖሚያዊው ጥቅም የሚሸፍን እንጂ ዋናውን ጂኦፖለቲካዊውን ጉልበት ግን በተቃራኒው የሚቀንስ ነው።


በእንደዚህ ዓይነት አቀራረብ ብንበለጥ ይህን ተዓምረኛ ግድብ የሚያስጨብጠንን የተጽእኖ ጉልበት በገዛ እጃችን ማስነጠቅ ይሆንብናል። ግብጽ ዘላለሟን በማስፈራራትና በብልጠት በኛ ኪሳራ ስትለማ የቆየች አገር ናት። ግብጽ ራሷ የመልማቷ ጉዳይ ሳይሆን ልማቷን ከኢትዮጵያ መቆርቆዝ ጋር አስተሳስራ የማየቷ ጉዳይ ነው ችግር የሆነው። ኢትዮጵያ ከዚህ ውትብትብ የግብጽ እንቅፋቶች በጥሳ እምትወጣው ይህ ግድብ ሳይዘገይና ሳይሸራረፍ በፍጥነትና በምልአተ ቁመና ተሰርቶ እውን ሲሆን ነው። “ለድርድር አይቅረብ” ያልነው ወሳኝ ጥቅምም የሚረጋገጠው በዚህ መንገድ ነው።

 

3) ኢኮኖሚያዊ …


ተካካሽ አጀንዳዎች ወዳልናቸው እንምጣ። ሁለተኛው የህዳሴው ግድብ የፋይዳ ምሰሶ ኃይል ማመንጨቱ ነው ብለናል። ይህ ገጽታ በባህርይው ኢኮኖሚያዊ በመሆኑ የሚካካስ (redressible) ነው። ይህም ገጽታ ቢሆን ግን መገለጫ አለው። ለምሳሌ ግድቡ በቶሎ ኃይል ማመንጨት እንዳለበት ይታወቃል። በፍጥነትና በሙሉ ዓቅም ኃይል ማመንጨት ይጀምር ዘንድ የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ብቻ በቂ አይደለም። ግድቡ ሙሉ ለሙሉ ውኃ መሙላት አለበት። አንዱ የግብጽ ስጋትም ይህ ግዙፍ ግድብ ውኃ የሚሞላበት ፍጥነትና ሁናቴ በምን ያህል ጊዜ የሚለውንና በየወቅቶቹ ካለው የተለያየ የወንዙ የውኃ ይዘት መጠን ጋር ከማጣጣም ጋር የተያያዘ ነው። ይህኛው የግብጽ ስጋት ግን ተገቢ ነው። ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ግድቡን ውኃ ለመሙላት ብትሞክር፣ ለምሳሌ ግድቡ እስኪሞላ ድረስ የሚፈሰውን ውኃ ሙሉበሙሉ ወደ ግድቡ ላስገባ ብትል ግድቡ ሞልቶ እስኪፈስ ድረስ ግብጽ ከዓባይ አንድም ጠብታ ውኃ ላይደርሳት ነው። ይህ ፈጽሞ ተፈላጊም ፍትሃዊም አይደለም። ስለዚህ ግብጽ በተራዘመ ሂደትና ከየወቅቱ ጋር በተጣጣመ ሁኔታ ግድቡ እንዲሞላ የምታቀርበው ጥያቄ ከትክክለኛ ጉዳትና ስጋት የሚመነጭ በመሆኑ ጉዳቱንና ስጋቱን ለመቀነስ እንዲቻል ኢትዮጵያ ልታጤነው የሚገባ የድርድር ይዘት ነው።


ግብጽ የጠየቀችውን ያህል የተራዘመ ጊዜ ይሁን የሚል አቋም ባይኖረኝም ኢትዮጵያ ካቀደችው ረዘም ያለ፣ ግብፅ ከጠየቀችው ጊዜ አጠር ያለ የመሙያ ክፍለ-ጊዜ እንደአማራጭ ለማስተናገድ የሚቻልበት መንገድ አለ። ኢትዮጵያ ለግድቡ የመሙያው ጊዜ ብላ ካቀደችው በላይ በረዘመ ሁኔታ ቢፈጸም ኪሳራው ኢኮኖሚያዊ ብቻ ነው የሚሆነው። በመሙያው ጊዜ መራዘም የሚከሰት ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ልክ ግብጽ ኢትዮጵያን በገንዘብ ብታካክስ ሁለቱም አሸናፊዎች የሚሆኑበት ሁኔታ ፈጠሩ ማለት ነው። ይኸኛው ሁለተኛው ዋና ጉዳይ በመሆኑ ልዩነቶችን በማቻቻልና ጉዳቶችን በመካፈል በገንቢ ድርድር የሚስተናገዱ ፋይዳዎች ያካተተ የግድቡ ገጽታ ነው። መፍትሄውም መተሳሰብና መግባባት ነው። ምክንያቱም ቅድም ከጠቀስነው የጂኦፖለቲካዊ ገጽታ ወጣ ያለና የአንዱ ወገን ተጠቃሚነት ለመጠበቅ ሌላኛው ትክሻ ላይ የሚያርፈውን ዕዳ በማካካስ የሚፈታ የኢኮኖሚ ጥቅም ጥያቄ ብቻ ስለሆነ።

