“ጥልቅ” ወይስ “ብቅ ጥልቅ” ተሃድሶ?

Friday, 12 January 2018 17:13

 

በአንድነት ቶኩማ

 

የካድሬዎች ስብሰባ ላይ አንድ ጊዜ በአጋጣሚ የመገኘት ዕድል ገጥሞኝ ነበር። በጊዜው የተሰበሰቡት ሁሉ የሚናገሩት አንድ አይነት ቋንቋ ነበር። ተስብሳቢዎች እምነታቸውና ፍርሃታቸው በአንድነት ሆኖ በላያቸው ላይ ወድቆ ነው ሃሳብ ይሰጡ የነበሩት። ግለሰቦች ነፃ አይደሉም ማህበራቸው እንጂ። ተመሳሳይ ምርት ይመስል እጃቸውን የሚያወጡት በአንድነት ነበር። “እስኪ መቼ እና የቱ ድርጅት ነው ይህንን ድርጅት አሸንፌው አውቃለሁ? ብሎ ሲናገር የተሰማው። የሞከሩ ነበሩ።” አለ ስብሰባውን የሚመራው ካድሬ። የራሱ ሃሳብ አይደለም። የራሱ ሃሳብ ኖሮት የሚያውቅ አይመስልም። ራሴን ስሞግት ይህ እንኳ ስህተት ነው፣ ሰው ሳያስብ እንዴት ይኖራል ስል እኖራለሁ ሁልግዜ ሳስበው። ስብሰባው የግንቦት 20 የድል በዓልን ምክንያት በማድረግ የተሰጠ ገለፃ ነበር። በዓሉ በደመቀ ሁኔታ እየተከበረ ነበር። የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች በአምባሻና በፖኘኮርን ደምቋል። ሙዚቃው በየቦታው ተለቋል። ሰው አልባ ድንኳኖች ሽሩባ በተሰሩ እና ከመንደር ለምን እንደተሰበሰቡ በማያውቁ ደካማ እናቶች ጠባቂነት ተተክለዋል። ወጣት የኢህአዴግ አባላት የተለያዩ እና የተለመዱ መዝሙሮችን እየዘመሩ በእየአውራ ጎዳናው በአይሱዚ መኪና ላይ ተጭነው እየሄዱ ይታያሉ።


የአንዳንድ ቀበሌ ስብሰባ ግን ከሚባለው በላይ ደማቅ ነበር። ጥናታዊ ፅሑፎችም ቀርበዋል። ጥናታዊ ፅሑፍ ካድሬያዊ መግለጫ በመሆናቸው ዕውቀታዊነት ይጎድላቸዋል። የተሰበሰበው የዕውቀት ግምትም አናሳ ነበር ማለት ይቻላል። በተለይም የፓርቲው አባላት የአቋም ድጋፍ ለመስጠት ብቻ የተቀመጡ ነበር የሚመስሉት።


ታዲያ በዚያ ስብሰባ ማግስት ነበር ማለት ይቻላል አገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ ችግር ውስጥ ወድቃ የታየችው። ባለፈው ዓመት መሆኑ ነው። እንደዚያ ባለ ቀውጢ ወቅት ነበር አንድ ሁኔታዎችን በቅጡ ያልተገነዘበ ግለሰብ (ካድሬ) የኢህአዴግ መንግስትን ጠንካራነት የተናገረው። የሚገርመው ግን ፓርቲው ከጥቂት ቀን በኋላ ነበር ወደ ጥልቅ ተሃድሶ ገብቻለሁ ያለው። ከመግለጫው በኋላ እንዳየነው ‹‹ጥልቁ ተሃድሶ›› ጥልቅ ሳይሆን ‹‹ብቅ ጥልቅ ተሃድሶ›› ሆኖ ነበር የተገኘው። በምን አወቅን ከዓመት በኋላ ሌላ ጠለቅ ያለ ተሃድሶ አደረግን ብለዋልና።


