አጤ ኢህአዴግ እና ኢትዮጵያ በነጋድራስ ገብረ ሕይወት ሃሳብ ላይ ተመርኩዞ የተሰጠ ምክረ ሃሳብ

Wednesday, 24 January 2018 14:22

 

- ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ለካ ሊቅ ኖረሃል!!!!

 

በአንድነት ቶኩማ

 

አሁን ሰሞኑን እንኳ የነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝን መጽሓፍ ሳነብ እጅግ ገረመኝ። የገረመኝ ምክር የማይወድ ሕዝብ ጥበብ እንዴት ሊጎድለው እንደሚችል ስለጠቆሙ ነበር። የመንግስት ሹመኞች ወይም ገዥዎችም ከእንደዚህ ዓይነት ማህበረሰብ ስለሚወጡ ችግሩን ያባብሰዋል። በመጀመርያ ‹‹አጤ ኢህአዴግ›› ያልኩበት ዋናው ምክንያት ዙፋኑ ላይ እንደወደዳችሁ ለብዙ ጊዜ ስለከተማችሁበት ነው። ባታውቁት ነው እንጂ ወደ አጤነት ከተሸጋገራችሁ ቆይታችኋል። እናንተም ይህን በደንብ የሚያሰረዳችሁ ሳያስፈልግ ወደ ልቦናችሁ ብትመለሱ ይገለጥላችኋል። እንዴት መቶ ፐርሰንት ልናሸንፍ ቻልን ብላችሁ ብትጠይቁ እንኳን መልሱ በቀላሉ ወደ አጤነት መሸጋገራችሁን ያሳያል።


ወደ ቁም ነገሩ ስመጣ ትንሽ የነጋድራስ ገብረ ሕይወትን ሃሳብ ላንሳ። ‹‹ የኛ የኢትዮጵያውያን ታሪክ እጅግ ያሳዝናል። ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ፍፁም የሆነ ሰላም አግኝተን አናውቅምና። የተወደደች አገራችን፣ ዘወትር በጠላቶች ተከባ ስትኖር ነበረች…›› ይላሉ። ይህ እንግዲህ ከመቶ አመት በላይ የሆነው ጽሁፍ ነው። ያሳዝናል! ። ይሻሻላል የምንለው ነገር ሳይሻሻል ለማየት በቅተናል። እንዘጭ እምቦጭ እንዳሉት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም መሆኑ ነው። የዚህ ዋናው ምክንያት አለመስማማት ነው ይላሉ ነጋድራሱ ሲተቹ። ‹‹እግዚአብሔር ብዙ በረከት ሰጥቶናል።›› (19) ብለው ያደንቃሉ።


ውዳሴውን ይቀጥሉና ‹‹ትምሕርትን በቶሎ መቀበል የሚችል ልቦናና የጦረኛን ባሕሪ፣ ማለፊያና ሀብታም አገርንም።›› ይላሉ። ኢትዮጵያውያንን ሲያደንቁ ነው። ግሩም ነው የግሩም ግሩም። ቀጥለውም ሃያሲነታቸውን ተጥቅመው ሕጸጻችንን አንጥረው ሲያወጡ እንዲህ ይላሉ። ‹‹ካለመስማማታችን የተነሳ ግን ሌሎች ሕዝቦች በአእምሮና በጥበብ እየበረቱ ሲሄዱ እኛ ወደ ኋላ ቀረን።›› ይሉናል።


ዛሬስ የምናየው ይሄው አይደለምን? የብሔር ብሔረሰብ ግጭት ምንድን ነው? ወይም ከምን የመጣ ነው? የደናቁርት ስብስብ ሲደራጅ የመጣ አይደለምን? ብዙዎቹ እኮ በጎሳ መዘናጠሉ መሰልጠን መስሎታል። ወይስ ማደግ መሰላችሁ? ወይስ መሰልጠን? ወይም የእርስ በርስ ግጭቱ ከየት የፈለቀ ነው? አንድም ካለማወቅ ሁለትም አፄዎች ማማው ላይ ለመሰንበት የሸነቆሩት ነገር ነው። የደናቁርት ቡልደዘሮች ብሎ ነበር ሎሬት (ብለቴን ጌታ) ጸጋዬ ገብረ መድሕን። ወይም በቀቀን ካድሬዎች በቀን (በጠራራ ፀሐይ) የጊዜው (አዲሱ) ወደ ማማ የመውጫው መንገድ መስሏቸው የሰበኩት ዲስኩር አይደለምን? “ሃይ የሚል የሌለበት አገር እኮ እንደ ጋለሞታ ቤት ነው” ያለው ማን ነበር? ብቻ ብሎታል።


