ይድረስ ለዋለልኝ መኮንን መቃብር ዓለም!

Wednesday, 27 December 2017 12:35

 

በአንድነት ቶኩማ

“ለክቡር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገ/የሱስ መጽሓፍ የተሰጠ ምላሽ መቃብር ዓለም” የምትለዋን ደብዳቤህን ካነበብኳት ሰነበትኩ። የነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝን በአፈወርቅ ገ/የሱስ ላይ ያቀረብኩትን ትችት ጠቅሰህ የደመደምከውን ደብዳቤ አንተ እንዳልከው ጠቅሼ “ሀሳብዎ ስላስኮረፈኝ ደግሞ መጽሓፍዎን ማየት ቀርቶ ጭራሽ ለማየት ትዝ እንዲለኝ አልፍልግም ነበር” እንዳልከው ስምህ ተደጋግሞ የሚነሳ የለውጥ ሰው ብትባልም ደብዳቤህን ሆነ የፅሁፍ ሰራህን ለመንበብ ቀርቶ ለማየት አልሻም ነበር። አሁን ግን ሃሳቤን ቀየርኩ። በዚህም ልጸፍልህ ወሰንኩ።

ሳላስተውል ሳይሆን አይቀርም። “የሚታይ ነገር ስላላገኘሁ እንደገና እንዳያት ተገደድሁ” እንዳልከው ሆነብኝ። ያኔ የእሳቸው ነገር ወይም መጽሓፍ ገለባ ነው ብለህ የተውከው በአእምሮ ህጻን ስለነበርክ መሰለኝ። በኋላ ላይ የሚጠቅም ነገር አገኘሁ ማለትህ ብስለት መጀመርህ ነበር። እኔም እንዳንተው ሁኜ ነው። የአንተ ደብዳቤ ጥቅም የለውም ስል ነበር። ልጅነት ነው። ዋለልኝ ሆይ አንተም ከእውቀትህ ይልቅ ሥሜትህና ልጅነትህ ያይል እንደነበር ደጋግሜ ደብዳቤህን ሳነበው ተገነዘብኩ።

አፈወርቅ “እስከትላንት ድረስ” ያሉትን ጠቅሰህ አፈወርቅን ስትወቅስ ገረመኝ። የወቀሳህ ምክንያት ደግሞ “ዛሬ ከሞላ ጎደል ትላንትናን እንደሚመስል አላውቁም መሰል (በአፄ ቴዎድሮስ እና በእነ አፄ ዮሐንስ ጊዜ) የኢትዮጵያ ደሀ ወታደር መጫዎቻ ነበር” አልክ። አይ ዋለልኝ ትናንት ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት ያልካት አገር እኮ ከሞላ ጎደል ብሶባታል። ጥርነፋው ተጠናክሮ ቀጥሏል። የአምባገነኖች መፈንጪያ ሆናለች ብንልህ የምታምን አይመስለኝም። ያውም የአንተን በታታኝ ፍልስፍና ተግተው አድገው። በዚህ አልወቅስህም ስል ኖሬያለሁ። አሁን ግን ሃሳቤን ለውጬ ልወቅስህ ወሰንኩ።

“ባርያ በገዛ ራሱ ማዘዝ እንደማይችል የኢትዮጵያ ደሀ በገዛ ራሱ ማዘዝ እንደማይችል የኢትዮጵያ ደሀ በገዛ ራሱ ጉዳይ ማዘዝ አይሆንለትም ነበር። የሚያዝዙበት ቀርፋፋ ጋሻ ያነገበና አንድ ባለኔ ጦር የያዘ፣ አንድ የመሸበት ደበናንሳ የጀራረገውና ተሰገባው በሥፍራው ተጣልቶ ፀሐይ የሚሞቅ ጎራዴ መሳይ በወገቡ ያገነበጠ ቅማላም ወታደር ነበር። ደሃው ወታደር ግን እሱን ደስ ላይለው የሌላውን ደስታ ሊከላከል ለገዛ ራሱ ሳያልፍት የድሀውን ንብረት ሲያፈርስ ይኖር ነበር” የሚለውን ጠቅሰህ አፈወርቅ በትናንትና እና በዛሬ መካከል ልዩነት አለመኖሩን ቢኖርም ትንሽ መሆኑን ቢረዱ ምነኛ በተገረሙ።” ብለሃል። ወይ ሞኙ ዋለልኝ! ዛሬስ ቢሆን ጓደኞችህ እና የጓደኞችህ ተከታዮች ምን እያደረጉ ይመስለሃል። ይህ ግፍ ዛሬ መኖሩን ብንነግርህ ምንኛ ትገረም። መቼም ከሞትክበት ተነስተህ ሞታችንን ልትታዘብ አትመጣም እንጂ ብትመጣም ምን ትል ይሆን?

