የዓለም ባንክ ከግብፅ ጋር ቢያደራድረንስ?

Wednesday, 24 January 2018 14:29

 

በታደሰ ኃ/ስላሴ (ኢንጂነር)

 

የዚህ አስተያየት መነሻ የሆነው ረቡዕ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም “ግብፅ ሱዳንን በማግለል የናይል ውሃ ስምምነት ቀዳ በመጣሏ፣ እራሷን ጠለፈች” በሚል ርዕስ በፋኑኤል ክንፉ የቀረበ ፅሁፍ የዓለም ባንክ አደራዳሪነት መቀበል የለብንም የሚል መልዕክት በማንበቤ ነው።

 

ከህዳሴው ግድብ ጋር ተያይዞ ከግብፅ ጋር የዓለም ባንክ ቢያደራድረን ጉዳት አልታየኝም። ሶስት ሆነንም ተደራድረን ሁለትም ሆነን ተደራድረን ቁምነገሩ እውነቱ ላይ መድረሳችን ብቻ ነው። በኔ እምነት እውነቱ የሚከተለው ነው።


· ግብፅ ትጎዳለች፡- ኢትዮጵያውያኖች እየሰለጠንን በአባይ ውሃ መጠቀምን ስንጀምር ግብፆች ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ምንም ከልካይ ሳይኖርባቸው ሙሉ በሙሉ ሲጠቀሙበት የነበረውን የአባይ ውሃ፣ አንድ ጠርሙስ እንኳ ብንቀንስ መጎዳታቸው አይቀሬ ነው፤


· የህዳሴ ግድብ ሥራ፡- የህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት እየተሠራ ስለሆነ የኤሌክትሪክ ማመንጨት ሥራ ደሞ እንደግብርና ሥራ አንድም ጠርሙስ ውሃ ስለማያስቀርባት ምንም ጉዳት አያመጣባትም ግብፆች ይህን አያውቁም ማለት ፀሐይ ከምዕራብ እየወጣች እንደማለት ሲሆን ታድያ በዚህ ግድብ መሠራት ግብፆች ጩኸታቸው የበዛው ለምንድን ነው?

ጭንቀታቸው የሚከተለው ይመስለኛል።


· የግድቡ ሙሊት የአባይ ውሃን ፍሰት ለጥቂት ዓመታት ይቀንሳል፡- ይህንን ነጥብ ለአንባቢዎቼ በአጭርና በግልፅ ለማስረዳት ልሞክር፤ ማናቸውም ግድብ ሲሠራ `Dead storage እና live storage” የሚባሉ ከግድቡ ጀርባ ውሃን የሚያቆሩበት ክፍሎች አሉት። “Dead storage” ከግድቡ ጀርባ ካለው መሬት የተፈጥሮ ከፍታ ተነስቶ ወደ ላይ የተወሰነ ከፍታ ድረስ በውሃው የሚሞላው ከፍታ ሲሆን “live storage” የሚባለው ከDead storage በላይ እስከ ግድቡ ጫፍ ድረስ ያለው የውሃ ብዛት ሲሆን በ“Dead storage” የሚጠራቀመው ውሃ - ከዓመት - ዓመት አይንቀሳቀስም አንዴ ከሞላ - ለዘልዓለም ግድቡ ጀርባ ይኖራል። “live storage” በያመቱ ከሚዘንበው የክረምቱ 3 ወሮች የሚገኘውን እያጠራቀምን - ዓመቱን ሙሉ በተወሰነ መጠን በየሰከንዱ እየለቀቅን መብራት ለማመንጨት የምንጠቀምበት ውሃ ነው።