ባለፈው የኢህአዴግ መንግስት ተጠሪ ንግግር ሲያደርጉ የፓርቲያቸውን ሃያልነት በኩራት ገልፀዋል። የኢህአዴግን ታላቅነት በድፍረት ሲናገሩ ተሰምቷል። ከዚህ ውስጥ ኢህአዴግን “የሚችለው የለም” የምትለው ሃረግ ሰቅጣጭ ናት። ምክንያቱም አንድ ቱባ ባለስልጣን ድርጅታችንን ማለትም ኢህአዴግን የሚችለው የለም ሲሉ ያስቃልም፤ ያሳቅቃልም። ለምን ቢባል ከማን ጋር ተወዳድሮ ማንን አሸንፎ የሚለው ስላልተጠቀሰ። ምናልባት ደርግን አሸንፈናል ከሆነ ኢህአዴግ ብቻውን አላሸነፈም። ሌሎች ሃይሎች ነበሩና። ደርግም መሸነፉ እውነት ቢሆን እንኳ ደርግ የተሸነፈው ራሱን ስላሸነፈ ነው የሚል አተያይ አለ።


የተናጋሪው ኢህአዴግን የሚችለው የለም የሚለው ንግግራቸው ምን አይነት ጊዜን ይጠቁማል? የትናንቱን ነው? የዛሬውን ጊዜ አመላካች ነው? ወይስ የወደፊቱን? አሊያም ዘላለማዊ ጀግንነቱን የሚጠቁም ነው? ሃረጉ የወደፊቱን የሚያጠቃልል ይመስላል። ይህ መፈተሽ አለበት።


ሌላው ይህ ሃረግ (ቃል) ከአውድ ጋር አልተጠቀሰም። ማለትም ለምሳሌ “ተቃዋሚ ፓርቲዎች” “ሻቢያ” “ሶማሊያ” “ግብፅ” ወይም ሌላ አካላት አልተጠቀሱም። በዚህ ሁኔታ ማንም አይችለውም የተባለው ኢህአዴግ ከማን ጋር ተወዳድሮ ነው? የሚል ጥያቄን ያጭራል። ከሻቢያ ጋር በነበረው ጦርነት ኢህአዴግነት ሳይሆን ያሸነፈው ኢትዮጵያዊነት ነው። ድሉ የኢትዮጵያዊያን ነው። ምሳሌ ላክል። ኢትዮጵያ ኤርትራን ማሸነፏ ለእኔ ድል አይመስለኝም። ሁለቱ አገሮች ተመጣጣኝ አይደሉምና። በአዲስ አገርና በዘመናት ከቆየች አገር ጋር የሚደረግ ጦርነት እኩልነት የሌለውን ድል ስለሆነ እርሱን እጅግ መዘመር ተገቢ አይደለም። ኢትዮጵያ ጣሊያንን በምኒልክ ጊዜ አሸንፋ ነበር። ምኒልክም ‘ፓርቲያቸውም’ አሁን የለም። በመሆኑም አንድ ጊዜ ጦርነትን ማሸነፍ ሁልጊዜ አሸንፋለሁ የሚል ሃሳብ ማምጣት የለበትም። በጭራሽ። ማሸነፍና መሸነፍ የጦርነት ወይም የውድድር ህግ ነው።


እኔ እንደሚገባኝ ኢህአዴግ ከሃያላን አገሮች ከአሜሪካ፣ ከእንግሊዝ፣ እንዲሁም ከቻይና ጋር ተወዳድረው (ተጋጥመው) አሸንፈው የሚችለን የለም እያሉ አይመስለኝም። ኢህአዴግ ያን ያህል ያብጣል የሚል ግምት የለኝም። ማበጥ ግን መብቱ ነው። የእኛ ድርሻ ከተቻለም በዚህ አቅጣጫ ዕብሪት ማስተንፈሻ የሚባል ‹‹እውነተኛ ጥልቅ ተሃድሶ›› ያደርጉ ዘንድ ማመላከት ነው። የዕብጠቱን መጠንና ጥልቀት መመርመር ብቻ ነው ተግባራችን። የዕብጠቱን የመነሻ ፍልስፍናንም የመመዘን ሃላፊነትም ቢኖረንም።
በመሆኑም ህወሓት /ኢህአዴግን ‘የሚችለው የለም’ የሚለውን ቃል ለመዋጥ ብዙዎች ይቸገራሉ። ተቀባይነት የሌለው ሃረግ ነው። ቃል ወይም ወኔ ብቻ ነው። ወኔውንም የተሰነቀው ከጭብጥ አይደለም ወይም ወኔው የተቀዳው ከእውነት አይደለም። ተጣርሶሽ ነው። ለመሆኑ ባለፉት 25 ዓመታት በግልፅ ከዚያም በፊት ከ15 - 17 ዓመታት በስውር ኢህአዴግ የተሸነፈ ድርጅት መሆኑን ያውቃሉ? ማንም ባገኘው አጋጣሚ ዘርሮታል። ለኔ ጥልቅ ተሃድሶው ጥልቅ የሚሆነው የሚከተሉትን ነገሮች ማሸነፍ ከቻለ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ሳይሆን ‹‹ብቅ ጥልቅ ተሃድሶ›› ነው የሚሆነው። በኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አካላት ሰሞኑን የተሰጠው መግለጫ ከብቅ ጥልቅ ወደ ጥልቅ መሸጋገሩን የሚከተሉትን ሃሳቦች በተግባር ፈፅሞ ሲገኝ ነው፡፡ እስከአሁን ባስተዋልነው ነገር ግን በሚከተሉት ጉዳዮች ተሸንፏል፣ ማሸነፉን የምናውጅለት፡-