አሁን ባለፈው እንኳ ‹‹አፄው ኢህአዴግ›› የፖለቲካ እስረኞችን ለመፍታት ያወጣውን መግለጫ አይቼ ተደንቄበታለሁ። መግለጫውና ምህረቱ በስንት መከራ ያወጣው መሆኑን ሁሉም ይገነዘበዋል። ቃሉ እና መግለጫውስ ስንት ጊዜ ተለዋወጠ? የመለዋወጡ ምክንያቱ ምንድን ነው ብሎ የሚጠይቅ የለም ማለት ጠያቂ የለም ማለት አይደለም። አስተውሉ!። ‹‹የላም ችግሯ አንድ ወቅት ጥጃ እንደነበረች መርሳቷ ነው›› ይባላል። ታጋዮች እንደነበራችሁ ጭራሽ ወደ መርሳት ደረጃ እንደደረሳችሁ ሳስበው እደነቃለሁ። ዙፋኑ ነው ያስረሳችሁ። ወይም ማማው። ሕዝቡንም አታምኑም። ሕዝባዊ ወገንተኛነት የምትሉት የት ሄደ? ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ‹‹እርስ በርሳችን መጠራጠርን አልተውንም›› እንዳሉት ሆኖ ነው እንጂ። ጥላችሁን መጠርጠር። ካድሬዎቻችሁን መጠርጠር። ራሳችሁን መጠርጠር። ጓዶቻችሁን መጠርጠር እንደ ዕውቅት ይዛችሁታል።


አሁን ማን ይሙት በኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኛ የለም? እኛም እናውቃለን እናንተም ታውቃለችሁ። ደግሞስ ሰሞኑን የፈታችኋቸው ሰዎች መፈታት በመጀመሪያ እናንተን ትልቅ ሰዎች እንደሚያደርጋችሁ ዘንግታችሁት ነውን? ይህ እኮ ወደፊት ለእናንተም ይጠቅማል። ቢያንስ ልጆቻችሁን ከመሸማቀቅ ያድናቸዋል። የገዥዎቻችን የእናንተው ልጆች በምን ያህል መሸማቀቅ እንደሚኖሩ ልጆቻችሁን መጠየቁ ብቻ ያስረዳችኋል።


ሰሞኑን ሰው ሁሉ የተገረመው እና የተደሰተው በመግለጫችሁ ነው ጥሩጡራን (ተጠራጣሪዎች) እንዳሉ ሆነው። በፈታችኋቸው እስረኞችም ቢሆን የተደሰተ አይጠፋም። ጥሩ ጅምር ነው። በፈለጋችሁበት ጊዜ ዜጎችን እየለቀማችሁ ወይም ቋንቋችሁ አልጣመንም በማለት ብቻ ማጎሪያ ውስጥ መክተትና ቸር መሆናችሁን ለመግለጽ መፍታት ወይም መልቀቅ ስራዬ ብላችሁ እንዳትይዙት። የሞኝ ዘፈኑ አንድ ነው የሚለው ተረት ከደረሰባችሁ ቆይቷልና ነው። ሁሉ ነገራችሁ ከመለመዱ የተነሳ እቅዳችሁን የማያውቀው ያልተጸነሰ ሰው ብቻ ነው። የሚድኸው ሕጻን ልጅ እንኳ ያውቀዋል። ማጋነን እንዳይመስላችሁ።