 ዋለልኝ ዝቅ ብለህ ‹‹ ዛሬም ያው ወታደር ሥርዓት መሃላውን ሲፈጽም  እንኳን ንጉሠ ነገሥቱን፣ አገሩን፣ ድንጋዩን፣ ተራራውንና ሸለቆውን ሊጠብቅ እንጂ ሕዝቡን ሊጠብቅ ቃል አልገባም።›› አልክ። ቀጥለህም ‹‹ቃል ስላልገባም አይጠብቅም።›› ብለሃል። ምን ያስገርማል ታዲያ ዋለልኝ። ሞኝ ነህ ለካ!!!

‹‹ወታደር እንደላሚቱ እረኛውን እንጂ ህዝቡን (ጌታውን) አሁንም አላወቀ።›› ብለሃል።  ልክ ነህ። የኛውን ዘመን መች አየኸው። ካድሬውን እንጂ ህዝቡን (ጌታውን) የማያውቅ ወታደር በዚች አገር ፈልቷል እኮ! ጨለማ ገዝፏል ወይም ሰፍቷል።

ዋለልኝ የአንተ ዘመን ምነኛ ጥሩ ነበር። የወታደሩን ግፍ ስትናገር ገረመኝ። ‹‹ወታደር (ፖሊስ) ዛሬም ያስራል፣ይፈርዳል፣ ቤት ይበረብራል፣ ይመዘብራል።›› ብለሃል። ምነዋ ዋለልኝ!!! ሳትሞት ስለጻፍከው  መሆን አለበት። ‹‹ይገላል›› የሚለውን አጥብቀህ ያልጨመርከው። በርግጥ ሞትም ባንተው ጊዜም ነበር። ይሄውልህ ዛሬማ ከአንተ ሞት ጀምሮ ወታደር ሊጠብቅ ቃል የገባውን ህዝብ ህጻናትን፣ ሽማግሌ፣ አሮጊት ሳይል አስቦ፣ አጥንቶ፣ በትኩረት ይገላል። ሞት በረከተ ወይም ረከስ ነው የምልህ። ደግሞ  ስም ጠቅሰህ የሐይሉ ገብረ ዮሐንስ መታሰርን እንደ የግፍ ግፍ አድርገህ ወስደኸዋል። እንዲህ ስትል ‹‹ያለፈው ዓመት ሰላማዊ ሠልፍና የዘንድሮውን በሰው ልጅ ሥራ ብዕሩ ቢያለቅስ መርዝ ተፋ (ብዕሩ) ተብሎ የታሰረው የሐይሉ ገብረ የሐንስ ታሪክ ምስክር ነው›› አልክ። አሁን እኛ ባለንበት ዘመን እንኳን ብዕር መርዝ ተፍቶ ወይም አልቅሶ ቀርቶ አሳቢያንን የሚጠረንፍ ህግ ወጥቷል። በል ተወው ቅንጡ ነበርክ መሰለኝ።