1. ዲሞክራሲን ማስፈን ሲችል፡-
ኢህአዴግ የተሸነፈ ድርጅት እንጂ ያሸነፈ አለመሆኑን የሚያሳዩ ነገሮች ነቅሶ ማውጣት ተገቢ ነው። ኢህአዴግ በሚመራበት ወይም እመራበታለሁ ባለው የድርጅት መርህ ተሸንፎአል። የመጀመሪያው ከስሙ ተነስተን ዴሞክራሲያዊ ያውም የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲ አጐናፃፊ ነኝ ይለናል። ይህ ግን ሐሰት ነው። ለምን ቢባል ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ አይነት ነውና። በኢህአዴግ ውስጥ ዲሞክራሲ የለም። ህዝብም የለም። የድርጅት ሥምና መልክ ምናልባት ይኖራል። አሁንማ ከእነአካቴው ድርጅትም የለም እየተባለ ነው። በዚህ ኢህአዴግ ውስጥ ዲሞክራሲ እንደሌለ ፃድቃን ገ/ትንሳኤ (ሌ/ጀኔራል) እና ገብሩ አስራት ገልፀዋል። ድርጀቱን “ፀረ ዲሞክራሲ ሃይሎች የመሸጉበት” ሲሉ። በመሆኑም በፀረ ዲሞክራሲ ሃይሎች የተሸነፈ ነው። ዲሞክራሲያዊነት የለም። በሌላ በኩል ህዝባዊ ድርጅት ሳይሆን የአድርባዮች ዞን ነው። የጥገኞችና የአለአግባብ መበልፀግ የሚፈልጉ ሃይሎች ምሽግ ነው። ከራሱ ከኢህአዴግ አንደበት እንደሰማነው ከሆነ “ግለኝነት እና ቡድነኝነት - ከመርህ አልባ ግንኙነት ጋር ተጋብቶ ግለኝነት የነገሰበት ድርጅት ነው ማለታቸውን እናስታውሳለን።

2. የመስመር መገለባበጥን ሲያሸንፍ፡-
ምሳሌ ለመስጠት ድርጅቱ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ከልማታዊ መንግስት በቀላሉና ባልተጠና መንገድ አጋብቷል። ከነጭ ኮሚኒስት ወደ ነጭ ካፒታሊስት ተሸጋግሯል። ይህ መሸጋገር የሆነው በአንድ ግለሰብ መገለባበጥ ምክንያት የመጣ ነው። “ሃቀኛ ኮሚኒስት ፅኑ ነው” የሚለውን ዘንግተው ይኖራሉ። እንኳን ህዝባዊ ሊሆን ድርጅታዊ እንኳ መሆን አልቻለም። አውራ ፓርቲና ተቃዋሚ የሚባል ድርጅታዊ ማጥቂያ መሣርያዎች መጣል አልቻለም። የዲሞክራሲ እጥረት ነው። “በምግብ ራሷን ያልቻለች ሃገር” እንደሚባለው “በዲሞክራሲ ራሷን ያልቻለች” የሚል እንዳይጨመርባት ማድረግ ሲችል ነው።

 

