የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣ አዋጅ (ረቂቅ)

Wednesday, 27 December 2017 12:40

 

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 49(5) የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም እንደሚጠበቅለት የደነገገ በመሆኑ፤

የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም በሕግ መወሰን እንዳለበት ሕገ-መንግሥቱ ስለሚደነግግና ለዚህም ሕግ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 55(1) መሠረት የሚከተለው ታውጇል።

 

ክፍል አንድ

ጠቅላላ

1.  አጭር ርዕስ

ይህ አዋጅ “የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም መወሰኛ አዋጅ ቁጥር     /2009” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል።

2.  ትርጓሜ

በዚህ አዋጅ ውስጥ፤

1)  “ሕገ-መንግሥት” ማለት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት ነው፤

2)  “አስተዳደር” ማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው፤

3)  “ክልል” ማለት የኦሮሚያ ክልል ነው፤

4)  “ልዩ ጥቅም” ማለት በሕገ መንግሥቱ እውቅና ያገኙ የአገልግሎት አቅርቦት፤ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉት፣ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ናቸው፤

5)  “የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች” ማለት በአዲስ አበባ ከተማ እና ዙሪያው ነዋሪ የሆኑ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን በሙሉ ያካትታል፤

6)  “የአዲስ አበባ ከተማ ወሰን” ማለት የከተማው አስተዳደር ከኦሮሚያ ክልል ጋር በሚያደርገው ስምምነት ተወስኖ ምልክት የተደረገበት ወሰን ነው፤

7)  “የአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ” ማለት ፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ነው፤

8)  “ሰው” ማለት ማንኛውም የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው።

 

3.  የተፈጻሚነት ወሰን

ይህ አዋጅ በአዲስ አበባ ከተማ ወሰን ውስጥ እና እንደአግባቡ በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ተፈጻሚነት ይኖረዋል።

 

ክፍል ሁለት

ክልሉ በከተማው አስተዳደር ስለሚኖረው የማኅበራዊ

አገልግሎቶች አቅርቦት ልዩ ጥቅም

4.  የትምህርት አገልግሎት

በአስተዳደሩ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች በአፋን ኦሮሞ የሚማሩበት ትምህርት ተቋማት በከተማ አስተዳደሩ ወጪ እንዲደራጁ ይደረጋል።

5.  የጤና አገልግሎት

በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ባሉ ከተሞችና ገጠሮች የሚኖሩ ነዋሪዎች በከተማው ውስጥ በሚገኙ የመንግሥት ሆስፒታሎች እና ጤና ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን እንደማንኛውም የከተማዋ ነዋሪ እንዲያገኙ ይደረጋል።

6.  ባሕል፣ ቋንቋና ሥነጥበብ አገልግሎቶች

1)  በዚህ አዋጅ የተመለከቱትን ልዩ ጥቅም አገልግሎቶችን ለኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ለማቅረብ እንዲቻል አፋን ኦሮሞ በከተማ አስተዳደሩ የሥራ ቋንቋ ሆኖ ያገለግላል።

2)  የኦሮሞ ሕዝብ ማንነት የሚያንፀባርቅ አሻራ በከተማው ውስጥ በቋሚነት እንዲኖር ከክልሉ ሕዝብ ጋር በተያያዙ ታሪካዊ ክስተቶች ስም መታሰቢያዎች እንዲኖሩ አመቺ የሆኑ እንደ አደባባዮች፣ ጎዳናዎች፣ ሠፈሮች እና የመሳሰሉት ቦታዎች እንደአስፈላጊነቱ በቀድሞ የኦሮሞ ስማቸው እንዲጠሩ ይደረጋል።

3)  በከተማው አስተዳደር የኦሮሞ ሕዝብ ባህልና ታሪክ የሚያንጸባርቁ ቴአትር ቤቶች፣ የመዝናኛ፣ የባሕል እና የኪነጥበብ ማዕከሎች በሚገነቡበትንና የሚተዋወቁበት ሁኔታዎች እንዲመቻቹ ይደረጋል።

4)  በከተማው አስተዳደር ውስጥ በሚገኙ ሙዚየሞች ውስጥ የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ፣ ባሕልና ወግ የሚያንጸባርቁ ቅርሶችና መጽሐፎች እንዲሟሉና እንዲኖሩ አስተዳደሩ ከክልሉ ጋር በመመካከር ይሰራል።

5)  በከተማዋ የመንግሥት የሚሰራጩ የመገናኛ ብዙሃን በአፋን ኦሮሞ ጭምር የሚጠቀሙበት ሁኔታ ይኖራል።

6)  ከኦሮሚያ ክልል ጋር በተያያዘ ከተማው የተቆረቆረበት በአፋን ኦሮሞ የቀድሞ ስሙ ፊንፊኔ አዲስ አበባ ከሚለው የከተማው መጠሪያ ጋር በሕግ ፊት እኩል እውቅና ይኖረዋል፤ የስሞቹን አጠቃቀም በተመለከተ በደንብ ይወሰናል።