ዋለልኝ  ስለ ዓለም ታሪክ የዘረዘርከውን ትተን ‹‹ ወደ አገር ቤት ጎራ ያልንማ እንደሆነ በእነ አጼ ቴዎድሮስና በእነ አጼ ዮሐንስ ጊዜ ከጅብ አምልጦ የቀረ ቆርበት የመሰለ  ጨርማዳ ጋሻ በብብቱ ያጠበቀና ባለቆዳ ወይም ሲሶ እንጨት ብረትመሳይ በጫንቃው አጋድሞ ዝቅ ያለ እንደሆነ፣ አንድ እከካም ነፍጠኛ ብቻውን ላይ  ያድር ከሆነ አንድ መንደር ሲያስር ሲፈታ ሲያስጨንቅ ነበር።›› ያሉት እውነት ከእውነትም በላይ ቢሆን ያንን ሆኖ እናገኘዋለን።›› ያልከው እውነት ነበር። የኛውስ ዘመን ምነኛ የከፋ እንደሆነ ደብዳቤ ስጽፍልህ ሳይገርምህ አይቀርም። እንዲያውም ጓደኞችህን ሳታገኛቸው አትቀርምና ሲፈጽሙት የኖሩትን እውነቱን ይነግሩሃል።

ፖሊስ  እንደ ሽፍታ  የሚፈራበት ዘመን ነው ያልከው በእኛ ዘመንም ቢሆንም ምንም አልተቀየረ። ለአፈወርቅ በጻፍከው ደብዳቤ ላይ ‹‹ፖሊስ  እንደ ሽፍታ የሚፈራበት፣ የሚሸኝበት መንገድ ሲሄድ ስንቅ የሚሰነቅለት፣ የሚያስገብርብት ቦታ መኖሩን የማያውቅ ምነኛ ደንቁሯል።›› ብለሃል። እኛስ ስንቅ ድግስ እና ሽኝት አይጠበቅብንም። አንተዋወቅም። ለግዳጅ ሲመጡ ስናያቸው ልዩ ፍጡሮች ይመስሉናል። ሳንለምዳቸው እና ሳይለምዱን እንኖራለን። የየት ሃገር ሰዎች እንደሆነ በቅጡ አይታወቁም።

በመቀጠል “ከእርስዎ እጅግ የቀደመው ፕላቶ የተባለው ፈላስፋ ይኽንኑ ታዝቦ ወታደሮች እንዲህ ሊሆኑበት የቻሉበትን ምክንያት ሲያስረዳ ወታደር ሲሰለጥን እንደ ውሻ መሆን አለበት፣ የቤቱን ሰው የማይነካ የውጭውን ዘራፊና ሌባ የሚጠብቅ፣ ጌታውን የሚያውቅ አገልጋይ መሆን አለበት።” አለ ብለሃል። ፕላቶ ተናገረው እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን ካወቀ ዘመን የለውም። ብዙ ጊዜ ሲነከስ ኖራልና። “ሕዝቡ (ጌታውን) አሳዳሪን የሚገርፋ ወታደርም ሥራውን አላወቀም ማለት ነው።” ብሏል ብለሃል።እንግዲህ ይህ ሁሉ ወታደር  አብዷል ማለት ነዋ!!! “ወታደር ይሰለጥን ዘንድ ትምህርት ጅምናስቲክ (ሰውነቱ እንዲጠነክር)፣ ሙዚቃ (ልቡ እንዲለሰልስ) ያስፈልገዋል።” ብሏል አልክ። የሰውነት ጥንካሬውን ተወውና የልብ መለሳለሱ ላይ እንወያይ። ሙዚቃውም ይቅርና የህዝቡን መከራ፣ የሰቆቃ ጩኸት እና ለቅሶ ሰምቶ ልቡ ያልሰለሰ በዘፈን ይለሰልሳል? እንዴት በዳንኪራና በሙዚቃ ልቡ ይለሰልሳል ብለህ ታስባለህ። የወጎኖቹን ጣር አይቶ ያለሰለሰ ልብ እንዴት በሙዚቃ ይለሰልሳል። ሞኝ ነህ ለካ!!! ብቻ የፕሎቶን አገር ሰዎች ባህሪ አላውቅምና እነሱ ይለሰልሱ ይሆናል። የኛን ተወው አለስላሽ ሙዚቃስ አለ ብለሃል?