ግብፆች “ለDead storage” የምትጠቀሙበትን ውሃ ስታጠራቅሙ እንጎዳለን የሚሉት እውነት ነው፤ የሚፈስላቸው ብዛት ቀነሰ ማለት ነው፤ እኛም የሚሉትን ሰምተን ይህን ቦታ በአፈር፣ በደለል ብንሞላላቸው የምንስማማ ይመስለኛል። አፈሩን - ደለሉን - ከየት እንዴት ታመጣላችሁ ቢሉ እነሱ ወይም ያው ሀብታም አደራዳሪያችንም (የአለም ባንክ) ገንዘብ ካበደረን ልንሰራው እንችላለን። ለኛው ስራ ፈት ወጣቶች ሰፊ ስራ ተገኘ ማለት ነው። አፈሩም ከአገራችን ተዝቆ አያልቅም። በብዛት ይገኛል። ይህ “የDead storage” ቦታ በውሃ የሚሞላበት ምክንያት ውሃው በቀላሉ በዚያው ቦታ በመገኘቱ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ደሞ ውሃው ደለል ይዞ ስለሚሄድ በዚህ ደለል ብንሞላው ከግብፆች ንትርክ እንድናለን።

· የግብፆች የተደበቀ ጭንቀት
ግብፆች ዋናው ጭንቀታቸው ኢትዮጵያውያን ጉልበት እና ስልጣኔን ባዳበርን ቁጥር የአባይ ውሃ የሁላችንም ስለሆነ አብረን ወይም በእኩልነት እንጠቀም ለማለት እና መብታቸውን ማስከበር ይችላሉ ብለው ስለሚያስቡ ነው። ለኛ ጉልበት ከሚፈጥሩልን አንዱ የህዳሴ ግድብና ከሱ የሚገኘው የመብራት ኃይል መሆኑን በሚገባ ያውቁታል። የአባይን ውሃ የምንቀንስባቸው ውሃውን ለእርሻ ስናውለው ብቻ ነው። አሁንም በበለስ - በፊንጫ - በደዴሳ - ለእርሻ ብዙ ሜ/ኩብ ውሃን ለስኳር ምርት እየተጠቀምንበት ነው፤ በጎጃምና በጎንደርም ለሩዝ ምርትም ሳይቀር እየተጠቀምንበት ነው። ኢትዮጵያውያን ለግብርና ሥራ የአባይን ውሃ ስንጠቀም ለግብፆች ከሚደርሳቸው እየቀነስን መሆኑን ማንም ሰው ሊክደው አይችልም። ይህ ሀቅ ነው፤ ኢትዮጵያውያኖች ውሃን የመፍጠር ችሎታ ላይ አልደረስንም፤ ከዝናብ የሚወርድልንን ከመጠበቅ በቀር። ሌላ አማራጭ እስከ አሁን አላገኘንም፤ በጥንቆላም ቢሆን ዝናብን ከመዝነብ ማገድ እንጂ ማዝነብ እችላለሁ ያለን አስማተኛ የለንም።

 

· የዓለም ባንክ የማደራደር አቅም፡-
የኢትዮጵያ ባለስልጣኖች (በ3ቱም መንግስታት የነበሩት) ከዓለም ባንክ ብድር ማግኘት ሲያቅታቸው የሚሰጡት ምክንያት ግብፆች አስከለከሉን የሚል ነው። የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶችና ምሁራን የአስተሳሰብ ድክመታቸውን የሚሸፈኑበት የግብጽ ዲፕሎማቶችና የግብፅ ምሁራን በዓለም ባንክ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ነው የሚሉትን በብዛት አንብቤአለሁ። አሁንም በቅርቡ የውጭ ጉዳይ ዲፕሎማቶቻችን ሱዳን ከጎናችን ካልቆመች (ግብጽና - ኢትዮጵያ) ለብቻችን አንወያይም እንዳሉ አንብቤአለሁ፡፡ በመቀጠልም በአዲስ ዘመንና በሪፖርተርም ጋዜጦችም በዓለም ባንክ አደራዳሪነትን ብዙ ተችተዋል። ግን ይቅርታ አርጉልኝና የዓለም ባንክ አደራዳሪነት በነዚህ በነዚህ ምክንያቶች ኢትዮጵያን ይጎዳል የሚል አሳማኝ ነጥብ አላነበብሁም። እኔ ከነዚህ ሁሉ ምሁራን በተቃራው በመቆም - የዓለም ባንክ አደራዳሪነት ይጠቅመናል እላለሁና የዚሁ ጋዜጣ አንባቢዎች አባካችሁ ከጎኔ ቁሙና እነዚህን ምሁራን ነን ባዮችን እንሞግታቸው። ከግብፆች ጋር ንትርክ ከመግባታችን በፊት ጉዳዩን በጥልቀት አጥንታችሁ አቋም ያዙበት፤ ይህ ጉዳይ ደሞ ሁላችሁንም የሚመለከት ነው። የዓለም ማህበር የፈቀደልንን ውሃ መጠቀም አትችሉም ብለው ግብፆች ጦርነት ቢጀምሩ የምታልቁት እናንተ ናችሁና። መቼም እኔን በ77 ዓመትህ ዝመት አትሉኝም።