 

ክፍል ሦስት

ክልሉ በከተማው አስተዳደር ስለሚኖረው ኢኮኖሚያዊ

አገልግሎቶች ልዩ ጥቅም

7.  መሬት አቅርቦት

ክልሉ ለተለያዩ መንግሥታዊ ሥራዎች እና ሕዝባዊ አገልግሎቶች የሚውሉ ሕንፃዎች የሚሠሩበትን መሬት ከሊዝ ነጻ እንዲያገኝ ይደረጋል።

8.  የውሃ አቅርቦት

የከተማው አስተዳደር ከክልሉ ከርሰ ምድርና ገጸ ምድር የሚያገኘው የመጠጥ ውሃ ምንጭ ጉድጓድ የሚቆፈርበት፣ ግድቡ የሚለማበት፣ ወይም የውሃ መስመሩ አቋርጦ የሚያልፍባቸው የክልሉ ከተሞች እና ቀበሌዎች በአስተዳደሩ ወጪ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል።

9.  የትራንስፖርት አገልግሎት

የከተማ አውቶቡስና ታክሲዎች ትራንስፖርት ስምሪት እንዲሁም የባቡር መሠረተ ልማት ዝርጋታና አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ያሉትን የክልሉ ከተሞች ያማከለ እንዲሆን ይደረጋል።

10.     የሥራ ዕድል

1)  በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በሚገኙ የክልሉ ከተሞችና ገጠሮች ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ወጣቶች በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባለው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል።

2)  በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የክልሉ ከተሞችና ገጠሮች ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ወጣቶች ከውሃ ልማት፣ ከደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ፣ ከቆሻሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት፣ ከተፋሰስ ልማት፣ ከትራንስፖርት አገልግሎት እና ከመሳሰሉት ጋር ተያይዞ የሚመነጭ ሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል።  

11.     የገበያ ቦታ አቅርቦት

$)  የክልሉ አርሶ አደሮች በተደራጀ መልኩ ምርቶቻቸውን የሚሸጡበት የገበያ ቦታ ይደራጅላቸዋል።

2)  የከተማ አስተዳደሩ በራሱ ወጪ የገበያ ቦታውን ገንብቶ ለግብይት ሥራ ምቹ እንዲሆን ያደርጋል።

12.     የኮንዶሚኒየም ቤት ተጠቃሚነት

በመንግሥት ወጪ ከሚገነቡ የኮንዶሚኒየም ቤቶች በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ሠራተኞችና ኃላፊዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ኮታ ተሰጥቷቸው በዕጣ ውስጥ እንዲካተቱ ይደረጋል።

13.     ካሣ የማግኘት እና በዘላቂነት የመቋቋም

1)  በአስተዳደሩ ውስጥ በልማት ምክንያት የሚፈናቀሉ አርሶ አደሮች ዘላቂ መቋቋሚያ የሚሆን ካሣ የማግኘት መብት ይኖራቸዋል።

2)  በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ከዚህ በፊት በልማት ምክንያት የተፈናቀሉ እና በቂ ካሣ ያላገኙ አርሶ አደሮች በጥናት ላይ የተመሠረተ የማቋቋሚያ ሥራ እንዲስራላቸው ይደረጋል።

3)  በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጾች (1) እና (2) የተመለከቱትን ጉዳዮች የሚመራ ራሱን የቻለ ጽሕፈት ቤት እንዲቋቋም ይደረጋል።

 

ክፍል አራት

ክልሉ በከተማው አስተዳደር ስለሚኖረው የተፈጥሮ ሀብት

አጠቃቀምና የአካባቢ ጥበቃ ልዩ ጥቅም

14.   የተፋሰስ ልማት

ለከተማው አስተዳደር የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የውሃ ምንጭ የተቆፈረበት፣ ግድብ የለማበት፣ ወይም የውሃ መስመር አቋርጦ የሚያልፍባቸው የክልሉ ከተሞች እና ቀበሌዎች በአስተዳደሩ ወጪ የተፋሰስ ልማት የሚያካሂዱበት ሁኔታ ይመቻቻል።

15.  ከአካባቢ ብክለት የመጠበቅ መብት

1)  በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ያሉ ከተሞችና ቀበሌዎች ከከተማው ከሚወጡ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎች ከሚደርሱ የአካባቢ ብክለትና ጉዳት የመጠበቅ መብት ይኖራቸዋል።

