ትውልድን ከአስተሳሰብ ቀውስ የሚታደጉ ልሂቃን ያለህ!

Wednesday, 07 February 2018 13:20

 

ኢዛና ዘመንፈስ

 

እንዳለመታደል ሆኖብን ከሩብ ምዕት ዓመት በላይ ያስቆጠረው የስር ነቀል ለውጥ ሂደታችን፤ ከምክንያታዊነት ይልቅ ስሜታዊነትን አጉልቶ ከሚያንፀባርቅ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የፀዳበት አጋጣሚ የለም። እናም ላለፉት 26 ዓመታት ያህል በዚች አገር ውስጥ ሲካሄድ የቆየው የድህረ ደርግ ኢትዮጵያ ባለብዙ ፈርጅ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሲወርድ ሲወራረድ ለመጣ የጭፍን ስሜታዊነት ችግር እንድንዳረግ ያደረገን ከመሆኑ የተነሳ፤ በተለይም “ተምሯል” ተብሎ የሚታመንበት የህብረተሰብ ክፍል ከምክንያታዊ አስተሳብ የማፈንገጥ አዝማሚያን ማሳየት ከጀመረ ዓመታት ስለመቆጠራቸው ደፍሮ መናገር ይቻላል። ይልቁንም ደግሞ አዲሱን የታሪክ ምዕራፍ በፀረ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊ የሀገር አንድነት ለመፈረጅ የሚቃጣውን አክራሪ አቋም ለሚያራምዱት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ ለመስጠት ያለመ የአንድ ወገን አስተሳሰብን በማንፀባረቅ ረገድ የሚታወቁ ልሂቃን፤ ምክንያታዊነትን ገድሎ የሚቀርብ ጭፍን ስሜት እንዲጠናወተን ያደረገ ጉልህ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸው የሚስተባበል ጉዳይ አይደለም።


ከዚህ አኳያ የሚስተዋለው አፍራሽ ተፅእኖ የመፍጠር አሉታዊ ሚና በዋናነት የሚገለፅበትን አግባብ አምኖ ለመቀበል የሚቸገር ሰው፤ ምናልባትም ከደርግ ውድቀት ማግስት ጀምሮ፤ እየታተሙ የተሰራጩ የግል ፕሬስ ውጤቶችን ያላነበበ ሊሆን እንደሚችል ይሰማኛል። አልያም ደግሞ በእነርሱ አማካኝነት ያለማቋረጥ ሲዛመት የቆየው የተቃውሞው ጎራ ፖለቲከኞች ጭፍን፣ ድፍን ያለ የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ነባራዊ ጥሬ ሀቁን ለማገናዘብ እንዳይችል የሚያደርግ ኢ-ምክንያታዊ አስተሳብን ያሰረፀበት ነው ብለን እናጠቃልል ዘንድ ተገቢ ይሆናል።


በግልጽ አነጋገር፤ አሁን አሁን ሀገራችን ውስጥ እዚህም እዚያም የሚታይ ተደጋጋሚ የደህንነት ስጋት ተደርጎ ሊወሰድ በሚችል መልኩ እየተስተዋለ ያለው ብሔር ተኮር የዕርስ በርስ ቁርቁስና ቅራኔ የሚገለፅበትን አሉታዊ ክስተት ያስከተለው መሰረታዊ ምክንያት፤ አብዛኛው የሀገራችን “ምሁር” ዜጋ አዘውትሮ የሚያራምደው ፖለቲካዊ አቋም፤ ከምንያታዊነት ጋር የተፋታና እነርሱ የማያምኑበትን ሃሳብ ህዝባዊ ተቀባይነት ለማሳጣት ያለመ ጭፍን ውግዘት (ማጥላላት) እንደመሆኑ መጠን፤ ይሄው ከትናንት እስከ ዛሬ የምናውቀው ጨለምተኛ አመለካከት የወጣቶቻችን ስብዕና ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እየጨመረ በመጣ ቁጥር የተፈጠረ የአስተሳሰብ ቀውስ ነው ተብሎ ይታመናል። ስለዚም ተማሪ ቤት ገብቶ ቀለም የመቁጠር ዕድል ካልገጠመው ኢትዮጵያዊ አርሶና አርብቶ አደር የህብረተሰብ ክፍል ይልቅ “ተምረዋል” የሚባሉት ወጣት ዜጎቻችን ይህቺን ከፈርጀ ብዙ ድህነት ለመውጣት ባለመ የልማት ጉዞ ላይ የምትገኝን ሀገራቸውን ለውድመት የሚዳርግ ዘረኝነትን ማራገብ ይዘዋል።