ዜጎች የእናንተ ቸርነት የማሰያ መስዋዕት ሊሆኑ አይገባም። መጀመሪያ መታስር ያልነበራባቸውን የህሊና ሰዎች ማሰር የለባችሁም። አግቶ መልቀቅን ባህል አታድርጉት። የአፈናው መንገድ ያለቀ ይመስላል። ሕዝቡ ግልጽ መልዕክት አስተላልፏል። ከዚህ በኋላ በማፈን መቀጠል አያዋጣም። አለማጎርን ባህል አድርጋችሁ ለመሸመት ሞክሩ። ቢከብዳችሁ እና ከተጠመቃችሁበት ከባህላችሁ ውጭ ቢሆንም አዲስ ነገር አንድ ቀን ነው የሚጀምረውና ጀምሩት። እኛም የማታውቁትን መንገድ ስትጀምሩ “ወፌ ቆመች” እያልን እንረዳችኋለን። ባንረዳችሁ እንኳ እንረዳችኋለን።


ሰሞኑን የ100 ዓመት እድሜ ልደታቸውን ያከበሩት በአቶ በለጠ ገብሬ በተጻፈ ‹‹በእድሜ ጎዳና ላይ የጉዞ ትዝታ መድብል ሁለት›› በተሰኘው መጽሐፍ አንድ ቁም ነገር አነበብሁ። በ1970ዎቹ ዓ.ም. የደርግ ሥርዓትን በመቃወም ተከሰው ከታሰሩ በኋላ ደረሰብኝ ያሉትን ሳነብ አዘንኩ። “በውሃ የተሞላ ላስቲክ በብልቴ ላይ አንጠልጥለው እንደሚገርፉኝ ሲዝቱብኝ ነበር” ብለዋል። እኒህ የተከበሩ አዛውንት የደረሰባቸውን ስድብ ለክብራቸው ሲሉ አፈወርቅ ገብረ የሱስ የተባሉት የጦቢያ ደራሲ እንዳሉት ‹‹አጠይመው›› ነገሩን ነገሩን እንጂ የደረሰባቸውስ እጅግ አጸያፊ ነበር። የሚገረመው መንግስቱ ኃይለማርያም ናቸው አሉ ‹‹እኝህን ሽማግሌ ምን አድርጉ ነው የምትሏቸው ይለቀቁ ብዬ አልነበረም?›› ብለው ተቆጥተው ያስፈቷቸው።


ታዲያ ምኑ ገረመኝ መስላችሁ? ሃብታሙ አያሌው የተባለውም ሰው ‹‹ከህወሓት ሰማይ ሥር›› በሚለው መጽሐፍ ውስጥ የደረሰበትን አንድ አይነት ነገር ገልጾ መገኘቱ ነው። በነገርየው ላይ ውሃ ማንጠልጠሉን እንዳሉት አቶ በለጠ ገብሬ። እናንተ ግን ይህን ከየት ተማራችሁት? ደርግ ያደረገውን ማድረጋችሁ ገርሞኝ ነው። ማስተባበል ብተሞክሩ የሚሆን አይደለም።


ተመልከቱ ሀብታሙ የተባለው ሰው ከአቶ በለጠ ገበሬ ጋር ያለቸውን የእድሜ ልዩነት። ከ70 ዓመት በላይ ነው። በእነዚህ ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብ ለውጥ አለማምጣቱን ነው የሚያሰየው። በተለይ ደግሞ ገዥዎቻችን። ደግነቱ ማዕከላዊ መዘጋቱ ነው መባሉ ነው። ይበል ያስብላል። ደግ ነገር ነው። መግላጫው ግን መሻሻል አለበት። ‹‹ደርግ 17 ዓመት ኢህአዴግ 27 ዓመት ያሰቃየበት ቦታ ወይም እስርቤት ሊዘጋ ነው›› መባል አለበት።


