የሲቪል ሰርቪሱና የፖለቲካው መስመር መደበላለቅ፤ የአዲስአበባ ጤና ቢሮን እንደማሳያ

Wednesday, 27 December 2017 12:23

 

(እሱባለው ተ.)

ተደጋግሞ እንደሚነገረው የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሙስናና ብልሹ አሠራር ዋንኛ ምንጩ የሲቪል ሰርቪሱ ዘርፍ ነው። የልማታዊ መንግሥትን ዓላማዎችና ፖሊሲዎች በብቃት መፈጸም የሚችል ተአማኒነት ያለው፣ በግልጽነትና በተጠያቂነት መርሆዎች ላይ ተመስርቶ አገርን ሕዝብንና ዜጋን የሚያገለግል ጠንካራና ውጤታማ ሲቪል ሰርቪስ መፍጠር እንደመልካም አስተዳደር ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ብቸኛ መንገድ ነው።

ሲቪል ሰርቪሱ አገራዊ የለውጥ አፈጻጸምን በየጊዜው በመገምገም በመሠረታዊ አሠራር ሂደት ጥናት (BPR) አፈጻጸም ላይ ይታይ የነበረውን ብዥታ በማስተካከል ከልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ባህርይ አንጻር እንዲሁም ውጤታማነትና ቅልጥፍናን በማጣጣም የማጠናከርና የማስፋፋት ሥራ እየተከናወነም እንደሚገኝ ይታወቃል።

መንግሥት በመጀመሪያውና በሁለተኛው የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት በሲቪል ሰርቪስ ዘርፍ አቅም የማጎልበትና መልካም አስተዳደርን የማስፈን ሥራዎችን ለማከናወን አቅዶ  ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በዚህም ሰፊ ዕቅድ መሠረት በአመለካከት፣ በዕውቀትና በክህሎት የመንግሥት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በብቃት መፈጸም የሚችልና አገልጋይ የሆነ ሲቪል ሰርቫንት (የመንግሥት ሠራተኛ) የመፍጠር ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

ይሁን እንጂ ይህ የሲቪል ሰርቪሱ ግዙፍ ዕቅድና ፍላጎት እንዳይሳካ ማነቆ ከሆኑና ለውጤታማነት መጓደል፣ ለአገልግሎት አሰጣጥ በሚፈለገው ደረጃ መዘመን አለመቻል ከሚጠቀሱ እጅግ በርካታ ምክንያቶች መካከል የሲቪል ሰርቪሱ እና የፖለቲካ መስመር መደበላለቅ እንደሁም ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ያላቸው ግለሰቦች በአመራር ደረጃዎች ጭምር የመቀመጣቸው ጉዳይ ይጠቀሳል።

ዘርዘር አድርገን እንመልከታቸው።

የሲቪል ሰርቪሱ እና የፖለቲካ መስመሩ መደበላለቅ፣

የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት በተለመደው አጠራር የመንግሥት መ/ቤቶች የመንግሥትን አዋጅና ፖሊሲዎች አርቃቂና አስፈጻሚ አካላት ናቸው። በሶስቱ የመንግሥት መዋቅሮች ማለትም ሕግ አውጪው፣ ሕግ ተርጓሚው እና ሕግ አስፈጻሚው ውስጥ የሲቪል ሰርቪሱ አካላት ሚና ቁልፍና የማይተካ ሚና ነው። በሙያቸው የሕግ ረቂቅ ያዘጋጃሉ፣ እንዲጸድቅ ያቀርባሉ፣ የሕዝብ የውይይት መድረክ ያመቻቻሉ፣ ሕጎች ከጸደቁ በኋላ በሥራ እንዲተረጎም በማድረግ ረገድ የጎላ ሚና አላቸው። በአጠቃላይ ሲቪል ሰርቪሱ የመንግሥት የመተንፈሻ  ሳንባ በመሆን የሚያገለግል ነው። ሲቪል ሰርቪሱ ሁሉን ወገን በእኩል የማገልገል ዓላማ ያለው በመሆኑ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ እንዲሆን ይፈለጋል።