ጉዳዩን ከዚህ የነውጥ ናፋቂዎቹ ቀለም ቀመስ ወጣቶች ቁጥር እየተበራከተ መምጣት አኳያ አንስተን እንመልከተው ከተባለም ደግሞ፤ አንድ ጉልህ እውነታ ሊገልጽልን እንደሚችል መገመት አይከብድም። እርሱም እዚች አገር ውስጥ በምክንያታዊ አስተሳሰብ አምነው ለማሳመን ፍላጎት የሚያንሳቸው ምሁራን እየተበራከቱ የመጡበት ሁኔታ የመኖሩን ጉዳይ ለመረዳት የሚያስችል መሆኑ ነው።


እንዲያውስ እኔን “ትውልድን ከአስተሳሰብ ቀውስ የሚታደጉ ልሂቃን ያለህ!” ያሰኘኝ ምክንያትም ከላይ ለማመልከት የተሞከረው ዓይነት እጅግ አደገኛ ብሔር ተኮር የጥላቻ ፖለቲካ እየተባባሰ ከመምጣቱ የተነሳ፤ የመቶ ሚሊዮን ህዝቦቿ የጋራ ህልውና የተመሰረተባትን ሀገራችንን ለከፋ ጥፋት የሚዳርግ ወደመሆን ደረጃ ሳይደርስ አልቀረም የሚል ስጋት ተሰምቶኝ ነው። እናም ከዚሁ የግል እይታ በሚመነጭ ትዝብት አዘል የስጋት ስሜት እንደ አንድ ለመላው የሀገሩ ህዝቦች ዘለቄታዊ የጋራ ዕጣ ፈንታ መቃናት የሚበጀውን ጠቃሚ ምክር ለመለገስ ከመሞከር ቦዝኖ የማያውቅ ዜጋ ልሰነዝር የምሻው ሃሳብ እነሆ የሚከተለውን ይመስላል።


በዚህ መሰረትም፤ ብዙውን ጊዜ የህሊና ፍርድን የሚጠይቅ ሚዛናዊ አስተያየት ላይ የሚያጠነጥን ምክንያታዊ ሃሳብ ከመሰንዘር ይልቅ፤ ኢህአዴግ መራሹን የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል ሂደት በፀረ የሀገር አንድነት ለመፈረጅ የሚቃጣው ጭፍን ስሜታዊነትን የሚያንፀባርቅ ውግዘትን እንደጠቃሚ ነገር የወሰዱት የሚመስሉ ወገኖች በሚያራምዱት የጥላቻ ፖለቲካ ምክንያት የሚከሰተውን አሉታዊ ክስተት በዘላቂነት ማስቀረት የሚቻለው ወጣቱን ኢትዮጵያዊ ትውልድ ካጋጠመው የአስተሳብ ቀውስ ትርጉም ባለው መልኩ የሚታደግ አዎንታዊ ተጽእኖ የማሳደር አቅም ያላቸው ቅን አሳቢ ልሂቃን ዜጎች የየራሳቸውን ገንቢ ሚና ይጫወቱ ዘንድ ምቹ ሁኔታ ስንፈጥር እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል። ይህን መሰረተ ሃሳብ በተሻለ መልኩ ለማብራራት ያህል የሚከተሉትን ጥቂት አንኳር ነጥቦች አንስተን ትንሽ ተጨማሪ ማብራሪያ ማከል እንደሚኖርብኝ ይሰማኛልና እነሆ አብረን እንመልከት

