ዛፉም አይወድቅ ምሳሩም ይለቀማል!!

Friday, 12 January 2018 17:17

 

ፋሲል ሣህሌ

 

አንድ የግል ጋዜጦች ወዳጅ የቱን ከየቱ አስበልጦ ለማንበብ ሲያማርጥ ጥሩ ሐሳብ መጣለትና "ተዓማኒ የሆነውን ብቻ አነባለሁ ተዓማኒውንም ለመለየት የተለያዩ ገጾቹን ማገላበጥና መመርመር ይኖርብኛል" ሲል ወሰነ፡፡ ለምርጫው መሳካት ጥሩ ውሳኔ መወሰኑ እያስደሰተው በእጁ የገባውን በጣም ታዋቂ ጋዜጣ ገጾች ገልበጥበጥ ሲያደርግ በትልቁ የተጻፈ የዜና ዕረፍት ርዕስ ተመልክቶ በተማረኩት ዐይኖቹ በችኮላ ታሪኩን ሲያነብ ሟች በስምም ሆነ በአባት ስም ሞክሼው ሆነው አገኛቸውና በሐዘኔታ ታሪካቸውን ማንበብ ቀጠለ፡፡ ከአረፍተ ነገር አረፍተ ነገር እየደመረ ቁልቁል የባለዜና ዕረፍት ሰውዬውን ታሪክ ሲያነብ ጽሑፉ የራሱ የህይወት ታሪክ መሆኑን ባለመጠራጠሩ "መቼ ነው የሞትኩት?" ሲል መልስ የለሽ ጥያቄ ሰነዘረ፡፡ ለካ ያም ትልቅ ጋዜጣ በትናንሾቹ ወሬኞች አሉባልታ ተደናብሮ ያልሆነ ዜና አትሞ ማውጣቱን ተረዳና "ከእንግዲህስ ማንንም….!!" አለ አሉ፡፡


ለዚህ አባባል መነሻ የሆነኝ ባለፉት 16 የሥራ ዓመቶቼ ከአስር ጊዜ በላይ ተመላልሼ ጎብኝቼው ስለማውቀው የለገደምቢ የወርቅ ማዕድን አንድ ተዓማኒነቱ የማያጠራጥር የሚመስል ቁመና ያለው ትልቅ ዓለም አቀፍ የዜና አውታር የዘገበውን ከእውነት የራቀ ሐተታ ማንበቤ ነው፡፡ “… ወርቅ መርዝ የሆነባት ምድር” በሚል ማራኪ ሐረግ የተጀመረው ዘገባ በሀገራችን ብርቅዬነቱን የማልጠራጠረውንና በነበረኝ አጋጣሚ የሥራ ሒደቱን በቃሌ እስከመያዝ ያህል በማውቀው ድርጅት ሕጋዊ ሰብዕና ላይ ከተራ ስም አጥፊነት የማያልፍ አሉባልታ ሲከምርበት ሰምቼና አንብቤ ተገረምኩ፡፡ መገናኛ ብዙኃን የመረጃ ምንጮች ናቸው ብለው ለሚያምኑ ሰዎች እንደዚህ ዓይነቱ ተቋም ኃላፊነት የሚሰማው ለሕዝብ፤ ለፖለቲከኞችና ለመንግሥት እውነታዊ መረጃን የሚያቀርብ አድርገው ይመለከቱታል፡፡


ከጥርጣሬ ለማምለጥ የታደለ አእምሮ ግን በማህበራዊ ድረ ገጾች ሁሉ የተዘገበውን እንደወረደ ከመቀበል ተቆጥቦ የወሬው ምንጭና የዜናው አቀባይ ማነው? ብሎ ይጠይቅና እውነታውን ይደርስበታል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በምንኖርባት ምድር ለዘመኑ ኢንተርኔት ተደራሽነት ያለው ማንኛውም ሰው የፈለገውን ዜና ፈጥሮ ማሰራጨት እንደሚችል ማጤን ብልህነት ነው፡፡ እናም አንድን ዜና ስናነብ ቢያንስ በሌላ አንድ ወይም ሁለት ተዓማኒነትን ባተረፉ የዜና አውታሮች ከነምንጩ የተዘገበ ዜና መሆኑን ማረጋገጥ ያሻል፡፡


ትዊተር የተሰኘው ድረ ገጽ ቅርብ ጊዜ ይፋ ባደረገው መረጃ ከ150 ሚሊዮን በላይ ንቁና የማያቋርጡ አባሎች እንዳሉት አሳውቆ እነዚህና ሌሎች ተጠቃሚዎች በየቀኑ ከ350 ሚሊዮን ጊዜ በላይ ሃሳባቸውን እንደሚያሰፍሩ ዘግቧል፡፡ ይህም አንድ ዜና በምን ያህል ቅጽበትና ስፋት በዓለም እንደሚሰራጭ ያመለክታል፡፡ ነገር ግን ወሬዎች በፍጥነትና በስፋት በአጭር ጊዜ ዓለምን ማዳረስ መቻላቸው የእውነትነታቸው ማረጋገጫ አይደለም፡፡ ፈረንጆች እንደሚሉትም "fast does not always mean accurate":: ለዚህም ነው ከላይ በጠቀስኩት ዘገባ ስሙ የተነሳው ድርጅት የተሰራጨበት መሰረተ-ቢስ ውንጀላና የአሉባልታ ዜና ማህበራዊ ኃላፊነትን አክብሮ፤ ለሰብዓዊ ፍጡር ደህንነትና ጤንነት ተጨንቆ፤ ለህግና ለህግ የበላይነት ቀበቶውን አጥብቆ ቆሞ ለሕሊና ፍርድ ብቃት ባለው ማረጋገጫ ከምንም በደል የጸዳ ንጹህ የማምረት ተግባሩን ጭቃ ሊለውሰው የሚችል እርግጠኛ ዜና መሆን ያልበቃው፡፡