በእርግጥ የእኛን ታሪክ በጥሩ ሁኔታ ገልጸኸዋል። ‹‹ የኛው ትምህርት ግን ተከተል አለቃህን ነው። ገደል ሲገባ ብታይ ‹ገደል ግባ› ነው ብለሃል።›› እውነት ነው። አሁን አለቃህን መከተል እንዳለ ሆኖ ጎሳህን፣ ጎጥህን፣ መንደርህን መከተል አለብህ የሚል ተጨምሮበታል።

“አፈወርቅ! በርስዎ ጊዜው ብዙ የተለወጠ ይመስለዎታል። ለኔ በመጠን ይለያይ እጂ በዓይነቱ የተለወጠ አይመስለኝም።” ብለሃል። እኔ እንኳን ብሶበታል ነው የምለው። ምን አይነት ውጥንቅጥ ውስጥ እንደለን ብንነግርህ ልታምን አትችልም። አሁን እንኳን ይህን ደብዳቤ እየጻፍኩ እንኳን ሶማሌ ወጎኖችህና ኦሮሞ ወገኖችህ ከባድ ችግር ላይ ወድቀዋል። በጎሳ ተደራጅቶ ሰው እየተዘናጠለ ለመሄድ ዛግጅት ላይ ይመስላል። አንተ እስር ቤት ያልከውን አምነው የሸፈቱ ጎጠኞች ተፈታችኋል የተባሉ ሆነውም ሊበታተኑ ነው።

“ስለ መጽሐፍዎ ጠቅላላ አስተያየት መስጠት ቢያስፈልግ በጊዜው የነበሩት ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ያሉትን ጠቅሶ ማለፍ ይበቃል” ብለህ በአንድ ምንባብ ትልቁን መጽሐፍ እንድጠቀለልከው እኔም የአንተን አጠቃላይ የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት መሆን ያስረዳከውን ፍልስፍና “እንኳን ደስ ያለህ ተበጣብጠን ልንጠፋ ነው።” በማለት ልናገር።

ዋለልኝ “የብሔረሰብን ጥያቄ በኢትዮጵያ የምትለውን ህዳር 17፣ 1969 እኤአ የተፃፈቸውን ምልክታህን አይቻለሁ። ደጋግሜ ነበር የተመለከትኳት። ለተማሪዎች እንቅስቃሴ እንደ መሰረት ተደርጋ ስትወሰድ ከርማለች። ከጽሁፉ እንደምረዳው የጎሰኝነትን አስተሳሰብ የሚቃወሙ ተራማጅ ኃይሎችን እግረ መንገድህን የተቸህበትም ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ዋለልኝ ሰዎች የአንተን ሃሳብ ይተቹ ዘንድ የምትፈቅድ አይመስልም። ‹‹የጽሁፌ አንባቢዎች የራሳቸውን አመለካከት በመምዘዝና በማጉላት ጽኁፌን ከመተቸት እንደሚታቀቡ ተስፋ አደርጋለሁ። ብለሃል። የአንተን አመላካት በሰው ላይ እያሰረጽክ እንዴት ቢሆን ነው የሰውን አመለካከት ልትሸሽ ያሰብከው። ለካ ያንተ ባህሪ ተጋብቶባቸው ነው ዛሬ የምናያቸው ጎጠኛ ተከታዮችህ ባሉበት ተቸንክረው የቀሩት። ሲምሉ እንኳ ይህ የሚለወጠው በመቃብራችን ላይ ነው ይላሉ። ይህ ምንድን ነው ምንችክና ነው። ይገርምሃል መገለባበጡንም ተክነውበታል። ነጭ ካፒታሊዝም እንደሚከተሉ ሰምተሃል? መቼም ይሄን ይሄን አይነግሩህም። ወደ ገዥ መደብ ያውም ጥገኛ ገዥ መደብነት!!!

ዋለልኝ ትልቅ የሚባውን ርዕሰ ጉዳይ ማነሳትህ ያስመሰግንሃል። ‹‹ እስካሁን ድረስ መፍትሄ ያልተገኘለት ወሳኝ ጉዳይ የብሔረሰቦች ጥያቄ ነው።›› ብለሃል። ዛሬም ቢሆ መልስ የተገኘለት መስሎ አልታየኝም። አንተ እንዳልከው ‹‹ አንዳንድ ሰዎች በሹፈት ጉዳዩን የጎሳ ያደርጉታል።›› ብለሃል። አሁን እኮ በተግባር የጎሳ እንጂ የብሄር ጥያቄ መጥፋቱን ተመለከትን። ጥያቄው “እኔ ብሔረሰቦች ማለትን እመርጣለሁ›› ብለሃል። ዋለልኝ ሥያሜው አያጣላም። ውጤቱ ግን ጎሰኝነት ሆኖ በተግባር ታየ። ለመበታተን የተዘጋጀ የጎሳ ጥርቅም ሆናለች ኢትዮጵያ።

