ለፖለቲካዊ ችግር ፖለቲካዊ መፍትሔ

Friday, 12 January 2018 17:11

 

ኢዛና ዘ መንፈስ

 

ኢህአዴግን ጨምሮ ዛሬም ድረስ ያሉ አብዛኛዎቹ የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጋሯቸው ተወራራሽ ባህርያት ስለመኖራቸው ደፍሮ መናገር ይቻላል። የመጀመሪያውና ምናልባትም ዋነኛው የሀገራችንን ፖለቲከኞች በእጅጉ የሚያመሳስላቸው ነጥብ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ህዝቦች እንደ ህብረተሰብ በሌላው ዓለም ማህበረሰብ ዘንድ የምንታወቅበት ህብረ ብሔራዊ የጋራ ማንነታችን ከተሰራበት ድርና ማግ የሚመነጩ፤ አወንታዊ አልያም ደግሞ አሉታዊ ጎኖችን የሚወራረሱበት አግባብ መኖሩ ነው። እንዲሁም ደግሞ በተደራጀ መልኩ የሚደረግ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴን ለሀገራችን ህዝቦች አስተዋውቀዋል ተብሎ የሚታመንባቸው፤ የ1960ዎቹ ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ፈላጊ ምሁራን ወጣቶች ላይ በወቅቱ ይንፀባረቅ ከነበረው፤ ግራ ዘመም ዕዮተ-ዓለማዊ አስተሳሰብ ጋር ተያይዞ የሚገለፅ የኢ.ዴሞክራሲያዊነት ግትር አቋም አሁንም ድረስ ሲፈታተነው የማይስተዋል ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኛ የለም የሚለው አስተያየት እንደ ሁለተኛ የሁሉም ፖለቲካዎች የጋራ ባህርይ ሊወሰድ የሚችል ሆኖ ይሰማኛል።


ይህን ስል ግን የፓርቲ ፖለቲካ ታሪካችን አሉታዊ ዳራም ሆነ ከኢትዮጵያዊያን የብሔር ብሔረሰብ ህዝቦች ማህበራዊና ስነ ልቦናዊ ስረ መሠረት የሚመነጩት ተወራራሽ ባህርያት የሚገለፁበት አግባብ እያንዳንዱ የሀገራችን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በዕኩል መጠን የሚታይ ተፅእኖውን እያሳደረ ነው ማለታችን አይደለም። ይልቅስ ዛሬም ድረስ ባሉት የሀገራችን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ተደጋግሞ የሚስተዋለው የአመራር አካላት ውስጣዊ የዕርስ በርስ ሽኩቻና የቡድን ጎራ ለይቶ መጠላለፍ ከሚከሰትበት የዘመነ መሳፍት ኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ሴራ የማውጠንጠን ጎጂ ባህል የፀዳ ድርጅት ይኖራል ብሎ መጠበቅ እንደሚያዳግት ልብ ትሉኝ ዘንድ ነው እኔ የፈለግኩት።


በሌላ አነጋገር የመጠን ጉዳይ እንደሁ እንጂ ከላይ ለአብነት ያህል የተነሱት የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ስር የሰደዱ ችግሮች አይመለከቱኝም ሊል የሚችል አንድም ፓርቲ፤ ድርጅት፤ ግንባር፤ አሊያም ደግሞ ህብረትና መድረክ ወዘተ በዚህ አገር ውስጥ ይኖራል ተብሎ እንደማይጠበቅ ይታመናል ማለቴ ነው። ይህ አስተያየት የተጋነነ መስሎ የሚሰማው አንባቢ ካለም ደግሞ፤ በተለይም ከ1960ዎቹ ዓመታት ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ ስም እየተመሰረቱ እንታገልለታለን የሚሉትን ዓላማ ከማሳካት አኳያ ብዙም ርቀው ሳይጓዙ ያልተጠበቀ የገዛ ራስ ውስጣዊ ድክመት እያጋጠማቸው ሲፈራርሱና የአንድ ወቅት ታሪክ ሆነው ሲቀሩ ስለተስተዋሉ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያስታውስ ዘንድ እመክረዋለሁ።