ሰሞኑን ከተፈቱት እሰረኞች ውስጥ በጣም ሰላማዊ የሆኑ ሰዎች ይኖራሉ የሚል ግምት ይኖረኛል። ከነዚህም ሰዎች ያልተፈቱ ብዙ አገር ወዳድ ነገር ግን ኢህዴግን የሚጠሉ በመሆናቸው የታሰሩ ይኖራሉ። ለምሳሌ የአማራ ልጆች በየቦታው ታስረው ወይም ታጉረው ይኖራሉ ይባላሉ። የሚታገልላቸው ስለሌሌ ነው እዚያው የሚቆዩት እየተባለም ነው። ይህ እውነት ከሆነ አማራን ለይቶ የማጥቃት እርምጃ የሚያዋጣ አይመስለኝም። አጤነት አንድ ቀን ይሟሟልና ደጋግሞ ማሰብ ይገባል። በዚህ ሥርዓት ውስጥ ተለይቶ ግፍ ደርሶብናል የሚሉ አማሮች ልጆቻቸውን ለከርቼሌ አሳልፈው ሰጥተው አንቀመጥም እንዳይሉ ማስተካከያውን በቶሎ ማድረግ ይገባችኋል። ስለ ደርግ ጥላቻ እጁን ዘርግቶ ተቀብሎ አቅፎ እና ደግፎ ዘር ማንዘራችሁን ሲረዳ የነበረ ሕዝብ የአማራው ሕዝብ ነበር። የተለየ ጥቃት ቢደርስበትም ባለውለታ ሕዝብ ነው እያሉ ነው።


ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ስለ ምኒልክ ፈራ ተባ እያሉ እውነቱን ለመናገር አስበው እንዲህ አሉ ‹‹እንግዲህ ከጸሐፊው ልብ ውስጥ ፍርሃት ተነሳ፣ የሽዎችን (የሸዋ ሰዎችን ለማለት ነው) አሳብ ሊመረምር ነውና። ዘመናይ ሁሉ ሊያመሰግኑት እንጂ ሊወቅሱት አይወድም። ስለዚህ የሸዋ ሰው ሳይቆጣ አይቀርም። ነገር ግን ሰውን ፈርቶ እውነቱን የሚሸሽግ ሰው እንደ ወንድ ይቆጠራልን፤ መንግሰቱን የሚወድ ሰው ያ ቅዱስ ቅዱስ የሚለው አይደለም ጥፋቱን ይገልጽለታል እንጂ።›› (ገጽ 12)። ዛሬም ከጸሐፊው ከእኔ ልብ ፍርሃት ተነሳ። እውነቱን እንነጋገር። አጤዎች ያመጸውን ነው የምትፈሩት። ሰላማዊ ሰውን አትፈሩም። የጎጃም ሕዝብ በእናንተ ጊዜ ብዙ መድሎ ይደርስብታል እየተባለ ነው። ሸዋስ ቢሆን የቂም በቀል ማሳረፊያ ሆኖ የለምን? ጎንደርም እንደዚያው። ኦሮሞውም እንደዚያው። ወሎም ያው ነው። ወደ ደቡብ ጎራ ያላችሁ እንደሆነም ያው ነው። ለኢትዮጵያ ከሚታገሉ ሕዝቦች ውስጥ እኮ እነሱም አሉበት። ልጆቻቸውን ፍቱ። ነገድራስ “ጎጃሜዎች ለአጼ ምኒልክ የተገዙት በምኒልክ ደግነት ምክንያት ነው” ብለዋል። ምነው ደግነታችሁ ለአማሮች ራቀ? ለአዲሱ ትውልድ ቂም እያቀባለችሁት መስሎ ስለታየኝ ልምከራችሁ ብዬ ነው። “የአባይ ዳር ጉማሬ፤ ወጥቶ አደረ ዛሬ” ይባል የለምን? ከእስር ቤት ይውጡ። ምክር ነው!። አለመስማት መብታችሁ ነው። ያለ መስማት መብታችሁ ግን ተከብሮ የሚቆይ አይመስለኝም። ውዴታን ያልተቀበለ ግዴታን ሊያጣጥም ተፈጥሮ ራሷ ታስተምራለችና።


የኢህአዴግን ነገር ስንመረምር ብዙ ግድፈት ይታይበታል። ብዙ ሰዎች ለፖለቲካው ብሎ ነው እስረኞችን የሚፈቱት ይላሉ። ልክ ነው። መቼም ለጽድቅ ብሎ አልመሰለኝም። ጥሩ ነዋ! ምን መጥፎ ነገር አለው። ኢህአዴግ ምህዳሩን አስፍቶ ካሸነፈ ምን ችግር አለ? የእርሱ ችግር እኮ ብቻዬን ልጋልብ ማለቱ ነው። ኢህአዴግ አገሪቱ ሰፊ መሆኗን ያወቀው አልመሰለኝም። ሰፊ ናት። ተቃዋሚዎችም ብቻችንን ያለ ኢህአዴግ እንሩጥ ማለታቸው እኮ ኢህአዴግነትን ተዋሱ ማለት ነው። ልክ አይደለም።