3. በወጥ አልባ የመስመር ዕውቀት ከመሸነፍ ሲያመልጥ፡-
የኢህአዴግ አደረጃጀት ወዛደራዊ ዓለም አቀፋዊነት ወይስ ጠባብ መንደርተኝነት? ድርጅቱ በኮሚኒስት መርህ የተመሰረተ ከሆነ ወይም ከነበረ ወዛደራዊ አለማቀፋዊነት ላይ ያጠነጠነ መሆን ነበረበት። አብሮነት ላይ ትኩረት የሚያደርግ። ድርጅቱ ይህን ኮሚኒስታዊ ፍልስፍና ታቅፎ መርሆውን እርግፍ አድርጐ ከመጀመሪያው የጣለ ነው። ብሔርተኛ ያውም ጠባብ ድርጅት ነው። የህወሓት ሰራዊት ከትግራይ ነፃነት በኋላ አልዋጋም ያለው እኮ በጠባብነት ተቀስቅሶና ተቆስቁሶ ስላደገና ስለመጣ ነበር። ድርጅቱ ጠባብነት እየዘረረና እያንደባለለው ያደገ ድርጅት ነው። ኢትዮጵያዊነት የድርጅቱን ዘውገኛ አስተሳሰቡን ሰብሮታል። የድርጅቱ ዘውገኛ አመለካከት የጉልበት መቅኖን ኢትዮጵያዊነት አፍስሶታል። መሸነፍ ማለት ይሄ ነው። ዝረራ። ተሃድሶው ለኢትዮጵያ ለአንድት የሚሰራ ድርጅት ካላደረገው ብቅ ጥልቅ ተሃድሶ እንጂ ጥልቅ ተሃድሶ ሊሆን አይችልም።

 

4. ፀረ - ህገመንግስት ሥርዓት አልበኛነትን ማስወገድ ሲችል፡-
ድርጅቱን ፀረ ህገ መንግስት ፍልስፍናዎች አሸንፈውታል። ህገ መንግስቱን ከለላ ሊያደርግለት ቀርቶ ሊጠብቀው አልቻለም። የፌዴራል አደረጃጀቱ ዋናው ባህልን፣ ቋንቋን እና መልክኣ ምድርን መሰረት አድርጐ ነው ይላል። ነገር ግን ፌዴራሊዝሙን በደንብ በጥልቀት ስንመለከተው ቋንቋን ብቻ መሠረት ያደረገ ነው። በዚህም ቢሆን ይህ አደረጃጀት በደቡብ ክልል አልተሣካም።

5. በመልካም አስተዳደር እጦት ከመሰቃየት ሲድን፡-
ህወሓት/ኢህአዴግ በመልካም አስተዳደር እጦት ተዘርሯል። ታዲያ ምኑ ላይ ነው “አይሸነፍም፣ የሚችለው የለም” የተባለው። ተፈረካክሷል እንጂ። ኢፍህታዊ የሃብት ክፍፍል ኢህአዴግን መጫወቻና መዘባበቻ አድርጐታል። ተሸንፏል። ከዚህ ጋር ድርጅቱ የሙስና መፈልፈያ ሆኗል። ዝሆኔ ሙሰኞች የጥቃቅን ሳር ሙሰኞችን ረግጠዋል። ለነገሩ በጥቃቅን የተደራጁትስ በሙስና ጉዳይ መች የዋዛ ሆኑ! ድርጅቱን ሙሰኛ ብቻ ወሮታል። “ልማታዊ መንግስት” የሚለውን “ሙሰኛና የብድር መንግስት” ቢባል ይሻላል። አንዳንዶች ወጥ ሙሰኛ ወይንም (Systemic) ሥርዓታዊ ሙሰኛ አጥቅቶታል ይላሉ። በዝረራ ተሸንፏልም የምንለው እዚህ ነው። እንዴትስ ማንም አይችለውም ይባላል? ተሃድሶው እውነት የሚሆነው ይህ ሲስተካከል ብቻ ነው።

 

6. በዘውገኛ ወረበሎች (በጋንጐች) ከመወረር አርነት ሲወጣ፡-
ምሣሌ ላንሳ። የንግዱ ማኀበረሰብ ወይም መንግስታዊ ነጋዴዎች ማለትም በዘርና በደም ንክኪ በሃብት የበለፀጉ ግን በመንፈስ የደቀቁ የግል እስር ቤት አላቸው ተብሏል። የነጋዴዎችን እስር ቤት ለመጀመርያ ጊዜ የጠቆሙት ጠቅላይ ምኒስትሩ ናቸው። የነጋዴው ያውም የጥቂቱ ማኀበረሰብ አባላት በሚገባ ኢህአዴግን ዘርሮታል። ወይም አሸንፎታል። ለዚህ ነው ባለፈው የተደረገው ተሃድሶ ብቅ ጥልቅ እንጂ ጥልቅ አይደለም የምንለው።