 

4) አካባቢያዊ …


የጋራ አጀንዳዎቹ የተባሉት ግን የተወሳሰበ መልክና ይዘት የላቸውም። እላይ ካብራራሁዋቸው ሁለት ቀዳሚ ጉዳዮች በሶስተኛ ዘርፍነት የሚፈረጅ የግድቡ ገጽታ ሁላችንም በጋራ የምንጋራው ነው። እዚህ ውስጥ ከግድቡ ግንባታ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ቁምነገሮች ለምሳሌ ያህል ብጠቅስ “የግድቡ መሰራት በአካባቢው አቀማመጥና ተፈጥሮ ስለሚኖረው አሉታዊ ተጽእኖ፣ ግድቡ እጅግ ግዙፍ ከመሆኑ ጋር መወሰድ ስለሚኖርባቸው የደህንነት ጥንቃቄዎችና ተያያዥ ጉዳዮች” እና የመሳሰሉትን ማለቴ ነው። እነዚህ ሁኔታዎች በተመለከተ ቅድም ከላይ ከጠቀስናቸው የልዩነት አጀንዳዎች ጋር በማያያዝ ካልተወሳሰቡና ራሳቸውን ችለው እስከቀረቡ ድረስ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በጉዳዮቹ ላይ አንድ ዓይነት ወይም ተቀራራቢ አቋሞ የማያራምዱበት ሁኔታ አይታየኝም። በዚህ ላይ አገሮቹ አቀማመጣቸው ግርጌ ወይም ራስጌ ከመሆናቸው ጋር በተነጻጻሪ ልዩነት አጋንነው የሚያቀርብዋቸው የጥንቃቄና የደህንነት ጉዳዮች ካሉም በምክንያትና በማስረጃ እንዲታዩ ማድረግ ነው። ከዚህ ውጭ ባለሙያዎችና ገለልተኛ ታዛቢዎች በሚያቀርቡዋቸው የጥናት ውጤቶችና የማስተካከያ ሃስቦች አገሮቹ ከየሁኔታቸውና ከእውነታዎቹ ጋር እያጣጣሙ ተግባብተው ሊሄዱበት የሚችሉ ብዙ ማጨቃጨቅ የሌለበት ሁኔታ ነው።

 

5) አነጋገራችን …


አንድ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ ሰው በቅርቡ ካይሮ ሄዶ እዛ ከተማ ዉስጥ ከተዋወቀው ባለ ታክሲ ጋር ስለውሃውና ስለሁለቱ አገሮች ወግ ይዞው ነበር። በመሃል ጋዜጠኛው ያልተለመደ እሚመስል አስተያየት ከግብጻዊው ይሰማል። ግብጻዊው ኢትዮጵያ ውሃ ገድባ ግብጽን ታስጠማለች በሚለው አያምንም። ስለ ግድቡ ሲያነሳበትም እንደ ችግር አላየውም። ግብጻዊው “እኔ ይህ አያሳስበኝም። ፖለቲከኞቻችን የሚጠቀሙበት የማስደንበርያ ፕሮፕጋንዳ ነው። ኢትዮጵያ ናይልን ያህል ገድባ ግብጽን ለማስጠማትና ራሷን ለማሰመጥ እምትፈልግበት ምክንያት አይኖርም፣ ዞሮ ዞሮ ውሃውን መልቀቋ አይቀርም።” ነበር ያለው።


ሌላ ኢትዮጵያዊ ምሁር ደግሞ ከአንድ ግብጻዊ ዶክተር ጋር ሲነጋገር የገጠመውን በፌስ ቡክ አጋርቷል። ይህኛው ግብጻዊ ዶክተር እሚለው ደግሞ ቅድም ካየነው ተቃራኒ ነው። “ኢትዮጵያና እስራኤል ተጋግዘው የግብጽን ጉሮሮ በውሃ ጥም ለመቅጣት እየሰሩ ነው” ብሎ ያምናል። ከሁለቱ ምሳሌዎች እምናገኘው ቁምነገር፣ ዲፕሎማሲያችን ጥሩ መረጃና ኮሚኔኬሽን ላይ አተኩሮ ቢሰራ ብዙ ድሎችና ወዳጆች ለማፍራት እሚኖረው ተስፋ ሰፋ ያለ መሆኑን ነው።