ከሁሉ ኢህአዴግ “አፈር ልሼ እነሳለሁ” የሚለው ነገሩ ነው የማያገባኝ። ለምን አፈር ይልሳል? መነሳቱን ለማድመቅ ሲል ነው ይህን የሚለው። አንዱ ካድሬ የተናገረውን በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የኢህአዴግ ካድሬ ሁሉ የተቀበለው ሃሳብ ነው። ኢህአዴግስ ሁልጊዜ ለምን አፈር ይልሳል? ደግሞ ይህን መናገሩ ነው የሚገረመኝ። አፈር መላሱን ሞያ አድርጎታል። ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ማለት ነው። ወይም አድሮ ቃሬያነት። ከፈለጋችሁ ከርሞ ጥጃ በሉት።


የኢህአዴግ ድርጅት ምንችክና ያጠቃዋል። ስንቱን ፖሊሲ መሰላችሁ ‹‹በመቃብሬ ላይ ነው የሚለወጠው›› የሚለው። ከመቀበር መለወጥ አይሻልምን? ካልተለወጡ መቀበሩ የት ይቀራል ብለው ነው። ወይ ፖለሲውን እያጠኑ መለወጥ ወይ መቃብርን ተገትሮ መጠበቅ ነው። ኢህአዴግ መቃብሩን እየቆፈረ መሰለኝ። ሞት ጠበቅነውም አልጠበቅነውም ይመጣል እኮ። ሞትን የምናሸንፈው አርቆ አስቦ፣ ርዕይን ከትውልድ ወደ ትውልድ በማሸጋገር ነው። ከዚያ ውጭ አፈር እልሳለሁ፣ መቃብሬ ላይ የሚለው ንግግሩን የኢትዮጵያ ሕዝብ “አድርጎት ነው” ሲል ይከርምና ተግባራዊ እንዳያደረገው እፈራለሁ። እናንተስ አፈር መላስ የሚለውን ቃል ምነው ደጋገማችሁት እሳ? ሌላ ምሳሌ የላችሁምን? ቢያንስ ይቺን አባባል እንኳ ቀይሯትና በራሳችሁ የቆማችሁ መሪዎች መሆናችሁን አሳዩን።


አጤ ኢህአዴጎች ጽንፈኛ ዲያስፖራ የሚሉትን ጸያፍ ቋንቋ እርግፍ አድርገው መተው አለባቸው። ከተው በኋላስ? መደራደር። እስኪ ማን ይሙትና ነው የኢህአዴግ ካድሬ የሆነ ልጁን ዲያስፖራ ያላደረገ ማነው? ‹‹ስንተዋወቅ አንተላለቅ›› እንዲሉ ነው። አጤዎች ትንሽ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት የመከሩትን ላሳያችሁ ‹‹ጃፓን የሚሉት መንግስትስ እንኳን ተምሮ የመጣለትን ሊያባርር ወደ ኤሮጳ ሒዶ የሚማርለትን ሲያገኝ በገንዘብ ያግዘው ነበር። የትምህርትን ቤት እከፍልለታለሁ ብሎ የሚመጣውንም የኤሮጳ ሰው እንኳን ሊከለክል በገንዘቡ እንዲመጣለት ይዋዋለው ነበር። ስለዚህም ሕዝቡ አይኑን ከፈተ፣ ሀብታምም ሆነ፣ በረታም፣ ታፈረም። ቺናና (ቻይና ማለታቸው ነው) እስያም የሚባሉ ሁለት መንግሰታትም የጃፓንን መንገድ በብዙ ትጋት መከተል ጀምረዋል።›› ይላሉ።