ተመልከቱ እነዚህ ነጋዴዎች የሃብት አፄዎች ናቸው። በጉልበታቸው አሸንፈው የወጡ። ወጥ ጉልበተኞች። ከእግር ጥፍር እስከ እራስ ፀጉር ማሸነፍን የታደሉ። መሸነፍ የማያውቁ። የፈለጉትን የሚያንቁ። ኢህአዴግን ያሸነፉ የንግዱ ማኀበረሰብ ጥገኛ አባላትን ማንነታቸውን እንዲህ አያቸዋለሁ። የሀብት ጉልበት ያመጣው አፄነት። ‹‹ከመንግስት ጋር በመጋባት የመጣ አፄነት››።
በዘውግ ከለላ የሰለጠነ አፄነት። በስውር የሃብት ምንጭ የመጣ አፄነት። እነዚህ የንግዱ ማኀበረሰብ አፄዎች ኢህአዴግን አሸንፈውታል። ያውም በዝረራ! በምን አወቅን? የአገሪቱ ቁንጮ ባለሥልጣን ነግረውናል! ኢህአዴግን የሚችለው የለም ይበሉን እንጂ አሸናፊው “ሙሰኛው ጠንካራ መሰረት” ያለው ነው ሲሉ ያውም አንድ እጃችን ታስሯል እስኪሉ ያደረሰ የሙስና አፄነት።

7. መንግስታዊ ሙስናን ነቅሎ ጥሎ ስናይ
ድርጅቱን ተቋማዊ ሙስናም ዘርሮታል። የዘውግ ሙስናም ወይም የመንደር ልጆች ሙስናም አንበርክኮታል። የአባላት (አድርባይ) ሙስና አንከባሎታል። የመርህ አልባ አባላት ድርጊት መሣቂያ መሣለቂያ ከዚያም መሣቀቂያ አድርጐታል። ታዲያ ድርጅቱን ማንም አይችለውም እንዴት ይባላል? ሁሉ የሚዘርረው ድርጅት ሆኗል እኮ!። knock out!!! ተሃድሶው ይህን ሽንፈቱን እንዲያሸንፍ ካልረዳው “ብቅ ጥልቅ” ተሃድሶ እንጂ “ጥልቅ” አይሆንም።

 

8. ዝግ በረኝነትን በተከፈተ በር ሲተካ፡-
ከዚህ ሌላ ኢህአዴግን ማንም የማያሸንፈው ድርጅት ነው የምንለው በነፃ ውድድር (ፉክክር) ተሸንፎ ስላየነው ነው። ለምን ተቀናቃኝ ፓርቲዎችን ያዳክማል? ለምን በጡንቻ ያምናል? በውይይት ተሸንፏላ!። ለመሆኑ ኢህአዴግ ውይይት ይወዳል? የኢህአዴግ ጉባዔ የጠንቋይ ስብሰባ ይመስል ባላውቃቢው ይናገራል። ከዚያም ካዳሚዎቹ አሜን ይላሉ። አስጠንቋዮች (ባለጉዳዮች) ተቀብለው ያስተጋቡታል። ጥልቁ ተሃድሶ ድርጅቱን ለውይይት ክፍት ካለደረገው ጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ አይደለም።


ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ማለት ይሄ ነው። “የጠንቋይ ማዕከላዊነት።” ፍርሃት ያጠቃው ድርጅት በመሆኑ ውይይትን ይፈራል። ውይይት ለኢህአዴግ የተጠመደ ፈንጅ ነው። ገብሩ አስራት እንደገለፁት እኛ ከተማ ከገባን በኋላ አዲስ ነገር የሆነብንና ለመቀበል የተሳነን ሁለት ነገር ነው ብለውናል።