ዋለልኝ በጽሁፍህ ጥሩ ጥያቄ አንስተህ መልሰህ ልታፈነግጥ ስትሞክር አየሁህ። “የኢትዮጵያ ህዝቦች የተዋቀሩት ከምንድን ነው?” ብለህ ትጥይቅና መልስ ሥትሰጥ “እኔ ከሰዎች እሚለው ቃል ላይ አሰምርበታለሁ ምክንያቱም በስነ ህዝብ አገላለጽ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ አንድ ብሄር አይደለችም።” ትላለህ። ግለሰብ ይቀድማል ማለት ነው። የሰው (የግለሰብ) ስብስብ ነው ሰዎችን የሚፈጥረው። ታዲያ ሰዎች በሰዎች ላይ ያደረጉትን ጭቆና ወደ ብሔር ደረጃ ወስደህ የብሄር ጭቆና ያልከው ከምን አምጥተህ ነው? ጎጃም፣ ወሎ፣ ጎንደር ጭቆና አልደረሰበትም ማለት አይሆንምን?

መልሰህ ሰዎች የሚለውን ብሔር ወደሚለው አውርደህ ባህል፣ አለባበስ፣ ቋንቋ፣ እና ሌሎችን መገለጫዎች ትገልጻለህ። ቀጥለህም የአማራና የከፊል ትግሬ ባህል ገነነ ብለሃል። በመሰረቱ ትክክል ሊሆን ይችላል። ዳሩ ግን አንድ የረሳኸው ነገር የጠቀስካቸው ጨቋኝ ብሔረሰቦች የሌለውን ባህል ለማጥፋት የዘመቱ አልመሰለኝም። የአማራን እና የትግሬን ባህል ለምን አልተጠፋፉም። ባህል ይወራረሳል እንጂ አይጠፋፋም። ይዋዋሳሉ ወይም ይወራረሳሉ። አስምሌሽን የሚባለው መሰለኝ።

ዋለልኝ ከሁሉ የገረመኝ እያንዳንዳቸው ብሔሮች ድንበር ወይም ወሰን አላቸው ያልኸው ነው። መቼ ነበር ይኼ ድንበር የመጣው ወይም የድንበር አከላለል እንዴት መጣ? ወይም ተከሰተ? ያም ሆኖ ዋለልኝ የአማራ የበላይነት በዝቷል ብለህ መልሰህ አማራ እዳይደራጅ ወይም መደራጀት የማይችል አድርገህ ታስቀምጣለህ።  የእምፔራሊዝም ጸባይ ስላለው አይደራጅም ያልከውን ለማስታወስ ነው። የአንተ ተከታዮችም ቢሆኑ ይህንኑ ይነግሩን ነበር። አሁን ግን አማራ መደራጀቱን ስትሰማ ምን ትል ይሆን? መደራጀት አይችልም ይሉ የነበሩት እንዚህ አካላት ተደረጅተውና ጠንክረው ሲመጡ ዴሞክራሲያዊብሔርተኞች ይሉት ጀምረዋል። አይ መዋዠቅ!!!!

በሌላ ቦታ የጎጃምን ህዝብን አመጽ ደግፈን የባሌውን ቸል እንላለን። የመንግስቱ ንዋን መፈንቅለ መንግስት አድንቀን የታደሰ ብሩን አመጽ የጎሳ አመጽ ብለን እናጣጥላለን ብለሃል። ትክክል ነው። ማንኛውም የትግል እንቅስቃሴ በሚዛናዊነት መደገፍ ይኖርበታል።