 

· የዓለም ባንክ አቋም፡- ዓለም ባንክ የአባይን ውሃ በጋራ ተጠቀሙበት የሚል አቋም እንደሚያራምድ አንብቤአለሁ። ብንተባበር ግብጽም፤ ኢትዮጵያም እያንዳንዳችን በዓመት እስከ 5 ቢሊዮን ዶላር ድረስ እንደምናገኝ በጽሁፍ አስቀምጧል። ይህም የሚሆነው ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ መብራት ኃይል አመንጭታበት ለግብጽ ብትለቅላት፣ ግብጽ ደሞ ለእርሻና ለቱሪስት ብትጠቀምበት የሚል ሲሆን ግብጽ የመብራት ኃይልን ከኢትዮጵያ ብትገዛ ኢትዮጵያ ደሞ የእርሻ ውጤቶችን ለግብጽ ብትገዛ ሁለቱም ከዚህ ከአባይ ውሃ በእኩልነት ተጠቃሚ ይሆናሉ የሚል ነው። ታዲያ ይህን ሀሳብ የሁለታችን ተደራዳሪዎች በጥሞና ሊያጤኑት አይገባም ትላላችሁ? ኢትዮጵያ በአባይ ላይ ቢያንስ አራት ቦታዎች ትልልቅ ግድቦች በመገንባት ብዙ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ለግብጽ ልትሸጥ ትችላለች፤ አንዱን ግድብ ለመሥራት ይኸው ኢህአዴግ ከመጣ ጀምሮ በ25 ዓመቶች አልጨረሰም፤ ለሌሎች 3 ግድቦች ሌላ 75 ዓመቶች መቆየት ተገቢ ነው ትላላችሁ? የካፒታል እጥረታችንን ሸፍነው ግብፆች እነዚህን 3 ግድቦች ቢገነቡልን ኢኮኖሚያችን የትናየት ያድጋል። የወጣት ሥራ ፈት ይጠፋል ያሉት ሲሚንቶ ፋብሪካዎች 100% ያመርታሉ። አሁን እኮ 10% አያመርቱም፤ “ሲሚንቶ ገዥ ስላጡ”። በዚህ ግብፆች እኛ አገር መጥተው ግድብ ቢሠሩ የምናገኘው ሌላ ጥቅም፤ አሁን ግብፆች የመብራት ኃይል ፍላጎታቸውን ለማሟላት ኑክለር ፓወር እየጀመሩ ነው። ይህን የኑክለር ፓወር የመብራት ኃይል ማመንጫ - በየቀኑ እየተቆጣጠሩ ነው። ይህን የኑክለር ፓወር የመብራት ኃይል ማመንጫ - በየቀኑ እየተቆጣጠሩ ማሰራቱ በጣም ከባድ ሥራ ነው። አንዱ ቢፈነዳ እነሱን ብቻ አያጠፉም፤ ለኛም ይተርፋል፣ ጎረቤታችን ስለሆኑ አብረን እንጠፋለን። ስለዚህ ከኒክለር ፓወር የመብራት ኃይል ከማመንጨት እንዲቆጠቡ ከኛ የአባይ ወንዝ ከሚያመነጨው እንዲገዙ ብንረዳቸው ሁለታችንም ለመኖር ዋስትና እናገኛለን። ጃፓን በዚህ የኑክሌር ፓወር ፍንዳታ ተወጥራ ተይዛለች። ጀርመን የኑክሌር ፓወር በአገራቸው እንዳይሰራ ብለው አውጀዋል።