ተመልከቱ ቻይና የት እንዳለች። ጃፓንማ የገነት ያክል ርቃናለች። እንኳን ተሳካላቸው!! ልብ አድርጉ አጤዎች! ነጋድራስ ይህን ያሉት ታላቅ ስለሆኑ ነበር። ራስ እምሩ ስለ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ሲናገሩ ‹‹እንደርሱ ያለ የተማረ ሰው በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ስምንት አይሞሉም›› ያሏቸው ሰው ናቸው። የሚገርመው በ20ዎቹ መጨረሻ ዕድሜ አካባቢ ውስጥ ሆነው ነው ይህን ያሉት። እናንተ ሌላው ቢቀር በትግል ውስጥ ብቻ ከ40 ዓመታት በላይ አሳልፋችኋል። በ20ኛው ዕድሜ አካባቢ ወደ ትግል ያስገባችሁን እውቀት ያለ መሻሻል ልትኖሩበት እንዴት ታስባላችሁ? ያኔ የምትጠሉትን አካባቢ አሁንም ትጠሉታላችሁ። ለምን? እትለወጡማ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” ነው!።


በውጭ አገር የሚኖሩ የአገራችሁን ልጆች ቶሎ ብላችሁ ታረቁ። እነሱ አዋቂዎች ናቸው። አገርን ይጠቅማሉ። አገሬውን አሳዳችሁ የፓክሲታን፣ የህንድ እና የቻይና “ምራጭ” መሰብሰቡ የሚያዋጣ አይመስልኝም። አይ አይሆንም ብላችሁ ቻይና ምናምን ብትሉ አለማወቃችሁን ነው የሚያሳየው። እናንተ ጽንፈኛ የምትሉት ስደተኛው እኮ ነው የአብዛኛውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ኑሮ የሚደጉመው። ልጆቹን እያዋረዳችሁ እናንተን የሚመርጥ ይመስላችኋልን? ለምሳሌ ያለፈው መንግስት የፖለቲካና የወታደሩ ልጆችን ያወቃችኋቸው አልመሰልኝም። ተጽኖአቸው ጠንካራ ነው። ላሳያችሁ።


ያለፈው መንግስት ጊዜ የነበሩ የወታደሩን እና ኢሠፓ አባላትን ወደ አምስት ሚሊዮን ነበሩ ብለን ብንወስድ እና የእነሱ ልጆችን ሶስት ሶስት ብናደርገው አስራ አምስት ሚሊዮን ደጋፊ አላቸው ማለት ነው። የእነሱ ልጆችን ሶስት ሶስት ብናደርገው አርባ አምስት ሚሊዮን ተሳታፊ ያልሆነ ነገር ግን የእናንተ ተቃዋሚ አለ ማለት ነው። በዚያ ላይ በተለያዩ ምክንያት ከእናንተ ጋር የተጣላ ግለሰብ እና ቤተሰብን ጨምሩበት፣ የዲያስፖራው ዘመድ አዝማድ ሲጨመርበት ስንት ደጋፊ ይኖረናል ትላላችሁ? ‹‹ያው በገሌ›› እንዳለቸው ድመት ያው እናንተ አለን ያለችሁትን አምስት ሚሊዮን አባላት ብቻ ይዛችሁ መግዛት አትችሉም። በዚህ ስሌት መሰረት ቢያንስ ማረፋችሁ አይቀሬ ነው። ለዚህ ነው በድርድር ወዳጅን ማብዛት ያለባችሁ የምለው።


ይህ ነው ተቀናቃኝን የማሸነፊያው መንገድ። ለካ እናንተ ተቃዋሚ ነው የምትሉት። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ኃይል ወይም የሰራዊት ብዛት አያዋጣም። በነገራችን ላይ አዲሲቷ ኢትዮጵያ የሚለውን አጼ ኃይለ ሥላሴ ናቸው መሰለኝ የጀመሩት። ‹‹በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ከእንግዲህ የማትነጣጠሉ፣ በሕግ ፊት ትክክለኛነትና ነፃነት ያላችሁ ሕዝቦች እንድትሆኑ እንፈልጋለን›› ብለው ነበር። ንግግራቸውን “ውሃ በላው” እንጂ። ደራሲ ጥላሁን ጣሰው የኢትዮጵያና የጣልያን ሁለተኛው ጦርነት ታሪክ ገጽ 166 አስፍረውታል።


አዲሲቷ ኢትዮጵያ የሚለውን ማደናገሪያ ደርግ ቀጠለበት። እናንተማ የእኛ ቋንቋ ብቻ ነው ብላችሁ አገሪቷን ዛሬ የፈጠራችኋት አስመስላችኋታል። አዲሲቷ ኢትዮጵያ ያው ነች የነበረችው። የተሻሻሉትን እና ያልተሻሻሉትን ሳንረሳ ማለቴ ነው።