ዋለልኝ የራያና እና የባሌን አመጽ ጭቁን ብሔረሰቦች ከጨቋኝ  ብሔረሰብ ነጻ ለመውጣት ያደረጉትን ትግል ነው እየተባለ እየተጻፈ ነው። በአንጻሩ  የጎጃሙን የገበሬዎች አመጽ በተራው ተዘንግቷል። ይህን መዘንጋት በማደናገር የሸፈኑ አዳዲስ የትምክህት ኃይሎች መኖራቸውን ብትሰማ ምን ትል ይሆን? አንተ የጻፍክለት፣ የተከላከልክት የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል “ፍታሃዊነትን” ዛሬ ብታየው ትደነግጣለህ። ጎሰኝነት ነግሷል። ለመተላለቅ ደረሰናል ወይም አፋፍ ላይ ነን። ከቻልክ አንተ ባለህበት ርዕሰ ጎሰኞች ዘመናቸውን ጨርሰው እየመጡ ናቸውና ተቆጣቸው። ቢያንስ አጥፍተው መሄዳቸውን ለአንተ ቢያምኑልህ።

የአንተ ተከታዬች የአንተን ጽሁፍ ይዘው አዲስና አዳዲስ ጥፋት እያመጡብን ነው። ከቻልክ አንድ ጊዜ ብቅ ብለህ አስተካክላቸው። አንተ የተናገርከውን ይዘው ሙጭጭ ያሉ ግትሮች በዝተዋልና እባክህ ምክር ቢጤ ስጣቸው። አንተ በነበርክበት ዘመን የተናገርከው ጥቂት በጣም ጥቂት እውነት ነበረው። ግን ከመጠን በላይ አጋነኸዋል። ብቻ መምጣት ካልቻልክ ልቡናህን አውሳቸው።

ዋለልኝ የገረመኝ ነገር ቢኖር ሕዝቦች የሰፊ መልካም ምድርና የሥነ ምጣኔ ሃብት ክምችት ጥቅም ሲገባቸው የመገንጠልን ጥያቄ ማቅረብ ያቆማሉ ያልከው ነው። ያንተው የጸዳች የግል ፍልስፍና አይደለችም። ተምራሃት ነው። ከሌኒን ወይም ከዛሬዋ ከፑቲን አገር። ስንቱ መሰለህ ከፑቲን አገር አንድነት ለምኔ ብለው የፈረጠጡት። የሥልጣን ጥመኞችም መገንጠልን ሊያቀነቅኑ እንደሚችሉ እንዴት ተዘነጋህ? የአንተም ተማሪዎች አንቀጽ 39ን ህገ መንግስቱ ውስጥ የደነጎሩት ከአንተው ከአባታቸው እና ካያታቸው ከሌኒን ብቻ ከወደዚያ አገር ገልብጠዋት ነው። ዋለልኝ የእያንዳንዱ አገር አውድ ቀርቶ ቴዎሪና ተግባር የተለያዩ እንደሆኑ ማመን ያስፍለጋል። በመሆኑም የአንተ ፍልስፍና ወድቋል።

ተከታዬችህ የአውሮፓ የተለያዩ አገሮችን ህብረት ተለምዶ ተወስዶ “አዲስ የፖለቲካ እና የሥነ ምጣኔ” ማህበረሰብ መፈጠር እያሉ ነው። ኢትዮጵያ የተለያየች አገር ይመስል። እንደ አውሮፓ አገሮች በፖለቲካና በኢኮኖሚ አዲስ ማህበረሰብ መፍጠር የሚባል ተይዟል። ተመልከት። የአውሮፓ ህብረት አገር አይደለም። በዚያ ላይ አዲስ ማህበረሰብ መፍጠር አላማቸው አይደለም። አዲስ ማህበረሰብም አልፈጠሩም። ከዚህ ውጭ ኢትዮጵያ አንድ አገር አውሮፓ ብዙ አገሮች ናቸው። ዋለልኝ አንተም ሆነ ተከታዮችህ ጥልቅ እውቀት ያነሳችሁ መሰለኝ። ዛፍ ያጣ ጉሬዛ ሆናችኋል እሳ!!!ቲዎሪያችሁን ተግባር ፈትኖ ጥሎታል። እባክህ ላስቸግርህ በዘር ወይም በጎሳ ወይም በጎጥ፣ በቀበሌ እና በመንደር ተለያይተን ሳንጠፋፋ ወዳጆችህን ምክር ቢጤ ለግሳቸው።