· የዓለም ባንክ አደራዳሪነት የሚጠቅመው ፡-
1. የዓለም ህዝብ በቂ ምግብ እንዲያገኝ ለግብርና ሥራ ውሃ በብዛት ማግኘት አለበት፤ ይህን ውሃ የማግኘት ዘዴ፣ ጨው ያለውን የባህር ውሃ ወይም የከርሰ ምድር ውሃን ጨውን ከውሃ ውስጥ የማጥፋቱን ዘዴ በርካሽ ቴክኖሎጂ እንዲሠራ ማድረግ ነው። ይህ ቴክኖሎጂ ተገኝቷል - ግን አሁንም ብዙ ገንዘብ ያስወጣል፤ የገንዘብ ወጭን እንዲቀንስ በዩኒቨርስቲዎች ብዙ ምርምር ማድረግ ያስፈልጋል። የአውሮፓና የሰሜን አሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች በዚህ ችግር ላይ ያላተኮሩት በነሱ አገሮች ብዙ ውሃ ስላላቸው ነው። ጨረቃ ላይ መድረስ የቻለ ጭንቅላት ይህን ጨውን ከውሃ የማውጣት ሥራ በቀላል ዘዴ እስከ አሁን በሰሩልን ነበር። የዓለም ባንክ ለኛ ዩኒቨርስቲዎች ይህን ቴክኖሎጂ ርካሽ ለማድረግ - በቂ ገንዘብ ቢመድብልን - ብሩህ አእምሮ ያላቸው የኛ ወጣቶች ቴክኖሎጂውን ቢፈጥሩልን የአባይን ውሃ የሚፈለገው ይጠፋና ግብፅና ኢትዮጵያ በሰላም ይኖራሉ። የዓለም ባንክም በገንዘቡ ለኛ ወጣቶች ሥራ ይፈጥራል።


2. በዲሞክራቲክ ኮንጎ ያለው የኮንጎ ወንዝ እስከ 3ሺ ቢልዮን ሜትር ኪዩቭ ውሃ አትንቲክ ውቅያኖስ በየዓመቱ እያፈሰሰ ነው። ይህን ሁሉ የሚያነታርከን የአባይ ወንዝ ደሞ ከ100 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ያነሰ የዓመት ፍሳሽ ያለው ወንዝ ነው። የአፍሪካ አገሮችና አለም ባንክ ተባብረን እነዚህን ሁለት ወንዞች ብናጣምር የሰሀራ በርሀን ሳይቀር ለእርሻ ማዋል ይቻላል። የኛም ኡጋዴንና መላው የሱማሌ አገር ውሃ ቢያገኝ ቻይናንና ህንድን ሊመገብ የሚችል በቂ ለም መሬትና በቂ ፀሐይ አለው። የኢትዮጵያ ሀይቅ በኩል ወደ ኡጋዴንና ወደ ሱማሌ ኬንያ በመውሰድ በአጭር ጊዜ የሱማሌን ህዝብን በእርሻ እንዲሰማራ ቢደረግ፤ አልሸባብ ከአህጉራችን ይጠፋል። አልሸባብም ሆነ በኮሀራም ጣፋጭ ኑሮን ካልቀመሱ ሞትን አይፈሩም፤ በጥይት እነሱን መጨረስ በጭራሽ አይቻልምና የዓለም ባንክን ገንዘብ ያላቸው እነቢልጌትስ ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖሩ ግብፅንና ኢትዮጵያን በማደራደር ከግጭት ሊያወጡን ይገባል። በነዚህ ምክንያቶች የአለም ባንክ ግብጽና ኢትዮጵያን ያደራድር እላለሁ።