በየጊዜው ምን ሆና ነው አዲስ የምትባለው። አፍርሶ የራስን ታሪክ ለመጻፍ የግድ አገሪቷን ትናንት የተፈጠረች ማድረግ የሚያስፍለግ አይመስለኝም። ካድሬዎቻችሁ የእናንተን ታላቅነት ለመቀበል የግድ ምኒልክን ማንኳሰስ የሚያስፈልግ ይመስላቸዋል ። ‹‹ልክ አይደለም›› መባል አለባቸው። ሌላው የሰራውን ዕውቅና ስትሰጡ ለእናንተ ሥራም እውቅና ታገኛላችሁ። ያልተዘራው አይበቅልም። ዝሩ ታጭዳለችሁ።


ነጋድራስ ‹‹አእምሮ የሌለው ሕዝብ ሥራት የለውም። ሥራት የሌለው ሕዝብ የደለደለ ኃይል የለውም። የኃይል ምንጩ ሥራት ነው እንጂ የሠራዊት ብዛት አይደለም። ሥራት ከሌለው ሰፊ መንግስት ይልቅ በሕግ የምትኖር ትንሽ ከተማ ሞያ ትሠራለች።›› ብለዋል። ትክክል ነው። እናንተ ግን በሠራዊት ብዛት ታምናችሁ ሰውን ስታምሱ ቆያችሁ። ካለፉት ሥርዓት መማር ከተሳናችሁ የነጋድራስ ምክርን ላውሳችሁ። ነጋድራስ የድሮውን ሲያነሳ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመንግስት ይልቅ የምኒልክን ግምባር ይፈራል ብለዋል። ዛሬሳ? ከሥርዓቱ ይልቅ የእናንተን ፊት ሲፈራ ከርሟል። አሁን ግን እናንተን መፍራት አቆመ። ይሔ ነው ችግሩ። የተራበ ሕዝብ መሪውን ይበላል ያለው ማን ነበር? ሕዝቡ ሥርዓትን አይፈራም።


ሥርዓቱን የጣሱት የአጼዎቹ የእናንተ የግል ምሩጣን ልጆች አይደሉምን? አሁን እንኳን እስረኞችን ስትለቁ ወገን የሌላቸው የመሰሏችሁን አጉራችሁ ሌሎችን መፍታታችሁ ምንድን ነው? ያለ ሥርዓት መኖር አይደለምን? ዝም ያሉ ወጎኖቻቸው የተነሱ ጊዜ ልትፈቷቸው ነውን? ሊቁ (ፕሮፌሰር) አፈወርቅ ገብረ የሱስ ምኒልክን ሲመክሩ ‹‹ደግ ነገር መምከር መደገፍ ነው እንጂ መድፈር አይባልም›› እንዳሉት ነው። ይህን ያሉት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት የሚያስነቅፍ ሆኖ በመገኘቱ መሆኑን አጤ ምኒልክ በሚለው መጣፋቸው በገጽ 105 ዘግበውታል።