እንግዲያውስ ይሄን የሀገራችን ፖለቲካና ፖለቲከኞች ከትናንት እስከ ዛሬ የሚታወቁበት እጅጉን ስር የሰደደ ውስብስብ ዕርስ በርስ እየተጠላለፉ ተያይዞ የመውደቅ ችግር፤ እንዴት መፍታት እንደሚቻል ያሳየ ረጅም የትግል ጉዞ ስለመጓዙ የሚነገርለት ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ ህዝቦች የፀረ ጭቆና ትግል መስመር ለምን ፈተናዎቹን በማለፍ ረገድ ‹‹ከሌሎች ፓርቲዎች የተሻለ ነው›› የሚያሰኘውን አንፃራዊ ውጤት እያመጣ እንደቆየ ለመመልከት የሚረዱንን አንዳንድ ነጥቦች ለማንሳት ነው እንዲህ መደርደሬ።


ስለሆነም እኔ ገና ከትጥቅ ትግሉ ዘመን ጀምሮ የማውቃቸው ከውስጣዊ ድክመት ለሚመነጭ ፖለቲካዊ ችግር፤ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን በተከተለ የግምገማና የውይይት ሂደት አማካኝነት፤ ጎጂውን ሃሳብ ከጠቃሚው እየለዩ የትግሉን ጉዞ ከመገታት የሚታደግ ፖለቲካዊ መፍትሔ ሲያስቀምጡ የተስተዋሉበት የታሪክ አጋጣሚ ጥቂት እንዳልነበር ደፍሮ መናገር ይቻላል። ለዚህ አስተያየቴ ተጨባጭ ምሳሌ ተደርጎ ሊጠቀስ የሚገባው የትጥቅ ትግሉ ዘመን ታሪክም፤ አንጋፋዎቹ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ህውሐትና ብአዴን የየራሳቸውን ድርብርብ ፈተና ለማመን በሚያዳግት የዓላማ ፅናት እየተሸገሩ ስለመምጣታቸው የምንረዳበት የውስጣዊ ትግል መድረክ እንደሆነም ደፍሮ መናገር የሚቻል ይመስለኛል።


ከዚህ አኳያ መወሳት ይኖርበታል የምለውም ደግሞ ‹‹ኢ.ህ.አ.ፓ.የገደለውን የትግል ወኔ ኢ.ህ.ዴ.ን ነፍስ ይዘራበታል!›› የሚል መፈክር አንግበው የተነሱ ጥቂት ተራማጅ ታጋዮች የዛሬውን ብአዴን፤ የያኔውን ኢ.ህ.ዴ.ን ከመመስረት ጀምሮ፤ የገጠማቸውን ድርጅታዊ የፖለቲካ አቋም መዋዠቅ ችግር ባልተቋረጠ ግምገማና ውይይት አማካኝነት እልህ አስጨራሽ ጥረት አድርገው የትግል መስመራቸውን ለማጥራት የቻሉበት የፖለቲካዊ መፍትሔ አሰጣጥ መድረክና እንዲሁም ህውሐት የአስር ዓመት የትጥቅ ትግል ጉዞውን የገመገመበት የ1977ቱ ጥልቅ ተሃድሶ ነው።


ይሄን ዓይነቱ ከግንባሩ አባል ድርጅቶች የጀርባ ታሪክ ጋር በተያያዘ መልኩ እየዳበረ የመጣ ለፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ የመፍትሔ አቅጣጫ የማስቀመጥ ጠቃሚ ተሞክሮ፤ ከደርግ ውድቀት በሁዋላም ጭምር ኢህአዴጋዊ የትግል ባህል ተደርጎ እስኪቆጠር ድረስ ሲሰራበት እንደቆየም ይታወቃል። ስለሆነም በ1993ዓ/ም የተካሔደውን ሁሉንም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ያካተተ የተሃድሶ መድረክ ጨምሮ፤ሌሎችም የገዢውን ፓርቲ መሠረታዊ ዓላማ የሚፈታተን የፖለቲካዊ አቋም መዋዠቅ (የአስተሳሰብ ብዥታ) ችግር ሲያጋጥሙ መሰል ፖለቲካዊ መፍትሄ ማስቀመጥ የተለመደ ጉዳይ እንደሆነ ማስታወስ ይቻላል።


