በ4ቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መሪዎች መካከል፣ ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮችና ውሳኔዎች፣ ኢህአዴግ ራሱን ለማዳን የወጠናቸው እንጂ፣ ለሀገራችን መሠረታዊ ፖለቲካዊ ችግሮች አንዳችም መፍትሔ የሚያስገኙ አይደሉም!

Wednesday, 31 January 2018 13:15

 

(የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ)

 

ከምርጫ 2007 ዓ.ም ማግስት ጀምሮ በሀገራችን በተነሳው ሕዝባዊ ቁጣና ተቃውሞ፣ ውጥረት ውስጥ የገባው የኢህአዴግ መንግስት፣ መሪዎች ከ17 ቀናት “ጥልቅ ግምገማ” በኋላ የሰጡት መግለጫ፣ ለሀገሪቱ ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ ቀውሶችና ችግሮች መፍትሔ መስጠት የሚችል አይደለም። ይልቁንም ከ3 ሳምንታት በላይ ግምገማ ያካሄደው የኢህአዴግ መንግስት ለብሔራዊ መግባባት ሲባል የፖለቲካ እስረኞችን እንደሚፈታና በዜጎች ላይ እጅግ ዘግናኝ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የሚፈፀምበትን ማዕከላዊ እስር ቤት እዘጋለሁ በማለት የፖለቲካ ውሳኔ ቢያሳልፍም እስከ ዛሬ ግን አብዛኛው የፖለቲካና የሕሊና እስረኞች አለመፈታታቸው የተሰጠው የኢህአዴግ መግለጫ ለፕሮፓጋንዳ ጠቀሜታ ነው የሚል ጥርጣሬ በሕብረተሰቡ ዘንድ አሳድሯል። የሕዝባዊ የተቃውሞው መሠረታዊ መንስኤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሥርዓተ መንግሥት ለውጥ ለማምጣት ያለው ተስፋ በመሟጠጡ ሲሆን፣ ኢህአዴግ ግን ችግሩን በበታች ሹመኞቹ ላይ በማሳበብ “ኢህአዴግ ይልቀቅ” የሚለውን የሕዝብ ጥያቄ አቅጣጫ አስቀይሮ፣ የካድሮዎችን የሥልጣን ሽግሽግ በማካሄድ “በጥልቅ እየታደስኩ ነኝ” በማለት ተጨፈኑ ላታልላችሁ እያለን ይገኛል።


“አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” እንዲል ኢህአዴግ በእንደዚህ ዓይነቱ ግልጽነት በጎደለው አካሄዱ አንድ ቦታ የተነሳውን ሕዝባዊ ተቃውሞ በዘመቻ መልክ ሊያረግብ ሲሞክር በሌሎች ቦታዎች የሚነሱ ተቃውሞዎች ሲፈታተኑት የሚኖር እንጂ፣ በሃገሪቷ ላይ ለሚያንዣብበው አደጋ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት አይችልም። ለዚህም በ4ቱ የኢህአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች መግለጫ በተሰጠ ጥቂት ቀናት በኋላ ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም በሰሜን ወሎ ዞን በወልድያ ከተማ የጥምቀትን በዓል ለማክበር በወጡት ወጣት ዜጎቻችን ላይ የተፈፀመው ግድያ አንዱ ማሳያ ነው። በሀገራችን በየአካባበው ለተከሰቱት የህዝባዊ ተቃውሞዎች ዋናው ምክንያት ህዝቡ በምርጫ ላይ ተስፋ ቆርጦ ወደ ሌላ የትግል አቅጣጫ መግባቱን በመቀበል፣ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ በእንግዲህ ለማካሄድ ቆራጥ አቋም ያልያዘ ቡድን በ17 ቀናት ግምገማው ቀርቶ ለ17 ወራት በግምገማ ተጠምዶ ቢከርምም የሀገራችን መሠረታዊ የፖለቲካ ችግሮች የሆኑት የፖለቲካ ምህዳር ችግሮች፣ ማለትም የነፃና ፍትሃዊ ምርጫ፣ የነፃ ፕሬስና ሲቪክ ማህበራት ያለመኖር ችግሮች፣ ብቃት ያለው ፍትሃዊ አስተዳደር፣ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ፣ የሰብዓዊ መብት መከበር መፍትሄ ሊያገኙ አይችሉም።


ሕዝቡ እያለ ያለው፣ “አሠራራችሁን አስተካክላችሁ በሥልጣችሁ ቀጥሉ” ሳይሆን “አገዛዛችሁ ይብቃን” እያለ ስለሆነ “ጥልቅ ተሐድሶ አድርገናል፣ በመካከላችን ያለውን ግንኙነት አስተካክለናል” የሚለው ጉንጭ አልፋና “ፋታ ስጡን” የጊዜ መግዣ የፖለቲካ ብልጠት፣ ህዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ አድማሱን አስፍቶ በሀገር አቀፍ እንደሚስፋፋ ኢህአዴግ አዙሮ ማየት አቅቶት ሁኔታውን ወደ ነበረበት ለመመለስ የተስፋ ህልም የሚያልም ይመስላል። የሥርዓት ለውጥ የፈለገን ሕዝብ ከለውጥ በስተቀር የሚያረካው ነገር እንደሌለ መታወቅ ያለበት ጉዳይ እንደሆነም ማስገንዘብ እንወዳለን።


በኢህአዴግ ኮሚኒስታዊ ዴሞራሲያዊ ማዕከላዊነት የሚመራው መንግስታዊ ስርዓት የህዝቦቻችንን መብቶች በመንፈጉ ምክንያት የሚቀሰቀሱትን ተቃውሞዎች ለማርገብ፣ በየአካባቢው “የሰላም ጉባኤ” እያሉ የሰለቸ የካድሬ ቅስቀሳዎችን በማካሄድ፣ የሀገሪቱን ሁኔታ ለአገዛዛቸው ለማመቻቸት የሚያደርጓቸው ጥረቶችም ለችግሩ መፍትሄ አይሆኑም። ስለሆኑም ለኢህአዴጎች በግልፅ መነገር ያለበት እውነታ፣ በሚከተሉት አክራሪ ኮሚኒስታዊ ቀኖና ምክንያት ለሀገሪቱ ችግሮች መፍትሄ መስጠት የማይቻላቸው መሆኑ ነው። ሕዝቡ በነፃ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒ ምርጫ በሀገራችን ፖለቲካ ሕይወት ላይ መወሰን መቻል ይኖርበታል። በመሆኑም ኢህአዴግ የህዝቡ ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ፣ ሀገራቸውን ከአደጋ ለመታደግ ከሚፈልጉ ሀቀኛ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ወገኖች ጋር በሀገራችን መሠረታዊ ፖለቲካዊ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ብሔራዊ ውይይት የሚደረግበት ሰፊ መድረክ በሚዘጋጅበት ሁኔታ ላይ በአስቸኳይ ምክክር መጀመር ይኖበታል። ከዚህም ብሔራዊ ውይይት ሀገራችን ኢህአዴግ ከከተታት የፖለቲካ አዘቅት ውስጥ የምትወጣበት መፍትሄ ይገኛል የሚል እምነት አለን።

 

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ
ጥር 18 ቀን 2010 ዓ.ም
አዲስ አበባ

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
84 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 498 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us