· ለኢትዮጵያ ምሁራኖችና ለኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች፡-
በዚህ የዓለም ባንክ በግብጽና በኢትዮጵያ ድርድር ውስጥ መግባት የለበትም ያላችሁ አምባሳደር ኃይሉ ወ/ጊዮርጊስ፣ አቶ ፈቅ አህመድ፣ ዶ/ር ደረጀ ዘለቀ እንዲሁም አቶ ዳደ ደስታ፣ ዶ/ር አታክልቲ ረዳ፤ አቶ ብርሃኑ በላቸው ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ እውቀታችሁን ስለአካፈላችሁን ምስጋናዬ ይድረሳችሁ። ሆኖም ከናንተ ምክር በተቃራኒው በመቆም የዓለም ባንክ በዚህ ድርድር ውስጥ በሰፊው ይግባ እያልሁ እሞግታችኋለሁ። ምክንያቶቼንም ከላይ አስረድቻለሁ። ህልም ፈርቶ መኝታ አይቀርም የሚባለውን የአበው አነጋገር እነዚህ ላይ እየጠቀስኩ በህዳሴ ግድብ ጉዳይ የግብጽን አቋም ሙሉ በሙሉ እናከሽፋለን ካላችሁ፣ ግብጽና ኢትዮጵያ በዓለም ባንክ አደራዳሪነት አንድ ለአንድ ቢሟገቱና - የዓለም ጋዜጦችና - ቲቪ - ሬድዮ ሰፊ ሽፋን ቢሰጡት እውነተኛው ትክክለኛው አሸናፊው ይታወቃል። ኢትዮጵያዊያን የተረታነው የተባበሩት መንግስታት የአባይን ውሃ በጋራ ተጠቀሙ ብለው በግንቦት 21 /1991 ሲወስኑ ነው። ለዚህ ውሳኔ ተገዥ መሆን የግድ ሲሆን በመቀጠልም በዚሁ ውሳኔ የሚደርሰንን የውሃ ብዛት ማህበሩ እንዲያሳውቁንና እንድንጠቀምበት የግብጽና የኛን ጉዳይ ለዚሁ ማህበር በማቅረብ የሚሉንን ብንሰማ፤ ግብፆችን እራቁታቸውን እናስቀራቸዋለን። የአምባሳደር ኃይሉ ወ/ጊዮርጊስ ብዙ ገፆች ያሉት መጽሐፍ በማናቸውም ዩኒቨርስቲ ለተማሪዎች መማሪያ እንዲሆን እየጠቆምኩ፤ የአባይን ወንዝ ምንነት በዝርዝር ለመረዳት፤ ለማጥናት ሲጠቅም የግብጽን ሙግት ለማክሸፍ ግን በካይሮ ኤምባሲ የሚገኙት በአቶ ግርማ የተፃፈው ትንሽ ገፅ ያለው መጽሐፍ ለሙግታችን ብዙ ጠቃሚ ሀሳቦች እንዳለበትም እጠቁማለሁ።


የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ህዝብ ለህዝብ በሚል ፈሊጥ የግብፆችን ልብ /የፕሬዝዳንቱ ሳይቀር/ ለማማለል በባህልና ቱሪዝም ሚኒስትራችን በእነ ዶ/ር ሒሩት ወ/ማርያም መሞከሩም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም እየጠቀስኩ በዚህ የክርክር ሸንጎ እኔም ሽንጤን ገትሬ ብዕሬን አሹዬ አለም ባንክ ማደራደሩ ጠቃሚ ነው የሚለውን ሀሳብ ይዤ እቀርባለሁ።


ኢትዮጵያ በዓለም ህዝብ የመጨረሻ ደሀ የሆነው ጥራዝ ነጠቅ ትውልድ፤ እንደ አቶ ፋኑኤል ያሉት፤ የኒዮ - ሊብራል - የኢኮኖሚ አስተሳሰብን ውድቅ አድርገው የሶሻሊስት የኢኮኖሚ አስተሳሰብን እስከዛሬ የሙጥኝ ብለው በመያዛቸው ነው። የኢህአዴግ ፈጣሪ ወደ ኒዮ-ሊብራል የኢኮኖሚ አስተሳሰብ ሊያስገቡን ሲሞክሩ ሞት እንደቀደማቸው አንባቢዎቼ ተረዱልኝ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
85 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 327 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us