እናም ይሄው ኢህአዴግን ከአብዛኛዎቹ የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለየ ስፍራ የሚያሰጠው ጠቃሚ የትግል ባህል የሚገለፅባቸው ድርጅታዊ እሴቶች ናቸው ግንባሩ በየወቅቱ የሚያጋጥሙትን ውስብስብ ፈተናዎች ሁሉ፤ እንደ ምንም ተጋፍጦ እያለፈ የትግሉን ጉዞ የማስቀጠል ታሪካዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ በማድረግ ረገድ ቁልፍ የሚባል አወንታዊ ተፅእኖ የሚያሳድሩት። ከዚህ የተነሳም ነው ኢህአዴግ በራሱ ውስጣዊ ድክመቶች ምክንያት ተገዝግዞ ሲወድቅ ማየትን የሚናፍቁት ፅንፈኛ ተቃዋሚዎች፤ ግንባሩ እንደ አንድ ጠንካራ ገዢ ፓርቲ የሚታወቅባቸውን ጠቃሚ የፖለቲካዊ ትግል ዕሴቶች ለማውደም ያለመ ፈርጀ ብዙ ደባ በመፈፀም ዕኩይ ተግባር ላይ መጠመድን እንደ አዋጭ የትግል ስልት የቆጠሩት።


በተለይም ደግሞ ከ1997ቱ ጠቅላይ ምርጫ በሁዋላ፤ የትምክህተኝነትንና የጠባብ ብሔርተኝነትን ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ከከረረና ከመረረ ፅንፈኛ አቋም በመነጨ መልኩ ሲያቀነቅኑ የሚስተዋሉት የተቃውሞው ጎራ ሃይሎች፤ ያለ የሌለ አቅማቸውን አሰባስበው የሚረባረቡት ኢህአዴግ እንደ አንድ በፀረ ጭቆና የትጥቅ ትግል ሂደት ውስጥ አልፎ የመጣ ገዢ ፓርቲ በረጅሙ የትግልና የድል አድራጊነት ታሪኩ ያዳበራቸውን ጠቃሚ ለፖለቲካዊ ችግር ፖለቲካዊ መፍትሄ ማስቀመጫ የድርጅታዊ ባህል እሴቶች ዋጋ ለማሳጣት ያለመ ደባ መፈፀም ላይ እንደሆነ ይታመናል።


እናም እነዚሁ ሃይሎች ከሀገር ቤት እስከ ባህር ማዶ ድረስ በዘረጉት የሴራ ፖለቲካ ፕሮፖጋንዳዊ መረባቸው አማካኝነት የሚያውጠነጥኑት ሃኬት፤ ኢህአዴግ መራሹን ፌደራላዊ ስርዓት ውስጥ -ውስጡን ገዝግዞ ስለመጣል አስፈላጊነት የሚሰበክበት ደባ የመሆኑን ያህል፤ ገዢው ፓርቲ አደጋውን በቅጡ ተገንዝቦ ትርጉም ያለው ለፖለቲካዊ ችግር ፖለቲካዊ መፍትሔ የመስጠት እርምጃ እንዳይወሰድ ለማድረግ ያለመ አሉታዊ ተፅእኖ የመፍጠር ግልፅና ህቡዕ እንቅስቃሴ የሚያካሂዱበት አግባብም እጅጉን ቅንነት የጎደለው ኢ-ሞራላዊ ተግባር ነው ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ ግን፤ዛሬም ድረስ ኢህአዴግን ‹‹ኢህአዴግ›› ለሚያሰኙት ድርጅታዊ የትግል ባህል ጠቃሚ እሴቶች፤ ህልውና መቀጠል በፅናት ሲቆሙ የሚያስተውሉ የግንባሩ አመራር አካላት እንዳሉ መረዳት አያዳግትም።