እንግዲህ የሐተታዬ ርዕስ “ትውልድን ከአስተሳሰብ ቀውስ የሚታደጉ ልሂቃን ያለህ!” የሚል አይደለም? ስለዚህም አሁን በቀጥታ የማልፈውም፤ አንድን ህብረተሰብ ወይም ደግሞ አንድን ትውልድ የሚባል አዎንታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር አቅም አላቸው ተብሎ የሚታመንባቸው ልሂቃን የትኞቹ ናቸው? የሚለውን ጥያቄ አንስተን መጠነኛ ግንዛቤ ሊያስጨብጥ የሚችል ምላሽ ለማስቀመጥ ሊኖርብን ነው። እናም እንደኔ እንደኔ በተለይም የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛ ከሆነው መሰረተ ሃሳብ አኳያ ትውልድን ከአመለካከት ቀውስ የሚታደግ ገንቢ ሚና የሚጫወቱ ልሂቃን ተደርገው መወሰድ ያለባቸው አካላት የትኞቹ ናቸው? የሚለውን ጥያቄ መመለስ እንብዛም ከባድ አይሆንም።
ምክንያቱም ደግሞ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ እዚህም እዚያም ተደጋግሞ እየተስተዋለ ያለውን እንደሀገር ሊያሳስበን የሚገባ የነውጠኝነት አዝማሚያ በመሪ ተዋናይነት ያንቀሳቅሱታል ተብሎ የሚታመንባቸው አካላትን ጨምሮ ሌሎችም ማህበራዊ፤ ሃይማኖታዊ ፖለቲካዊ ተቋማት ኢ-አመክኖአዊ ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ ለየትኛውም ወገን የማይበጅ ስሜታዊነትን ማስከተሉ እንደማይቀር የየራሳቸውን አባላት (ተከታዮች) በቅጡ ማስተማር እንደሚጠበቅባቸው ይታመናልና ነው።


ስለሆነም እኔ “ትውልድን ከአስተሳሰብ ቀውስ የሚታደጉ ልሂቃን ያለህ!” ስል፤ በተለይም የዜጎችን መንፈሳዊ ህይወት የማረቅ ተልዕኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱት የእምነት ተቋማትን ጨምሮ፤ ትምህርት ቤቶችን፤ የመገናኛ ብዙኃን ባድርሻ አካላትንና እንዲሁም ደግሞ የኪነጥበብ (የሥነ ጥበብ) ሙያ ዘርፍ ውስጥ ከሚያደርጉት የየራሳቸው ገንቢ ጥረት በሚመነጭ አስተምሮ አማካኝነት፤ ዕውቅናን (ዝናን) ያተረፉ ግለሰቦች ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን፤ በምክንያታዊ እሳቤ ላይ የተመሰረተ አሳማኝ አቋም እንዲኖራቸውና በአንፃሩ ለመላው የሀገራችን ህዝቦች ዘለቄታዊ የጋራ እጣፈንታ የማይበጀው አክራሪ ብሔርተኝነት ሊያስከትልብን ስለሚችለው ፈርጀ ብዙ ጥፋት ጠንቅቀው እንዲረዱ የሚያደርግ አዎንታዊ የአመለካከት (የአስተሳሰብ) ተፅዕኖ በማሳደር ረገድ መጫወት የሚጠበቅባቸውን ያህል ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ አይደሉም ማለቴ ነው።