አንደኛው ሥር ነቀል ተቋማዊ ለውጥ ማድረጋችን ሥህተት ነበር። ምክንያቱም ከሌላው ጋር ለመስራት የማንችል መሆናችንን ያሣያል ብለዋል። ይህም የመጣው ከጠባብነት የተነሳ ነው። የሽምቅ ውጊያ አስተሣሰባችን ይሉታል። ሁለተኛው ችግራችን የፖለቲካ አቅጣጫችን ለመወሰን ምልዓተ ህዝብን አለማሳተፋችን ነው ይላሉ።


እንደ እርሳቸው አባባል በድርጅት ውስጥ የበላይ አካላት አምነን ያፀደቅነው ለህዝቡ ማውረድ ነበር አካሄዳችን። ትክክለኛ ነው፣ ይበጅሃል፣ በማለት አቋማችንን ህዝቡ ላይ መጫን ነበር ባህላችን ብለውናል (ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ ገጽ 149)። ለዚህ ነው የጠንቋይ ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ነው የምንለው። ፀረ ውይይት አቋሙ አሁንም መሸነፉን ያሳብቃል። በህወሓት ቋንቋ ዝግ በረኝነት ማለት ይህ ነው።

9. ሰባዊ መብትን አክብሮ ሲገኝ፡-
ህወሓት /ኢህአዴግ ፀረ ውይይት ድርጅት ነው። ይህ ብቻ አይደለም ነፃነት የሚል ስም ይኑረው እንጂ ነፃነትን አያውቅም። “ነፃነትን የማያውቅ ነፃ አውጭም” ተብሏል። ነፃ ተቋማትን አጥፍቷል። ነፃ ሚዲያን ከሚገባው በላይ አዳክሟል። ሥራ አጥነት ተበራክቷል። ርሃብና ሞት በዝቷል። የአፈናና የጭቆና ምርቱ በዝቷል። የሰው ልጅ ሰብአዊ መብቶች አልተከበሩም። በመሆኑም ድርጅቱን ኢሰባዊነት አሸንፎታል። የሰው ልጆች መሰረታዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ ተንደዋል ወይም ከሚገባው በላይ ተገድበዋል። ገዳቢ ድርጅት ነው። “ከአምባ-ገነንነት” ወደ “አገር- ገነንነት” ተሸጋግሮአል። አምባ ሰፈር መቀመጫ ማለት ነውና። ኢህአዴግ ከዚያም አልፎአል። ይህን በፍጥነት እርምት ወስዶ እና አሻሽሎ ካልታየ ተሃድሶው ተሃድሶ አይሆንም።

 

10. ዙፋን ናፋቂነትን ሲያርም፡-
ህወሓት/ኢህአዴግ እንደመጣ ወይም አገሪቱን እንደተቆጣጠረ የኢህአዴግ ስልጣን “የዛፍ ላይ እንቅልፍ” ነው ብሎን ነበር። በነገሩ የሳቅን ብዙዎች ነበርን። አሁን ስንመለከተው ግን ኢህአዴግ ውስጥ ሥልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ የሚሆንባቸው ለአዋቂዎችና ጠያቂ (መጠይቃዊ) ባለሥልጣናት ብቻ ነው። ኢመጠይቃዊ ባለሥልጣን ከዛፍ ላይ እንቅልፍ ወደ ዛፍ ላይ ዙፋን ተሸጋግረዋል። ወይም ከዛፉ ላይ እንቅልፍ ወደ የስልጣን ሽርሽር ተሸጋግሯል። ዙፋኑን ነግሰውበታል። መውረድ፣ መውደቅ፣ መንገዳገድ የላቸውም። እነዚህን የመሣሰሉ ነገሮች የሌሉበት ሥልጣን ያለው በዚህ ድርጅት ነው። በስልጣን ማማ ላይ መክተም ብቻ ነው ዋና ግቡ። ድርጀቱ በዙፋን ናፋቂነት ተሸንፏል። እንዲያውም ሥርወ መንግስት መስርቷል። አንዳንዱ ሥልጣንና መስሪያ ቤትማ ርስት ሆኖ እየታየ ነው። ርስታዊ ባላባትነት አሸንፎታል። ስልጣንን ማጋራት አለማወቁ ብቻ ሳይሆን አለመፈለጉን እስካላረመ ድረስ አልታደሰም።