የሰብአዊ መብት አያያዝ ችግር ወይም ቅጣት በአውሮፓ ተሰምቶ ሲወራ ሰምተው ነው ይህን ያሉት። የእናንተስ የሰብአዊ መብት አያያዛችን ሲነቀፍ ስንት ዘመን አለፈ። እንዴት በእናንተ ጊዜ ሰው በብሔሩ ይሰደባል። እንዴትስ አረመኔያዊ የእስር ቤት አያያዝ ሊኖረን ቻለ? ደጋፊዎቻችሁስ እንዴት ይህ ግፍ አስደሰታቸው? ሰብአዊ መብት ይከበር ብዬ በመጻፌ ‹‹…ደንቆሮ የሆነ ያገሬ ሰው እንዴት ደፍሮ ጣፈው ብሎ እንዲሰድበኝ አውቃለሁ። ብልህ የሆነ ሰው ግን እንኳን ይነቅፈኝ እሱም ጭምር በታቸለው የሚጠቅም ነገር ለንጉሱ ይጠቁማል።›› ብለዋል። ዛሬም ጭፍን ካድሬዎቻችሁ ሳይበሳጩብኝ አይቀርም። ሰብአዊ መብት ይከበር ሲባል የሚካፋው ብዙ የኢህአዴግ ካድሬ መኖሩን አልዘነጋውም። ብልህ ካድሬ ግን ይህን በልቡ ያኖራል፡፤ ቢያንስ የጊዜን ተለዋዋጭነት ተገንዝቦ ‹‹ነግ በኔ›› ሲል ጥሩ ሊሆን ይሞክራል። ሰሞኑን እንኳን የፖለቲካ እስረኞችን እንፈታለን ባላችሁ ጊዜ ምን አይነት ሞገስ እንዳገኛችሁ አስተውላችኋል? የአገር ገጽታ ግንባታ እያሉ የሚያወሩ ካድሬዎቻችሁን አትመኑ። እነሱ ናቸው በድብቅ የምትሰሩትን የሚያጋልጡት። ካድሬን ያመነ ጉም የዘገነ አይነት ነው። ጅብ በበላበት ይጮሃል ይሉ የለ የአገራችን ሰዎች። ብቻ ግምት ነው!


ሰበብ ፈላልጌ አጤነታችሁን ልናገር እንጂ። ብተሰሙኝ ደስ ይለኛል። ባለፈው አቶ ለማ መገርሳን ‹‹አኮቴት ዘ ለማ መገርሳ›› ብዬ የአድናቆት መጣጥፍ አቅርቤ ነበር። ሰሞኑን መግለጫችሁን ሰምቼ በለመደው እጄ እናንተን ለማድነቅ ብዕሬን ሳነሳ ምን እንዳስፈራችሁ አለውቅም የቀረበቻችሁበትን መንፈስ ለማደፍረስ ወዲህና ወዲያ ስትሉ እያየሁ ነው። በዚህ ምክንያት የልቤን አድናቆት ተዘረፍኩ። እናንተ ናችሁ የዘረፋችሁኝ። የጀመራችሁትን ንጹሕ መንፈስ አታደፍርሱት። ፈርታችሁ ሳይሆን አይቀርም። ትግሬው አለቃ ተወልደ መድህን “መብራት ሳይነድ አያበራም” ብለዋል ነገድራስ ገብረሕይወት በገጽ 13። እናንተም ለዋጭ ሆናችሁ ኢትዮጵያን ለማብራት ንደዱ። ዋጋ ክፈሉ እና እስረኞችን ፍቱ፡፤ በውጭ ካለው ተቃዋሚ ኃይል፤ ነፍጥ ካነሱትም ጋር ተደራደሩ። ነፍጥ አንስታችሁ ወደ ስልጣን የመጣችሁ ናችሁና የነፍጥን ኃይል አትዘነጉትም።


አዲስ ነገር ለመፍጠር አትፍሩ። ‹‹ስለዚህ የዓለምን ታሪክ ብንመለከት አዲስ ሥርዓት የሚያወጣ ንጉስ ሁሉ በህይወቱ ሳለ መከራ አይለየውም።›› ይላሉ ነጋድራስ። እስከዛሬ የመጣችሁበትን የአፈና እና የጎጥ ጥበት እርግፍ አድርጋችሁ ጣሉት። ለውጥ ማለት ይህ ነው። ሁሉ ሰላም ነው። ሁሉም ሰላም አይደለም። መንገዳችሁ ነው ምርጫውን የሚወስነው፤ ወይ ሰላሙን ወይ ድፍርሱን። አገር ከምትፈርስ የፓርላማውን ወንበር ብታካፍሉ ምን አለበት? የእናንት ካድሬዎች የምግብ ፍላጎት ካልተሟላ አገሪቷ የራሷ ጉዳይ ይባላልን? ‹‹አጤዎች አይታረሙም›› የሚሉ አሉ። ምናልባት አጤነታችሁን ለመተው አስባችሁ ከሆነ ብዬ ነው ይህን ሃሳብ ያነሳሁት። አጤ ኢህአዴግ እና ኢትዮጵያ እጣቸውን ያወቀ ወዲህ ይበል ብዬ ልሰናበታችሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
116 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 466 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us