ለዚህ ደግሞ አሁን ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከምትገኝበት ወቅታዊ እውነታ ጋር በተያያዘ መልኩ ያልተለመደ ዓይነት የመፍረክረክ አዝማሚያ የታየበትን፤ የአንዳንድ ከፍተኛ የኢህአዴግ መራሹ መንግስት የስራ ሃላፊዎች ሰሞነኛ ክስተት ተከትሎ፤ የግንባሩ ስራ አስፈፃሚ ለተከታታይ 17 ቀናት ባካሔደው ዝግ የስብሰባና ግምገማ መድረክ ላይ፤ ያጋጠሙ ፖለቲካዊ ችግሮችን በተለመደው ዴሞክራሲያዊ የውስጥ ትግል ባህል ስለመፍታት አስፈላጊነት ተነስቶ ተስፋ ሰጪ ሊባል ወደሚችል ሀገራዊ የጋራ መግባባት የተደረሰበት ሁኔታ ስለመፈጠሩ የሚያመለክት መልካም ዜና ዓርብ ታህሳስ 20ቀን 2010ዓ/ም ፋና ብሮድካስቲንግ መዘገቡን ማስታወስ ተገቢ ይመስለኛል።


በግልፅ አገጋገር፤ ካለፈው መስከረም ወር 2010 ዓ/ም ጀምሮ ከከፍተኛ የፌደራሉ መንግስት የስራ ሃላፊነታቸው ለመልቀቅ ፈልገው ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጥያቄ ስለማቅረባቸውና በኋላም ጥያቄያቸው ተቀባይነት ስለማግኘቱ ጉዳይ በመገናኛ ብዙሃን እየተዘገበ የሰነበተው አቶ በረከት ስምኦንና አቶ አባዱላ ገመዳ ሰሞኑን የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት የተካሔደ ጥልቅ ውይይት ላይ አቋማቸውን ለውጠው በትግሉ ለመቀጠል እንደወሰኑ ጭምር ነው ዜናው አክሎ ያተተው። ታዲያ ከዚህ ወቅታዊ ተጨባጭ እውነታ በተሻለ መልኩ ኢህአዴግ ለፖለቲካዊ ችግሮቹ ፖለቲካዊ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን የማስቀመጥ ጠቃሚ የትግል ባህል ያዳበረ ድርጅት ስለመሆኑ የሚያሳይ ማረጋገጫ ያስፈልጋልን ወገኖቼ!? እንደኔ እንደኔ ግን አያስፈልግም ባይ ነኝ።


ስለዚህም፤ ሁለቱ አንጋፋ የኢህአዴግ ታጋዮች (አቶ አባዱላና አቶ በረከት) በዚህ ሀገራችን ኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆማ በምትገኝበት እጅጉን አሳሳቢ የፈተና ወቅት፤ ከታሪካዊው ሃላፊነታቸው የማፈግፈግ አዝማሚያን ያሳዩበት አግባብ፤ ትክክል አለመሆኑን ተረድተው አቋማቸውን ለመቀየር መወሰናቸው፤ ለመላው የትግሉ ሰማዕታት የገቡትን ክቡር ቃል እንደመጠበቅ ሊቆጠር የሚችል የእውነተኛ ታጋይ መገለጫ ባህሪ ነውና እነሆ ልባዊ አድናቆቴ ይድረሳቸው። ምክንያቱም ደግሞ በረከትና አባዱላ፤ ኢህአዴግ መራሹን የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል ጉዞ ለቀው መሔድ አይኖርባቸውም ማለት ባይቻልም ቅሉ፤ ሁለቱም አብዛኛውን ዕድሜያቸውን የፈጁባቸው መሰረታዊ የትግሉ ዓላማዎች ለአሳሳቢ ቅልበሳ አደጋ የተጋለጡ መስለው በሚታዩበት በዚህ ወሳኝ ወቅት መሆኑ ግን ፈፅሞ የሚደገፍ ጉዳይ አይደለም።