በሌላ በኩል የገዥው ፓርቲ የፖለቲካ መዋቅር አለ። ገዥው ፓርቲ ፕሮግራሙን ለማስፈጸም ሲቪል ሰርቪሱን ይፈልገዋል። እናም የሲቪል ሰርቪሱ ሥራ ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ ሳይገባ ጎን ለጎን ፕሮግራምና ዓላማውን ለማስፈጸም የመሥራቱ ጉዳይ በየትም ሀገር ያለና ተለመደ ነው።

ነገርግን እጅግ ያልተለመደውና የዕለት ተዕለት የሲቪል ሰርቪሱ ሥራውን በነጻነት እንዳያከናውን እንቅፋት ከሚሆኑት ጉዳዮች አንዱ በተቋማት የሥራ አመራር ሥራ ውስጥ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ጣልቃ የመግባቱ ጉዳይ በዋንኛነት የሚጠቀስ ነው። በሲቪል ሰርቪሱ ጣልቃ የሚገቡ አካላት ገዥውን ፓርቲ ኢህአዴግ ለመጥቀም በማስመሰል ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ ከምንም በላይ ነገሩን የከፋና አደገኛ ያደርገዋል። ምክንያቱም በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ የኢህአዴግ አባላት የሆኑ እና ያልሆኑ ወገኖች አሉ። ፖለቲካ ጨርሶ መስማት የማይፈልጉ ገለልተኛ ባለሙያዎችም አሉ። የፖለቲካው ጣልቃ ገብነት ያውም በኢህአዴግ ስም ታጅቦ ሲቀርብ በተለይ አባል ያልሆነውን ሀይል ራሱን ከብዙ ነገር እንዲያገል አንድ ምክንያት ይሆናል። የአገልጋይነት መንፈስን ያበላሻል።

ከዚህ ጹሑፍ ጋር እንደአንድ አብነት ታስቦ የተያያዘው ደብዳቤ ብዙ የሚነግረን ነገር አለ። ተቋሙ የአዲስአበባ ጤና ቢሮ ነው። የጤና ቢሮው የኢህአዴግ ህዋስ ስለአንድ የመ/ቤቱ ባልደረባ ለቢሮው ሀላፊ ሪፖርት አድርገዋል። (ሪፖርቱ ትክክል ነው ወይንስ አይደለም የሚለው የዚህ ጹሑፍ ጸሐፊ ትኩረት አይደለም።) ደብዳቤው የተፈረመው በቢሮው የኢህአዴግ ህዋስ ሰብሳቢ ሲሆን ማህተሙ ግን የመንግሥት ተቋም የሆነው የጤና ቢሮ የሪከርድና ማህደር አገልግሎት ነው። የቢሮው ምክትል ሀላፊ የግንባሩን ደብዳቤ ተቀብለው ጉዳዩ በዲሲፕሊን ኮምቴ እንዲታይ መርተውታል። (የደብዳቤው ቅጂ ተያይዟል) እንግዲህ በፖለቲካ መስመሩ በተጀመረ ግምገማ አንድ የመንግስት ሠራተኛ በሲቪል ሰርቪሱ ሕግ መሠረት በዲስፕሊን ጉዳዩ ሊታይ ተፈርዶበታል ማለት ነው። ይህ የሲቪል ሰርቪሱና የፖለቲካው መደበላለቅ ትንሽዬ ማሳያ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ክስተት አንዳንድ ሀይሎች ከፓርቲው ፍላጎት ውጭ የያዙትን ሥልጣን እስከምን ድረስ ለጥጠው ለመጠቀም እንደሚሞክሩ ተጨማሪ ማሳያ ነው።

ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ባለቤቶች በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የመሰግሰግ ጉዳይ፣

ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በማቅረብ ሥራ መቀጠር፣ ዕድገትና ሹመት ማግኘት እንዲሁም ልዩ ልዩ የውጭ ሀገር ከፍተኛ የትምህርት ዕድሎችና ሥልጠናዎችን ማግኘትና የመሳሰሉት በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የተንሰራፋ ከፍተኛ ችግር ሆኗል። በአማራ፣ በኦሮሚያ በቅርብ ደግሞ በአዲስአበባ በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በግል ማህደራቸው ያያያዙ ግለሰቦችና አመራሮች ራሳቸው እንዲያጋልጡ በተሰጠው ቀነ ገደብ ምንም እንኳን ቁጥሩ ከሚገመተው አንጻር ጥቂት ቢሆንም የችግሩን ስፋት ሊጠቁም የሚችል ቁጥር የያዘ ሕገወጥ ሀይል ተገኝቷል። ራሱን ደብቆ ያደፈጠው ሀይልም ወደፊት በግል ማህደር ማጣራትና በጥቆማ ተይዞ ተገቢውን ቅጣት ማግኘቱ የማይቀር ሆኗል።

ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ያላቸው ግለሰቦች እንዲህ በዝቶ መታየት በአንድ በኩል የሲቪል ሰርቪሱ ደካማነት አንድ መገለጫ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ የተሰገሰጉ ኪራይ ሰብሳቢ ሀይሎች ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ብዙ ርቀት ሊጓዙ እንደሚችሉ ጠቋሚ ነው። ከምንም በላይ ተምሮ፣ ለፍቶ ሥራ በማጣት የቤተሰብ ሸክም ለመሆን የተገደደ ወጣት በበዛበት ሀገር ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ያላቸው ሰዎች በወሳኝ ቦታዎች ጭምር መቀመጥ የትምህርትን ዋጋ የሚያሳጣ አደገኛ ውጤት ያለው ነው። በተጨማሪም ሐሰተኛ ማስረጃ ባለቤት የሆኑ ግለሰቦች በራስ የመተማመን አቅም የጎደላቸው ናቸው። በዚህ ምክንያት በአቅማቸው ሊሰሩና ለፈጽሙ የሚችሏቸውን ጉዳዮችን እንኳን ባለመፈጸምና በሙስናና በብልሹ አሠራር ጭምር በመዘፈቅ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ሕዝብንና መንግሥትን የማራራቅ ተግባራትን ይፈጽማሉ። ብዙዎቹ ሕገወጦች በበታችነት ስሜት የተጎዱ በመሆናቸው (በተለይ በአመራር ቦታ የተቀመጡት) ሰፊውን ሠራተኛውን በማዋከብ፣ ከሥራ በማፈናቀል፣ በትንሽ በትልቁ በመወንጀልና በማሸማቀቅ ለሕገወጥ አድራጎታቸው መደበቂያ ጫካ ሲያመቻቹ የሚውሉ ናቸው።

የሲቪል ሰርቪሱ እና የፖለቲካ መስመሩ መደበላለቅ ምንም እንኳን ኢህአዴግ እንደመርህ የሚቀበለው አለመሆኑን ደጋግሞ የገለጸና አቋሙን ያሳወቀ ቢሆንም ችግሩ ሲንሰራፋ አይቶ እንዳላየ መሆኑ ወይንም ቁርጠኛ አመራር አለመስጠቱ እንዲሁም ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ያላቸው ግለሰቦችና አመራሮች ቁጥር መንሰራፋት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ የአገልጋይነት መንፈስ ተንኮታኩቶ እንዲወድቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው በአሳዛኝነቱ ዛሬም የሚነሳ ነው። እናም ኢህአዴግ የተጠቀሱትን ችግሮች በመቅረፍ ረገድ አሁንም ከፍተኛ የቤት ሥራ ይጠብቀዋል። እጅግ የረፈደ ቢሆንም እንኳን መዘግየት ከመቅረት ይሻላልና፤ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ከሕዝብ ጋር እጅና ጓንት በመሆን፣ በስሙ እየማሉ በሕገወጥ መንገድ ለመበልጸግ የሚጥሩ ግለሰቦችን ከየተቋማቱ ለቅሞ ለሕግ ለማቅረብ ሊተጋ ይገባል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
92 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 135 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us