11. መንደርተኝነት ጥሶ ሲወጣ፡-
ድርጅቱ ሌሎችን በጠባብነት እየከሰሰ በጠባብ ሃይሎች የኮሰሰ ነው። መንደርተኝነት ይታይበታል። ከመጀመሪያውም ከሶሻሊስት አለም አቀፋዊ አስተምህሮ አፈግፍጓል። ከኢትጵያዊነትም አፈግፍጓል። ስልታዊ አይደለም አቋማዊ ነው። በትግራይ “የትግራይ ልጆች” ብቻ መታገል ይገባቸዋል የሚለው የበረሃ አቋሙ በቂ ማሳያ ነው። ከአለም አቀፋዊነት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነትም በታች የወረደ ነው። በመንደርና በቀበሌ ደረጃ የተዘወገ ነው። ኢህአዴግን የድርጅቶች ሹክቻ አሸንፎታል። በኢህአዴግ ውስጥ የበላይ ሆኖዓል እየተባለ የሚታማ ድርጅት አለ። የበላይ ካለ የበታች አለ። የበታቾቹ በራሳቸው ይህን አምነዋል። የበታችነት የሚሰማቸው የድርጅት አባላት ህዝቡ ይህን ሃሳብ ሲያነሳ እና ሲታገል ይደሰታሉ። በውስጣቸው የታጨቀውን የበታችነት የሚታገልላቸው ስለሆነ ነው። ሌላ አይደለም። ይህ የሚያስደስታቸው ይህ ትግል ምናልባት መዘወሩን አሽቀንጥሮ ወደ ላይ ያስፈነጥረናል ከሚል ሊሆንም ይችላል። ህወሓት ኢህአዴግን አሸንፎታል እየተባለ ይወራል። ይህ እስካልተስተካከለ ድረስ ተሃድሶው ዘበት ነው። ብቅ ጥልቅ ብቻ!

 

12. ተንበርካኪነትን ሲጸየፍ፡-
ኢህአዴግ ተንበርካኪ ነው። ይህን ያሉት እነ ሥየ አብርሃ ናቸው። የኒኦ-ሊብራሊዝም ተቃዋሚው ደንበኛ የኒኦ ሊብራሊዝም ሰለባ ሆኖ ተገኝቷል። ድርጅቱ በውጭ ሃይሎች ላይ የተንጠለጠለ ጥገኛ ድርጅት ነው። የተላላኪ ጦረኝነት (ፕሮክሲይ ዎር) የሚባለው የዚህ ደንበኛ ማሳያ ነው። አንድ ጊዜ ፕሬዝዳንት ኦባማ አሜሪካውያን ሶማሊያ ገብተው አይዋጉም አሉን።
ለምን ለሚለው ጥያቄ ሳይጠየቁ የሰጡት መልስ ኢትዮጵያውያን ጐበዝ ተዋጊ ናቸው አሉን። ይህ ተላላኪነት ነው። ተንበርካኪነት። የኢህአዴግ አንበሳነት በሰላማዊ አሮጊቶችና ህፃናት ላይ ብቻ ነው። ኢህአዴግን ህፃናት አይችሉትም። አሮጊቶችም አይችሉትም። ተንበርካኪነትን ግን ሊቋቋም አይችልም። ፖለቲካዊ ብልጠት አይምሰላችሁ። ሥሪት ነው። አባላቱ አልባኒያ ሆነዋል። አረብን መስለዋል። ሙስሊም መስሎ የሙስሊሙን አለም ለማሳመን የተላከው ግለሰብ ምስክር ነው። ነጭ ኮሚኒስት ሆነዋል። ነጭ ካፒታሊስትም መስለዋል። ሽታቸው ልውጥውጥ የሚለው ተንበርካኪ ስለሆኑ ነው። የሐሰት ፕሮፖጋንዳው ከዚያ የፈለቀ ነው። ድርጅቱ “ኢህአዴግ ማንም አይችለኝም” ለማለት የሞራል ብቃት የለውም። ወይንም በማሸነፍና በመሸነፍ መካከል ያለው የትርጉም ልዩነት አልገባውም። አሊያም እያሸነፈ የሚመስለው በራሱ ጩኸት በዝግ በረኝነት ባህሪው ታፍኖ የካድሬ ስብከት እያዳመጠ ነው።


