የጭድ እሳት

Wednesday, 07 February 2018 13:17

 

አለማየሁ አሰጋ

 

የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ሰሞኑን “ኢራፓ ኢሕአዴግን የመገነዝ ኃላፊነት የለበትም!!” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችና በኢህአዴግ መካከል በመካሄድ ላይ ከሚገኘው ድርድር በራሱ ውሳኔ መውጣቱን አሳውቆናል።


ኢራፓ፣ በአገሪቱ የመንግስት ታሪክ የአመለካከት፣ የመደራጀትና ለፖለቲካ ስልጣን የመፎካከር ፖለቲካዊ መብቶችና ነጻነቶችን ለመጀመሪያ ጊዜ ያረጋገጠው የኢፌዴሪ ህገመንግስት ውጤት ነው። ይህ ህገመንግስት በስራ ላይ በዋለባቸው ያለፉት ሃያ ሶስት ዓመታት በፌደራልና በክልላዊ መንግስታት ደረጃ የተለያየ ፖለቲካዊ አመለካከትን የሚያራምዱ በርካታ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራጅተዋል። በነጻነትም አመለካከታቸውን በማራመድ ለፖለቲካ ስልጣን ሲፎካከሩ ቆይተዋል። ፓርቲዎቹ እንደየባህሪያቸው አመቺ ባሉት መንገድ የፖለቲካ ተሳትፎ እያካሄዱ ይገኛሉ። ኢራፓም ከእነዚህ አንዱ ነው።


በአገር አቀፍና በክልል ደረጃ የሚንቀሳቀሱት እነዚህ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገሪቱ እስካሁን በተካሄዱ አምስት ምርጫዎች ላይ ተሳተፈዋል። በተለይም እስከ ሶሰተኛው ዙር ምርጫ ደረስ በርካታ ፓርቲዎች በፌደራል እና በክልሎች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ውስጥ ውክልና ለማግኘት በቅተው ነበር።


ይሁን እንጂ ከአራተኛው ዙር ምርጫ በኋላ ምርጫዎቹ አሳታፊ፣ ነጻና ዴሞክራሲያዊ የነበሩ ቢሆንም፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በ50+1 አብላጫ የምርጫ ስርዓት በተወዳደሩባቸው የምርጫ ክልሎች አሸናፊ ሆነው በምክር ቤቶች ውስጥ ውክልና ማግኘት አልቻሉም። በአራተኛው ዙር ምርጫ ኢህአዴግ በተወዳደረባቸው አራት ክልሎች ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባና ድሬደዋ ከተማ አስተዳደሮች ከሁለት መቀመጫዎች በስተቀር ሁሉንም አሸንፎ ነበር። በአምስተኛው ዙር ምርጫ ደግሞ በተወዳደረባቸው ክልሎች ሙሉ በሙሉ መቀመጫዎቹን ማሸነፍ ችሏል። የአፋር፣ የኢትዮጵያ ሱማሌ፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ የጋምቤላ፣ ከፊል ሐረሪ ክልሎች ደግሞ በየክልሎቹ አሸናፊ በሆኑ ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወክለዋል።


በየምርጫዎቹ ላይ ተወዳድረው የምክር ቤት መቀመጫዎችን ማሸነፍ ያልቻሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ከ50 በመቶ በታች የሆነ የጥቂት መራጮች ድምጽ አግኝተዋል፤ ይህ ሁኔታ ከፍተኛው የስልጣን አካል የሆኑ የፌደራልና የክልል መንግስታት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ውስጥ በሚፈለገው ደረጃ የህዝብ ድምጽ ሊሰማ የማይችልበትን ሁኔታ አስከትሏል።


የኢፌዴሪ መንግስትና ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግም ይህ የህዝብን ተሳትፎ የሚገድብ ሁኔታ ተገቢ አለመሆኑን አምነው የአገሪቱን የዴሞክራሲ ምህዳር ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ በማስፋት የህዝብ ድምጾች ያለገደብ ሊሰሙ የሚችሉበት ስርዓት መዘርጋት አለበት የሚል አቋም ያዘ። ይህን ማድረግ የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ጥሪ አቀረበ።