የሚገረምህ ነገር ዋለልኝ ኢትዮጵያ  የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት ናት ያልከውን ወጣቶች እየሻሩት ነው። አበቃ!!! ቀይና ነጭ ጤፍ ነን፤ ነበርንም። አብረን የምንበጠር፣ አብረን የምንፈጭ አብረን የምንቦካ አብርን የምንበላ። አብረን አገር መስርተናል። ኢትዮጵያዊነት ሱሱ ነው እያሉ ነው። ይህን ሲሉ የባህል፣ የቋንቋ፣ የፖለቲካ ትስስሩን ለመግለጽ ነው።

ይገርምሃል አቶ ጥላሁን ጣሰው የሚባሉ ጸሐፊ “ወቅቱ ኢትዮጵያዊነትን ማጠናከር ይጠይቃል›› በሚለው ጽሑፋቸው (ሪፖርተር ታህሳስ 4 ቀን 2010 ዓ.ም.  በወጣው ጋዜጣ ላይ) የአንተንና የብርሃነ መስቅልን አስታሳሰብ በጥልቀት ቃኝተዋል። በመግቢያቸው ላይ የሰው ማመዛዘን የሚችለው በግንባራችን በኩል ያለው የአዕምሮ ክፍል የሚዳብረው ከ25 ዓመት በኋላ ነው ብለው ይጀምራሉ። ነገሩን ያነሱት የእናንተን በተለይም የአንተን የማመዛዘን ችሎታ በመጠራጠራቸው ይመስላል።

ለምሳሌ የአንተን ኢትዮጵያን የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት ናት ማለትህን በደምሳሳው (በግልብ) የተነገረ አድርገው ወስደውታል። “ዋለልኝ ሮማን ፕሮቻዝካ አማራ ብሎ ካጠቃለላቸው ትግራዮች፣ ጎጃሜዎችና ኦሮሞዎች ውስጥ ጣሊያኖች እንዳደረጉት ኦሮሞዎችን ነጥሎ በማውጣት ጎጃሞችን ከሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎች በመደመር የአማራና የትግራይ ገዥ የነፍጠኛ ሥርዓት የሚለውን እሳቤ አራመደ።” ይላሉ። ወጥ አለመሆንህን ለማሳየት ነው። ወይም ሲተቹ ነው። እንዲያውም “ዋለልኝ በግልብ አስተሳሰብ ሶሻሊስት ኤርትራ ሶሻሊስት ባሌ በማለትም በጠቅላይ ግዛቱ የሚመሰረቱ ሶሻሊስት አገሮች ሊሆኑ እንደሚችሉ ሁሉ ለመጻፍ አያወላዳም።” ይሉሃል። አስተውል ዋለልኝ እኒህ ጸሐፊ ትችት ሲያቀርቡ “በግልብ አስተሳሰብ ብለውሃል። እንዲያውም ዋለልኝ ከጀብሃ ጋር ስትሰራ ስለነበር ኢትዮጵያን የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት ስትል የኤርትራን ክፍለ ሃገር በተመለከተ ምንም አላልክም። ኤርትራ የብዙ ጎሳዎች ክፍለ ሃገር ናትና። ጸሃፊው ስለ እርሷ ለመናገር አልደፈርክም ብለውሃል።

ዋለልኝ አዲስ አገር መመስረት ያስፈልጋል ብለህ ተከራክረህ ነበር። እንዲያውም አቶ ጥላሁን ‹‹ሮማን ፕሮችዝካ በግልጽ ኢትዮጵያን ለማዳከም የራስን እድል በራስ መወሰን አስፈላጊ ነው ያለውን የጠላት ፕሮፖጋንዳ በሚያስንቅ መልኩ ዋለልኝ ኢትዮጵያ የምትባል ብሔራዊ አገር የለችም በማለት ህልውናዋንም የካደ ጽሁፍ አቀረበ።›› ሲሉ አቅርበዋል። አይ ዋለልኝ!!! አሁን አንተ የለህም ኢትዮጵያ ግን አለች። ግን ቆስላ ነው ያለችው።