ኢህአዴግማ መች ኢትዮጵያዊነትን ማሸነፍ ቻለ? ለ4ዐ ዓመት ሊያጠፋው ሞክሮ አልቻለም። ባንዲራውንና የባንዲራውን ክብር ለማጣጣል ሞክሮ ተሸንፏል። የባንዲራ ቀንና ህግ ያስወጣው መሸነፍ ነው። ዝረራ ይባላል። በነፃ ምርጫ ውድድር ተሸንፏል። 1ዐዐ% ያሸነፈው እኮ ብቻውን ድንኳን ወጥሮ ነው። ሰው አልባ ውድድር። ተሃድሶው ኢትዮጵያዊነት እስካለነገሰ ድረስ ተሃድሶ አይደለም።


በሽንፈት ሸለቆ እየተንከባለለ ማንም አይችለውም ማለት አይቻልም። ምናልባት በተሸነፈበት ሸለቆ ውስጥ ያገኛቸውን አንድ ሁለት ትንኞች በእግሩ ደፍጥጧል መሰል ኢህአዴግን የሚችለው የለም የሚባለው ለዚያ ነው።


እንደ እውነቱ ከሆነ ኢህአዴግ ከፍልስፍናውም ርቆ ርቆ አሁን ራሱም የለም። ኢህአዴግ የሚለው ምህፃረ ቃል ሲተነተን የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ማለት ነው። አሁን በዚህ ሥም የተመሰረተው ፓርቲ የኢትዮጵያ ሊሆን አይችልም። በዘውግ ስለተደራጀ የኢትዮጵያን ህዝብ ሙሉ ውክልና ለማግኘት የደነቀረው ቃል ይመስለኛል። ህዝቦች የሚለው አባላት ለማለት ካልሆነ በስተቀር የህዝብ ውክልናው ጥያቄ ውስጥ ነው። ዴሞክራሲው የለም። አብዮት ያካሄደ እንጂ አብዮታዊ (Progressive) ያልሆነ ድርጅት ነው። መስመሩ፣ አመራሩና አካሄዱ የተዛባና ተሃድሶ የሌለው ነው። ለዚህም የተሃድሶው የዘመን ርቀት አመላካች ነው። ለነገሩ በድርጅቱ ግንባር የለም። አዛዥና ታዛዥ ብቻ ነው ያለው። ናዛዥና ተገዥ ነው ያለው። የኢህአዴግ ታጋዮች እንጂ ኢህአዴግ የለም።


በነገራችን ላይ የህወሓት ታጋዮች እንጂ ህወሓት እንደ ድርጅት የለም። ትግራይ ነፃ ወጥታ አላየንማ! የኤርትራ ነፃነት ኤርትራን ነፃ አወጣለሁ ብሎ በተግባር ነፃ መንግስት መሥርቶ አይተናል። ህወሓት ግን መዝሙሩ እንጂ ገቢሩ የለውም። የሥነልቦና፣ የባህልና የታሪክ ትስስሩ አይፈቅድለትም። አልፈቀደለትምም። የትግራይ ሕዝብና መሬት የኢትዮጵያ መሠረትነቱን በቀላሉ የሚለቅ አይደለማ! በመሆኑም ህወሓት ተሸንፎአል። አላማውን አላሳካም። በኢህአዴግና በኢትዮጵያ ጥላ ሥር የተሸጐጠ ድርጅት ነው። አድርባይነት ይታይበታል። ነጥሮ አልወጣም። እንደ ብአዴን ‹‹ህዝባዊ ወያኔ ትግራይ ንቅናቄ (ህወትን)›› ሊሆን አልቻለም። ወይም ከነጻ አውጭነት ወደ ዴሞክራሲያዊ ግንባር መሸጋገር አልቻለም ሌሎችም ድርጅቶች ያሉ አይመስለኝም። በመሆኑም ኢህአዴግ ተብሎ የነበረው ድርጅት አባላት ያለ ኢህአዴግ ሥልጣን ማማ ላይ አሉ። ድርጅቱ ተሸንፏል የምንለው ለዚህ ነው። ጥልቁ ተሃድሶ ከዚህ በላይ ያሉትን ሃሳቦች ካልዳሰሰ ብቅ ጥልቅ ተሃድሶ እንጂ ጥልቅ ተሃድሶ ሊሆን አይችልም። ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› ይሉ ነገር እንዳይሆን!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
112 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1011 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us