ይህን ተከትሎ በ2009 ዓ.ም የካቲት ወር ላይ ከተጀመረው ከዚህ ድርድር ውስጥ ጥቂት ፓርቲዎች ራሳቸውን ቢያገሉም አስራ ሰባት ያህል ፓርቲዎች ግን የሚደራደሩበትን አጀንዳ ወስነው ወደድርድር ገብተዋል። ድርድሩ አሁንም በመካሄድ ላይ ይገኛል። የድርድሩ ዓላማ የምርጫ ህጎችን በማሻሻል የፖለቲካ ምህዳሩን ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ በማስፋት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁሉም የህዝብ ድምጾች ሊሰሙ የሚችሉበትን የምርጫ ስርዓት መፍጠር ነው።


በዚህ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አስራ ሁለት የድርድር አጀንዳዎች ላይ ተስማሙ። ለድርድር ከተያዙት ጉዳዮች መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ፣ የምርጫ ህግ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ስነምግባር አዋጅ ቀዳሚዎቹ ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያግዛሉ የተባሉት የፀረ-ሽብር ህግ፣ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት ህግ፣ የበጎ አድራጎትና ማህበራት ማደራጃ አዋጅ፣ የታክስ አዋጅ እና የመሬት ሊዝ አዋጅ በዋና የድርድር አጀንዳነት ተይዘዋል። የልማት ተነሺዎች የካሳ ክፍያ ሁኔታም በንኡስ የድርድር አጀንዳነት ተይዟል።


ኢራፓ እስካሁን በተካሄዱት ከምርጫ ጋር ተያያዥነት በሆኑ የድርደሩ ዋነኛ ጉዳይ የነበሩት አዋጆች ላይ በሰጥቶ መቀበል መርህ ተደራድሮ በርካታ የአዋጆች አንቀጾች እንዲሻሻሉ፣ እንዲሰረዙና እንዲቀየሩ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተስማምቷል። ፓርቲው ከተመሰረተ ጀምሮ በብቸኝነት በፕሬዝዳንትነት ሲመሩት የነበሩት አቶ ተሻለ ሰብሮ ለስልጠና በሚል ወደአሜሪካ ከተጓዙ በኋላ ነበር ከድርድሩ መውጣቱን ያሳወቀው። በዚህ ወቅት የጸረሽብርተኝነት አዋጁ ላይ ነበር ድርድሩ ሲደረግ የነበረው። ኢራፓ በጸረ ሽብር አዋጁ ላይ ለድርድር ያቀረበው ሃሳብ አዋጁ ሙሉ በሙሉ ይቀየር የሚል ነበር። በመሰረቱ ኢራፓ ይህን አቋም የያዘበትን አሳማኝ ምክንያት አላቀረበም። አዋጁ ሙሉ በሙሉ ተቀይሮ በምን አይነት ህግ መተካት እንዳለበትም አላመለከተም፣ ይዞ የቀረበው አማራጭ ህግም የለም።


በመጨረሻም “አዋጁ ሙሉ በሙሉ ይለወጥ የሚለው አቋሜ ተቀባይነት ካላገኘ በድርድሩ አልቀጥልም” የሚል አቋም ያዘ። የተቀሩት ፓርቲዎች ግን እንዲሻሻሉ በተስማሙባቸው የጸረሽብርተኝነት አዋጁ አንቀጾች ላይ የህግ ባለሞያ ማብራሪያ እንዲቀርብ ወስነው ይህን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።