ምክንያቱም እነዚህን የመሳሰሉት የህብረተሰብን የአስተሳሰብ ቁመና ከመቅረጽ አኳያ የማይተካ በጎ ተፅዕኖን የማሳደር አቅም ይኖራቸዋል ተብሎ የሚታመንባቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ የየራሳቸውን ተልዕኮ በአግባቡ ለመወጣት የሚጠበቅባቸውን ያህል ቅን ጥረት እያሳዩ ቢሆን ኖሮማ፤ ለሀገር አውዳሚው የሁከትና ብጥብጥ ተግባር ማስፈፀሚያነት የተማሩ የሚመስላቸው ነውጥ ናፋቂ ወጣቶች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን ሲጨምር ባልተስተዋለ ነበር።


ስለዚህ አሁንም ቢሆን ብዙ አለመርፈዱን በቅጡ ተገንዝበን፤ ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል ክፉኛ ሲፈታተነው የሚስተዋለውን የአስተሳሰብ ቀውስ ወረርሽኝ የሚያረክስ (የሚገታ) ፍቱን መፍትሔ ማፈላለግ እንደሚጠበቅብን ሊሰመርበት ይገባል። በአጭሩ ይህቺን የመቶ ሚሊዮን ህዝቦቿ የጋራ ህልውና የተመሰረተባትን ሀገራችንን በዜጎቿ የብሔር ማንነትን መሰረት ያደረገ የዕርስ በርስ ግጭትና መናቆር ለማፈራረስ ያለመ መሳፍንታዊ የፖለቲካ ሴራ በመዶለት የተጠመዱት የጥፋት ኃይሎች ማዛመት የያዙትን መርዘኛ ፕሮፖጋንዳ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ህብረተሰብ አምርረን ማውገዝ እንደሚኖርብን በየመገናኛ ብዙኃኑ አዘውትረው የመናገር ድፍረት ያላቸው ታዋቂ ምሁራን፤ የኪነጥበብ ሰዎች፤ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እጅጉን እንደሚያስፈልጉን ነው የወቅቱ አጠቃላይ የአመለካከት ድባብ ከመቸውም ጊዜ ይልቅ አፍ አውጥቶ የሚናገረው።


ይልቁንም ደግሞ ትግርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያንን እንደ የአንድ ብሔር ተወላጅ ህዝብ የጭፍን ጥላቻ ሰለባ በማድረግ ረገድ የሚገልፅ የተቃውሞ ፖለቲካን የሚያቀነቅኑት ጽንፈኛ ቡድኖች ሳይሳካላቸው እንዳልቀረ ለመረዳት የተለየ ዕውቀት አይጠይቅም። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ በኢትዮጵያውያን ወንድማማች ህዝቦች ዘመናትን ያስቆጠረ የአብሮነት ታሪክ ውስጥ አንብዛም ያልተለመደ እጅግ በጣም አስነዋሪ የዘረኝነት ተግባር የሚያስከትለው ጉዳት የጥላቻ ፖለቲካና ፖለቲከኞች ጥቃት ግንባር ቀደም ኢላማ እየተደረጉ ያሉትን የትግራይ ተወላጅ ወገኖችቻችንን ብቻ እንዳልሆነም ልብ ማለት ይገባል።


አለበለዚያ ግን፤ ከለየላቸው ኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ህዝቦች ታሪካዊ ጠላቶች ጋር እየተመሳጠሩም ጭምር በሚያውጠነጥኑት የሃኬት ሴራ ምክንያት፤ የጋራ ህልውናችን የተመሰረተባትን ሀገር ለብተና አደጋ እስከ መዳረግ የሚደርስ ፖለቲካዊ ቀውስን ለማባባስ ሲሉ እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩት ስልጣን ናፋቂ ተቃዋሚዎች ዕርስ በርስ እንድንተላለቅ የሚያደርግ የጥፋት እሳት ሲጭሩ እያየን እንዳላየን ማለፉ መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ መገመት አያዳግትም። ለማንኛውም እኔ እዚህ ላይ አብቅቻለሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
97 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1078 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us