እናማ ዋለልኝ የአንተ የሶቪየት ህብረት የብሔር ብሔረስብ ፍልስፍና ፍቅር ሲፈርስ ያንተ ጥገኛ ተከታዮች ወይም በአንተ የተጠመቁት አዲስ ፍልስፍና ይዘው ብቅ አሉ። “አዲስ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር” የምትል። ከዚህ በላይ እንደተነሳው ሞዴላቸው የአውሮፓ ህብረት ነው። የአገሮች ህብረት እንዴት ለአንድ አገር ምሳሌ ሊሆን ይችላል። ዋለልኝ የባህል መስተጋብርን እረስተው ፖለቲካውና ኢኮኖሚው ላይ ተሳፍረዋል። በግብይት ጊዜ ባህል መወራረሱን ዘንግተው ነው። በተጨባጭ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ከአለም ባህል ጋር እየተዳቀለ ነው እኮ። ይገርምሃል አሁን የእንግሊዝ ከአውሮፓ መውጣት ሌላ ችግር ሆኖባቸዋል። ተከታዮችህ ሌላ ሞዴል ማጥናታቸው አይቀርም። ባዘኑ። ዕውቀታቸውን ከሃገራቸው ባህል ማዳቀል አልቻሉም። ዋለልኝ የአንተው የእጅ ሥራ እንዴት ለውጥ የማያውቁ ሸክላ አድረገህ ብትሰራቸው ነው መሰንጠቅ እንኳ ያላሳዩት። በ20 ዎቹ መጀመሪያ የጻፍከውን በ70 ዓመታቸው አመዛዝነው ክለሳ ማድረግ ወይም ማሳየት የተሳናቸው። አይ ያ ትውልድ!!!

ዋለልኝ ይግርምሃል ኢትዮጵያ የቆየች ጥልቅ የባህል መስተጋብር ያለትና ተወራራሽ፣ በፈረቃ ህዝቦቿ የገዟት አገር ናት የሚሉ መንፈሶች መነሳታቸውን ላረዳህ እወዳለሁ። ኢትዮጵያ ሱስ የሆነችባቸው። በዚህ ነዲድ የአገር አስተሳሰብ ያንተን ግርፎች የሚያንቀጠቅጡ። ይኄ መችም ለአንተና ለተከታዮችህ መርዶ ነው። ወዳጄ ሆይ ቢመርም መርዶውን ተቀበል። ምናልባት አንተ ባለህበት ሁሉም አንድ መሆኑን፣ ሁሉም ሲሞት በሰውነቱ እንደሆነ እንጂ በጎሳው አለመሆኑን ተገንዝበህ ተለውጠህ ከሆነ ተለወጫለሁ ተለወጡ በላቸው።

ወይ ጉድ እረስቼው ዋለልኝ። አፈወርቅን ለመውቀስ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝን ዋቢ አድርገህምኒልክን ለማወደስ ዮሐንስን መሳደብ የግድ አይደለም የምትለዋን ጠቅሰሃል። ልክ ነበርክ። አሁን የኛም ዘመን በዚህ አባዜ ተይዟል። ዘመነኛ መሪዎቻችንን ለማወደስ አጼ ዮሐንስን ሳይጠቅሱ አጼ ቴዎድሮስን እና ምኒልክን አየተሳደቡ ናቸው። ብድር በምድር መሆኑ ነው። ምክራቸው የመለወጥ ተስፋ ካለቸው። ካልሰሙህ ችግር የለም አንድ ቴዲ አፍሮ የሚባል ብላቴና በሙዚቃ ቃና ቴዎድሮስንና ምኒልክን ትንሳኤ አላብሷቸዋል። ታያለህ ለማ መገረሳን፣ ገዱ አንዳርገቸውን፣ አብይን (ዶ/ር ) እና ሌሎች ደፍረው የጎጡን ፈፋ ከታሻገሩ አክብሮት አይነሳቸውም። ብላቴናው የዋዛ አይደለም!!! በቃ ልሰናበትህ አበዛሁብህ ብቻ ትርፍ ሰዓት ይኖርሃል ብዬ ነው የዘበዘብሁህ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
119 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 85 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us