ከአራት ዓመት በፊት የግድቡን መደላድል ለመገንባት የአባይ ወንዝ ከመስመሩ ዘወር ተደርጎ እንዲፈስ ሲደረግ ባለስልጣኖቻችን መግለጫዎች ሲሰጡና እና ሚዲያዎቻችን ዜናውን ሲያስተላልፉ “የአባይን ወንዝ አቅጣጫ ማስቀየር”፣ በእንግሊዝኛው divert የሚል ቃል ነበር የተጠቀሙት። ይህን ተቀብለው የግብጽ ሚዲያዎችና ፖለቲከኞች አራገቡት። ለግብጾች ጭራሽ የአባይ ወንዝ መዳረሻ ሜድትራንያን መሆኑ ቀርቶ ለዘላለሙ ወደ ቀይ ባህር የተቀለበሰ ያህል ነበር ስሜቱ። ወዲያው ማስፈራርያዎች፣ ዛቻዎችና የጦርነት ጉሰማዎች ከግብጽ ምድር ማስተጋባት ጀመሩ። የዓለም ሚድያዎችና ታላላቅ መድረኮች ጉዳዩን እያነሱ ይወያዩበት ጀመር። ይህ ሁሉ የሆነው የአባይ ፈለግ አንድና ሁለት ኪሎ ሜትሮች ዘወር ብሎ እንዲፈስ በመደረጉ ብቻ ነበር። ለምሳሌ ቃሉ divert መሆኑ ቀርቶ detour የሚል ቢሆን ኖሮ የግብጽ መሪዎች ሆን ብለው ይህ ሁሉ አቧራና ጭስ ለማስነሳት ሰበብ ያጡ ነበር። የሚድያና የዲፕሎማሲ ቋንቋዎቻችን ጥንቃቄም ጥበብም ይጎድላቸዋል።
ለምሳሌ አንድ ኢትዮጵያዊ ምሁር “ግድብ የሚለውን ቀርቶ የውሃ ባንክ” ቢባል የታች ግርጌ ህዝቦች ውሃው በፈለጉት ጊዜ እንደ ጥሬ ገንዘብ deposit, save and withdraw እሚያደርጉት፣ ውሃውን ከአላስፈላጊ ትነትና በሃሩራማ ወቅት የበረሃ ጉዞ ለመታደግ የባንክ ማቆያ መኖሩን ለመቀበል የተሻለ የስነ ልቦና ዝግጁነት ሊገነቡ ይችላሉ ሲል ይመክራል። እንደውም ለዉሃ ባንክ አገልግሎቱ ክፍያ እሰከመክፈል እንዲያስቡ ሊደረጉ ይችላሉ። ይህ ለምሳሌ ያህል አንድ ተቆርቋሪ ያቀረቡት ሃሳብ ነው። እዚህ ላይ የተፈለገው ቁምነገር በጥሩ ቋንቋና ዲፕሎማሲ ፖሊሲዎቻችንና ጥቅሞቻችንን ምን ያህል ማገዝና ማስከበር እንደሚቻል ማሳየት ነው።


በአጠቃላይ ይህንን እጅግ ውስብስብ የድርድር መድረክ በአሸናፊነት ለማለፍ በሚያደርጉት ጥረት የኢትዮጵያን የዘመናት ጥያቄ የሆነውንና በግድቡ በኩል ሙሉ በሙሉ መረጋገጥ ያለበትን ጂኦፖለቲካዊ ጥቅም ፈጽሞ ባለማስነካት፣ የግብጽን እውነተኛ ቁልፍ ስጋቶች በማቃለል፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ቢቀንሱ ማካካሻ በመሻት፣ ለግድቡም ለሁላችንም ደህንነት ጥንቃቄ መደረግ ስለሚገባቸው ዝግጅቶች ደግሞ በጥናትና ማስረጃ ላይ በተመሰረቱ መግባባቶች እንዲከናወኑ በማስቻል፣ ቋንቋቸን ዓላማ ያለውና የተገራ እንዲሆን በማድረግ፣ ሁሌም ቀልባችን ከኢትዮጵያ ጥቅሞችን ሳንነቅልና የግርጌ አገሮቹን ሳንጎዳ፣ ኢትዮጵያ የተሟላ ድል ተጎናጽፋ እንድትወጣ ማድረግ እንችላለን። ዲፕሎማሲውም ለዚህ አገልግሎት መዋል አለበት። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለኢትዮጵያ ትልቁ የልማት ህዳሴ ማብሰርያ፣ የዲፕሎማሲና ጂኦፖለቲካዊ ጉልበት መጎናጸፍያ፣ የሰላምና የትሥሥር ጉርብትና ማጠናከርያ፣ ዋጋውም ከግምት በላይ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
160 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 229 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us