እንኳንስ በእነርሱ ደረጃ የሚታወቅ ከፍተኛ የኢህአዴግ ነባር አመራርና ይሄው እኛ ራሳችን ከትምክህትና ከጠባብ ብሔርተኝነት አስተሳሰብ ጋር የሞት ሽረት ሊባል የሚችል ግብግብ ገጥመን ህብረ ብሔራዊውን የፌደራል ስርዓት ከተጋረጠበት በቀለም አብዮተኞች የመፈራረስ አደጋ በመታገድ ረገድ የሚጠበቅብንን አወንታዊ አስተዋፅኦ ለማበርከት ስንሞክር የምንስተዋለው እኮ፤ እልፍ አዕላፍ የትግሉ ሰማዕታት የወደቁለት መሰረታዊ ዓላማ መና እንዳይቀር ነው።


ስለሆነም ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የጀመረው የጥልቅ ተሃድሶ መርሐ ግብር እንዲህ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ስፋትና ጥልቀት እየጨመረ ሄዶ፤ ግንባሩ በሀገራችን የፖለቲካ ፓርዎች ታሪክ ውስጥ የተለየ ስፍራ እንዲይዝ የሚያደርጉትን የውስጣዊ ችግር አፈታት ድርጅታዊ የትግል ባህል ዕሴቶቹን፤ ለተተኪው ወጣት የአመራር ትውልድ ሊያስረክብ የማይችልበት ምክንያት እንደማይኖር የሚያመለክት ነው ማለት ይቻላል በስራ አስፈፃሚው ሰሞነኛ የግምገማ መድረክ ማጠቃለያ ላይ ስለተወሰነው ውሳኔ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዓርብ ታህሳስ 20 ቀን 2010 ዓ.ም ያስደመጠን ዜና።


ከዚህ አኳያ ሲታይ፤ በተለይም ካለፈው የመስከረም ወር መጀመሪያ 2010 ዓ.ም ወዲህ አንዳንድ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የአመራር አካላትን በእጅጉ የታዘብንበት ከግንባሩ የትግል መስመር የማፈንገጥ አዝማሚያ፤ የከፋ ሀገራዊ ቀውስ ሳያስከትል የጋራ ግንዛቤ ተወስዶበታል የሚል ተስፋ ብናሳድር ተገቢ እንደሚሆንም ነው የሚሰማኝ። በእርግጥም ደግሞ ስርዓቱን እንደ ስርዓት ላልተጠበቀ የቅልበሳ አደጋ የሚያጋልጥ ፖለቲካዊ የአመለካከት ችግር ሲያስከትልብን እየተስተዋለ ያለው መሰረታዊ ጉዳይ፤ እውነተኛውን የኢህአዴግ ታጋይ ለጊዜያዊ ጥቅም ሲል ብቻ የግንባሩ አባል ድርጅቶች መዋቅር ውስጥ ተሰግስጎ ከሚያምታታው አድር ባይ መለየት የሚያስችል ትክክለኛ የአቋም መለኪያ መድረክ መጥፋቱ እንጂ ሌላ አይደለም።


ስለዚህም መላው የሀገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፈርጀ ብዙ መስዋእትነትን ባስከፈላቸው የዘመናት ፀረ ጭቆና ትግል የተቀዳጁትን ሕገ መንግስታዊ መብትና ነፃነት እንደተራ ነገር ቆጥረው የቀለም አብዮት ሰለባ ሊያደርጉት ከሚሹት ፅንፈኛ ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች ጋር መሞዳሞድን እንደ ‹‹መቻቻል›› ወይም ደግሞ የተለየ እውቀት እንደሚጠይቅ የፖለቲካ ጥበብ ሊወስዱት የሚቃጣቸው አድርባዮች እስካሉ ትርጉም ያለው ለውጥ አይመጣምና ሊታሰብበት ይገባል እላለሁ።

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
114 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1020 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us