በመሰረቱ ድርድር በሰጥቶ መቀበል መርህ የሚመራ ነው። ኢራፓ እኔ የሰጠሁት አቋም ተቀባይነት ካላገኘ በድርድሩ አልቀጥልም ማለቱ፣ ይህን የሰጥቶ መቀበል የድርድር መርህ ይጻረራል። እስካሁን በሰጥቶ መቀበል መርህ ሲደራደር የቆየው ኢራፓ ድንገት አዲስ አመል አብቅሎ ከድርድሩ ለመውጣት የመወሰኑ ነገር ሰበብ ፍለጋ ይመስላል። ይህ ከድርድሩ የመውጣት አቋም ከፓርቲው የመነጨ መሆኑም ያጠራጥራል።


በተለይ ከፕሬዝዳንቱ የውጭ አገር (አሜሪካ) ጉዞ ጋር ተያይዞ ሲታይ፣ ድርድሩ ህገወጥ የተቃውሞ እንቅስቃሴያቸውን እንዳያረክስባቸው በሚሰጉ በውጭ አገር ያደፈጡ ተቃዋሚዎች ተጠልፈው ይሆናል የሚል ጥርጣሬ ይጭሯል። የአሜሪካው ግብዣ ራሱ ከድርድሩ መውጣትን መስዋዕት በማድረግ የተገኘም ሊሆን ይችላል። ከድርድሩ መውጣት የገንዘብ ድጋፍም ሊያስገኝ ይችላል። እድሜ ለኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ጠላቶች፤ ዶላር ሞልቷል።


ያም ሆነ ይህ፤ ኢራፓ ከድርድሩ መውጣቱን በይፋ ያበሰረበት በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የተለቀቀ መግለጫ፤ በድርድሩ ሂደት ምንአልባት ኢሕአዴግን ወደ ሕዝባዊነት፣ ሕዝቡን ደግሞ ወደ ሥልጣን ባለቤትነት ሊቀይሩ የሚችሉ እድሎች እንደሚፈጠሩ ተስፋ በመሰነቅ፣ ራዕይ ፓርቲም ወደ ድርድሩ ሊገባ ችሏል። ሆኖም ግን ኢሕአዴግ በአሳዛኝ ሁኔታ ድርድሩን ለሕዝባዊ ትግሉ ማዳፈኛ፣ ይውረድልን ጥያቄው ማስታገሻ፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ማስተንፈሻ፣ ለራሱ ደግሞ የማጣጣሪያ ትንፋሽ መግዢያ፣ አድርጎ ሲጠቀምበት ከርሟል ይላል። አያይዞም የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ የድርድሩ የዓመት ጉዞ ለአገራችንም ሆነ ለሕዝባችን ያበረከተው ምንም ፋይዳ እንዳልነበረው ገምግሟል . . . ብሏል። በኢራፓ መግለጫ ላይ የሰፈሩት ሌሎች ሃሳቦች የተለመዱ ባዶ ጩኸቶች በመሆናቸው፣ ከላይ የተጠቀሰውን የመግለጫውን አንኳር ጉዳይ ነጥለን ከእውነታው አኳያ እንመለከት።


ኢራፓም የተሳተፈበት ድርድር፣ በመግለጫው ላይ እንደተገለጸው ፋይዳ የሌለው አልነበረም። ይህ ነጭ ውሸት ነው። ድርድሩ ሁሉም የህዝብ ድምጾች፣ አናሳ ድምጾችም ጭምር በመንግስት ውስጥ ውክልና አግኝተው የሚደመጡበትን ሁኔታ በመፍጠር የህዝብን የስልጣን ባለቤትነት የሚያረጋግጥ ስምምነት ላይ የተደረሰበት ነው። ኢራፓ ለዚህ የድርድሩ ውጤት ዋጋ መስጠት አልፈለገም።


ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚያስታውሰው ኢራፓም እንደሚያወቀው፣ ድርድሩ በምርጫ አዋጆች ነበር የጀመረው። የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሰነምግባር ደንብና የምርጫ አዋጁ ላይ ድርድር ተካሂዶ በርካታ አንቀጾች እንዲሻሻሉ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ከእነዚህ መካከል ህገመንግስታዊ ማሻሻያን እስከማድረግ የሚዘልቀው በምርጫ ህጉ ላይ የሰፈረውን የምርጫ ስርዓት የሚቀይር ስምምነት ተጠቃሹ ነው። ይህ ስምምነት የድርድሩ ታሪካዊ ውሳኔ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።


በድርድሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በኢፌዴሪ ህገመንግስትና በምርጫ ህጉ ላይ ያለው የአብላጫ ድምጽ የምርጫ ስርዓት ተሻሽሎ፣ የአብላጫና የተመጣጣኝ ውክልና ቅይጥ እንዲሆን ተስማምተዋል። በቅይጥ የምርጫ ስርዓቱ፤ 80 በመቶ በአብላጫ ምርጫ ድምፅ፣ 20 በመቶ ደግሞ በተመጣጣኝ ድምፅ የፓርላማው ወንበር እንዲያዝ ስምምነት ላይ ተደርሷል።


የአብላጫና ተመጣጣኝ ድምጽ ቅይጥ ትይዩ የምርጫ ስርዓት በፌዴራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በክልል ምክር ቤቶች እንዲሁም በአዲስ አበባና ድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር ተግባራዊ የሚደረግ እንዲሆንም ፓርቲዎቹ ተስማምተዋል፤ ኢራፓም ጭምር። ፓርቲዎቹ የተስማሙበት የአብላጫና ተመጣጣኝ ቅይጥ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውክልና ስርዓት አሁን ያለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ላይ 110 ተጨማሪ መቀመጫዎች እንዲኖር ያደርጋል። ታዲያ ከዚህ በላይ ለህዝብ ፋይዳ ያለውና ለስልጣን ባለቤትነት እድል የሚያመጣ ውሳኔ ምን ይሆን?


ከላይ የተገለጸውን የምርጫ ስርዓቱን እስከማሻሻል የሚዘልቀው የድርድሩ ስምምነት ታሪካዊ ነው። ይህ ስምምነት ተደራዳሪ ፓርቲዎቹንም በታሪክ ተጠቃሽ ያደርጋቸዋል። ኢራፓ እንደሚገመተው በውጭ ኃይሎች ግፊት ወይም ማባበል ከታሪካዊው ድርድር መውጣቱ ይህን ታሪካዊ ድርሻን በመወጣት ተጠቃሽ ሊያደርገው ይችል የነበረውን እድል እንደመግፋት ይቆጠራል።


ኢራፓ ከድርድሩ ለመውጣት መወሰኑ በተለይ ውጭ አገር የሚገኙ ህገመንግስታዊ ስርዓቱን የማፍረስ ፍላጎት ያላቸውን፣ ይህን ለማድረግ ከሃገሪቱ ጠላት ጋር እስከማበር የዘለቁ ቡድኖችን ጭብጨባ ሊያስገኝለት ይችል ይሆናል። ዶላርም ሊያስገኝ ይችል ይሆናል። የአገሪቱን ዴሞክራሲ በማጎልበት የህዝቡን የልማትና የሠላም ፍላጎት ከሟሟላት አንጻር ሲታይ ግን ቀሽም ውሳኔ ነው።


ኢራፓ በእልህ አስጨራሽ ሰላማዊ ትግል ራሱን እያጎለበተና ተመራጭ እየሆነ ከመዝለቅ ይልቅ፣ በውጫዊ ግፊት ጯሂ አቋሞችን በማንጸባረቅ እንደ ጭድ እሳት ቦግ ብሎ ጠፍቶ ሰሞነኛ ፓርቲ መሆን እየመረጠ መሆኑን ሊያስተውል ይገባል። በዚህ አካሄድ ፕሬዝዳንቱ በተደጋጋሚ የቪኦኤ የአማርኛ ፕሮግራም እንግዳ መሆን ይቻሉ ይሆናል። ፓርቲያቸውን ራሱን ችሎ የቆመና የህዝብ ድጋፍ ያለው፣ የስልጣን ውክልና ሊረከብ የሚችል ግዙፍ ፓርቲ ማድረግ ግን አይችሉም።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
80 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 447 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us