ያ ትልቅና ግዙፍ የዜና አውታር ከ150 ሚሊዮን የተዊተር አምደኞች ዓይነት የአንዱን ፎቶግራፍ ለጥፎና የ350 ሚሊዮን በላይ የግለሰብ ወሬዎች ክምችት ውስጥ የሁለት ሶስቱን ተዓማኒ አድርጎ ዜናውን ሲሰራ ለትዝብት ከመጋለጥና ለክብሩ ወርደት ከመከናነብ ያለፈ ዕርባና ያለው ተደማጭነት ሊያተርፍበት አልቻለም፡፡ የእኔም ትዝብት የእዚሁ ውጤት አካል ነው፡፡ አሳዛኙ ደግሞ ያ የዜና ምንጭ ወሬውን ያገኘው ከግለሰብ መሆኑን አጢኖ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሌሎች ሰዎች ጭምር የተሳተፉበት አለመሆኑን አመዛዝኖ የወሬውን ትክክለኛነት ከማጣራት በፊት እከሌ እንደዘገበው ብሎ ማናፈስ የእምቧይ ካብ ከመከመር ያለፈ አለመሆኑን መረዳት ተስኗቸው ለግል ፍላጎታቸው እርካታ ብቻ የሚናወዙና "በወደቀ ዛፍ ላይ ምሳር ይበዛበታል" የሚል ብሂል ተጠቃሚ ለመሆን የተመኙ ብዙዎች መታያታቸው ነው፡፡


ደስ የሚለው ግን አሉባልተኞቹ ያለሙት ዛፍ አይወድቅም፤ ምሳሮችም ተለቅመው ያልቃሉ!! ከሶስት ዓመታት ተኩል በፊት የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ለአንድ የህትመት ጋዜጣ በላከው ስንኝ በተመሳሳይ አሉባልታዎች መሰላቸቱን ለማመልከት

"ደግሜ ደግሜ ስሰማው ሰለቸኝ፤
ታከተኝ አሁንስ በቃ እጅ እጅ አለኝ፡፡
የሰውዬው ነገር ምን ዓይነት እድል ነው፤
ሁሌ የምሰማው ዛሬም ነገም ያውነው፡፡
ቅንጣት ያላየውን ወሬ እየቀጠለ፤ ሰው ሁሉ ማማቱን ቢተወው ምናለ?" ሲል አንባቢን አናግሮ ነበር፡፡
ዘረፈው!! አፈሰው!! የማይባል የለ፤ አንዲት ሳንቲም ኪሱ መክተቱ የታለ?


ለዛሬው ርዕሰ ጉዳዩ መነሻ የሆነውን ሐሳብ ተንተርሶ ብዙ እየተባለ ለመሆኑና ትላልቅ ምሁራን ነን ባዮች ሳይቀሩ ለሚያናፍሱት የከንቱ ጥላቻ ወሬ በርካታ መረጃዎችን መደርደር ቢቻልም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች በወቅቱ የሰጡት አርኪ ምላሽ ስለሰጡበት መድገም አያሻም፡፡ በተመሳሳይ አሉባልታዊ ክስ ከዓመታት በፊት በጥቂት ግለሰቦች ተጀምሮ የነበረውን ዘመቻ ለመመርመር የቻለው የዓለም አቀፉ የአካባቢ ደህንነት ጥበቃ ድርጅት እንኳን ጉዳት ደርሶ ይቅርና ከማንም ቀድመው ጉዳት ሊደርስ ይችላል በሚል የበሰለ አመራር የጉዳት ምንጭ ሊሆን የሚችሉ መሰረቶችን በማስወገድና ከዚያ ያለፈ እንኳን ቢፈጠር ከጥርጣሬ ነጻ ለመሆን የፋብሪካውን ዝቃጭ በዘመናዊ መንገድ አጣርተው ለመጠጥ ንጹህ ውኃ መሆኑ ከመረጋገጡ በፊት ከክልሉ አጥር ውጭ እንዳይፈስ የተወቃሽ ኩባንያው የስራ ኃላፊዎች እያከናወኑ ያሉበትን አርአያነት ያለው ተግባር ተመስጋኝና ተሸላሚ አድርጎ ለዓለም ሕብረተሰብ አስተዋውቆት እንደነበር የዘገባዎች ማህደር አገላብጦ መረዳት ለሚሻ መጠቆሙ ይበቃል፡፡


ታዲያ ዛሬን ዛሬ ወለደውና አጋጣሚውን በመጠቀም ነገር ቆስቁሶ በወደቀ ዛፍ ላይ…. ዓይነት ከንቱ ምኞትን በመተው ከላይ በጠቀስኩት ስንኝ ቋጠሮ አስፍሬው እንደነበረው


ሰው ሁሉ………. እርግፍ አርጎ ትቶ የአሉባልታን ነገር፤
እውነትን ጨብጦ በውሸት ሳያፍር፤
ሥራውን አድንቆ ያለአንዳች ጥርጥር፤
ምናለ ቸሩን ሰው ባለሀብቱን ቢያከብር?
የእግዚአብሔር ስጦታ ጸጋው ሳይጎድልበት፤
ከችግር ተላቆ ዳግም እንድናየው ብንጸልይለት!!

እላለሁ፡፡ ምክንያቱም "ዛፉም አይወድቅም ምሳሮችም ተለቅመው ያልቃሉና" ነው!!
በቸር ይግጠመን

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
96 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1026 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us