2)  ከአዲስ አበባ ከተማ በሚወጡ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎች ከሚደርሱ የአካባቢ ብክለትና ጉዳት የክልሉን ከተሞችና ቀበሌዎች ለመጠበቅ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ እንዲካሄድ ይደረጋል፤ በግምገማው መሠረት አስፈላጊው የማስተካከያዎች ይደረጋሉ።

3)  በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ያሉ ከተሞችና ቀበሌዎች ደህንነቱ ሳይጠበቅና ቁጥጥር ሳይደረግበት ከተቀመጠው ደረጃ በላይ ወደ ክልሉ በተጣሉ ወይም በፈሰሱ ቆሻሻዎች ምክንያት በሰው፣ በእንስሳትና በተፈጥሮ አካባቢ ላይ ለደረሰው ጉዳት በሕግ አግባብ ከአስተዳደሩ ካሳ የማግኘት መብት ይኖራቸዋል።

4)  ለአዲስ አበባ ከተማ ልማት የሚውሉ የግንባታ ማዕድናት ማግኛ ሥፍራዎች የአየር ብክለት እንዳያስከትሉ እና ለደን ልማት ወይም ለሌሎች ልማቶች መዋል እንዲችሉ እንዲያገግሙ ይደረጋል።

5)  ለአዲስ አበባ ከተማ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ማከሚያና ማስወገጃ ቦታዎች እንዲሁም መልሶ መጠቀሚያ ስፍራዎች አስተዳደሩና ክልሉ በጋራ ባጠኗቸው ቦታዎችና ሳይንሳዊ መስፈርቶችን ባሟሉ ሁኔታዎች እንዲተዳደሩ ይደረጋል።

 

ክፍል አምስት

ስለጋራ ምክር ቤት

  

16.  የጋራ ምክር ቤት መቋቋም

1)  በዚህ አዋጅ ውስጥ የተጠቀሱትንና ሌሎች የጋራ ጉዳዮችን ክልሉ እና አስተዳደሩ የሚወያዩበትና የሚወስኑበት የጋራ ምክር ቤት (ከዚህ በኋላ “ምክር ቤት” ተብሎ የሚጠራ) በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል።

2)  የምክር ቤቱ ተጠሪነት ለፌዴራል መንግሥት ይሆናል።

17.  የምክር ቤቱ ዋና መሥሪያ ቤት

 የምክር ቤቱ ዋና መሥሪያ ቤት አዲስ አበባ ነው።

18.  የምክር ቤቱ ዓላማ

የምክር ቤቱ ዓላማ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 49(5) መሠረት የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያተሳሰሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በዚህ አዋጅ የተዘረዘሩት ልዩ ጥቅሞች በተጨባጭ ተግባራዊ እንዲሆን መከታተል፣ መገምገምና ለአፈጻጸሙ ቅልጥፍና ድጋፍ ማድረግ ይሆናል።

19.  የምክር ቤቱ አባላት

የምክር ቤቱ አባላት ከአስተዳደሩ ምክር ቤትና ከክልሉ ምክር ቤት በእኩል ቁጥር የሚወክሉ ይሆናል።

20. የምክር ቤቱ ተግባርና ኃላፊነት

የምክር ቤቱ አወቃቀር፣ ተግባርና ኃላፊነት፣ የሥራ ዘመን፣ የስብሰባ ሥነ-ሥርዓት፣ የአባላት ሥነ-ምግባር እና በጀት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣ ደንብ ይወሰናል።

 

ክፍል ስድስት

ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

21. የመተባበር ግዴታ

ይህን አዋጅ እና እዋጁን ተከትለው የወጡ ደንቦችንና ምክር ቤቱ የሚያወጣውን መመሪያና ውሳኔዎች ሥራ ላይ ለማዋል ማንኛውም ሰው ወይም አካል የመተባበር ግዴታ አለበት።

22. ተፈጻሚነት ስለማይኖራቸው ሕጎች

ይህን አዋጅ የሚቃረን አዋጅ ወይም ውሳኔ በዚህ አዋጅ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚነት አይኖረውም።

23. ደንብና መመሪያ የማውጣት ሥልጣን

1)  የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህንን አዋጅ በሥራ ላይ ለማዋል የሚያስፈልጉ ደንቦችን ሊያወጣ ይችላል።

2)  ምክር ቤቱ ይህንን አዋጅና በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) መሠረት የወጡ ደንቦችን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ መመሪያዎችን ሊያወጣ ይችላል።

24.     አዋጁ የሚጸናበት ጊዜ

ይህ አዋጅ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የጸና ይሆናል።

አዲስ አበባ            /2009 ዓ.ም

 

ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ

ሪፐብሊክ ፕሬዚደንት¾

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
142 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 489 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us